የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መግለጫ
መጋቢት 1፤ 2008ዓም፤
ዋሽንግቶን ዲሲ፤
የአፈጻጸም ማጠቃለያ፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የካቲት 6፤ 2008ዓም (February 14, 2016) በአሜሪካ የሜሪላንድ ጠቅላይ ግዛት ሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ ባደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ “የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” መመሥረቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ምክርቤቱ የተመሠረተው ሕዝባዊ ጉባዔው ከመካሄዱ በፊት በነበሩት ሦስት ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ወገኖች ባካሄዱት ስትራቴጂካዊ ውይይት ነበር፡፡ ምክርቤቱ “የእኛ ለኛ” ወይም የሕዝብ ለሕዝብ ንቅናቄ ሲሆን ዕርቅ፣ የጉዳት ፈውስና ርትዓዊ ፍትሕ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን መካከል ለማምጣት የሚተጋ ይሆናል፡፡
አጀማመር፤
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ገና ከጅማሬው ቀዳሚው ዓላማ ያደረገው በአገራችን ሕዝብ ዘንድ ዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ማምጣትን ነበር፡፡ ሃሳቡ የተጠነሰሰው የጋራ ንቅናቄው በይፋ ከመመሥረቱ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ይህም የሆነው የዛሬ 12ዓመት በአኙዋክ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት አሰቃቂ ተግባር በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ሕመምና ስቃይ ያንንም ተያይዞ ባመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ በአመጽ፣ በግድያ እና በብቀላ ዑደት ውስጥ ባለችው አገራችን ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ ሊያመጣ የሚችል ብቸኛው ተስፋ ከዚህ የብቀላ አዙሪት በመውጣት ይቅርታን፣ ዕርቅንና ርትዓዊ ፍትሕን መፈለግ ሊኬድበት የሚገባ አዲሱ መንገድ መሆኑ በየጊዜው ግልጽ እየሆነ መምጣቱ ከዚህ ምክርቤት ምሥረታ ጋር አብሮ የሚጠቀስ እውነታ ነው፡፡
በመሆኑም ይህ የዕርቅና ፍትሕ ሃሳብ እጅግ እየጎላ ሲሄድ የተስተዋለው አቢይ ነገር ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ነጻነትና ፍትሕ እስካልመጣ ድረስ የአኙዋክ ሕዝብ ለብቻው ነጻነትና ፍትሕ ሊጎናጸፍ አይችልም የሚለው ሆነ፡፡ ስለዚህ በዘር በተከፋፈለች አገራችን ተግባብቶ ለመኖር የሚችል ኅብረተሰብ ለመመሥረት የሚቻለው እያንዳንዳችን ከታገትንበት የዘር፣ የጎሣ፣ የነገድ፣ … ሣጥን በመውጣት ሌሎችን እንደራሳችን በመመልከትና ከዘር ወይም ከማንኛውም ልዩነታችን በፊት ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መስጠት የሚያግባባ ሃሳብ እየሆነ ሄደ፡፡ በመጨረሻም ለተለያዩ የኢትዮጵያ ልጆች እውነት፣ ነጻነት፣ ፍትሕ፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማምጣት በ2000ዓም (በ2008 የአውሮጳውያኑ አቆጣጠር) ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቀናቄ (አኢጋን) ተመሠረተ፡፡ ይህም በተከፋፈሉ ወገኖች መካከል ዕርቅን፤ እንዲሁም የሌሎች ወገኖችን ችግር እንደራስ የማየት ማኅበራዊ ኃላፊነት የመውሰድና ለተግባራዊነቱም ጥረት ወደማድረግ እየገፋ ሄደ፡፡
ባለፉት 24 ዓመታት በአገራችን በተከሰተው የመከፋፈልና የመለያየት ሥራ ምክንያት አንዳችን ለሌሎቻችን ያለን ስሜት እየረገበና እየጠፋ ከመምጣቱ የተነሳ የሌላው ስቃይ የማይሰማን ሆነናል፡፡ አኙዋኮች በተጨፈጨፉበት ጊዜ የቀዳሚነቱን ቦታ ወስዶ ጩኸቱን ያሰሙት አኙዋኮች ነበሩ፡፡ ግፍ ሲፈጸም በቀዳሚነት ኃላፊነቱን ወስደው ጩኸታቸውን የሚያሰሙት የተጠቂው ወገኖች ብቻ መሆናቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም በአንድ አገር ላይ ተወልደን ይህ ዓይነቱ “እኔን አይመለከተኝም” አካሄድ የበረታው እርስበርስ ተገናኝተን የመነጋገርና የመወያት ልምምዳችን አናሳ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፉት በርካታ ዓመታት የጋራ ንቅናቄው ኅብረትን ከመፍጠር አኳያ የተለያዩ መድረኮችን በማካሄድ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በመጥራት፣ ሰልፎችንና ውይይቶችን በማድረግ አንዱ ለሌላው መብት የሚቆምበትንና ለዕርቅ የሚሠራበትን መንገዶች ሲያመቻች ቆይቷል፡፡ በመቀጠልም ከኅዳር 6፤2007ዓም ጀምሮ የጋራ ንቅናቄው በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮጳ የተለያዩ ከተሞች አሁን ወደ ተመሠረተው ምክርቤት ዓላማ የሚወስድ “ለመተማመን እንነጋገር” በሚል ርዕስ የተለያዩ ስብሰባዎችን አካሂዷል፡፡
የአገራችን ቀውስ የወሰደን መንገድ፤
አገራችን በአሁኑ ወቅት ያለችበት ሁኔታ ከመቼውም ይልቅ እጅግ አሳሳቢና አስጊ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ቅርብ ጊዜያት የሚካሄዱትን ሁኔታዎች ስንመለከት ባስቸኳይ አንድ ነገር ካልተደረገ የወደፊቱ ኅልውናችን አደጋ ላይ እንደሚወድቅ እሙን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ወገኖችን በማሰባሰብ የሶስት ቀናት ተቀራርቦ የመወያያ ቦታ በማዘጋጀት በአገራችን ጉዳይ ላይ አቋም ለመውሰድና ይህንኑ ውሳኔ የካቲት 6፤2008ዓም/February 14, 2016 ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡
ወቅታዊውን ሁኔታ ብቻ በመመልከት በተለይም እጅግ የተንሰራፋውን ጭቆና፣ ሙስና፣ እየተካሄደ ያለውን የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞ፣ ችጋር፣ እና ሌሎችንም ሁሉ የችግሩ ጀማሪ በሆነው በህወሃት/ኢህአዴግ አናት ላይ ማድረግ አይከብድም፡፡ ይህም ህወሃት/ኢህአዴግን ከመንበረ ሥልጣን ማስወገድ እንደ መፍትሔ እንድንቆጥር ሊያደርገን ይችላል፡፡ ሆኖም በአገራችን ዕርቅ፣ የጉዳት ፈውስ፣ ርትዓዊ ፍትሕ በሕዝብ መካከል እስካልተደረገ ድረስ የወደፊቱ ኅልውናችን አሁን ካለንበት እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በርካታዎች የሚያምኑት ሐቅ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር አስቀድሞ “ለመተማመን እንነጋገር” መድረክ ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ የጋራ ንቅናቄው ደጋፊዎችና ወዳጆች ከሌሎች ጋር በመሆን በሶስቱ ቀናት ተቀራርቦ የመወያያ ቦታ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ ከምግብና መልካም ጨዋታ በተጨማሪ የግል ታሪኮች ተወስተዋል፤ ትርከቶች በግልጽ ተነግረዋል፤ አመለካከቶች ያለገደብ ይፋ ሆነዋል፤ አንዱ የሌላውን ሸክም እንዴት መሸከም እንዳለበት ከግል ልምምድ ትምህርት ተወስዷል፤ ጎሣዊ ጥበት በሰብዓዊነት ሰፍቷል፤ አዲስ ግንኙነት ተመስርቷል፤ የመጣላት ሳይሆን ተከባብሮ የመኖር አመለካከት ሥር ሰድዷል፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተስፋም ፈንጥቋል፡፡
“የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” አመሠራረት
ከሦስቱ ቀናት ተቀራርቦ የመወያየትና የመነጋገር ጊዜ በኋላ በቦታው የተገኙት ተሳታፊዎች “የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” እንዲመሠረት በሙሉ ድምጽ አጽድቀው ወስነዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ዘላቂና ትርጉም ያለው መፍትሔ ለማግኘት የሚችሉበት ዓይነተኛው መንገድ ከጉዳታቸው ሁሉ ተፈውሰው፣ በዕርቅ ተስማምተውና ርትዓዊ ፍትሕ ማስፈን ሲችሉ እና የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእነዚህ መሠረቶች ላይ ሲመሠርቱ እንደሚሆን የምክርቤቱ ዋንኛና ተቀዳሚ ተልዕኮም ይኸው እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የምክርቤቱን ዓላማና ግብ በተመለከተ ተሰብሳቢዎቹ በወሰኑት መሠረት የሚከተሉት ሆነዋል፤
ዓላማ፤
ኢትዮጵያውያን የእርስ በእርስ ውይይት እንድንጀምር በማድረግ አንዱ የሌላውን ትርከት ለመስማትና ይህም ወደ መደማመጥ፣ መግባባት፣ ይቅር መባባል፣ መንጻትና ሥርየት መርቶን ሰላምና ፍትሕ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉት ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲሰፍን ማድረግ ከምክርቤቱ ዓላማዎች ቀዳሚው ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ምሬት፣ ቁስል፣ ሐዘን፣ ፍርሃትና የውስጥ ለቅሶ ለመስማት ጆሮ የሚሰጥበትና እንደ ራሱ አድርጎ የሚቀበልበት ይህንንም የዘር፣ የቀለም፣ የጎሣ፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት ብልጫና ልዩነት ሳያደርግ መተግበር ሌላኛው ዓላማ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የምክርቤቱ ዓላማ በቀዳሚነት ትኩረት አድርጎ የሚከወነው ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር ሳይሆን ሰፊውን ሕዝባችንን በሚያጠቃልል መልኩ የአንድ ለአንድና የእኛ ለእኛ ግንኙነት በመመሥረት ሆኖ ይህንንም ከሌሎች የምክርቤቱ ዓላማዎች ጋር አብሮ የሚያራምደው ይሆናል፡፡
ግቦች፤
የምክርቤቱ አራት አስቸኳይ ግቦች የሚከተሉት ናቸው፤
- በመጪዎቹ ስድስት ወራት የምክርቤቱን መዋቅር ይፋ ማድረግ፤
- በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ መቻቻልን፣ መተማመንን፣ እኩልነትንና ፍትሕ እንዲስፋፋ ማድረግ፤
- የምክርቤቱን ተልዕኮና ዓላማ ለማጎልበት የኢትዮጵያን የሃይማኖት፣ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ በመድረስ መግባባት፣ ስምምነትና ሽርክና እንዲኖር ማድረግ፤
- ሚዲያውን በመጠቀም በኢትዮጵያውያን መካከል ከደረሰው መጎዳዳትና ቁስል የጉዳት ፈውስ ለማግኘትና ወደ ዕርቅ እና ርትዓዊ ፍትሕ መድረስ ይቻል ዘንድ መትጋት የምክርቤቱ ግቦች ይሆናሉ፡፡
የጋራ ንቅናቄው ሕዝባዊ ስብሰባ፤
ስብሰባው የካቲት 6፤ 2008ዓም (February 14, 2016) ሲጀመር የአኢጋን አመራሮች በሦስቱ ቀናት ተቀራርበው ሲሰሩ ለነበሩት ወገኖች ምስጋና ከሰጡ በኋላ የጋራ ንቅናቄው አመራር የሆኑት አቶ ዳዊት አጎናፍር ሕዝባዊ ስብሰባውን ከፍተዋል፡፡ ሌላዋ የጋራ ንቀናቄው አመራር ወ/ት ኢየሩሳሌም ወርቅ “የአገር ፍቅር” በሚል ርዕስ ስሜትን የሚኮረኩር ወቅታዊ ግጥም አንብባለች፡፡ የአኢጋን የዲሲ አካባቢ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተስፋ መኮንን ተሰብሳቢውን እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉ ሲሆን የጄኖሳይድ ዎች ፕሬዚዳንት ዶ/ር ግሬጎሪ ስታንተን የዘር ዕልቂትን በተመለከተ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ምን እንደሆኑ ትምህርታዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቀጥሎም የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት መግለጫ በአራት የተለያዩ ቋንቋዎች ማለትም በኦሮምኛ፣ በአማርኛ፣ በትግሪኛ እና በእንግሊዝኛ ተነቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሦስቱ ቀናት ተቀራርበው ሲሰሩ የነበሩት ተሳታፊዎች እንደ ኢትዮጵያዊ በዜግነታቸው ያሳለፉትን የህይወት ልምምድ ለተሰብሳቢው አካፍለዋል፡፡ ከጉባዔተኛው የተለያየ ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ሞቅ ደመቅ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በወቅቱ የተቀረጹትን በተለያዩ ክፍሎች እያደረግን እያተምን እንገኛለን፡፡
ለምክርቤቱ ምሥረታ ምክንያታዊ መነሻ፤
በአገራችን ሥር ለሰደደው ችግር መፍትሔ ለማምጣትና ለሁሉም የምትሆን አገር እንድትኖረን ለማድረግ ዓይነተኛው መሣሪያ ዕርቅ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው ወገኖች በብዙ መልኩ የተከፋፈለች አገራችንን ጉዳዮች በተመለከተ ለሦስት ቀናት የፈጀ ውይይትና ምክክር ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ሕዝባችን ለተጋፈጠው የተለያዩ ግጭቶች፣ ቀውሶች እንዲሁም የአገራችንን ሕዝብ እየጎዳ ላለው ችጋር፣ ውጥረት፣ መከራ፣ ሰቆቃ፣… መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው በቅድሚያ በመካከላችን ያለውን ግጭትና አለመግባባት በማስወገድ እንደሆነ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህም አካሄድ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ የተሰባሰቡበት፤ የዕርቅንና ርትዓዊ ፍትሕ በአገራችን እንዲሰፍን ዓላማው አድርጎ የሚሠራ ቡድን መመሥረት አስፈላጊ እንደሆነ ታመነበት፡፡ ከዚህም መረዳት በመነሳት “የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” ሊመሠረት ችሏል፡፡
ይህ የብዙሃንን ሃሳብ በመወከል የመፍትሔ ድምጽ ለመሆን የሚሠራ ምክርቤት በአገራችን ለዘመናት የተከሰተውን ስቃይ፣ መከራ፣ ሰቆቃ፣ መገለል፣ መናቅ፣ መገፋት፣ ጦርነት፣ ሙስና፣ ብክነት፣ በዘርና በጎሣ ላይ የተመሠረተ ጥላቻ፣ መከፋፈል፣ እንግልት፣ እስር፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ … በሙሉ ፈውስና ርትዓዊ ፍትሕ የሚያስፈልገው በመሆኑ ይህ ትውልድ ለሚቀጥለው የሚያስተላልፈው ጥላቻ፣ በቀል፣ መራርነትና ቂምን እንዳይሆን የዚህ ምክርቤት ተቀዳሚ ዓላማና ተግባር ይሆናል፡፡ ይህ እኛው ለእኛው በግለሰብ ደረጃ ጀምሮ ራሳቸውን በተለያየ ቡድን የሚጠሩ ወገኖችን እስከማቀራረብና አገራዊ ዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ እስከማስፈን የሚደርስ ይሆናል፡፡
በምክርቤቱ ምሥረታ ተሣታፊ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የኦሮሞው ተወላጅ አቶ ሮባ አህመድ ኢፍትሃዊነት በመቃወም ሲሰማ የነበረው ጩኸትና ምሬት ከአያታቸው ወደ አባታቸው ቀጥሎም ወደራሳቸው ሲተላለፍ የመጣ ቢሆንም ወደ ልጆቻቸው ማስተላለፍ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፤ በዚህ ዓይነቱ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የወሰኑትም ለዚሁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዘመናት የተከሰተውን ህመም፣ ስቃይ፣ ቂም እና ምሬት እንደ ኢትዮጵያዊ ተቀራርበን ለመሥራት ያሉንን አማራጮች እንዳበላሹብን በመናገር መጪው ትውልድ በነጻነት እንዲኖር ይህ የመከራ ዑደት ማቆም እንዳለበት አጽዕኖት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡
በአንድ ወቅት የተከሰተ አስከፊ ገጠመኝ ፈውስ ካላገኘ ቂም ቋጥሮ ሲያመረቅዝ እየቆየ ለትውልድ የሚተላለፍ በመሆኑ አብሮ ለመኖር ዕንቅፋት ይሆናል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ በኅብረተሰቦች መካከል አብሮ የመኖርን ተስፋ በማጨለም ብቀላንና አመጽን ይወልዳል፤ መተማመን ይጠፋል፤ ለአንድ ዓላማና በጋራ ተስማምቶ መሥራት የማይታሰብ ይሆናል፡፡ አንዱ ሌላኛውን “ጠላት” በማለት ቀን ጠብቆ “ጠላት” ያለውን ጥሎ ሌሎችን በጉልበቱ እያደቀቀ የሚኖርበትን ጊዜ ይጠብቃል፡፡ ተሳክቶለት በሥልጣን ኮርቻ ላይ በተቀመጠበት ቀን ያለመውን በማሳካት በሌሎች ዘንድ ቂምንና በቀልን ይፈጥራል፤ እንዲህ እያለ ያልተፈወሰ ህመም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤ በኢትዮጵያችን ያለው ሁኔታ ይህንን የሚመስል ነው፡፡ ህወሃት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ለበደል ፍትሕ አመጣለሁ ቢልም አስቀድሞ የተከሰቱ ቁስሎች ፈውስ ሳያገኙ እና ዕርቅ ሳይመጣ ሒደቱ በመቀጠሉ ህወሃት በተራው በደል ፈጻሚ ሆኖ የልዩነቱን መጠን አሰፋው፡፡ በህወሃት በደል እየደረሰባቸው ያሉት ደግሞ የእነርሱ ተራ የሚደርስበትን ቀን በመጠበቅ የመከራውን ዙር ለመቀጠል ወረፋ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ ዕርቅ፣ የጉዳት ፈውስና ርትዓዊ ፍትሕ ሊመጣ ይችላል ብሎ መጠየቅ አግባብነት ያለው ነው፡፡ ከሞላ ጎደል የተጎዳዱት ክፍሎች ሁሉንም የአገሪቱ ኅብረተሰብ የሚጠቀልል በመሆኑ ከእነዚሁ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት በመገናኘት በትውልድና በየወገናቸው የተፈጸመውን በደል በመወያየት መግባባት ላይ መድረስ እንዲችሉ ማድረግ አንደኛው መንገድ ነው፡፡ ከዚያም በኅብረተሰብ መካከል መተማመን እንዲፈጠር መነጋገር መጀመር ቀጣዩ ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ንግግር በአብዛኛው የሚያተኩረው አንዱ ወገን ደርሶብኛል ያለውን ቁስል ምን እንደሆነ ሲናገር ለመስማት ጆሮ በመስጠት ነው፡፡ ስለ በደሉ መከሰት ከታሪክ እያጣቀሱ መነታረክና አንዱ ሌላውን ለማስተማር መሞከር ሳይሆን አንድ ወገናችን አሞኛል፤ ተጎድቻለሁ ሲል ያንን ጉዳቱን ለመስማት ጆሮ መስጠት ወደ መተማመን ይወስድና ያም ደግሞ በተራው ወደ ዕርቅ ያመጣናል፡፡ ለመታረቅ መተማመን ያስፈልጋል፤ ለመተማመን ደግሞ መነጋገር ይገባል፡፡ ይህ የዕርቅ ዋንኛው ሃሳብ ነው፡፡
ከዓመጽ፣ ከመከፋፈል፣ ከደመኛነትና ከኢፍትሃዊነት በመሸጋገር የተሻለና የሌሎችን መብቶች የሚያከብር ተግባር መፈጸም በርትዓዊ ፍትሕ ሥር የሚካተት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በወንጀለኛ መቅጫ መሠረት፤ ሕግ በሚጣስበት ጊዜ ሕጉን የጣሰው ሰው የሚገባውን ቅጣት ያገኛል፡፡ የዚህ ወንጀለኛ መቅጫ አካሄድ አንድ ነው፤ ማን ምን አደረገ፤ ምን ዓይነት ቅጣት ይገባዋል የሚል ነው፡፡ ይህ አካሄድ ትልቁን ጥፋተኛም ሆነ ትንሹን ጥፋተኛ በኩል ዓይን በማየት ቅጣት የሚበይን ሲሆን በተቋም ደረጃ ተንሰራፍቶ በሚገኘው ኢፍትሃዊነት ላይ የመዋቅር ለውጥ እንዲደረግ ዋስትና የማይሰጥ ነው፡፡
የርትዓዊ ፍትሕ ዋንኛ ትኩረት የተጎዳው ማነው? የሚለው ላይ ሲሆን ለዚህ ለተጎዳው አካል ምን መደረግ አለበት? ይህንን ማድረግ ያለበት ማነው? የሚሉትን ጉዳዮች በቅርብ የሚከታተል ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የተፈጸሙትን ስህተቶች ለማረቅ የሚደረገው ጥረት ስህተቶቹን ከማስተካከል ጀምሮ እንደ አስፈላጊነቱ ከአካባቢ ጀምሮ እስከ ክልል እንዲያም ሲል በአገር ደረጃ መለወጥ ያለባቸውን ሁሉ ስልታዊ በሆነ መልኩ ተቋማዊ ለውጥ የማድረግን ተግባር ርትዓዊ ፍትሕ የሚጠቀልል ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በኅብረተሰቡ ዘንድ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ሕዝቡን የመስማት፤ ጉዳቱን ለማዳመጥ ጊዜ በመስጠት ግልጽነትን ማበረታታትና በደል ወደ ፈውስ ተሸጋግሮ ሰላም፣ ፍትሕና እኩልነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው የርትዓዊ ፍትሕ መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ልዩነት በዓመጽ አሠራር ገርስሶ በመጣል አንዱ ፍትሕን በሚቆጣጠረው ሁኔታ ወንጀለኛን ለፍርድ ማምጣት ርትዓዊ ፍትሕ አያሰፍንም፡፡ ጥቂቶችን ሥልጣን ላይ አስቀምጦ ፍትሕን ለማስፈን ከመሞከር ይልቅ እጅግ የተንኮታኮተውን እና የብዙዎችን በደል የተሸከመውን አሠራር በመጠገን የጉዳት ፈውስ በማምጣት የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በመተራረቅ ዘላቂ ሰላም በመካከላቸው እንዲሰፍን ማድረግ የርትዓዊ ፍትሕ አሠራር ነው፡፡
በመሆኑም የዚህ ምክርቤት ዋንኛ ግብ በኢትዮጵያ ዕርቅ፣ የጉዳት ፈውስ፣ ርትዓዊ ፍትሕና ሰላም ይሰፍን ዘንድ እና ከማያቋርጠው የዓመጽ፣ ኢፍትሐዊነትና ጭቆና አዙሪት ለመውጣት ኢትዮጵያን ሊወክሉ የሚችሉ የሕዝብ ድምጽ የሚሆኑ ወገኖችን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማውጣጣት ይህንን ዓላማ እንዲተገብሩ ማድረግ ነው፡፡ ተልዕኮውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሆኖ የተነጣጠሉና የተከፋፈሉ ወገኖች አንዱ ስለሌላው ከማውራት ይልቅ እርስበርስ የሚነጋገሩበትን መድረክ ማመቻቸት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን አሠራር ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ እና ከዚያም በላይ እንዲጎለብት በማድረግ አንዱ የሌላውን የዘመናት ሕመም፣ ስቃይ፣ የልብ ሸክም፣ ኃፍረት፣ ጭንቀት፣ ምሬት ጊዜ ሰጥቶ እና እንደራሱ አድርጎ የሚያዳምጥበት፤ የሚረዳበት፣ የሚያስተውልበት ዕድል መፍጠር ነው፡፡ መነጋገር ወደ መደማመጥ፣ መደማመጥ ወደ መተማመን፣ መተማመን ደግሞ ወደ ዕርቅ ይመራናል፡፡ ይህ ምክርቤት የተመሠረተው ይህንኑ ለማድረግ ነው!
ስለሆነም ይህ በጋራ ንቅናቄው የዓመታት ጥረት የተመሠረተው ምክርቤትም ሆነ አባላቱ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ወይም ጊዜያዊና ግልብ አንድነት ለመፍጠር ምንም ዓላማና ፍላጎት የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ መፍትሔ አልባ ለመሰለው የአገራችን ችግር በዋናነት መሠረት ሊጥል የሚችለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ውይይት ወይም የእኛ ለእኛ ንግግር ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ ሁሉ እንዲጀመርና ይህም ውይይት መተማመንን እንዲፈጥር ይህም ጎልብቶ መተራረቅን እንዲያመጣልን ነው የምክርቤቱ ዓላማ፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ምክርቤት ውስጥ መካተት የማይችል አይኖርም፡፡ ምክርቤቱ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወደ መተማመን የሚያደርስ ንግግር እንዲጀምር ለሁሉም ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህ የሕዝብ ኃይል ጎልብቶ የከፋፈለንና እንዳንገናኝ ያደረገንን የቀድሞ የጥል ታሪክ ቀይሮ፤ ጥላቻን አምክኖ፤ ምሬትን አስወግዶ፤ ቂምን በፈውስ ለውጦ የወደፊት ትውልድ በመተማመንና በመከባበር የሚኖርባት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት ያደርጋል ብሎ የጋራ ንቅናቄው ያምናል፡፡
ስለዚህ የዕርቅን ሥራ አሁኑኑ እንጀምር፤ በአካባቢያችን ካሉ ወገኖች ጋር እንነጋገር፤ ከምናምናቸውና እኛን ከሚመስሉ ጋር ብቻ ሳይሆን እኛን አይመስሉም ከምንላቸው ባለንበት ቦታ – በቤተ አምልኮ ይሁን በሥራ ቦታ ወይም በመኖሪያ አካባቢ አብረውን ካሉ እንጀምር፡፡ “እነርሱ ለምን አያነጋግሩኝም” አንበል፤ እኔ አነጋግራቸኋለሁ በማለት ወደ መተማመን የሚወስደንን ግንኙነት እንጀምር፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በግምትና በይሆናል ያሰብናቸው ነገሮች እየተወገዱ በእውነታ ላይ ወደተመሠረተ እርግጠኝነት ይሸጋገራሉ፡፡ ይህም መተማመንን ፈጥሮ መተራረቅንና ፈውስ ለእያንዳንዳችን ይሰጠናል፡፡
አዲስ ግንኙነት ወደ አዲስ ሕይወት፤ ይህም ወደ አዲስ ተስፋ መርቶን አዲስ የተፈወሰች የሁላችንም ኢትዮጵያ በዚህ የእኛ ዘመን እውን ለማድረግ ፈጣሪ ሁላችንንም ይርዳን!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅንቄ (አኢጋን)
_______________________________________________________
ለተጨማሪ መረጃ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡- Obang@solidaritymovement.org
Ayalew says
Will you post Ato Obang Metto’s Speech please.
Thank you
eunetu says
I am glad to hear this timely information. If you send me its main objective and means to accomplish its goal, trust me I have something to contribute for our innocent people mocked by his own jealous children!!!
God bless Ethiopia!
”Eunetu”