ወርቅነህ ገበየሁ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን በህወሃት ተሹሟል። ይህ ከታማኝ ምንጭ የደረሰን መረጃ ነው። መረጃው እንደሚጠቁመው፤ እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ሹመቱን ያጸደቁለት፤ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገና በስልጣን ላይ እንዳሉ ነበር። የህወሃት ሰዎች፤ “የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሃገሪቱ አሁን የገባችበትን አስከፊ ችግር ይፈታል” የሚል ቅኝት ይዘው ወደ ምዕራቡ አለም እንዲሰማሩም ተደርጓል። ከሀገሬው ሕዝብ ይልቅ የአሜሪካ እና የአውሮፓን ልብ መግዛት ከቻሉ ለተለመደው የበጀት ድጎማ ዋስትና ያገኛሉ። ሁሉም ወገኖች ሳይስማሙበት በሸፍጥ የተፈጸመው ይህን ሹመት ከአሜሪካ ባለስልጣናት ይሁንታ አግኝቷል ተብሏል። የአሜሪካ መንግስት ይህንን ሹመት ለመቀበል ሁለት ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ምክንያት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሮሞ ስለሆነ የተቀሰቀሰውን የቄሮ አመጽ ሊያስቆም ይችላል በሚል የተሳሳተ መረጃ ሲሆን ሁለተኛው እና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ አገዛዙ የኢትዮጵያን ሳይሆን ይልቁንም የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ፍቃደኛ በመሆኑ ነው።
የወያኔ ባለስልጣናት “እኛ ከሌለን ሃገሪቱ ትበታተናለች!” የሚል የማስፈራርያ መፈክር ይዘው ምእራባውያንን ለሶስት አስርተ-ዓመታት ሲደልሉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ራሳቸው እያጠናከሩ ያሉትን አልሻባብ ማንሰራራት እንደ አጀንዳ ይዘው ብቅ ብለዋል። በያዝነው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራ አንድ ቡድን በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በመገኘት፤ አገዛዙ ከተወገደ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚኖራት ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ውስጥ እንደሆነ ገለጻ አድርጓል።
የአሜሪካ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን መቃወሟ ይታወሳል። ይህ ተቃውሞ ለሁለተኛ ግዜ መሆኑ ነው። የአስቸኳይ ግዜ አዋጆችን ብቻ ሳይሆን አገዛዙ የሚያወጣቸውን አፋኝ ህጎች እና አዋጆች ሳይቃወሙ ያለፉበት ግዜ የለም። የመለስ መስተዳደር አልሻባብን ለመምታት ሶማልያን በወረረ ግዜም አሜሪካ በአደባባይ ተቃውሞዋን አሰምታለች። ይሁን እንጂ የወረራ ትእዛዙ ከአሜሪካ በስውር እንደመጣ ወደ ኢትዮጵያ ይገባ የነበረው ወታደራዊ ቁሳቁስ ምስክር ነው። አሜሪካኖች ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲፈጸም ለማስመሰል ይቃወማሉ እንጂ በተግባር አንድም እርምጃ ሲወስዱ አይታይም።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የችግሩ ቁልፍ መሆናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረው እንዲወርዱ መደረጉ በድንገት የመጣ ዱብ-እዳ እንደ ነበር አሁን ይፋ እየሆነ ነው። ሃገሪቱ ለገባችበት ውስብሰብ ችግር፣ መፍትሄው የእሳቸው ከስልጣን መውረድ መሆኑን በብሄራዊ ቴሌቭዢን ተናግረው እንዲወርዱ ማድረጋቸው አሳማኝ ባይሆንም፤ አቶ ሃይለማርያም ይህን ከማለት ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳልነበራቸው ተገልጿል።
ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ወርቅነህ እንዲሆን ህወሃት ወስኗል። ሙሉ ስሙ ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን ሲሆን፣ ለምርጫ ቦርድ ያስመዘገበው ግን ወርቅነህ ገበየሁ ነገዎ ነው። የአያቱን ስም አንዳንዴም “ነገዬ” ይለዋል። “ነገዎ”ም ሆነ “ነገዬ” – ሁለቱም በማጭበርበር ኦሮሞ ለመሆን የወጡ ስሞች ናቸውና ለውጥ አያመጣም። ይህ ሰው ከየት ተነስቶ አሁን ያለበት ስፍራ እንዴት እንደደረሰ ከዚህ ቀደም በስፋት ስለሄድኩበት አሁን አልደግመውም።
በሙስና ታስሮ ከነበረበት የሻሸመኔ እስር ቤት በድንገት ተጠርቶ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነርነት ማዕረግ ሲሰጠው፤ ጥቂት እንኳ አልተግደረደረም። ዘሩን እና ሸሚዙን ቀይሮ ወንበሩ ላይ ቁጭ አለ። ከዚያ በስሩ ከነበረው ከሃሰን ሽፋ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ማስፈጸም ሙሉ ስራው አደረገ። አፈናው፣ ቶርቸሩ፣ ግድያው ሁሉ በኦህዴድ ስም፣ በኦሮሞ ስም ይፈጸም ነበር። ኮሚሽነር ሆኖ ከፈጸመው እጅግ የከፋ ወንጀል መካከል በምርጫ 97 ወቅት በሕዝብ ላይ የደረሰው ስቃይ እና ግድያ ይጠቀሳል። በዚህ ዙርያ ተሰይሞ የነበረው አጣሪ ኮሚሽን ያሰባሰበው ዘግናኝ ዘገባ ለታሪክ ተቀምጧል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ማንገራገራቸው ለስልጣናቸው መልቀቅ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። በዚህም ምክንያት “ለዘብተኛ” የሚል ስም ወጥቶላቸዋል። ህወሃቶች ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን የፈለጉበት ምክንያት በአመራር ብቃቱ እንዳልሆነም ግልጽ ነው። “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” እንዲሉ በእጁ ላይ ቀድሞ የሰራው የሙስና ወንጀል እና ደም ስላለ፣ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም በሚል እሳቤ እንደሆነ ይነገራል።
ሃገሪቱ አሁን የገባችበትን ችግር ልትላቀቅ የምትችለው ሕዝብ ላይ በደል የፈጸመን ሰው መሪ ማድረግ አይደለም። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሕዝብን የባሰ ያስቆጣዋል እንጂ እነሱ እንዳሰቡት ፍርሃት እንዲያድርበት አያደርግም። ይህንን አድርጎ ስለ ሰላም ማሰብ፣ ይህንን እያደረጉ በስልጣን መቆየት፣ ፈጽሞ የማይታሰብ እንደሆነ ሕዝብ በተግባር እያሳየ ይገኛል።
ሃገሪቱ ብሄራዊ ችግር ውስጥ ነች። ወያኔ ይህንን ብሄራዊ ቀውስ እንደ እድል ተጠቅሞ ለእውነተኛ ብሄራዊ መግባባት ቢጠቀምበት ለራሱም ይበጀው ነበር። እንደ ለማ መገርሳ ያሉ አስታራቂ ሚና እየተጫወቱ ያሉ፣ ሕዝብ የሚፈልጋቸውን መሪዎች ወደ መድረክ የማምጣቱ እድል አሁንም አለ። ኳሱ በነሱ እጅ ላይ ነው። ሰዓቱ ሳይረፍድ ይህንን እውን ማድረግ ይችላሉ። ይህ ዕድል ካመለጣቸው ግን አወዳደቃቸው የሚያምር አይሆንም።
ምዕራቡ አለምም ቢሆን የሃይል ሚዛን እያየ ነው የሚቀየሰው። ከግብጹ ሆስኒ ሙባረክ እና ከቱኒዥያው ቤን አሊ የበለጠ የአሜሪካ ወዳጅ አልነበረም። በነዚህ አንባገነኖች ላይ ሕዝብ ሲነሳባቸው፣ አሜሪካም ተነሳች!
ክንፉ አሰፋ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Alem says
መለስ የሞተ ሰሞን ለሦስት ወር ህወሓት ግራ ተጋብቶ ነበር። ስብሃት አንድ ነገር ይላል፤ ቀጥሎ በረከት። የተደራጀ ተቃዋሚና ጥሩ መሪ ስላልነበረ ወቅቱ ባከነ። ህወሓት ሕዝቡን ሲቻል በገንዘብ፣ ካልሆነም በትዛዝ ከየመስሪያ ቤቱ ቲሸርት አስለብሶ ለቅሶ አስወጣ። የመለስ ሞት እንግዳ ነገር ስለነበረ ገሚሱ ጮቤ ሲረግጥ ህወሓት በግርግር መሓል ዕድሜውን አራዘመ።
አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በስድስት ወር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተዘናግቶ ትግሉን ማቋረጥ የለበትም። በአዋጁ ማግሥት ጎንደር አድማ መምታቱ ትክክለኛ ሂደት ነው። በኦሮምያም መቀጠል አለበት። ትግሉን ማብረድ ትልቅ ስህተት ነው። የዓለም መንግሥታት (አሜሪካና አውሮጳን ጨምሮ) የህወሓትን ዱሪዬነት ችላ ማለት የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል። ሌላኛው፣ ዶ/ር ብርሃኑና ግንቦት ሰባት እንዳበቃላቸው ማወቅ አስፈላጊ ነው። የሚንደፋደፉት ዶ/ር ብርሃኑ የአንድ ቡድን መሪ መሆን ስለሚፈልግ እንጂ ከሚካሄደው ትግል አንጻር ምንም ፋይዳ አይኖረውም። ለኢሳይያስ ቀዳዳ ከፍቶ አገራችንን ለሦስተኛ ዙር ውንብድናው አሳልፎ ለመስጠት ካልሆነ።
ትግሉ በኢኮኖሚና በፖለቲካ እኩልነት ተሳትፎ ላይ ማተኮር አለበት። ትግሬና አማራ ኦሮሞ መሪ ሆነ አልሆነ ጉዳይ አይደለም። ህወሓት የሳተው ሁሉን የትግሬ በማድረጉ ነው። አንድ ምሳሌ፣ ትግራይ ውስጥ ከየትኛውም ክልል ሄዶ ንግድ ማቋቋም አይችልም። የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ፣ በኦሮምያ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ ወዘተ ንግድ አላቸው። የአንበሳ አውቶቡስ የክፍለሃገር አገልግሎት በህወሓት “ሰላም” አውቶቡስ መተካቱ። “ሰላም” አውቶቡስ በህወሓት “ሜቴክ” መገጣጠሙ፤ “ሜቴክ” በመንግሥትና በኤፌርት ድጎማ መንቀሳቀሱ። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ከ20 ዓመት ወዲህ የትግራይ ተወላጆች እንዲሠፍሩ መደረጉ። የወርቅ ንግድ፣ የቀርቀሃ፣ የከተማ መሬት ይዞታ፤ ወዘተ ጉሙዝ በርታና የወሎ፣ ወዘተ ተወላጆች ተገፍተው ባንድ ቡድን እጅ መደረጉ። ጋምቤላን ለትግራይ ተወላጆች ከመቆጣጠሩ በፊት በጋምቤላ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋና ማፈናቀል አደረሰ። በዘራፊው አላሙዲን በኩል ወርቁን ለሙን ምሬት ኢንዱስትሪውን መርጦ በውስጃ ገዛው። ትርፍ ከህወሓት ጋር የሽርክና ሆኖ ማለት ነው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ጦር ሠራዊት ወዘተ ሌላ ኢትዮጵያዊ እንደ ባዕድ ተቆጥሮ መገለሉ። ይኸ የተዘረዘረው መቆም አለበት። በፖለቲካው አንጻር። ህወሓት ዋነኞቹ የኢሕአዴግ አባላት ኦህዴድና መአህድ በራሳቸው መቆም እንደቻሉና ሕዝብ እንደተከተላቸው ገብቶት ተርበትብቷል። አሁን የሚያደርገው ወይም የሚሞክረው የለማደትን ክፍፍል መፍጠር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪ ካጣ ሰንብቷል። አሁን የሚያስፈልገው ሕዝቡ ተባብሮ መሪነቱን መረከብ ነው። ሕዝቡ ጫና መፍጠሩን እስከቀጠለ ህወሓት “ፓርቲ” ብሎ ራሱ ያቋቋመውን ቢያፈራርስ ለውጥ አያመጣም። ስለዚህም ነው ትግሉ በስድስት ወር አዋጅ ሆነ በማንኛውም ምክንያት መተጓጎል የለበትም ያልኩት። ትግሉ ከበረደ እንደገና መቀስቀስ ከባድ ነው፤ ያኔ ነው ህወሓት ወታደር ልኮ ማስፈራራትና መግደል የሚቀናው። ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች። የትግራይ ተወላጆችም ጭምር። እኩልነት ግን በሃብት ክፍፍል፣ በፖለቲካ ተሳትፎ መታየት አለበት። እስክንድር ነጋ ስለሚወዳት አገሩ በጋዜጣ ላይ አሳቡን ለመግለጽ ህገ መንግሥት ስለሚፈቅድለት የህወሓት ድጋሚ ፈቃድ አያሻውም። ህወሓት ማስተዳደር እንዳቃተው በሙስና እንደተዘፈቀ ከአገር አልፎ ዓለም አውቆ ጨርሶታል። ስለዚህ ማንም ዜጋ የህወሓትን አመራር ግፍ በንግግር በጽሑፍ በሰላማዊ ሰልፍ ለመንቀፍና ለመቃወም ፈቃድ አያስፈልገውም። ፈቃድ ካስፈለገማ ህወሓት ፈቃጅ ሆነ ማለት ነው። ህወሓት በ25 ዓመት ውስጥ የማይታመን ውሸታም ግፈኛና ሌባ መሆኑን አስመስክሯል። ይሻሻላል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነው። ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያሳትፍ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት።
ባለፉት ወራት አባዱላ ኃላፊነቴን ለቀቅሁ አለ፤ በረከትም። ትንሽ ቆይቶ ወደ ሥልጣናቸው ተመልሰዋል ተባለ። አሁን ደግሞ ኃይለማርያም። ኃይለማርያም ደቡብ የወከለው ግለሰብ አይደለም፤ የመለስ ሎሌ እንጂ። አሁን ደግሞ ሽፈራው ሽጉጤ ኃይለማርያምን ከደቡብ ህብረት እንደተወከለ አድርጎ ለማታለል እየሞከረ ነው። ህወሓት ትንሽ ቆይቶ ኃይለማርያምን በሌላ መልክ ይመልሰዋል።
በኦሮምያ፣ በአማራ በደቡብ ክልሎች ኗሪው ሥራ ፈትቶ፣ ንብረቱ ተግዞ ትግራይ መላኩና ማስቆም አለበት። የትግራይ ተወላጆች በቤንሻንጉል በጋምቤላ በአዲስ አበባ ያፈሩትን ገንዘብና ንብረት፣ እዚያው ለአካባቢው ጥቅም ከማዋል ይልቅ ወደ ትግራይና ወደ ውጭ አገሮች ባንክ ማሸጋገር ከግፍም ግፍ ነው። መቆም አለበት። ከደርግ ባርነት ነጻ ያወጣናችሁ እኛ ነን ይሉናል። እና ለመዝረፍ እንደ ጠላት በጥይት ለመግደል እንችላለን ለማለት ነው? ደርግን ነፍጠኛ ሲል የነበረው ህወሓት የባሰ ነፍጠኛ ሆኖ ተገኘ። ደርግ ወንጀል ቢያደርግም የኢትዮጵያን ሕዝቦች እኩልነትና የአገሪቱን ክብርና ድንበር አስከብሮ ነው። እኩልነት እኩልነት እኩልነት። ከዚህ ውጭ የሚደረገውን የኦሮሞና የአማራ ቄሮ በዓይነቁራኛ ተከታትሎ ማስቆም አለበት።
ንጉሱ ዘኢትዮጵያ says
.
“አብይ መሀመድ በሕወሓት ተመርጧል። እሁድ የይምሰል ቮት ይደረግበታል።” የሚለውን ሄና አልሰማችሁም????????