ዛሬ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር እሁድ መጋቢት 15 ቀን 2005ዓ.ም ነው፡፡ የዚህችን ዕለት ውሎየን ነው እንግዲህ የማካፍላችሁ፡፡ እኔም እንዳቅሜ የቤተሰቤን ፍላጎት አፍኜ አልጀዚራን ብቻ በመክፈት በማየው ነገር ሁላ በንዴት ስፎገላ ነው የትም ሳልሄድ ቤቴ ተከርችሜ የዋልኩ፡፡ እርግጥ ነው ከሰዓት በኋላ የኢትዮጵያንና የቦትስዋናን የዓለም እግር ኳስ አፍሪካዊ የማጣሪያ ጨዋታ ተከታትያለሁ – ሀገሬ አንድ ለዜሮ በማቸነ‹ፏ›ም ተደስቻለሁ፡፡ የተቀረውን ግን አታንሱት – እኔ ግን ላነሳው ነኝ፡፡ (አይ የኛ ሀገር ነገር! በ‹ቸ›ና በ‹ሸ› አጠቃቀም ሳይቀር እንናቆር ነበር እኮ! ምን ቢዞርብን ይሆን!)
በነገራችን ላይ ዘመነ ምፅዓት አሁን ካልሆነ መቼም አይሆንም፡፡ ይህ ድምዳሜየ በዛሬው ውሎዬ ብቻ የተደረሰበት እንዳይመስላችሁ – ዛሬ አጠናከረልኝ እንጂ የቆዬ ነው፡፡ በዚያ ላይ በለሲቱ ስታቆጠቁጥ የጊዜውን መድረስ መረዳት እንደሚቻለን የቀደመ ጥቆማ አለ፡፡ የጎንደሩ ዋርካም ቅርንጫፉ መሬት ሳይረግጥ አይቀርም፡፡ በዚያም ሆነ በዚህ ዘመኑ ቀርቧል፡፡
በቅድሚያ ግን ምንም እንኳን ጥቂት ቢሆኑም በዚህ የመርዶ ዘመን ውስጥ የደስታ ስሜት ያጫሩልኝን ሁለት ያህል ወቅታዊ ዜናዎችን ልግለፅ፡፡
ቀዳሚው እስራኤልና ቱርክ ዕርቅ አውርደው የጠብን ግርዶሽ የገፈፉበት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ስምምነት ነው – በኦባማ አነሳሽነት፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ግትርነት ቢወገድ፣ እልኸኝነት ቢሸነፍ፣ዕብሪትና ትምክህት ቢለዝቡ ይሄኔ ዓለማችን በሰላሙ ጎዳና የትና የት በደረሰች! የሰላም መውረድ የሚያስከፋቸውና በሀገራቱ መታረቅ አንዳች ጥቅም ይቀርብናል ብለው የሚያምኑ ጽንፈኞች ቢቀየሙም – የማይጠበቅም አይደለም – ይህ ጅምር በጣም ተስፋ የሚሰጥና በስፋት መለመድም ያለበት መልካም ነገር ነው፡፡ ፍቅርን የሚጠላ ጤነኛ አይደለም፡፡ ጥላቻን የሚሰብክና በውጤቱም አንዳች ፍላጎቱን ለማሳካት የሚቋምጥ የሥነ ልቦና ልምሻ የተጠናወተው ዕብድ ነው፡፡
ሁለተኛው ዛሬ ግብጽ ላይ የተሰበሰቡት የሦርያው መሪ የባሽር አላሳድ ጎሣ አባላት አላዊቶች የወሰዱት ግን ሊሆን ከሚገባው ጊዜ እጅግ ዘግይቶ የታዬው እርምጃ ነው፡፡ ይህ ስብሰባ ምንም እንኳን እጅግ ከመዘግየቱ የተነሣ የብዙዎችን ቀልብ ሊስብ የመቻሉ ነገር አጠያያቂ ቢመስልም ፈረንጆች ‹ጨርሶ ከመቅረት ዘግይቶም ቢሆን (መድረስ፣ማድረግ…)›(Better late than never.) እንደሚሉት አሁን የአሳድ መጨረሻ በሚመስል ሰዓት ላይ ይህን ማድረጋቸው – ካለማድረጋቸው ስለሚሻል – ወቅቱ የሚፈልገው ተገቢ እርምጃ ነው ብለን ልናወድሰው ይገባናል፡፡ የአላዊትን ጎሣ እንደሚወክሉ የተነገረላቸው በግብጽ የተሰበሰቡ ወገኖች ዛሬ በደረሱበት ስምምነት መሠረት ራሳቸውን ከአሳድ የጥፋት ተልእኮ በመነጠል ሀገሪቱን ከተጨማሪ ውድመት ለመታደግ የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ መቁረጣቸውን አሳውቀዋል፡፡ የነዚህ ወገኖች ቆራጥነት በሦርያ ምድር ብቻ ተወስኖ የሚቀር መሆን የለበትም፡፡ የኢትዮጵያውያኑ ወያኔዎች መብቀያ የትግራይ ሕዝብም በተመሳሳይ ሁኔታ የዚህ ዓይነት ቆራጥ ውሳኔ በማስተላለፍ በትግራይ ሕዝብ ደምና ስም የሚነግደውን ሕወሓት/ኢሕአዲግን መቃወምና ሲቻል አካሄዱን እንዲያስተካክል ማድረግ አለበለዚያም ነጥሎ ብቻውን በማስቀረት እስካሁን ለፈጸማቸውና አሁንና ወደፊትም ለሚፈጽማቸው ታሪካዊ ነውሮችና ወንጀሎች ሁሉ ተጠያቂው ራሱ የወያኔው ጀሌ ብቻ እንዲሆን ለታሪክ አጋልጦ መስጠት ይኖርበታል፡፡
‹ዓለም አሁን ካላለፈች መቼም አታልፍም› ዓይነት ድምዳሜ ላይ መድረሴን ከፍ ሲል ጠቁሜያለሁ አይደል?
ተመልከቱ፡-
ራሽያ፣ አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ከተፈጥሮም፣ ፈጣሪ አለ ብለን ለምናምን ወገኖች ደግሞ ከፈጣሪም ሕግጋት ውጪ ‹ወንድ ከወንድና ሴትም ከሴት እንድንጋባ በሕግ ይፈቀድልን› ብለው – እንዲያው ያላንዲት ቅንጣት ሀፍረት – በግልጽ ሰልፍ የሚወጡ ዜጎች ቁጥር በጣም ብዙ እየሆነ መጥቷል (ለነገሩ የዚሁ ችግር ፍንጣቂ ወደኛም ሀገር ደርሶ መዘዙን እያየን በዝምታ ተቀምጠናለ፡፡ ጎበዝ – ይሄ ዘመን እኮ የማያሰማን ነገር የሌለው እየሆነብን ነው!)፡፡ በዛሬው ዕለት ከወደራሺያ የተናፈሰው ዜናም ይሄው ነበር፡፡ ባልጠፋ ወንድ – ሴት ሴትን ስታገባ፣ ባልጠፋ ሴት – ወንድ ወንድን ሲያገባ የዓለም የተፈጥሮ ሚዛን እንዴቱን ያህል እንደሚዛባ ይታያችሁ፤ ይህም ብቻ አይደለም – ለነገር በሚመስል ሁኔታ ሰው ፍርድ ቤት ድረስ ሄዶ ከእንስሳት ጋር ጋብቻ ልፈጽም ብሎ ሲሟገት፣ ሰው የገዛ የሥጋ ዘመዱ ጋር ካለአንዳች ሀፍረትና እንዲያውም በኩራት ስሜት ሲቃበጥ(incest)፣ ካለዕድሜው ከእምቦቀቅላዎች ጋር አለውድ በግድ አስገድዶ ሲደፍር፣ ካለወሲብ የሙያ ተልእኮውን አልወጣም ብሎ ሙያን በድሪያ ሲለውጥ … በስፋትና እንደነውርም ሳይቆጠር ልናይ የቻልነው በዚህኛው የኛ ተብዬው ዘመን ነው፡፡ እዚህ ላይ መብት ሌላ – ተፈጥሮን መቃረን ሌላ፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ የምን ምልክት ነው? ድረሱበት! ‹የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 – ምናምን› እያልኩ አንባቢን ማሰልቸት አልፈልግም፡፡ ዓለምን በጥሞና እንድታስተውሉ ግን ላስታውስ እወዳለሁ፡፡
በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሣ፡-
በአሁኑ ወቅት ዓለም በታላላቅ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ወረርሽኞች እየታመሰች ናት፡፡ ከአፍሪካ ብንጀምር – ዛሬ እኩለ ቀን አካባቢ የመካከለኛው አፍሪካ ‹ሪፓብሊክ›(Central Africa ‘Republic’ /C.A.R/) ዋና ከተማ ባንጉዪ ሴሌካ በሚባሉ አማፂያን ቁጥጥር ሥር ገባች፤ የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው አምባገነን መሪም – መቼም ስም አይገዛምና ወደ ኮንጎ ‹ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ› ሸሸ – ‹ፈረጠጠ› ላለማለት መፈለጌን አስቡልኝ – የኛም የቆዬ ጉድ ስላለ ይህን ለማለት የሞራል ብቃት የሌለኝ መሆኔን በትህትና እገልጣለሁ፡፡ በእግረ መንገድ የዕለቱን ዜና ‹እየዘገብኩላችሁ› ነው፡፡
በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ ከመቶ በላይ የታጠቁ አንጃዎች ያሉበት የሦርያ የተቃዋሚዎች ጎራ ስምምነት አጥተው እየተተራመሱ ናቸው – ለጠላታቸው ተመቹለት፡፡ አዲስ በተሾመው የተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ላይም ዋናው አንጃ ቅዋሜ አለው በመባሉ የቅንጅቱ ሊቀ መንበር ሥራውን በገዛ ፈቃዱ እስከመልቀቅ በደረሰ መልክ የውስጥ ቅራኔው ጦዟል፡፡ አሳድን ያህል ነፍሰ በላ የጋራ ጠላት አስቀምጠው ርስ በርስ እየተናቸፉ ናቸው – ሲገርሙ፤ ምን ነካቸው? የኞችም ገና ወጡ ሳይወጠወጥ አራት ኪሎ ላይ ቂጢጥ ማለት በሚፈልጉ ድንጋይ ራስ ስግብግብ ዜጎች ምክንያት ከሺዎች ቦታዎች እየተበጣጠሱ ከመጠንሰሳቸው የሚጨነግፉ፣ ከመብቀላቸው የሚጠወልጉ የትግል አምባዎች ከቁጥር በላይ ናቸው – ‹የሕዝብ አለኝታዎችና ዕንባ አባሾች!›፡፡ ይህ የሚያሳየው የሕዝብ ስቃይ ተባብሶ እንዲቀጥል የሚፈልግ የእርኩስ መንፈስ ውላጅ በየሀገራቱ ሥር በሰደደ ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡ ዓለም አታሳዝንም? እኛስ?
የሥልጣን ሱስ ከለከፈ ሳያስገድል አይለቅምና የቤናዚር ቡቶን ዕጣ ፋንታ ባይኑ በብረቱ የተመለከተው – ምናልባትም ሞቷ ባያስደስተው ያላስከፋው (የሚባልለት) የፓኪስታኑ ፐርፌዝ ሙሻራፍ መንግሥት ሊያስረው እንደሚችል እየተጠቆመና ታሊባንም በምስል የተደገፈ የግድያ ማስጠንቀቂያ እያስተላለፈለት ‹ሀገሬ ፈልጋኝ ጥሪ አስተላልፋልኛለች› በሚል የቂል ፈሊጥ ዛሬ ወደ ትውልድ ቀዬው ወደ ካራቺ አምርቷል(ሀገሩ ‹ሙሻራፍዬ ናልኝ› ብላ ጥሪ ያስተላለፈችበትን ሬኮማንዴ አልጀዚራዎች ደርሷቸው ከሆነ ባለማሳየታቸው ወይም ቢያንስ የሚመለከተውን ሰው ባለመጠየቃቸው ያዘንኩ መሆኔን እዚህች ላይ ጠቀስ ላድርግ መሰለኝ)፡፡ ለማንኛውም የነፍሰ በላዎቹን የታሊባንንና የአልቃኢዳን የአጥፍቶ መጥፋት ዘመናዊ ሥልት ልናይ የምንችልበት ‹ወርቃማ ዕድል› ከፊታችን ተደቅኗል ብለን እንገምታለን፡፡ በዚያም ላይ ‹ፍየል ሲሰባ ሾተል ያሸታል› ብለን ምራቂ ቢጤ ጣል እናድርግበት፡፡
የራሽያዊው ቱጃር ቦሪስ ማን‹ትንስኪ› ሞትም የተዘገበው ዛሬ ነው፡፡ በሰው ጣልቃ ገብነት እንደሞተ ሥጋታቸውን የጠቆሙ አልጠፉም፡፡ ይህም የሚያሳየን የገዳዮች እጅ ምን ያህል ረጂም እንደሆነና የሰው ልጅ ጭካኔ ጠርዝ መድረሱን ነው – ብዙ ሀብት ከሞት እንደማያድንም ጭምር፡፡ እንደተባለው ሰውዬው ታዋቂና ባለብዙ ሀብት ነበር፡፡ ግን ሀብትም ንብረትም ከበሬታና ስመጥርነትም እየከዱት መጥተው ‹እየደከረተ› ስለነበር ራሱን አጥፍቶ ሊሆን እንደሚችል የገለጡ ተንታኞች አሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ ሀብትም ዝናም እንደሚጠፉ መገንዘብ ከብልህ ይጠበቃልና የወያኔ ዲታዎች ከዚህ ይማሩ፡፡ እናም በልተው የማይጨርሱትን ሀብት ከማግበስበስ አባዜ ወጥተው ለሀገር ማሰብ ይጀምሩ – ጊዜ ካላቸው፡፡
ቆጵሮስ እንደግሪክና ስፔይን ሁሉ በኢኮኖሚ ምች ተመትታ አበሳዋን እያየች ናት፡፡ ምድረ አውሮፓን እንደዋግ የመታው የገንዘብ ዕጥረት ይህችን ሚጢጢዬ የደሤት ሀገር ምስቅልቅሏን አውጥቶ አብዛኛውን ሕዝቧን ለበረንዳ አዳሪነትና ለለማኝነት እንዳይዳርግ ሥጋት አለ፡፡ ከዚህ አንጻር ከተመለከትን እንደፀጉራም ውሻ አለች ሲሏት ሞታ እንዳትገኝ የሚፈራላት ታላቋ እናታችን አሜሪካም ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚገመቱ ሥራ አጦች(49 ሚሊዮን)፣ በረንዳ አዳሪዎች(3 ሚሊዮን)፣ ለማኞች፣ ሀሽሸኞችና ሀሺሻሞች፣ ቀበኞችና ዐብዶ እሚያሳብደው ኑሮ ያሰከራቸው የለዬላቸው ወፈፌዎች እንደሚገኙባት እየተዘገበ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ይዋል ይደር እንጂ ወዴት እንደሚያመራ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ 16 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ አናት ላይ ቆልሎ፣ እንደሌሎች ምሥኪን ሀገሮች ወርቅ ሳያሲዙ በእምነት ብቻ የወረቀት ገንዘብ በገፍ እያሳተሙ ዓለምን ማጭበርበር የማይቻልበት ዘመን የባተ እንደሆነ ማጣፊያው ያጥራል፡፡ ማን ነበሩ ‹ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም› የሚል መጽሐፍ የደረሱት? እዚህ ላይ ታዲያ ሞቅ ያለው ኢትዮጵያዊ ፡-
የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ፤
ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ! ብለህ እንዳትፎክር አደራህን፡፡ ‹አንቺም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ፤ እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብሽ› የሚልም አይጠፋም፡፡ የሆኖ ሆኖ የክፉ ቀን መጠጊያችን ናትና የመሥራች አባቶቿን የነጆርጅ ዋሽንግተንን ቀዳማዊ ምኞትና ህልም አስታውሶ ፈጣሪ ያስባት፡፡
ጥቂት እቀጥላሁ፤ የጀመርኩት ወሬ ጣመኝ፡፡ የሰዎች ድንቁርና ከመቼውም ዘመን በላቀ ሁኔታ እየተመሰከረ ነው፡፡ በፓኪስታን ሀገር በተደነገገ የነቢዩ መሀመድንና የቅዱስ ቁርዓንን ስም በከንቱ ማንሳትና ማጠልሸት (blasphemy) ሕግ የተነሣ እየታዬ ያለው ጉድ በዛሬው ውሎዬ ከፍተኛ የመናደጃየ ነጥብ ሆኖ ውሏል – በዜና ሳይሆን በሌላ ፕሮግራማቸው፡፡ በዚህ ሕግ ሰበብ እየተሠራ ያለው በልጆቼ ቋንቋ ‹ፊንታ› – ቃል የማይገኝለት የከፋ ወንጀል ልበለው – የፈጣሪን ቅጣት በደቂቃዎች ውስጥ ማስከተል ነበረበት፡፡ የጠሉትን ሰው በዚህ ክስ መክሰስና ሌላ ማስረጃ ሳያስፈልግ ከሳሹ ለክሱ እውነተኝነት ቁራንን ብቻ በመምታት የጠላውን ወይም በስኬቱ የተመቀኘውን ወይም የተቀያየመውንና የተጣላውን በተለይም ክርስቲያን የሆነን ሰው አንገቱን ማስቀላት ወይም በድንጋይ ማስወገር ወይም በጥይት ማስደብደብ ‹መብቱ› ነው – የዓለም ሞኝነት እንዴት ይገርማል እባካችሁን? በዚህች ዓለም ተፈጥሮ እንደሰው ከመኖር ይልቅ በእናት ማኅፀን ውስጥ ውሃ ሆኖ መቅረት እንዴት ታላቅ ዕድል ነው? በውሸት ለመክሰስ፣ በውሸት የሃይማኖት መጽሐፍን ለመምታት፣ በሀሰት ክስና ባልተረጋገጠ ‹ጥፋት› ሰውን ለመግደል የሚያስችል ምን ዓይነት ክፉ መንፈስ ይሆን የሰዎችን መላ ሰውነት የሚቆጣጠር? – ይህን ሕግ ለማሻሻል የአንድ ግዛት አስተዳዳሪ በፓርላማ ሃሳብ ቢያቀርብ በአክራሪ የሃይማኖቱ መሪዎች ጀብደኛ ስብከት አእምሮው የተጠለፈ አንድ የራሱ አጃቢ በጥይት ደብድቦ ገደለው – ሰዎች ከዶሮ የማይሻል አእምሮ ያለን መሆናችንን ሳስበው ያስደነግጠኛል፡፡ አንድ ዶሮ፣ በሌላ ዶሮ ከንቱ ስብከት ተታሎ ጓደኛውን አይገድልም – ውሻም፣ዝንጅሮም፣ጦጣም፣ቀበሮም እንዲሁ፡፡ ሰው የዶሮን ያህል እንኳን የማመዛዘን ችሎታ ቢኖረው ኖሮ ዓለማችን በተሻለ ሁኔታ ውስጥ በተገኘች፡፡ በዚህ ዓይነት ሰይጣናዊ መንገድ በሕግ የተጠለሉ አጋንንት በዚያች ሀገር ስንቱን ሕዝብ እንደፈጁ መዛግብትን አገላብጡና ተናደዱ ማለትም ተረዱ፡፡ በኢትዮጵያ የዘረኝነት ዛር ዳንኪራ እየረገጠች ምድረ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚልን ወገን አማራን ከትግሬ፣ ኦሮሞን ከጉራጌ ሳትለይ በሠይፏ እንደምትቀነጥስ ሁሉ በፓኪስታንና መሰል እስላማዊ ሀገራትም ስሟንና መልኳን ለውጣ በሃይማኖት ስም የአዳሜን አንገት ባልተወለደ አንጀት እየጨረገደች ናት፡፡ ሲዖል በዚህ – ሲዖል በዚያ፡፡ ሲዖል በላይ፤ ሲዖል በታች፡፡ ሲዖል ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ፡፡ የትም ሂድ፤የትም ግባ – ምድር አሁን የለየላት ሲዖል ሆናለች፡፡
እርግጥ ነው – መሬት ለጥቂት ብልጣ ብልጦች ምድረ ገነት ናት፡፡ ለቢሊዮኖች ግን ገሃነም ናት፡፡ እንደካርሎስ ስሊም፣ ቢል ጌትስና ዋረን ባፌ ላሉ የዓለም ማቴሪያላዊ ቁንጮ ሀብታሞች ምድር የምትንሰፈሰፍላቸው ገነት ናት (በቅርቡ የፎርብስ መረጃ መሠረት እነዚህ ሰዎች እንደቅደም ተከተላቸው 69፣ 61 እና 44 ቢሊዮን ዶላር ያላቸው የናጠጡ ከበርቴዎች ናቸው)፡፡ በርሀብና በቀላል ህክምና ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች የሚረግፈውን የዓለም ከርታታ ዜጋ ደግሞ በሌላ በእሳት የተሞላ የብረት ቅርጫት ውስጥ ሆኖ ሲጠበስና ሲገነተር አስቡት፡፡ ቆጥረው ሳይሆን አንድደውት ለማይጨርሱት ገንዘብ – ሰዎችን አላግባብ መዝብረው – ለሁሉም እኩል ባልተሰናዳ የጨዋታ ሜዳ በጭቁኖች ጉልበት ተንጠላጥለው ይህን ያህል ሀብት የሚያከማቹ መዥገሮች የዓለምን ኢኮኖሚያዊ ትስስርና የሀብትን ፍትሃዊ ክፍፍል እንዴቱን ያህል እንደሚያዛቡት፣ ዓለምን አሁን ለገባችበት አረንቋ እንዴት እንዳጋለጧትም ይታያችሁ፡፡ በነዚህ ዓይነት ሰዎች የኋላ ግፊትና ምሪት የሚሽከረከሩ መንግሥታትና ቅን ታዛዦቻቸው የመንግሥታቱ ባለሥልጣናትም ሕዝቦችን ለማደኽየት ምን ያህል ቀን ከሌት እንደሚተጉ ይታያችሁ፡፡ የዓለም አብዛኛው ሕዝብ በርሀብና በችግር ሰቆቃ እያጣጣረ በሚገኝበት ሁኔታ ስንትና ስንት በትሪሊዮንና ምናልባትም በኳትሪሊዮን የሚገመት ዶላር ለሣተላይቶች ማምጠቂያና ለሕዋ ምርምር፣ ለመሣሪያ ማምረቻና ግዥ፣ ለመከላከያ በጀት፣ ለጦርነትና ለስለላ፣ ለሥራ ፈት ፖለቲከኞች ደመወዝና ለፍሬ ፈርስኪ ስብሰባዎችና ጉዞዎች አበል፣ ፍሬያማ ላልሆኑ ስማዊ ተቋማትና አግባብነት ለሌላቸው ፕሮጀክቶች… በከንቱ ይባክናል – የዕንቆቅልሽ ዓለም፡፡ ይህ በሰለጠነ ባልሰለጠነ ሀገርና አህጉር ተብሎ የማይወሰን ሰይጣናዊ የዓለም አስተዳደር ዛሬና አሁን ያልፈረሰ መቼ ይፈርሳል? ንገሩኝ እንጂ! ‹የጨው ተራራ ሲናድ ብልህ ያለቅስ ሞኝ ይስቅ› ይባላል፡፡
አዎ፣ ይህ አሁን ያለው የዓለም ሥርዓት እንክትክቱ የሚወጣበት ዘመን በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ፍጥነት እንደአቦሸማኔ እየተወረወረ በመምጣት ላይ ነው – ጧት ላይ ይሁን ማታ፣ ተሲያት ላይ ይሁን ውድቅት ላይ ብቻ ሳይታሰብ ከች ይላል – ከማሰብ ባለፈ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው – ሃሌ ሉያ፡፡
ዘመኑ መሪም ተመሪም አቅላቸውን ስተው፣ ሰውነታቸውን አርክሰው ለዓለማዊ ፍላጎቶቻቸውና ለስሜቶቻቸው ተገዝተው ከሞላ ጎደል ሁሉም ወደሥጋ ገደል እየገቡ ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ የትኛውንም የሬዲዮንም ሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያ አሁኑኑ ክፈቱ፡፡ ምን ትሰማላችሁ? ምንስ ታያላችሁ? የሚያስደስት ወይንስ የሚያስከፋ? ለመሆኑ የዜና ጣዕማችሁስ ምን ዓይነት ነው? ይበልጥ የሚያረካችሁ የጥፋት ዜና ነው ወይንስ የልማት? አንወሻሽ – የልማትና የደስታ ምንጭ የሚሆን ዜና እምብዛም አያስደስተንም – ቢያንስ ብዙዎቻችንን፡፡ እኛ እንቅርና የዜና ተቋማቱም የሚቀናቸው የሀዘንና የመርዶ ወሬ እንጂ የደስታ አይመስልም፡፡ በ’sensational’ ዜናነት ሁሉም ተረባርቦ ሊያቀርብልህ የሚፈልገው የግድያና የዕልቂት፣የአደጋና የመቅሰፍት ዜናዎችን ነው፡፡ ያን ነው አንተም አፍህን ከፍተህ ‹ፐፐፐፐ…ወይ ስምንተኛው ሺ!› እያልክ የምትከታተለው፡፡ ሳትወድ በግድህ ‹sadist› እንድትሆን ተመቻችተሃል፡፡ እንዲህ ያደረጉህም የዕውቅ የዜና ማዕከላቱ (so called main stream media) ሥውር ባለቤቶች የአንተን መደሰት ሳይሆን መቆዘም ስለሚፈልጉ ነው፤ የነጻ ትግልን የውሻሸት ቡጢ፣ የሆሊውድንና የሌሎች -ውዶችን ትራጄዲ ፊልሞችን፣የዘፈን ግጥሞችን(lyrics)…ብታጤን ከሞላ ጎደል የሁሉም ማዕከላዊ ጭብጥ አስቆዛሚና አሳዛኝ እንጂ ለደስታ አጫሪነት የሚዘጋጁ አይደሉም – ባጭሩ እንድታዝን ካልሆነ እንድትደሰት የሚዘጋጅልህ ነገር ከስንት አንድ ነው፡፡
በዚያ ላይ በወሲብ ልክፍት እየተዳራህና በመጠጥ ስካር ጥምብዝ እያልክ ሰውነትህንና ገንዘብህን እንድትጨርስ ከትዳርህም ሳትሆን ከራስህም ሳትሆን የመርገምት ሰለባ ሆነህ መቅኖ አጥተህ እንድትቀር፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ከቀዳሚው ደገኛ የሃይማኖት መስመርህ እየወጣህ የመንገዳቸው ተጓዥ እንድትሆን በፊልሞችና በልዩ ልዩ ኦዲዮቪዥዋል ዝግጅቶች ነጋ ጠባ ትከተባለህ፡፡ ደስታቸውን ለብቻ ሀዘናቸውን ለአንተና ለመሰሎችህ ወይም ለጋራ ያደርጉልህና አንተ በሀዘን ተቃኝተህ ‹ዛሬ ደግሞ ምን ተፈጥሮ ይሆን?› ብለህ በሀዘን ስትቆራመድ እነሱ ዓለማቸውን ይቀጫሉ – ቲቪውንም አያዩት – አንተ እያለህ እነሱ ለምናቸው ብለው ይጨነቁ! አንተ የተፈጠርከው እነሱን ልታኗኑር እንጂ ቀድሞውንም ቢሆን ልትኖር እንደማይፈቅዱልህ አስተውል፡፡ የትም ኑር፣ የየትኛውም ሀገር ዜጋ ሁን ከነሱ እሥር ቤት አታመልጥም – በነሱ መሠሪነት ምክንያት ብዙዎች ይሳሳታሉ፤ ወደ ወንጀለኝነት ዓለምም ሳይወዱ በግዳቸው የሚገቡ አሉ – ያኔ በተጠመደላቸው የአሸባሪነት ክስ ይጠለፉና ለዳግም ጥቃት ይጋለጣሉ፤ ይሁንና እነሱም እኛም ያው የ‘ታላላቅ ወንድሞች’ [Big Brothers] እሥረኞች ነን፡፡ እርግጥ ነው – በዚህች ዓለም ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነውና – እሥር ቤቱ ሊሰፋ ወይ ሊጠብ፣ ይህኛው ከዚያኛው ይበልጥ ሊመች ወይ ላይመች ይችላል ፡፡ ነገር ግን ዕወቀው ምን ጊዜም በእነሱ እሥር ቤት ውስጥ ነህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ኑር፣ አሜሪካም ሂድ፣ የመለስ ውዱዳነ አንደበት ወደሆኑት ሆኖሉሉም ግባ ቲምቡክቱ መደብህ ማለትም ዕጣህ ከአብዛኛው ሕዝብ ጋር ከሆነ ግፋ ቢል በተፈቀደና ከቁጥጥር ባልወጣ ሰላማዊ ሰልፍ ስትንጫጫ ትውል ይሆናል እንጂ ያው ድሃ ነህ፡፡ ድሃ እንደሆንክም ወደመጣህበት ትመለሳለህ፡፡ አንተ ለነሱ ከቁንጫም በታች ነህ፡፡ የእነሱን መኖር ትርጉም ለማሰጠት ብቻ የምትኖር ተናጋሪ እንስሳ ነህ – ለጊዜው፡፡
ከቃለ ዐዋዲው ውጪ በሥውር ልጆችን ወልዶ የሚያሳድግ ሊቀ ጳጳስ እንደልብ በሚታይባት፣ ከየንስሃ ልጁ የሚያመነዝር ቀሲስ በሞላባት፣ ከሞቱ በኋላ በሥጋ ፈተና ሕይወት ዘርተው ዓለምን የሚቀላቀሉ መነኮሳት በተጥለቀለቁባትት፣ ካልባለቁ ወንዶችና ሴቶች ሕጻናት ሳይቀር በየቢሮው የሚሸራሞጡና የሚማግጡ ‹ታላላቅ› የሀገር መሪዎች በሚከበሩባት ፣ ፍርድ የሚያዛባ ጉቦኛ ዳኛና ካለሙስና የደም ሥሩ የማይንቀሳቀስ ባለሥልጣን በየማዕዘናቱ በናኘባት፣ የሰውን ሥጋ ካልበላ የማይጠረቃ ስግብግብ ነጋዴ በተትረፈረፈባት፣ ድሆች ሀገሮችን በቅራንቅቦ ሸቀጧ የምትወር ቻይናና በጉልበቷ ጣልቃ እየገባች ለርሷ የሚመቹ አምባገነኖችን የምትሾም አሜሪካ በነገሡባት፣ በ‹ኦስቴሪቲ ሜዠር› ሕዝብን የሚያስደገድግ የአውሮፓ ኅብረት በገነነባት፣ ለዜጎች መብት በተለይም ለሴቶቻቸው መብት ቅንጣት የማይጨነቁና መኪና እንኳ እንዳያሽከረክሩ በሕግ የሚከለክሉ የዐረብ ሀገራት እነሱ የፈጠሯቸው ያህል በሚሰማቸው ምሥኪን ዜጎቻቸው ላይ እንደልብ በሚፏልሉባት፣ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እንደጥንታዊው የሀሙራቢ ዘመን ጥፋተኛ የተባለን ዜጋ – ለምሳሌ ተራ በሆነ የወሲብ ግንኙነት የተከሰሱ ዜጎችን – በጭካኔው ወደር በማይገኝለት ኋላ ቀር የቅጣት ዓይነት አንገትን የሚቀሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሀገራት በሚገኙባት፣ ‹ያንተን ጀሃነብ የሚያስገባ ሃይማኖት ክደህ የኔን ጀነት የሚያስገባ ሃይማኖት ካልተከተልክ አትጸድቅምና ሠይፌህ አንተም እኔም ጀነት እንገባለን› ብለው የሚያምኑ ‹ሰዎች› በሞሉባት፣ ፈጣሪን ትተው ገንዘብን የሚያመልኩ ዜጎች እንደአሸን በፈሉባት፣ የጥንቆላውና መተቱ ቱማታ ሀገር ምድሩን ባስለቀቀባት፣አሰለጦች በብዙ ሺዎች በሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ተቧድነው በአፍዝ አደንግዝ ስብከታቸው እያነሆለሉ የሕዝብን ላብና ወዝ በሚመጡባት … ጎስቋላ ምድር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዛሬና አሁን ካልመጣ መቼም አይመጣም፡፡ ይህን ስል ‹ይመጣል›ን እያሰመርኩበት እንጂ እየተገዳደርኩ እንዳልሆነ በትህትና ልገልጽ እፈልጋለሁ፡፡
በሦርያ፣ በሶማሊያ፣ በኢራቅ፣ በፊሊፒንስ፣ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በህንድ፣ በበርማ፣ በአፍሪካ ብዙ አገሮች፣ በሰሜንና ደቡብ ኮሪያዎች፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ … የምናየው የሰላም ዕጦት፣ የኑሮ ውጣ ውረድና የንጹሓን ሕዝቦች ዕልቂት የምን ምልክት ነው? በአሜሪካና በአውሮፓ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ የድሆች ዋይታና ልቅሶ ማስተጋባት የምን ምልክት ነው? የዓለም ‹ለምግብ ባላነሱ ለሥራ ባልደረሱ› ሕጻናት መጥለቅለቅ የምን ምልክት ነው? ከሚሠሩ እጆች ይልቅ የሚመገቡ አፎች በምድራችን ላይ የመብዛታቸው ምሥጢር ምን ይሆን? የዓለማችን በወንጀሎችና በወንጀለኞች መጥለቅለቅ የምን ምልክት ነው? የመሪዎችና የተመሪዎች ኅሊናስነት እየተባባሰ መምጣት የምን ምልክት ይሆን? የሆዳምነትና የስግብግብነት ከወትሮው በተለዬ መስፋፋት የምን ምልክት ነው? በየሀገራቱ በስፋት የምናየው ጎርፍና እሳት የምን ምልክት ነው? በየጊዜው የሚከሰተው የመሬት መናወጥና ሱናሚን የሚያስከትል የዐውሎ ነፋስ ነውጥ የምን ምልክት ነው? የምናየው የኒኩሌር ጦርነት ዳር ዳርታ ምን አመላካች ይሆን? የምናየው የመካከለኛው ምሥራቅ ፍጥጫና የመሬት ንጥቂያ ወይም የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የምን ውጤትና ምንን ጠቋሚ ነው? ኃይለኝነት የሚሰማው ቡድንም ሆነ ሀገር ደካማውን ለማጥቃትና ለማንበርከክ ይህን ዘመን በተለዬ ሁኔታ መምረጡ ለምን ዓላማ ይሆን? የምናየው ዓለም አቀፍ የድሆች ዋይታና ሰቆቃ የምን ምልክት ነው? ጩኸታቸውንስ የሚሰማ ሰማያዊ አካል ይኖር ይሆን? ለመሆኑ በዚህን ዓይነት ከፍተኛ በችግር የመወጠር ደረጃ ዓለማችን ተቀስፋ የተያዘችበት ከአሁን ሌላ፣ ሌላ ዘመን ተመዝግቧል ወይ?
አሁን የደረሰችበትስ ዕፁብ ድንቅ የሥልጣኔ ጫፍ ለጥፋቷ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ ምን ፈየደላት? ርሀብን አጠፋ? በሽታን አስወገደ? ድህነትን ቀነሰ? ሰብኣዊ ርህራሄን አሠፈነ? በዓለም ዙሪያ ዘረኝነትን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ የሥልጣኔ ደረጃንና መሰል ሰውኛና የተፈጥሮ ልዩነቶችን መሠረት አድርጎ ሕዝብን ከሕዝብ እያባላ ያለው ማን ነው? ለምን? በተለይ አሁንና ዛሬ ለምን? ለምንድነው አቅልን የሣተ ሩጫ የበዛው? የት ለመድረስ ወይንም ምን እንዳይሆን ከወዲሁ ለማስቀረት ታስቦ ይሆን? ወይንም ምን ሳይሆን በፊት ማንን ምን ለማድረግ ታቅዶ ነው? ይህች የምንገኝባት መቶ ክፍለ ዘመን በሥልጣኔ ደረጃ ጫፍ ከመድረስና ከሌሎች ነገሮችም አኳያ ካለፉ ሺዎች ምዕተ ዓመታት ሁሉ ስትነጻጸር ለምን በጣም ተለዬች? ለመሆኑ ኮምፒውተር መቼ ተፈለሰፈ? በተራቀቀ ሁኔታ ሥራ ላይ መዋል የጀመረውስ ከመቼ ወዲህ ነው? የመሬት ውስጥ ነዳጅስ መቼ ተገኘና ለመጀመሪያ ጊዜ በየትኛው ዓመት ላይ ጥቅም ላይ ዋለ? መኪና የተሠራው መቼ ነው? ሥልክስ? ቴሌግራምስ? ፋክስስ? ኢንተርኔትና ኤሜልስ? አውሮፕላንስ? ኤሌክትሪክስ?… ግዴላችሁም ነቃ እንበል፡፡ ‹ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር› ይባላልና አንዳች ነገር እንጠርጥር፡፡ ጥላሁን ‹ያዋከቡት ነገር…› ያለው ወዶ አልነበረም ለካ…፡፡ ‹ፈራሁ፤ እኔ ፈራሁ…› ያለውስ ማን ነው? በበኩሌ ፈርቻለሁ፡፡
ግን ግን አላዊቶች ደግ አደረጉ፡፡ የኞችም ይህን ፈለግ እንደሚከተሉ ተስፋ እናድርግ – ማምሻም ዕድሜ ነው’ኮ፡፡ በቀጣይዋ ሥነ ቃል ቀመስ ግጥም ልለይ፡፡
“ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ”፤
ክልፍልፊት ዓለም ፊት ሳታዞርብኝ፤
ደጉ ዘመን አልፎ ክፉው ሳይነግሥብኝ፤
የ‹ገና ነው› ዜማ ማተቤን ሳይነጥቀኝ፤
የሕይወት መግቢያ በር አድራሻው ሳይጠፋኝ፤
“ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ”፡፡
ሰው እንደበርበሬ ሳይለወጥብኝ፡፡
korktu says
Dont exhibt your profound ignorance by reverbating what psydo and gutter presses used to dispel the derg’s venomus propaganda to dwarf the struggle against perptrators and dictator of Mengestu, by deminishing the sacrifice of the true sons and daugters of Ethiopians, as if they died just for amharic alphabets “sh” and “ch”. than a noble cause for a change of the Feudal system and of the regime usurped power by means of arms under the motto of PEOPLE PROVISIONAL GOVERNMENT. I think the writer of this piece better read more than becoming a tool of woyane who always stand long in the act of disparaging the noble struggle of the then generation. Because they never want the new generation emulate the sacrifices paid in wiping the dictators out.