የአቶ ጌታቸው ረዳን የአማራ ነገድ ጋዜጠኞች እና ልሂቃኖች አማራውን በማዳከም የወያኔ መጋዝ ይዘው በግዝገዛው ሴራ ላይ እየተሳተፉ ናቸው። “ኢሳት” ጭምር። ጌታቸው ረዳ የሚለውን ጽሁፍ ሳነብ፣ ምንም እንኳ ከስብሰባው አዘጋጅ ከሞረሽ ወገኔ መግለጫ ይወጣል ብዬ ስጠብቅ እስካሁን ባላይም፣ በኢሳት ሴራ በጣም ማዘኔንና፣ የሞረሽ ወገኔን ደግሞ “እሰጥ – አገባ” ውስጥ አለመግባት የድርጅቱን በራስ መተማመን ያሳየኝ ክስተት መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ።
ሞረሽ ስብሰባውን ሲጠራ በማስታወቂያው፡-
በኢትዮጵያና በአማራው ነገድ ላይ እየተፈጸመ ስላለው ጥፋት እና ጥፋቱን ለመከላከል አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ማድረግ ስላለበት ተግባር ለመመካከር የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ጥልቅ እውቀት ያላቸውን ሶስት ምሁራንን ፕሮፌሰር ጌታቸው ሓይሌን፣ ዶክተር ሃይሌ ላሬቦ እና አቶ ጌታቸው ረዳን በአስረጅነት ጋብዘናል። ይልና በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲገኝ ይጋብዛል።
በሞረሽ ወገኔ የግብዣ ጥሪ ላይ እንደምናየው፣ ኢትዮጵያዊውን ሁሉ ለውይይት ሲጋብዝ ቅሬታም ካለ ቅሬታን በመድረኩ ላይ ተገኝቶ እንደማሰማት፣ ለምን ሰው ወደ ስብሰባው እንዳይሄድ ኢሳት በዚያው ሰዓት እና በዚያው ቀን ስብሰባ መጥራት መረጠ? ብሎ መጠየቅ ከጀሌነት ራስን ነጻ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፤ ሰው ለኢሳት ለሚያደርገው የገንዘብ አስተዋጽኦ የመጠየቅ መብቱም ነው ብዬ አምናለሁ።
ሞረሽ ወገኔ በጁላይ 27 “ቅሬታን ስለማሳወቅ” ብሎ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል።
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በ፴፩ኛው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ዝግጅት ለሰኔ ፳፮ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም. (July 3, 2014) ሕዝባዊ ስብሰባ መጥራቱን ኢሣት እያወቀ፣ ማስታወቂያውንም በራሱ ዝግጅት ከሦስት ጊዜ በላይ ለሕዝብ አሰምቶ እያለ፣ የኢሣትን ዓመታዊ የገንዘብ ማሰባሰቢ ዝግጅት ድሮ ያደርግ የነበረበትን ቀን ትቶ፣ ሞረሽ-ወገኔ ሕዝባዊ ስብሰባ በሚያዘጋጅበት ቀን እና ሰዓት ለማድረግ መወሰኑ፣ “ጠብያለሽ በዳቦ” ሆኖ ተሰምቶናል። ይህም የኢትዮጵያውያን ተቋሞች እንዲጠናከሩ እንጂ፣ እንዳለፉት ሁሉ ተቋሞች እንዳይፈርሱ ዓላማቸው አድርገው የተነሱትን እንደሞረሽ ያሉ ድርጅቶችን የጠነከረ አቋም የሚፈታተን ሆኖ ተሰምቶናል።
ስለሆነም፦
1. ኢሣት በሣንሆዜ ሊያደርገው ያሰበውን ዝግጅት ቀኑን ለሌላ ቀን እንዲደርግ አጥብቀን አበክረን እንጠይቃለን።
2. በዐማራው ላይ የሚፈጸሙ ግፎች እና በደሎችን ኢሣት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ባላነስ መልኩ የዜና ሽፋን እንዲሰጠው ከማክበር ጋር እናሳስባለን።
ይህ አቤቱታ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ቦርድ ይድረስ እንጂ ቦርዱ ለቅሬታ ማሳወቂያው መልስ ከመስጠት ይልቅ የሞረሽን ስብሰባ ለማደናቀፍ ካቀደው ሴራው አልተቆጠበም። ለምን?
ኢሳት በኢትዮጵያኖች የገንዘብ እርዳታና ተሳትፎ የተቋቋመ እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያኖችን በጋራና በእኩልነት የሚያሳትፍ ከመሆን አልፎ ወገን በመለየት ለአንዱ አቀንቃኝ ለሌላው እንቅፋት መሆን አልነበረበትም። ኢሳት የራሱ ባለቤትነት የሌለው፤ ግንቦት 7 እና የአክራሪ ብሄረተኞች በውስጥ ሆነው በበላይነት የሚያሽከረክሩት ነው እየተባለ ለሚታማው ማስተማመኛ ካልሆነ በቀር በሞረሽ ስብሰባ ላይ ያሳየው ተንኮልና ሴራ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።
ኢሳት ከአማራው ህዝብ የሚፈልገው ገንዘቡን እንጂ የአማራውን ህዝብ አይደለም የሚባለውን ወሬ ከዚህ በፊት እንዳልታመነ ወሬ ሰምተን ከማለፍ ይልቅ ቆመን ኢሳትን ከመጠየቅና ከመጠራጠር አልፈን የሳንሆዜው የኢሳት ድርጊት ለወሬው ማስተማመኛ ከመሆን ያለፈ ለኢሳት የፈየደለት ነገር ያለ አይመስለኝም። በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ኢትዮጵያዊነት በአንድ መድረክ ተገናኝቶ እንዳይነጋገር እንቅፋት እየሆኑ ከኢትዮጵያኖች በተለይም ከአማሮች የገንዘብ እርዳታ መጠየቅ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንደሚሉት፣ አይን ያወጣ የሰው ንቀት ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ አማራው ኢሳትን በገንዘብ እስከረዳ ድረስ፣ በኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን መፈናቀል፣ መገደልና መታሰር ወዘተ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ እኩል ትኩረት ሰጦ ማስተናገድ ይገባል። “ከአማራው ህዝብ ገንዘቡን ብቻ ነው የምንፈልገው” የሚለው ፈሊጥ በሂደት የኢሳትን ማንነት መፈታተኑ እንደማይቀር ኢሳትና ደጋፊዎቹ ሊያስቡበት ይገባል። “እዩኝ! እዩኝ! ያለች ደብቁኝ! ደብቁኝ ትላለች” እንደሚባለው፣ ዛሬ መድረኩን ይዘናል ተብሎ የአንድን ህዝብ መፈናቀል፣ መገደልና መታሰር ህዝብ እንዳያውቅ የሚደረግ ተንኮልና ሴራ ነገ ያስጠይቃል።
tasewanete@gmail.com
Leave a Reply