በጋሞ ጎፋ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ አልጌ ቀበሌ ፖሊስ በንፁሃን ላይ የጭካኔ እርምጃ መውሰዱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በአባያ ሀይቅ ዙሪያ በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩት ነዋሪዎች መሬት ትንባሆ ለሚያለማ ባለሀብት እንደተሰጠባቸው መነገሩን ተከትሎ የአካባቢው ሽማግሌዎች ከሶስት ጊዜ በላይ ለክልሉ አስተዳደር ማመልከቻ ቢያስገቡም መልስ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ አስተዳደር ምንም አይነት መልስ ባይሰጥም የዞኑ አስተዳደር “መሬቱ ትንባሆ ለሚያለማ ባለሀብት ተሰጥቷል” የሚል ውሳኔ በማስተላለፉ ነዋሪዎቹ ይህን የዞኑን አስተዳደር ውሳኔ እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ ይህን የህዝቡን ተቃውሞ ተከትሎም ፖሊስ በአባያ ነዋሪዎች ሰፈር እየመጣ እያስፈራራ እንደሚመለስ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የካቲት 30/2007 እንደተለመደው ፖሊስ ነዋሪዎቹን ለማስፈራራት ወደ ሰፈር በሄደበት ወቅት ነዋሪዎቹ ፖሊሶቹን “ከሰፈራችን ውጡልን!” እንዳሏቸው ተገልጾአል፡፡ ይሁንና ፖሊስ ከሰፈራቸው እንዲወጡለት የጠየቁትን አዛውንቶችን ጨምሮ ነዋሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ ተገልጾአል፡፡ ፖሊስ አዛውንቶቹ ላይ ድብደባ መፈጸሙን የተቃወሙ ወጣቶች ላይ ጥይት በመተኮስ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ወስዷል፡፡ በወቅቱም አንድ ሰው ሲሞት ከ8 ሰዎች በላይ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ተገልጾአል፡፡
እስካሁን ድረስ በንጹሃኑ ላይ የጭካኔ እርምጃ የወሰዱት ፖሊሶች ምንም አይነት ህጋዊ እርምጃ እንዳልተወሰደባቸውና በስራ ገበታቸው ላይ እንደሚገኙም የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ ፌስቡክ ገጽ)
Leave a Reply