• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ሥነ-ኪን (ጥበብ) ጥቅሟና ገጽታዋ በሀገራችንና በተቀረው አፍሪካ

January 16, 2015 08:55 pm by Editor Leave a Comment

ኪነት (ሥነ-ኪን) በሀገራችን ለሀገራችን ጠቅማ የነበረውን ያህል የማንንም ሀገር አልጠቀመችም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በፈር ቀዳጅነት ማለቴ ነው፡፡ እንዴት ቢባል

1. እናት አባቶቻችን ሊሉ የፈለጉትን ነገር በጊዜውና ያለጊዜው በቦታውና ያለቦታው በመግለጽ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዴት ባለ መንገድ ልናሻግረው እንችላለን የሚል የጋለና የታመቀ ስሜት መነሣሣት እና መንፈሳዊ ፍላጎት ከውስጣቸው አቀጣጥላ የራሳችንን ፊደል እና አኃዝ ወይም ቁጥር መፍጠር መቅረጽ እንዲችሉ አድርጋለች፡፡

2. በዓይነቱ ልዩ የሆነ የሰማያዊ እና መንፈሳዊ ጥዑመ ዜማ ባለቤት አድርጋናለች፡፡

3. በዚህም ቀደምት እና ኅብረ ዝማሬንም ለዓለም እንድናስተዋውቅ አድርጋናለች፡፡

4. ዓለም በድጋሚ ሊያንፃቸው ወይም ሊቀርጻቸው የማይችላቸውን ከወጥ አለቶች የተፈለፈሉ ውብና ድንቅ ረቂቅ የኪነ-ሕንፃ  ውጤት የሆኑ አብያተ-መቅደሶች ባለቤት አድርጋናለች፡፡

5. የራሳችን የሆኑ የዜማ መሣሪያዎች ባለቤት አድርጋናለች

6. ነጻነታችንን ጠብቀን እንድንኖር ያስቻለንን የሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔ በተለያዩ መንገድ ለምሳሌ በቀረርቶ በፉከራ በሽለላውም ከደማችን አዋሕዳለች ከውስጣችን ገንብታለች ወዘተ ወዘተ ፡፡

ባጠቃላይ ‹‹በሁሉም ረገድ›› ይሄንን ስል በመዳፈር አይደለም በመተማመን ነው በሁሉም ረገድ ራሳችንን የቻልን እንድንሆን አድርጋናለች፡፡ እንደሌሎቹ ከአንዱ ፊደልን ከሌላው አኀዝን ከሌላም ሌላን በመቃረም ራሳችንን ሙሉ ለማድረግ አልሞከርንም ከማንም ምንም አልተዋስንም ይልቁንም አዋስን እንጂ፡፡ ይሄንን ለመረዳት የመረጃ እጥረት ካልኖረን በስተቀር ይሄንን እውነት አሌ የሚል ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ ባጠቃላይ ኪነት በሀገራችን እንዳጀማመሯ እስከአሁንም በረከቷን መስጠት ቀጥላበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ማንም ላይደርስብን የት በደረስን ነበር፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለሷ የሚገባትን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ስላልቻልን ጥበቃና እንክብካቤ የሚያደርጉላትን በየጊዜው እያዘመነችና እያበለጸገች ስትሔድ እኛ ግን እየጫጨንና እየኮሰስን መሔድ ግድ እንዲሆንብን ሆኗል፡፡

ይህ ምን ማለት ነው?፡- ረጅሙን የሀገራችንን ታሪክ ስንመለከት ኪነት በሀገራችን ፍጹም ወይም ሙሉ ለሙሉ ነጻ እንዳልነበረች እንረዳለን ወይም በሁሉም መስኮች መንፈሳዊ ዓለማዊ ሳይባል አገልግሎት እንድትሰጥ አልተፈቀደላትም ነበር፡፡ ማለትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሊባል በሚችል ደረጃ ኪነት በመንፈሳዊና ተዛማጅ አገልግሎቶች ካልሆነ በስተቀር ለዓለማዊ ጉዳዮች እንዳትውል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ጫናዎች ነበሩባት፡፡

ይህንን ተጋፍተው ለዓለማዊ አገልግሎቶች ለማዋል የሞከሩትንም በሕይወት ሳሉ አደለም ሞተውም እንኳን ታሪካቸው እንዳልሆነ ሆኖ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ዐፄ ተክለሃይማኖት 1ኛን ያስታውሷል፡፡ እርሳቸውም ዳንኪረኛ ቤተመንግሥቱንም የዳንኪራ ቦታ አደረጉት ተብለው ዛሬም ድረስ የሚጠሩት ዐፄ የሚለውን ንጉሣዊ መጠሪያን ተገፈው ርጉም ተክለሃይማኖት በመባል ነው፡፡ እኚህ ንጉሥ የዐፄ ፋሲል የልጅ ልጅ ልጅ ነበሩ የገዙትም ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር 1698-1700 ዓ.ም፡፡

ተራው ዜጋም ቢሆን በዚሁ መንገድ ከሔደ አዝማሪ የሚል ቅጽል እየተሰጠው እንዲሸማቀቅና ለትውልዱ የሚተርፍ አጥንት ሰባሪ ሽሙጥና ውግዘት የተነሣ ዘር ማንዘሩ ሁሉ ለግቢ ወይም ለጋብቻ እንዳይፈለጉና እንዲገለሉ ይደረግ ነበር፡፡ ከያኔያኑ እንዲያደርጉ ይፈቀድ የነበረው በየሰርጉ በየ ግብረ ሰላሙ (ግብዣ) እና በሌሎች ማኅበራዊና መንፈሳዊ በዓላት ሁሉ እየተገኙ ውዳሴ አምላክ መንፈሳዊ መልእክቶችን፣ የሀገር ፍቅርን ስሜት ሊሰጡ የሚችሉ ቀስቃሽና መልእክት ያዘሉ ግጥሞችን ስንኞችን፣ ቀረርቶና ፉከራ፣ ምክርና ተግሳጽ ዓይነቶችንና ትምህርታዊ ነገሮችን ብቻ ነበር፡፡ ይህ ጠንከር ያለ አቋም ለመንፈሳዊያኑ ለሃይማኖት አባቶችና ለግብረገባዊያኑ (Moralists) ፍጹም ተገቢ ትክክልና ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ተልእኮ እና ግዴታን እረኝነታቸውን መወጣት ሲሆን ለዓለማዊያኑና ለከያኔያኑ ግን ፍጹም ስሕተትና ነጻነትን መንፈግ ነበር፡፡

ጫና የነበረበት በዘፈኑ ወይም በአዝማሪዎቹ ላይ ብቻ አልነበረም ለምሳሌ ያህል ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽን የወሰድን እንደሆነም ካሉን ጥንታዊ ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ ቅርሶቻችን ውስጥ ለምልክት እንኳን አንዲት ዓለማዊ የሆነ ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ ማግኘት አንችልም፡፡ የራሳችን የሆነ ጥንታዊ የአሣሣል ዘይቤ አለን የአሣሣል ዘይቤውን ጨምሮ የሥዕል ጥበባችን በሃይማኖታዊ ምክንያት ከሁለት አውታረ መጠን እንዳያልፍ ተደርጎ ኖሯል፡፡ ምንም እንኳ የራሱ የሆነ ጥራትና ብቃት ያለው ቢሆንም ለምሳሌ የአካል ምጠናንና (ፕሮፖርሽንንና) ጠባብ ሥፍራን አጣጥመው የሚያልፉበት የአሣሣል ስልታቸው አስደናቂና ለዘመናዊ ሥዕል ሠዓልያን እንኳን አስቸጋሪና እጅግ የሚፈትን ነው፡፡ አሠራሩን ለመረዳትና ለማድነቅ ራሱ ለባለሙያ ካልሆነ በቀር ለሌላው ሰው የሚገባ አይደለም፡፡ ይሄውም ቢሆን ግን ሙሉ ለሙሉ ያገለገለውና እንዲያገለግል የተደረገው ቤተክርስቲያንን ወይም መንፈሳዊ ተግባርን ብቻ ነበር፡፡

ቅርጻ ቅርጾቻችንንም ስናይ አሁንም የራሳችን የሆነ በጣም የተራቀቀ የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች አሉን ነገር ግን ያገለገለው ቤተክርስቲያንን ወይም መንፈሳዊ አገልግሎትን ብቻ ነው፡፡ በሌሎች ዓለማት ወይም አብያተ ክርስቲያናት የሌሉ ብዛት ያላቸው አስደናቂና ውብ ውብ የተለያዩ ዓይነቶች በተለያየ ቅርጽ ጌጥና መልክ የተሠሩ በኛው ጥበብ በውስብስብ የኃረጋት ሥራ የተጌጡና የተንቆጠቆጡ የተለያዩ የመስቀል ዓይነቶች (processional crosses) ፣ ጽላቶች እና ታቦቶች፣ መንበሮች እና ሌሎች ንዋዬ ቅድሳት አሉ ከዚህ ወጥቶ ግን ለዓለማዊ ተግባራት ለመጠቀም እንኳን የሞከረ አስቦት የሚያውቅ ያለም አይመስለኝም፡፡

የሃይማኖት አባቶች የመንግሥትንም ጡንቻ ጭምር በመጠቀም ይህንን ያደርጉ የነበረበት ዋነኛው ምክንያት መንፈሳዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ንዋዬ ቅድሳት ውጪ ሌላ ዓለማዊ ነገርን ቀርጾ ወይም ሥሎ እቤቱ መስቀልና በጥበባዊ ዋጋው ስሜትን ማርካት እንደ ጣዖት አምልኮ ከመቆጠሩ የተነሣ ነው፡፡ ወደ ሩቅ ምሥራቅ የሄድን እንደሆነ የሸክላ ሥራ የጥበብ ሥራ ውጤት የተለያየ የሥዕል ጌጥ ለምሳሌ የዘንዶም ሆነ የድራጎን ሥዕልና ቅርጽ የተደረገበት የሸክላ ሥራ ያለምንም አገልግሎት እቤት ውስጥ አንድ አማካኝ ስፍራ ተሰጥቶት ማየት የተለመደና ባሕላቸውም ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ለአምልኮ እንዲያ ያደርጉ የነበረበት ዘመን አልነበረም ማለት ባይቻልም የጥበብን ሥራ ከማድነቅ አንጻርም ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኛ አባቶች ግን ይህ ድርጊት ፈጽሞ የማይታሰብና የሚወገዝ ጣዖት አምልኮ ነው፡፡ በመሆኑም የሸክላ ሥራ ጥበባችንን ከቤት ውስጥ ቁሳቁስነት የዘለለ አገልግሎት እንዳይኖረውና ከዚህም የተነሣ የሸክላ ሥራችንም እድገቱ የተገደበ ሊሆን ችሏል፡፡ እንደሩቅ ምሥራቆቹ የዘመነና ወቅቱን የጠበቀ ለውጥ ያሳየ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን ሁሉ ይታዩና ይስተናገዱ የነበሩት በዚሁ ያስተሳሰብ ማዕቀፍ በመሆኑ ለእድገታቸውም ሆነ ከእድገት ለመወሰናቸው አስተሳሰቡ ዐቢዩን ድርሻ ወስዷል፡፡

በዚህም ምክንያት ይህ መሠረታዊ አስተሳሰብ በሕዝቡ ሰብእና በመስረጹ ሕዝቡ ለጥበብ ሥራዎች የሚሰጠው ዋጋ በዚህ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ግድ ብሎ ቆይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ለዓለማዊ ሥዕሎችና ሌሎች የጥበብ ሥራዎች ሊሰጠው የሚገባው ጥበባዊ ዋጋ፣ አክብሮትና አድናቆት ለመንፈሳዊያኑ ሥዕሎችና ሌሎች የጥበብ ሥራዎች የሚሰጠውን ያህል ሊሆን ያልቻለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በብዙ ትውልድ የኖረ በመሆኑ ከዚህ እያወቀውም ሳያውቀውም ሲወራረሰው ከመጣ ለመንፈሳዊ ካልሆነ በቀር ለዓለማዊ የጥበብ ሥራዎች ዋጋ ያለመስጠት አስተሳሰብ ወጥቶ እንደ ምዕራባውያኑ ለሥዕልም ሆነ ለሌሎች ጥበባዊ ሥራዎች የሚገባቸውን ጥበባዊ ክብርና ዋጋ የመስጠት አስተሳሰብ ለመድረስ ከዚህም በኋላ ብዙ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችን እገምታለሁ፡፡

በርግጥ ዛሬ ላይ ለዘፈን የነበረው አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ እንዲያውም እላፊ ሀገርን በማይጠቅም አቅጣጫ ሁሉ እየሄደ ነው፡፡ ለዓለማዊ ሥዕሎችና ለሌሎች የጥበብ ሥራዎች ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ እንግዲህ ልንገነዘብ የምንችለው ነገር ቢኖር እናት አባቶቻችን ጥበብን ከዜማ ጀምሮ እስከ ቅርጻ ቅርጽ እግዚአብሔር ለሚከብርበት ጉዳይ ከሆነ በምን ያህል ጥንቃቄ ምጥቀት ርቀትና ድካም የሚሰስቱት ነገር ሳይኖራቸው በመላ ኃይላቸው አራቀው እንደተጠቀሙባት መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጥበብ ከዚህ ወጥታ ለዓለማዊ ተግባር እንዳትውል ግን ከባድ ማዕቀብ ጥለውባት እንደነበር በግልጽ ተስተውሏል፡፡ የሆነ ሆኖ እንዲህ እንዲህ እያለች ኪነት አሁን ላለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡

The Music of Ethiopiaበዘመነ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግን ቢያንስ በአመለካከት ደረጃም ቢሆን ከያኔያን እና ኪነት አንጻራዊ የሆነ ክብርና ነጻነት አግኝተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የርግማን ወይም የመጥፎ ዕድል ጉዳይ ሆኖ ይሁን የሌላ እንጃ ሀገራችንን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ በኪነትና በመንግሥታቱ መካከል ከባድ የሆነ የጥቅም ግጭት ይታያል፡፡ ኪነት እኔ ለእውነትና ለሕዝብ ጥቅሞች ጥብቅና መቆም የተፈጠርኩበትና የማልደራደርበት አቋሜ ነው ስትል እነኚህ መንግሥታት ግን ይህንን ልባቸውን የሚያዞርና የሚያጥወለውል አቋሟን ጨርሶ ሊወዱላት አልቻሉም፡፡ እንድትሠራ ከፈቀዱም እጇን በመጠምዘዝ የነሱ ፕሮፖጋንዲስት (ለፋፊ) ሆና ነው፡፡

በዚህ አለመግባባት የተነሣ ኪነት በኋላ ቀር ሀገሮች መንግሥታት ተቀፍድዳ መያዙዋ ሳያንሳት ጭራሹን እንድትከስም የተለያ ጫናዎች ይደረግባታል፡፡ የዚህ አንዱና ዋነኛ መገለጫ የሚሆነው በተለይ በአሁን ጊዜ ብዙ የኋላ ቀር ሀገሮች መንግሥታት የከያኔያኑን የኪነት ሥራዎችን የቅጂ መብት ባለማክበርና ባለማስከበር ኪነት በራሷ ጊዜ እንድትከስም የማድረግ ሸርና ተንኮል ውስጥ መጠመዳቸው ነው፡፡ በኅትመት ለሚቀርቡ የኪነት ሥራዎችም እንዲሁ የኅትመት ዋጋን በማናርና የወረቀትን ዋጋ በመጨመር የኅትመት ሥራዎች እንዲጠፉ ወይም እንዲዳከሙ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነኚህ መንግሥታት ኪነትን ለምን እንደሚጫኗት ሲጠየቁ ልክ እንደተማከሩ ሁሉ የሁሉም ምላሽ አንድ ዓይነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እሱም ኪነት ቅንጦት (Luxury) ነው በማለት፡፡

የኋላ ቀር ሀገሮች መንግሥታት ያልተረዱት ነገር ቢኖር ለሕዝባቸው ኪነትን ወይም ተግባረ ኪንን ቅንጦት ነው ስለሆዳቹህ መሙላት ብቻ አስቡ ሲሉ ለገዛ ሕዝባቸው ያላቸውን ዝቅተኛ ግምት እያንጸባረቁ ከመሆኑም በላይ እየሰደቡትና ሰድበውም ለሰዳቢ እየሰጡት መሆኑን ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለይበትና የሚበልጥበት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ እንስሳት የሚበልጥባቸው ረሀብ ሆዳቸውን የሚሞላ ነገር ሲሆን የሰው ልጅ ግን ከሆዱ ረሃብ በበለጠ የሕሊናው ረሀብ የሚብስበት መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ሕዝብ የቱንም ያህል ደሀ ቢሆን በዚያ ሕዝብ የዕለት ተዕለት የሕይወት መስተጋብር ውስጥ እንደየአቅሙ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የኪነት ወይም የሥነ-ኪን እሴቶችንና ጥቅሞች ሳያጣጥም የቀረበት አንድም ዘመን የለም፡፡ ማፍቀርና መፈቀር ስሜትንና ፍላጎትን በኪናዊ መንገድ መግለጽ ለሀብታም ብቻ የተሰጠ ጸጋ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ በየትኛውም የድህነት ዓይነት ያለ ደሀም ጸጋ ጭምር ነው፡፡ ፍቅርም በሉት ሌላ ኪናዊ ስሜት ወይም አድራጎት ገንዘብ የሚገዛው ወይም የገንዘብ አቅም የሚፈጥረው ሳይሆን ከሰውነት ተፈጥሮና ስሜት የሚመነጭ ጸጋ ነው፡፡ ፍቅርም በሉት ሌሎች ስሜቶች ደግሞ የሚገለጹበት ብቸኛ መንገዳቸውና ጣራ ምሰሶ ማገራቸው ቢኖር ኪነት እና ኪነት ብቻ ናት፡፡ ኧረ እንዲያውም ፍቅርም ሌሎች ኩነታዊ ስሜቶችም ያለኪነት ወይም ሥነ-ኪን ምንም ህልውና የላቸውም፡፡ ፍቅር ከኪነት የምትበረከትልን ትሩፋት ሆና ኖራለች ትኖራለችም፡፡

አንድ የሚገርም ነገር አለ ከአዕዋፍ፣ ከእንስሳትና ከአራዊትም ተቃራኒ ጾታቸውን ለመማረክ ሲሉ የድምፅ ቅላጼን ወይም ዜማን ጨምሮ ማራኪ የሰውነት እንቅስቃሴን በማድረግ ተቃራኒ ጾታቸውን የሚማርኩበት ተፈጥሮአዊ ተሰጥዖ ያላቸው መሆናቸው፡፡ ታዲያ ይልቁንም የሰው ልጆችማ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደምን አይሻሉ አይገባቸውስ? እናም ኪነት ለሰው ልጆች ሆድን ከሚሞላ ምግብና መጠጥም በላይ መሆኗን ቅንጣት እንኳን ልንጠራጠር አይገባም ይህንን የመረዳት አቅም ካልቸገረን በቀር፡፡ ልብ ብለን ባንገነዘበው ይሆናል እንጂ ወገኖቼ ምግብና መጠጥን በማምረት ሂደትም ሆነ በልማት ግንባታ ሥራ ሁሉ እኮ ቢሆን ቀድማ የምትገኘው ኪነት ናት፡፡ ገበሬው የእርሻ ሥራውንም ሆነ ተጓዳኝ ተግባራቱም በሚያከናውንበት ወቅት እኮ ‹‹በርዬ ሆይንና›› ሌሎች እንጉርጉሮዎችን በመጫወት ከበሬውና ከአካባቢው አውድ ጋር በሚፈጥረው መግባባትና መቀናጀት የስሜት መነቃቃት ዳቦ ወይም እንጀራ እንደሚገኝ፣ በተለያዩ የደቦ የወንፈል ወይም የወበራ ሥራዎቹም ዋነኛ ማነቃቂያው የሚያዜማቸውና የሚጨፍራቸው የሚያንጎራጉራቸውም ዝማሬዎች መሆኑ ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡

ባጠቃላይ ያለ ሥነ-ኪን የሚነቃቃ የሚከሰት የሥራ ወይም የሞያ ዓይነት ጨርሶ የለም፡፡ በሥልጣኔ እርካብ ላይ ለመቆናጠጥ ብቸኛው መንገድ የኪነት መንገድ ነው ለዚህ ማስረጃ ለመጥቀስ ያደጉ ሀገሮችን ተሞክሮ መቃኘቱ መጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ለምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ከያኔያኑ ሆነው እናገኛቸዋለንና ነው፡፡ አንድ በሠዓሊነቱ ታዋቂ የሆነ ሰው ሌዮናርዶ ዳቬንቺ ለመጀመሪያ ጊዜ የበረርትን (የአውሮፕላንን) እና የሌሎች ከሺህ የሚበልጡ የኪነብጀታ (የቴክኖሎጂ) ውጤቶችን ንድፍ ገና ቀድሞ ማውጣቱን ልብ ይሏል፡፡ ይህ ሰው ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ በሚል ቅጽል ስሙ ይታወቃል፡፡ ከዚህና ከሌሎች የጥበብ ሰዎች ህይዎት የምንማረው ነገር ቢኖር የኪነትንና የሥልጣኔን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታነት ነው፡፡

እንግዲህ ኪነት ከምትሰጣቸው የትየሌሌ ጥቅሞች ውስጥ አንዷን ቅንጣት በመምዘዝና በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ማለትም ኪነት ወይም ተግባረኪን የመዝናኛና ደስታን መፍጠሪያ መንገድ ናት በማለት ከጥጋብ ጋር በማገናኘት ወይም የቅንጦት ነው በማለት ኪነትን ወይም የጥበብ ሥራን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ ማለት ሌሎችንም ጥቅሞቿን ማጣት እንደሆነና ብቻም ሳይሆን ከዘርፈ ብዙ ጥቅሞቿ አንጻር ያለኪነት ሥልጣኔ ጨርሶ የሚታሰብ እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡ ለነገሩ እንዲያው በከንቱ ደከምኩ እንጂ የብዙ ኋላ ቀር አገሮች መንግሥታት እውነቱን አተውት አይመስለኝም የሚያመካኙትን ነገር ቢያጡ ወይም ለሽፋን ይህንን ይናገራሉ እንጂ ማንም እንደሚገነዘበው ዋነኛውና ትክክለኛው ምክንያታቸው ግን በእጅጉ ከዚህ የተለየ ነው፡፡

የኋላ ቀር አገሮች መንግሥታት ኪነትን የሚጨቁኑበት ዋነኛ ምክንያት ኪነት የየአስተዳደሮቻቸውን ድክመቶች ስለምታጋልጥና የሕዝብ ብሶት መተንፈሻ መንገድ ሆና ስለምታገለግል ሕዝቡን ታነቃብናለች ብሎም ታሳምጽብናለች ከሚል ዕረፍት የሚነሳ የደነቆረ የራስ ወዳድነት ሥጋታቸው የተነሣ ነው፡፡ እንጂ አሁን ማን ይሙትና እያደረጉት ያሉት ነገር በነጻ ኅሊናቸው አስበው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ይጠቅማል ብለው ነው ለማለት እጅግ የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እላይ ያተትናቸውን ሐቆች ይስቱታል ተብሎ ስለማይገመት፡፡ እንደዛ ዓይነት ጭንቅላት ካላቸውማ ምኑን ሀገር ተመራ? ነገር ግን ጉዳዩን ከሀገርና ሕዝብ ጥቅም አንጻር ከመለካት ይልቅ ከግልና ከቡድን ጥቅም አንጻር የመለካትና የመመዘን የደነቆረ አባዜ የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የአህይት አስተሳሰብ የተነሣ የቱንም ያህል ሀገርና ሕዝብን ጠቃሚ ጉዳይ ቢሆን ከግልና ከቡድን ጥቅማቸው አንጻር ሲያዩት ግን የማይመቻቸው ከሆነ ሀገርና ሕዝብ ሲጎዱ ይኖራሉ እንጂ ፍንክች የማለት ወይም የመለሳለስ ፍላጎት አይደለም ዝንባሌ እንኳን አያሳዩም፡፡ በዚህ የደነቆረ የአህይት አስተሳሰብ የእኛን መንግሥት ተብየ የሚያህል መንግሥት በዚህች አህጉር የለም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በይነ ሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) እና ልማታዊ ለሆነ አስተዳደር “ሁሉም የአፍሪካ መንግሥታት ነን ይላሉና ማለቴ ነው” ነን ካሉ ዘንዳም እንግዲያውስ ኪነት በየትኛውም የዓለም ክፍል ለበይነ ሕዝባዊ አሥተዳደር የሥጋት ምንጭ ሆና አታውቅም ሁነኛ አጋር እንጂ፡፡ ነገሩ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ካልሆነ በስተቀር፡፡ በይነ ሕዝባዊ አሥተዳደር ኪነትን እንደዋነኛ አጋሩ ይቆጥራል፣ ለኪነት ትልቅ ክብር ይሰጣል እምነትም ይጥልባታል፡፡ ለምን ቢባል ለዚያ አሥተዳደር ማንም ሊያደርግለት ከሚችለው በላይ የገዛ አጋሮቹና ወገኖቹም እንኳ ቢሆኑ ሊነግሩት የማይፈልጉትንና የማይደፍሩትን እንከኖቹን ትጠቁመዋለችና፣ ክፍተቶቹን ታመለክተዋለችና፣ ለተቃናና ለተወደደ አሥተዳደሩ እርዳታዋን በጅጉ ይሻዋልና፡፡ ይህም ስለሆነ ነው ዲሞክራሲ ወይም በይነ ሕዝብ እንደሰፈነባቸው የሚነገርላቸው ሀገሮች ሁሉ ኪነት በፍጹም ነጻነትና ልዕልና ሥራዋን እድትሠራ ማድረጋቸው፡፡ ለሥራዋ መቃናትም በሁሉም ረገድ ድጋፍ በማድረግ እንድትጠነክር ማድረጋቸው፡፡ የጨለማው አህጉር መሪዎችስ ከዚህ የሚማሩት ነገር አይኖር ይሆን?

እንደ ሕጉ ከሆነ አፍሪካዊ ማንም ከያኔ ቢሆን ምንም ዓይነት የኪነት ሥራ ይሥራ ግብር እስከከፈለና ዜጋ እሰከሆነ ጊዜ ድረስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሀገሩ መንግሥት መብቱን ሊጠብቅለትና ሊያስጠብቅለት ይገባ ነበር፡፡ የቅጂ መብቱን ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሀገሩን መንግሥት ደጅ የሚጠናበት የሚለማመጥበትና የሚማፀንበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ እነኚህ መንግሥታት በተለይም የእኛው መንግሥት ተብዬ የአንድ ጎጥ ቡድን፤ አንድ ከያኔ የሠራው ሥራ ሕገ-ወጥ ወይም የሚያስጠይቅ ወንጀል ሆኖ ከተገኘ በሕግ አግባብ ጠይቆ ማስቀጣት ይችላሉ፡፡ ሕግ ስል ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን መሠረት ያደረገና ተቀባይነት ያለውን ሕግ ማለቴ እንጂ የመንደር ወይም የጎጥ ደንብ ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት በሌለው አካሔድ ከያኔያኑንም ሆነ ኪነትን የሚያጎሳቁሉበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡

ዜጎች ለየመንግሥቶቻቸው ግብር የሚከፍሉት ስለሦስት ምክንያቶች ነው፡-

1. ደኅንነታቸው እንዲጠበቅላቸው
2. ለሀገር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት
3. የዜግነት መብታቸው የሆኑትን መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት

ከዚህ አኳያ መብቱ ያልተከበረለት ዜጋ ግብር የመክፈል ግዴታ አይኖርበትም ማለት ነዋ! ሲጀመር መንግሥታዊ ግዴታውን መወጣት የማይፈልግ ወይም ያልቻለ መንግሥት ነኝ ባይ ሥርዓት መብቱን ሊያከብርለት ባልፈለገው ወይም ባልቻለው ሕዝብ ላይ ተጭኖ የመኖር መብት የለውም፡፡ ሆኖ ከተገኘ ግን ሕዝቡ ግብርና ቀረጥ የሚከፍልበት ዓላማ ጨቋኞችን በራሱ ላይ ለማፈርጠም ብቻ ይሆናል፡፡ አንድ ከያኔ ግብሩን አምጣ መብትህን ግን አልጠብቅም አላስጠብቅምም ሊባል የሚቻልበት ሕጋዊ አካሄድስ አለን? ቡድናዊ በሆነ ጭፍን አመለካከት የተነሣ የአንድ ሀገርና ሕዝብ ሁለንተናዊ መሠረት የሆነችን ጥበብ ማጎሳቆል ምን ያህል ኢፍትሐዊነት እንደሆነ መረዳት የማይችል ጭንቅላት ይኖር ይሆን? እንዴ! ምን መሆኔ ነው? ኖሮማ አይደል እንዴ ጥበብ በሀገራችን ድምጥማጧ እንዲጠፋ እየተደረገች ያለው? ይሄንን ነው መፍራት ወገኖቸ፡፡ ከዚህ የሚከፋ ምንም ነገር የለም ለጥበብ ፊቷን ያዞረች ሀገር የትም አትደርስም እንዳይመስላቹህ፡፡ እንደቀድሞው እንኳን ሃይማኖትን ሀገርንና ሕዝብን ብቻ እንድታገለግል ቢደረግ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ አሁን እኮ ኪነት ከቀድሞው በተቃራኒ ብላሽ ብላሹን ነገር ነው እንጅ ሀገርንና ሕዝብን ግን እንዳታገለግል እኮ ነው የተደረገው፡፡

የዚህ አደጋው ይታያቹሀል? ለጥበብና ለጥበበኞች ጥበቃና እንክብካቤ አለማድረጋችን ከስንት ዘመን አንዴ የምናገኛቸውን የሚፈጠሩትን የሕዝብን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቁ ዕውቅ ዕውቅ ተወዳጅ ከያኔያኖቻችንን (ድምፃዊ፣ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ወገኛ፣ ተረበኛ፣ ደንካሪ ወዘተ) እየተሰደዱ እነሱን ማጣታችን ሀገር ሕዝብ ምን ያህል እንደሚጎዱ ልብ ብላቹህት ታውቃላቹህ? እነኝህ ድንቅ ፍጥረቶች ያንቀላፋን የተኛን የተደበረን ማኅበረሰብ ለመቀስቀስ ለማነቃቃት በኃይል ለመሙላት ለማንቀሳቀስ እንዚአብሔር የሚልካቸው የጥበብ ሐዋርያት እንደሆኑስ ታውቃላቹህ? እነከሌ እነከሌ እያልኩ ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ዐይናሞቻችን ተገፍተው እግራቸው ወዳመራቸው ተሰደው ከሀገር በመውጣታቸው ከእነሱ ጋራ ንቃታችንም ጉልበታችንም ቅስማችንም ስሜታችንም አብሮ እንደሄደና እንደሚሄድ በድናችን ብቻ እንደሚቀርስ ታውቃላቹህ? ቅመሙን ያጣና ጨው የሌለው ወጥ ምን ምን ይላል? እንደዛ ነው የሆነው፡፡ እነዚያን እነዚያን የመሳሰሉ ከያኔያን የእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁኔታው ምቹ ቢሆንና እዚሁ ከእኛው ጋራ ከጥበብ የተላኩበትን ሥራቸውን እየሠሩ የሚኖሩ ቢሆኑ ኖሮ የት ልንደርስ እንችል እንደነበር መገመት ትችላላቹህ? ኧረ ወዲያ! ያልታደልክ ሕዝብ ሾተላይህን ነቅለህ ጥበብ ሕይዎት እንድትዘራብህ አታድርግና አንቀላፋ ተኛ እሽ? የተሻለ ቀን የሚመጣልህ መስሎሀል! ተቀብረህ ትቀራታለህ፡፡

ይህ በሀገራችን በኪነትና በከያኔያን እየነፈጸመ ያለው ደባ በምዕራቡ ዓለም ቢከሰት ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ታውቃላቹህ? ከያኔያኑ በማኅበራቸው አማካኝነት መንግሥታቸውን ከሰው ፍርድ ቤት ይገትሩት ነበር፡፡ የመንግሥት የሆኑ የብዙኃን መገናኛዎቹም አንዷንም ቢሆን የኪነት ሥራዎቻቸውን እንዳያጫውቱና እንዳያቀርቡ በማሳገድ መንግሥታቸውን ሳይወድ በግዱ መብታቸውን ጠብቆ እንዲያስጠብቅ ያደርጉት ነበር፡፡ እስቲ አስቡት አንድ የብዙኃን መገናኛ የኪነት ሥራዎችን እንዳያቀርብ ከተከለከለ ሌላ ሊያቀርበው የሚችለው ምን ሊኖረው ይችላል? ምንስ አቅርቦ የአየር ጊዜውን ይሸፍናል? ደግነቱ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት የከያኔያኑን መብት ጥያቄ ውስጥ አስገብተው አይውቁም፡፡ እንዲያውም ከከያኔያኑም በላይ ለመብቶቻቸው መጠበቅ መንግሥቶቻቸው ቀናኢ እና ትጉ ናቸው፡፡ ጥቅሟን ያውቃልና፡፡

ዩ ኤስ አሜሪካን የወሰድን አንደሆን ከሆሊውድ የፊልም (የምትርኢት) ሥራዎች የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ ከዋና ዋና የገቢ ምንጮቿ ውስጥ አንዱ መሆን ችሏል፡፡ የሙዚቃ ኢንደስትሪዋም (የዘፈን ምግንባብዋም) እንደዛው፡፡ አሁን አሁን በተራቀቀ የኪነ-ብጀታ (የቴክኖሎጂ) መስፋፋት ምክንያት የከያኔያኑ የቅጂ መብቶች ተደፍሮ ወይም ተዘርፎ ሲገኝም ከከያኔያኑ በላይ ዕረፍት አጥቶ ተጠያቂዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚተጋው እና የሚዋትተው እራሱ መንግሥት ነው፡፡ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች፡፡ አንደኛው ግብር እስከከፈሉ ጊዜ ድረስ መብታቸውን ማስጠበቅ ግዴታው ስለሆነ ሌላው ደግሞ የሥነ-ኪንን ጥቅሞች ላለማጣት፡፡ ይህም በመሆኑ ነው የሥራዎቻቸው ጥራት የመጠቀውና ሥራዎቻቸውንም ዓለማቀፋዊ ማድረግ የቻሉት፡፡ እንዴት ያስቀናል!

በስተመጨረሻ ለጨለማው አህጉር መንግሥታት በተለይም ለኛው የጎጥ ቡድን የምለው ነገር ቢኖር እናንት ሆይ! እባካቹህ ነገሮች ሁሉ መልካምና ቀና የሚበጅና ደስ የሚያሰኝ ይሆኑልን ዘንድ ፊታችሁን ወደ ኪነት ወይም ወደ ጥበብ ሥራዎች በምሕረት መልሱ፡፡ ዓይኖቻችሁን ግለጡ ይህን ብታደርጉ የአርባ ዓመታቱ መንገድ የአራት ሰዓታት ብቻ ይሆንላቹሀል፡፡ አይ አይሆንም አያሻንም ብትሉ ግን የአራት ሰዓታቱን መንገድ በአራት መቶ ዓመታትም መዝለቃቹህ የሚያጠራጥር ብቻ ሳይሆን በርግጠኝነት ከቶውንም የሚቻላቹህ አይሆንም፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው አህጉሪቱ ፈቀቅ ማለት የተሳናት፡፡ እናም እባካቹህ እባካቹህ እባካቹህ ይሄ ለመረዳት የሚከብድ የሮኬት ሳይንስ (የውንጫፍ መጣቅ) አይደለም፡፡ ተረዱ ተለወጡ እንጂ ጃል?

amsaluእንዲህም ስላቹህ ግን ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እንደኛው ጨለማ እንዳይመስሏቹህ፡፡ እንዲያውም ካላቹህ እንደኛው ያሉቱ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እዚሁ ሩቅ ሳንሄድ ኬንያን ብናይ የኬንያ መንግሥት የኪነት ሥራዎችን ለማበረታታት በኪነት ሥራ ላይ ምንም ዓይነት ቀረጥ አትቀርጥም፡፡ አየ እነሱ ያገኙትን ዕድል እኛ ብናገኘው ካለን የጥበብ ሀብት አንጻር ምን ያህል መጠቀም በቻልን ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

amsalugkidan@gmail.com

ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 110 የካቲት 2006ዓ.ም. (ስዕል: the house of words by Wosene Worke Kosrof)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የእምዬ ምኒልክ አዳራሽ October 30, 2023 10:27 am
  • የኢትዮጵያ መከላከያ መሥራች አጼ ምኒልክ መሆናቸውን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናገሩ October 26, 2023 01:30 pm
  • ጥቅምት 15 ለምን? October 26, 2023 01:29 am
  • “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” October 26, 2023 12:57 am
  • “ውትድርና ሕይወቴ ነው” October 26, 2023 12:13 am
  • መከላከያ በሁሉም መስክ ኢትዮጵያን የሚመጥን ኃይል እየገነባ ነው October 20, 2023 05:07 pm
  • “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትምህርት ቤት እኩል ነው በችሎታው ነው እንጂ የሚመዘነው” ፕ/ር ብርሃኑ October 20, 2023 04:47 pm
  • 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ታሰሩ October 18, 2023 04:29 pm
  • በተማሪዎች ፈተና ውጤት ለታየው ውድቀት ትምህርት ሚ/ር ኃላፊ መሆን አለበት ተባለ October 18, 2023 04:00 pm
  • ቀይ ባሕር እና ዓባይ “የኅልውና ጉዳይ ናቸው”፤ “መተንፈሻ ወደብ ያስፈልገናል” October 13, 2023 10:04 pm
  • ከ3,106 ትምህርት ቤቶች 1,328ቱ (44%) አንድም ተማሪ አላሳለፉም October 10, 2023 01:51 pm
  • “አቋጥሬ” በአማራ ክልል እያጫረሰ ነው፤ ” ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም ” ነዋሪዎች October 10, 2023 09:07 am
  • እሸቴ አሸባሪ፤ ቲዲኤፍ/ትሕነግ “ሰማዕት” – የዘመናችን ጉድ! October 7, 2023 06:47 am
  • በወልቃይት 1.1ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ ለመሰብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሠራተኛ ይፈለጋል September 27, 2023 10:42 am
  • በአማራ ክልል ሰላም ዕጦት ከ90.5 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቶች ቆመዋል September 27, 2023 08:41 am
  • ወርቁ አይተነው የሸሹት ከዝርፊያ፣ ውንብድናና ዕዳ ጋር በተያያዘ ነው September 21, 2023 02:38 pm
  • ወደ አማራ ክልል ሊተላለፍ የነበረ መሣሪያና ሰነድ ተያዘ September 19, 2023 04:35 pm
  • በትግራይ መርዶ በይፋ ሊታወጅ ነው September 19, 2023 04:22 pm
  • ጃርቶች ለምን ይጮኻሉ? September 19, 2023 04:37 am
  • “ዐቢይ ግድቡን ሸጦታል” ጌታቸው ረዳ September 11, 2023 10:18 am
  • አቶ አገኘሁ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ዋጋ እንደሚከፍሉ ተሰማ September 10, 2023 06:52 pm
  • ለዋዜማ ሬዲዮ “ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ” ያደርጋል ያላችሁት ረቂቅ ሰነድ የታለ? September 10, 2023 01:58 am
  • ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም September 8, 2023 02:31 pm
  • የትግራይ መፍረስ በርዕሰ መስተዳደሩ አንደበት September 8, 2023 02:49 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule