አቶ መለስ መሞታቸውን መንግስት አላምንም ማለቱ ጉጉት ፈጠረ። መለስ ታመዋል የሚለው ወሬ ሹክ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ የሁሉም ጆሮ በመለስ እስትንፋስ ማለፍና አለማለፍ ዙሪያ የሚሰጡትን መግለጫዎችና ዜናዎች ማሳደድ ላይ ተጠመዱ። እስካሁን ለንባብ ባይበቃም አቶ መለስ ረጅም ሰዓት የፈጀ የአእምሮ ቀዶ ጥገና ካደረጉ በኋላ መንቃት በሚገባቸው ሰዓት ውስጥ ባለመንቃታቸውና ምንም ዓይነት የመንቃት ምልክት ማሳየት ባለመቻላቸው ሃኪማቸው “clinically dead” በማለት በህክምናው ረገድ ማረፋቸውን ተናግረው ነበር፡፡ ግን ህይወታቸው አላለፈችም የሚል ሪፖርት ማቅረባቸውን የቅርብ ምንጮች ከነገሩኝ ቆይቷል።
ሃኪማቸው እጃቸውን አጥብቆ ሲይዝ ምንም ምላሽ ባለመስጠታቸው በሙያው ቋንቋ የተስፋ መቁረጥ ሪፖርት ያቀረቡት ሃኪማቸው ከቀናት በኋላ በተመሳሳይ እጃቸውን ሲጨብጥ መለስም ያዝ በማድረግ ምላሽ ሰጡ፤ ከዚያ በኋላ ነበር እነ አቶ በረከት “መለስ አሉ” የሚል የውሃ ቀጂ አይነት እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ መስጠት የጀመሩት። ቀነ ቀጠሮ አስቀምጠው መለስ ህዝብ ፊት እንደሚቀርቡ ሲገልፁ የነበሩት አቶ በረከት ለመጨረሻው መርዶ ራሳቸው አይናቸውን አጥበው “ዛሬ ከባድ ሃዘን ላይ ነን። መልካም ወሬ ይዤ አልመጣሁም” በማለት ለወዳጆቻቸው መርዶውን አጠናከሩ።
ኢህአዴግ በመለስ ሞት ላይ የሚከተለውን ጊዜ የመግዛት ሩጫ ለማጠናከር አገር ውስጥ በነጻ ፕሬስ ስም የሚልከሰከሱትን ጋዜጦች ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት አሽከር ወይም “ቅምጥ” ሚዲያ መሆናቸውን አረጋግጦልናል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻ መግለጽ ይቻላል” በሚል በየመድረኩ የሚከራከሩት የፎርቹን ጋዜጣ ባለቤት፤ አቶ መለስ አገር ቤት ገቡ በማለት በቀይ ቀለም ሰበር ዜና አስነብበዋል። አቶ በረከት ስማቸው እንዳይጠቀስ አስጠንቅቀው የሰጡትን ወሬ በደማቅ ቀለም ያስተጋባው ፎርቹን የጻፈው ዘገባ ሃሰት መሆኑን አውቆ ራሱን ከኢንተርኔት ማማ ላይ እስከመሸሸግ ደርሶ ነበር። እንግዲህ የፎርቹን ባለቤት አቶ ታምራት የተዘረሩት እንደዚህ ነበር። አዲስ አድማስ የሚባለው ጋዜጣ ደግሞ እንዲሁ ስማቸው እንዳይጠቀሱ የጠየቁ ባለስልጣንን ጠቅሶ መለስ ቤተ መንግሰት ሆነው ከአራት ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት አገር እየመሩ እንደሆነ አስነበበ። አይ የኛ ሚስጢር ፈልፋዮች። ሪፖርተርም አቶ መለስ አሜሪካ በመዝናናት እየታከሙ ይገኛሉ ብሎ ቀለሙ የማይታወቅ ጠምባራ ዜና ለጠፈ። ይህን ጊዜ ነበር አንድ ተረብ በፌስ ቡክ ያየሁት “ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስና ፎርቹን አሳ እንዳይበላሽ በሚቀመጥበት ትልቅ ፍሪጅ ለታሪክና ለትውልድ መቀመጥ አለባቸው” በማለት ያሽሟጠጠው ስላቁ ለገባን ይገባናል።
በባሪያና በሎሌ መዋቅር ተገርግዶ፣ በአንድ ሰው ላይ ተቸክሎ ላለፉት 21 ዓመታት በጠመንጃ አስገዳጅነት ኢትዮጵያና ህዝቧ ላይ የተንሰራፋው ኢህአዴግ በድንገት መለስን መክሰሩ ቀድሞውንም ቢሆን ያልነበረውን ድርጅት ደራሽ ውሃ ጠርጎት እንደሚሄድ ቆሻሻ አግበስብሶት እንዳይወስደው ዝግጅት ለማድረግ ይመች ዘንድ ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱ የቆዩት እነ አቶ በረከት “መለስ አሉ” ባሉበት አንደበት የመለስን ህልፈት አመኑ። ቅድመ ቀብሩና የቀብሩ ስነ ስርዓቱ ላይ የተቆመረውን የፖለቲካ ቁማር ለተመለከተ በርግጥም ክህደቱ የዝግጅት ጊዜ ለማግኘት ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ያም ሆነ ይህ ህወሃቶች ጊዜ አግኝተው ሁሉንም አስኪደውታል።
“አስገራሚ፣ ታሪካዊና በትውልድ የማይረሳ” የተባለለት የአቶ መለስ የቀብር ስነስርዓት ከሁለት ሳምንት የሃዘን አዋጅ በኋላ ተጠናቋል። ለቀብራቸው 150 ካሬ ሜትር ቦታ የተከለለላቸው አቶ መለስ በህይወት ቆመው ከነቤተሰቦቻቸው የመኖሪያ ቤት ለመቀለስ 75፣ 90ና 105 ካሬ ሜትር ቦታ ከሚሰጣቸው በላይ ለአስከሬናቸው ከሊዝ ክፍያ ውጪ ለቀብር ሰፊ ቦታ በመውሰድ የመጀመሪያው ሟች ኢትዮጵያዊ ሆነዋል። ወደፊት ሊደረግ ከታቀደውና ከታሰበው ውጪ ማለት ነው።
የምስጋና ጎርፍ የወረደለቸው አቶ መለስ “በአገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ” ኢትዮጵያዊ ተደርገው ታሪክና ዝና ሲበጅላቸው እስኪታክት ድረስ ሰምተናል። አገራቸውን የሚወዱና ላገራቸው እድገት ሌት ተቀን ሲሰሩ ያለ እረፍት ባተው ማለፋቸው ህልፈታቸውን መራራ እንደሚያደርገው ባለሟሎቻቸው አስተጋብተዋል። ከ19 ዓመታቸው ጀምሮ ለህዝብ ሲሉ ራሳቸውን እንደ መስዋዕት በግ አድርገው ያቀረቡ ተደርገው፣ በአድናቆት ስሞች ታጅበው አንድ ክንድ መሬት ዘልቀው ላይመለሱ አፈር ተመልሶባቸዋል። የፖለቲካው ጡዘት፣ የመለስ ፍላጎትና ስወር አጀንዳ ላይ ያጠነጠነው ያገራችን ፖለቲካ ጦሱና ጥምቡሳሱ በቀላሉ ስለማይለቀን ስማቸውን ዘወትር ከጉድጓድ ለመፈለግ እንገደዳለን።
ለመሆኑ አቶ መለስ የተደረገላቸው ሁሉ የሚገባቸው፣ በተደጋጋሚ ታዞዦቻቸው እንዳሉት አገራቸውን የሚወዱ የዲሞክራሲ አባት ነበሩ? የሚመሩትን ህዝብና አገር ጥቅም በማስቀደም የሚታወቁ ኢትዮጵያዊ ስብዕና ያላቸው መሪያችን ነበሩ? ጭራሹኑ የሚመሩትን ህዝብና አገር አክባሪ ነበሩ? ባልተገደበ ስልጣንና ባልተገደበ የስልጣን ጊዜ በትረ መንበሩን ተፈናጠው ለ21 ዓመታት ሲገዙ የህዝብ አዎንታ ተቀብለው ይሆን? ብዙ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል። ታዲያ ለነዚህና መሰል የመለስ ማንነትና ግብር ላይ የሚንከባለሉ ጉዳዮችን አንስተን ብንጠይቅ መልሱ አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ አይሆንም።
ለመንደርደሪያ ይህንን ካልኩ የጽሁፌ መነሻና መድረሻ ወደ ሆነው ሃሳብ ላምራ። ከበርካታ የኑሮና የሙያ ባልደረቦቼ ጋር በመለስ ሞት ዙሪያ ስንወያይ አንድ የሚያሟግት አጀንዳ ተነሳ። አጀንዳው ባጭሩ “የኢትዮጵያ ህዝብ ሰለባ ሆነ” የሚል ነው። በመለስ ሞት ሳቢያ ሃዘን ለመድረስ ይሁን ለወሬ የህዝብ ጎርፍ መታየቱ ህዝቡ የኢህአዴግ ሰለባ መሆኑ አሳዛኝ ጉዳይ እንደሆነ አድርገው የወሰዱት በሌላ በኩል ደግሞ በህዝብ ተስፋ ቆርጠናል የሚሉ አጋጥመውኛል።
“የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ ከአገር ውስጥ አልፎ ዲያስፖራውንም አመንዥጎታል” የሚል መከራከሪያ የሚያቀርበው የሥራ ባልደረባዬ “ስለ አቶ መለስ ህልፈት መረጃ የሚያቀብል አማራጭ መገናኛ ባለመኖሩ አይኖች ሁሉ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ለመቸከል ተገደዋል። አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ መስማት ደግሞ እምነትን ባይንድም ሊሸረሽር ግን ይችላል” ባይ ነው።
“የአቶ መለስ አስከሬን አቀባበል ይደረግለታል ስርጭቱን በቀጥታ ከኢቲቪ ተመልከቱ፣ የአቶ መለስ የቀብር ስነስርዐትና ፍትሃት በቀጥታ በኢቲቪ ይተላለፋል” ወዘተ የሚሉትን ዜናዎች አንዳንድ በዳያስፖራ የሚገኙ የተቃዋሚ ድረ ገፆች ወሬያቸው አድርገውት እንደነበር የሚጠቁመው ባልደረባዬ “የኢህአዴግ ስብከት ሰለባ የሆነው አገርቤት ያለው አማራጭ ሚዲያ የሌለው ህዝብ ብቻ ሳይሆን በውጪ አገር አማራጭ መገናኛ መጠቀም የሚችሉትም ናቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ይናገራል።
የቴክሳስ ነዋሪ የሆነው ሌላ ተከራካሪ በማስጠንቀቂያ ይጀምራል። “ህዝብ ጥፋተኛ ሆኖ አያውቅም፤ ህዝብ ላይ መፍረድ የሚጀምር የፖለቲካ ትግል ራሱ ላይ ሞት የማወጅ ያህል ነው” ይላል፡፡ ለማስጠንቀቂያው ማብራሪያ አለው። “በመጀመሪያ ደረጃ ኢህአዴግ በጎንዮሽና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የሰበሰባቸው አባላት ከልብ ባይከተሉትም ቀላል ቁጥር የላቸውም። እንደሚወራው በሚሊዮኖች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከስራም ሆነ ከተለያዩ ጥቅማቅሞች እንዳይስተጓጎሉ ቀብር ማድመቅ አለባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ቀብር ወጣ፣ ለቅሶ ደረሰ፣ አስከሬን አጀበ፣ አለቀሰ የተባለው ህዝብ ለምን ምን እንዳደረገ በነጻ ሚዲያ ተጠይቆ ሃሳቡን በነጻነት ሲሰጥ አልገለጸም። አንድ ሚዲያ (ኢቲቪ) በተጠና መንገድ ያቀረበውን መረጃና ስዕል ተመልክቶ “ህዝብ ተሰለበ” ማለት አግባብ አይሆንም፤ ይህ አደገኛ አካሄድ ሊታረም ይገባዋል።”
“በተጠና የተሰራ” ስለሚለው የኢቲቪ ፕሮፖጋንዳ ሲያብራራ “የተቀረፁትን ምስሎች በጥንቃቄ ሲመለከታቸው ውስን ሰዎች አስተያየት የሚሰጡበት፣ ከሩቅ የተቀረጸ ህዝብ ካሳዩ በኋላ አሁንም አቅርበው የተመረጡ አስተያየት ሰጪዎች የሚቀርቡበት፣ በቅርበት (close up) የሚያለቅሱ ሰዎች ተለቅመው በየመካከሉ ህዝብ እያሳዩ የሚከቱበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ማስተዋሉን” በዋቢነት የሚገልጸው የቴክሳሱ ተከራካሪ “አቶ መለስን የሚወዱና በሳቸው አማካይነት ተጠቃሚ ሆኑ በርካቶች መኖራቸውም የማይካድ” መሆኑንን ያስገነዝባል።
በጀርመን አገር ነዋሪ የሆነው ሌላው ባልደረባዬ “ላለፉት 21 ዓመታት የራሱን ግዛት ሲገነባ የኖረ፣ ከሱ ሌላ ማንመም ሰው እንዳይታይ አድርጎ የገዛ፣ መረጃና አማራጭ መገናኛዎችን ጠርቅሞ በመዝጋት ብቻውን ሲመለክ የኖረ ሰው ሲሞት አስደንጋጭ” እንደሆነ ይናገራል። “ንጉሱ ሲሞቱ ፀሐይ ጠለቀች ተብሎ ነበር። መንግስቱ ሲኮበልሉ አገር አበቃላት ተብሎ ነበር። መለስ ሲሞቱ አማራጭ እንዳለው በውል ያልቀረበለት ህዝብ “ቀጣዩ ምን ይሆናል” በሚል ደንግጦ አደባባይ ቢወጣ አይደንቅም” ይላል።
“በ1997 ምርጫ ወቅት የተፈጠረው ጠባሳ መዘዙ አሁን ድረስ እንዳለ የሚናገርው ይኸው የጀርመን ነዋሪ፤ ተቃዋሚዎች እርስ በርስ የሚጣሉ፣ የሚከፋፈሉ፣ ከኅብረታቸው ይልቅ ልዩነታቸውና አለመግባባታቸው ጎልቶ መታየቱ… ህዝብ ማን አማራጭ አለን? ብሎ እንዲጠይቅ፣ መለስም ይህንን ክፍተት በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት መኖራቸውን” አስታውሶ “ተቃዋሚዎች የሚዲያ እጥረት፣ አፈናና የአቅም ችግር ቢኖርባቸውም የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ህዝብ ጋር መድረስ የሚችሉበት አሰራር ነገ ዛሬ ሳይባል ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው” በማለት ሌላ አነጋጋሪ አጀንዳ ያስቀምጣል።
መለስ ገና በ1983 ዓ ም የአዲስ አበባ ቤተ መንግስት እንደረገጡ የአገሪቱን ሠንደቅ ዓላማ ከማናናቅና ጀምሮ አንዱን ብሄር ከሌላው ጋር የሚያናቁር በመርዝ የተለወሰ ፖለቲካቸውን መርጨት ጀመሩ። “ነፍጠኛ” የሚለውን ሃረግ ባንድ ብሄረሰብ ላይ ለጥፈው ተበታትነው የሚኖሩ ዜጎች በጅምላ እንዲጨፈጨፉ ምክንያት ሆኑ። በርካቶች ከኖሩበት ምድር ሃብትና ንብረታቸውን ጥለው እንዲፈናቀሉ ተፈረደባቸው። ይህ ብቻ አይደለም መለስ ለኤርትራና ለኤርትራ ጥቅም መከበር ባላቸው የማያወላውል አቋም ኢትዮጵያ በህገወጥ ንግድ እንድትዘረፍ የሚያመች ፖሊሲ ነድፈው አንድ እግር የቡና ተክል የሌላት ኤርትራ ቡና ላኪ በመሆን ከአፍሪካ ግንባር ቀደም አገር እንድትሆን አስቻሉ።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራር ሰጪነት ከወገን ይልቅ ኤርትራውያን ታምነው ዜጎች በመጤዎች እንዲረገጡ፣ እንዲገረፉ፣ እንዲታሰሩ፣ እንዲዘረፉና እንዲሸማቀቁ አደረጉ። ይህ ብቻ አይደለም ዓለም ማመን እስኪያቅተው ድረስ ኢትዮጵያ ወደብ አያስፈልጋትም ብለው ህጋዊና ታሪካዊ የአሰብ ወደቧን በጥድፊያ ለኤርትራ አዛወሩ። ኢትዮጵያዊያንን በቅኝ ገዢነት ለሚወነጅለው ሻዕቢያና ተከታዮቹ ተሽቀዳድመው እውቅና በመስጠት የኢትዮጵያን ህዝብ አሳፈሩ። “ለመዋጋት የምትፈልጉ ካላችሁ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” በሚል የሚመሩትን ህዝብ ተዛበቱበት። አገሪቱ የእርሻ ውጤቶቿን አሰባስባ ወደ ውጭ በመላክ የምታገኘውን ምንዛሪ ለጅቡቲ እየገበረች የጅቡቲ ተንበርካኪ እንድትሆን ፈረዱባት። ታፍሮና ተከብሮ የኖረ ህዝብ እንዲቀል አደረጉ።
ከታላቁ ምሁርና ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር አስራት ጀምሮ ኦሮሞው፣ አማራውና መለስን የተቃወሙ ሁሉ እንዲገደሉ፣ እንዲታሰሩና ቶርች እንዲደረጉ ከፍተኛ በጀት የሚበላ የአፈና ተቋም በማቋቋም አገሪቱን አማራጭ መረጃ እንዳይሰራጭባት በሯን ዘግተው የቀድሞ ታሪክና መልካም ገድል እንዲኮስስ ከፍተኛ በጀት መድበው እስከ መመለክ የሚያደርስ ስብዕና ተከሉ። ይህ አካሄዳቸው ያላማራቸው ባገር ክህደት ወንጅለዋቸው ከዛሬ ነገ አበቃላቸው ሲባል አንሰራርተው የተነሱባቸውንና ልዩ ሃሳብ የሚያራምዱትን የትግል አጋሮቻቸውን በሉ። በህይወት ያሉት መንቀሳቀስ በማይችሉበት ሁኔታ አቀዘቀዙዋቸው። እንግዲህ አገር ይያዝ የሚባልላቸውና ህዝብ ደረቱን እየደቃ ቀበራቸው የሚባሉት አቶ መለስ በቅንጭቡ እንዲህ ይመስላሉ።
ኤርትራ የምትባለዋ አንድ ክፍለሃገር ጉልበት ፈጥራ ኢትዮጵያን ለመውረር መነሳቷ አስገራሚነቱ ብቻ ሳይሆን ወኔውን ከየት አገኘችው የሚለው ስላቅ በኢትዮጵያ ህዝብና በትግራይ ምስኪን ወገኖች ላይ ተግባራዊ የተደረገው አሁንም በመለስ የአቋም መርመጥመጥ መሆኑ ማንም ሊያብለው የማይችለው እውነት ነው። ኢትዮጵያዊያን ላይ የተወረወረው ንቀት እንዳለ ሆኖ ንቀቱ ሊተገበር ዝግጅቱ መጠናቀቁ ሲገለጽ “ኤርትራና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ጅራፍ አይጮህም” በማለት ውርደታችን ላይ ስላቅ ያርከፈከፉት በትግራይ ህዝብ የሚምሉት አቶ መለስ ናቸው። የሃይደር ህጻናት በቦንብ ሲቆሉ፣ በቦንብ ሲታጨዱ አቶ መለስ “ኢትዮጵያ የአየር ሃይል አያምርባትም” ብለው አስተማማኝ መከላከያችንን አፍርሰውት ነበርና የሚከላከል አልነበረም። ይልቁኑም የኢትዮጵያ ጀቶች ተዘርፈው ኢትዮጵያውያንን እንዲፈጁ የፈቀዱት ራሳቸው አቶ መለስ የጦር ሃይሎች አዛዥ እንጂ ሌላ ማንም አልነበረም። ለኚህ ሰው ነው አገር ማቅ የገባ እስኪመስል “አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስነ ምግባር” የተላበሰ ለቅሶና ሃዘን የታወጀላቸው። ድንቄም ሃዘን!! ነገ ሲገለጥ የሚሳቅበት የሚበን ተረት!!
ሌላው እንደ ቀላል የተያዘው ጦርነቱን ለመመከት የሁለት ዓመት ዝግጅት ሲደረግ ሽባ የነበረውን የመከላከያ አቅም “ሆ” ብሎ ያፈረጠመው የኢትዮጵያ ህዝብ ውለታው በሳምንታት ውስጥ ተዘንግቶ የልጆቹ ደም የውሻ ደም እንዲሆን ያደረጉት አቶ መለስና አቶ መለስ ብቻ መሆናቸው ነው። በቀድሞው እልሁ ቆስቋሽነት የተመመው አይበገሬው የኢትዮጵያ ሰራዊት ቂሙን ረስቶ ጦርነቱን ባጭር ቀን በድል ከተወጣ በኋላ ሞቱና አጥንቱ እንደ ተራ ነገር ተቆጥሮ “የያዝከውን ቦታ ለቀህ ውጣ” የተባለው አሁንም በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ እንጂ ሌላ በማንም ትዕዛዝ አልነበረም። የሻዕቢያ አጀንዳ ያኔ መዘጋት ሲችል፣ ባሸናፊነት የተደመደመን ጦርነት ወደ ፍርድ ቤት በመምራት አሰብን በመስጠት የተጀመረው ኢትዮጵያን የማሳነስ ስትራቴጂ ባድሜን ለማስረከብ ተስማምቶ ተዘጋ። ወንድሞቻችን ህይወታቸው የተዘራበት፣ አጥንታቸው የተከሰከሰበት፣ ደማቸው የጎረፈበት፣ ስጋቸው የተበጣጠሰበት ምድር መጨረሻው ሃፍረትና ክህደት ሆነ። አቶ መለስ በማጭበርበር ክህሎታቸው “ባድሜ ለኢትዮጵያ ተፈረደ” ብለው አቶ ስዩም ለህዝብ መግለጫ እንዲሰጡ ሲያዙ ወይም መንግስታቸው በበነጋው በየድረገጹ ይፋ የሚሆነውን እውነት አጣሞ እንዲያቀርብ ማዘዛቸው ምን ያህል ለህዝብና ለአገር ያላቸውን ክብረ ነክ አቋም የሚያሳይ ነው። አኚህ ሰው ናቸው “ባገራቸው ጥቅም የማይደራደሩ” የተባለላቸው። “አገራቸውን ከምንም በላይ የሚወዱ” ተብሎ እሳቸው የማይፈልጉት ታሪክ የሚጻፍላቸው። “ላገራቸው ልዕልና ሲሉ እረፍት የሚባል ነገር ሳያዩ ያረፉ ታላቁ ባለብሩህ አእምሮና ባለራዕይ መሪ” ተብሎ የሚዘፈንላቸው።
በየትኛውም ጊዜና ዘመን መከራከሪያ የማይቀርብለትን የ1997 ምርጫ ሽንፈት በአልሞ ተኳሾች ያስገለበጡ፣ ወላጆችን ያለጧሪ ያስቀሩ፣ “ድምጻችን ለምን ይነጠቃል” በሚል የተቃወሙ ወገኖችን እስር ቤት በማጎር የማይረሳ ጥቁር ጠባሳ ያስቀመጡ፣ የሚቃወሟቸውን በአንድ ጀንበር ህግ እያዘጋጁ ህጋዊ መስለው የሚያሳድዱ፣ አገሪቱ ውስጥ የተለየ ሃሳብና አቋም ማራመድ እንዳይቻል ነጻ ፕሬስን የዘጉ፣ ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት እየወነጀሉ እስር ቤት የሚያጉሩ፣ እንዲሰደዱ የሚያደርጉ፣ ሰርተው ያገኙ ባለሃብቶችን በማክሰም እሳቸው ያፈሯቸው “ልማታዊ” ባለሃብቶች እንዲተኳቸው ያደረጉ፣ አባትና ልጅ፣ እህትና ወንድም የማይተማመኑበት የስለላ መዋቅር መኖሪያ ቤት ድረስ ያስዘረጉ፣ ድህነትን የዓላማ ማስፈጸሚያ በማድረግ የሚበሉት የሌላቸው ዜጎች ወገኖቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሰልሉ የሚያስችል መዋቅር የዘረጉ፤ እሳቸው የፈጠሩትን ስርዓት የማይደግፉ ከስራ እንዲባረሩ የሚፈርዱ፣ አዲስ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ፕሮግራም ደራሲ በመሆን በቅንጅት ወቅት ድጋፍ የሰጡ ዜጎች ጦም አዳሪ እንዲሆኑ ፈርደው በርካቶች በሰበብ አስባቡ ከስራ እንዲሰናበቱና ከሃላፊነታቸው ወርደው በካድሬዎች እንዲተኩ ላደረጉ ዘረኛ መሪ ህዝብ አነባ እያለ ኢቲቪ ይነግረናል። እኛም ይህንኑ እንደ በቀቀን በማስተጋባት “የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይታመን ነው፤ አሽቃባጭ ነው …” በጅምላ እፈርጃለን፡፡
በብሔር ብሔረሰቦች ስም የሚገዘቱት አቶ መለስ የኦጋዴን ህዝብ ተከቦ ያለ አንዳች የምግብ አቅርቦት ለዓመታት እንዲደቅ ከተደረገ በኋላ በጅምላ እንዲጨፈጨፍ ያደረጉ መሪ ናቸው። ምስኪኑ የጋምቤላ አኙዋክ ሕዝብ እትብቱ ከተቀበረበት የነፍሱ መፈጠሪያ ምድር ላይ እንዲፈናቀል፣ ሲቃወም እንዲረሸን፣ በጅምላና በተናጠል እንዲገደል፣ እንዲታሰር የፈረዱበት የጎረቤት አገር ገዢዎች አይደሉም። አሁን ለኦጋዴን ህዝብና ለአኙዋክ ወገኖች የመለስ ሞት ምናቸው ነው? የዛፍ ጥላ ስር ከልጆቻቸው ጋር ተቀምጠው ፈጣሪያቸውን አንጋጠው የሚማጸኑ አዛውንትን ከነቤተሰቦቻቸው እንዲረሸኑ ትዕዛዝ የሚሰጡ መሪ በየትኛው የህሊና ዓይን እምባ ይወርድላቸዋል? የበላን ያብላላል ካልሆነ በስተቀር፡፡
ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። አቶ መለስ ኢትዮጵያዊ ቃና የሌላቸው መሪ ስለመሆናቸውና ኢትዮጵያን ከቶውንም እንደማይወዷት ለማንም የተሰወረ አይደለምና ወደ መቋጫዬ ላምራ። ለማንም የተሰወረ አይደለም ስል ግን ከላይ እንዳልኩት በሙስና ለነቀዙትና የበላን ያብላላል ያልኳቸው አይመለከትም። ከባልደረቦቼ ጋር ስንነጋገር በተነሳው የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ “ሰለባ” የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ አንድ ልበል። በርግጥ አማራጭ መሪ የሌላቸው ወይም አማራጭ መሪህ እገሌ ነው ወይም አማራጭ መሪያችን እገሌ ናት ያልተባለ ህዝብ አምባገነንም ቢሆን መሪው ሲሞት ይደነግጣል። ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር “እኔ ከሌለሁ” በሚል አስከሬን፣ መቃብር፣ ዋይታ፣ ኢንተርሃምዌ፣ የርስ በርስ ሰው ሰራሽ የዕልቂት ሪፖርት /አኬልዳማ/ እየደረሰ በተቆጣጠረው ሚዲያ በማስተላለፍ ህዝብን ሲያስፈራራ የኖረ መሪ ሞቱ ቢያስደነግጥም አይገርምም። የሚገርመው “ህዝቡ የፕሮፖጋንዳው ሰለባ ሆኗል” የሚለውን አደገኛ ከህዝብ የሚለይ ትርጉም አልባ አስተያየት መስማት መጀመራችን ይመስለኛል። ምናልባትም ለዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ከተገዛን አቶ መለስ አልሞቱም ወደ ማለቱ እናመራለን።
ኢህአዴግ በጥልፍልፍ ጥርነፋና ድህነትን ምክንያት ያደረገ አደረጃጀት እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ ማህበራትና የአነስተኛ ስራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች የያዘቸውን አባላት ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ አስከሬናቸውን ሊቀበል የወጣው በአጋጣሚ ሳይሆን በድርጅታዊ መዋቅር ነው። እስከጎጥ በወረደ መመሪያ ወደ ጎዳና የወጣው ህዝብ፣ በተለይም ዋንጫ እንደወሰደ የመንደር ቡድን አስከሬን የያዘውን መኪና አጅበው “ሆ-ይና ሆ..” ሲሉና “ትጨርሰዋለህ” እያሉ ስለ አባይ ሲፎክሩ ሃዘን አይመስልም ነበር። እነሱን ደምረን የመለስ ሞቱ አሉ ወሬ ለሁለት ወር ያሰለቸው ህዝብ ለማረጋገጥ ለወሬም መውጣቱ አያከራክርም። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ግን በድርጅት ተዋረዳዊ መዋቅር ክፍያና አበል ተሰጥቶ የተከናወነው ቤተመንግስት ወ/ሮ አዜብና ልጆቻቸውን ለቅሶ የመድረስ ሂደት አንድም ባህላችን፣ በሌላ መልኩ ተደፍሮ የማያወቅን ቤተመንግስት ለማየትና “ቤተመንግስት ገባሁ” ለሚለው ወሬ ሲሉ የነጎዱ ይበዙበታል። ለነገሩ ኢህአዴግ ሆን ብሎ ይህን ያደረገው ለወሬ እንደሆነ ስለሚረዳና አንዱ የቅስቀሳው አካል እንደሆነ ስለሚያምንበት ነው። እዚህ ላይ ቆቅነታቸውን መዘንጋት የዋህነት ይሆናል። የመለስ ሞት ከታወጀ በኋላ ያረጋገጥነውም ይህንኑ ነው።
በመለስ ሞት ቅድመ ዝግጅት አድርጎ የመጣው ኢቲቪ “ጎዳና ላይ የማድረው አቶ መለስን ተማምኜ ነው” በሚል የሚያወናጭፈው የሚቀረና ቅስቀሳ ከመሳቂያነት ሊያልፍ አይገባውም። ለማስታወቂያ እንኳን ብቁ አይደለም። አገርና ህዝብ አሁን ከምንጊዜውም በላይ “መሪዬ ማን ነው?” እያሉ ነውና ይህንን መሪ ፈልጎ ማግኘት፣ ራሱን ሸሽጎም ከሆነ “እኔ መሪ ነኝ” ብሎ እንዲወጣ ድጋፍ የምንሰጥበት ወቅት ይመስለኛል። ምን ተባለ ምን ህዝብ ስህተት የለበትምና ወደ ህዝብ ለመድረስ ሁሉም የአቅሙን ማድረግ ይገባዋል ባይ ነኝ። ህዝብም አማራጮቹ ወደሱ ሲመጡ ተቀብሎ ሊያግዝ ግድ ይለዋል። በውጪ አገር ያለነው ግን ከሁሉም በተለየ አማራጭ ሚዲያ አውሮፓና አሜሪካን አልፎ አገር ቤት የሚዘልቅበትን አግባብ ማገዝ ለነገ የሚባል አይሆንም። ራሳችን መረጃውን ፈልፍለን አውጥተን ህዝባችንን ማሳወቅ አለብን እንጂ “የነገውን ለቅሶ በተመለከተ ኢቲቪን ተከታተሉ፤ ለቅሶም በዚያው ድረሱ” እየተባለ የሚሰራው የማስታወቂያ ሥራ ቆም ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ዛሬ የታየው አብይ ችግርና የሰለባነት ጥያቄ የአማራጭ ሚዲያና መረጃ የማጣት ችግር ነውና የመረጃ ረሃብ ላለበት ህዝብ በቅድሚያ የመድረስ ጥያቄ የፖለቲካው ስራ ሀ፣ሁ መሆን ይገባዋል!!
*******************************************************************************************
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Meaku says
Guys, great Job.