“ያለመከሰስ መብቴ አልተነሳም መንግሥት የሚያውቀው ሕመም አለብኝ” አቶ መላኩ ፈንታ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር
“እኔ በተጠረጠርኩበት ወንጀል ልጠየቅ ቤተሰቦቼን ግን ለምን? ምን ዓይነት አገር እየሆንን ነው?” አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር
“ታዋቂ ግብር ከፋይና ታዋቂ ስለሆንኩ በዋስ ልለቀቅ” አቶ ከተማ ከበደ፣ የኬኬ ድርጅት ባለቤት
“የዋስ መብቴ ተጠብቆ ሥራዬን ላስተካክል ለሠራተኞቼ ደመወዝ ልክፈል” አቶ ስማቸው ከበደ፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት
ቀረጥና ታክስ በማጭበርበር፣ አራጣ በማበደርና በመመሳጠር ሕገወጥ ዕቃዎች እንዲያልፉ ያደረጉ ተጠርጣሪዎችን ክስ በማቋረጥ፣ የተከለከለ ሲሚንቶ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባና ሕገወጥ ዕቃዎች ያለፍተሻ እንዲያልፉ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ፖሊሶችና በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቡድን በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነ አቶ መላኩ ፈንታ፣ ሰኞና ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት ጀመረ፡፡
በፌዴራል ፖሊስና በኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊሶች ታጅበው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች፣ በእነ አቶ መላኩ የምርመራ መዝገብ ሰባት፣ በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የምርመራ መዝገብ 11 እና በእነ መሐመድ ኢሳ መዝገብ ስድስት ናቸው፡፡
ባለፈው ሰኞ 24ቱም ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ ከኮሚሽኑ መርማሪዎች ጋር ስለተጠረጠሩበት ጉዳይና በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በእሥር ቤት ደረሰብን ስላሉት ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥሰት የተከራከሩትና ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት፣ በሚኒስትርነት ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ የዓቃቢያነ ሕግ ዋና ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ወልደሰማያት፣ ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ አቶ መርክነህ አለማየሁ፣ የቃሊቲ ጉምሩክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስመላሽ ወልደማርያም፣ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ፣ በኢትዮጵያና በውጭ አገሮች የሕክምና ሥራ እንደሚሠሩ የተናገሩት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ፣ የኮሚሽኑ መርማሪዎች ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርቡት አቤቱታ ለተጠርጣሪዎቹ እንዳልደረሳቸው በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎቹ በምን ሁኔታ፣ ለምን፣ መቼ እንደተያዙና በዕለቱ ምን ሊደረግላቸው እንደፈለጉ ለችሎቱ እንዲያስረዱ ጠየቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ መንግሥት የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጐን በመተውና ሥልጣናቸውን በመጠቀም፣ እነሱም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር፣ በቀረጥና ታክስ ማጭበርበርና አራጣ የማበደር ክስና የተከለከለን ሲሚንቶ በሕገወጥ መንገድ በማስገባት ወንጀል የተመሠረተን ክስ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. መሆኑን፣ ቢሮአቸውና ቤታቸው መበርበሩን፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉትና ቤታቸውና ቢሮአቸው የተበረበረው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑን መርማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ የተጠረጠሩበትን ወንጀል በማስረዳት ቃላቸውን መቀበል መጀመራቸውን ተናግረው፣ የተጠርጣሪዎቹን ቀሪ ቃል መቀበል፣ የምስክሮችን ቃል መቀበልና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ሥራ ስለሚቀራቸው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድላቸው መርማሪዎቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት እስከቀረቡበት ዕለት ድረስ የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊሶች የሠሩትን የምርመራ ሥራ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ተቀብሎ ከተመለከተ በኋላ፣ ተጠርጣሪዎቹ ስተለጠረጠሩበት ጉዳይና በቁጥጥር ሥር ስላሉበት ሁኔታ እንዲያስረዱ ፍርድ ቤቱ የመጀመሪያውን ዕድል ለአቶ መላኩ ፈንታ ሰጥቷል፡፡
በጠበቃ የተወከሉት አቶ መላኩ የተጠየቀባቸውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በሚመለከት ጠበቃቸው እንዳስረዱት፣ አቶ መላኩ በተገኙበትና ምስክሮች ባሉበት ቢሮአቸው ለሁለት ቀናት ተበርብሮ ታሽጓል፡፡ እሳቸው ተፈጸመ ስለተባለው ነገር የሚያውቁት ጉዳይ የለም፡፡ ፖሊስ የሚፈልገውን ነገር ከወሰደ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ አያስፈልገውም፡፡ አቶ መላኩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን የተናገሩት ጠበቃው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር 361/95 ቁጥር 12(4) መሠረት ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙና ምክር ቤቱ በራሱ ጊዜ ያለመከሰስ መብታቸውን ካላነሳው በስተቀር ያለመከሰስ መብት ያላቸው ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተጥሶ መታሰራቸው አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የአቶ መላኩ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ በተጨማሪነት ያስረዱት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(2) ማንኛውም ተጠርጥሮ በሕግ ጥላ ሥር ያለ ሰው ከትዳር ጓደኛው፣ ከቅርብ ዘመዶቹ፣ ከጓደኞቹ፣ ከሃይማኖት አማካሪው፣ ከሐኪሙና ከሕግ አማካሪው ጋር የመገናኘትና የመጐብኘት መብት የተሰጠ ቢሆንም፣ አቶ መላኩ ይህንን መብታቸውን መነፈጋቸውን በማስረዳት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ መላኩ መንግሥት የሚያውቀው ሕመም እንዳለባቸውና በቅርቡ ሕክምና ቢያደርጉም አለመዳናቸውን፣ አሁን ያሉበት ሁኔታ ስሜቱና ሕመሙ ለከፋ ችግር ሊዳርጋቸው ስለሚችል ደህና ሐኪም ቤት ወይም ባሉበት ቦታ ሐኪም መጥቶ እንዲታዩ እንዲታዘዝላቸው ጠበቃው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁም አግባብ አለመሆኑን አክለዋል፡፡
ከአቶ መላኩ በመቀጠል የተናገሩት የዓቃቢያነ ሕግ ዋና ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ወልደሰማያት ሲሆኑ፣ በፍርድ ቤት መያዣ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ዕለት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ቢሮአቸው መበርበሩንና በዕለቱ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተወስደው እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት መኖሪያ ቤታቸው መበርበሩን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከሰነድ ጋር የተያያዘ ከሆነ ከዚያ በላይ ሊኖር ስለማይችል ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አስፈላጊ ስላልሆነ ዋስትና ተከብሮላቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ሕክምና ሲከታተሉ ከርመው ወደ አገር ቤት ከተመለሱ ገና አንድ ሳምንታቸው መሆኑን በመግለጽ፣ እሳቸውም እንደ አቶ መላኩ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(2) እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ለፍርድ ቤት ማስረዳት የጀመሩት አቶ መርክነህ አለማየሁ ናቸው፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሁለትና ሦስት ጊዜ የተላለፈው መግለጫ ይታይልን፣ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን አገኘሁት ባለው መግለጫው ኮሚሽኑ ለወራት ባካሄደው ጥናትና ክትትል በቂ የሰነድና የሰው ማስረጃ ካሰባሰበ በኋላ፣ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል ብሏል፡፡ ታዲያ አሁን 14 ቀናት ወስዶ ሰነድና የሰው ማስረጃ የፈለገው ለምንድነው? ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን መግለጫ አስቀርቦ ይመልከትልን፤” ብለዋል፡፡ አቶ መርክነህ ከተያዙ በኋላ በቢሮአቸውም ሆነ በቤታቸውም ብርበራ መደረጉን ተናግረው ኮሚሽኑ አስሮ ለማቆየት ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ እንደሌለው፣ እሳቸው ዓይነ ስውር በመሆናቸው ዓይነ ስውርነት የመጨረሻው ገደብና ተፈጥሮአዊ እስር ቤት በመሆኑ አስሮ ማጣራት ተገቢ ባለመሆኑ በዋስ እንዲለቃቸው ጠይቀዋል፡፡ እስር አስፈላጊ የሚሆንበት ልዩ ልዩ ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት አቶ መርክነህ፣ እሳቸው ግን እያንዳንዷን ዕርምጃ የሚንቀሳቀሱት በሰው ተመርተው መሆኑን፣ አሁን የታሰሩበት ጣቢያ ፎቅ በመሆኑ ሲወጡና ሲወርዱ በንብርክካቸው መሆኑን በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲጠብቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስላለባቸው በየአሥር ደቂቃው ወደ መፀዳጃ ቤት ሲመላለሱ እስረኛም ሊሰለቻቸው ስለሚችልና በራሳቸው ለመሄድ ሲሞክሩ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ሊገቡ እንደነበርም አክለዋል፡፡ የቅርብ ክትትልና የሕግ ሰው እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ፣ መታሰራቸው ግድ ከሆነ የጠየቁት ሊሟላላቸው ስለሚገባ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውና ወይም በገደብ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ በሰንሰለት ያላሰሯቸውን የኮሚሽኑ መርማሪዎችንም አመስግነዋል፡፡
አቶ አስመላሽ ወልደማርያም የአቶ እሸቱ ቃል እንዲመዘገብላቸው በማመልከት ክርክሩን በአጭሩ አቁመዋል፡፡
የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ በጠበቃ የተወከሉ ሲሆን፣ አቶ መርክነህ በኢቲቪ ላይ ያነሱትን ጥያቄ በድጋሚ አንስተዋል፡፡ በመግለጫው ከመንግሥት በላይ ታማኝ እንደሌለ በማከል አላስፈላጊ እስር ያለፍርድ መቅጣት ስለሚሆን፣ ደንበኛቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ጠበቃው አቶ መላኩ የጠየቁት ሕገ መንግሥታዊ መብት ለእሳቸውም ደንበኛ ተፈጻሚ እንዲሆን ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪዎች ለሦስት ቀናት የሚፈልጉትን ሰነድ በርብረው ከወሰዱ በኋላ ድርጅቱን አሽገው በመሄዳቸው፣ ከ600 በላይ ሠራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው አደጋ እያንዣበበባቸው በመሆኑ ድርጅቱ እንዲከፈት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ የሰው ምስክርና ተጨማሪ የሰነድ ፍለጋ ከእሳቸው ጋር ስለማይገናኝ በዋስ ቢለቀቁ፣ ከፍተኛ ግብር ከፋይና ታዋቂ በመሆናቸው ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለም አስረድተዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኀን በፍርድ ሒደቱም ላይ ይሁን በደንበኛቸው ሰብዕና ላይ ተፅዕኖ ስለሚፈጥሩ፣ ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳይሰጥ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ስማቸው ከበደ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት ምርመራ ጊዜ እንደሚቃወሙ ገልጸው፣ ቤታቸውና ቢሮአቸው ከሦስት ጊዜ በላይ መበርበሩንና የልጆቻቸው የትምህርት ቤት መገልገያ ሳይቀር መፈተሹን አክለዋል፡፡ የኮንስትራክሽንና የሆቴል ሠራተኞች ደመወዛቸው ስላልተከፈላቸው መቸገራቸውን ተናግረው፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸውና ሠራተኞቻቸውን እንዲያስተካክሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የ40 ዓመት ጐልማሳ መሆናቸውንና የሚኖሩት በውጭ አገር መሆኑን ገልጸው፣ ሥራቸው ሕክምና መሆኑን፣ በኢትዮጵያና በውጭ አገር ታካሚዎች እንዳሏቸው በማስረዳት ስለተከሰሱበት ጉዳይ ምንም እንዳልተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ግንቦት 5 ቀን (ፍርድ ቤት የቀረቡበት ቀን) 2005 ዓ.ም. ወደ ውጭ ይሄዱ እንደነበር ተናግረው፣ የሚያክሟቸው ሕሙማን በውጭና በአገር ቤትም ስላሉ እንዲያሳውቋቸው እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
መርማሪዎቹ በዋናነት በተጠርጣሪዎቹ የተነሱት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(2) መብት እንዲከበርላቸውና ሌሎችም ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ ስላነሱት ያለመከሰስ መብት በወቅቱ ስላልነገሯቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በመገናኛ ብዙኀን የተገለጸው ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ስለሚበቃ ማስረጃ እንጂ፣ በምርመራው ከተጠርጣሪዎቹ ቃል መቀበል፣ ሰነድና የሰው ምስክሮች መሰብሰብ እንደሚቀራቸው ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ባለሥልጣንና ባለሀብት ስለሆኑ በዋስ ቢወጡ ባላቸው ተሰሚነትና ግንኙነት ተጠቅመው ምስክሮችን ሊያባብሉና ሰነድ ሊያጠፉ ስለሚችሉ የዋስትና መብት መፈቀዱን እንደሚቃወሙ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ቤተሰብ ያልጐበኛቸውና የሕግ አማካሪና ሌላም የጠቀሱት ነገር ያልተደረገላቸው፣ የተያዙት ዓርብ ዕለት በመሆኑ ቀጣይ ቀናት ቅዳሜና ዕሑድ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በምርመራና ብርበራ ላይ ስለነበሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕክምናን በሚመለከት በማዕከላዊ አሁን በታሰሩበት ቦታ በቂ ሕክምና እንዳለ፣ ከዚያ ካለፈም ፖሊስ ሆስፒታል ስላለ ወደዚያ ሊወስዷቸው እንደሚችሉ አውስተዋል፡፡ አቶ መርክነህን በሚመለከት መንግሥት ያቀረበው ማረፊያ ቤት በመሆኑ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ፣ መፀዳጃ ቤቱ ግን ደረጃውን የጠበቀና ንፁህ መሆኑ አስረድተዋል፡፡ ሰው መድበው እየተንከባከቧቸው መሆኑን ተናግረው ከዚያ ባለፈ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ስለታካሚዎቻቸው በውጭ ያሉ ዶክተሮችና በአገር ውስጥ ያሉትንም እንዲያነጋግሩ እንደሚያመቻቹላቸው ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ “ወንጀሎች የማን ሥልጣን ናቸው? ያለመከሰስ መብት ለማነው የሚሰጠው? ከየት ለማን? እንዴት ነው የሚሰጠው?” በሚለውና ተርጣሪዎቹ የጠየቋቸውን የመብት ጥያቄዎች እንዲሁም መርማሪ ፖሊሶች ባነሱት የመቃወሚያ ሐሳብ ላይ ብይን ለመስማት ለማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የአዳር ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ በሁለተኛ የምርመራ መዝገብ የቀረቡት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሕግ ማስከበር ኃላፊ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ባለቤታቸው ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ፣ የባለቤታቸው እህት ወ/ሮ ንግስቲ ተስፋይ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ጥሩነህ በርታ፣ አቶ ተስፋዬ አበበ፣ አቶ ነጋ ገብረእግዝአብሔር፣ አቶ ሙሌ ጋሻው፣ አቶ አሞኘ አወቀ፣ አቶ ሀብቶም ገብረመድህንና አቶ ምህረተአብ አብርሃ ሲሆኑ፣ ቀኑ በመምሸቱ ለማክሰኞ በአዳር ተቀጥረው ነበር፡፡ በሦስተኛ ምርመራ መዝገብ የቀረቡት ከናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመጡ ተጠርጣሪዎች አቶ መሐመድ ኢሳ፣ አቶ ሰመረ ንጉሴ፣ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ፣ አቶ ማርሸት ተስፋዬ፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋዬና አቶ ዳኜ ስንሻውም በአዳር ለማክሰኞ ተቀጥረው ነበር፡፡
ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ቀጥሎ የዋለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎችና የነጋዴዎች የፍርድ ቤት ውሎ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ብይን ከመስጠቱ በፊት ስለ አቶ መላኩ ፈንታ ያለመከሰስ መብት በሚመለከት የቀረበውን አቤቱታ በሰነድ ተደግፎ መቅረብ እንዳለበት ፍርድ ቤቱ ስላመነበት፣ ማስረጃቸውን ለግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ አዟል፡፡ በእሳቸው የምርመራ መዝገብ የቀረቡት ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜም ለመርማሪው ተፈቅዶለታል፡፡ በሌላ የምርመራ መዝገብ በአዳሪ ተቀጥሮ የነበረው የአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ፣ የአቶ በላቸው በየነ፣ የአቶ ጥሩነህ በርታ፣ የአቶ ተስፋዬ አበበ፣ የአቶ ነጋ ገብረእግዚአብሔር፣ የአቶ ምህረተአብ አብርሃ፣ የአቶ ሙሌ ጋሻው፣ የአቶ አሞኘ አወቀ፣ የኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ፣ የአቶ ሀብቶም ገብረመድህን፣ የወይዘሮ ንግስቲ ተስፋይና ሰኞ ዕለት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተነገረው የገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ኃላፊ አቶ ተወልደ ብስራት ክርክር ተደምጧል፡፡
ከአቶ ምህረተአብ አብርሃ በስተቀር ሁሉም ተጠርጣሪዎች በጠበቃ ተወክለዋል፡፡ አቶ ገብረዋህድ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበት ጊዜ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ “እኔ በሠራሁት ወይም በተጠረጠርኩበት ጉዳይ መጠየቅ ያለብኝ እኔ ነኝ፡፡ መቀጣትም ካለብኝም እኔ ራሴ እቀጣለሁ፡፡ ልጄ ታስሯል፣ ባለቤቴ ታስራለች፣ ለምን ቤተሰቦቼ? ምን ዓይነት አገር እየሆንን ነው?” በማለት የቤተሰቦቻቸው መታሰር አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከላይ በእነ አቶ መላኩ የምርመራ መዝገብ የቀረበው መሆኑ በኮሚሽኑ መርማሪዎች የተነገራቸው አቶ ገብረዋህድ ፍርድ ቤቱ ከትናንትና በስቲያ በሰጠው ትዕዛዝ በሕግ አማካሪ፣ በቤተሰብ፣ በሃይማኖትና በጓደኞቻቸው የመጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተግባራዊ እንዳልሆነና ጠበቃ ማግኘት ባለመቻላቸው ጊዜያዊ ጠበቃ ማቆማቸውን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለምን ትዕዛዙ እንዳልተፈጸመ መርማሪዎችን ጠይቋል፡፡ መርማሪዎቹ በሰጡት ምላሽ በመሥሪያ ቤቱ አሠራር፣ ተጠርጣሪዎች በሕግ አማካሪዎቻቸው መጐብኘት የሚችሉት ረቡዕ እና ዓርብ ብቻ መሆኑንና ቀሪዎቹ ቀናት የምርመራ ጊዜያት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን በመቀጠል ተጠርጣሪዎች በሕግ አማካሪዎቻቸው የመጐብኛ ጊዜ ረቡዕ እና ዓርብ የተደረገው ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ እንዲያስረዱ መርማሪዎቹን በድጋሚ ጠየቀ፡፡ መርማሪዎቹ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለእስረኞች ኃላፊ ለኮማንደር ብርሃኑ አበበ መንገራቸውንና ማስረዳት የሚችሉትም ለእሳቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ የጠየቃቸውን ጥያቄ ለመመለስ ከኃላፊነታቸው ውጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ወደ ማዕከላዊ ቢሄዱም መርማሪዎቹ ከላይ የጠቀሱትን በመድገም ሊያገናኟቸው እንዳልቻሉ፣ በችሎት የነበሩ መርማሪዎችን አግኝተው ቢያነጋግሯቸውም ምላሽ እንዳልሰጧቸውና ደንበኞቻቸውን አግኝተው መመካከር እንዳልቻሉ አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መጨረሻ ላይ ብይን ሰጥቶበታል፡፡
የመርማሪዎች፣ የፍርድ ቤቱና የጠበቆች ክርክር ካበቃ በኋላ ስለ አቶ ገብረዋህድ ጠበቃቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ገብረዋህድ የተጠረጠሩት ከአቶ ነጋ ገብረእግዚአብሔር፣ ከአቶ ምህረተአብና ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር፣ በፍራንኮቫሉታ የተከለከለ ሲሚንቶ እንዲገባ ማድረጋቸውንና ክስ እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል መሆኑን የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊስ በድጋሚ ለጠበቆቹ አስታውሷል፡፡ የተያዙትም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑንና ብርበራም የተካሄደው ሕጉን በጠበቀ መንገድ መሆኑን አክሏል፡፡ የአቶ ገብረዋህድ ጠበቆች የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊስ ስለደንበኛቸው መጠርጠር የጠቀሰውን ጉዳይ በማለፍ፣ በባለቤታቸው ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ ላይ በብርበራ ወቅት ተፈጽሟል ያሉትን ኢሰብዓዊ ድርጊት አስረድተዋል፡፡
ኮሎኔል ሃይማኖት ሰብዓዊ መብታቸውን በሚጋፋ ሁኔታ ራቁታቸውን ሆነው ወደላይ ከፍ ብለው እንዲዘሉ እየተደረጉ መፈተሻቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ሰብዓዊ ክብራቸው መነካቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ገብረዋህድ በፍርድ ቤት ሳይፈረድባቸው ስማቸውን የሚያጠፋ ዘገባ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እየተላለፈ መሆኑን የገለጹት ጠበቃቸው፣ ተጠርጥረው ባሉበት ወቅት ንፁህ ሆነው መገመት ስላለባቸው ፍርድ ቤቱ ዘገባውን እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡ ባለቤታቸው፣ የባለቤታቸው እህትና ልጃቸው እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልጃቸው በዋስ እንዲለቀቁና እሳቸው ብቻ በተጠረጠሩበት ወንጀል መከራከር እንዳለባቸው የተናገሩት የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ ልጆቻቸው በሜዳ ላይ መበተናቸውን፣ ከማናቸውም ቤተሰብ ጋር እንደማይገናኙና በአንድ ክፍል ተዘግቶባቸው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ልጃቸው እነሱ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ መፈታቱን በመሀል አሳውቋል፡፡ በባለቤታቸው እጅ የተያዘው የቤት ካርታ ዋናው (ኦሪጅናል) ሳይሆን ብሉፕሪንት መሆኑንና ዋናው በመርማሪ ፖሊሶቹ እጅ እንደሚገኝ ጠበቃቸው ሲናገሩ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት በመሀል ገብተው ሰነዱን ለመደበቅ ሳይሆን ልጆች እንዳያበላሹባቸው እህታቸው ቤት ለማስቀመጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በበቂ ዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ አቶ በላቸው በየነም እንደ አቶ ገብረዋህድ ወንጀለኛነታቸው ሳይረጋገጥ ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ፣ በሚሠራጨው ዘገባ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸው ሁሉ አንገታቸውን እየደፉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(2) የተከበረላቸው የመጐብኘት መብትን በሚመለከት በሌሎቹ የቀረበው አቤቱታ ለእሳቸውም እንዲመዘገብላቸው ተናግረዋል፡፡ በቤታቸውና በቢሮአቸው ተበርብሮ የተገኘ ነገር ስለሌለ ዋስትና እንዲጠበቅላቸው ጠበቃቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ጥሩነህ በርታ ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጭ ተጥሶ ቤታቸው የተበረበረው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት መሆኑን፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት በመሆኑ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው እስካሁን መረበሻቸውን፣ ምንም የተገኘ ነገር ስለሌለ በዋስ እንዲለቀቁ እሳቸውም ጠይቀዋል፡፡ ቤታቸው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበሩንና ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ድርጊት የተፈጸመ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ አበበ ልብ ድካም፣ ኮሌስትሮልና ሌሎችም ሕመሞች ስላሉባቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ሰኞ ዕለት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ ተወልደ ብስራት የተጠረጠሩበትን ጉዳይ እንደማያውቁት፣ ቃላቸውን እንደሰጡ የኮሚሽኑ መርማሪ ቢገልጽም በአንድ ቅጽ ላይ ስማቸውን ከማስፈር ያለፈ ምንም የሰጡት ቃል እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በመርማሪዎቹ ስለተከሰሱበት ጉዳይ ከተገለጸላቸው በኋላ፣ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ መረበሽ እንደደረሰባቸው በመናገር የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው አመልክተዋል፡፡ አቶ ነጋ ገብረእግዚአብሔር በጠበቃቸው በኩል እንደተናገሩት፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮን ይቃወማሉ፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ የቀረው ሰነድና ማስረጃ እንደሌለ በመገናኛ ብዙኅን ገልጿል፡፡ ተሰበሰበ የተባለው ሰነድም ከእሳቸው ጋር አይገናኝም፡፡ በዋስ ቢወጡ ሰነድ ያጠፋሉ፣ ምስክር ያባብላሉና ያስፈራራሉ በሚል መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን ተቃውሞ፣ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ “ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተመሳጥረህ ወንጀል ሰርተሃል” ስለተባለው ጉዳይ መርማሪው ከማን ጋር፣ ምን ወንጀል እንደተፈጸመ በማስረጃ ስላላቀረበና እሳቸውም የማወቅ መብት ቢኖራቸውም የተሰጣቸው ማስረጃ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በተከለከለ የፍራንኮቫሉታ ፈቃድ ሲሚንቶ ስለማስገባታቸውና የተመሠረተን ክስ እንዲቋረጥ ስለማድረጋቸው በማስረጃ የቀረበ ነገር ስለሌለ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ “ዝም ብሎ በተበጀ ነገር ነው የተከሰስኩት፣ በሕይወቴ ከሲሚንቶ ንግድ ጋር በተያያዘ ኤልሲ ከፍቼ አላውቅም፡፡ በምን እንደተከሰስኩም አላውቅም፣ በቢሮዬና በቤቴ ብርበራ ተደርጎ ሰነዶች ተወስደዋል፤” ያሉት የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትርና በሙስና ወንጀል ተከሰው ከአምስት ዓመታት በላይ በማረሚያ ቤት ቆይተው የተፈቱት አቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ ምህረተአብ አብርሃ ናቸው፡፡ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በሌላ ክልል የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውንና ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል እንደማይመለከታቸው የተናገሩት አቶ ሙሌ ጋሻው ሲሆኑ፣ የሚፈለገው ነገር በቤታቸውና በመሥሪያ ቤታቸው ብርበራ ተደርጎ ስለተወሰደ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ያነሱትን የመከራከርያ ነጥብ በመድገም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁት አቶ አሞኘ አወቀ ናቸው፡፡ ልጆቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁና ለዕለት ጉርሳቸው የሚሆን ነገር እንደሌለና ገንዘባቸው በሙሉ በቁጥጥር ሥር መሆኑን፣ ከውጭ አገር የመጡ ዘመዳቸው ፓስፖርት እሳቸው ቤት እንደታሸገበትና ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት መኪና ስለሌላቸው እንደተቸገሩ በማስረዳት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኮሎኔል ሃይማኖት እህት ወይዘሮ ንግስቲና ልጃቸው አቶ ሀብቶም ገብረመድህን የታሰሩት ሰነድ አሽሽተዋል በሚል መሆኑን በመጥቀስ፣ በሙስና ስላልተጠረጠሩ እንዲለቀቁ ጠበቃቸው ጠይቀዋል፡፡ መልስ የሰጡት የኮሚሽኑ መርማሪዎች ተጠርጣሪዎች ስለተያዙበት ጉዳይ ማስረዳታቸውንና በሰነድ ላይ ማስፈረማቸውን፣ ምርመራው ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ የጠየቁት የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ካላቸው ከፍተኛ ሥልጣንና ገንዘብ አንፃር ሰነድ ሊያሸሹ፣ ምስክር ሊያባብሉና ሊያስፈራሩ ስለሚችሉ ዋስትናውን ተቃውመዋል፡፡ በመገናኛ ብዙኅን ኮሚሽኑ የገለጸው ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ የሚያበቃው የሰነድና የሰው ማስረጃ እንዳለው እንጂ፣ ስለ አጠቃላይ ምርመራና ማስረጃ ውጤት አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በመላው አገሪቱ በመሆኑ ምርመራው ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡ ስለመብት ጥሰት የተነሳውን ጥያቄ በሚመለከት “ምንም የተጣሰ መብት የለም” ብለዋል፡፡ ቤተሰብም ሆነ ጠበቃ እንዳልጠየቃቸው ተናግረዋል፡፡ መርማሪዎቹ ቀደም ብለው ሲናገሩ ስለቤተሰብ ጥየቃ እንደማይመለከታቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ብርበራን በሚመለከት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንጂ ሌሊት እንዳልበረበሩም መርማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአግባቡ መያዛቸውን በመናገር ከላይ ካሉት ጋር የሚጣረስ ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሰነድ ሲያሸሹ ተያዙ ስለተባሉት ኮሎኔል ሃይማኖት፣ ወይዘሮ ንግስቲና አቶ ሀብቶምን በሚመለከት የቀራቸው ነገር ምን እንደሆነ? ሰነድ እንዳያሸሹ እንጂ ሌሎቹ ከተጠረጠሩበት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑና አለመሆኑ መርማሪዎች እንዲያስረዱ ጠይቋል፡፡ መርማሪዎቹም ተጠርጣሪዎቹ በተለይ ኮሎኔል ሃይማኖት ካላቸው ተሰሚነት አንፃር (አሁን በሥራ ላይ አይደሉም) ሰነድ ሊያጠፉና ሊያስጠፉባቸው እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱም ከሙስና ጋር ስለሚገናኝ መለቀቃቸውን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ በሰጠው ብይን፣ የኮሚሽኑ መርማሪዎች እንዳቀረቡት ጉዳዩ ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር የተጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መፈቀዱን፣ በሌላ በኩል ተጠርጣሪዎቹ ካለባቸው ኃላፊነት አኳያና ማኅበራዊ ግንኙነት አቋም አንፃር ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ በይኗል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተጠርጣሪዎች ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰጠውን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበሩ የእስረኞች ኃላፊ ኮማንደር ብርሃኑ አበበ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀርበው እንዲያስረዱም አዟል፡፡
በሦስተኛ የምርመራ መዝገብ የቀረቡት የናዝሬት ጉምሩክ መሥሪያ ቤት ድንገተኛ ፍተሻ ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢሳ፣ አቶ ሰመረ ንጉሴ፣ አቶ ዘርይሁን ዘውዴ፣ አቶ ማርሸት ተስፋዬና አቶ ዳኜ ስንሻው፣ የሕግ ሰው አግኝተው ለመወከል አለመቻላቸውን በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ትዕዛዝ ለመርማሪዎቹ ሰጥቶላቸው ቤተሰቦቻቸውንና የሕግ አማካሪ እንዲያገኙ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ፖሊሶቹ የተጠርጣሪዎቹን ጥያቄ ግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ይዘው እንዲቀርቡ ታዘው ይዘው ባለመቅረባቸው ዕድሉ ሊታለፋቸው ይገባል በማለት ተቃውመዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ትዕዛዝ ተግባራዊ እንዳልሆነ መመልከቱንና እነዚህም ተጠርጣሪዎች ተመሳሳይ ዕድል እንዳጋጠማቸው ግምት በመውሰድና የመርማሪ ፖሊሶቹን ተቃውሞ በማለፍ፣ ተጠርጣሪዎቹ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም በጠበቃ ተወክለው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ችሎቱ ተጠቃሏል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የናዝሬት ጉምሩክ የሕግ ማስከበር ኃላፊ አቶ ተመስገን ጉልላት 160 ሺሕ ብር ይዘው ወደ ጋምቤላ በመሄድ ወደ ሱዳን ለመሸሽ፣ ለጋምቤላ ጉምሩክ ኃላፊ ለአቶ ጌታቸው አሰፋ 80 ሺሕ ብር ሰጥተው ሊያልፉ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር; AP Photo)
Leave a Reply