• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የክርስቲያንና የሙስሊም ፍቅር በገለምሶ

May 5, 2014 07:15 am by Editor 8 Comments

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለገለምሶው መምሬ ሙላቱ የምትተርክ አንዲት ጽሑፍ ለጥፌ ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ግን ያቺ ጽሁፍ መሀል መንገድ ላይ ተቆርጣ የቀረች ሆና እየታየችኝ ነው፡፡ ስለዚህ ለናንተም፤ ለወገንም፣ ለታሪክ ጸሓፊያንም እንዲጠቅም ይህችኛዋን ሐተታ እጨምርበት ዘንድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በ1981 የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ይመስለኛል፡፡ ከትምህርት ቤት መልስ የጨዋታ ጓዶቼን ፍለጋ “ኒብራ” ከተሰኘው የገለምሶ ከተማ ዋነኛ ጎዳና ወረድኩ፡፡ ጓዶቼን ብዙም ርቀት ሳልሄድ ከትልቁ የጋሽ መሐመድ በከር መደብር በረንዳ ላይ አገኘኋቸው፡፡ እዚያም የኳስ ጨዋታ ሰዓታችን እስኪደርስ ድረስ በትረባና በፉገራ መናቆር ጀመርንና አንዱ ሌላውን ለማብሸቅ ይሞካክር ገባ (በጊዜው ትረባ፣ ፉገራና ለከፋ ጊዜያችንን የሚገፋልን ትልቅ መዝናኛችን ነበር)፡፡ እኛ የነበርንበትን በረንዳ በስተግራ በኩል ተጎራብቶ ወደ ታላቁ የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድና “ሐድራ” ወደሚባለው እስላማዊ ማዕከል (መስጊዱ የሐድራ አንድ ክፍል ነው) የሚያስወጣ መንገድ አለ፡፡ መንገዱ በወቅቱ በጎርፍ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ወደ አስር የሚደርሱ የቀን ሰራተኞች ድንጋይ እየቀጠቀጡ የተቦረቦረውን የመንገዱን የመሀለኛውን ክፍል ይሞሉትና በድንጋዩ ላይ አሸዋ እየመለሱ ይደመድሙት ነበር፡፡

ይህ የምላችሁ መንገድ በጎርፍ የተጠቃው በዚያን ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ዘወትር ክረምቱን ጠብቆ ከካምቦ ተራራ በሚወርደው ሀይለኛ ጎርፍ እየተደረመሰ አሳሩን ያያል፡፡ የከተማው ማዘጋጃ ቤት በመንገዱ ዳርና ዳር የፍሳሽ መውረጃ ቢሰራለትም ጎርፉ በጣም ከባድ በመሆኑ የተሰራለትን መውረጃ በመተው ወደ መሀል መንገድ ዘው ብሎ እየገባ መንገዱን ማበላሻሸቱ የየዓመቱ ትዕይንት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መኪና ይቅርና ሰዎችና የጋማ ከብቶችም በዚያ ዳገታማ መንገድ ሲወጡና ሲወርዱ መከራቸውን ነው የሚያዩት፡፡

ክረምቱ ካለፈ በኋላ መንገዱ ይጠገናል፡፡ ጥገናው የሚከናወነው በአብዛኛው በነጋዴ ግለሰቦች እንጂ በማዘጋጃ ቤቱ አይደለም፡፡ ታዲያ ከላይ በጠቀስኩትና ወሩንና ቀኑን በዘነጋሁት የ1981 አንደኛው ዕለት መንገዱን የሚያስጠግነው ግለሰብ ከወትሮው የተለየ ሆነብኝና በደንብ አየሁት፡፡

ሰውየው ቄስ ነው፡፡ መንገዱ ደግሞ ወደ መስጊድ የሚያስወጣው ትልቁ መንገድ ጎዳና፡፡ ቄሱ ወደ መስጊድ የሚያስወጣውን ትልቁን መንገድ ያስጠግናል!! አጃዒብ! በልጅነት አዕምሮዬ ተገረምኩ፡፡ በጣም ተደመምኩ፡፡ እናም በአቅራቢያችን የነበሩትን ጋሽ መሐመድ በከርን ስለሰውየውና ስለመንገድ ጥገናው ጠየቅኳቸው፡፡

“ዛሬ መንገዱን የሚያስጠግነው ቄስ ነው እንዴ?”

“አይ ቄሱ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ነው”

“የቱ ቤተክርስቲያን?”

“መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ነዋ! በገለምሶ ስንት ቤተክርስቲያን ነው ያለው?”

“ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? የመስጊድን መንገድ ነው እንዴ ቤተክርስቲያን የሚያስጠግነው?”

“እንዴት ሊሆን አይችልም? እነርሱስ ቢሆኑ የኛ ሰዎች አይደሉም እንዴ? እኛስ ቤተ ክርስቲያናቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ቢጠቃ ዝም ብለን እናያለን እንዴ?”

ጋሽ መሐመድ የነገረኝ ነገር እውነት መሆኑን በደንብ ያረጋገጥኩት በአስር ሰዓት ገደማ ቄሱ ለሰራተኞቹ ክፍያ በፈጸሙበት ወቅት ነው፡፡ በነጋታውም እኒያ ቄስ ሰራተኞችን አሰማርተው መንገዱን ሲያስጠግኑ ነበር የዋሉት (እኚያ ቄስ የአካባቢያችን ተወላጅ አልነበሩም፤ ለዚህም ነው ስማቸውን ያልያዝኩት፡፡ ሆኖም ቀጠን ብሎ ዘለግ ያለው ሰውነታቸው፣ ጠይም መልካቸውና ሰልካካ አፍንጫቸው እስከ አሁን ድረስ ይታወሱኛል፤ ብዙ ጊዜም ሰማያዊ ቀለም ያለው ቆብ ነው በራሳቸው ላይ የሚያደርጉት)፡፡

ልብ ያለው ይበል! እንዲህ አይነት ታሪክ በገለምሶ ተፈጽሟል፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ወደ ሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ የሚያስወጣውን መንገድ በራሷ ገንዘብ አስጠግናለች፡፡ በገለምሶ የክርስቲያንና ሙስሊሙ ፍቅር እስከዚህ ድረስ ነበር፡፡ ዛሬ በአካል እዚያ ባልኖርም ይህ የጥንት ፍቅራችን አሁንም ድረስ እንዳልቀዘቀዘ ቤተሰቦቼ ያወጉኛል፡፡

*****  *****  *****

“የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድስ ለክርስቲያኖችና ለቤተክርስቲያኒቷ ምን አድርጎ ያውቃል?” ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም መቼስ! እንዲያ ከሆነ የሚከተለውን ታሪክ ላጋራችሁ፡፡

የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ “ሐድራ” የሚባለው እስላማዊ ማዕከል አንዱ ክፍል ነው- ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ይህ ሐድራ የሚባለው ማዕከል ከትልቁ መስጊድ ሌላ የቁርአን መማሪያ (ቁርአን ጌይ)፣ የዒልሚ መማሪያ (ቤይተል ዒልሚ)፣ የሴቶች መማሪያና መስገጃ፣ የዚክሪና አውራድ ማድረጊያ፣ የአዛውንቶችና የሽማግሌዎች መኖሪያና ሌሎች በርካታ ቤቶች አሉት፡፡ እንዲሁም “ቤይቱል ሐድራ” የሚባለውና የሁሉም እንግዶች ማረፊያ የሆነው ቤት (በስፋቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ልደት አዳራሽ የሚያክል) በዚሁ ሐድራ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህ ቤቶች ሁሉ ከዓመት እስከ ዓመት ተመሳሳይ አገልግሎት ነው የሚሰጡት፡፡ በመውሊድ ጊዜ ግን አገልግሎታቸው ይቋረጥና በበዓሉ ለመታደም የሚመጡትን እንግዶች ያስተናግዳሉ፡፡ በየቤቶቹ ውስጥ ሰለዋትና መንዙማ ይደረጋል፡፡

በገለምሶ የሚከበረው መውሊድ ሞቅ ደመቅ ያለ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለሀገራት ይመጣሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር (ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና የመን) በርካታ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን እንግዶች ለማስተናገድ በትንሹ አስራ አምስት በሬዎችና ሶስት ግመሎች ይታረዳሉ፡፡ ግመሎችና በሬዎቹን የሚገዙት ግን የሐድራው ሰዎች አይደሉም፡፡ ድሮ በሼኽ ዑመር አሊዬ እጅ የተማሩ ሼኮችና ሌሎች የሼኽ ዑመር ወዳጆች ናቸው ከብቶቹን የሚያመጡት፡፡

ታዲያ የሐድራው ሀላፊዎችና የመስተንግዶ መሪዎች ወደነርሱ የሚመጡትን ከብቶች በሙሉ አያርዷቸውም፡፡ በቅድሚያ አንድ ወይም ሁለት በሬ ለሴቶች ይሰጥና የከተማው ሴቶች ከልዩ ልዩ ክፍለ ሀገራት የሚመጡ ወይዛዝርትን እንዲያስተናግዱበት ይደረጋል (በሐድራ ውስጥ ሴትና ወንድ መቀላቀል ክልክል ነው፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ምግባቸውን ለየራሳቸው ነው የሚያዘጋጁት፤ ደግሞም የሁለቱም ጾታ ሰዎች ከተፈቀደላቸው ክልል ውጪ መውጣት የለባቸውም)፡፡

በማስከተልም አንድ በሬ ለስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎች ይሰጣል፡፡ እንዲህ የሚደረግበትን ምክንያት በትክክል ባላውቅም በዘመኑ በነበረው ልማድ የተነሳ የበሽታው ተጠቂዎች መሸማቀቅ ሳይደርስባቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተናግዱ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይመስለኛል፡፡ በሬዎቹ ለሴቶችና ለስጋ ደዌ ህሙማኑ የሚላኩት ግን ለግብዣና ለፌሽታ ብቻ አይደለም፡፡ በመስተንግዶው የሚታደሙት ሰዎች ሰለዋት ስለሚያደርጉና የነቢዩን ገድል በመንዙማ ስለሚያወድሱ ነው፡፡ እንዲያ የማያደርግ ጀመዓ ለመውሊድ ከመጣው በሬ አንዳች ድርሻ የለውም፡፡

ነገር ግን ይህ መመሪያ የማይመለከተው አንድ ክፍል አለ፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን! በዓሉን የማታከብር ሆኖም ከመውሊድ በሬዎች የራሷ ድርሻ የነበራት ብቸኛ አካል እርሷ ነበረች፡፡ ለዚያውም ለርሷ የሚደርሳት አንድ በሬ ብቻ አይምሰላችሁ! ሁለት በሬዎችን ነው በየዓመቱ የምታገኘው፡፡

የዚህ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ዕድሜዬ ከፍ ካለ በኋላ ግን ምክንያቱን የሐድራው መሪ የሆኑትን ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅን ጠይቄ ከአንደበታቸው ተረዳሁ (ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ የሐድራው መስራች የነበሩት የሼኽ ዑመር አሊዬ ልጅ ናቸው- አሁን ዕድሜአቸው ከዘጠናው ተሻግሮ ወደ መቶ ዓመት እየተጠጋ ነው)፡፡

ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ሁለት በሬዎች በየዓመቱ ለቤተክርስቲያን የሚሰጥበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ነበር ያስረዱኝ፡፡

“እነዚህ ክርስቲያኖች ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንደኛው የአዳም ልጆች ናቸው፡፡ በሀይማኖት ብንለያይም የአንድ ሀገር ሰዎች ነን፡፡ ከዚያም አልፎ የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ነን፡፡ በሬዎቹ ወደኛ የሚመጡት በዓላችንን በደስታ ለማክበር እንድንችል ነው፡፡ እኛ በሬዎቹን አርደን በዓላችንን በደስታ ስናከብር ክርስቲያን ወገኖቻችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ እስልምናችን ጎረቤቶቻችንንም ማስደሰት እንዳለብን ያዘናል፡፡ ስለዚህም ነው በሬዎቹን ወደ ቤተክርስቲያን የምንልከው”፡፡

*****  *****  *****

እንዲህ ዓይነቱን ውብ ባህል ምንድነው የምትሉት? “መቻቻል” ነው የሚባለው ወይስ ሌላ ስም አለው? እኔ ግን “መቻቻል” አልለውም፡፡ ይህ በተመን የማይመነዘር ፍቅር ነው እንጂ “መቻቻል” የሚለው ዘመን ወለድ ታፔላ የሚለጠፍለት አይሆንም፡፡ “መቻቻል” ሲባል አንዱ ወገን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሌላውን የሚያስከፋ ድርጊት በሚፈጽምበት ጊዜ ሌላኛው ወገን በትዕግስት ችሎ ማለፍ ይገባዋል የሚል እድምታ ያለው ይመስለኛል፡፡ በኔ ከተማ ግን ፍቅር ሰባኪ የሆኑት ሼኮች እና ቄሶች ክፋት ሊፈጸም የሚችልባቸውን ሽንቁሮች ሁሉ ቀድመው የደፈኗቸው በመሆኑ “መቻቻል” የሚባለው አነጋገር እዚያ ዘንድ ተራ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ በዚያች እትብቴ በተቀበረባት መሬት ያየሁትና የሰማሁት “ፍቅር” ነው እንጂ “መቻቻል” አልነበረም፡፡

በኔዋ የገለምሶ ከተማ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ነበረን፡፡ በሌላው ኢትዮጵያስ ቢሆን? ዲግሪው (መጠኑ) ይለያይ ይሆናል እንጂ ተመሳሳይ ታሪኮች ሞልተዋል፡፡ እንዲህ በህብረት የኖረውንና ፍቅርን የተቋደሰውን ህዝብ የፖለቲከኞች ወሬ ሆድና ጀርባ ሊያደርገው ከቶ አይቻለውም፡፡ ፖለቲከኞች ይህንን በሌሎች ሀገራት በስለት እንኳ ተፈልጎ የማይገኝ ውብ ባህላችንን በዓለም ዙሪያ ቢያስተዋውቁልን ነው የሚያምርባቸው፡፡

እኛ አንድ ነን፡፡ ወንድማማቾች ነን፡፡ ፍቅር ነን፡፡ ክብር ነን፡፡ ህብር ነን፡፡ ሰሞነኛ ወሬ አያለያየንም፡፡

—–

አፈንዲ ሙተቂ

ነሐሴ 21/2005

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. Biruk Abraham says

    May 5, 2014 08:55 am at 8:55 am

    Min malet endalebign alawkewum a great brotherhood love!

    Reply
  2. alex says

    May 5, 2014 09:42 am at 9:42 am

    wow what amazing history? lovely people with beautiful culture, this is really a great asset to our country Ethiopia, very unique culture!!! I LOVE IT!

    Reply
  3. abudalis says

    May 5, 2014 09:13 pm at 9:13 pm

    ABO ! Endezih new FIKIR malet JORO YALEH SIMA ASTEWUL ENDIHM NORENAL !!!

    Reply
  4. sam says

    May 6, 2014 01:21 am at 1:21 am

    Wow it amazing history beautiful culture thank you so much you share your witness! !

    Reply
  5. solomon says

    May 6, 2014 11:22 pm at 11:22 pm

    afende endet yale biruh lebe yaleh sew neh. Ene sera sejemer mejemera mechera astemare hogne new yehedekut. Tiz yelegnal enate yanebachew enba oromo ager tebelo eko new. Gen ezaa fikir agegnew. Telekum tinishum gashe new yemeleh. Yezane mechera(1993) meberat aneberem ande abat kesachew benesa endewesed yefekedelugn aleresawum ye lejochachew astemare selehonch becha. Yezane mechara balhed bechefen telacha temoleche eker aleneberem. Ene badekubet butajiram mejemera betam telik mesged nibir yeteseraw kezaya bekababeyachen yeneberu talak ye emenet abat ke mesegedu ategeb yalewen mariam betekeresten endesera kerashew ena sewen astebaberew genzdm setewal. Betam metefowen geze be wolajochachen belahat alefenew ahun politics eyerebesehew new.

    Reply
  6. Aschalew says

    May 7, 2014 02:19 pm at 2:19 pm

    this is not something to fool any body it is fact and here i am to witness it.Many thanks our brother Afendi.

    Reply
  7. ezra says

    May 8, 2014 01:04 am at 1:04 am

    ውድ ወንድማችን afendi! እዉነታው አንተ እንደጻፍከው ሆ ሳለ ግን በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል አቦ። ይሄንን የመሰለ በፍቅር ተዋዶና ተፈቃቅሮ የኖረዉን ህዝባችንን አዲስ መጤ ወጠጤዎች እነ ጃዋርን የመሠለ ደናቁርት እነሆ ለፈረንጅ ማደጎነታቸዉን ለማረጋገጥ የራሳቸዉን ማነነት ንቀው እንዳበደ ዉሻ ከማንነታቸው ጋር ተጋጭተው ሁሉምንም ይናደፋሉ/ ይለክፋሉ። መጥኔ

    Reply
  8. senu says

    May 9, 2014 02:23 am at 2:23 am

    Gosh yehe yemeyasteset zena new !!! WOW !!!

    bertu weyane engaygebabachu ,, berun atebqachu zegut
    Long live Ethiopia

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሤራ አክሻፊው ጎንደር ለሦስተኛ ጊዜ ታሪክ ሠራ May 10, 2023 09:25 am
  • ማር በከፍተኛ ደረጃ የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል May 9, 2023 09:24 am
  • ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ መጠየቁ ለሰላም ንግግሩ ዕንቅፋት ሆነ May 4, 2023 01:12 am
  • መረጃ ቲቪ ያጋራው አሳሳች መረጃ May 2, 2023 12:37 pm
  • “ከፈጣሪ በታች መከላከያ የሁላችን ዋስ ጠበቃ ነው፤ ትልቅ ይቅርታ እንጠይቃለን” April 13, 2023 10:19 am
  • በትግራይ የ”ልጆቻችን የት ናቸው?” ጥያቄ እየተሰማ ነው April 13, 2023 08:56 am
  • በትህነግ የፈረሰው የአክሱም ኤርፖርት ያስከተለው ዘርፈብዙ ኪሣራ April 13, 2023 03:21 am
  • “የከተማው ነዋሪ በመሰላቸቱ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ ችግር” ገጥሟቸዋል April 12, 2023 09:23 am
  • ከዕድሜ ልክ እስከ 20 ዓመት ቅጣት ተበይኖባቸዋል April 11, 2023 02:58 pm
  • የኡጋንዳ የክልሎች ሚኒስትር በቆርቆሮ ሌብነት ተጠርጥረው ታሰሩ April 10, 2023 03:59 pm
  • ታከለ ከተነሳ በኋላ የመዐድን ሌቦች እየተያዙ ነው April 6, 2023 02:53 pm
  • አገር ለማተራመስ ያለመ የምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አክቲቪስቶች ህቡዕ ቡድን ተያዘ April 4, 2023 10:07 am
  • በ10 ዓመት ውስጥ ከ44 ቢሊየን ዶላር በላይ ሸሽቷል April 4, 2023 09:26 am
  • አየር ጨብጦ አሁን ያለውን መንግሥት ከሥልጣን ልቀቁ አይሆንም March 29, 2023 09:47 am
  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule