የጎልጉል ወዳጅ ወለላዬ “እኚህ ሰው ማናቸው?” በሚል ርዕስ ግሩም ዝግጅት ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። ይህንን ዝግጅት በጥያቄና በግጥም መልክ የሚያቀርቡት እንደመሆኑ ምላሹም በግጥም እንዲሆን አንባቢያንን እርሳቸውም እኛም እናደፋፍራለን። ወለላዬ ከተለያዩ የግልና መሰል የህይወት ውጣውረዶች በኋላ አሁን ዝግጅታቸውን እንደገና ጀምረዋል። ጎልጉልም በደስታ እንኳን ደህና መጡ ይላቸዋል። የመጨረሻው “እኚህ ሰው ማናቸው?” ፲፫ኛው ነበር የዚያን መልስ ከአዲሱ ጥያቄ ጋር አቅርበናል። ወዳጃችን ወለላዬ በድጋሚ እንኳን ደህና መጡ ምስጋናችን ይድረስዎ።
ከዚህ በፊት ኮሎኔል ታምራት ይገዙን አቅርቤ መልስ ሳልሰጥ አቋርጨ ነበር። አሁን ከመልሱ ጋር አዲስ ልኪያለሁ
መልስ
ይዘን የቀረብነው ምስላቸውን በፊት
ይባሉ ነበረ ኮሎኔል ታምራት
ኮሎኔል ታምራት ታምራት ይገዙ
የሰሩ ሰው ናቸው ላገራቸው ብዙ።
ላሁኑ “እኚህ ሰው ማናቸው? – ፲፬” ደግሞ ወለላዬ የሚከተለውን አቅርበዋል። ምላሻችሁን በግጥም በመመለስ ለዝግጅቱ ውበት እንድትሰጡ ለማደፋፈር እንወዳለን። በሚቀጥለው መልሱን በግጥም እናቀርባለን።
የድሮውን ዘመን ታሪክ ያልተረዳ
ላለንበት ዘመን ይሆናል እንግዳ
ለምሳሌ እኝህ ሰው ባገራችን ታሪክ
በምን ስራቸው ነው የሚታወሱት ሰርክ
ብዙ አይጨነቁ ግጥም ልጻፍ ብለው
ያለውን ወርውሩ ዋናው ታሪኩ ነው።
Yimeku Tamirat says
እነድኔና እንዳንተ ስደት የቀመሱት
ለሀገር ነጻነት ተግተው የደከሙት
በአገር፣ በፍርድና በጽሕፈት ሚኒስቴር
በአሩሲ፣ ኢሉባቡር አገር አስተዳደር
ያገለገሉ ሰው ከመሆንም በላይ
ቅድስጌ ማርያምን አሠሩ በድንጋይ
በአባታቸው ቡልጌ፣ በናታቸው መንዝ
ወልደ ጊዮርጊስ ማለት ፀሐፌ ትእዛዝ።
Bombu says
ኣንቱ ኢትዮጵያዊ ተመርጦ ታሪኩ
በጥያቄ ሲቀርብ በጣፈጠ መልኩ
ጎልጉል መድረክ ሰጥቶ እኛም ስንሳተፍ
አንዳንዴ ሲቀናን ባብዛኛው ግን ሲከሽፍ
በዕረፍት የሁን ወይም በሌላ ምክንያት
በመሐል ተቋርጦ ለጥቂት ወራት
የነበረው እንካችሁ እኚህ ሰው ማናችው
ወለላዬ መጣ ሊያገጣጥማቸው
ፎⶆቸውን ከላይ የምናያቸው ሰው
ታላቅ ሐላፊነት ባገር ላይ ተረክበው
ባገር ወዳድነት አገልጋይ በትጋት
ከነበሩት ሰዎች ከሌሎች ባንድነት
የቅርብ ረዳትም እንዲሁም ወዳጅ
ከሥልጣንም ሥልጣን ከንጉሱ ደጅ
አክሊሉ ሐብተወልድ ሌሎችም ታዋቂ
ያገርን መመሪያ ለውጭው አርቃቂ
ሆነው ሲጨነቁ ሲወጡ ሲወርዱ
እኚም ሰው አሉበት ከሌሎች እንዳንዱ
ፀሐፊ ነበሩ ትዛዝም ተቀባይ
ወልደጎርጊስ አንቱ የትጉሕ ተወካይ
ብዬ ባጠቃልል እንደዝች ባጭሩ
ከምኞትም ጋር ነው ዛሬ በነበሩ»
Nibret Yalew says
እኝህ ሰው- አባታቸው ቆዳ በማልፋት የተለያዩ ባህላዊ እቃዎችን በመስራት ይተዳደሩ ነበር፡፡ እኝህ ሰው በሊሴ ገብረማረያም ትምህርት ቤት እስከ አምስተኛ ክፍል ተምረዋል፤ አዕምሯቸው ፈጠን ሲሆን፣ ፈረንሳይኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ ሰው ነበሩ፤ በጊዜው የሁለተኛ ደረጃ እና የኮሌጅ ትምህርት በአገር ውስጥ ሰለማይሰጥ ሊከታተሉ አልቻሉም፤ በስራው ዓለም በአንድ ሚኒስተር መስርያቤት የመስራት እድሉን ቢያገኙም ለትምህርት ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ፈረንሳየኛ በማስተርጎም ስራ ላይ መሰማራቱን መረጡ- እየሰሩ የቋንቋም ሆነ ሌሎች ችሎታዎችን በልምድ ሊያዳብሩ ስለወደዱ፡፡
….ከለዕታት በአንዱ ቀን መኮነን ሃብተወልድ አስም ታመው ወደሆስፒታል ስለገቡ ከእሳቸው ጋር የመተዋወቅ እድሉን አገኙ፤ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮነንም አቶ መኮነን ሃብተወልድን ሊጠይቁ በመጡበት ወቅት ስለ እሳቸው ብቃት እና ችሎታ በአቶ በመኮን አማካኝነት ይገነዘባሉ…ከዝያም በወቅቱ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ታሞ ስለነበር እኝህ ሰው እንዲያስታምሙት እና ቋንቋ እንዲያስተረጉሙ ወደፈረንሳይ ይላካሉ…. በፈረንሳይም ስለዘመናዊ መንግስት አስተዳደር፤ ስለፖለቲካ እና መስል እውቀቶችን ከተለያዩ መፃህፍተ አንብበውና ተመራምረው በእውቀት ላይ እውቀት ጨምረው ይመለሳሉ- ሰውየው በአገኙት አጋጣሚ መማር ይሻሉእና፡፡
ከዚያም (እንደ ኢትዮ. አቆጣጠር ከ1932 እስከ 1947) በመጀመርያ የአገር ግዛት ሚንስትር፤ ቀጥሎም ፀሐፊ ትዕዛዝ በመሆን የአገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ሊጨብጡ የቻሉ እና በስልጣን ዘመናቸውም ውጤታማና ፍሬያማ ተግባራትን የከወኑ፣ “በመጨረሻም ስልጣኑን ሁሉ ጠቅልሎ በመያዝ ጃንሆይን ሊፈነቅሏቸው ነው” ተብለው ስለተጠረጠሩ ከሹመታቸው ወርደው የአሩሲ ክፍለ ሃገር ገዥ ሆነው የተላኩ ድንቅ እና ታላቅ ሰው ናቸው …. በችሎታቸው እና በየአጋጣሚው ከልምድ እና ከህይወት እየተማሩ ከትንሽ ቦታ ወደ ዙፋን የተጠጉ አስገራሚ ሰው ናቸው……ፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ!!