• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

በሽብርተኝነት የተከሰሱ 29 ተጠርጣሪዎች በነፃ እንዲሰናበቱ ተጠየቀ

November 26, 2012 08:34 am by Editor Leave a Comment

–    የተከሰሱበት ሕግ ለትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይላክ ተባለ
–
    የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ክስ ተለይቶ እንዲቀርብ ተጠይቋል

የሽብር ድርጊቶችን በመፈጸም፣ ሕገ መንግሥቱንና መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፈራረስ ሙከራ ወንጀልና ለሽብርተኝነት ድጋፍ በመስጠት ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው 29 ግለሰቦችና ሁለት ድርጅቶች፣ የተከሰሱት ሕገ መንግሥቱን ጥሶ በወጣ ወይም በሚቃረን ሕግ በመሆኑ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠበቆቻቸው ጠየቁ፡፡ ከሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ተጠርጣሪ ወይዘሮ ሐቢባ መሐመድ መሐሙድ በስተቀር፣ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በጋራ አሥር ጠበቆችን ያቆሙ ሲሆን፣ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት የክስ መቃወሚያ ሐሳባቸውን ኅዳር 13 ቀን 2005 ዓ.ም. አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከፋፍለው የቀረቡትን አራት ክሶች በንባብ አሰምቶ እንደጨረሰ፣ የተጠርጣሪዎቹ ተከሳሾች የመጀመሪያ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል፡፡ በወንጀል ሕጉ 130 እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 መሠረት በቀረበው መቃወሚያ ላይ ጠበቆቹ እንዳብራሩት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እኩል ደረጃ ኖሯቸው አንድ አካል ተደርገው በሥራ ላይ ይውላሉ የተባሉት ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሰነዶች ናቸው፡፡ እነዚህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውስጥ ቁጥር 217ኤ (11) ላይ የፀደቀው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ እ.ኤ.አ ዲሴምበር 16 ቀን 1966 ፀድቆ እ.ኤ.አ ማርች 23 ቀን 1976 በሥራ ላይ የዋለው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳንና ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብዓዊና አዋራጅ አያያዞችንና ቅጣቶችን ለማስቀረት የተደረጉ ስምምነቶች እንደሚገኙ በተቃውሟቸው ጠቁመዋል፡፡ እንደጠበቆቹ ገለጻ፣ አዋጅ ቁጥር 652/2001 ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ይቃረናል፡፡

ጠበቆቹ አዋጅ 652/2001 እንዴት ሕገ መንግሥቱ እንደሚቃረን ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፣ በሕገ መንግሥቱ የአንድ ሰው የመኖሪያ ቤትና የግል ሕይወቱ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደማይደፈር መደንገጉን ገልጸዋል፡፡ ያለ ሕግ አግባብና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አንድ በርባሪ ፖሊስ የግለሰብ ቤት መሄድ የማይችል መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ የተጠርጣሪው ግለሰብ ቤተሰቦች ወይም አባላት ከሌሉ፣ በሕጋዊ መንገድ ለብርበራ የተሰጠውን ትዕዛዝ ትቶ እንደሚመለስ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤትም ቢሆን የብርበራ ፈቃድ ሲሰጥ የግለሰቡን የግል ሕይወት ለመድፈር የሚያስችል መብት እንደማይሰጥም ጠቁመዋል፡፡ በተቃራኒ በድብቅ መረጃ መሰብሰብን የሚፈቅደው አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 18 ሕገ መንግሥቱንና የሰውን ክብር እንደሚቃረንም አስረድተዋል፡፡

ጠበቆቹ በደንበኞቻቸው ላይ የቀረበውን ክስና የተጠቀሰባቸውን የፀረ ሽብር ሕግን፣ ከሕግ አውጭው ፓርላማ ጀምረው ይቃረናል እስካሉት ሕገ መንግሥት ድረስ እንዴት እንደሚቃረን ሲያስረዱ ከዓቃቤ ሕግና ከፍርድ ቤቱ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ በክሱ ላይ ብቻ አተኩረው መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ በተደደጋሚ ከመናገሩም በተጨማሪ፣ ዓቃቤያነ ሕጉም ከመቀመጫቸው በተደጋጋሚ በመነሳት ጠበቆቹ የሚያቀርቡት መቃወሚያ ከሕጉ ውጭ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጠበቆቹ በበኩላቸው፣ ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ ሲያቀርቡ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ለማቅረብ የሚያስችለው የሕግ ሥነ ሥርዓት ስለሌለ፣ በተደጋጋሚ እየተነሳ ተቃውሟቸውን ማስተጓጐል እንዲያቆም እንዲታዘዝላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ጠበቆቹ ክሱን የሚቃወሙበትን ሐሳብ ቀጥለው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በደንበኞቻቸው ላይ የተጠቀሰውና በዋናነት ክስ የተመሠረተበት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የማንንም ዜጋ ቤት መበርበርንና መድፈርን ብቻ ሳይሆን፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝንና ማሰርን፣ ከፍርድ በፊት ንፁህ ሆኖ የመገመትን፣ በሕግ ፊት እኩል ሆኖ የመታየት መብትን በመደምሰስ ሕገ መንግሥቱን እንደሚቃረን አስረድተዋል፡፡

ደንበኞቻቸው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተይዘው፣ ታስረውና ከሕግ አግባብ ውጭ ምርመራ ተፈጽሞባቸው፣ ከሕግ ውጭ በተገኘ ማስረጃ ተከሰው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃቸውን የሻረውና የነጠቃቸው ሕገ መንግሥቱን ጥሶ የወጣው አዋጅ ቁጥር 652/2001 ሰለባ ሆነው እንጂ፣ ምንም ያላጠፉና የተከበሩ አባቶች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና ለሁሉም ዜጋ በአርዓያነት ሊወሰዱ የሚችሎ ዜጎች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ ሕገ መንግሥቱን በመቃረኑ ተፈጻሚ ስለማይሆን ደንበኞቻቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ያነሱት ተቃውሞ፣ በተከሳሾቹ ላይ የተጠቀሰው የፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ ሦስት የሚደነግገው ፍጻሜ ስላገኘ የሽብርተኝነት ድርጊት መሆኑን ጠቁመው፣ አንቀጽ አራት ደግሞ ፍጻሜ ስላላገኙ የሽብርተኝነት ድርጊቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ደንበኞቻቸውን በአንቀጽ ሦስት የተከለከሉ የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ከሷቸው ሳለ፣ በድጋሚ አንቀጽ አራትን በመጥቀስ በአንቀጽ ሦስት የጠቀሰውን ወንጀል ለመፈጸም በማቀዳቸው፣ በማሴራቸውና በመሰናዳታቸው መከሰስ አለባቸው ማለቱ ሕጋዊ አለመሆኑንና እንደማያስኬደው አስረድተዋል፡፡ ተፈጸመ በተባለው ጉዳት በምንና በማንኛውም ሁኔታ ጉዳቱን እንዳደረሱ ባልተገለጸበት ሁኔታ አንቀጽ 32(1)ሀን መጥቀስ አግባብ ባለመሆኑ ክሱ መሰረዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ድርጊቶች ተፈጸሙ የተባለበት ቀንና የማነሳሳት ተግባር ተፈጸመ የተባለበት ጊዜ የተለያየ መሆኑን፣ በሰውና በንብረት ላይ ተፈጸመ በተባለው ወንጀል ላይ ቀጥታ ፈጻሚዎቹ እያሉ ደንበኞቻቸው አነሳስተዋል በሚል፣ የፈጸመው ማን እንደሆነ ሳይለይ ተለይቶ ባልቀረበበት ሁኔታ መከሰሳቸው አግባብ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ተከሰው በቀላል እስራት ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ፣ አነሳስተዋል የተባሉት ደንበኞቻቸውን በፀረ ሽብር ሕግ መክሰስ “ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው” የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌና በወንጀል ሕጉ ላይ “የወንጀል ሕግ ልዩነት ሳያደርግ በሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚ ይሆናል” የሚለውን ድንጋጌ በግልጽ የሚቃረን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውድቅ እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡

ጠበቆቹ በመቃወሚያቸው ያነሱት ተቃውሞ በደንበኞቻቸው ላይ የቀረበው ክስ ተነጣጥሎ እንዲቀርብላቸው ነው፡፡ በተለይ በፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 3 እና 4 የተጠቀሱት አግባብ የክስ አቀራረብን በሚመለከት የወንጀል ሕግ 116 የሚያዘውን የሚጻረሩ መሆኑን ነው፡፡ የወንጀል ድርጊት ተፈጸመበት የተባለው ቦታና ጊዜ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በክሱ ላይ ወሩ በውል ተለይቶ ካልታወቀበት 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ከማለት ውጪ መቼና በማንኛው ቀን እንደሆነ አለመጠቀሱንም ተናግረዋል፡፡ ፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የወጣው ወይም ሕግ ሆኖ የፀደቀው ነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ነው፡፡ በመሆኑም ደንበኞቻቸው ሊከሰሱ የሚገባው ሕጉ ከወጣበት ከነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ተከሳሾቹ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ክሱ በህቡዕ የተደራጁት የፀረ ሽብር ሕጉ ከመውጣቱ በፊት ወይም ከወጣ በኋላ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ለይቶ ባላወቀበት ሁኔታ የቀረበባቸው በመሆኑ፣ በወንጀል ሕጉ 111 መሠረት ክሱ ውድቅ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ ውስጥ ጅሀድ፣ የሃይማኖት አስተማሪዎች (የኡስታዞች ቡድን) የዳኢዎች ቡድን፣ አክራሪ አስተሳሰብና አስተምህሮት፣ አስተምህሮትን የሚሰብኩ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራም፣ ወዘተ የሚሉ ለ1996 የወንጀል ሕግም ሆነ ለፀረ ሽብር አዋጁ ባዕድ የሆኑ ቃላትና ሐረጐችን በክሱ አላግባብ መጠቀሙን ጠበቆቹ ጠቁመዋል፡፡ የተጠቀሱት ቃላት ሐረጐች በሕግ አነጋገሮች ውስጥ የሌሉ ብቻ ሳይሆን ቃላቱ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ በመሆናቸው ፖለቲከኞች ወይም ኢኮኖሚስቶች የሚጠቀሙባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ከፊሎቹም የዓረብኛ ቃላት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛ ክሱ ያነሳቸው የክስ ነጥቦች እርስ በርስ የሚቃረኑ ለመሆናቸውም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ተከሳሾቹ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፈራረስ ሙከራ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በመጥቀስ ክስ የመሠረተባቸው፣ በአንዋር መስጊድ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚያነሳሱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ አመኔታ የሚያሳጡ ንግግሮችና ጽሑፎችን ተጠቅመው፣ ለአመጽና ለሽብር ተግባር በማዘጋጀት ረብሻ አነሳስተዋል መባሉ እውነት ሆኖ ቢገኝ እንኳ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን እንጂ ወንጀል መፈጸም አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንድን ሐሳብ የመያዝ ነፃነትን ቀርቶ መገለጹ እንኳን ገና ለገና የሚያመጣውን አደጋ መሠረት አድርጐ ሊገደብ እንደማይችል ወይም አይገደብም የሚለውን ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 የሰጠውን መብት የጣሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሌላው ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ያደመጠው የክስ መቃወሚያ፣ ለብቻቸው ጠበቃ ያቆሙትን የሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወይዘሮ ሐቢባ መሐመድ መሐሙድን የክስ መቃወሚያ ነው፡፡ ወይዘሮ ሐቢባ በኦሮሚያ ክልል አስፋፍተዋል የተባለው አክራሪነት ምን ማለት እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ በግልጽ አለማስረዳቱን፣ ከ28ቱ ተጠርጣሪዎች ጋር አብረው መከሰስ እንደሌለባቸውና ክሳቸውም ለብቻው ተነጥሎ እንዲቀርብ ጠበቃቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

ወይዘሮ ሐቢባ በኦሮሚያ ክልል አሠሩ የተባሉትን መስጅድ የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የሚያውቀውና ፈቃድ ያለው መሆኑን፣ ለሰደቃ የሚሆን ቁሳቁስ ይዘው ተገኝተዋል የተባለው ዓይነቱ እንዳልተጠቀሰና እሳቸውም ለሰደቃ የሚሆን ቁሳቁስ ይዘው አለመገኘታቸውን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ያደመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት፣ ዓቃቢያነ ሕጉ በተቃውሞው ላይ ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡ ዓቃቢያነ ሕጉ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ሰፊ በመሆኑ ጊዜ ተሰጥቷቸው አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ጠበቆቹ ግን “ሕጉ የሚለው የክስ መቃወሚያ እንደቀረበ ወዲያውኑ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት ይሰጣል ነው፡፡ በመሆኑም አሁኑኑ ምላሽ ወይም አስተያየት እንዲሰጥ ይታዘዝልን፤” በማለት በዓቃቤ ሕግ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከተመካከረ በኋላ የክስ መቃወሚያ እንዳቀረበ ዓቃቤ ሕግ ወዲያውኑ አስተያየቱን ይስጥ የሚል የሕግ ሥነ ሥርዓት አለመኖሩን በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ ለኅዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም. አስተያየቱን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ችሎቱን አጠናቋል፡፡

በዕለቱ በነበረው ችሎት ከአንዳንድ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በስተቀር፣ የተከሳሾች ቤተሰቦችም ሆኑ ሌሎች ታዳሚዎች አልተገኙም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ችሎቱ ሞልቷል በመባሉ ነው፡፡ በዕለቱ ከፍርድ ቤቱ አጥር ውጭ በርካታ ሰዎች የተሰባሰቡ ቢሆንም ወደ ውስጥ መግባት አልቻሉም፡፡

ሙሉ ዘገባው የሪፖርተር ጋዜጣ ሲሆን ዘጋቢው ታምሩ ጽጌ ነው።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Law Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የሲኖዶሱ ውዝግብ አካሄድና መጪው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ February 6, 2023 02:03 am
  • የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ተራዘመ፤ ተጠባቂው ዕርቅ ፍንጭ እያሳየ ነው February 3, 2023 05:17 pm
  • የብላቴ: የውጊያ ማርሽ ቀያሪ ሠራዊት መፍለቂያ ማዕከል February 3, 2023 10:06 am
  • በኢትዮጵያ 27 በመቶ የሚሆነው የአእምሮ በሽተኛ ነው ተባለ February 3, 2023 09:47 am
  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule