ሀገር በብረት ሲታጠር — ‘ግንቦት ሃያህ’ ሲከበር፤
አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር — ዘመን በዘመን ሲቀየር፤
የስራ-ፈቶች ስብስብ መንጋ — ‘ፓርላማህ‘ሲከፈት ሲዘጋ..፤
ሱፍህን ገጥግጠህ — ከረባትህን ጠፍረህ፣
ወዝህን አሳምረህ — ካሜራ ፊት ቀርበህ፣
ጉሮሮህን..ጠርገህ — ፊትህ የከመርከውን ‘ሃያ ገጽ’ ገልብጠህ፣
ቁጥር እየቆጠርክ፣ አሃዝ እየጠራህ…፣
“ምናምን..ሺ.ቶን፣ ሚሊዮን ስልቻ፣
አምርተን አስገባን በዚህ ዓመት ብቻ…”፣
እያልክ ስትደሰኩር — ትንፋሽህ እስኪያጥር፣
ሰምቼህ ሳበቃ፣ የግርምት ጥያቄ እስኪማ ልሰንዝር፤
በልበ-ሙሉነት “ጠግብን በላን” ያልከው፣
ሕዝቡን ቆጥረህ ይሆን? ወይስ የቤትህን ያንተኑ ግሳት ነው?!
ስርህ ተግተርትሮ፣ ላብ እያሰመጠህ፣
ያቀረብከው ‘ሪፖርት‘ እንዲያ ተውረግርገህ፣
የራስህን በጀት፣ የጓዳህን ወሬ፣
ወይስ የምስኪኗን ኢትዮጵያ ሀገሬ?
እኮ ታዲያ የታል? የተትረፈረፈው፣
የእህል ዘር፣ የእህል ምርት..የት የተከተተው?
እባክህ ንገረን ጎተራው ወዴት ነው?!
እንደልቡ አፍሶ ሕዝብ የሚጠግብበት፣
የተትረፈረፈው…የተከማቸበት፣
ንጉስ አብዱላህ አገር ከሳዑዲ አረቢያ?
ከ’ካራቱሪ’ አገር ወይስ ከኢንዲያ?
ወይስ ከ’ሸራተን’ ከ’ሚድሮክ’ መጋዘን?
የት ይሆን ጎተራው? በነካካ አፍህ ጨክነህ ብትነግረን¡
አገር ያለውማ ሕዝቡን እሚያከብር፣
የራሱ አልበቃው ሲል ለመጥገብ ሲቸገር፣
ከሞኝ ደጃፍ ወርዶ፣ ሸጋ ሞፈር ቆርጦ፣
ባላድ፣ በስሙኒ..ጋሻ መሬት ገዝቶ፣
ያገር ደን መንጥሮ — የሰው-ሰው አባሮ፣
መሬት አለስልሶ፣ ውሃ ቦዩን ጠልፎ፣
ቀለቡን ይሰፍራል፤ ምርቱን አትረፍርፎ፤
እሱ ነው እሚያምርበት!
አደባባይ ቆሞ ለሕዝብ ቢያቀርብ ‘ሪፖርት’።
እንጂማ አንተማ፣ ክፋት-ምቀኝነት…
መቅኔህ ድረስ ዘልቆ፣ አጥንትህን ቦርቡሮ፣
መላ ሰውነትህ በጥላቻ-በእልህ..በቅንቅን ተወሮ፣
በዚያቹ በምስኪን ባዶ ጎጆው ቀንተህ፣
ያያት-ቅድማያቱን ርስት ቀዬ ነጥቀህ፣
በባዶ አንጀቱ በጥይት ቀጥቅጠህ፣
አገርህን ንቀህ፣ ወገንህን ጠልተህ፣
በ’ፌደራል ፖሊስ‘ ለባዕድ ዘብ ቆመህ..፣
ካሜራ ፊት ቀርበህ አረፋ እየደፈቅህ፣ “ጠግበን በላን” ያልከው፣
ምጸት ነው! ምጸት ነው! ለምስኪን ያገር ልጅ ሁለተኛ ሞት ነው!!
ጌታቸው አበራ
ጥቅምት 2007 ዓ/ም (ኦክቶበር 2014)
Leave a Reply