ባለፈው ሰሞን ወያኔ ኢሕአዴግ ላለመው የጥፋት ተልእኮ ወሳኝ ክንውኑን መተግበሩ ይታወሳል፡፡ ወያኔ ለጥፋት ተልእኮው በእጅጉ የሚረዳውን ወሳኝ የጥፋት ሥራ የመሥራቱን ያህል ከእምነተ-አሥትዳደር (ፖለቲካ) ፓርቲዎች (ቡድኖች) አንሥቶ እስከ ሕዝባዊ ማኅበራት (Civic organizations) ድረስ ያሉ ሁሉ ልብ ሳይሉት ወይም በቅጡ ሳይረዱት ቀርተው ይሁን ምን አላውቅም ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡት ሲቀሩ ሳይ እጅግ ተገርሜያለሁ፡፡
ወያኔ በአሩሲ ሔጦሳና በሐረር ጨለንቆ ላይ ፋሽትት ጣሊያን ለሰበው የቅኝ ግዛት ይዞታ ዘለቄታ ሲል በነበረው ስልት (Strategy) ተአማኒነት እንዲኖረው በእውነተኛው ታሪካችን ላይ ሆን ብሎ በክፋት የፈጠረውን ፈጠራ በርዞ የሕዝባችንን አንድነት፣ ሰላም፣ ጥምረት፣ ወንድማማችነት (እኅትማማችነት)፣ መተማመን ለመፈረካከስና ለአገዛዙ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲጠቀምበት የነበረውን ድርሰት ወያኔ ሐሰት እንደሆነ እያወቀ ነገር ግን ላለው ተመሳሳይ የጥፋት ዓላማ ከወደቀበት በማንሣት የፈጠራ ሠማዕታትን የሚዘክር የመታሰቢያ ሐውልት አስገንብቶ አስመርቋል፡፡ እንደሚታወቀው ፋሺስት ጣሊያን አስቀድሞ የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ክፍል በኋላም መላውን ኢትዮጵያን ይዞ በነበረበት ወቅት ሕዝቡን አዳክሞ ቅኝ አገዛዙን ለማጽናት እንዲያስችለው በፋሺስታዊና የቅኝ አገዛዝ ስልት (Strategy) ሕዝቡን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በሞያ ወይም በሥራ ዓይነቶች ሳይቀር ከፋፍሎ ያናቁር ለማፋጀትና ለማባላት ይጥር እንደነበር ታሪክ ዘግቧል፡፡
ፋሺት ጣሊያን ይህ እኩይ ሴራው ያሰበውን ያህል ሳይሠምርለት ቀርቶ በጀግኖች አርበኞቻችን ድል ተመትቶ ተባረረ፡፡ ነገር ግን ሰላዮቹ ሚሲዮኖችና ሀገር አሳሾቹ ሀገራችንን ለመበቀል ሰላምና አንድነት እንዳይኖራት ለማድረግ ብዙ እኩይ ፈጠራዎቻቸውን እውነት አስመስለው በመጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ዛሬ አሸባሪዎቹ ወያኔ ኦነግና ሻቢያ የኦሮሞን ሕዝብ በሔጦሳና በጨለንቆ ተፈጽሞብሀል የሚሉትን በጅምላ ጡት እጅና ብልት የመቁረጥ ቅጣት ወይም ግፍ ተፈጽሟል ብሎ የጻፈ ሚሲዮን ወይም አሳሽ አንድ እንኳን የለም፡፡ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች እከሌ እከሌ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ እንደዚህ በሚለው መጽሐፍ እነደጻፈው እያሉ የጠቀሷቸውን መጻሕፍትም ከሀገር ውጪ ያሉ ወዳጆቻችንን ሳይቀር አስቸግረን መጻሕፍቱ አሉበት በተባሉ ቦታዎች አፈላልገን ስናነብም በሚገርም ሁኔታ ከሚሉት ጋራ ጨርሶ የማይገናኝና የሌለ ፈጠራ ሆኗል፡፡ ይሄ ምንን ያመለክታል ወገን?
ይሄን ብለው የሚያወሩ ወገኖች ዐፄ ምኒልክ ሀገርን መልሶ አንድ ለማድረግ በዘመቱበት ወቅት ከጦር አበጋዞቻቸው ዋናዋናዎቹ የኦሮሞ ተወላጆች እንደነበሩ አያውቁም፡፡ ለምሳሌ የጦሩ አበጋዝ (ዋና ሹም ወይም ኃላፊ) ራስ ጎበና ዳጬ ነበሩ፡፡
ጥቂት የማንባል ዜጎች በየሕሊናችን “ወያኔ ይሄንን ሐውልት የሠራው እውን ከማስተዋል ማነስ ብቻ ነው ወይስ ከጀርባው እንዳች ነገር አለው?” የሚለው ጥያቄ እየፈራነውም ልናስበው ሳንፈልገውም ገፍቶ ይመጣብናል፡፡ ገፍቶ ከመጣም በኋላ ልንተወው ወይ ልንመልሰው ለማንፈልገው ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመመለስ ስንሞክር የሆነ አስጨናቂ ስሜት ይጫጫነናል፡፡ የምናውቀውን እውነታም ላለማመን ከራሳችን ጋር ከባድና የማያዋጣ ሙግት እንገጥማለን፡፡ ሳንቋጨውም ባለበት መተውን እንመርጣለን፡፡ አደጋው እንግዲህ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አደገኛ ነገር በእንጭጩ መታረም መቀጨት ካልቻለና ጊዜ እያገኘ በሄደ ቁጥር ስር እየሰደደ፣ እየከበደ፣ እየጠነከረ የሚሔድ መሆኑና ካደገ፣ ከከበደ፣ ስር ከሰደደ፣ ከጠነከረና ከአደጋ ቀለበት ውስጥ ከከተተን በኋላ የጠነሰሰውን አደጋ ከመጋት ውጭ ለማረም ለማስተካከል የማንችል መሆኑ፡፡ ከዚህ የሔጦሳና የጨለንቆ የፈጠራ ሠማዕታት የመታሰቢያ ሐውልቶች ከማንም በላይ የደነገጡ ግራ የተጋቡና ያዘኑት በተቃውሞ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ታዋቂ የኦሮሞ ልኂቃን ናቸው፡፡ ተፈጽሟል የተባለው ድርጊት እንዲሁ ከመወራቱ ውጪ ለመፈጸሙ አንድም መረጃ እንደሌላ በመግለጽ ጭምር፡፡
ወያኔ ይሄንን የጥፋት ሥራ ከመሥራቱ በፊት ከዚህ ሥራ መቅደም የነበረበትን ሥራ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ያለ እንዳች ማሰለስ ሥራዬ ብሎ በሚገባ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረውን በዘርና በጎጥ ያልተገደበ ያልታጠረ የአንድን ሕዝብና የአንዲት ሀገር አስተሳሰቡን በማፈራረስ ዜጎችን “ወደ ክልልህ” እየተባሉ እስከ መፈናቀልና መሰደድ የደረሰ በዘርና “ክልል” ብሎ በጠራው የሀገር ቅርጫ አጥብቦ ከፋፈለው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የመጥፋት ያህል ደበዘዘ፣ ብሔርተኝነት ነገሠ፣ በኢትዮጵያዊነት መለያና ቀለም ቦታ ዘርና ብሔርተኝነት ተተካ፣ ዜግነት በብሔር ተተካ፡፡ በውጤቱም ሀገራዊ (ብሔራዊ) ስሜት ጠፋ ሕዝቡ ተፈራቀቀ ተራራቀ፡፡ ወያኔ ይሄንን እኩይ ሥራ በአጥጋቢ ውጤት እንደሠራ ካመነ በኋላ የእኩይ ዓላማውን ቀጣይ ምዕራፍ በቅርቡ ተግብሯል፡፡ ሦስተኛውንና የዚህን እኩይ ድርጊት የመጨረሻ ምዕራፍ በያዘለት የጊዜ ቀጠሮ ለመከወን ያስባል፡፡
ይህ ዓይነት ዘውጋዊ የእምነተ-አሥተዳደር (የፖለቲካ) አስተሳሰብ ሀገራትን ለምን ዓይነት ችግር እንደዳረገ የዓለም ታሪክ በሚገባ ያስረዳናል፡፡ ሩቅ ሳንሔድ ሩዋንዳን የወሰድን እንደሆነ ለምን ዓይነት አደጋና እልቂት እንደዳረጋት ሁሉም የሚየውቀው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ ሩዋንዳዊያን ጣሊያን በእኛ ላይ እንዳደረገው ሁሉ ቅኝ ገዥዎቻቸው በሠሩት የመከፋፈልና የማባላት ሴራ ከደረሰባቸው ከዚያ አሳዛኝና ዘግናኝ የእርስ በእርስ እልቂት በኋላ ዛሬ ላይ ሩዋንዳ ውስጥ እኔ ሁቱ ነኝ እኔ ቱትሲ ነኝ እኔ ትዋ ነኝ በማለት ማንነትን በዘር ለመግለጽ መሞከር የተወገዘና በሕግ የተከለከለ ሆኗል፡፡ አንድ ሩዋንዳዊ ራሱን ማንነቱን ለመግለጽ በፈለገ ጊዜ እኔ ሩዋንዳዊ ነኝ በማለት ነው እራሱን የሚገልጸው፡፡
እኛ ታዲያ ዘርን መሠረት ካደረገው የዘውግ እምነተ-አስተዳደር (ፖለቲካ) አስተሳሰብ ለመውጣትና እኔ ትግሬ ነኝ፣ እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ ጉራጌ ነኝ፣ እኔ አማራ ወዘተ. እያልን ማንነታችንን ከኢትዮጵያዊነት አጥበን በዘራችን በመግለጽና አንድነታችንን ከሚከፋፍል የዘውግ ፖለቲካን ለመተው ለመጣል የግድ እንደ ሩዋንዳ ያለ የዘር ፍጅት ውስጥ ማለፍ ይኖርብናል ወይ? ብልጥ ከሌላ ይማራል ነበር ብሂላችን፡፡ ይህ እንዲሆን ካልተፈለገ በስተቀር ይሄንን መረዳት ይሳናቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ ሂደቱም ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ያለው ይሄንን እውነት ነው፡፡ የእኛ መሪዎች አቶ መለስን ጨምሮ ሩዋንዳ በየጊዜው የዚህን የዘር ፍጅት ለማሰብ በዓል ባዘጋጀች ቁጥር ይሄዳሉ ሥነ ሥርዓቱንም ተካፍለው ይመጣሉ፡፡ እጅግ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር እያደረጉት ካለው አደገኛና እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ሥራቸው መረዳት እንደሚቻለው ሩዋንዳ የሚመላለሱት የዘር ፍጅትን እንዴት ማነሣሣት እንደሚቻልና ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ድክመት ጥንካሬውን ተምረው በተሻለ አፈጻጸም እንዴት መከወን እንደሚችሉ ለማጥናት ይመስላል፡፡ አንድነት የነበረውን ሕዝብ እስኪበቃቸው ድረስ እየሰበኩ በዘር በሃይማኖት ከለያዩና ካራራቁ በኋላ ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት ቂምና በቀልን በመፍጠር የዘር ፍጅት ለመፍጠር አንዱን ሕዝብ በሌላው ላይ ያነሣሣሉ ይቀሰቅሳሉና፡፡
ይህ እኩይና ሳይጣናዊ ዓላማ ባይኖራቸው ኖሮ ከአንድ መንግሥት በሚጠበቅ ኃላፊነት፤ እንኳን ጠላት ለጥፋት ዓላማው የፈጠረውን ፈጠራ አንሥተው ሊቀሰቅሱ ሊያነሣሱ ይቅርና በትክክል የተፈጸመ የተደረገ ጉዳይ ቢሆንም እንኳ ጉዳዩ ሊፈጥር ከሚችለው የማይፈልግ አደገኛ አሉታዊ ውጤት አንጻር አሁን እያደረጉት ካለው ድርጊት ሁሉ በተቆጠቡ ነበር፡፡ እያደረጉት ያሉት ግን ከዚህ ፍጹም የተቃረነውን ነው፡፡ በሔጦሳና በጨለንቆ ያስገነቧቸውን ሐውልቶች ብናይ እኔ ምን ዓይነት የሞራል (የግብረ ገብ) ደረጃና ሰብእና ቢኖራቸው እንደዚያ ያለ የሚያየውን ሁሉ የሚሰቀጥጥ የሚያስደነግጥና የሚዘገንን ቅርጽና ገጽታ ያለው ሐውልት ለምን ሊያቆሙ እንደቻሉና እንደፈለጉ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ የዚያ ድርጊት ሰለባ ናቸው ለሚሏቸው ወገኖች የሕሊናና የሥነ ልቡና ጤና እና ደኅንነት እንኳን አልተጠነቀቁም አልተጨነቁም፡፡ የእነዚያ የተሠው የተባሉ ወገኖች ወገን ነኝ የሚል ሁሉ ይሄንን ሰቅጣጭ አስደንጋጭ ሐውልት ባየ ቁጥር ሕሊናው ይቆስላል ይደማል ይህ ስሜትም ወዲያውኑ የበቀል ስሜትን ይወልዳል፡፡ የሐውልቶቹ ቅርጽና ገጽታ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጥር በሚችል መልኩ የተቀረጹት ሆን ተብሎ እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ ይልቅ ይሄንን ያስገነቡ ወገኖቻች ቀና ቢያስቡ ኖሮ እንኳንና ድርጊቱ አለመፈጸሙን እያወቁ ድርጊቱ ተፈጽሟል ብለው የሚያምኑ ቢሆኑም እንኳ በሆስፒታል (ዐቢይ የህክምና ማዕከል) እና መሰል የአገልግሎት መስጫ የልማት ግንባታዎች ተገልጾ ቢሆን ኖሮ ኅብረተሰቡ በአገልግሎቱ ከመቀጠሙም ባሻገር ከእንደዚያ ያለ ሐውልቱን በመመልከት ከሚፈጠር የሥነ-ልቡናና የሕሊና ሁከት ቁስለትና ጉዳት በተገላገሉ በተረፉ ነበር፡፡
በተለይ ከነዚህ ሐውልቶች መገንባት በኋላ በየአካባቢው ያሉ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚደርስባቸው ጥቃት በዓይነትና በመጠን ጨምሯል ተባብሷል፡፡ “እንናንተ የሚኒልክ ዘሮች ናቹህ” የምትባል ቃል በመጠቀም ብቻ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቡና ጥቃት እያደረሱባቸው ለከባድ ሰቀቀን ጭንቀት እና ሥጋት እየዳረጓቸው ይገኛሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችንን ዛቻ ማስፈራሪያውን በመፍራት ወልደው የከበዱበትንና ሀገራቸውን ጥለው ለቀው ለመውጣት ተገደዋል፡፡ በብዙኃን መገኛኛዎች እንደተሰማውም በተለያዩ አካባቢዎች እዚህ ከቅርብ ስሉልታ ሳይቀር ልቀቁ እየተባልን አደጋም እየተጣለብን ነው፡፡
ወያኔ ከትናንት እስከ ዛሬ የሕዝብ (የመንግሥት) የብዙኃን መገናኛዎችን በመጠቀም ኢንተርሀምዌዮቹ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ የተለያዩ መንገዶቹን በመጠቀም ያነጣጠሩበትን ብሔረሰብ ለማስመታት በአቶ ጥልማሞት ትእዛዝ ተደርሶ በሬዲዮ ፋና (Radio Mille Collines) ይተላለፍ ከነበረው እጅግ አረመኔያዊ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሣሣ ረጅም የማፋጃ ድርሰትን ጨምሮ እስከ ትናንትናው የባህርዳሩ የመላው ኢትዮጵያ ስፖርት ውድድር እስከ ተደረገው ሴራ ድረስ የሕዝብ (የመንግሥት) የብዙኃን መገናኛዎችን በመጠቀም ለማጫረስ ለማፋጀት ያልተጣረ ጥረት የለም፡፡ በባህር ዳሩ የስፖርት ዝግጅት ላይ ወያኔ የኦሮሞ ብሔረሰብን የሚዘልፉ የሚሰድቡ ምንደኞችን አዘጋጅቶ እያስጨፈረ በማሰደብ ያንኑ ድርጊትም በኦሮሚያ ቴሌቪዥኑ (RTLMC, Radio Television Libre des Mille Collines) የቀጥታ ሥርጭት ለኦሮሞ ሕዝብ ያሳይ ነበር፡፡ የወያኔ ቅጥረኞች ይሄንን ሲያደርጉ ሥራው የወያኔ ነበርና የፌዴራል ፖሊስ አጠገባቸው ሆኖ አንዳችም ዓይነት ፍርሐትና መጨነቅ አይታይባቸውም ነበር፡፡ ፌዴራሎቹም በእነሱ ላይ አንዳችም ዓይነት የእርምት እርምጃ አልወሰዱም ነበር፡፡
እንደ የፖለቲካ ፓርቲ የገባው ንቁና ኃላፊነት የሚሰማው የፖለቲካ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ከምንም ነገር በላይ በታላቅ ንቃት እልህና ቁጭት ማስተዋልና ቁርጠኝነት ይሄንን የራሱን የተቀናበረ ሸረኛና እኩይ ሒደት ጠብቆ ዛሬ ላይ ሐውልት ግንባታ ድረስ የደረሰውን የማፋጃ፣ የማባያ፣ የማስተላላቂያ እንቅስቃሴ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍን ጨምሬ የተለያዩ የመቃወሚያ መንገዶችን በመጠቀም አሸባሪዎቹ ወያኔና አጋሮቹ ኦነግና ሻቢያ እየመረዙት ያለውን ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ እንዲደርሰው በማድረግ ሀገርንና ሕዝብን መቀመቅ ለመክተት ከሚጠነጠነው ሴራ እራሱን እንዲያርቅ እንዲጠብቅ ተባባሪ እንዳይሆን ማድረግ ማስቻልና ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም እየተሠራብን ያለውን የኢንተርሀምዌዮች እንቅስቃሴ ሴራ ማጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄንን በማድረግ ችግሩ ቢረፍድብንም ሳይመሽብን ከወዲሁ ሊቀረፉ እንዲችሉና የየዋህነት ይሁን የምን ምንነቱ በቅጡ ባልታወቀው ዝምታችን ድነገት ነገ ከተፍ ከሚልብን ከአስፈሪው አደጋ ሕዝብንና ሀገርን ይታደጉ፡፡ የተጣለባቸውን ሀገራዊና ሕዝባዊ አደራ ሳይመሽ ይወጡ፡፡ እኩዩን ሰይጣናዊ ሴራ ያክሽፉ፡፡ ይህ ኃላፊነት የእነዚህ አካላት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋም ጭምር ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ ዓመታትም በኋላ በፖለቲካ ፓርቲ (በእምነተ-አሥተዳደር ቡድን) ደረጃ ተመሥርተው ወያኔ በግላጭ በዓይናቸው ሥር እየሠራው ያለውን እኩይና ሰይጣናዊ ሴራ ማወቅ፣ መረዳት፣ መገንዘብ፣ የሚያስከትለውን አደጋ ከርቀት ማየት፣ ማሽተት ካልቻሉና እንደፖለቲካ ፓርቲ መውሰድ ያለባቸውን ተገቢና ወቅታዊ እርምጃ በሰዓቱ መውሰድ ካልቻሉ ጨርሶ ምኑም አልገባቸውምና፣ አልበሰሉምና አልነቁምና አልበቁምና ፓርቲዎቻቸውን አፈራርሰው እየቤታቸው ይቀመጡ፡፡
ወያኔ ለማንም የሀገር ልጅ በማይገባና ሊገባም በማይችል የጥፋት ዓላማ ሀገርንና ሕዝብን መርዞ ለዚህ አድርሶናል፡፡ በእርግጥ ምንጊዜም ቢሆን በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ምንም ቢደረጉ ቢመከሩ ቢዘከሩም የማይሰሙና የማይገባቸው ፈጽሞ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፀረ-ማኅበረሰባዊ ሰብእና (Anti-social personality) ያላቸው ዜጎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ሰብእና ያለባቸው ግለሰቦች “መቸም ቢጤ ከቢጤው ጋር” ነውና የሚወዳጀው አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ተሳስበው በአንድ የመቧደን ዕድል ያገኛሉ፡፡ ይህ ሰብእና ያለባቸው ቡድኖች የጠላት መጠቀሚያ ለመሆን እጅግ የተመቹ ናቸው፡፡ በሀገራችን ከዐሥርት ዓመታት ወዲህ እንዲህ ዓይነት ሰብእና ያላቸው ዜጎች የመንግሥትን ሥልጣን የመጨበጥ ዕድሉን አግኝተው ብዙ ነገሮችን እያበላሹ እያጠፉ እንዳሉ ዐይተናል እያየንም ነው፡፡ ከተበላሹትና ከጠፉት እሴት ሀብቶቻችን ብዙዎች በሚያሳዝን ሁኔታ ድጋሚ ላናገኛቸው ያጣናቸውና የምናጣቸውም ናቸው፡፡ በይነ ሕዝባዊ (ዴሞክራሲያዊ) ሥርዓት በሌለበት ሀገር እንዲህ ዓይነት ሰብእና ያላቸው ዜጎች ሥልጣን ለመጨበጥ ሰፊ ዕድል አላቸው፡፡
አንድ ሕዝብ በእነዚህ ዓይነት እኩያን ቡድኖች ላይ ነቅቶ መከላከል ካልቻለና ድርጊቶቻቸውን በዝምታ ለመመልከት ከመረጠ ሕልውናውን እስከማጣት ድረስ የሚያደርሰውን ዋጋ መክፈሉ የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህ ችግር በሀገራችን እንደመኖሩ እኛንም ዝምታችን ከባባድ ዋጋ አስከፍሎናል እያስከፈለንም ይገኛል፡፡ ዓለም እንደ አንድ መንደር መጥበቧ ታላቅ እንቅፋት ሆነባቸው እንጂ እንደ ጥንቱ እንደድሮው በአንድ ቦታ የተደረገውን በሌላው ያለው የማያውቅበት የማይሰማበት ዘመን ላይ ብንሆን ኖሮ ወያኔ በተለይም አማራን ከምድረገጽ ሳያጠፋ እንድ ምሽት ማሳለፍ ባልመረጠ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በዘመነ ሉላዊነትም (Globalization) ቢሆን ዓለም የደረሰበት ዘመናዊ አስተሳሰብ ሳያግዳቸው ለ 23 ዓመታት ጥፋት እያሴሩ ሲዳዳቸው እንዳየናቸው ዝንባሌያቸው ይሄንን ማድረግ ነው፡፡ ከዓለም ዕይታ ውጪ ሆኖ እንዴት ለማድረግ እንደሚቻል ቸገራቸው እንጂ፡፡ በጅምላ ማለቴ ነው እንጅ በተናጠል ወይም በጥቂት በጥቂቱ መመንጠሩንማ ከተያያዙት ይሄው 23ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡
የአንድ ሀገር ሕዝብ መሆናችንና አንድ የጋራ ሀገር ያለን ወንድማማች (እኅትማማች) መሆናችን ተዘንግቶ “አንተ አማራ ነህ ውጣ ልቀቅ” ከተባለ ቆንጨራ አለመጨመሩ ነው እንጅ ከሩዋንዳው የኢንተርሀምዌ ፍጅት በምን ተለየ? ለነገሩማ ቆንጨራን ከሩዋንዳ ቀድመው በበደኖ፣ በአቦምሳ፣ በአርባጉጉ፣ በወለጋ ወዘተ. የፈጁበት የእኞቹ አልነበሩም? በሩዋንዳ ያ ዘግናኝ የዘር ፍጅት ከመከሰቱ በፊት የነበረው እንቅስቃሴ ይሄው ነበር፡፡ አንድን ዘር ነጥሎ በጥላቻ በመመልከት “ሀገራችንን ልቀቁ” የሚል፡፡ ያ እልቂት በሩዋንዳ በድንገት ከመከሰቱ በፊት ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ያህል የጥላቻ ፖለቲካ ሲነዛ ከርሞ ነበር፡፡ ያሰቡትን ጥቃት ጥቃቱ የታሰበባቸውን ዘሮች ብቻ ነጥሎ ለማጥቃት እንዲያስችላቸውም መታወቂያቸው ላይ ብሔረሰባቸው እንዲሰፍር ተደርጎ ነበር፡፡ እኛንም እኮ ለዚህ ሲያመቻቹን ነው መታወቂያችን ላይ ብሔረሰባችን ከየት እንደሆነ እንዲሰፍር ማድረጋቸው፡፡ አሸባሪዎቹ ወያኔና አጋሮቹ ኦነግና ሻቢያ የቤት ሥራዎቻቸውን እንደማጠናቀቃቸው መጠን ክርስቶስ ይታደገን እንጂ ከፊታችን ባሉ ጊዜያት ቆንጨራ ላለመጨመሩ ምን ማረጋገጫ አለን?
አቶ መለስ ይሄንን ማለትም ሕዝብን በዘሩ ምክንያት እያፈናቀሉ “ውጡልን ልቀቁልን” ስለሚለው ጉዳይ ተጠይቀው ሲመልሱ “የክልሉ መንግሥት መብት ነው እንደመሰለው ማድረግ ይችላል” ብለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ አቶ መለስ አልገባቸውም እንጂ ይሄንን ሲሉ “በእርግጥ እኔ ተብሏል የሚል እምነት የለኝም ሐሰተኛ ውንጀላ ነው” ነገር ግን ወያኔ ተብሏል እያለ እንደለፈፈው ሁሉ በምርጫ 97ዓ.ም ዋዜማ ተቃዋሚዎች “እቃ ወደ ቀበሌ ትግሬ ወደ መቀሌ” ብለዋል እያለ ይከስ የነበረውን ክስ ጥፋት አይደለም ትክክለኛ አባባል ነው ብለው እያረጋገጡ ነው፡፡
ሐሰተኛ የፋሺስት ሴራ መሆኑ እየታወቀ ከግብር አባታቸው ፋሺስት ይሄንን እኩይ ሴራ በመውረስ “እንዲህ አድርገውህ ነበር” እያሉ መቀስቀስ አጸፋውን እንዲመልስ መገፋፋት ማነሣሣት የቆንጨራን መተላለቅ ለመጋበዝ ካልሆነ ፍቅርን መተሳሰብን እንድነትን ለማምጣት ለመመሥረት እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እመኑኝ እነዚህ ወገኖች እንዲህ ዓይነት እኩይ ሰይጣናዊ ሐሳብ ባይኖራቸው ኖሮ እንኳን እውነት ያልሆነውን እውነት ቢሆን ኖሮም እንኳ እያደረጉት ያለውን ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው አድራጎት በፍጹም በፍጹም ባልሞከሩት ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሴራ እንደ አያጅባጅቦ ሁሉ አመሃኝቶ ለመብላት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
መጨረሻ የሚሉት ሰዓት ሲደርስ ወይም ለእነሱ አስቸጋሪ ሆኖ የታያቸው ሰዓት ሲመጣባቸው ምንም ነገር ሳያሳስባቸው ልክ የተቀበረን ፈንጂ አንዲት ቁልፍ በመጫን ማፈንዳት እንደሚቻል ሁሉ መቀመጫችን ላይ የቀበሩብንን ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ፈንጅ ስስ ብልቱ የት እንደሆነ በሚገባ እንደማወቃቸው መጠን የሆነ ቦታ አንዲት ነገር በማድረግ ብቻ አፈንድተው ሊያባሉን ሊያፋጁን ሊያጫርሱን በሚችሉበት ሁኔታ አመቻችተው አስቀምጠውናል፡፡ ወገን ሆይ! እባክህ ይሄንን የተሸረበብህን የተተበተበብህን የተጠነሰሰብህን የተቆመረብህን የእልቂት ሴራ ጠንቅቀህ ዐውቀህ የትም ቦታ፣ መችም ቢሆን፣ ምንም ቢፈጠር የሕዝብ ደም የተጠሙ አጋንንትን ነቅቸብሀለሁ “እንቢ” በማለት ተፋቅረህ ተዋደህ ተከባብረህ ጠላትህን አሳፍር፡፡ ከተደገሰልህ እልቂት፣ ሞት፣ ጥፋት አምልጥ ዳን፣ ሀገርን ከመፍረስ ታደግ፡፡ አምላክ ይርዳህ፡፡
ወያኔ ይሄንን ሐሰተኛ የጥፋት የፈጠራ ታሪክ አዲስ በቀረጸው የኢትዮጵያ ታሪክ የትምህርት ዓይነት እንዳካተተው ይነገራል፡፡ እርግጡን ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የምንረዳው ይሆናል፡፡ አገዛዙ ካለውና ከምናውቀው እኩይ ዓላማው እንጻር ስናየው ግን ይሄን አይደለም ከዚህም የከፋ ሊያደርግ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡
ሌላው አበክሬ ማስገንዘብ የምሻው ነገር ቢኖር የምዕራቡ ዓለም መንግሥታትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች “ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ጀርባ ማን ነበረ” የሚለውን ለጊዜው እንተወውና በሰው ልጆች ታሪክ “እጅግ ዘግናኙና ተወዳዳሪ የሌለው የዘር ማጥፋት” በመባል የሚታወቀውን የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት እንዳይከሰት ማድረግ እየቻሉ በመዘናጋታቸው ይህ በመሆኑ እየተጸጸቱ ያ የዘር ፍጅት በየዓመቱ በታሰበ ቁጥር በሚያወጧቸው መግለጫዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ወንጀልና የወንጀል ሰለባዎች (victims) ያላቸው የያገባኛል መንፈስ (concern) ይሄንን ያህል ከሆነ ወያኔ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ምን ለማድረግ ምን እየሠራ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉና ያለፈው ስሕተታቸው እንዳይደገም ምን እያደረጉ ነው? የወያኔን እኩይ ሴራ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም፡፡ አይደለምና ይሄንን ያህል ግዙፍ ጉዳይ የዕለት ተዕለት ጥቃቅን ጉዳዮቻችን እንኳን ከእኛ ቀድመው በወቅቱ በሰዓቱ ዐውቀው ለእኛም ሳይቀር የሚያሳውቁን እነሱው ናቸውና፡፡
ታዲያ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ዝምታው ለምንና ምንስ እስኪሆን ድረስ ነው? በዚህ ኃላፊነት የጎደለው ዝምታና ዳተኝነት በሚፈጠር ችግር ዳግም እንደገና “በመዘናጋታችን እንዳይከሰት ልናደርግ እንችል የነበረው ችግር በመከሰቱ እናዝናለን እንጸጸታለንም” እያላቹህ የአዞ እንባ በማንባት እንድታላዝኑልን ከቶውንም አንሻም፡፡ ኃላፊነታቹህንና ግዴታቹህን መወጣት ካለባቹህ በቋፍ ካለ አደጋ ላይ ነንና ነገ ሳይሆን ዛሬ ከዛሬም አሁን ድረሱልን፡፡ ታሪክና አጋጣሚ የጣለባቹህን ኃላፊነት ሳትወጡ ቀርታቹህ በምትደጉሙትና በምትረዱት በምትደግፉት “መንግሥት” ለሚፈጠረውና ለሚፈጸምብን አደጋና ችግር ሁሉ ሙሉ ኃላፊነትን ትወስዳላቹህ፡፡ በውጪ የምትኖሩ ዜጎቻችን ሁሉ ሳትዘገዩ ይሄንን ጉዳይ በሰላማዊ ሰልፎችና በተለያዩ መንገዶች ለሚመለከተው ሁሉ እንድታስገነዝቡ አበክሬ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ይህ የታፈነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
aradaw says
“ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ጀርባ ማን ነበረ” የሚለውን ለጊዜው እንተወውና በሰው ልጆች ታሪክ “እጅግ ዘግናኙና ተወዳዳሪ የሌለው የዘር ማጥፋት” በመባል የሚታወቀውን የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት እንዳይከሰት ማድረግ እየቻሉ በመዘናጋታቸው ይህ በመሆኑ እየተጸጸቱ ያ የዘር ፍጅት በየዓመቱ በታሰበ ቁጥር በሚያወጧቸው መግለጫዎች ያረጋግጣሉ፡፡ It is nice to hear that you recognize the Ruwanda’s massacare but in your article “ዝምታሽ አልበዛም ኢትዮጵያዬ?, you clearly said “ለመንግሥት አንገብርም በማለታቸው እንደነበር ሳያፍሩ ይናገራሉ፡፡ ይባስ ብለውም መሥዋዕትነት የከፈሉ ወገኖች ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡ ይታያቹህ ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች የአንድነት እንቅፋቶች ሆነው እያለ መሥዋዕትነት የከፈሉ ይሏቸዋል፡ You said shamelessly ” ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች ” Who are you? What type of person are you? What is the difference between you and the Perpetrators’ and killers of Ruwanda who massacred thousands of people. Their justification is no different than yours , who said “ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች “,. The Rwandas’ killers used the same thing the enemies of Rwandans when they committed this atrocious crime. Please stop spreading hatred and bigotry.