ሚስት ከቤቷ ጥጋ ጥግ ትንንሽ ጊዜያዊ ጉልቻ ጎልታ ካንዱ ወዳንዱ እየተዛወረች ስራዋን ስትሰራ፣ ስትቀቅል፣ ስታነኩር፣ ስትጋግር፣ ስትወጠውጥ … ድንገት ባንዱ አቅጣጫ እሳቱ መልኩን ቀየረ። ቀስ ብሎ ለካስ ወደ ቤቱ ተዛምቶ ነበርና ቤቱ ነደደ። እሳቱን ያዩ ለማጥፋት እየተሯሯጡ ደረሱ። አልሆነም የቤተሰቡ መኖሪያ ነደደ። ቤቱ የቆመው ለመቀጣጠል በሚያመች ማዋቀሪያ ነበርና ወደ አመድ ተቀየረ። ልክ እንደ ጎሳ ፖለቲካ!! እንደ ግንቦት 20 ዓመዳማ ፍሬዎች!!
እሳቱን ለማጥፋት የሞክሩት ጎረቤቶች አዘኑ። “እሳት በቀላሉ የሚበላው ቤት ይዘሽ ዙሪያውን እሳት ማቀጣጠል አልነበረብሽም” ብለው ገሰጿት። ማጣፊያው ያጠራት ሴት “እባካችሁ ባለቤቴ ሲመጣ አትንገሩት” አለቻቸውና ተማጸነች። ጎረቤቶቿ በንግግሯ ተገርመው “ከሄደበት ሲመጣ የሚገባበት ካገኘ ማን ይነግረዋል” ብለዋት ተሰናበቷት። “ቤት ባገር ይመሰላል” እያለ የሚያስተምረኝ የመሰየሚያ ቤት ባልደረባዬ ታወሰኝ፡፡
የተለመደው ሰላምታዬን በቅድሚያ ኑሮ ለሚያላምጣችሁ … ለኑሮ ችጋር ሰለባዎች ይሁን!! ክረምት/ቡሄ መጣ። ክረምት ስጋት የሆነባችሁ ኗሪዎች “አንድዬ ይከልላችሁ” ከማለት የዘለለ ምርቃት የለኝም። ዶፉን፣ ውርጩን፣ ቁሩን …. በደጅ ሁናችሁ የምትገፉት የ”ኗሪዎች” “አኗኗሪዎች”፣ በወጉም አኗኗሪ መሆን እንኳን ያቃታችሁ፣ ለናንተም ምርጫ ደርሷል። አሁን እናንተን ምን ብለው ይሆን “ምረጡኝ” ብለው የሚጀነጅኗችሁ? ለነገሩ እኮ ዝናብ ሲመጣ የሚያነቡ ቤት ውስጥ ያሉ የውጪ/ደጅ አዳሪዎች ከናንተ ይበዛሉ። በፈረቃ የሚተኙትስ ከናንተ በምን ይሻላሉ? አረ ስንቱ … ቀኝኑ ዘ-ቄራ ነኝ!! ቋሚን አሳንሰው ለሙት መንፈስ በሚገብሩና በሚሰግዱ መመራትም ያው የደጅ ኑሮ ማለት ነው። ያለ ህግ መገዛትም ያው የዱር ኑሮ ነው !! ሲያስጠላ!!
ነብስ ይማር፣ ነብስ ያሽርልን!! ደጅ መውደቅ መከራ ሆነ። ደጅ በወደቁት ላይ ሌሎች ደጅ አዳሪዎች ማከል እንዲቆም የጠየቁ – “ታጨዱ” ። ለሰላማዊ ጥያቄ ያለ ጥይት መፍትሄ የለም ወይ? ያለ ጠብ መብ መንጃ አማራጭ የለም እንዴ? ሰዎች በተሰበሰቡ ቁጥር መደንበር ለምን? ያ ግብር የሚገባበት “የባቢሎን ሽራፊ” በደም ተነከረው የሲኦል ካባው አልቆበት ይሆን? ግራ የሚያጋባ ነው እኮ!! ቀጭኑ ተጨነቀ!!
የኢትዮጵያ ወቅታዊ አቋቋም እዛም እዛም እሳት የለኮሰችውን ሴት ይመስላል። ኦሮሚያ የእሳት ነበልባል አለ። አማራ ክልል እሳት ከረመጠ ውሎ አድሯል። ደቡብ ያለው እሳትም ልንደድ አልንደድ እያለ ነው። ሶማሌ ክልል ያለው እሳት ሃፎቱን እየሰበቀ ነው። አፋር ክልል በራሁ ጠፋሁ የሚል እሳት አለ። ጋምቤላ ከራሷ እሳት ሌላ ከአጎራባቿ የሚነደው እሳት እያጋላት ነው። ሁሉም ጋር እሳት አለ። እሳቱ ከያቅጣጫው ቤንዚን እየተርከፈከፈበት ነው። ኢህአዴግም በየቀኑ እሳቱን እየቆሰቆሰ 23 ዓመታትን “ደም ግብሩ” አድርጎ ልደቱን ለማክበር እየተክለፈለፈ ነው።
ላለፉት 23 ዓመታት የጎሳ ፖለቲካና ጥላቻ እየተጋቱ ያደጉ ትውልዶች ዙሪያውን እየፎከሩ ነው። የኢትዮጵያዊነት ልጓማቸውን ኢህአዴግ በጣጥሶ ስለጣለው ፉከራው ገደብ እንዳይለቅ ያስፈራል። ቀጭኑ ከየአቅጣጫው በሚሰማው በርግጓል። ለነገሩ ያልበረገገ ማን አለ? የገደሉ፣ ያስገደሉ፣ እየገደሉ ያሉ፣ ወደ ፊትም ለመግደል ቃታ ላይ የተጣዱ፣ ከሁሉም በላይ “እርሙና ግፉ በስማቸው የሚፈጸምባቸው” ተጨንቀዋል። ወደ ልቡና ወደ ቀልቡ የሚመለስ አልተገኘም። 23 ዓመታት ለትምህርት አልሆነም። አገሪቱ በጥላቻና በቂም እየነፈረች የሚያዝን መሪ ድምጽ አልተሰማም።
የሃይማኖት መሪዎችም በባቢሎን ቅሪት ተለውሰው፣ በካድሬነት ካባ ተሸፍነው “እረኝነታቸውን” ረስተውታል። “ደ-መና ሲሆን ዝናብ እንደሚመጣ” መለየት አልቻሉም። ታውረዋል። ልቡናቸው ደንድኖ የሎጥን ሚስት ሆነዋል። ደጉ መንፈስ ስለራቃቸው እይታቸው ከከርሳቸው ማለፍ አልቻለም። አማኑኤል ያለው “እብድ” ትዝ አለኝ። “የሚፈራ፣ የሚከበር ጠፋ፣ ማንን ፊት እናስቀድም? ማን ነው ቀልብ ያለው? መቅደስ ውስጥ ማን አለ? ክፋት፣ ክፋት፣ ክፋት….” እያለ ይጮህ ነበር። እንዲህ ስላለ ታስሯል። ተጠፍሯል። ቀናነት መጥፋቱ ያስጨነቀውን “ቀና” ሰው፣ ቀናነት የጎደላቸው አስረው ላርጋክቲን ይወጉታል። ግን ማን ነው በሽተኛ? ቀጭኑ ጠየቀ!!
አማኑኤል የጤነኞች መከማቻ ነው። አማኑኤል በቤት ጣጣ፣ በሃቴቴና በውቃቢ፣ በጋኔን “ግብር አነሰኝ” ቁጣ ከሚመጡት በስተቀር አብዛኞቹ የተነኩበት ጉዳይ ያሳዝናል። ካንዳበታቸው የሚወረወረው ሁሉ እውነት ነው። “አገሬ አይ እድልሽ” እያሉ የሚለፈልፉ፣ “አትግደል፣ አትግደል፣ አትግደል … “ እያሉ የሚወተውቱ፣ “ልብ ያለው ልብ ይበል፣ ልብ ያለው ያስተውል፣ አዳምጡን፣ ስሙኝ፣ ጆሯችሁን አቁሙ” እያሉ የሚያስጠነቅቁ ውብ ሰዎች አማኑኤል “እብድ” ተብለው አሉ። የሚገርመው ጡረተኛዋ ቀዳማዊት እመቤት ናቸው “የበላይ ጠባቂያቸው” አይ አለም!!
አንድ ጊዜ አንድ የአማኑኤል ሰራተኛ የነገሩኝ ታወሰኝ። አማኑኤል ሆስፒታል ያሉ ታካሚ እህቶች “ውርጃ ይከናወንላቸዋል” አለኝ። የሰማሁትን ማመን አቃተኝ። እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ማብራሪያ አቀረብኩ። ሰራተኞች እንደሚተናኮሱዋቸው/እንደሚገለገሉባቸው ተረዳሁ። አፈርኩ። አመመኝ። አሁን ማን ነው ጤነኛ? የሚገርመው ውርጃ የሚፈጽምላቸው የግል ተቋም እንዳለ መሰማቱ ነው። ጉዳዩን ብዙም ማጣራት ባልችልም “እብዶች” ስለማርገዛቸው ከበቂ በላይ ማስረጃ አለ። ወ/ሮ አዜብ እንደ አሁኑ ሳይተነፍሱ ይህንን እንኳን ለፍርድ ቢያቀርቡ ምንኛ ከኖረው ሃጢያታቸው ሁሉ በነጹ ነበር!! መስመር ሳትኩ መሰል ወደ መነሻዬ ልመለስ።
አዎ ቤት አገር ነች። ቤት ከተቃጠለ መጠለያ የለም። በተለይ በግራም በቀኝም መሸሻ የሌላቸው ምስኪኖች ያሳዝናሉ። “አለን አለን ሲሉ፣ ይናዳል ገደሉ” ተብሎ የለ!! ከተናደ ተናደ ነው። ደርግ ሲናድ ጥላ ሳይቀር ያስደነግጥ ነበር። ሲናድ ጥላም ያስፈራል። ሲናድ ስንቄን፣ ሃብቴን፣ ወርቄን፣ ፋብሪካዬን፣ ህንጻዬን፣ መኪናዬን፣ ቤተመንግስቴን…. የሚባል ዘባተሎ ሃሳብ የለም። ሁሉም እንደ ጉም ይተናል። እንደ ሴትየዋ ቤት “ዓመድ” ይሆናል። ዓመድ!! ታዲያ ያ-ክፉ ሃሳብ ሳይሰለጥን ሁላችንም ወደ ልባችን ብንመለስስ? ስለ ሰላም ብናለቅስ? ይቅር ባይነት “ዓመድ” ከመሆን ይሰውራልና !! ከግንቦት ሃያ ያተረፍነው የጎሳ ፖለቲካ ምሱ ዓመድ ነውና 23ኛውን “በዓል” የግንቦት 20 ዓመዳማ ፍሬዎች!! ብንለውስ? ክብር ይህንን ጊዜና የተሰውበትን ዓላማ ሳይመለከቱ ላለፉ ታጋዮች!! ግን ይህንን በደማቸውና ባጥንታቸው ላይ የተገነባውን “ዓመድ” የሚያደርግ የፖለቲካ ቀመር ከሚያዩት ሞታቸው አይሻልም? ፍሬዎቹን ኢህአዴግ በሰፊው ስለሚመጣባቸው አልፌያቸዋለሁና። ለማመጣጠን ኢቲቪን ይመልከቱ!!
Leave a Reply