መንታ መንገድ – የኢህአዴግና የአሜሪካ ወዳጅነት ወዴት?

ቻይና ኢህአዴግን ትታደጋለች? ወይስ ኢህአዴግ ይታዘዛል?

አሜሪካኖች ነጻ እንድታወጡን አንጠይቃችሁም። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ያውቃል። እናንተ ግን በነጻነት መንገዱን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑበት … ዶናልድ ያማሞቶ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ነች ብለኸን ነበር መቼ ነው መንገዱን የምናቋርጠው? ከመንገዱ ላይ ገለል በሉልንአቶ ኦባንግ ሜቶ

እንዴት እዚህ ተደረሰ?

የኢህአዴግን የአገዛዝ ዘመን ተቃዋሚዎችን አጃቢ አድርጎ የህግ ሽፋን በመስጠት የሚያራዝመው ዋና ተቋም ምርጫ ቦርድ፣ የፕሬስ ነጻነት፣ የመናገርና የመሰብሰብ ነጻነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሕግን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነት፤ ወዘተ በኢትዮጵያ ነጻ ከሆኑ ኢህአዴግ ከፊትለፊቱ ካለው ምርጫ የመዝለል አቅም እንደሌለው ይታመናል። ስለዚህም እነዚህን ጉዳዮች ለድርድር አያቀርባቸውም። ኢህአዴግ ከጅምሩ በህዝብ የማይታመነውና እውቅና የሚነፈገው ራሱን በነጻ አውጪ ስም (ህወሃት) የሰየመ መንግስት ስለሆነ ነው። ነጻ አውጪ እየተባለ አገር መምራቱም አቅዶ፤ ተልሞና መድረሻውን አስልቶ የሚጓዝ ስለመሆኑ ያሳብቅበታል። ለዚህም ይመስላል ስርዓቱ በሙስና የሸተተ፣ በግፍ የገለማ፣ የሚመራውን ህዝብ የሚገል፣ የሚያስር፣ የሚያሰቃ፣ መንግስት ሆኖ የሚሰርቅ፣ ብሔራዊ ክብርን የሚጠላ፣ ህብረትንና አንድነትን የሚጠየፍ፣ ጎሳና ጠባብ አመለካከት ላይ የተቀረጸ፣ በተራና በወረደ ተግባሩ ለመንግስትነት የማይመጥን መሆኑን የተረዱት አጋሮቹ አሁን ያመረሩበት ደረጃ ስለመዳረሳቸው ምልክቶች እንዳሉ አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል ተናግረው ነበር።

ኢህአዴግ ከአሜሪካ ጋር የመሰረተው ግንኙነት ከቶውንም ንፋስ እንደማይገባው ተከታዮቹ ሙሉ በሙሉ ያምናሉ። በተለይም የህወሃት ሰዎች አሜሪካ ከህወሃት ጋር ያሰረችው ቀለበት የሚወይብ አይመስላቸውም። የአሜሪካና የ”ህወሃት ፍቅር” ትምክህት የሆነባቸው የአሜሪካን ባለስልጣናት ህወሃት ኢትዮጵያን እስከ ዘላለም እንዲመራ ልዩ ቅባት እንደቀቡት የሚናገሩም አሉ። አሜሪካ ለህወሃት/ኢህአዴግ የምትሰጠው ጭፍን ድጋፍ ሊጤን እንደሚገባው በማሳሰብ ተስፋ ሳይቆርጡ የታገሉና የሚታገሉ ደግሞ ይህ ትምክህት አንድ ቀን እንደሚተነፍስ በእምነት ሲናገሩ ቆይተዋል።

ኦባንግ ሜቶ

ኦባንግ ሜቶ

ኢህአዴግን በዲፕሎማሲና በሰከነ የትግል ስልት መታገል ይበልጥ አዋጪ እንደሆነ ከሚያምኑት ወገኖች መካከል አቶ ኦባንግ ሜቶ ቅድሚያውን ይይዛሉ። አቶ ኦባንግ የሚመሩት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የሚያራምደውን እምነት አስመልክቶ “ከወረቀትና ፒቴሽን ከማስፈረም ያልዘለለ” በማለት የሚቃወሙና የሚተቹ የመኖራቸውን ያህል ልብና ቀልብ ሰብስበው የሚከተሏቸው ወገኖች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ ነው። እምነትም እየተጣለባቸው ነው።

በወገኖቻቸው ብቻ ሳይሆን በውጪው ዓለም ያላቸው ተቀባይነት፣ ብሎም አመኔታ እንዲሁ ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ ወኪል ተደርገው እየተወሰዱም ነው። አቶ ኦባንግ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ታላላቅ መድረኮች ሲሳተፉ የሚያቀርቧቸው ንግግሮችም ቀልብ የሚገዙና መልዕክታቸው የሰፋ በመሆኑ ሰፊ አድማጭ አላቸው። ሰሞኑንን በአሜሪካ ምክርቤት (ኮንግረስ) የጸደቀውን ድንገተኛ ውሳኔ አስመልከቶ “ኢህአዴግ ሳይወድ በግዱ በሩን በርግዶ ይከፍታል” ባይ ናቸው። ውሳኔውንና የውሳኔውን አካሄድ ከአነሳሱ ጀምሮ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው እንዲሁ ከመሬት ተነስታ ሳይሆን በከፍተኛ ትግል ነው። ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል የአውሮፓ አገሮችም የአሜሪካን ፈለግ እንዲከተሉ ሥራችንን አጠናክረን ጀምረናል” ብለዋል።

አዲሱ ውሳኔ ሕግ እና የኢህአዴግ ህልውና!

እያነጋገረ ያለው የእርዳታን አጠቃቀም አስመልክቶ ጥር 31 ቀን 2014 በአሜሪካን ኮንግረስ የፀደቀው አዲስ ውሳኔ ሕግ ነው። ውሳኔው አሜሪካ የምትሰጠው ርዳታ በትክክል ህዝብን ሳይጎዳ በስራ ላይ መዋሉንና አለመዋሉን እንዲቆጣጠር ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መ/ቤት (State Department) ትዕዛዝ የተላለፈበት ነው። እንግዲህ ይህ ትዕዛዝ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የሚነሱት መከራከሪያዎች በርካታ ቢሆኑም በምላስ “ነጻ ነኝ” የሚለውና በግብር “ለጌቶቹ ጥሩ ባሪያ” በመሆን 22 ዓመት የዘለቀው ኢህአዴግና ከአሜሪካ ግንኙነታቸው በነበረበት መንገድ ስለመዝለቁ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ አብዛኞች ይስማማሉ። አሜሪካ ከዚህ ውሳኔ የደረሰችው በወፍ ዘራሽ ሳይሆን በሂደት እንደሆነ በመጥቀስ አቶ ኦባንግ ሜቶ ከሚያቀርቡት ሃሳብ ጋር ይስማማሉ።

የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች መረጃ ላይ ተንተርሰው ለሚያወጡት ሪፖርት “ተራ የማበሻቀጪያና የማጣጣያ” መልስ በመስጠት፣ ሲለውም ተቃዋሚዎችን የሚደግፉና የኢህአዴግ የኢኮኖሚና የፖለቲካ እምነት /የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎዳና/ “ቅንቅን” የሆነባቸው የምዕራብ አገራት “ተላላኪ” በማስመሰል አሁን ድረስ ሲዘልፋቸው መቆየቱ አይዘነጋም። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት አሁን አዲስ ለጸደቀው የአሜሪካ ቅድመ ሁኔታ ላይ ያተኮረ የርዳታ መርሃ ግብር እነዚህ ክፍሎች በቁጥጥርና በክትትል በኩል ሪፖርታቸው ዋና ግብዓት ስለሚሆን ኢህአዴግ መንታ ፈተና ውስጥ እንደሚወድቅ ቅድመ ትንበያዎች አሉ።

በዚሁ መነሻ ኢህአዴግ የህልውናው መሰረት የሆነውን እርዳታ ለማግኘት “የፖለቲካ አመለ ሸጋ ሆኖ የዘጋቸውን በሮች ከፍቶ የሚመጣውን የህዝብ ወሳኝነት መቀበል፣ አሊያም በሂደት ሰልሎና ተሽመድምዶ መክሰም የመጨረሻው እድል ፈንታው ይሆናል” የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም።

ኢህአዴግ በመንታ መንገድ ላይ – የህጉ ተጽዕኖ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ አንጻር

ውሳኔውን ከፖለቲካው እንደምታና ከኢኮኖሚው ጣጣ ጋር በማያያዝ አስተያየት የሰጡን እንደሚሉት ከሆነ ጉዳዩ አደጋ አለው። እንደሚታወቀው የኢህአዴግ አገዛዝ ከጠቅላላው የምዕራብ መንግስታት ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ በየዓመቱ ያገኛል። ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕርዳታ ከአጠቃላይ አመታዊ በጀቱ 50% የሚሆነውን ይሸፍንለታል። ከአሜሪካን ብቻ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ በዕርዳታ መልክ ያገኛል። ይህም ከአሜሪካ የሚገኘው ርዳታ ብቻውን የበጀቱን አንድ ሶስተኛውን ይሸፍንለታል።

በዚህ መነሻ የኮንግረሱ ውሳኔ በኢህአዴግ አገዛዝ ላይ ያልጠበቀው ዱብ ዕዳ እንደሆነ በጀርመን የልማት ኢኮኖሚክስ ባለሙያው (Development Economist) ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ ይናገራሉ። ይህ እሳቸው “ዱብዕዳ” ያሉት ውሳኔ የፖለቲካ ውዝግብ ማስነሳቱ የማይካድ ነው። ኢህአዴግ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የሚያገኘውን ድጎማና ርዳታ ለምን ተግባር ሲያውለው እንደነበር ከማንም በላይ ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ከቅድመ ሁኔታ ጋር የተያያዘ የዕርዳታ አሰጣጥ ከኢኮኖሚ ይልቅ የፖለቲካና የስነልቦናው ተፅዕኖው እንደሚያስከትልበት እኚሁ ምሁር ያስረዳሉ።

ከአጠቃላዩ የማክሮ ኢኮኖሚ አንጻር ውሳኔው ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ በዝርዝር በማስቀመጥ አስቀድሞ መናገር ባይቻልም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል መገመት እንደማያዳግት ዶ/ር ፈቃዱ ከጎልጉል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። “ከአጭርና ከመካከለኛ ጊዜ አንፃር ስንመለከተው የአገዛዙን የኢኮኖሚ አካሄድ ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል” ያሉት ባለሙያው፣ “… ወደፊት አዳዲስ የስራ መስክ መክፈት፣ በኢኮኖሚው ዕድገት፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና በውጭ ሚዛን ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተፆዕኖም ቢሆን ይህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ይሁንና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እርስ በርሱ የተያያዘ ስላልሆነና፣ አብዛኛው ህዝብም በኢንፎርማልና ከእጅ ወደ አፍ በሚገኝ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚተዳደርና የሚሳተፍ ስለሆነ ሊጎዳ የሚችለው በዘመናዊ መስክ የተሰማራውን ሰራተኛና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ነው” በማለት ቅድመ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ሲያብራሩም ከቅድመ-ሁኔታና ከጥብቅ ቁጥጥር ጋር የተያያዘ በዕድገት ስም የሚፈስ ዕርዳታ በአጠቃላይ ሲታይ በህዝቡ ኑሮ መዛነፍ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ዝቅተኛ መሆኑንን የሚያመለክቱት ዶ/ር ፈቃዱ፣ ከ10-11በመቶ “ያለማቋረጥ” አደገ በሚባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ መሻሻል ጋር ተያያዥነት እንደሌለው ይናገራሉ። ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠለት እርዳታ  ቢቀነስ ወይም እንዳለ ቢታገድ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በቁርጥ ማስቀመጥ እንደሚያዳግትም ባለሙያው ይጠቁማሉ።  በዚህ ዓይነቱ የዕርዳታ አካሄድ እስካሁን የተጎዳው ህዝብ በመሆኑ የዕርዳታው መቀነስ ወይም መታገድ አገዛዙን እንጂ በዚያ አካባቢ የሚኖረውን ህዝብ በቀጥታ የሚመለከት አይሆንም። በህዝብ ኑሮ ላይ የሚከተለውን ማህበራዊ ኪሳራ ተምኖ ማስቀመት ቢችግርም “ወያኔ ቅድመ ሁኔታውን  ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ በተለይም በቀጥታ በኗሪው ህዝብ ህይወት ላይ አዎንታዊ ውጤት ማሳየቱ ግን የማይቀር ነገር ነው” ሲሉ ግርድፍ ምልከታቸውን ያኖራሉ። በሴፍቲኔት፣ በአነስተኛና ጥቃቅን፣ ወዘተ የህዝቡን ኑሮ እየቀየርኩ ነው የሚለው “ልማታዊው” ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት በቅድመ ሁኔታ የተወጠረ ዕርዳታ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ቀውስ ያመጣል በማለት የራሱን ቅንብር እንደሚሰራ የሚከራከሩም አሉ፡፡

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

ፖለቲካዊ ይዘቱን የዳሰሱት ዶ/ር ፈቃዱ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን በመጠቆም ለውይይት የሚጋብዝ ፍንጭ ሰጥተዋል። “ውሳኔ ሕጉ ያካተታቸው ቅድመ ሁኔታዎች ከረዥሙ አጠቃላዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር ስናየው ግን በዕውነቱ እንደዚህ ዓይነቱ ከቅድመ-ሁኔታ ጋር የተያያዘ ዕርዳታ ላይጎዳው ይችላል። አገዛዙ ከምዕራቡ አገራት የሚመጣበትን ግፊት የሚቋቋም መስሎት የሚታየው ከሆነ ፊቱን ወደ ቻይናና ወደ ሌሎች ቅድመ ሁኔታን ከማያሰቀድሙ አገሮች ዕርዳታ በማግኘት ከአሜሪካን የሚሰጠውን ዕርዳታ ሊያካክስና በነበረበት ሁኔታ ለመቀጠል መንፈራገጡ” አንደማይቀርም አመላክተዋል። ይህ ግምታቸው ግን ጥርጣሬያቸው እንዳለ ሆኖ ነው።

“ኢትዮጵያ ካለችበት የጂኦ ፖለቲካ፣ የአፍሪካ ህብረት ዕምብርትና መቀመጫም ስለሆነች ቻይናዎች ከራሳቸው የንግድ መርህ አንጻር ዕርዳታውን ከመስጠት ወደኋላ ሊሉ አይችሉም” ሲሉ የጉዳዩን ሌላ መልክ ያሳዩት ዶ/ር ፈቃዱ፣ አማራጩ ከአሜሪካንም ሆነ ከተቀረው የምዕራቡ ዓለም ጋር ተላትሞ ወደ ቻይና ፊትን በማዞር የሚደመደም ከሆነ አገዛዙ ዕድሜውን ለማሳጠር ራሱ እንደወሰነ የሚቆጠርበት ይሆናል። ኢህአዴግ አምርሮና የመጣው ይምጣ በሚል ቅድመ ሁኔታዎችን አላሟላም፣ ዕርዳታችሁንም አንፈልግም የሚል ከሆነ አሜሪካን አማራጭ ለመፈለግ ልትሞክርና ይህንንም እንደማስፈራሪያ ተጠቅማ ልትለሳለስ” እንደምትችል ዶ/ር ፈቃዱ አመላክተዋል።

እንደወያኔ የሚታዘዝላት ድርጅትና መሪ እስካላገኘ ድረስ ኢህአዴግ ላይ አደጋ እንዲነግስ ወይም ከነጭራሹ እንዲወገድ አሜሪካ ትሰራለች ብለው እንደማያምኑም ገልጸዋል። “እንዲያውም” አሉ ዶ/ር ፈቃዱ “በኮንግረሱ የፀደቀው ህግና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) እንዲቆጣጠረው የተደረገው የዕርዳታ አሰጣጥ ዘዴ፣ የኦባማ አስተዳደር ሌላ መንገድ ፈልጎ ኮንግረሱን በማለፍ፣ በቀጥታ ከአሜሪካን የውጭ ዕርዳታ አሰጣጥ ጋር ባልተያያዘ መንገድ የኢህአዴግን አገዛዝ በተዘዋዋሪ ሊረዳበት የሚችልበት መንገድ እንደሚኖር መጠራጠር ይቻላል” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ። ገደቡ በተለይም አገዛዙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ጥበቃን፣ የፀረ-ሸበርተኝነትን፣ የድንበር ጥበቃንና እንዲሁም የመከላከያ አዛዡን ስታፍ ሰራተኞች ስለማይመለከት ተጽዕኖው በወታደሩ ላይ ዝቅ ያለ መሆኑንን አንደማሳያ ይጠቁማሉ።

ፍርድ ቤቶችን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ቁጥጥር ስር ውጭ ማድረግ፣ የሚዲያ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና የመሰብስብ ነፃነት፣ እንዲሁም ሌሎች በቅድመ ዕርዳታው መስፈርት ሆነው የተዘረዘሩትን አንኳር ጉዳዮች ኢህአዴግ አጥብቆ የሚፈራቸውና ህልውናውን አደጋ ላይ የሚጥሉት በመሆናቸው በቀላሉ ለመቀበል የሚያዳግተው መስፈርቶች እንደሆኑ ለማንም ግልጽ ነው ሲሉ ዶ/ር ፈቃዱ ተናግረዋል። ይልቁኑም “እስካሁን ድረስ ለምን ዘገዩ? የሚመለከተው አካልም ሆነ የኦባማ አስተዳደር እስካሁን ድረስ ምን አስጠበቃቸው? አሁን ምን አዲስ ነገር ታያቸው? እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሰቃይ ላይ አልነበረም ወይ? ለ22 ዓመታት የአገዛዙ የጭቆና ድርጊት ከአሜሪካ መንግስት የተሰወረ ጉዳይ ነበር ወይ? የሚሉት ጉዳዮች ሲነሱ የጸደቀውን ህግ ጉዳይ በጣም እንቆቅልሽ ያደርገዋል” በማለት ከጉዳዩ ጀርባ አንድ በጊዜ ሂደት እየጠራ የሚሄድ ጥቅል ጉዳይ ስለመኖሩ አመላካች እንደሆነ ምሁሩ ያስረዳሉ። በዚሁ መነሻ ፓለቲካዊ ትርጉሙ በቀላሉ ሊታለፍ የማይችልና ለአገዛዙ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥርበት እንደሚሆን መገመቱ ከባድ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

“በሌላ ወገን ግን ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ለሚደረገው ትግል አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለውን ያህል፣ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖም ሊኖረው ይችላል። ምናልባት አገዛዙ የተወሰኑ ነገሮችን የሚያሟላ ከሆነ ተቃዋሚው ኃይል ወደ መመቻመች /ኮምፕሮማይዝ/ ውስጥ በመግባት ለአጠቃላይ ነፃነት የሚደረገው ትግል አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነትና የብልጽግና ጉዳይ የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው በሚፈልገው አካሄድ ብቻ የሚወሰን ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ አጠቃላይ ስጋታቸው ያስቀመጡት ዶ/ር ፈቃዱ፣ አጠቃላይ ህዝቡን የሚጠቅም የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሀብት ክፍፍል፣ በተለይም የመሬት ጥያቄ፣ እስከዛሬ ድረስ የተፈጠረው አዲስ የይዞታና የህብረተሰብ ግኑኝነት፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ዲሞክራቶች በሚፈልጉት መንገድ ላይፈቱ በሚችሉበት ሁኔታ መሰናክል ይደርስበታል። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ህግ የዛሬው አገዛዝ ወደፊት በስልጣን ዙሪያ ሊኖረው የሚችለው ተሳትፎ፣ የኃይል አሰላለፍ ጉዳይና የፓለቲካው አወቃቀርና አካሄድ ጉዳይ ላይ፣ የኢኮኖሚያዊና የህብረትሰብ ግኑኝነት፣ ማለትም የሀብት ክፍፍልና አዲስ ሀብት በአዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪያ የመፍጠር ጉዳይ፣ የማህበራዊ ጥያቄ ጉዳይ፣ እነዚህና ሌሎች ለአገሪቱ የወደፊት እንደህብረተሰብ መኖርና መገንባት አንፃር በሰፊው ካልታየና ተቃዋሚ በሚባለው ጭንቅላት ውስጥ ካልተብላላ አደጋም ሊኖረው ይችላል።

በሌላ አነጋገር የዕድገታችንን ጉዞ ሊያጣምመው ይችላል። ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ህግ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ቢሟላና አገዛዙም እንደፖለቲካ ኃይል ተፎካካሪ ሆኖ የሚቆይ ከሆነ ወደፊት ለሚወሰዱ አገርን የሚጠቅሙ የዕድገት ዕርምጃዎች መሰናክል እንደሚሆን መጠርጠር ይቻላል። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ አገዛዝ ባሻገር ሊገነባው የሚችለው አዲስ ኢትዮጵያ የብዙ ዓመታት ህልም ሆኖ ሊቀር እንደሚችል የራሳቸውን አማራጭ ምልከታ አስቀምጠዋል። ሌላኛውንም መንገድ አካተዋል።

በሌላው በኩል ደግሞ ይህ ውሳኔ ህግ በገዢው መደብ ውስጥ ቅራኔን መፍጠሩ እንደማይቀር፣ ህይወታቸውን ከአሜሪካን መንግስት ጋር ያያዙ ኃይሎች፣ በተለይም ግፊቱ እየበዛ ሲሄድ ወደፊት የሚመጣባቸውን አደጋ በማጤን ውሳኔ ህጉን በከፊልም ሆነ መሉ በሙሉ ተግባራዊ እናድርግ በሚሉ (ዘመናዊ ወያኔዎች) እና ውሳኔ ህጉን አንቀበልም በሚሉ አክራሪ ኃይሎች መሀከል ፍጥጫ መፈጠሩ እንደማይቀር ዶ/ር ፈቃዱ ግምገማቸውን አኑረዋል።

ቀጥሎስ?

በጉዳዩ ዙሪያ ከጎልጉል ጋር ወደፊት ሰፊ ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፈቃዳቸውን የገለጹት አቶ ኦባንግ “እዚህ የተደረሰው በወፍ ዘራሽ ዝም ተብሎ አይደለም፤ ብዙ ተለፍቶ ነው። የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ ጥያቄ ሲቀርብላቸው አሜሪካን ምክንያት ሲያደርጉ ነበር። አሁን ሊያቀርቡ የሚችሉት አንዳችም ምክንያት የለም። አጠናክረን ስራችንን እንሰራለን። ሰክነን እንታገላለን። ኢህአዴግ ሳይወድ በግዱ በሩን ይከፍታል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከአውሮፓ አገራት ጋር አጋሮቻቸው በመሆን ስራቸውን በአዲስ መልክ እያጠናከሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ይህንን አዲስ ህገ ውሳኔ በማስረጃነትና በማቅረብ የአውሮፓ መንግሥታም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ፤ በሚሰጡት ዕርዳታም ሆነ ድጎማ ላይ ኢህአዴግን ተጠያቂ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ መርዳት ባይችሉም እንኳን ኢትዮጵያውያን ለሚያደርጉት ትግል እንቅፋት እንዳይሆኑ አበክረን እንወተውታለን ብለዋል አቶ ኦባንግ፡፡

አዲስ ስለ ጸደቀው ውሳኔ ህግ ለተጠየቁት “ብዙ ለመናገር ጊዜው ገና ነው። ኢትዮጵያዊያን በጎሳና በዘር የደም አዙሪት ውስጥ እየፈሩ እንዲኖሩ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ ግን ማክተሚያው የተቃረበ ይመስለኛል፤ ኢህአዴግ እኔ ሥልጣን ከለቀቅሁኝ በአገሪቷ ውስጥ ደም መፋሰስ ይሆናል፤ ኢንተርሃምዌ የዘር ዕልቂት ይካሄዳል፤ የአፍሪካ ቀንድም ቀውስ ውስጥ ይገባል፣ ወዘተ በማለት እየዘላበደ የተቃዋሚውን ኃይል ከማዳከም አልፎ ሕዝቡ ፍራቻ ውስጥ በማስገባት አሜን ብሎ እንዲኖር የተጠቀመበት ማደንዘዣ ኃይሉ እየደከመ መጥቷል፤ ይኽኛው የውጭው ነው” የሚል ጥቅል መልስ ሰጥተዋል።

የመንታው መንገድ መሃንዲስ – ቻይና?

ቻይና ከኢህአዴግ በተለይም ከህወሃት ከፍተኛ ሰዎች ጋር አላት ከሚባለው “የተለወሰ ሽርክና” አንጻር አሜሪካ የምትሰጠውን የበጀት ድጎማና ርዳታ በየዓመቱ እየሸፈነች ኢህአዴግን ትታደጋለች የሚለው ጉዳይ ቻይና ከምትከተለው መሰረታዊ የንግድ እምነትና አንጻር በዜሮ የሚባዛ እንደሆነ ይነገራል። ቻይና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነዳጅና ማዕድን እየተከተለች የምትገባበት ኢንቨስትመንት እያከሰራት እንደሆነ የሚናገሩ ክፍሎች ቻይና የሃይል ሚዛኑን ተመልክታ ርምጃዋን ከማስተካከል ያለፈ ስራ እንደማትሰራ ይናገራሉ።

china_africa_usበሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን ይፋ ሆኖ የሰነበተውና የቻይናን “የዓይን ቀለም” የቀየረው የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር የኢትዮጵያ ጉብኝትና የፖለቲካ መሞዳሞድ በቻይናና በኢህአዴግ መካከል የግንኙነት መሻከር እንደሚፈጥር የፖለቲካ እሳቤ አለ፡፡ ኢህአዴግ ከቻይና ታሪካዊ ጠላት ጃፓን ጋር በግልጽ ይህንን ዓይነቱን “ያደባባይ ፍቅር” ማሳየቱና የፖለቲካ ቅርጫ ውስጥ መግባቱ የምዕራቡ ወዳጅ ከሆነችው ጃፓን ጋር በመወገን በምዕራባውያን የድጎማ ዕቀባ ጭስ እንዳይታፈን መተንፈሻ እየፈለገ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሰጥቶ በመቀበል፣ አበድሮ በመውሰድና የአምባገነኖችን ህልውና ለማስጠበቅ የሚውል ቴክኖሎጂን በመገንባት አፍሪካን እያለበች ያለችው ቻይና ኢህአዴግ ከምዕራባውያን የሚያኘው እርዳታ ቢቋረጥበት ከብድር በዘለለ በየዓመቱ ሌሎቹ እንደሚያደርጉት በጀት እየደጎመች የኢህአዴግን  ነፍስ ለመጠበቅ የምትምልበት ዘመን ሊኖር እንደማይችል ከግምት በላይ የሚናገሩ ክፍሎች፣ ኢህአዴግ መለሳለስ በመሳየት ቆዳውን ሊቀይር ይችላል የሚለው እምነት አላቸው። አሜሪካ አሁን የያዘችው አቋም ከምትከተለው አዲሱ ፖሊሲዋና በሂደት የኢትዮጵያ ጉዳይ ተመርምሮ የተያዘ ስለሆነ እንደ HR2003 በውስዋስ (ሎቢ) ሊቀለበስ የሚችል እንዳልሆነ አጥብቀው ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ ዲፕሎማት ጠቅሰን ገመዱ በኢህአዴግ ላይ እየከረረ እንደሚሄድ በዘገብን ወቅት “ኢህአዴግ በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች እስር ቤቶችን እንዳይጎበኙ እንደከለከለው ማድረግ አይችልም … በደቡብ ሱዳን ያለው የፖለቲካ ቀውስ፣ በሶማሊያ ጭብጡ ያለየለት ሁከት፣ በኤርትራ ያለው የዛለ መንግስት እጣፈንታና የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ ጥቂቶች እንዲበለጽጉ ያደረገው ኢህአዴግ መጨረሻው አሜሪካንን በእጅጉ ሃሳብ ላይ ጥሏታል። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሰፋ የሄደው ቁርሾና የጥላቻ ፖለቲካ ሳይፈነዳ ኢህአዴግን ማረቅ የአሜሪካ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል። ይህንን አጀንዳ አሜሪካ በቀላሉ ተጭበርብራ የምትቆልፈው አይሆንም። ኢህአዴግ በጎሳ ደምና እኔ ከሌለሁ አገርና አፍሪካ ቀንድ ይተራመሳል በሚል የሚነግደውን ንግድ አሜሪካኖቹ ተረድተዋል ብለን ነበር፡፡ የአሜሪካው ምክርቤት እንደራ የሆኑት ክሪስ ስሚዝ “በሽብር ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ተባብሮ መስራት ህዝብን ለማፈንና ረግጦ ለመግዛት ዋስትና አይደለም” በማለት መናገራቸውን ከዲፕሎማቱ አስተያየት ጋር አክለን ነበር፡፡

አዲስ የወጣውን ውሳኔ ህግ አሜሪካ በኢህአዴግ ላይ ፊቷን እያዞረች መሆኗን ማሳያ ነው በማለት የሚወስዱ ክፍሎች ይህ ህግ ከቀድሞው HR2003 ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የዛሬ አስር ዓመት፤ HR2003 በምክር ቤት ደረጃ የእንደራሴዎችን ከፍተኛ ድጋፍ ካገኘ በኋላ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት (ሴኔት) አጽድቆት በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ የአሜሪካ ፖሊሲ እንዳይሆን በመደረጉ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች መከኑ። በወቅቱ የህጉ መርቀቅና እንዲጸድቅ የተጀመረው እንቅስቃሴ ያስበረገገው ኢህአዴግ ጡረተኛ የሴኔት አባላት ከሚመሩት ዲኤልኤ ፓይፐር ከተባለ የውስዋስ (ሎቢ) ቡድን ጋር ከፍተኛ በጀት በጅቶ ታገለ። ባፈሰሰላቸው መጠን ወትዋቾቹ ባልደረቦቻቸውን ጠመዘዙና ህጉ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው አዲስ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ህግ እንዳይሆን ተደረገ።

አሁን አዲስ የወጣው ህገ ውሳኔ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ምንም ዓይነት በገንዘብ ለኢትዮጵያ ፖሊስና የጦር ኃይል ከመለቀቁ በፊት የኢህአዴግ ሸሪክ የሆነውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መስሪያቤት ገንዘቡን ለሚፈቅደው የምክርቤት አከፋፋይ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ አካላት በነጻነት የሚሰሩ መሆናቸውን፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የሃይማኖት ነጻነት መኖሩን፣ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ጋዜጠኞች ያለ ወከባና አፈና ሊሰሩ መቻላቸውን ማረጋገጫ መስጠት አለበት፡፡ በሌላ በኩልም በሶማሊ ክልል የሰብዓዊ መብትና ግብረሰናይ ድርጅቶች በነጻነት መንቀሳቀስ መቻላቸውን፣ ለወታደርና ለፖሊስ ኃይላት ስልጠና የሚሰጠው ገንዘብ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ለሚገኙ ክፍሎች እንዳይደርስ የሚያረጋግጥ ሰነድ፣ እነዚህን መብቶች በጣሱ የሠራዊቱና የፖሊስ አባላት ላይ ምርመራ በማድረግ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ምን እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ሰነድ በማቅረብ ይሆናል፡፡

ከዚህም ሌላ “የልማት ዕርዳታ” እና “የኢኮኖሚ ድጋፍ ፈንድ” በሚል ለታችኛው ኦሞ ሸለቆና በጋምቤላ ለሚኖሩ የሚሰጠው ዕርዳታ በምንም ዓይነት መልኩ ነዋሪዎቹን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ አስገድዶ በማፈናቀል ተግባር ላይ እንዳይውል፤ የነዋሪዎቹ ህይወት በሚያሻሽል ሥራ ላይ ብቻ የሚውል መሆኑ እና ከነዋሪዎቹ ጋር በምክክር የሚደረግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ መ/ቤቱ ይህንን ሳያረጋግጥ ገንዘብ መውሰድ አይችልም፡፡ ኢህአዴግን ለመደገፍ በሚል የተዛባ መረጃ በማቅረብ ገንዘቡን ወስዶ ለኢህአዴግ እንዲደርስ ቢያደርግ እንኳን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የኢትዮጵያን ሁኔታ አስመልክቶ የሚያወጡት ዘገባ ዕውነቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያጋልጥበት ይሆናል፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር በተጨማሪ የገንዘብ ሚ/ር መ/ቤት (Department of Treasury) በኢትዮጵያ ውስጥ አስገድዶ ከመኖሪያ ቦታ ከማፈናቀል ጋር በተያያዘ ለሚደረግ እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንዳይሰጥ ለዓለምአቀፉ የፋይናንስ ተቋም ዋና ዳይሬክተር መመሪያ እንዲሰጥ ታዟል፡፡

ይህንን እና የመሳሰሉ የትም የማያፈናፍኑ መመሪያዎች ያካተተው ውሳኔ ህግ የራሱ የሆኑ ተጽዕኖዎች ያመጣል እየተባለ በሚጠበቅበት ሁኔታ ለሚከሰት ማናቸውም ዓይነት ክፍተት ቻይና ከኢኮኖሚ ጥቅሟ አኳያ ለኢህአዴግ መድህን ሆና ልትቀርብ የምትችልበት ሁኔታ በብዙዎች አንድ አመኔታ የሚጣልበት አይደለም፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ ያለው ኢህአዴግ ከመጪው ምርጫ አኳያ እንዲህ ዓይነት በቅድመ ሁኔታዎች የታጠረ ህገ ውሳኔ አክብሮ ይቀበል ይሆን? ወይስ ፊቱን በአሜሪካ ላይ በማዞር በእብሪት ቻይናን ታደጊኝ ይላታል? መንታው መንገድ በዚህ የሚያቆም አይመስልም – የራሱን መንታ መንገዶች እየከፈተ ይሄዳል የሚሉ ፍንጮችም እየታዩ ነው፡፡


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Comments

  1. oh! GOD give us our FREEDOM !

  2. Freedom is attained from struggle and hard work. Not from divine intervention . We have been stretching our hands to invisible god to do our home work on our behalf since woyane set foot as home spun colonial force. we have then waited for god to show his prowess over woyane by demolishing this brutal regime once and for all. Because woyane never believes in the existence of god. So had been engaged in act of killing millions of Ethiopians mercilesely ,robbed resources of the country .But to the disappointment of the believers , nothing came from the sky as punihsment. Rather the woyane thugs solidified its power and has continued its iron rule than ever before. so do we have to keep on praying to god or fight resolutely to wipe out these termites from the page of history? as to me i go for challenging the woyane until death than waiting god to do my home work .

  3. ደስ የሚል የአሜሪካኖች አባባል አለ (( ልታሸንፋቸው ካልቻልክ ከአሸናፊዎች ጋር ተባብረህ አሽናፊ ሁን)) ተወደደም ተጠላም ከአሜሪካ ጋር ያልወገነ መንግስት ዳገቱ ብዙ ነው

Speak Your Mind

*