ቁጥሮቹ አስገራሚ ናቸው – ማለቴ ለኢትዮጵያ። በ1997 ዓ.ም፣ (ከአስር ዓመት በፊት መሆኑ ነው…) የአገሪቱ ገበሬዎች ጠቅላላ የእህል ምርት 119 ሚሊዮን ኩንታል ነበር። አምና ደግሞ፣ 236 ሚሊዮን ኩንታል። እነዚህ፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቁጥሮች… ስህተት ይሆኑ እንዴ? ሊሆኑ አይችሉም ለማለት አስቸጋሪ ነው። አንደኛ ነገር፣ አስደናቂው የእድገት መረጃ፣ ከሌሎች በርካታ መረጃዎች ጋር ሲጋጭ፣ ምን ታደርጉታላችሁ?
መስኖ፣ … እንደድሮው ነው (1% ለመሙላት ብዙ ይቀረዋል)!
መቼም፣ ከእርሻ እድገት ጋር አብሮ፣ የመስኖ ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም። ባለፉት አስር አመታት፣ የመስኖ እርሻ ተሻሽሎ ይሆን? አልተሻሻለም – ከጫት እርሻ በቀር። መስኖን በመጠቀም፣ የጫት ማሳዎችን የሚስተካከል የለም።
በበሬ ማረስ? እሱም በሬ ከተገኘ ነው!
ለእርሻ ስራ፣ ሁለት በሬ ካላቸው ገበሬዎች ይልቅ፣ ምንም በሬ የሌላቸው ገበሬዎች ይበዛሉ። በግብርና ከሚተዳደሩ 15 ሚሊዮን የገጠር ቤተሰቦች መካከል፣ ስንቶቹ ምንም በሬ እንደሌላቸው አስቡት – ስድስት ሚሊዮን ተኩል።
ወተትና ቅቤ? ከአንዲት ላም አንድ ሊትር ተኩል?
ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በገጠር የወተት ምርታማነት፣ ምን ያህል እንዳደገ ጠይቁ። ምንም አላደገም የሚል ምላሽ ነው የምታገኙት – ከስታትስቲክስ ኤጀንሲ።
ስጋ? ለዓመት በዓል ከተገኘ!
የገጠር ነዋሪዎች አመጋገብ እንዳልተሻሻለም፣ የበርካታ ዓመታት መረጃዎች ያሳያሉ። ከአገሪቱ የከብቶች ብዛት ጋር ሲነፃፀር፣ የገጠር ነዋሪዎች ለእርድ የሚያውሏቸው የከብቶች ብዛት፣ 1% አይሞሉም። ለእርድ ከሚውሉ ፍየሎችና በጎች ይልቅ፣ በየአመቱ በበሽታ የሚሞቱት በእጥፍ ይበዛሉ።
እንቁላል? በዓመት አንድ እንቁላል!
ሌላው ቀርቶ፣ እንቁላል እንኳ ብርቅ ነው። ጠቅላላውን የእንቁላል ምርት፣ ገበያ አውጥተው ሳይሸጡ፣ ራሳቸው ቢመገቡት እንኳ፣ በአማካይ ለአንድ የገጠር ነዋሪ፣ በአመት ከአንድ እንቁላል በላይ አይደርሰውም።እነዚህ መረጃዎች በሙሉ፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየዓመቱ በሚያወጣቸው የተለያዩ ሪፖርቶች ላይ የተገለፁ መረጃዎች ናቸው። ታዲያ፣ አስደናቂው የእህል ምርት እድገት፣ ከእነዚህ መረጃዎች ጋር አይጋጭም? በእርግጥ፣ በእንስሳት ምርት ላይ ምንም እድገት አልተመዘገበም ማለት፣ በእህል ምርት ላይም እድገት ሊፈጠር አይችልም ማለት አይደለም ይላል መንግስት። ለዚህም ይመስላል፤ ሰሞኑን “የእንስሳት እና የአሳ ልማት ሚኒስቴር” ለብቻው እንዲቋቋም የተደረገው።
(“አሳ… እንስሳ አይደለም እንዴ?” የሚል የእግረመንገድ ጥያቄ ብናነሳስ! ለነገሩ፣ ይሄ የመስሪያ ቤቶች አሰያየም፣ ቅጣምባሩ እየጠፋበት መጥቷል። ‘ሥም ካልረዘመ፣ ቁም ነገር የደከመ’ ይሆናል የተባለ ይመስል፣ ‘እና’ የሚል ማስረዘሚያ መጨመር በዝቷል። የጤና ሚኒስቴር፣ ብሎ በአጭሩ ከመግለፅ ይልቅ… የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር… ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፣ የጤና ጥበቃ፣ የበሽታ መከላከልና የህክምና አገልግሎት ሚኒስቴር ተብሎ፣ ሥሙ እንዲረዝምለት ይደረግ ይሆናል። Ministry of Health አይደል የሚባለው? ሌላው ደግሞ፣ የእንግሊዝኛ ቃላት ብዛት! ‘ሚኒስቴር’ የሚለው ስያሜ ሳይቆጠር ማለቴ ነው። ፐብሊክ ሰርቪስ… ይህንን በትክክል የሚገልፅ አጭር የአማርኛ አገላለፅ ስላልተገኘ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። እሺ፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርስ? … የግንባታ ሚኒስቴር ሊሉት ይችሉ ነበር።)
ለማንኛውም፣ የእንሰሳትና የአሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴርን፣ በአጭሩ የእንስሳት ልማት ሚኒስቴር ሊባል ይችላል። እንደ መንግስት ገለፃ ከሆነ፣ በእህል ምርት ላይ የታየው እድገት፣ እውነተኛ እድገት ነው። በእንስሳት ምርት ላይ፣ ተመሳሳይ እድገት እንዲፈጠር ነው፤ አዲስ የእንሰሳት ልማት ሚኒስቴር የተቋቋመው ብሏል መንግስት።
ሊሆን ይችላል። መንግስት እንደገለፀው፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ በየአመቱ በሪፖርቶቹ እንደዘረዘረው፣ የእህል ምርት ባለፉት አስር ዓመታት በእጥፍ አድጎ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ መረጃዎቹ መፈተሽ አለባቸው። ለዚህም ነው፣ ከሌሎች መረጃዎች ጋር ይጋጫል በሚል፣ የመጀመሪያውን ጥያቄ ያነሳሁት።
በአንድ በኩል፣ ‘መደበኛ ስህተት’ ይከሰታል። የመረጃ አሰባሰብና አተናተን፣ ሙያዊ መመዘኛዎችን ሁሉ ቢያሟላ እንኳ ስህተቶች እንደሚፈጠሩ ይታወቃል። ግን፣ ሳይንሱ፣ ለዚህም መፍትሄ አለው።
መፍትሄውን፣ የስህተቱን መጠን መጠቆም ነው (Standard Error ይሉታል)። ለምሳሌ፣ ኤጀንሴው የአምናው የአገሪቱ የእህል ምርት፣ 236 ሚ. ኩንታል እንደሆነ ሲገልፅ፣ ከዚሁ ጋር አብሮ ‘መደበኛውን ስህተት’ ጠቁሟል። ብሳሳት ብሳሳት፣ ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል አይበልጥም ብሏል ኤጀንሲው። በሌላ አነጋገር፣ በእርግጠኛነት ምርቱ መጠን፣ ከ231 ሚ. ኩንታል አያንስም፤ ከ241 ሚ. ኩንታል አይበልጥም” እንደማለት ነው። “በእርግጠኛነት” የምትለዋን አገላለፅ ልብ ብላችኋታል? በቃ፣ “መደበኛው ስህተት”፣ መፍትሄ አገኘ ማለት ነው።
ግን፣ ሌሎች የስህተት አይነቶች አሉ – የሙያ መመዘኛዎችን ባለማሟላት ምክንያት የሚፈጠሩ ስህተቶች። ለእህል ምርት የሚውለው የመሬት ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ለመገመት ምን ያህል አስቸጋሪና አወዛጋቢ እንደነበር ሰምታችሁ ይሆናል። ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ነው? ወይስ አስር ሚሊዮን ሄክታር? ይሄን በትክክል አለማወቅ፣ በእህል ምርት ግምት ላይ ከፍተኛ ልዩነት ያስከትላል – የ23 ሚ. ኩንታል ልዩነት። በዚያ ላይ፣ ዝርዝር መረጃ እንዲሰበስቡ የተመደቡ ሰራተኞች፣ ባለማወቅ ወይም በዳተኝነት የሚፈፅሙት ብዙ ስህተት ይኖራል።
የገጠሩ፣ ዳገትና ቁልቁለቱን እየወጡና እየወረዱ፣ ከአርባ ሺህ የገበሬ ቤተሰቦች መረጃ የሚሰበስቡ፣ የማሳ ስፋት የሚመትሩ ከሦስት ሺ በላይ ሰራተኞች የሚፈፅሙት ስህተት፣ ምን ያህል ችግር እንደሚፈጥር አስቡት። የአንዱ ሰራተኛ አንዲት ስህተት፣ ትንሽ ልትመስል ትችላለች። ነገር ግን፣ የኋላ ኋላ፣ የመጨረሻው ሪፖርት ላይ፣ በሦስት መቶ የተባዛ ስህተት ነው የምናገኘው። እንዴት መሰላችሁ? መግቢያ ትኬት የገዙ ሦስት መቶ ደንበኞች የተስተናገዱበት ፊልም ቤትን አስቡ። የመግቢያ ትኬት ዋጋ፣ ሃያ ብር ነው? ወይስ ሰላሳ ብር? ይህንን ለማረጋገጥ ከሰነፍን፣ ስህተቷ፣ የአስር ብር ስህተት ልትመስለን ትችላለች። ነገር ግን፣ ፊልም ቤቱ፣ ከትኬት ሽያጭ ምን ያህል ገቢ እንዳገኘ ስናሰላ ግን፣ ልዩነቱ ይሰፋል – በ6ሺ ብር እና በ9ሺ ብር።
“የአስር ብር ልዩነት ናት” ብለን በዳተኝነት የናቅናት ስህተት፣ የኋላ ኋላ “የሶስት ሺ ብር” ስህተት ልታስከትል ትችላለች። በእነዚህና በሌሎች በርካታ ችግሮች፣ የተከበበ ነው፣ መረጃ የማሰባሰብና የመተንተን ሙያ። ያው፣ በባለሙያ መረጣ፣ በስልጠና፣ በክትትል፣… ለቁጥጥርና ለማመሳከር በሚያመች አሰራር … ወዘተ፣ ችግሮችን ለማስወገድ መጣጣር የግድ ነው። ግን፣ ነገሩ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ከኋላቀር ባህልና ከስልጣኔ ባህልም ጋር የተቆራኘ ጉዳይ ነው። ከኋላቀር ባህል ዋና ዋና ባህርያት መካከል አንዱ፣ “ለመረጃ ብዙም ክብር እና ትኩረት ያለመስጠት ዝንባሌ” ነው።
ምን ማለቴ ነው? ‘ለመረጃ’ (ለእውነታ፣ ለእውቀት… ለሳይንስ) ብዙም ክብር በሌለበት ኋላቀር አገር ውስጥ፣ በአጭር ስልጠና ወይም ተቆጣጣሪ በመመደብ፣ ሁነኛ መፍትሄ ይገኛል ብሎ መገመት፣ አላዋቂነት ነው። ቢሆንም፣… ለዘለቄታው፣ ከድንዛዜ ነቅተን፣ ሳይንስን የሚያከብር ስልጡን ባህል ለማዳበር ካልጣርን በቀር፣ አስተማማኝ መፍትሄ እንደማናገኝ ባያጠራጥርም፤ እስከዚያው፣ ለጊዜው… አጫጭሮቹን ስልጣናዎችንም ሆነ የክትትልና የጥንቃቄ አሰራሮችን… እንደምንም ለመጠቀም መጣጣር ያስፈልጋል። ሙሉ ለሙሉ፣ አስተማማኝ ውጤት ባያስገኝም፤ ስህተቶችን ለመቀነስ ይረዳል። ያው፣… ከኋላቀር ባህል የሚመነጩ እነዚህ ስህተቶችን ሳንዘነጋ ነው፤ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ልዩ ልዩ ሪፖርቶችን ማገናዘብ የሚኖርብን።
እንዲያም ሆኖ፣ በየጊዜው አዳዲስ ስህተቶችን እስካልፈጠረ ድረስ፣ በየዓመቱ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ለንፅፅር ጠቃሚ ናቸው። አንደኛ፣ ለንፅፅር ስንጠቀምባቸው፣ የየአመቱ ስህተት፣ በከፊልም ቢሆን እርስ በርስ የመጣፋት እድል አለው። ሁለተኛ፣ ሌላ ምን አማራጭ አለ? ለጊዜው፣ ከኤጀንሲው ሪፖርቶች ውጭ፣ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለም – ጭፍን ስሜትና ጭፍን ግምት ይሻላል ካላልን በቀር። እናም፣ በአስር ዓመታት ውስጥ፣ የእህል ምርት በእጥፍ አድጓል የሚለውን መረጃ በመቀበል እንጀምር።
(በዓለም ደረጃ ሲታይ፣ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን አትርሱ። ግን፣ ለኢትዮጵያጵያ ግን፣ ታይቶ የማይታወቅ እድገት ነው።)
አሁን ጥያቄው፣ ‘ይሄ አስደናቂ እድገት እንዴት ሊመጣ ቻለ?’ የሚል ነው። የመቶ ሚሊዮን ኩንታል እድገት በሰባት ዓመታት ውስጥ?
ምን ተዓምር ተፈጠረ?
ከዚያ በፊት የነበሩ ዓመታትን ደግሞ ተመልከቱ። በ1988 ዓ.ም፣ የአገሪቱ የእህል ምርት 94 ሚ. ኩንታል ነበር።
የምርቱ መጠን፣ ለአመታት ከዚህ በላይ ብዙም ፈቅ አላለም። 1995 እና 96 ዓ.ም ድረስ፣ እድገት አልታየም። የእህልም ምርት፣ እዚያው ከ95 እስከ 100 ሚ. ኩንታል ገደማ ነው፣ ሲረግጥ የነበረው። የሕዝብ ቁጥር በየአመቱ ይጨምራል። ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሲጨምርና፤ የእህል ምርት ሲደነዝዝ ምን ማለት እንደሆነ ይገባችኋል። ድህነት እየተባባሰ ነበር ማለት ነው።
እናም፣ ድንገት በአዲሱ ሚሌኒዬም ምን ተፈጠረና ነው፣ በአስር ዓመት ውስጥ የእህል ምርት በእጥፍ መት መቶ ሚሊዮን ኩንታል የጨመረው? የእህል መጨመሩ አይደለም ጥያቄው። ባይጨምር ኖሮ፣ ቢያንስ ቢያንስ የ30 ሚሊዮን ኩንታል እህል በእርዳታ ካልተገኘ፣ ብዙዎች በረሃብ ይሞታሉ። የጭማሪው መጠን ነው አከራካሪ ሊሆን የሚችለው።
ለምን አከራካሪ ይሆናል? መስኖ ሳይስፋፋ እድገት?
እንግዲህ፣ ከ97 ወዲህ የገበሬዎች ምርታማነት በእጥፍ ከጨመረ፣ በተወሰነ ደረጃ ጥሪት የማፍራት ተጨማሪ አቅም አይፈጥርላቸውም? ለምሳሌ፣ ለእርሻ፣ ለምግብ እና ለገበያ የሚጠቅሙ የቤት እንስሳትን መግዛትና ማርባት አይጀምሩም? የእርሻ አሰራራቸውን አያሻሽሉም? ለምሳሌ በመስኖ?
ሁለቱም፣ በተግባር አልታዩም። መስኖ ቢስፋፋ ኖሮ፣ የዘንድሮው ድርቅ እጅጉን ፈታኝና አስጨናቂ ባልሆነ ነበር።
በመስኖ ሁለት ሦስቴ በዓመት ማምረት… እየተባለ ብዙ ቢወራም፣ ያን ያህልም የመሻሻልና የመስፋፋት ፍንጭ አይታይበትም። መስኖ ተስፋፍቷል ከተባለ፣ በኢትዮጵያ ገጠሮች ሳይሆን፣ በኢቢሲ ካሜራዎችና ስቱዲዮ ውስጥ መሆን አለበት። ከዚያ ውጪ፣ በገበሬዎች እርሻ ላይ፣ ከአስር ዓመት በፊትም ወደ 170ሺ ገደማ ሄክታር ብቻ ነበር በመስኖ የሚለማው። የጫት ማሳዎች ላይ 20ሺ ሄክታር ጭማሪ የመስኖ እርሻ ከመታየቱ በቀር፣ ለውጥ አልመጣም። የአምናው የመስኖ ልማት፣ 190ሺ ሄክታር ገደማ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ሌሎች ጥንታዊ የእርሻ አሰራሮችም አልተለወጡም።
በሬ፣ ካልተከራዩ ችግር ነው።
እርሻ፣ እንደጥንቱ በበሬ የሚታረስ መሆኑ አይደለም ችግሩ። በበሬ ማረስም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ጥንድ በሬ ካላቸው ገበሬዎች ይልቅም፣ ምንም በሬ የሌላቸው ገበሬዎች ይበዛሉ።
ከአምስት ዓመት በፊት፣ በአገሪቱ ገጠሮች የነበሩት የገበሬ ቤተሰቦች ወደ 13 ሚሊዮን ገደማ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 5 ሚሊዮን ያህሉ ቤተሰቦች፣ አንድም በሬ አልነበራቸውም።
ዛሬስ?
በቅርቡ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከጠቅላላ 15 ሚሊዮን ገደማ የገበሬ ቤተሰቦች መካከል፣ ሁለት በሬ ወይም ከዚያ በላይ ያላቸው፣ አምስት ሚሊዮን አይሞሉም። ምንም በሬ የሌላቸው ደግሞ፣ ስድስት ተኩል ሚሊዮን። በበሬ ማረስ፣ እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አልሆነም ማለት ነው።
ወደ እንሰሳት ሃብት እናምራ።
ከአስር ዓመት በፊት፣ በ97ዓ.ም፣ ከመቶ የገጠር ቤተሰቦች፣ ሃያዎቹ ቤተሰቦች በሬም ሆነ ላም አልነበራቸውም። ዛሬስ? ዛሬም ተመሳሳይ ነው። በ2007 ዓ.ም፣ ከመቶ የገጠር ቤተሰቦች መካከል፣ 23ቱ ቤተሰቦች፣ በሬና ላም የላቸው። በአጠቃላይ፣ ግማሽ ያህሉ የገበሬ ቤተሰብ፣ ወይ ምንም ከብት የለውም፤ አልያም ከአንድና ከሁለት በላይ ከብት የለውም።ምናልባት፣ የእነዚህ ገበሬዎች ኑሮ ባይሻሻልም፣ የሌሎች ታታሪ ገበሬዎች ኑሮ በፍጥነት እየተሻሻለ ቢሆንስ? ደግሞም፣ ኑሮ የሚለካው፣ በከብቶች ቁጥር ላይሆን ይችላል። የጠወለጉና የደከሙ፣ ደርዘን ከብቶችን ከማንጋጋት፣ አንድ ጥጃ በማደለብና፣ አንዲት በወተት የምታንበሸብሽ ላም በመንከባከብ፣ የበለጠ ገቢ ሊገኝ ይችላል።
ማደለብ? ማደለብ… የሚባለው እንኳ እንርሳው። አብዛኛው ገበሬ (ማለትም ከ99% በላይ የሚሆነው ገበሬ)… ከብት የሚያረባው፣ አንድም የእርሻ በሬ ለማግኘት ነው። አልያም ለወተት ሲል ነው። ይሄ ባለፉት አስር አመታት ቅንጣት ታህል ለውጥ እንዳልታየበት፣ በየአመቱ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርቶች ይመሰክራሉ። በ1997 እና በ2007 መካከል ምንም ልዩነት የለም። የሚደልቡ ከብቶች፣ 1% እንኳ አይሆኑም።
እሺ። ወተትስ?
የወተት ምርትም ቅንጣት አልተሻሻለም የሚል መልስ እናገኛለን – ከኤጀንሲው ሪፖርቶች። በሁለት አቅጣጫ ልናየው እንችላለን።
በአማካይ ለአንድ የገጠር ነዋሪ ምን ያህል ወተት ይደርሰዋል? በዘጠኝ ቀን አንድ ሊትር ወተት። ይሄ አልተለወጠም። በአስር አመታት ውስጥ።
ከአንዲት ላም ምን ያህል ወተት ያገኛሉ? ብለን መጠየቅም እንችላለን። በ97 ዓ.ም እና በ2007 ዓ.ም መካከል ብዙም ልዩነት የለውም። ትንሽ ቀንሷል። ግን በጣም ተቀራራቢ ነው። በቀን አንድ ሊትር ተኩል አይሞላም – ከአንዲት ላም የሚገኘው የወተት መጠን።
በአጭሩ፣ የእርሻ በሬ ችግር፣ አልተቃለለም። የወተት ምርትም አልተሻሻለም።
ምናልባት፣ ገበሬዎች “የፕሮቲን” ፍጆታቸውን ከፍ እያደረጉ ከሆነስ?
ማለቴ፣ ስጋ መብላት ካዘወተረ ማለቴ ነው። ለማድረግ ነ ስለጨመረ ቢሆንስ?
በ97 ዓ.ም፣ የገጠር ነዋሪዎች፣ ሶስት መቶ ሺ ገደማ ከብቶችን ለእርድ አውለዋል። በአመት፣ አንድ በሬ ለ200 ሰዎች እንደማለት ነው። በ2007 ዓ.ምስ? ያው ተመሳሳይ ነው። ለሁለት መቶ ሰዎች፣ በአመት አንድ በሬ! ለአርባ ቤተሰብ፣ በአመት የአንድ በሬ ቅርጫ እንደማለት ነው። ይህም በአስር አመታት ውስጥ አልተሻሻለም።
በግና ፍየልስ? በአማካይ ከሰባት ቤተሰቦች መካከል አንዱ ብቻ ነው፣ በአመት በግ ወይም ፍየል የማረድ አቅም የነበረው። በ2007 ደግሞ፣ ከስድስት ቤተሰቦች መካከል፣ በግ ወይም ፍየል የማረድ አቅም ያለው፣ አንዱ ቤተሰብ ነው።
ያው፣ ገበሬዎች ሥጋ መብላት አልጀመሩም። የ“ፕሮቲን” ፍጆታ፣ ብዙም አልተለወጠም። በዶሮ እና በእንቁላል ካላካካሰው በስተቀር!
አሳዛኙ ነገር፣ ግማሽ ያህሉ የገጠር ቤተሰብ፣ ዶሮ አያረባም። ምናልባት፣ የዶሮ በሽታ እያስቸገረው ይሆናል። የዶሮ እርባታ፣ በእውቀት ካልሆነ በቀር አያዋጣም።ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን እንደሚለው ከሆነ፣ ካቻምና፣ 80 ሚሊዮን ጫጩቶች ተፈልፍለዋል። ግን 50 ሚሊዮን ያህል ዶሮዎች ደግሞ ሞተዋል። አምና፣ 90ሚ. ጫጩቶች ተፈልፍለዋል። ግን፣ 60ሚ. ዶሮዎች ሞተዋል።
ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፤ ባለፉት አስር አመታት፣ የእንቁላል ምርት ምንም አልጨመረም። የገጠሩ የሕዝብ ብዛት፣ በ15 ሚሊዮን ጨምሯል – ወደ 80 ሚሊዮን ገደማ። በአመት የሚገኘው የእንቁላል ምርት ግን 100 ሚሊዮን ገደማ ላይ ቆሟል። ከገበያ የተረፈ እንቁላል፣ ለአንድ ሰው በአመት አንድ እንቁላል ላይደርሰው ይችላል።
ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ቤተሰቦች፣ የአንድ በሬ ባለቤት ናቸው። ለማረስ፣ በተውሶ ወይም በኪራይ አንድ በሬ ማሟላት ይኖርባቸዋል። ሁለት በሬ ወይም ከዚያ በላይ ያላቸው የገጠር ቤተሰቦች፣ ወደ 4 ሚሊዮን ገደማ ነበሩ – የዛሬ አምስት አመት።
የቤት እንሰሳት ነገርም፣ በጣም ችግር ውስጥ ስለሆነ ይመስላል መንግስት፣ አሁን ለብቻው የሚኒስቴር መስሪያቤት ያቋቋመው።
(በዮሃንስ ሰ. የተጻፈ – ከአዲስ አድማስ የተወሰደ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply