• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ሉዓላዊነትና መብት

December 5, 2012 03:28 am by Editor Leave a Comment

ሶርያ አሮጌ አገር ነው፤ ታሪኩ ረጅም ነው፤ ከሶርያ ጋር ሲወዳደር አሜሪካ ሕጻን ነው፤ ነገር ግን ለብዙ ወራት በሶርያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነትና በቅርቡ በአሜሪካ የተደረገውን ምርጫ ስንመለከትና ስናነጻጽራቸው፣ የሶርያ ሕዝብ እርስበርሱ ሲጨራረስ አሜሪካኖች በጥቂት ቀናት ውስጥ ሐዝቡ ድምጹን ሰጥቶ ምርጫው ተጠናቅቆ በሰላም የሥልጣን ርክክብ ተደረገ፤ ዕድሜ የመብሰል ምልክት ላይሆን እንደሚችልና ፍሬ-አልባ እንደሚሆን መረዳት እንችላለን፤ ከርሞ ጥጃ እየሆኑ ዕድሜ መቁጠር፤ በሶርያ የሚካሄደው ጦርነት ግን አንድ ሰው፣ በሺር አላሳድ፣ እስቲሞት ድረስ መጋደሉና አገር መፈራረሱ ይቀጥላል፤ ዓለምም፣ የተባበሩት መንግሥታትም፣ የአረብ ማኅበርም ሁሉም ከንፈሩን እየመጠጠ የሶርያን ሕዝብ ስቃይ ያያል፤ የፍልስጥኤማውያንንም ስቃይ እንዲሁ፡፡

ለምን አንዲህ ይሆናል? ምክንያቱ ሉዓላዊነት የሚባል ነገር ነው፤ ሉዓላዊነት ምን ማለት ነው? በመሠረቱ ሉዓላዊነት ሦስት ሀሳቦችን ያዘለ ይመስለኛል፤ አንዱ ሥልጣን ነው፤ ሁለተኛው ከበላዩ ሌላ ሥልጣንን የማይቀበል ነው፤ሦስተኛው አጥር ነው፤ በኋላ አንደምናየው ሥልጣንም፣ የበላይነትም አጥር አለው፤ ለወጉ ሉዓላዊነት ማለት ራስን ችሎ ከውጭ ድጋፍ ሳይፈልጉ መቆም ነው፤ ከውጭ ምንም ዓይነት የበላይ ሥልጣንን አለመቀበል ነው፤ በአገሮች መሀከል ተደጋግሞ የሚሰማው በራሳችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብን እየተባለ መከላከያ የሚሰጠው ከሉዓላዊነት መሠረት በመነሣት ነው፤ በዚህ ዓይነት መልኩ ብዙ ጊዜ ሥራ ላይ ቢውልም በሉዓላዊነት ሀሳብ አጠቃቀም ላይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡

ሉዓላዊነት የሚለው ሀሳብ ከሁለት በጣም ከተለያዩ መሠረቶች የሚነሣ ነው፤ በአንድ በኩል የሕዝብ ሉዓላዊነት አለ፤ በሌላ በኩል የአገዛዝ ሉዓላዊነት አለ፤ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት በሆነበት፣ ሕዝብ በነጻነትና በሕጋዊ ሥርዓት በተካሄደ ምርጫ ተወካዮቹን ሰይሞ ራሱ የሚቆጣጠረውን መንግሥት ባቋቋመበት አገር ሉዓላዊነት ማለት የሕዝብ የሥልጣን የበላይነት ነው፤ ሉዓላዊ፣ የአገሩ ባለቤት፣ የአገሩ የበላይ ባለሥልጣን የሆነ ሕዝብ ማለት ነው፤ በአገሩ የበላይ ባለሥልጣን የሆነ ሕዝብ መንግሥት የሚባል ድርጅት ያቋቁምና ውክልና ይሰጠዋል፡፡

በአንጻሩ በአገዛዝ ስር ያለ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት አይደለም፤ ሥልጣንም የለውም፤ የአገሩ ባለቤት ሆኖ ሙሉ ሥልጣንን የጨበጠው አገዛዙ ነው፤ ስለዚህም ሉዓላዊነት የሕዝቡ ሳይሆን የአገዛዙ ነው፤ ነገር ግን ከሕዝቡ የተለየ አገዛዝ የአገር ባለቤት ነው ማለት ለሰሚው ግራ ስለሚሆን የይስሙላ ምርጫ እየተደረገ አገዛዞች ሁሉ ሕዝቦቻቸውን እየረገጡ ለመግዛት (አንዳንዴም በ99.7 ከመቶ እያሸነፉ!) የሚረገጡትን ሕዝቦች ፈቃድ ያገኙ እያስመሰሉ ጡሩምባቸውን ይነፋሉ፤ የሚራብና የሚጠማ፣ የታረዘና የተጎሳቆለ፣ ከዓመት ዓመት በውጭ ምጽዋት የሚኖር፣ በየዕለቱ ግፍን የሚቀበል ሕዝብ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ፈቃዱን ለአገዛዝ ሰጥቷል ብሎ የሚያምን አገዛዝ ብቻ ነው፡፡

ወደሶርያ ስንመለስ ሕዝቡ የአገሩ ባለቤት አይደለም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ሉዓላዊነት የለውም፤ ሉዓላዊነቱን በጉልበት የጨበጠው አገዛዙ ነው፡፡

ዓለም በሙሉ፣ የተባበሩት መንግሥታትም ጭምር የሶርያን አገዛዝ ሉዓላዊ አድርገው ይመለከቱታል፤ እውነተኛው የሉዓላዊነት ባለቤት የሆነው የሶርያ ሕዝብ ሲደቆስ የሐዘን ስሜት ያድርባቸው እንደሆነ እንጂ ሕጋዊ አቅዋም ሊይዙና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ይቸገራሉ፤ አይችሉም፤ ምክንያቱም የሶርያን ሕዝብ ሀብትና ጉልበት ለጊዜው የሚያዝዝበት አገዛዙ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ለትክክለኛው የሉዓላዊነት ባለቤት፣ ለሕዝቡ እውቅና ለምን አይሰጥም? የቂል ጥያቄ ይመስላል፤ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ አብዛኛዎቹን ወንበሮች የያዙት አገዛዞች ናቸው፤ ስለዚህ አገዛዞቹ ለነሱ የተመቸውን ሁኔታ በመለወጥ ራሳቸውን የሚያሰናክሉበት ምክንያት ምን አለ? ይህ አንድ ምክንያት ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የአሜሪካና የአውሮፓ ዴሞክራሲያዊ አገሮችም ቢሆኑ በሦስተኛ ዓለም አገሮች ውስጥ የእነሱን ጥቅም ለማራመድ የሚሻላቸው አገዛዝ ነው፤ በዴሞክራሲ አገር ውስጥ ብዙ ውጣ-ውረድና ልፋት ያጋጥማቸዋል፤ ነጻ ጋዜጦች የተለያዩ ሀሳቦችንንና አስተያየቶችን ያናፍሳሉ፤ ምሁራን የተለያዩ ጥናቶችን ለሕዝብ እያቀረቡ ያስተምራሉ፤ የፖሊቲካ ቡድኖች የተለያዩ አስተያየቶችን ለሕዝብ ያስጨብጣሉ፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለአሜሪካና ለአውሮፓ አገሮች አይመቻቸውም፤ ለእነሱ ቀላል የሚሆንላቸውና የሚመቻቸው ከአንድ አምባ-ገነን ጋር ለብቻ ተነጋግረው የሚያጎርሱትን አጉርሰውት እነሱ በፈለጉት አቅጣጫ የሚዘውሩትን ነው፤ ስለዚህም ለሕዝብ ሉዓላዊነት ግድም የላቸው፤ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙት የሰብአዊና የዴሞክራሲ ድርጅቶች ከመንፈሳዊና ከሰብአዊ መሠረት ተነሥተው ጠንካራ ቢሆኑም የፖሊቲካውን ኃይል ሙሉ ለሙሉ መቋቋም አይችሉም፤ ይህ የሚሆነው አምባ-ገነኑ ጠግቦ ወይም በአጋጣሚ ከኃያል መንግሥት ጋር አስኪላተም ድረስ ነው፤ ያን ጊዜ ጉዳቱ ከጥቅሙ ስለሚያመዝን ፊቱን ያዞርበታል፤ በሙባረክ ላይ የደረሰው ይህ ነው፤ ሕዝቡ የጠላው አምባ-ገነን ለአሜሪካና ለአውሮፓም አይበጅም፤ የአምባ-ገነኑን ተፈላጊነት ለማስመስከር ሲሞት ሕዝቡ እንዲያለቅስ ይደረጋል፡፡

ሦስተኛም ምክንያት አለ፤ እንደሩስያና ቻይና ያሉ ኃያላን የሆኑት አገዛዞች ትንሽ ትንሽ እያጎረሱ በንግድ በኩል የሚያገኙትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚመሳሰሏቸውን አገዛዞች ይደግፋሉ፤ ለዚህ ነው ሩስያና ቻይና የአል በሺርን ግፍ ዓይናቸውን ጨፍነው የሚደግፉት፤ እነሱም ቢሆኑ ምጥጥ ከአደረጉት በኋላ የሚጋጥ ነገር ሲጠፋ ወዳጅነታቸውም አብሮ ይጠፋል፡፡

ዓለም-አቀፍ ሕግ እውነተኛውንና በሕዝብ ሥልጣን ላይ የቆመውን ሉዓላዊነት ከመደገፍ ይልቅ ባለጉልበቱን አገዛዝ መደገፍ ይቀናዋል፤ ለዚህ ነው የሰብአዊ መብቶችን በመርገጥ ስማቸው የገነነ አገዛዞች እንኳን በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ውስጥ አባል ሆነው የሚመረጡት፤ አንዱ ምክንያት እንደተገለጸው የተባበሩት መንግሥታት በአብዛኛው የአገዛዞች ስብስብ ስለሆነ ወር-ተራ እየገቡ በመረዳዳታቸው ነው፤ ሌላው ምክንያት ምናልባት ከስብሰባዎቹ ይማሩ ይሆናል የሚል አጉል ተስፋ ነው፡፡

ሉዓላዊነትን የምናይበት ሌላ መንገድም አለ፤ ሕዝብ ሉዓላዊ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ሕዝብ ማለት እያንዳንዱ ዜጋ በእኩልነት ቆሞ የሚታይበት ስብስብ ነው፤ሰው በዜግነቱ ሰውነቱን አያጣም፤ ሰውነቱ የተፈጥሮ ሲሆን ዜግነቱ በሕግ የተከለለ ነው፤ ዜጋ ማለት በሕግ የታጠረ ሰው ነው፤ ግለሰብ የምንለው ነጠላው ሰው ሰውም ነው ዜጋም ነው፤ ስለዚህም ለአንድ አገርም ሆነ ለአንድ ሕዝብ የሉዓላዊነቱ መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ነው፤ ከሉዓላዊነት ተነሥተን ወደሰውነት ደረጃ ስንገባ (ሰዎችን ሁሉ እኩል አድርገን) እያንዳንዱ ሰው ሰብአዊ መብቶች አሉት፤ እነዚህ መብቶች የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድ ላይ ይዘው በሰውነት የታጠሩ ናቸው፤ ቀጥለን ወደአገር ደረጃ ስንወርድ ደግሞ ሰብአዊ መብቶች ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት ይዘው በዜግነት የታጠሩ ይሆናሉ፤ በሰውነት ደረጃ በሰዎች መሀከል ልዩነት የለም፤ በዜግነት ደረጃም በዜጎች መሀከል ልዩነት የለም፡፡

ወደሶርያ ጉዳይ ስንመለስ ተጽእኖ ለማድረግ የሚችለው የዓለም-አቀፍ ማኅበረሰብ ሶርያን የሚመለከተው በሰውነት ደረጃም ሆነ በዜግነት ደረጃ አይደለም፤በጥቅም መለኪያ ነው፤ ለዚህ ነው የሶርያ ሕዝብም ሆነ የፍልስጥኤማውያን ሕይወት ዋጋ-ቢስ የሆነው፤ ለዚህ ነው በአገሩ ውስጥ የባለቤትነት መብት የሌለው ግለሰብ በሕዝብነት ወይም በዜግነት ደረጃ ውስጥ ሲገባ ገለባ የሚሆነው፤ ለገለባ ማንም ግድ የለው፡፡

ሰብአዊ መብቶች ተጣሱ ወይም ተረገጡ የሚባለው በግለሰብ ደረጃ ያለውን አጥር፣ በዜግነት ደረጃ ያለውን አጥር፣ በሰውነት ደረጃ ያለውን አጥር የሚያፈርስ ለሕግ ግድ የሌለው ጉልበተኛ ሲነሣ ነው፤ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ!

Mesfin Woldemariam Blog

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የተንጋደደው የገዱ መልስ February 6, 2026 03:05 pm
  • ሻዕቢያ “አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል …” February 4, 2026 01:15 pm
  • አደራ ጠባቂው የኢሉአባቦር ሕዝብ February 4, 2026 12:14 pm
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን January 28, 2026 09:56 am
  • በአሜሪካ ጥምር ዜግነት እንዲቀር ጥያቄ ቀረበ January 27, 2026 03:05 pm
  • “ከህወሓት፣ ከሻዕቢያ፣ ከግብፅ ሰዎች ጋር ሆኖ እንዴት የአማራን ጥያቄ ማስመለስ ይቻላል?” ኮሎኔል ፈንታው January 25, 2026 04:23 am
  • የኢትዮጵያ አየር ኃይል: ለአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያዎቹን የአየር ኃይል አብራሪዎች ያሰለጠነ ተቋም January 25, 2026 03:50 am
  • የአማረ ሪፖርተር እያደረሰ ያለው የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ January 22, 2026 01:56 am
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule