
በስደት ላይ ያለው ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ
የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ማህበር
የአቋም መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን።
በስደት ላይ ያለው ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ዙሪያ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት መነሻ በማድረግ ያወጣውን መግለጫ በመደገፍ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ማህበር የተሰባሰብን ተወካዮች ባካሄድነው አስቸኳይ ጉባኤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በሰፊው ተመልክተን የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ምዕ. ፪ ከቁ. ፲፰ ጀምሮ “ልጆቼ ሆይ ይህቺ የመጨረሻዋ ሰዓት ናት እኛም የመጨረሻዋ ሰዓት እንደሆነች አውቀን በአንድነት እንቁም” ብሎ ባስተማረን መንፈሳዊ መሪ ቃል መሠረት የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖ እንዳሻው እየዘረፍ እና እየገደለ ያለው በደም የተጨማለቀውን ወያኔን በአንድነት ሆነን በቃ ልንለው ይገባል።
የእናት ሀገሩ ፍቅር እንደ እግር እሳት የሚያቃጥለው ወጣት ትውልድ እምቢ ለሀገሬ! እምቢ ለነፃነቴ! ብሎ ግንፍሎ ወጥቷል። በአንፃሩ ሥልጣን ያሰከረውና ገንዘብ ያሳበደው ወያኔ ያገኘውን ሁሉ መግደልና መጨፍጨፉን ቀጥሏል። ሁሉም እንደሚያውቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት የተጣሰባት፣ የዲሞክራሲ ጭላንጭል የጠፋባት፣ የዘር መድልኦ አገዛዝ የሰፈነባት የአምባ ገነኖች መፈንጫ ሆናለች። የወያኔ የግፍ አገዛዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለድህነት ለርሃብ ለዕርዛት ለስደትና ለመሐይምነት ዳርጎታል።
ውድ ኢትዮጵያዊ ወገን!
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው የኢትዮጵያ ውድ ልጆች በየቀኑ በወያኔ ጥይት መቀላት ብቻ ሳይሆን በወያኔ ቆመጥ ተደብድበው እየተገደሉ ደማቸው እንደ ጅረት ውሃ እየፈሰሰ ከሞት የተረፉትም ለቀጣይ ግድያ እንዲጠባበቁ በጅምላ እየታሰሩ ናቸው። የዘረኛው ወያኔ የግፍ አገዛዝ ፅዋው ሞልቶ ከፈሰሰ ቆዬ። በመሆኑም እኛ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ-ቤተክርስቲያን መዋቅር በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሥር የተሰባሰብነው የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ማኅበር አባላት ይህን የአቋም መግለጫ በጋራ አውጥተናል።
፩ኛ/ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕ.ወ.ሓ.ት የባርነት ቀንበር ተላቆ የሰላምና የነፃነት አየር እንዲተነፍስ ትግሉን በየአቅጣጫው እንዲያፋፍም ጥሪ እናቀርባለን። እኛም በማንኛውም ረገድ አስተዋጸኦ ለማበርከት ቃል እንገባለን።
፪ኛ/ አረመኔውንና ዘረኛውን የወያኔ ቡድን ለማንበርከክ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተደራጀና በተቃናጀ መልኩ በየቦታው ዘብ ይቁም።
፫ኛ/ የሀገር አለኝታ የወገን መከታ የሆነው ወጣቱ ትውልድ እንደ ጽጌረዳ አበባ በየቦታው እየረገፈ ነው። እናት ልጇን ተነጥቃ ግንባሩ በአጋዚ ጥይት ተበርቅሶ ሲወድቅ እያየች የወላድ አንጀቷ አልችል ብሏት የሀገር ያለህ፤ የወገን ያለህ፤ ድረሱልኝ እያለች ትጮሃለች። ከዚህ የበለጠ ምድራዊ ገሀነም ምን ሊኖር ይችላል? በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰን ይህንን ዘረኛና ገዳይ ቡድን ልናስወግደው ይገባል በማለት ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
፬ኛ/ ሀገር በቀል የሆነው ከሀዲ ወራሪ ኃይል ቀደም ብሎ በነደፈው የከፋፍለህ ግዛ ያረጀና ያፈጀ ሥልት ሊሠራለት አልቻለም። ሕዝቡም ነቅቶበታል። አንድ ለአምስት በሚል አደረጃጀት ያዋቅረውን የሰሜን ኮሪያ ኮምኒስታዊ የአፈና አገዛዝ ሰንሰለት ኢትዮጵያዊ ወገናችን በጣጥሶ ጥሎት በአንድነት ፀንቶ ቆሟል። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ እስከሚሆን ድረስ የነፃነት ትግሉ ይቀጥላል። እኛም ድጋፋችንን እንቀጥላለን።
፭ኛ/ ወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች የፍልሰታ ፆምን ምክንያት በማድረግ በየቤተክርስቲያኑ በጸሎትና በሱባኤ ላይ ናቸው። በስቃይና በመከራ ላይ ያሉትን ወገኖቻቸውንም ዕለት በዕለት በጸሎት ያስባሉ።በአንፃሩ ግን ወያኔ በሃይማኖትና በእምነት ውስጥ ገብቶ ታጋይ ካድሬዎቹን በካሕናት ስም እያሰማራ ቤተክርስቲያናችንን እያመሰ ይገኛል። እውነተኛ የሃይማኖት አባቶች የሆናችሁ የወያኔን አፀያፊና ዘግናኝ ድርጊት ልታወግዙ ይገባል። በኢትዮጵያም ሆነ በየትኛውም የዓለም ክፍል የምትገኙ አባቶች ሕዝባዊ ወገናዊነታችሁን የምትገልጹበት ጊዜ አሁን ነው እንላለን።
እግዚአብሔ አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቅ ሕዝቧንም ይባርክ። አሜን።
አባቶች ካስተማሩኝ እንጅ መፅሀፍ ቅዱሳዊ እውቀት የለኝም። መቼም “ህገ-ወጦቹ አባቶች ስላስተማሩህ ነው፤ ህጋዊዎቹ አባቶች እኛ ነን” እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ለመሆኑ የሀይማኖት አባቶች መንግስትን ለመጣል የአቋም መግለጫ እንዲያወጡ ኢየሱስ ክርስቶስ አስምሯቸዋልን? የቀደሙት አባቶቻችንስ በፅናት አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጡ እንጂ እነሱ ሸሽተው ልጆቻቸውን ሙቱ ብለው ነበርን? እናንተ ታዲያ…