ከአንድ አመት በፊት የሳውዲ አረቢያ መንግስት በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሃገር ዜጎች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው የግዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ አያሌ ኢትዮጵያውያን ጅዳ እና ሪያድ ከተማ ወደሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ግቢ መጉረፋቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ከነበረው ስርዓት አልበኝነት ህይወታቸውን ለመታደግ አቅሙ የቻለ ጎረምሳ ልብሶቹን በሻንጣ አጭቆ እግር አውጭኝ ሲል አይን ያልገለጹ ህጻናት ልጆቻቸውን በወጉ መሰብሰብ ያልቻሉ እናቶች ለክፉ ቀን ትሆነኛለች ብለው ገዝተው ያስቀመጡጥን ወርቅ እና የተለያዩ ጌጣጌጦቻቸውን የያዘች አነስተኛ ሻንጣ አንጠልጥለው ከቀማኞች ይታደገናል ወዳሉት በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ቅጠር ግቢ በማቅናት ለተውሰኑ ቀናቶች በመጠለል ሻንጣዎቻቸው በካርጎ ጭነት እንደሚላክ ቃል ተገብቶላቸው ብጣሽ ጨርቅ እንኳን ሳይዙ ባዶ እጃቸውን ወደ ሃገር ቤት ማቅናታቸው ይነገራል።
በወቅቱ በዚህ መልክ ወደ ቆንስላ ጽ/ቤት ቅጠር ግቢ የሚመጣውን ወገን ሃብትና ንበት በሃላፊነት ተረክቦ ወደ ሃገር መላክ የሚችል አካል ባለመኖሩ በጅዳ እና አካባቢው የሚኖሩ ታዋቂ ግለሰቦች ከዲፕሎማቱ ጋር በመተባበር “ወገን ለወገን” የሚል አንድ ኮሚቴ በማዋቀር ኢትዮጵያኑ በሰላም ሃገር እንዲገቡ ሰፊ የማስተባበር ዘመቻ ይካሄድ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ይህ ኮሚቴ ወደ ሀገር ተመላሽ ወገኖችን ስምና አድራሻ እየመዝገበ በአደራ ተቀብሎ ከሚሰበስበው ንብረት ባሻገር በተለያዩ ግዜያት በአሰሪዎቻቸው ተደብድበው ተድፍረውና ደሞዛቸው ተነጥቆ ወደ ቆንስላው ቅጠር ግቢ የሚመጡ እህቶች ጉዳይ ተድበስብሶና በደልን ተሸክመው ወደ ሃገር መሸኝት እንደሌለባቸው በማመን የቆንስላው ባለስልጣናት በዚህ ዙሪያ አንድ አይነት ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ያደርግ በነበረው ግፊት ኮሚቴው ከተሰጠው ሃላፊነትና ተግባር አፈንግጦል በሚል ቅሬታ በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ካድሬዎችና የአሰሪ እና ሰራተኛ ኤጀንሲ ደላሎች በተፈጠረው አለመግባባት የማህበሩ መስራቾች በቆንስላው ዲፕሎማቶች ትዕዛዝ ወደ ቆንስላው ግቢ እንዳይገቡ በመታገዳቸው የወገን ለወገን ህልውና ገና ከጅምሩ በአደራ የተረከበውን ንብረት ሜዳ ላይ በትኖ ከስመ።
በዛኔው መንገደኛ እና ሻንጣ በተለያዩበት የጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት የጎዞ መስተንግዶ አሳዛኝ ድራማ በተፈጠረው ስርአት አልበኝነት የተጠቀሱትን ሻንጣዎች ከአደጋ ለመከላከል ባሉበት ሁኔታ ሸራ ለብሰው ቀሩ። እህቶች ለአመታት ይደርስባቸው የነበረውን እንደወላፈን የሚፋጅ የአረብ ወይዛዝርት ቁጣ እና ግልምጫ ተቋቁመው ባገኙት ደሞዝ የሸመቱት ወርቅና የተለያየ ጌጣጌጦችን የያዙ ሻንጣዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አገልግሎት አቆመ በሚል ሰንካላ ምክንያት ወደ ሃገር እንዳይልኩ በቆንስላው ዲፕሎማቶች እገዳ ተጣለበት። የጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት ቅጠር ግቢ ተቆልሎ የሚታየው ይህ ሻንጣ ለወራት ዝናብ እና ፀሃይ እይተፈራረቀበት ባለቤት አልባ ሆኖ ድፍን አመት ካስቆጠረ በኋላ ሰሞኑን በሻንጣዎቹ ላይ አስነዋሪና አሳዛኝ ተግባር መፈፀሙ ተስማ። በተለይ በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ግቢ ውስጥ ከተደረደሩ ሻንጣዎች ውስጥ የአባዛኛው ቁልፍ መሰበሩን የሚናገሩ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ሻንጣዎቹ ላይ የተፈፀመው ዘረፋ የዲፕሎማቱ እጅ እንዳለበት በመረጃ አስደገፈው ይናገራሉ። ድርጅታዊ ጉባኤ የምትለዋን ቃል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ማታ ማታ ያለወትሯቸው ቆንስላው ግቢ የሚያድሩ ከዲፕሎማቱ ጋር የቀርብ ግንኙነት ያላቸው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባላት ግንባር ቀደም የዚህ ወንጀል ተዋናይ ሳይሆኑ እንደማይቀር ይጠረጠራል። እስክሁን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የተለያዩ ሻንጣዎች ቆልፍ እየተሰበረ በጥንቃቄ ብርበራ እንደተካሄደበት በተጨባጭ፡ ማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን የሰማያዊ “ማንዋል” ፓስፖርት የአገልግሎት ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ ፓስፖርት ለማስለወጥና ለማሳደስ የጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት በተከስተው የባለጉዳዩች መጨናነቅ ዲፕሎማቱ ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ቆንስላ ጽ/ቤት ለሚገባው ተስተናጋጅ የ3 ወር እና ከዚያ በላይ ቀጠሮ እየተሰጠው ሲሸኝ በሌላ አቅጣጫ ለሚስተናገድ ባለጉዳይ ከ5 ቀን ባልበለጠ ግዜ ውስጥ ሁሉም ነገር እንዲሚያልቅለት የሚናገሩ ባለጉዳዩች ዲፕሎማቱ እየሰጡ ባለው በሙስና የነቀዘ አገልግሎት ክፉኛ መማረራቸውን ይናገራሉ፡፡
በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልጋዩች በሚል ሽፋን ከዲፕሎማቱ ጋር ጥብቅ ቁረኝት ያላቸው የዚህ ወንጀል ተባባሪ ደላሎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ዙሪያ ለማነጋገር በቅርቡ በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ሃላፊ ሆነው የተሾሙትን አምባሳደር ውበሸትንም ሆነ ዲፕሎማት ሼሪፍ ኬሬን በአካል ለማገኘት ያደረኩት ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።
(Ethiopian Hagere Jed Bewadi ለጎልጉል የላኩት – ፎቶ በቆንስላ ቅጠር ግቢ የተቆለለው ሻንጣ)
Leave a Reply