ይህን ፅሁፍ ነፃ አስተሳሰብን ከሚያውኩ ግላዊ ባህርያት ነፃ በመሆን ማንበብ ያስፈልጋል። የጎሳ፣ የብሄር ወይም የቋንቋ መለያ አጥር ውስጥ ከቆምን የፅሁፉ አላማም ሆነ ይዘት በውል ላይታየን ይችላል። ቢታየን እንኳን ምናልባት ግምገማችን ሊዛባ ይችላል። ምክንያቱም መልእክቱን ወይም አላማውን የምንገመግመው ከቋንቋችን፣ ከብሄር ማንነታችን ወይም ከትውልድ ቀያችን አንፃር ስለሚሆን ሚዛናችን ወይም ግንዛቤያችን ስህተት ይሆናልና ነው። ሰው መቼም ሲያስብ፣ ሲወስንና እርምጃ ሲወስድ አስተሳሰቡን፣ አወሳሰኑንና እርምጃ አወሳሰዱን በስሜት ሀይል ከሆነ መነሻው፣ መንገዱም ሆነ ግቡ ስህተት መሆኑ አይቀርም። ውጤቱም ጥፋት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ መነሻው ያስተሳሰብ፣ ያወሳሰንና የድግጊት መነሻችን ነፃ አእምሮ ሳይሆን ስሜት ብቻ ስለነበረ ይመስለኛል። ሰው በእውነቱ ሳይሆን በስሜቱ ከተመራ መደረሻው ውድቀት መሆኑ አይቀርም። እኔ የምደግፈው እገሌ የሰጠውን ሃሳብ ወይም የያዘውን አቋም ነው፦ ምክንያቱም ብሄሩ የኔ ስለሆነ፤ እንቶኔ የተባለው ፓርቲ ደጋፊ ነኝ፤ ምክንያቱም አባላቱ የኔ ብሄር አባላት ስለሆኑ በሚል መስመር ብንሄድ የት እንደምንደርስ ለማወቅ ነጋሪ አያስፈልገንም። በጥቅሉ ያመለካከታችንና የፍርዳችን ትክክለኝነት መስፈሪያው ነፃ መረጃ ወይም ነፃ አእምሮ መሆኑ ቀርቶ ያልተመረመረ ጭፍን ወገንተኝነት ከሆነ ውጤቱ የዘለአለም ጥፋት ነው። ጥፋቱም ከግልና ቡድን አልፎ ላገርና ህዝብ ይተርፋል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አበሳና ፍዳ ምንቹ ይህ ሳይሆን አይቀርም። ብዙዎቻችን እምነትና አቋም የምንይዘው፣ ውሳኔና ፍርድ የምንሰጠው በማስረጃ ሳይሆን በፍረጃ መሆኑ ስለሚታይ የፅሁፌ መልእክት የዚህ ክፉ አባዜ ሰለባ እንዳትሆን ሰግቼ በዋና ከማልወጣው የሃሳብ ባህር ውስጥ ገባሁ እንጂ አነሳሴ እንኳን ስለሰው ግንዛቤ ወይም ያስተሳሰብ ህግ ለመደስኮር አልነበረም። እናም ወደነጥቤ ልመለስ። ግን ለምወደው የትግራይ ህዝብ የምሰጠው ማሳሰቢያ አንባቢ ከቋንቋና የብሄር ማንነት ነፃ በሆነ አመለካከት እንዲመዝነው አደራ ማለቴን አልተውም።
ዛሬ በትግራይ ህዝብና በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የወደፊቱን ዘለአለማዊ ህይወት የሚወስን ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሯል። አጋጣሚው እንደሁኔታው ክፉም በጎም ሊሆን ይችላል፣ ይህን የሚወስነው የትግራይ ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ ዛሬ ወሳኝ በሆነ የታሪክ ነጥብ ላይ ቆሟል። በዚህ ወሳን ነጥብ ላይ ቆሞ የሚሰጠውም ፍርድም ሆነ የሚወስደው ምርጫ ወንድሙ ከሆነው የቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የሚኖረውን የወደፊት ግንኙነት እስከወዳኛው ይወስናል። ምርጫውም በቋንቋና በዘር በሚመስሉት ጥቂት ግለሰቦችና በሌላው ኢትዮጵያዊ መካከል ነው። ምርጫው ቀላል ላይሆን ይችላል ግን ወሳን ነው።
በአንድ በኩል በብኼር ማንነትና በቋንቋ ሚዛን በጭካኔው ወደር የሌለውንና አንድ ሃሙስ የቀረውን የጥቂት አንባገነን ግለሰቦችን ቡድን መወገን ወይም ፍትህ ከተጓደለበት የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ቆሞ ለሃቀኛና አስተማማኝ ዲሞክራሲ አብሮ በመታገል ወንድም ከሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በማይበጠስ የታሪክ ገመድ ተሳስሮ ለዘለአለም መኖር ነው። በዚህ ወሳን ወቅት ከቋንቋና ብሄር መጀሳሰል በቀር ባመለካከት ከማይወክሉት ጥቂት ገዢዎች ጋር መወገንና ከብዙሀኑ ህዝብ ጋር መቆራረጥ እጅግ አስፈሪና አደገኛ ምርጫ ነው።
በእኔ አስተያየት አሳምሬ የማውቀውና ደጉ የትግራይ ህዝብ ብዙሃን ወንድሞቹን በጥቂት አንባገነኖች ይለውጣል ብዬ አልገምትም። የትግራይ ህዝብ እስከማውቀው ድረስ ሰላማዊና በኢትዮጵያዊነቱ ጥርጥር የሌለው ቅን ህዝብ ነው። እንደአለመታደል ሆኖ ክልሉ ለረጅም ጊዜ በጦርነት ቁም ስቅሉን ሲያይ የኖረ ህዝብ ቢሆንም በሌሎች ለደረሰበት መከራ ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝ ተጠያቂ አድርጎ አያውቅም። በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ከህዝብ ጋር ተስማምቶ ከመኖር በቀር ከማንኛውም ጎሳወይም ብሄር ጋር የተለየ ግጭት ውስጥ ገብቶ የሚያውቅ አይመስለኝም። የሚታወቀውም በሰላማዊነቱና ተግባቢነቱ ነው።
ይሁን እንጂ እንደማንኛውም ህዝብ ሲደርስበት የነበረውን ጭቆና ሰበብ በማድረግ በትከሻው ላይ ተንጠላጥለው ስልጣን ላይ የወጡ እፍኝ የማይሞሉ ብልጣብልጦች በስሙ በመነገድ ሌሎች ወንድሞቹ ከገዢዎች ጋር በአንድ አይን እንዲመለከቱት ያላደረጉት ጥረት የለም። በስሙ ገዝተዋል፣ ጨቁነዋል፣ ገድለዋልም። ለትግራይ ህዝብ ፍትህና ነፃነት የሞቱትን ሺዎች አፈር አልብሰውና ቃልኪዳናቸውን አጥፈው ለትግራይ ህዝብ ሳይሆን እፍኝ ለማይሞሉ ታማኝ ትግሬዎች፣ አማሮች፣ ዖሮሞዎች፣ ጉራጌዎችና ሌሎች አገልጋዮቻቸው ቀለብ ሰፋሪ ሆነዋል። የትግራይ ህዝብ ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ገዢ ቡድን ያገኘው ጥቅም ስም ብቻ ነው። የግፍ አገዛዛቸው ሰለባ ከመሆንም አላመለጠም። ይባስ ብሎ ቋንቋውን በመናገርና በስሙ በመጨቆን በገዛ ወገኖቹ በክፉ አይን እንዲታይ አድርገውታል።
ይልቁንም ከመቼውም በባሰ ዛሬ በሚገኝበት አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል። በአንድ በኩል ከጥቂት ብልጣብልጦች በቀር እንደህዝብ ባላተረፈበት ስርአት እንደጨቋኝ ህዝብ ስለታየ ስርአቱ ቢፈርስ እጠቃ ይሆናል በሚል ስጋት ግፈኞቹን እስከነጉድፋቸው ለመደገፍ ሲያመነታ በሌላ በኩል ደግሞ በጠራራ ፀሃይ የፈጸሙት ግፍና መከራ ለፍትህና ዲሞክራሲ ቀናኢ የሆነውን ህዝብ ሆድ ማሻከሩ አይቀርም። ለፍትህና ዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና እኩልነት ልጆቹን የገበረው የትግራይ ህዝብ እኩልነትና ነፃነት የጠየቁ ሰላማዊና ለጋ ወጣቶች ደም በየአደባባዩ ሲፈስ አበጀ የሚል አይመስለኝም።
የሆነው ሆኖ ዛሬ የትግራይ ህዝብ ከፊቱ ወሳን ምርጫ ቀርቦለታል። ምርጫው ከገዢው መደብ ጋር በማበር ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እስከወዳኛው መቆራረጥ ወይም ለፍትህና ዲሞክራሲ ደሙን እየገበረ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመወገን በታሪክ ሞገስና በህዝብ ዘንድ ዘለአለማዊ ፍቅርና ክብር መጎናፀፍ ነው። የትግራይ ህዝብ ምርጫ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ህዝባዊነት እንደሚሆን የምጠራጠርበት ምክንያት የለኝም። ለምን ቢባል በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ከቋንቋውና ብሄርብሄሩ በቀር በምግባሩ የትግራይን ህዝብ ስለማይመስል ነው። ለምን ቢባል የትግራይ ህዝብ ወንድሙ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ ጥያቄ በንፁህ ህሊና እንጂ በቋንቋና በብሄር ዳኝነት ይዳኘዋል የሚል እምነት ስለሌለኝ ነው። ለምን ቢባል የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ የማይታረም የታሪክ ስህተት ለመስራት ይወስናል ብዬ ስለማላምን ነው። ለምን ቢባል የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እንደቡድን የከዳውን የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ ዳግም ይከዳዋል ብዬ ስለማላምን ነው። ስንት የታሪክ ፈተና በጽናት ያለፈው የትግራይ ህዝብ ይህን ልላ የታሪክ ፈተና ይወድቃል ብዬ አልገምትም።
መልካሙን ለማየት ያብቃን።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Tadesse says
A very nice idea,if if took the wrong way,it will surely be a disaster for the people of Tigray,a man with out history is like a tree with out roots.This is not our history,our history is Ethiopia under God.
Tadesse says
Another thing is that we have no any relation with these brutals like Abay Weldu.