• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? እሱ ሲፈቅድ ነው? ወይስ ጌታው ሲፈቀድለት?

April 24, 2014 08:52 am by Editor Leave a Comment

አንድ

በአለፈው ሳምንት (ፋክት ቁጥር 36) ወይዘሮ መስከረም የተለያዩ መጻሕፍትን በመጥቀስ በሴቶች ላይ ያለውን መጥፎ ጫና በደንብ ያስመሰከረች ይመስለኛል፤ ግን እኮ በሴቶች ላይ ያለው ጫና የቆየ፣ ክፉና ጎጂ መሆኑን ማንም ያውቀዋል፤ ቁም-ነገሩ ያለው ከዚያ የባህል ጭነት በራስ ጥረት ወጥቶ፣ ነቀፌታንም ሆነ እርማትን ለመቀበል ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንደመስከረም በአደባባይ ሀሳብን በመግለጽ በአገርና በወገን ጉዳይ መሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ የተቻለን ሁሉ ማድረጉ ላይ ነው፤ ለዚህ ነው ይህንን መልስ የምጽፈው፤ ወይዘሮ መስከረም በአጋጠሟትና በምታያቸው እንቅፋቶች ላይ ማተኮርዋ እንደርስዋ መንፈሳዊ ወኔው የሌላቸውን ያስፈራራቸዋል እንጂ አያበረታታቸውም፤ የማንንም አፍአዊ ጫና ተቋቁመው በራሳቸው የውስጥ ኃይል እንዲመሩ እናድርግ።

አንድ መጽሐፍን በመጥቀስ ወይዘሮ መስከረም የሚከተለውን ጽፋለች፡–

ፈጣሪ የሠራውን  ውጫዊ  ገጽታን ማሽሞንሞን በቂ እንደሆነ ሲነገራት የኖረች ሴት፣ በምን ተነሳሺነት አእምሮዋን የሚመግብ  እውቀት ልትሻ ትችላለች? … በልጅነት እውቀትን  ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት በጉብዝና ወራት አላዋቂ በመሆን ቢወቀስ ትርጉም አይኖረውም፤ … ››

ወይዘሮ መስከረም ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው (ልብ በሉ ሴት አላልሁም፤) መሆንዋን እንዴት እስከዛሬ ሳታውቅ ቀረች? ባለመጽሐፉም ይሁን መስከረም የሔዋንን ታሪክ ሳያነሡ መቅረታቸው መሠረታዊ ስሕተት ነው፤ በተጠቀሱት ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አንድም እውነትን የሚመስል ነገር የለም፤ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› ከማለት በፊት የሔዋንን ሥራ ቆም ብላ ብታስታውስ የጠቀሰችውን መጽሐፍ እኔ እንደምነቅፈው ትነቅፈው ነበር፤ የሔዋን ታሪክ የሚነግረን የሚከተለውን ነው፡ ‹‹ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም  መልካም እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፤ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፤›› ዘፍ. 3

የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ ማለት ‹‹እንደእግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቁ›› ሆኑ ማለት ነው፤ አሁንም ሔዋን መስከረምና ባለመጽሐፉ እንዳቀለሏት አለመሆንዋን መረዳት ይቻል ነበር፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ሔዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛና የነጻነት እናት ነች ለማለት ይቻላል! በአንጻሩ አዳም የፍርሃት አባት ነው፤ ‹‹ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤›› ያለው እሱ ነው! ስለዚህ ወይዘሮ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› የምትለውን በድላለችና ይቅርታ መጠየቅ ሳያስፈልጋት አይቀርም!

ሔዋን የተጠቀመችው ውጫዊ ገጽታን የሚያሽሞነሙን ሳይሆን የውስጥን የመንፈስ ኃይል ቆፍሮ በማውጣት ነበር፤ በዚህ የውስጥ ኃይል ለሚጠቀም ከውጭ ግፊት አይጠብቅም።

‹‹እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት›› አይወቀስም፤ ትላለች ወይዘሮ መስከረም፤ እየተገፉ የሚገኘው ባርነት ነው፤ እውቀት የሚገኘው በነጻነት ነው፤ መገፋት ከእውቀት ያርቃል እንጂ ወደእውቀት አያስቀርብም፤ የመስከረም ዋናው መልእክት ሰላቢውን እንጂ ሰለባውን አትውቀስ የሚል ነው፣ ወይም የኔ ሀሳብ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ዓይነት ሆኖባታል፤ ለመሆኑ ሰለባ የሚሆን ከሌለ ሰላቢ ይኖራል ወይ? ሰለባ ከመሆን በፊት ሰለባ ላለመሆን መጣር አንዱ የኑሮ ዓላማ አይሆንም ወይ? ከዚህ በፊት ስለጨቋኝና ተጨቋኝ ደጋግሜ ጽፌ ነበር፤ ጭቆና የጨቋኙ ባሕርይ የሚሆነውን ያህል የተጨቋኙም ባሕርይ ይሆናል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የሚጠቅመውን ያህል ለተጨቋኙም ጭቆና ይጠቅመዋል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የኑሮው መሠረት የሆነውን ያህል ለሚርመሰመሱት የጨቋኝ ሎሌዎች ጭቆና የኑሮ መሠረታቸው ነው፤ እንዲህ እያለ ወርዶ ወርዶ የጭቆና ጠቃሚነት ለሎሌው ሎሌ፣ ለሎሌው ሎሌ ሎሌ … በኢትዮጵያ ምናልባትም የመጨረሻዋ የጭቆና ሰለባ ሚስት ትሆናለች፤ ወይም ልጆች ይሆናሉ! ጨቋኝና ተጨቋኝ የባሕርይ ቁርኝት አላቸው፤ አንዱ ያላንዱ አይኖርም፤ ወይዘሮ መስከረም ይህ እውነት ያልሆነበት ሁኔታ ወይም አጋጣሚ የምታውቀው ካለ ብታጋራን ደስ ይለኛል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤›› የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱትንና በቁማቸው የሞቱትን ሲያመሳስላቸው ነው! ለእኔ የሚታየኝ እንዲህ ነው።

መስከረም ብዙ ታላላቅ ሴቶችን ጠቅሳለች፤ በእስዋ ግምት ሁሉም በአባታቸው ወይም በባላቸው እየተገፉ ወደትልቅነት መድረኩ የወጡ ናቸው፤ አዙራ ብታየው የጠቀሰቻቸውን ሴቶች ገፉ የምትላቸው ወንዶች መጀመሪያውኑ በሴቶቹ ተገፍተው እንደነበረስ ሊታሰብ አይገባም? ምናልባት ከጠቀሰቻቸው ሴቶች ይልቅ መስከረም የሄለን ኬለርን ታሪክ ብታስታውስ ኖሮ መገፋትን አታነሣም ነበር፤ ሄለን ኬለር በሕጻንነትዋ ዓይኖችዋም ጆሮዎችዋም ሥራቸውን አቆሙ፤ የሄለን ኬለር የመንፈስ ጥንካሬ ከውስጥዋ አዲስና የተሻሉ ዓይኖችንና ጆሮዎችን እንድታበቅልና እንድትማር፣ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያዋ ሴት ምሩቅ ለመሆን እንድትበቃ አድርጓታል፤ ይህች አስደናቂ ሴት ከመቶ ሠላሳ ዓመታት ግድም በፊት ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የነበረውን አጥር ሰብራ፣ ዓይኖችዋ ባለማየታቸውና ጆሮዎችዋ ባለመስማታቸው የገጠማትን እክል አሸንፋ ራስዋን ከወንዶች በላይ ለማድረግ በቅታለች።

መገፋትን የሚፈልግ ሁሉ፣ ካልገፉት የማይነቃነቅ ሁሉ፣ ሬትን ሲግቱት ይጣፍጣል እያለ የተቀበለ ሁሉ፣ ዶሮ ማታ፣ ዶሮ ማታ፣ እያሉ አታልለው እንኳን ዶሮ የለም ሹሮ ሲሉት የማይናደድ ሁሉ፣ ምኞቱ ልደግ ልመንደግ እያለ ሲነዘንዘው በአፈና ጭጭ የሚል ሁሉ ለወቀሳ ብቻ አይደለም ለውርደትም ክፍት ነው፤ ስለዚህም ተወቅሶ ከውርደት ከዳነ ወቀሳው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፤ ዞሮ ዞሮ የሰው ልጆች ሁሉ — ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ-አሮጊት፣ ባለሥልጣን ተራ፣ ገበሬ ነጋዴ፣ ወታደር ፖሊስ፣ አስተማሪ አስተዳዳሪ፣ ዳኛ ጠበቃ፣ ሀኪም መሀንዲስ፣ … — የፈለገውን ቢሆን ላለበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የራሱና የግሉ ነው፤ ራሱን የሚገነባው ወይም ራሱን የሚንደው ራሱ ነው፤ ሰበብ እየፈለጉ ከዚህ ኃላፊነት መውጣት ቀላል ቢመስልም ተመልሶ እምቦጭ ነው፤ ዳገቱን ለመውጣት የሚመረውን እውነት መቀበል ያሻል።

በመጨረሻም በማናቸውም መንገድ፣ በማናቸውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ወደቁልቁለት የሚገፉትን ወይም የሚነዱትን ‹‹እምቢ!›› ብሎ ድምጹን ያላሰማ ገደል ገብቶ ሲንፈራፈር ከራሱ በቀር የሚወቅሰው የለም፤ አቅመ-ቢስነት ከውጭ አይመጣም።

ሁለት

አንድ በሀርቫርድ የኒቨርሲቲ ያጋጠመኝን ነገር መግቢያ ላድርገውና ልቀጥል፤ በአንድ ሴሚናር (የጥናት ውይይት) ላይ አንድ ጥቁር አሜሪካን ፕሮፌሰር ወደአሜሪካ በባርነት በመጡት አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ በመዘርዘር አስረድቶ አሁን ለእነሱ ልጆችና የልጅ ልጆች ካሣ መከፈል አለበት የሚል ክርክር አነሣ፤ ካሣውን የመክፈል ግዴታ የሚጣለው ማን ላይ ነው? ካሣውንስ የመቀበል መብት የሚሰጠው ለማን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ሳናነሣ ብዙ ሌሎች ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ — እነዚያ ከአፍሪካ በባርነት ተይዘውና ተሸጠው የመጡት ሰዎች ዛሬ የሉም፤ እነሱ በባርነት ሞተዋል፤ ዛሬ በሕይወት የሚገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ነጻነታቸውን አግኝተው ባለሙሉ መብት ዜጎች ሆነዋል፤ በአንጻሩ ደግሞ ለባሪያዎች ነጻነት የተጋደሉ ነጮች አሉ የእነዚህ ልጆች ከባሪያዎቹ ወይንስ ከጌቶቹ ወገን ይመደባሉ? ዛሬ ለልጆቻቸው ካሣ ይከፈል ማለት ልጆቹ የራሳቸውን ነጻነት ችላ ብለው ከአባቶቻቸው ባርነት ጋር እንዲቆራኙ ማድረግ አይሆንም ወይ? የባርነት ምልክቶችን ሁሉ ደምስሰው ነጻ ሰዎች ለመሆን የመጀመሪያው ግዴታ ራስን ችሎ በሁለት እግሮች መቆም ነው፤ ካሣ ክፈሉን ማለት አንደኛ ዋጋ ለማይሰጠው ነጻነት ዋጋን በማውጣት ማርከስ ነው፤ ከሰውነት ወደቤት እንስሳነት መውረድ ነው፤ ሁለተኛ በጌታና በባርያ መሀከል ያለው ግንኙነት መልኩን ለውጦ እንዲቀጥል መድረግ ነው፤ የውይይቱ ባለቤት እኔ ያቀረብሁትን ሀተታ እንዳላሰበበት ቢናገርም የእኔ ጥያቄ የተወደደ አልመሰለኝም፤ ካሣ ተቀባዮች ባርነታቸውን ካሣ ከፋዮች የባሪያዎች ባለቤትነታቸውን ጠብቀው እንደተቆራኙ መቀጠላቸው ባርነትን አያጠፋም፤ ለእኔ ጤናማ አልመሰለኝም።

ባሪያና ኃላፊነት አይተዋወቁም፤ ባሪያ ለገዛ ራሱ ኑሮም ቢሆን ኃላፊነት የለውም፤ ለምግቡም ሆነ ለልብሱ፣ ለመጠለያውም ሆነ ለቀብሩ ኃላፊነት የለበትም፤ ለሁሉም ነገር ኃላፊነቱ የጌታው ነው፤ ከባርነት መውጣት ማለት፣ ከባርነት መላቀቅ ማለት ነው፤ ለገዛ ራስ ሕይወት፣ ለገዛ ራስ ኑሮ ሙሉ ኃላፊነትን መሸከም ነው፤ ስለዚህም ከባርነት ወደነጻነት መሻገር ከግድዴለሽነት ወደኃላፊነት መሻገር ነው፤ ስለዚህም ከግዴለሽነት ወደኃላፊነት ሳይሻገሩ ከባርነት ወደነጻነት መሻገር አይቻልም! ኤልሪድጅ ክሊቨር የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው (Soul on Ice) የሚል መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ አፍአዊ ምልክቶችን ዘልቆ የሚገባ የነጻነትንና የባርነትን ባሕርያት ያሳያል፤ በአንድ በኩል በሴት ባርያና በወንድ ጌታ መሀከል ያለውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በወንድ ባርያና በሴት እመቤት በኩል ያለውን ግንኙነት በግላጭ ያወጣዋል፤ ባርነትን የባሕርዩ ያደረገ መገለጫው ለምንም ነገር ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑ ነው፤ ለምንም ነገር ሳያስብ፣ በትእዛዝ ብቻ መመራት የተመቸው ባርያ ነው።

ደግ ጌታ በራሱ ተነሣሺነትና በራሱ ፈቃድ ባሪያውን ነጻ ቢያወጣው ባሪያው ሙሉ በሙሉ ነጻ የሚሆን አይመስለኝም፤ በሕግ ነጻ ይሆናል፤ በውስጡ ግን ገና ከባርነት አልተላቀቀም፤ ከጌታው ጥገኛነት ለመውጣት ባለመዘጋጀቱ በኑሮውም ቢሆን ከጌታው አልተላቀቀም፤ ሳይለቀለቅ ከነእድፉ እንደተሰጣ ልብስ ነው፤ ተፈቅዶለት ከባርነት የወጣ ገና ነጻነትን አላገኘም፤ ከባርነት ለመላቀቅ በፍላጎቱና በፈቃዱ ወስኖ ነጻነቱን ከጌታው በግድ ፈልቅቆ ማውጣት አለበት፤ ለምን? የነጻነቱንና የሰውነቱን ቁርኝት ተገንዝቦ፣ የዜግነት እኩልነቱን ተረድቶ፣ በሰውነትም በዜግነትም ጌታህ-ነኝ ከሚለው የማያንስ መሆኑን አምኖ በቆራጥነት ሲነሣ ነው፤ የሰውነቱንና የዜግነቱን ልክ፣ የነጻነትን ትርጉምና ጣዕም አውቆ በትግል ነጻነቱን ሲያገኝ ያለጥርጥር ከባርነት ወጣ ማለት ይቻላል፤ አለዚያ ነጻነቱን በስጦታ፣ በጌታው መልካም ፈቃድ የሚያገኘው የነጻነት ሙሉ ባሕርይ አይኖረውም።

የአፍሪካን አገሮች ብንመለከት የመረረ የነጻነት ትግል የተካሄደባቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አልጂርያ፣ ዚምባብዌ ናቸው፤ እንደሚታወቀው እነዚህ አራቱም አገሮች ለአውሮፓውያን ሰፈራ የታጩ ነበሩ፤ ምናልባት በእነዚህ ዘገሮች ለነጻነት የተደረገውን ትግል መራራ ያድረገው ዋናው ምክንያት አፍሪካውያኑ አገር-አልባ ሆነው እንዳይቀሩ የነበረው ስጋት ሊሆን ይችላል፤ በአንጻሩ ሱዳን የነጻነት ትግል አልነበረም፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት ስለሆነ ቶሎ ነጻነትን በመስጠትና ወዳጅ በመፍጠር፤ በሶማልያም በኩል እንዲሁ ቶሎ ነጻነትን በማሸከም ምዕራባውያን ወደፊት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እየቀረጹ ነበር ለማለት ይቻላል፤ ግብጾች ከስንት ሺህ ዓመታት በኋላ ነው አሁን በዘመናችን ወንዶችና ሴቶች በአደባባይ ወጥተው እምቢ! በማለት ሙባረክን ያስወረዱት! ለነጻነት የመታገሉ ልምድ ስለሌላቸው፣ በዚያም ላይ ባህልና ሃይማኖት ተጨምሮበት ሙባረክን አስወርደው ነጻነትን አላገኙም፤ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ሕዝብም አጼ ኃይለ ሥላሴን አስወርዶ ነጻነቱን አላገኘም::

እያንዳንዱ ሰው የተፈጠረው ከነፍላጎቱና ፍላጎቱን ለማሟላት ካለው አዛዥነት ጋር ነው፤ ባርያ ፍላጎቶቹን ለማሟላት አዛዥነቱ የለውም፤ አዛዡ የራሱ ፈቃድ ነው፤ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሰው ወና ሰው ነው፤ ዋናውን የሰውነት ባሕርዩን ያጣ ባዶ ዕቃ ነው፤ ከባዶ ዕቃ ውስጥ የሚወጣ ነገር የለም፤ ለዚህ ነው ለነጻነቱ መታገልና በራሱ ጥረት ድልን ለመጎናጸፍ የማይችለው።

(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am
  • Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women July 4, 2025 01:48 am
  • በሞርሞን ቤ/ክ ዕርዳታ የኪዳነምህረት ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማምለኪያ ሥፍራ አገኘች July 2, 2025 01:28 pm
  • የበረከት ስምዖን “አየር ላይ ትዕይንት” አየር ላይ ተበተነ July 2, 2025 01:24 am
  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule