ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ሀገራቸው በጠላት ስትወረርና ሉዓላዊነታቸዉ ሲነካ ከያሉበት ተጠራርተው ዘር ፆታ ኃይማኖትና ባህል ሳይገድባቸው በየዘመናቱ የተነሱብንን ታሪካዊ ጠላቶቻችን በማይናወጥ ኅብረታቸው እንዲሁም ከአለት በጠነከረ ፅናት ሁሉንም እንደየ አመጣጣቸው መክተው ኢጥዮጵያችንን ዛሬ ላይ አድርሰዋታል፡፡
ታሪካችን ከምድር ሃይላችን አኩል በአየር ሃይላችንም ይለካል፡፡ በምስረታ ታሪኩ ከ95 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአየር ክልላችንና የግዛት አንድነታችን በማስጠበቁ ረገድ በወርቅ ቀለም የተፃፈ ታላቅ ታሪክ ያለው በሀገሪቱ አንጋፋው የአቪዬሽን ተቋም ነው።
እኛ ኢትዮጵያዊያኖች በስርዓቶች መለዋወጥና የተረጋጋ መንግስት በየወቅቱ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ከነበርንበት ከፍታ የቁልቁለት ጉዞ መውረዳችን ዛሬ በበለጠ ቁጭት ለተሻለ ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ሊያነሳሳን እንጂ ያለፉትን ስህተቶች በመድገም የታሪክ ተወቃሽ ልንሆን በፍፁም አይገባም።
ቁጭት እልህን ይወልዳልና ምስጋና የዘመኑ አቭዬሽን ቴክኖሎጂ ሳይንስ ለገባቸውና ወቅቱ የሚጠይቀውን የአመራር ክህሎት ታጥቀው የዚህን ገናና ተቋም ስሙን ዳግም ለማደስ ቆርጠው ለተነሱ አዲስ አመራሮች ይሁን እና ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ በተለይም በሰው ኃይል አቅሙ በመሰረተ ልማት በአቭዬሽን ቴክኖሎጂ ሽግግርና በዘመናዊ የአየር መከላከያ ግንባታ ታላላቅ ስኬቶችን በማስመዝገብ የቀድሞ ገናና ስሙንና ክብሩን ለማስመለስ ይበልጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ጀግናው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሀገርም አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፉ የደማቅ ገድል ባለበት የሆኑ በራሪዎችን የአቭዬሽን እንጂነሮችንና ስመጥር ቴክኒሺያኖችን ያፈራ የቁርጥ ቀን ጀግኖች መፍለቂያ ነው።
ተቋሙ በዚህ ሁሉ የውጣ ውረድ ጉዞው በበረራው መስክ ዘመን በማይሽረው ስራቸው ታሪክ በልዩነት የሚያስታውሳቸው ፓይለቶቹ የሰማይ አናብስት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አሁን ለቆመችበት መሰረት ስማቸው እነሱ እንደቀዘፉት ሰማይ ሁሌም በክብር ከፍ ብሎ ይወሳል።
ከእነኝህም መካከል በሶማሊያ ጦርነት ላይ ልዩ ጀብድ የፈፀሙት ብ/ጄ ለገሰ ተፈራ፤ ብ/ጄ አሸናፊ ገ/ፃዲቅ፤ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እንዲሁም ታጠቅ በሚለው የበረራ ኮድ ስማቸው የሚታወቁት ኮ/ል ባጫ ሁንዴን ጨምሮ በህልውና ዘመቻ ተሳትፈው በሚያልፍ ህይወታቸው የማያልፈውን ታሪክ በደማቸው ፅፈው ያለፉት ኮ/ል ታጋይ ኃይሉ (ታንጎ)፤ ኮ/ል ሚካኤል ሰረበ፤ ኮ/ል ለማ ታፈሰ፤ ኮ/ል ተፈራ አያለው ሌሎችም ወጣት በራሪና ቴክኒሺያን ጀግኖቻችን በእሳት ተፈትነው ያለፉ ወርቆቻችን ምንጊዜም በክብር የምንዘክራቸው የሀገር ባለውለታዎቻችን ናቸው።
ወደዛሬው ባለታሪካችን የህይወት ጉዞ ስንመለስ 45 ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን ማስታወሳችን የግድ ይላል። ወቅቱም እንደ ኢትዮጵያዊያን ዘመን አቆጣጠር ሃምሌ 1969 ዓ.ም የሶማሊያዉ መሐመድ ዚያድባሬ መንግስት የታላቋ ሶማሊያን የመገንባት ህልሙን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ እንደምቹ አጋጣሚ በመውሰድ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ጦሩን በምስራቅና ደቡባዊ ምሰራቅ የሀገራችን ግዛቶች ዘልቆ በማስገባት ታረካዊ ስህተት ፈፅሟል።
በሉዓላዊነታቸው የማይደራደሩት ኢትዮጵያዊያንም ወረራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስ የሄዱበት ርቀትና ከየአቅጣጫው ቀፎው እንደተነካ ንብ ሆ ብሎ በመነሳት ያሳዩት ያልደፈርም ባይነት ተጋድሎ ከአሸብራቂ ድሎቻችን ታሪክ በደማቁ ቀለም ሰንዶታል።
በተለይም በዛ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይልና በራሪዎቹ የሰማይ ላይ አርበኞች በጊዜው ወታደራዊ የኃይል አሰላለፍ የቁጥር ብልጫ እንዳለው የሚገመተውን የሶማሊያ አየር ኃይልና ሜካናይዝድ እግረኛ ሰራዊታቸውን በማሽመደመድ የሀገራችን ክብር በማስመለሱ በኩል ለተገኘው ድል ቁልፍ ሚናን ተወጥቷል።
ከነኝህ የአየር ሃይል ጀግኖች መካከል “ታጠቅ” በሚለው የበረራ መለያ ኮድ ስሙ የሚጠራው ታላቁ ጀግናና የሰማዩ አርበኛ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ ይገኝበታል፡፡
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ የገጠሙትን መሰናክሎች ሁሉ በታላቅ ጀግንነትና ብልሃት አልፎ የዚያድባሬን እብሪት ያስተነፈሰው ይህ ቆራጥ ጀግና ከሐምሌ 1969 እስከ የካቲት 1970 ዓ ም በተካሄደው የካራማራ ጦርነት በአየር ለአየር ውጊያ የጠላት አውሮፕላኖችን ከጥቅም ውጪ ያደረገ ሲሆን በተለይም 2 የጠላት ሚግ 21 አውሮፕላኖችን በአየር ለአየር ውጊያ መትቶ ከመጣል ባሻገር የጠላትን ከባድ መሳሪያና የሎጅስትክስ አቅርቦት ማዕከል በማውደም ለካራማራው ድል ስኬት ወሳኝ አስተዋፅኦ ያበረከተ ጀግና ናቸው።
በ1940 ዎቹ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል የተቀላቀለዉ ምርጡ በራሪ ኮ/ል ባጫ ሁንዴ ወደ አየር ኃይል በረራ ት/ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ በቴክኒሽያንነት ሰልጥኖ ተመርቋል፡፡
ከዚያም ዘመኑ የሚጠይቀውን የአቭዬሽን አቅምና የበረራ ክህሎት ለማሳደግ ከሀገር ውስጥ ስልጠና በተጨማሪ በአሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ታላላቅ የአየር ኃይል አካዳሚዎችም ተጨማሪ ስልጠናዎችን ወስዶ ባመጣዉ ከፍተኛ ማዕረግና ውጤት መሰረት የተለያዩ ሽልማቶችም ተበርክቶለታል።
ከ45 በላይ የወራሪው ሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖች ከስራ ውጪ ሲሆኑና ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ባደረጉት ያልተቋረጠ ድጋፍ አስከ አፍንጫው የታጠቀው ግዙፍ እግረኛና ሜካይናይዝድ ኃይልን ከጥምር ጦሩ እግረኛ ኃይላችን ጋር ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ጥቃት ወደግብአተ መሬቱ ሲወርድ የኮ/ል ባጫ ሁንዴና የሌሎች በራሪ ንስሮቹ የአየር ኃይል ጀግኖቻችን ተጋድሎ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለክብሯ የሚዋደቁላትን የቁርጥ ቀን ልጆች እንዳሏት የሚያሳይም ነዉ፡፡
ለወደር አልባው ጀግንነቱና ለፈፀመው ታላቅ ጀብድ ከወቅቱ መንግስት የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ 1ኛ ደረጃ የላቀ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ የነበረው ይህ ታላቅ ባለውለታ በውል ባልተገለፀ ምክንያት የሚወደውን የውትድርና ሙያና የደከመላትን ሀገር ትቶ በስደት ከ30 ዓመት በላይ በኖረበት የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት በ2008 ዓ ም ከዚህ አለም በሞት ተለይቶ ቀብሩም በዚያው አሜሪካን ሀገር መፈፀሙ ይታወቃል።
ሆኖም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለሀገር ባለውለታዎቻችን በተሰጠው እውቅናና ክብር መሠረት የጀግናው በራሪ ኮከብ አፅም በኢፌዴሪ አየር ኃይል፣በቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አለም አቀፍ ኅብረትና በኢትዮጵያ አየር ኃይል ቬትራንስና ቤተሰብ የጋራ ጥረት ጥር 15 ቀን 2015 ዓ ም አፅሙ በእናት ሀገሩ ምድር በቅድስት ስላሴ ካቴዲራል ከሌሎች ኢትዮጵያን ጀግኖች ጎን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።
አሁን በምንገኝበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ ሀገራችንን በውትድርናው መስክ ለማገልገል እድሉ የገጠመን የዚህ ዘመን የሰራዊት አባላት የኮ/ል ባጫንና መሰል ጓዶቻቸውን አደራ መጠበቅ በደም የተፃፈውን ደማቅ ታሪካቸውን ይበልጥ ማደስ ግድ ይለናል፡፡
ኮሎኔል ባጫ ለሀገራቸዉ ደማቅ ታሪክ ፅፈዉ አልፈዋል ሀገራዊ የጀግንነት ታካቸዉ ግን እሰወዲያኛዉ ከትዉልዱ ጋር ይዘልቃል፡፡
ፍቅሬ በቀለ፤ ፎቶግራፍ ከአየር ኃይል አርካይቭ፤ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
Leave a Reply