• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ምርጫ ቢቀርስ?!

June 1, 2015 07:07 am by Editor 1 Comment

* “በየ5 ዓመቱ ምርጫ እያሉ ህዝብን ከማሰቃየት፣ እንደነ ሰሜን ኮርያ እና ቻይና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ነው ብሎ ማወጁ ይመረጣል”

* “ኢህአዴግ ያሸነፈው ወደ ዘረፋ ስለገባ ነው እንጂ ተቃዋሚ ስለተዳከመ አይደለም”

* ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች የምርጫ ውጤቱን አንቀበለውም አሉ

* ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎች ውንጀላ መሰረተቢስ ነው ብሏል

ባለፈው እሁድ በተከናወነው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተወዳደሩ ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣የምርጫውን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ጠቅሰው የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በ442 የምርጫ ክልሎች ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ እንዳሸነፈ መግለጹን ተክትሎ  መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና መኢአድ የምርጫውን ውጤት አንቀበለውም ብለዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እጩዎች ለውድድር ያቀረበው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ምርጫውን አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፤ የምርጫውን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች በመፈጸማቸው የምርጫውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበለው ጠቁሟል፡፡

በቅስቀሳ ወቅት በአባላትና ደጋፊዎች ላይ ወከባ መፈፀሙንና በምርጫው ዕለት ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውን የጠቀሰው መድረክ፤ ጉድለቶቹንና ግድፈቶቹን ዘርዝሮ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ማመልከቱንና ምላሹን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ረቡዕ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ 442 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ያስታወቀ ሲሆን ኢህአዴግ ሁሉም ላይ ማሸነፉን ጠቁሞ፣ የተቃዋሚዎች ውንጀላ ሙሉ በሙሉ መሰረተ-ቢስ አሉባልታ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡

የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ “የዘንድሮ ምርጫ ውጤት ከ2002 ምርጫ የባሰ የሃገሪቱን ዲሞክራሲ ያጨለመ ነው” ብለዋል፡፡ “ባለፈው ምርጫ ቢያንስ ሰረቁ ነው የሚባለው፤ አሁን ግን ዘረፋ ነው ያካሄዱት” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ኢህአዴጐች በሪከርድነት የያዙትን 99.6 በመቶ ውጤት ወደ መቶ ለማሳደግ አስበው ያደረጉት ይመስለኛል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ኢህአዴግ ያሸነፈው ወደ ዘረፋ ስለገባ ነው እንጂ ተቃዋሚ ስለተዳከመ አይደለም” ያሉት የመድረክ አመራር፤ “ምርጫ በዚህ ሀገር ላይ በትክክል የማይካሄድ ከሆነ በየ5 ዓመቱ ምርጫ እያሉ ህዝብን ከማሰቃየት፣ እንደነ ሰሜን ኮርያ እና ቻይና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ነው ብሎ ማወጁ ይመረጣል” ብለዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ የምርጫ ውጤቱን ተመልክቶ “ስልጣን ወይም ሞት” የሚለውን አመለካከቱን መፈተሽ እንደሚገባው ጠቁመውም መንገዱ ብዙ ርቀት አያስኬድም ብለዋል፡፡ “ኢህአዴጎች በዚህ አካሄዳቸው ከቀጠሉ ማንንም የማትጠቅም ኢትዮጵያን ትተው እንዳይሄዱ ደግመው ደጋግመው ማሰብ አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል – ዶ/ር መረራ፡፡ “ህዝቡ ሰላማዊና ህጋዊ ትግሉን መቀጠል አለበት” ያሉት የፓርቲው አመራር፤ “ምርጫው ተጭበረበረ ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንተኛም፤ ህዝቡ ከኛ ጋር ስለሆነ ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

በምርጫው ከኢህአዴግ ቀጥሎ የተሻለ ድምፅ ያገኘው ሠማያዊ ፓርቲ ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ ምርጫው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከተካሄዱት ምርጫዎች ጋር እንኳ ሊወዳደር የማይችል እጅግ ኢ-ፍትሃዊ፣ ወገንተኛና ተአማኒነት የሌለው በመሆኑ የምርጫውን ሂደትም ሆነ ውጤት አልቀበለውም ብሏል፡፡

“ነፃነት በሌለባት ኢትዮጵያ ህዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው” ያለው ፓርቲው፤ “በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስትም በህዝብ ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እስከሚከበሩ ድረስ የነፃነት ትግሉ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም ሰማያዊ  አስታውቋል፡፡

በዘንድሮ ምርጫ የተሳተፈው ምርጫውን ሊያስፈፅሙ የሚችሉ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉ እያስገነዘበ መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ በምርጫው ምክንያት የተቃዋሚ ተወዳዳሪዎች፣ ታዛቢዎችና አባላት በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች አፈናና እንግልት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ “በህገ ወጥ አሰራሮች ታጅቦ የተከናወነ” ሲል የገለጸው የዘንድሮ ምርጫ፤ በምንም መመዘኛ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ሂደት ያልታየበት በመሆኑ ሂደቱንም ውጤቱንም አልቀበለውም ብሏል ሰማያዊ ፓርቲ፡፡

ከኢህአዴግና መድረክ ቀጥሎ በርካታ እጩዎችን ለምርጫው ያቀረበው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ በቅድመ ምርጫው ወቅት ኢዴፓ በሚዲያ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ሳንሱር እየተደረጉበት መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸውን አስታውሰው፣ በምርጫው ላይ ችግር መታየት የጀመረው በሂደቱ ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሂደቱ ወከባዎች በዝተውብን ነበር ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ በነዚህ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ፓርቲያቸው በሂደቱ መሳተፍ መቀጠሉን ጠቁመው ሂደቱ ከህግ አፈፃፀም አንፃር ዲሞክራሲያዊ ነበር ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና ኮሚኒኬሽን ኃላፊው አቶ ደስታ ተስፋሁ በሰጡት አስተያየት፤ “ሂደቱ ጥሩ ነው ብለው ወደ ምርጫው ከገቡ በኋላ ውጤት አይቶ ሂደቱ ትክክል አልነበረም ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የኢዴፓን ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች በሂደቱ አምነው ከገቡ በኋላ ህዝብ እንዳልመረጣቸው ሲያውቁ ምርጫው ተቀባይነት የለውም ማለታቸው እኛ ካላሸነፍን ከሚል አባዜ የሚመነጭ ነው ያሉት  አቶ ደስታ፤ በምርጫው ህዝቡ መብቱን በትክክል ተግባራዊ ስለማድረጉ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ታዛቢዎች ያረጋገጡት በመሆኑ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለት ለህዝቡ ውሳኔ ያለመገዛት ፀረ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ “ፓርቲዎች ህዝብ ለምን አልመረጠኝም ብለው ራሳቸውን መገምገም እንጂ ድክመታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር የለባቸውም” ብለዋል አቶ ደስታ፡፡

ከምርጫው በፊት የገዢው ፓርቲ አባላት ህግ በመጣስ ብዙ አፈናዎችና ወከባዎች ሲፈጽሙ ነበር ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት፤ በምርጫው እለት የፓርቲያቸው ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውን ጠቁመው፣ “ታዛቢዎች በሌሉበት የተካሄደው ምርጫ ተአማኒ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡ “ምርጫው ሚስጢራዊ በሆነ ሁኔታ አይደለም የተከናወነው” የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “መራጮች እየተገደዱ ሲመርጡ ታዝበናል፣ አሁንም ድረስ ታዛቢዎቻችን ለምን የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆናችሁ በሚል እየተዋከቡብን ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቅድመ ምርጫውም ሆነ የምርጫው እለት እንዲሁም ውጤት አገላለፁ የምርጫ ደንቦችንና ህጎችን ሙሉ በሙሉ የጣሰ ነው ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ምርጫ ቦርድ ከአደረጃጀት አኳያ ራሱን ሊፈትሽ የሚያስገድደው ሂደት ተስተውሏል ብለዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱ አገላለፅ ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ውጤቱን ሙሉ ለሙሉ ለምን መግለፅ እንዳልተቻለ ጠይቀዋል፡፡

“መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ ለማግኘት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም የተወሰነ ወንበር በፓርላማ እንደምናገኘን  ጠብቀን ነበር፤ነገር ግን ምርጫው አሳታፊ ባለመሆኑ አልተሳካም” ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው የሚጠብቀው ዓይነት ምርጫ እንዳልተደረገ ጠቁመውም አሳታፊ ባልሆነ ሂደት ሰላማዊ ትግሉን የትም ማድረስ እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡

ኢዴፓ ስትራቴጂውን እንደገና በመቀየር ለተሻለ ትግል እንደሚዘጋጅ በመጠቆምም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ፓርቲው በምክንያታዊነት መንቀሳቀሱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር ከፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ባለፈ በተለየ ሁኔታ መነጋገር እንደሚፈልግም ዶ/ር ጫኔ አስታውቀዋል፡፡ ሌላው የምርጫ ተፎካካሪ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ እንዲሁ፤ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ “የተሰራው ስራ ለሀገር የሚበጅ አይመስለኝም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ምርጫው ትክክለኛ አይደለም፤ አንቀበልም” ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ተስፋ የሚያስቆርጥ የምርጫ ውጤት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበባው፤ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት የማይቻል ከሆነ የፓርቲዎች መኖር ጥቅም የለውም ብለዋል፡፡ ምርጫ የህዝብ ፍላጎት በትክክል የማይገለፅበት ከሆነ የትግሉ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል ሲሉም አቶ አበባው አክለዋል፡፡

የምርጫ ውጤቱን ረቡዕ ማታ መስማታቸውን የተናገሩት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ ስለ ምርጫው መረጃዎች እያሰባሰቡ እንደሆነና አቋማቸውን ለመግለጽ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ መወያየት ስላለበት ምላሽ ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፌድሃግ) በበኩሉ፤ ህዝብ ለመረጠው አካል እውቅና እንደሚሰጥ ጠቁሞ፣ ለቀጣይ ምርጫ  ድክመትና ጥንካሬውን ገምግሞ ዝግጅት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ 442 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን በሁሉም ክልሎች ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋሮቹ ማሸነፋቸውን ገልጧል፡፡

ምርጫው በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ ያለምንም ችግር አሳታፊ፣ ፉክክር የታየበትና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ተጠናቋል ያሉት የቦርዱ አመራሮች፤ ከምርጫው ጋር የተገናኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታዎችን መሰረተቢስ ናቸው በማለት ውድቅ አድርገዋቸዋል፡፡ “በምርጫው እለት ታዛቢዎችን ተባረውብናል፣ ኮሮጆዎች ሳይፈተሹ ድምፅ ተሰጥቷል፣ ኮሮጆዎች ተቀይረዋል፣ ምርጫው ተጭበርብሯል – የሚሉት መሰረተ ቢስ አሉባልታ ነው” ብለዋል – አመራሮቹ፡፡ (አለማየሁ አንበሴ፣ አዲስ አድማስ – የዜናው ርዕስ በጎልጉል የተቀየረ)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News Tagged With: Full Width Top, Middle Column

Reader Interactions

Comments

  1. Dejene M says

    June 20, 2015 06:44 pm at 6:44 pm

    ዶ/ር መራራ በምርጫ ወቅት ፉክክር ጥሩ ነበር ነገር ግን በኦሮሞ ህዝብ ዉስጥ ኦህድድ ከደሙ ጋር ስለተቀላቀለ ከዝህ በሃላ ብዙ መድከም አያስፈልግም።

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የእምዬ ምኒልክ አዳራሽ October 30, 2023 10:27 am
  • የኢትዮጵያ መከላከያ መሥራች አጼ ምኒልክ መሆናቸውን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናገሩ October 26, 2023 01:30 pm
  • ጥቅምት 15 ለምን? October 26, 2023 01:29 am
  • “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” October 26, 2023 12:57 am
  • “ውትድርና ሕይወቴ ነው” October 26, 2023 12:13 am
  • መከላከያ በሁሉም መስክ ኢትዮጵያን የሚመጥን ኃይል እየገነባ ነው October 20, 2023 05:07 pm
  • “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትምህርት ቤት እኩል ነው በችሎታው ነው እንጂ የሚመዘነው” ፕ/ር ብርሃኑ October 20, 2023 04:47 pm
  • 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ታሰሩ October 18, 2023 04:29 pm
  • በተማሪዎች ፈተና ውጤት ለታየው ውድቀት ትምህርት ሚ/ር ኃላፊ መሆን አለበት ተባለ October 18, 2023 04:00 pm
  • ቀይ ባሕር እና ዓባይ “የኅልውና ጉዳይ ናቸው”፤ “መተንፈሻ ወደብ ያስፈልገናል” October 13, 2023 10:04 pm
  • ከ3,106 ትምህርት ቤቶች 1,328ቱ (44%) አንድም ተማሪ አላሳለፉም October 10, 2023 01:51 pm
  • “አቋጥሬ” በአማራ ክልል እያጫረሰ ነው፤ ” ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም ” ነዋሪዎች October 10, 2023 09:07 am
  • እሸቴ አሸባሪ፤ ቲዲኤፍ/ትሕነግ “ሰማዕት” – የዘመናችን ጉድ! October 7, 2023 06:47 am
  • በወልቃይት 1.1ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ ለመሰብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሠራተኛ ይፈለጋል September 27, 2023 10:42 am
  • በአማራ ክልል ሰላም ዕጦት ከ90.5 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቶች ቆመዋል September 27, 2023 08:41 am
  • ወርቁ አይተነው የሸሹት ከዝርፊያ፣ ውንብድናና ዕዳ ጋር በተያያዘ ነው September 21, 2023 02:38 pm
  • ወደ አማራ ክልል ሊተላለፍ የነበረ መሣሪያና ሰነድ ተያዘ September 19, 2023 04:35 pm
  • በትግራይ መርዶ በይፋ ሊታወጅ ነው September 19, 2023 04:22 pm
  • ጃርቶች ለምን ይጮኻሉ? September 19, 2023 04:37 am
  • “ዐቢይ ግድቡን ሸጦታል” ጌታቸው ረዳ September 11, 2023 10:18 am
  • አቶ አገኘሁ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ዋጋ እንደሚከፍሉ ተሰማ September 10, 2023 06:52 pm
  • ለዋዜማ ሬዲዮ “ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ” ያደርጋል ያላችሁት ረቂቅ ሰነድ የታለ? September 10, 2023 01:58 am
  • ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም September 8, 2023 02:31 pm
  • የትግራይ መፍረስ በርዕሰ መስተዳደሩ አንደበት September 8, 2023 02:49 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule