አዲስ በተያዘው የአውጳውያን ዓመት አሜሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ የበላይነትን ሊያረጋግጥላት የሚችል ፕሮግራም ነድፋለች፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ የሆነውን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ላይ የተነደፈውን ዕቅድ የሚያስፈጽሙ 35 የአፍሪካ አገሮችም ተመርጠዋል፡፡
ምንም እንኳን ዜናው ይፋ ከሆነ የቆየ ቢሆንም የአሜሪካንን የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) እንዲመሩ የታሰቡት ሪፓብሊካኑ ቸክ ሔግል ቀዳሚ ተወዳዳሪ መሆናቸው እስከሚገለጽ ድረስ የብዙዎችን ቀልብ አልሳበም ነበር፡፡ የአሜሪካንን ጦር ሠራዊት በየአገሩ በማዝመት ጉዳይ ላይ ጽኑ የተቃውሞ አስተሳሰብ የሚከተሉት ሔግል እንዲህ ዓይነቱን ፕሮግራም ለማስፈጸም ገጣሚ ሚኒስትር እንደሚሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ይፋ እንዳደረገው በአፍሪካ በየጊዜው እያገረሸ የሄደውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ሌሎች በክፍለ አህጉሩ የሚነሱ ቀውሶችን ለመከላከል የሚል ዕቅድ የወጣለት ፕሮግራም በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ፕሮግራም የሚያተኩረው ጦርነት ወይም ሁከት በተፈጠረ ጊዜ የአሜሪካንን ወታደሮች በየቦታው ከመላክ ይልቅ አፍሪካውያንን ለራሳቸው ችግር ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችል የአሜሪካ ወታደራዊ መኮንኖች ለአፍሪካውያኑ የተለያየ ወታደራዊ ሥልጠና ለመስጠት ወደዚያው ያመራሉ፡፡
መቀመጫውን በካንሳስ ጠቅላይ ግዛት የራይሌ ምሽግ ባደረገው በ1ኛው የእግረኛ ዲቪዚዮን ሥር የሚገኘው ሁለተኛው ብርጌድ (ወይም በልዩ ስሙ ጩቤ ብርጌድ) የሚውጣጡ አሰልጣኝ መኮንኖች በሊቢያ፣ ሱዳን፣ አልጄሪያና ኒጀር የሚገኙ የአልቃይዳ ደጋፊዎችን ዋና ዒላማ በማድረግ በቅድሚያ እንደሚንቀሳቀሱ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ከአልሸባብ ሚሊሻዎች ጋር ጦር የገጠሙትን ኬኒያና ዑጋንዳንም እንደሚያግዙ ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡
ይኸው በቡድን እየተደራጀ ሥልጠና የሚሰጠው የወታደራዊ መኮንኖች ስብስብ በአንዳንድ ቦታዎች በጥቂት መኮንኖች ብቻ በሌሎች አገሮች ደግሞ በመቶዎች በመሆን ሥልጠናውን እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡ መኮንኖቹ ሥልጠናውን ለመስጠት በሚቆዩበት ጊዜያት ሁሉ የባህል፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ፣ ወዘተ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚላኩበትን አገር በተመለከተ የአጭር ጊዜ ሥልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ አላላካቸውም ጥቂት በጥቂት ይሆናል፡፡
በፕሮግራሙ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ጄኔራል ሬይመንድ ዖዲዪርኖ አሜሪካ ከዚህ በፊት የነበራትንና አሁን በአዲሱ ፕሮገራም የሚኖራትን ሚና ሲገልጹ “ከዚህ በፊት ስንከተል የነበረው ስትፈልጉን ጥሩን ዓይነት ነበር፡፡ አሁን ግን ከዚያ ባለፈ መልኩ” እንደሚሆንና ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር በስፋት የተለየ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካን የዕዝ ማዕከል (አፍሪኮም) እንዲመሩ የታጩት ጄኔራል ዴቪድ ሮድሪጌዝ በበኩላቸው ሲናገሩ “እኛ እዚያ የምንሄደው የእኛ አሠራር እንዴት እንደሆነ ልናሳያቸው አይደለም፤ የራሳቸው አሠራር እንዴት ተግባራዊ መሆን እንደሚችል ለማስተማር ነው፡፡ የጦር ሠራዊታቸው አሁን ያለበትን ሁኔታ ከተመለከትን በኋላ የት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለበት እናሠለጥናቸዋልን፤ እናዘጋጃቸዋለን” ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ወዘተ ብርቅ በሆነባት አፍሪካ ይህ ዓይነቱ የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ በአምባገነኖች የተሞላውን አህጉር የበለጠ ጨለማና ተስፋ ቢስ እንደሚያደርገው የአፍሪካ ጉዳይ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብዛኛዎቹ አምባገነን መሪዎች ህዝባቸውን ለመርገጥና በሥልጣን ለመቆየት የአሜሪካ ወዳጅ መሆን እንዲሁም ይህንን ዓይነት በቀዳሚነት የአሜሪካንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ወታደራዊ የበላይነት በአገራቸው እንዲካሄድ መፍቀድ ቀላሉ መንገድ እንደሚሆናቸው አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
ሟቹ ጠ/ሚ/ር በአገር ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ሶማሊያንን በመውረር የአሜሪካ ጠንካራ ወዳጅ በመሆን በሥልጣን ለመቆየት አማራጭ እንዳደረጉት አሁን ያሉትም ሆነ ሌሎቹ አምባገነን መሪዎች ይህንኑ መስመር እንደሚከተሉ ከተለያዩ የዜና ምንጮች የሰበሰብነው የአፍሪካውያን ምሁራን አስተያየት ይጠቁማል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትን አሸባሪዎች ሳይሆን በአገር ውስጥ የዴሞክራሲ፣ የመብት፣ ወዘተ ጥያቄ የሚያነሱ ሁሉ በአሸባሪነት እየተፈረጁ ለሥቃይ የተዳረጉበት፤ መብት ረገጣው የተስፋፋበት እና ምዕራባውያን ከዝምታ ወይም ከውግዘት ያላለፈ ጠንካራ እርምጃ ሊወስዱ የማይፈልጉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡
የአፍሪካንን ጉዳይ በቅርብ በሚከታተሉ ዘንድ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ይኸው የአሜሪካ ወታደራዊ የበላይነት በይፋ ከተነገረው አሸባሪዎችን የማጥቃትና የመቆጣጠር ዋና ዓላማ ሌላ ዕቅድ አለው የሚል የመከራከሪያ ነጥብ ቀርቦበታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረግ አፍሪካን እየተቆጣጠረች የመጣችውን የቻይናን እንቅስቃሴ በቅርብ ሆኖ ለመከታተል እንዲያመች ነው የሚል ጠንከር ያለ አስተያየት በእነዚሁ ወገኖች ተሰጥቶበታል፡፡ ከአሜሪካ ጋር በወታደራዊ ስምምነት በመተባበር ወይም ከቻይና ጋር በኢኮኖሚ በመተሳሰር በየትኛውም መልኩ ቢሆን የአፍሪካ አምባገነኖች የአገዛዝ ዘመናቸውን የሚያረዝሙበት ምቹ አማራጭ ማግኘታቸው ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡
ፕሮግራሙን በተመለከተ ከአፍሪኮም እስካሁን ወደ መቶ የሚጠጉ የምደባ ጥያቄዎች መቅረቡን የተናገረው የዜና ዘገባ ዝግጁ የሆኑትና ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁት የመጀመሪያዎቹ ወታደራዊ መኮንኖች በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ አፍሪካ እንደሚያቀኑና ጨምሮ አስታውቋል፡፡ (ፎቶ፡ sott.net)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
ሙስጠፋ says
የለየለት የ 21ኛው ክፍለዘመን ቅኝ ግዛት! ከእንግድህ ዘርፈውና ገለው የማይጠግቡት የአፍሪካ መሪዎች አጋጣሚውን በመጠቀም እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ሁኔታ በደንብ ተመቻችቶላቸዋል። ካሁን በኋላ <> ሁሉ በአፍሪካ አንባገነን መሪዎች አሸባሪ እየተባለ ለአጋራቸው ለአሜሪካኖች ሪፖርት ይደረጋል። ዎቸሁ ጉድ! አሜሪካ ስለ አፍሪካ ህዝብ ተጨንቃ በእያንዳንዱ አገር ወታደሮቿን አሰማርታ ልጠብቀን አቀደች። ለመሆኑ አፍሪካ ውስጥ ከአፍሪካውያን መከላከያ አቅም በላይ ገዝፎ የሚታይ ስጋት አለን? ምን አይነት ማጭበርበር ነው እየተሰራ ያለው? መቼም ለፖለቲከኞች ማማካኛ አልቃኢዳ እሚባል ስም ስላለ የፈለጉትን በዚህ ስም ሽፋን ለማድረግ አመችቷቸዋል። እኔን እንቆቅልሽ የሆነብኝ ሌላው ቀርቶ በአለም ላይ እዚህ ቦታ ይህ ነው እሚባል ጽ/ቤት እንኳ የለለው በስም ብቻ የነገሰው አልቃኢዳ ለሁሉ ነገር ማማካኛ የመሆኑ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ኡማር ማለት እንደዚ ነው።
danny says
Great post.
zobbel says
ሙስጠፋ በጥሩ አስቀምጠኸዋል። ይህ ነው መጠየቅ ያለበት ጉዳይ። ሁልጊዜም አፍሪካን “ልናሰለጥን” “ለአረመኔው ሃይማኖት ልናስተምር” “ከኮሚኒዝም (ከሶቪየት) ጥቃት ለመከላከል” በሚሉ ቅንብሮች ነበር ባልሰራችው የሰው ማጥፊያ መሳሪያ ስትታወክ የኖረችው በመሆኑም ባለችበት እንድትቀር ያደረጓት። በመጨረሻ የኮሚኒስስት አገሮች ቁንጮ የነበረው አገር ሰልፍ ሲያሳምር ደግሞ እንደ ሶስታ ዓመት እድሜ ህፃን ልጅ “አልካይዳ” ከሚባለው ቡጊ ማን (boogeyman) ልንጠብቃችሁ ነው ይባላል። ጥቃቱ መጨረሻ የለውም። ክፍለ ዓለምን ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የሆነውን የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ ጭምር ነው።
The-Secret says
ትልቁ ችግር ብዙዎቹ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ፖለቲከኞችና ምሁራን እጅግ ሲበዛ ውሸታሞችና ለህሊናቸው ሳይሆን ለሆዳቸው ያደሩ ስለሆነ እውነቱን አይናገሩም፡፡የአሜሪካ በአፍሪካ የወታደራዊ የበላይነት ብሎ አይነት አነጋገርም በራሱ የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ይህ አሁን ምን የሚሉት ዘገባና እርእስ ነው?ለምን ጎልጉል እውነቱን አይናገርም?እርእሱ መሆን የነበረበት “አሜሪካ የጥንቱን የአውሮፓውያን ቀጥተኛ ቅኝ ግዛት አሁን በአዲስ መልክ በዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት እያስቀጠለች ነው::” መባል ነበር ያለበት፡፡ሊቢያን ሲወሩ አምባገነንነትን ለመዋጋትና ዲሞክራሲን ለማስፈን ብለው እንደ አዳኝ መሲህ ተመስለው ነው ጋዳፊን ከስልጣን ያስወገዱት፡፡አምባገንንም ቢሆን ቅሉ ግን ፓን አፍሪካኒስት የሆነው የጋዳፊ መኖር ለአሜሪካና ምእራባውያን ላቀዱት የቅኝ ግዛት መስፋፋት ትልቅ እንቅፋት ስለሚሆን ጋዳፊን አስወገዱና አሁን ቀጥተኛ ወረራቸውን በአሸባሪነት ሽፋን እያከናወኑት ነው፡፡ጋዳፊንም ሲወሩ “No-Fly-Zone” የሚል ሲሰሙት ለስሜትና ለአእምሮ የሚመችና ቀለል ያለ አባባል ወይንም “Euphemism” በመጠቀም ነበር ወረራውን በኔቶ አማካኝነት ያከናወኑት፡፡ታዲያ ድሮውነስ እንደ ድሮው ወራሪ ጣሊያን አፍሪካን ዳግም ቅኝ ልንገዛ ነው የመጣነው ብለው አሜሪካና አውሮፓውያን ዳግም እንዲመጡ መጠበቅ እጅግ የለየለት የክፍለ ዘመናችን ታላቅ ምሁራዊ ደደብነት(Intellectual Ignorance) ነው፡፡በዘመነ ቀዝቃዛው ጦርነት አፍሪካንና ታዳጊውን አለም ለመውረርና የማይፈልጉትን አገዛዝ ገልብጦ የሚፈልጉትን ቅጥረኛ አገዛዝ በምትኩ ስልጣን ላይ ለማውጣት ኮሙኒዝምን መዋጋት የሚለው ሰበብና ምክንያት ነበር፡፡አሁን ያ የቀዝቃዛው ጦርነት የለም ሌላ አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት ግን እየተፈጠረ ነውና ከኮሙኒዝም ሌላ ሰብብና ምክንያት ሲጠፋ አዲስ ልእለ ሃያል እየሆነች ከመጣችው ከእንደ ቻይና ጋር ያለውን የአለም የተፈጥሮ ሀብት ቅርምትና ፉክክር ለማከናወን የግድ ሌላ ሰበብ መፈጠር አለበት፡፡ይህም በቦታና በጊዜ ገደብ የሌለውን አንድ አሸባሪነት የሚባል መናፍስት መፍጠር ግድ ሆነ ማለት ነው፡፡የአለም ታሪክንና የአገዛዞችን መሰሪ አሰራር በቅጡ ለመረመረ በእርግጥ ይህ ስልት አዲስ አይደለም፡፡ወያኔም የሚወስደውን እርምጃ ህጋዊ ሽፋን ለመስጠትና ከህዝብ ዘንድ ቅቡልነትንና ድጋፍን ለማግኘት ሲል ብዙ ወንጀሎችን እንደሚፈፅም የአደባባይ ሚስጥር አይደለም እንዴ?ማለትም ህገ-ወጥ ስራን ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የግድ አንድ ሰበብና መክንያት መፈጠር አለበት፡፡ስለዚህም አሸባሪነትና አሸባሪነትንም መዋጋት የሚባለው ነገር በብዙሃኑ ዘንድ ሰሙና ወርቁ በቅጡ ያለየ ነገር ነው፡፡ስለዚህም በአንድ በኩል አሸባሪነት አለ በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪነት የሚባል ነገር የለም፡፡ስለዚህም በአጭሩ ወደ ነጥቡ ስንመጣ አሁን በአሸባሪነትና አሸባሪነትን መዋጋት በሚባል ሽፋን በአለም ላይ በአሜሪካና ምእራባውያን በረቀቀና በተቀነባባረ መንገድ እየተፈፀመ ያለው ዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ወይንም Neo-Colonialism ነው፡፡ይህንን ለመጠርጠርና ለመረዳት ያልቻለ ሰው ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረረው አሸባሪነትን ለመዋጋት ነበር ብሎ የማሰብ ያህል ነው፡፡ነው ወይነስ ቢሮ ውስጥ በአንድ ወንድ ጎልማሳ ሌላ አይነት ስራ የተሰራባት ወጣት እስከዚህ ድረስ አልጠረጠርኩም ነበር ስትል እንደነበረውና አይ የለም ስታረግዥ ትጠረጥሪያለሽ እንደተባለው አይነት ቀልድ ነው?የውስጥ አገዛዞች በትንሽ በትልቁ ለስልጣን በተናቆሩ ቁጥር የውጪ ወራሪ ሃይል መግባት አለበት የሚባል ከሆነ አቅጣጫው ወዴት ነው? እረ ጉድ ነው ጎበዝ የሌላውን እያወራን የኛን ጉድ እረሳነውሳ፡፡በቅርቡ እኮ የተከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በአሸባሪዎች የተከበበች ነች ብለውን የለም እንዴ?ስለዚህም አሸባሪነትን መዋጋት በሚል ሽፋን እኛም ነገ ከነገ ወዲያ እንደ ሶማሊያ በአሜሪካኖች ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (Drone Attack) እየተቀጠቀጥን አበሳችንን ልናይ ነው ማለት ነው?እረ ይቅርታ ይህ አይነት ወሬ ለህዝብ በዚህ ወቅት አይወራም እረ ምክንያቱም ደግሞ አሁን ወቅቱ ስሜታችንን የገዛው የአፍሪካ ዋንጫ እኮ ነው፡፡በዚያ ላይ ደግሞ ብሄራዊ ቡድናችን 1 ለ 1 ስለወጣና እኛም በዚህ የደስታ ስሜት ተጥለቅለቀን ይህ አይነት ሙድ ሰራቂ ወሬ በዚህ ወቅት መወራት የለበትም፡፡ብዙሃኑ ህዝብ ደግሞ ሙዱንና ስሜቱን የሚጠብቅለት አገዛዝ ነው እንጂ የሚፈልገው ይህ አይነት መርዶ ነጋሪና ለአእምሮና ለስሜት የማይመች ነገር አይወድም፡፡አዎ ጲላጦስም እኮ ክርስቶስን ልፍታላችሁ ወይንስ ወንበዴውን በርባንን ብሎ ሲጠይቅ ህዝበ አይሁዳውያን ለጲላጦስ የሰጡት ምላሽ አይ ወንበዴውን በርባንን ፍታውና በምትኩ ክርስቶስን ስቀለው ነበር ያሉት፡፡ወያኔም ይህችን የኢትዮጵያ ህዝብ ባህሪ በቅጡ የተረዳ ይመስላል፡፡ስለዚህም ብዙወን ጊዜ አንድ ተንኮል ሲያስብ ቅድሚያ የህዝብን ቀልብና ስሜት ወደ አንድ ቀልብ የሚስብ ጊዚያዊ ነገር እንዲያተኩር ያደርጋል፡፡በአለም ላይ ያሉትም መሰሪ አገዛዞችም የዋህና ልብ ያልገዛውን በስሜት የሚመራውን ብዙሃኑን ህዝብ በዚህ መንገድ ነው የሚጫወቱበት፡፡
ስለዚህም ዛሬ አፍሪካ በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ ወደ ዳግም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማጥ ውስጥ ስትገባ አሸባሪነትን መዋጋት ነው እየተባለ እንደ ዋዛ እየተነገረን ነው ማለት ነው፡፡ምናልባትም መለስ አንድ ወቅት ላይ መጪው ዘመን ለአፍሪካ የድቅድቅ ጨለማ ዘመን ነው ያሉት አባባል ምናልባትም ሳይታወቃቸው በተዘዋዋሪ ይህ ነገር እንደ ነቢይ በውስጣቸው ታይቷቸው ጭምር ይሆንን?
እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና አለምን ይባርክ !!!
Oumer says
The secrit ena mustef betkkl abrartachhutal