ትላንት ረቡዕ በአዘርባዣን የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻና ፍትሓዊ እንደማይሆን የብዙዎች ግምት ነበር፡፡ ከ10ዓመት በፊት ከአባታቸው ሥልጣን በውርስ የተረከቡት ፕሬዚዳንት ዒልሃም አሊዬቭ የጋዜጠኞችን እና የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ በመገደባቸው የምርጫው ውጤት ምን እንደሚሆን ለመገመት ያዳገተ አልነበረም፡፡ እንደ ኢቲቪና ሬዲዮ በአገሪቷ መንግሥት የሚቆጣጠረውና ለገዢው ፖለቲካ መሣሪያነት የዋለ ሚዲያ በመኖሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የነጻ ንግግር ገደብ እንዳሳሰባቸው ሲጠቁሙ ቆይተዋል፡፡ ቢቢሲም የምርጫው ውጤት አስቀድሞ የተወሰነ መሆኑን ዘግቦ ነበር፡፡
ምርጫ ተካሂዶ ቆጠራው ከመፈጸሙ በፊት የአዘርባዣን ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ለብልህስልኮች (smartphones) አዘጋጅቶ የለቀቀው ግብረታ (app) ፕሬዚዳንቱ በ72.76 በመቶ ማሸነፋቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡ እኤአ በ2003 በተካሄደው ምርጫ አሊዬቭ በ76.84በመቶ በ2008 ደግሞ በ87በመቶ “ማሸነፋቸው” ይታወቃል፡፡
የምርጫው ኮሚሽን ከምርጫ በፊት የወሰነው የፕሬዚዳንቱን ነጠብ ብቻ ሳይሆን የተሸናፊዎቹንም ውጤት ወስኖ ማስቀመጡ በዚህ በተላለፈው መልዕክት ላይ በግልጽ ይታያል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪ የነበሩት ጃሚል ሃሳናሊ 7.4በመቶ ማምጣታቸውን አክሎበታል፡፡
መረጃው ከተለቀቀ በኋላ ወዲያውኑ የተመለሰ ሲሆን መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ግብረቱን (app) የሰራው ኩባንያ በስህተት የ2008ዓም ምርጫ ውጤትን ነበር የለቀቀው የሚል ነበር፡፡ በ2008 ደግሞ ፕሬዚዳንት አሊዬቭ 87በመቶ “ማሸነፋቸው” በገሃድ የሚታወቅ ጉዳይ በመሆኑ ማስተባበያው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ማሸነፋቸው አስቀድሞ የተወሰነላቸውና አሁን ደግሞ በስፋት እየተዘገበላቸው ያለው አሊዬቭ በመንግሥታቸው ቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩ “የአገሬ ዜጎች እምነታቸውን በእኔ ላይ በማድረግ እና ወደፊት ለምናከናውነው የአገራችን ልማት መሳካት በማሰብ ስለመረጡኝ በጣም አመሰግናለሁ” ብለዋል፡፡
የአሊዬቭን ልማታዊ ፓርቲ በመደገፍ የመረጠው ልማታዊ መራጭ ሲናገር “ፕሬዚዳንታችንን የመረጥነው ለአዘርባዣን እንደ ዒልሃም አሊዬቭ ዓይነት ባለራዕይ መሪ የትም ስለማይገኝ ነው” ብሏል፡፡ ከተቃዋሚው በኩል አስተያየቱን የሰጠ ደግሞ እንዲህ በማለት ምሬቱ ገልጾዋል፤ “የዚህ አገር ባለሥልጣናት በዚህች አገር ያለውን ሃብት እንደፈለጉ እንደሚዘርፉ ሁሉ አሁን ደግሞ ድምጻችንን ዘርፈዋል፡፡”
ፕሬዚዳንቱ የምስጋና ንግግሩን የተናገሩት የድምጽ ቆጠራው ከመጠናቀቁ በፊት ሲሆን በሚናገሩበትም ወቅት 85በመቶ ማሸነፋቸውና በድጋሚ ፕሬዚዳንት መሆናቸው በይፋ እየተነገረ ነበር፡፡
በ1997 በአገራችን ላይ በተካሄደው ምርጫም ድምጽ ተቆጥሮ ከመጠናቀቁ በፊት አቶ መለስ በኢቲቪ መስኮት ብቅ ብለው ኢህአዴግ ማሸነፉንና የአገር መሪነቱ መረከቡን ማወጃቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱም እርሳቸው በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ 197 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው በማስረጃ በመረጋገጡ አቶ መለስን ለፍርድ ለማቅረብ ሁሉን ዓቀፍ ጥረት እየተካሄደ ነበር፡፡
በቀጣይ በተካሄደው ምርጫ በአዘርባዣን በተካሄደው በተለየ መልኩ ኢህአዴግ በ99.6በመቶ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመቆጣጠሩ ኢትዮጵያ “የልማታዊ ዜጎች” አገር ለመሆን በቅታለች፡፡
በኢትዮጵያ በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ እንደ አዘርባዣን ዓይነት ስህተት እንዳይከሰትና ከምርጫው አንድ ሳምንት በፊት የምርጫ ኮሚሽን ውጤት እንዳያወጣ የሰጉ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትና በዚህ ረገድ ኢንሣ፣ ኢቲዮ ቴሌኮም፣ ኢቲቪና የምርጫ ኮሚሽን ልማታዊ ተግባራቸውን እንዲወጡ አስቀድመው ያስጠነቅቃሉ፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply