* የሰሜኑ ኮከብ አብርሃ ደስታ እንኳንም ተፈታህ!
የሰሜኑ ኮከብ ወንድም አብርሃም ደስታ ከእስር እንደሚፈታ ቢገመትም ዘንድሮ ሲሆን እንጅ ሲባል ለማመን ተቸግሬያለሁና ዛሬን መቆየት ነበረብኝ ። እናማ የሰሜኑ ኮከብ ደፋሩና ለእውነት ግንባሩን የማያጥፈው የመቀሌው አብርሃም ደስታ ” እውነት ተፈታ ” ሲባል ሰማሁ ፣ ደስ አለኝ ! አብርሽ
እንኳንም ከቤተሰብ ፣ ከዘመድ አዝማድና ወዳጅ አፍቃሪ ወገንህ ጋር ተቀላቀልክ እልሃለሁ ፣ አብርሽ!
ከሁሉ አስቀድሞ አብርሃም ሃብታሙ ከተኛበት ሲጎበኘው የሚያሳየውን ምስል ስመለከት በደስታ ኩራት ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ማንባቴ አልቀረም … ሁለቱ ወንድሞች ገርድሰው የጣሉት ልዩነትና ህብረታቸው ሳውቀው ዛሬ እንደ ብርቅ ነገር አስደሰተኝ ! በዚህ ዛቢያ ስማስን የዘር ፖለቲካው ክፋት አንደርድሮ ወደ ሌላ አቅጣጫ ወረወረኝ … ከምንም በላይ በበቀል ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ አካሄድ አደገኛነት ታይቶኝ በደፈናውም ቢሆን መብተክተኬ ግድ ሆነ …
በእኛ ሐገር ዲሞክራሲያዊ የበቀል ፖለቲካ ሰለባዎችን አሰብኩና በደስታየ መካከል ከፍቶኝ ቆዘምኩ ስለ ፍትሃዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እየተለፈፈና እየተደሰኮረ መሬት ላይ ያለው እውነታ ሌላ ነው ። ባሳለፍናቸው ሁለት አስርት ቅርብ አመታት በስደቱ የሆነውን እውነት ስለተናገርን ብቻ ” አይናችሁን ላፈር ” ከተባሉት መካከል አንዱና ቀዳሚው ብሆንም ነገር ላለመቀላቀል ብቻ የእኛ ነገር ልተወው ፣ መነሻየ ስለሆነው በሐገር ውስጥ እየሆነ ስላለው ፣ በዴሞክራሲያዊ በቀል ፖለቲካው ዳፋ ተጠቂ ስለሆኑት ትንታግ ወጣት ጎልማሳዎቹ ጥቃት ጥቂት ላውሳ ..
የሰሜኑ ኮከብ የምንለው አብርሃም ደስታና መሰክ ወንድሞች በሰላማዊ መንገድ ” ሐገር አለን! ” ብለው ሀሳባቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልጹ የገዥው አካል የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን አስታወስኩት … እርግጥ ነው ብዙዎች በሐገር ወገናቸው ድጋፍ ከፍተኛ ትምህርት ተምረው ፣ ለሐገር ወገናቸው የድርሻቸውን ማድረግ እንዳይችሉ መስራት የሚችሉበት እድሜያቸው ወህኒ እየበላው ነው … ለሃገራቸው ቀናኢ ሆነው ድምጻቸውን ባሰሙ በቀጥታና በስውር ተንኮል፣ በበቀል ፖለቲካ እየተጠለፉ ነው … ቤተሰብና ቀሪ ዘመናቸው በፖለቲካ አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ በበቀል ሲገለሉና ሲሰቃዩ ለመገኘቱ እውነት ማሳያ ታይተው የጠፉ ፖለቲከኞች ፣ ጋዜጠኞችና ልሂቃን ሞልተውናል !…
ለዲሞክራሲያዊው የበቀል ፖለቲካ አካሄድ ጥሩ ማሳያ ብዙ ወንድም እህቶች ቢኖሩም ህክምና ለማግኘት በስቃይ ላይ ሆኖ ደጅ የሚጠናው ጎልማሳ ፖለቲከኛ ሐብታሙ አያሌው በቅርብ የምናገኘው አስረጅ ማሳያ ይመስለኛል! ከራሱ ከገዥው ፖለቲካ ፖርቲ ተፈልቅቆ የወጣው ሐብታሙ እውነትን ተከትሎ የተጓዘበት መንገድ ለወህኒ ዳርጎት ፣ በዚያው በወህኒ የተፈጸመበት በደል ህመም በሽታውን አባብሶበት፣ ከወንጀለኛነት ነጻ ተብሎ ሲለቀቅም የአቃቤ ህግ ይግባኝ ክስ የሀብታሙን የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት አሳግዶታል! ሃብታሙ በጸና ህመሞ አልጋ ላይ ሆኖ ነፍሱን እንዲታደጉ ደጋግሞ አቤቱታ ያቀረበላቸው የፍትህ አካላት የሃብታሙን የነፍስ አድን ጥያቄ ማስረጃ ተቀብለው ሳለ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው አልገኝ ብለው ቸግሮናል! ይህ መሰሉ ግፍና በደል ስሙ ማን ይባላል ? እስኪ ንገሩን?
በዜጋው ላይ የዘር መድልኦ ነግሶ ፣ ግፍ ልኩን አጥቶ ፣ ፍትህ ሲዛባ ፣ የወጣው ሐገር መመለስ ሞት መስሎት ፣ ሐገር ያለው ነፍሱ በሬ ሃገሩን ጥሎ መውጣት ሲሆን ሕልሙ ማየት የሚያመውን ያህል ህመም አለ አልልም! ዲሞክራሲያዊው የበቀል ፖለቲካ አካሄድ ሃገሬውን ሐገር አልባ ስሜት አውርሶ ተስፋ ቢስ እያደረገው ነው ! በተለይ እንደ ምክያታዊው ወጣት ፖለቲከኛ እንደ አብርሃ ደስታ ያሉት ወንድሞች ጥፋተኛ ተብለው ያሳሰራቸው ጉዳይ አላሳምን ብሎን ፣ መታሰርን ስንቃወም ብንከርምም ፣ ሲፈቱ የምንደሰተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስለተቀላቀሉ እንጅ የታሰሩበት ምክንያት አሳማኝ መረጃ ቀርቦና አሳምኖን አይደለም!
በእኛ ሐገር ፖለቲካ ቁማር ነው … ዘባተሎው ፖለቲካ ስልጡን መሪ አጥቷል ! … ከሐገር እና ለወገን ጥቅም “ያገባናል ” ያሉ ይጮሃሉ ፣ መንግስት ሰበብ አስባብ ፈልጎ ቀና ያሉትን አንገት ለመስበር ያሳድዳል ፣ ያስራል … ” ያገባናል ” ያሉት ጩኸት ላንዳፍታ ይነሳና ተራግቦ ይረሳል … ያነሱት የህዝብና የሐገር ጉዳይ ይረሳና ጀግኖቻችን “ፍቱልን” ፣ ” አሳክሙልን! ” ብለን እንድንጮህ ያደርጉናል ፣ ሲፈልጉና ሲፈቅዱ አንገላተው ይፈቷቸዋል ፣ የታመሙትንም ቢሆን ህመሙ በልቶ ሊጨርሳቸው ሲል ፈጣሪን ከፈሩ ህክምና ይሰጧቸዋል ፣ ፈጣሪን ካልፈሩ በበቀል አሽተው ይወረውሯቸውና እያለቀስን እንኖራለን
የሰሜኑ ኮከብ አብርሃም ደስታ ከዚህ መሰሉ የእኛ ፖለቲካ አዙሪት ገብተህ ከወህኒ በመውጣትህ ደስ ብሎኛል ፣ ደስ ብሎናል ! እነሱም የሚፈልጉት የታሰርክበት ጉዳይ አስረስቶ ” እንኳንም ተፈታህ ” እንድንል ቢሆንም ርቀህባቸው ስለተጎዱ ቤተሰቦች ፣ ስለዘመድ አዝማድና ወገን አፍቃሪዎችህ ሲባል እንኳንም ተፈታህ!
ወዳጅ የሐገር ልጅ አብርሽ አሽቃባጭ ሆነህ ከተደላደለው ወንበር እንዳሻህ መሆን ሲቻልህ ፣ ስለ እውነት ለወገኖችህ የከፈልከውን መስዋዕትነት ግን ማንም አይረሳውም!
እንወድሃለን!
ነቢዩ ሲራክ
ሐምሌ 2 ቀን 2008 ዓም
Leave a Reply