በአንድ ወቅት የዓለም ገናና ንጉስ የነበረው የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነፆር ለ43 ዓመታት ባቢሎንን ገዝቷል፤ በስተሰሜን ሶሪያ በምዕራብ በፍልስጤም እስከ ግብፅ ግዛቱን አስፋፍቷል፡፡ ይህ ንጉስ ህጎችን ከመቀፅበት ይደነግጋል፣ ይለውጣል፡፡ ለእሱ ስርዓት ተገዥ ያልሆኑትን ያስራል፣ ይገርፋል፡፡ ንጉስ ናቡከድነፆር በጣም የሚፈራ እና ኃይለኛ ንጉስ ቢሆንም ከመውደቅ ግን አልዳነም፡፡ ለማንኛውም የዚህ ንጉስ ታሪክና የሀገራችን መንግስት ስርዓት ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገሮች ስላሉ እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡
ንጉስ ናቡከድነፆር በዘመኑ በጣም የሚፈራ እና የማይደፈር እንደመሆኑ መጠን የፈለገውን የማድረግ መብት ነበረው፡፡ በዚህም መሰረት ነው የሌለባቸውንና መልክ መልከኞችን ጥበብና ዕውቀት የሞላባቸውን በብልሀት ዳኞችንና አስተዋዮች የሆኑትን በንጉሱም ቤት መቆም የሚችሉ ብላቴናዎችን በእስራኤል ልጆች ከነገስታቱ እና ከመሳፍንቱ ዘር ይመጣ ዘንድ ለጃንደራቦቹ አለቃ ለአስፋኔዝ ነገድ ዳንኤል 1,3,4፤ የተመረጡትም ወጣቶች ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ፡፡ በእርግጥም እነዚህ ወጣቶች ጤናማ አዕምሮና አካል እንዲሁም ጥልቅ ማስተዋል ጥበብና ዕውቀት ነበራቸው::
ንጉስ ናቡከደነፆር እነዚህን ወጣቶች ከባቢሎናውያን ስርዓት ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ ንጉስ የከላዳውያንንም ትምህርት ቋንቋ ያስተምራቸው ዘንድ ጃንደረቦቹን አዘዘ፡ ፡ ንጉሱም በእርሱ ዘንድ እንዲቆሙ ስለሚፈልግ ከንጉስ መጠጥና መብል በየዕለቱ እንዲወስድላቸው አዘዘ፡፡ ስማቸውንም ቀየረ፡፡ ንጉስ የእነዚህን ወጣቶች ስም የቀየረው በራሱ መስመር ለሱ እንዲስማማው እና የእሱ ተገዥ እንዲሆኑ ለማሳወቅ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ስማቸውንም ቢቀይረው የዓላማ ፅናታቸውን ግን መቀየር አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ናቡከደነፆር የግዛቱን አንድነት ለማጠናከር በማሰብ በዱር ሜዳ አንድ የወርቅ ምስል አቆመ፡፡ የምስሉ ርዝመት 60 ክንድ (27 ሜትር) ወርዱ 6 ክንድ (2.7 ሜትር) ነበር፡፡ ንጉስ በዚሁ ምስል የምረቃ ሰነ ስርዓት አዘጋጅቶ መሳፍንቱንና ሽማምንቶቹን፣ አገር ገዥዎቹን፣ አማካሪዎቹን፣ የህግ አዋቂዎችን ሰብስቦ ላሰራው የወርቅ ምስል የእምቢልታና የዘፈን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ተደፍተው እንዲሰግዱ፣ ካልሰገዱ ደግሞ በሚነደው የእቶን እሳት ውስጥ እንደሚጣሉ ተነገራቸው፡ ፡ ሙዚቃው መሰማት ሲጀምር ያ ሁሉ ባለስልጣን ተደፍቶ ሲሰግድ እነዚያ አስተዋይና ጥበበኞች ወጣቶች ግን ቀጥ ብለው ቆሙ፤ የወጣቶችን አለመስገድ ያዩ የንጉሱ ታማኞች ንጉሱ ዘንድ ሄደው ወጣቶቹን ታማኝነት በማጉደልና ሀገርን በመክዳት ወንጀል እንዲያቃጥላቻ ጠየቁ፤ ንጉሱም ላሰራው ምስል እንዲሰግዱ፣ እምቢ ካሉ ግን እቶን እሳት ውስጥ እንደሚጥሏቸው ቢያስጠነቅቃቸውም አንሰግድም ብለው ከአቋማቸው ሳይነቃነቁ ቀሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ይህ አምባገነን የነበረ ንጉስ የፈቀደውን የሚገድል፣ የሚያስር፣ የሚመታ እና የሚያዋርድ እንዲሁም ለእሱ ተገዥ የሆኑትን ደግሞ ከፍከፍ የሚያደርግ ነበርና እነዚህን ሶስት ወጣቶች ከዚያ ከሚቀለቀል እቶን እሳት ውስጥ ከተቷቸው፡፡
ኢህአዴግ እንደ ናቡከደነፆር
በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግ እየሰራ ያለው ይህንኑ የንጉስ የናቡከደነፆር አይነት ስራ ነው፡፡ በፈለገው ሰዓትና ቀን ህገ መንግስቱን ይሽራል፣ ይለውጣል፡ ፡ ማሰር መምታትና መግደል ካሰኘው ያደርገዋል፡፡ እሱ በሚጠራው ሰልፍና ስብሰባ ላይ በግዳጅ እያስወጣ ፓርቲው ህብረትና አንድነት እንዲሁም ሙሉ ኃይል ያለው ያስመስላል፡፡ በትምህርት ውጤታቸው የላቁ ልጆችን በየትምህርት ቤቱ እየዞረ አባል እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የ‹‹ኢህአዴግዝም››ንም እምነት ይከተሉ ዘንድ በወጣት ሊግና ፎርም አደረጃጀት ይጠይቋቸዋል፡፡ ከዚያም በየስብሰባው ሚሪንዳና ቦንቦሊኖ እያደለ በብሔር ብሔረሰቦች ዘፈን እያስጨፈረ ስለ ደርግ ጭፍጨፊነት እና ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭራቅነት እየሰበካቸው እሱን እሱን ብቻ እንዲያመልኩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚሁ የኢህአዴግዝም እምነት ጠንካራ አምላኪ ከሆንክ ደግሞ ያለ ውድድር ስራ መግባቱ፣ ሹመትና እድገቱ፣ ቤትና መኪናው፣ 10ኛ ክፍልን ሳትጨርስ አመራር ቦታ ላይ መቆሙ፣ በቃ ምን አለፋህ… ሁሉ በእጅህ ነው፡፡
ኢህአዴግ ከድሮው ንጉስ ናቡከደነፆር የሚለየው ሳይሰራ ሊያሰግድ የሚጥር ግትር መሆኑ ነው፡፡ ማሰገዱ በጎ ባይሆንም የድሮው ንጉስ ያሰግድ የነበረው ለህዝብ የሚታይ ነገርን ሰርቶ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን እንዲሰገድለት የሚፈልገው በማይታየው፣ በሌለውና ባልተሰራው ስራው ነው፡፡ በአጭሩ ያላዩት እንዲያምኑት የሚፈልግ የዘመኑ ነብይ ለመሆን ይሞክራል፡ ፡ ትራንስፎርሜሽን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስትና ሌሎችም…. የሚጨበጡ የሚያዙ አይደሉም፡፡ እነዚህ የማይጨበጡ ነገሮችን ግን ከምንም በላይ አጋንኖ ያቀርባቸዋል፡፡ በእነዚህ ስራዎች፣ ለእነዚህ ‹‹መሃንዲስ›› ለተባሉት ካድሬና መሪዎቹ እንድንሰግድለት ይጠብቃል፡፡
በአጠቃላይ ልክ በድሮ ዘመን የነበረው ናቡከደነፆር ያደርግ እንደነበረው ለኢህአዴግና ለመሪዎቹ ለሰገደ ሁሉ ከሚገባው በላይ ከአገርና ከህዝብ ጥቅም ይሰጠዋል፡፡ ይዘርፋል ማለት ይቀላል፡፡ ኢህአዴግ ሳይቀር ያወጣውን ህግ ጠቅሶ ‹‹መብቴ ነው!›› እያለ፣ ለመስገድ አሻፈረኝ ያለ ግን እንደ ሶስቱ ወጣቶች የዘመኑን የእሳት ነበልባል ይቀምሳል፡፡ ወደ እስር ቤት ይወረወራል፡፡ ይደበደባል፡፡ ከስራ ይባረራል፡፡
ነገር ግን አንተ እውነተኛው የኢትዮጵያ ልጅ ከራስህ ጥቅም ይልቅ የሀገርህን ጥቅም የምታስቀድም ከሆነ እና ከምግብ ይልቅ ነፃነት፣ ከብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን፣ ከውሸት ይልቅ እውነትን መርጠህ ይህን መንግስት ከተቃወምክ ወይም ከተቸህ የኢህአዴግ አምላኪዎች በገባህበት እየገቡ ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ስድብና ዱላ መለያህ ያደርጉልሀል፡፡ ይህ ነገር ግን አቋምህን ሊያስቀይረው አለመቻሉን ሲያውቁ ደግሞ ደስ የምትል ውሸት አቀናብረው ፊልም ይሰሩ እና አሸባሪ፣ ከዳተኛ፣ የሀገር ጠላት ብለው ንጉስ ናቡከደነፆር እሳት ውስጥ እንደከተታቸው ሶስቱ ወጣቶች ሁሉ ኢህአዴግም ይወረውርሃል፡፡ ከደበርከውም ያስወግድሃል፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ዛሬም አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤልን የመሳሰሉ ወጣቶች እንዳሉ ያወቀ አልመሰለኝም፡፡
በእርግጥ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ወጣቱ ሀገራዊ ጉዳይ አያገባኝም ብሎ እርፍ ብሎ ቢታየውም ዛሬ ደግሞ እንደ አዲስ መታሰርም መደብደብም ሆነ መሞት የማይፈሩ፣ ባመኑበት እንጂ ለማያምኑበት ነገር የማይገዙና የማይንበረከኩ፣ ጥቅማ ጥቅም የማያታልላቸው፣ ለመብታቸው የሚታገሉ ለሀገራቸው ክብር የሚቆረቆሩ እና ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሀገራቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ወጣቶች ማቆጥቆጥ ጀምረዋል፤ በቅለዋል፡፡ እናም ኢህአዴግ ሆይ! እንደ ንጉስ ናቡከደነፆር ከመሆንህ በፊት መንገድህን አስተካክል! (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)
asdf says
I like your thoughts!!!
Netsanet says
Well said; better to stay poor than being woyane’s servant. Trading country for money/personal advantage is morally wrong; Historical mistake especially for young people. Woyane will be gone; country and people always live forever. Lemialf Ken, Cadre Mehon, Tizibt New Tirfu. Better to die with dignity.