የዓለም ህዝብ ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን ድል ያደረገውን የጥቁር ጦር መሪ አጤ ምኒልክን ለማወቅ እጅግ ጓጓ፡፡
ምስላቸውን ለማየት ተቁነጠነጠ፡፡
ሙሉ ታሪካቸውን ለመስማት ተንሰፈሰፈ፡፡
ይህንኑ ተከትሎም፤ “እንኳንም ደስ አለዎት” ለማለት ከቁጥር የበዙ ደብዳቤዎች ይጎርፉላቸው ነበር፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በፖስታ ቤት በኩል የኢትዮጵያ ቴምብር የተለጠፈበት መልስ እንዲላክላቸው ይጠይቁ ነበር፡፡
ለምን… ?
ቴምብሩ ላይ ያለውን የምኒልክን መልክ ለማየት፡፡
ባለ ብዙ ዝናና ክብር ባለቤት የሆኑትን የምኒልክን ጥቁር ፊት ለማየት፡፡
የሰው ሀገር ሰው ሁሉ፤ “ዝናውን እንደሰማሁ መቼ ሄጄ ባየሁት”፣ “በጀግንነቱ እንደ ተማረኩ መች ተጉዤ ባገኘሁት”፣ “ካሁን ካሁን ፈቅዶልኝ ወታደር ሆኜ ባገለገልኩት” ያለላቸው አጤ ምኒልክ የኛ ናቸው፡፡
በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን ያንበረከከ የጥቁር ጦርን የመሩት ንጉስ የኛ ናቸው፡፡
መወድስ የማይበዛበት የአድዋ ድልም የኛ ነውና፣
እንኳን ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ለምንኮራበት በዓላችን በጤንነት አደረሰን! (ምንጭ: ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር – Hiwot Emishaw)
Leave a Reply