“ክሴን አቋርጫለሁ” ከማለት ባለፈ ምክንያቱን ከመናገር ተቆጥቧል
ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2006 ዓ.ም. በድንገት ተይዘው ከታሰሩ በኋላ፣ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸውና የሰነድና የሰው ማስረጃ ቀርቦባቸው፣ ለብይን የተቀጠሩበትን ቀን እየተጠባበቁ ከነበሩት አሥር ተከሳሾች መካከል አምስቱ በድንገት ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈታታቸው እያነገጋገረ ነው፡፡
ለተከሳሾቹም ሆነ ወክለዋቸው ለሚከራከሩላቸው ጠበቆቻቸው ምንም ዓይነት መረጃ ሳይደርሳቸው በድንገት፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ ክሱን አቋርጣል፡፡ በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ ከእስር ተለቃችኋል፤›› የተባሉት ተከሳሾች ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬና ጦማሪያን ዘለዓለም ክብረትና ማህሌት ፋንታሁን ናቸው፡፡ ክሱ እንደተቋረጠ በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ከማወቃቸው በስተቀር፣ ከክሱ ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለመሆናቸው ወይም በተፈለገ ጊዜ በዚሁ ክስ የሚከሰሱ ስለመሆኑ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(2) ማለትም የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ፣ በንዑስ አንቀጽ 4 ማለትም የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሴርና በማነሳሳት ሙከራ፣ እንዲሁም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) ሀ እና ለን በመተላለፍ፣ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር፣ በመላ ሐሳባቸውና አድራጎታቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቧል፡፡ ጉዳይዋ በሌለችበት እየታየ ካለችው ጦማሪ ሶልያና ሽመልስ በስተቀር በሁሉም ተከሳሾች ላይ 18 የሰዎች ምስክሮች፣ የሰነድ፣ የሲዲና ቪሲዲ ማስረጃዎችንም አቅርቦ ጨርሷል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ ነገር ግን በፌዴራል ማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን በመከታተል ላይ ካሉት ዘጠኝ ተከሳሾች ውስጥ፣ ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ ተከሳሾች ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር ተፈተዋል፡፡
ተከሳሾቹ ከእስር የተፈቱት የኢፌዴሪ አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 16(6) መሠረት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በቂ ምክንያት ሲኖረው በሕግ መሠረት ክሱን ማቋረጥ እንደሚችል የሚገልጸውን ድንጋጌ ተጠቅሞ ክሱን በማቋረጡ ነው፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለፍትሕ ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በተከሳሾቹ ላይ የመሠረተውን ክስ ያቋረጠ ቢሆንም፣ አዋጁ ‹‹በቂ ምክንያት ሲኖረው በሕግ መሠረት ክሱን ያነሳል›› ለሚለው በየትኛው ሕግ እንደሆነ ዝርዝር ማብራሪያ አለመስጠቱ የሕግ ባለሙያዎችም ግልጽ እንዳልሆነላቸውና ግራ እንዳጋባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቂ ምክንያት ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡
የተከሳሾቹ ክስ የተቋረጠው ከፍትሕ ሚኒስቴር መዝገቡን እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን፣ ፍርድ ቤቱም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተከሳሾቹን እንዲፈታ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት እንደሆነ በመገለጹ፣ ሪፖርተር ማብራሪያ ለማግኘት ፍትሕ ሚኒስቴር በመሄድ ጠይቋል፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትር ዴኤታዎች በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ መሆናቸው በመገለጹ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ማስተባበሪያ ኃላፊው አቶ ደሳለኝ ተሬሳ የተከሳሾቹ ክስ በአዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 16(6) መሠረት መቋረጡን ከመግለጽ ባለፈ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አልቻሉም፡፡
መንግሥት በተከሳሾቹ ላይ የጀመረውን ክስ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ማቋረጡን ከመናገር ባለፈ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠቡ ተፈቺዎችም ሆኑ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ውዥንብር ውስጥ መግባታቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ ተከሳሾቹ በድንገት ክሳቸው ተቋርጦ በመፈታታቸው ደስተኛ ቢሆንም፣ ክሱ ሲቋረጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለመሆናቸው ወይም በድጋሚ የሚከሰሱበት ስለመሆኑ አለመገለጹ ግራ የሚያጋባ በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል ግልጽ ማድረግ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ ተፈቺዎቹ ‹‹በነፃ ተፈትተናል ብለው ያለምንም ሰቀቀን መኖር ይችላሉ? ተፈቺዎቹና ጠበቆቻቸው ክሱ ስለተቋረጠበት ምክንያት ማወቅ የለባቸውም? ያለምንም ማብራሪያ ብድግ ብሎ ክሴን አንስቻለሁ ማለት ምን ማለት ነው? ሕጉ በቂ ምክንያት ወይም ጥሩ ምክንያት (Good Cause) ሲል ምን ማለቱ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሕግ ባለሙያ አንስተው፣ በቂ ማብራሪያ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡
ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እንዴት እንደተለቀቁና ስለመለቀቃቸው ቅድመ መረጃ እንደነበራቸው ወይም እንደሌላቸው ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ እሱና ሌሎቹ ታሳሪዎች እስከተለቀቁበት ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ 10፡30 ሰዓት ድረስ፣ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ላይ የትችት ማብራሪያ ማቅረብ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የመጀመሪያ የትችት ጽሑፋቸውን ለጠበቆቻቸው ሰጥተው፣ የመጨረሻውን (በጠበቆች ተጽፎ ለፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትችት) ለማየት ጠበቆቻቸውን እየተጠባበቁ እንደነበሩ ተናግሯል፡፡ በተጠቀሰው ሰዓት በእስር ላይ የሚገኘው አጥናፍ ብርሃኔና እሱ ባሉበት ዞን መዝናኛ አዳራሽ ውስጥ ሆነው፣ በኢቢሲ-3 የሚተላለፍ ፊልም እያዩ እንደነበር የገለጸው ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ በጠባቂዎች ዘወትር እንደሚደረገው ከእስር የሚለቀቁ ሰዎች ስም በድምፅ ማጉያ ሲጠራ፣ የአባቱ ስም ትክክል ባይሆንም ‹‹ተስፋለም›› የሚል ስም መስማቱን ገልጿል፡፡
የእሱን ስም የሚጠራው ተሳስቶ እንደሆነ በመገመት ፊልሙን በማየት ላይ እያሉ በተደጋጋሚ በመጠራቱ፣ ወደሚጠራው ሰው ጠጋ ብለው ስም ዝርዝር ሲመለከቱ፣ የዘለዓለምንና የአስማማውን ስም በማየቱ ‹‹የሆነ ነገር አለ›› በማለት፣ ወደ አስተዳደር ሄደው ሲጠይቁ ‹‹ስምህ እየተጠራ አልቀርብ ያልከው አንተ ነህ?›› ተብሎ ሲገባ፣ የሞላው ቅጽ ተረጋግጦ ‹‹ውጣ›› መባሉን ተናግሯል፡፡
‹‹አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ታስሬ እንዴት በድንገት ውጣ እባላለሁ? በምን ምክንያት?›› የሚል ጥያቄ ማንሳቱን የገለጸው ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ ክሱን አቋርጦ ነው›› መባሉንና የመፈቻ ካርኒ (እንደ ሰርተፊኬት የምታገለግል) ሲሰጠው በካርኒውም ላይ ‹‹ክሱ ተቋርጧል›› ከሚል ውጪ ምንም የተገለጸ ነገር እንደሌለ አስረድቷል፡፡ የማረሚያ ቤቱ የውጭ በር ላይ ሲደርስ ማመን አቅቶት ቆም ብሎ ግራና ቀኝ ሲመለከት ምንም ነገር ማጣቱን የተናገረው ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ ማረሚያ ቤት የሚለብሰውን ፒጃማ እንደለበሰ ባጃጅ ውስጥ ገብቶ ልብሱን እንደቀየረና ከባለባጃጁ ስልክ ጠይቆ መፈታቱን መጀመሪያ ያበሰረው ለእህቱ መሆኑን ገልጿል፡፡ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ እሱም ሆነ ጓደኞቹ ጠበቃቸውን አቶ አመሐ መኰንን አግኝተው ሲያነጋገሩ፣ ጠበቃውም ቢሆኑ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደተለቀቁ እንደማያውቁ መናገራቸውን ጋዜጠኛ ተስፋለም ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
በለው ! says
>>>በቂ ምክንያትና ምስክር በመጥፋቱ ተፈቱ! ወይንስ የክስ መቋረጥና መቀጠል!?
ኀይለመለስ “መብራት የሚቆራራጥባቸው ቦታዎች እንጂ የጠፋበት ከተማ የለም!” “መብራት ከጠፋ ሳምንታችን የተቦካው የእንጀራ ሊጥ ሾምጥጦ ተደፋ” ይላል ሕዝቡ….
____” የሞት የፍርድ እንደዋዛ !” ዕድሜ እሥራት እንደቀልድ!፲ እስከ ፳፭ ዓመት ፅኑ አሥራት እንደፌዝ!
“በሕዝብ ፻ ከመቶ ደምፅ አግኝቶ የተመረጠን መንግስት ተአማኒነት በማሳጣት!..ሕገመንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኀይል ለመናድ!በህዝብ የተመረጠን መንግስት ዕውቅና በመንፈግ…ባልተፈቀደላቸው ሀዘን ላይ በመካፈል…በሕቡ ተደራጅተው ስላነበቡና ስለፃፉ! መንግስት ሙስናን ይቆጣጠር! የጋራ የሀብት ተጠቃሚነት አላድልዎ!ህብረብሔር ባህልና ሃይማኖት የህዝብ አብሮነት ይዳብር ስላሉ?…እስኪሪብቶ እንደ ጦር ሚሳየል…የጋዜጣ አምድ እንደ ባሕር ማዕበል ያሰጋት ኢኮኖሚን በሞኖፖሊ የጠቀለለች የፓርላማ ወንበር በልኩ ያነፀ፣ በጦር መሳሪያና በወታደር ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ የሆነች የህወአት/ኢህአዴግ ወያናይት ሀገር ስትሸበር አያሳዝንም!? እናንተ ለእኛ በእኛ ብቻ የምትኖሩ ይቺ ሀገር ያለእኛ እድገትም፣ ጠባቂም፣ አዋቂም፣ የሌላት የምትፈራርስ ሀገር ብሎ በማስፈራራት የ፶ ዓመት በሥልጣን የመቆየት ራዕይ ያለው አውራው ፓርቲ፣ መንግስትና አጋሮቹ ፣ ኢህአዴግ ተፎካካሪም አማካሪም የማይፈልግ ምንስ ቢያደርግ ምንስ ቢሰራ ማነው ከልካይ?>>> we blog, because we care! የሚሉት ወጣት ጦማሪያን በመሠረቱ ግራ የሚያጋባው አፈታታቸው ሳይሆን የእሥር ሁኔታቸው ነበር። የእያንዳንዱ ግለሰብ ክስ አመሠራረት ቀድሞ ከተከሰሱና ከተፈረደባቸው ግለሰቦች የክስ አመሠራረትና የተጣላባቸውን ፍርድ አመሳስሎ የተቀዳ (copy paste) ቆርጦ ቀጥል ነው። ሌላው ከአሸባሪው ሕግ ጋር አንቀፅ በአንቀፅ ተፈልጎ እያንዳንዱ እሥረኛ ከ፲ ዓመት አስከ እድሜ ልክ ፅኑ እሥራት የሚያስፈርድብትን ሐተታ አቅርበዋል።
>>> በሞትና በእድሜልክ ጽኑ እስራት ሊያስቀጡ በሚችሉ ወንጀሎች ተከሰው የነበሩት ጋዜጠኞች እና ጦማርያን ክሳቸው ተቋርጦ በድንገት ከእስር የመፈታታቸው ምክንያት:-
— “ኦቦ ሁሴን እመጣለሁ ስላሉ እሥረኖች ተፈቱ?…ያሠራቸው/ያሳሠራቸው የአሜሪካ መንግስት ነበር? ኦባማ ኢትዮጵያ የመምጣት ዕቅዳቸው ቢሰረዙ ተፈችዎች የተቋረጠው ክስ ተቀጥሎ ደግመው ይታሠራሉን? ኦባማን ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ ህግና ሀገመንግስታዊ ሥርዓታችን በላይ አደለህምና አትምጣ በለው! በእርግጥ ያደጉ ሀገሮች ማበደርና ማስለመን እንጂ በፍትህ ሥርዓታችንና በፖለቲካችን አያገባቸውም የሚለው ኢህአዴግ ዛሬ ምን አንበረከከው?ኢኮኖሚው ከአሜሪካ እኩል ስለሆነ የዓለም መንግስታት እያለቀሱለት ስለሆነ ነው አያደርገውም!!ኢህአዴግ በውጭ ሀገራት በሚደርስበት የሰብዓዊ መብት እረገጣ ተቃውሞ በአሜሪካ ሴናተርና በአውሮፓ መፅዋች ሀገሮች ሎቢይስቶች ዋጋቸው እየጨመረ መክፈል ተስኖት ይሆን?
—የአርበኞች ፯ ግንባር የሠላም ትግል እንቢ ስላለው በሚገባው ቋንቋ አነጋግራለሁ ሲል ኀይለመለስ ደስአለኝ እኔም ሕዝቡን አነጋግራለሁ ስላሉ ነውን!? **ምንአልባት ወደ ሰሜን ለቡጡቡጥ መሄዳችን ነው ሕዝቡን ተነስ እንነሳ ከማለታችን በፊት እጅ እንንሳ ብለው ይሆን!? እንግዲህ በቁጥር ሶስት የወንድማማች የመፈቃቀድ ጦርነት በመሐል የሚማገደው ተረኛ ማን ይሆን? ኢንቨስትር? ዲያስፖራ? ልማታዊ አርቲስትና ጋዜጠኛ? ካድሬው?
–“ድንገት ተጠርተን ውጡ ተባልን አላመንም!ውጪ በር ላይ ክሱ ተቋርጧል የሚል የመውጫ ወረቀት ሲሰጠን እውነት መሆኑንና መፈታታችንን አረጋገጥን!” ድንገተኛው እሥር መጀመሪያ በኤፍኤም ዛሚ፣ፋናና አይጋ ፎረም ላይ ይገለፅ ነበር አሁን እንዴት ነገሩ ቀድሞ በዛሚ ኤፍኤም ሳይዘመዘም ድንገት መፈታት! ለመሆኑ ፳፻፯ ምርጫ ያሸነፉት ፭፻፵፯ ሰዎች ከየት ሀገር ናቸው!
—ፍትህ ሚ/ር ፈተህ ልቀቅ አለ…ፍርድ ቤቱ በሕግና ዳኛ በአወዛጋቢ ምስክርና ከበቂ በላይ ማስረጃ ለአንድ ዓመት ሲያሟግት የነበረውን ከፍተኛ የወንጀል ጉዳይ በቀጭን ትዕዛዝ ሲሰርዝ “ይርጋ ወይስ ይጥና” አለው? እንግዲህ ብርቱካን ሚደቅሳን ያስታውሷል። “የነጭ ደምና የጥቁር ደም አንድ ነው ብሎ ነጩን በነፃ ፈቶ ከሀገር ሲያስወጣ ኢትዮጵያዊውን ጥቁር አጥብቆ ያሰረው ማን ነበር?
>>> እንደእኔ ከሆነ ሁሉንም እሥረኞች በነፃ የሚያወጣቸው ከበቂ በላይ ማስረጃቸው “በሕቡ ተደራጅተው ግለሰቦችን በመመልመል ህገመንግስታዊ ሥርዓቱንና ሕገመንግስቱን በኀይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” የሚለው ክስ አንዱና ዋነኛው አካል ነው። ***”በ፳፻፯ የሀገራዊ (ፌደራላዊ) ምርጫ ኢህአዴግ ፭፻፵፯ መቀመጫ ያለምንም ተቀናቃኝ አሸንፏል። ….ድምፃችን ተቀማ ብለው በሕቡ ተደራጅተው ሰለጠኑ ከተባሉትና መንግስት ለመገልበጥ የዓለም አቀፍ ሕግ አንቀፅ ፲፱ ትምህርት ከተከታተሉት አንድም ሰው ምንም ቦታ ላይ ስለምርጫው መቀማትና መጠቅለል ሲቃወም በፍፁም አልታየም…. ሕገመንግስቱም፣ሥርዓቱም፣ ፓርላማውም ሥራውን በሠላም ቀጥሏል። እንግዲህ ግለሰቦቹ አላግባብ በሐሰት በተከሰሱበትና በተንገላቱበት በሥም ማጥፋትና የወጣትነት መልካም ሥምና ዝና በመጉደፉ ከሥራ፣ከትምህርታቸው፣ የመምረጥ መመረጥ መብታቸው በመገፈፉ ወንጀል ካሳ የመጠየቅ መብታቸው ሊከበር ይገባል።
***እንግዲህ አውራው ገዢ ፓርቲና መንግስት መሬት በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከሯን፣ ዓለም በፖለቲካ አመለካከት መቀየሯን በ፳፩ኛውክ/ዘ ላይ መድረሳችን የገባቸው ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ዕኩልነት፣ ከ፲፩ ከመቶ መብለጡን ፺ሚሊየን ሕዝብ ከ፶፵፯ ፓርላማ የኢህአዴግ አባላት ወንበር/መቀመጫ በላይ መሆናቸውን ከተረዳ…የመናገርና የመጻፍ መብት ህግና ደንብ ገደብ ውስጥ እውነታን ያዘለ እስከሆነ ለሀገርና ሕዝብ ጠቃሚ መሆኑን ከተረዳ…ለሀገራዊ ዕርቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። የተቃዋሚን ሀሳብ ተቀብሎ ስሕተትን ማረም፣ መካርና ጉድፍ ነቃሽ አያሳጣኝ ማለት የዕድገትና ለውጥ መሠረት ነው። *** “እሥር ቤቶች ወደ ቤተመፃሕፍት ቤት የሚለወጡበት ዘመን ሥርዓትና ሀገር እንጂ ወጣት የሚቀበርበት፣ዜጋ የሚሸማቀቅበት ክልል አይሁን! እንግዳስ አህአዴግ ከደርግ በምን ተሻለ ገድሎ የጥይት ባለማስከፈሉ ጎዝጉዞ በማርዳቱና በማስተዛዘኑ ወይንስ ዓለም በቃኝን ዘግቶ ኢትዮጵያ በቃቸኝን በመክፈቱ? ሌላውም ጎራ ነገሮችን ከማክረር ማረገብን መርጦ በተገኘው አጋጣሚ የሀሳብ የበላይነቱን በሰላማዊ ትግል ዙሪያውን ከቦ አንድንትን በማሳየት ጎጥና ዘረኝነትን በመስብር ህወአት/ኢህአዴግን ማስተማር ይጠበቅበታል። ሠላም ለሁሉም በቸር ይግጠመን