የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የደቡብ ክልል የመንግስት ጉዳዮችን ጠቅሶ እንደዘገበው “ሪፖርተር ጋዜጣ 3ምክትል ርእሰ መስተዳድሮች ከሃላፊነታቸው ተነሱ በማለት ያወጣው ዘገባ መሰረተ ቢስ” ብሎታል። ይሁን እንጂ ሪፖርተር ከሃላፊነታቸው ተነሱ ያላቸው ሶስት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች በስልጣን ላይ ስለመኖራቸው ያለው ነገር የለም።
ዜናውን አስተባበለ፣ ጉዳዩንም ወደ ህግ ሊወስድ ዛተ የተባለው የክልሉ የመንግስት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተጠቀሰበት ዜና ከዚህ የሚከተለው ሲሆን፣ ዜናው ከሪፖርተር በኩል ስላለው የዜናው መረጃ እውነተኛነት አላካተተም። ሪፖርተር ለሰራው ዜና ምንጮቹ የተሳሳቱ ከሆነ ዜናውን ቀደም ሲል በሰራበት መጠንና ቦታ ይቅርታ ለመጠየቅና ራሱን በራሱ ማስተባበል ይጠበቅበታል።
ዜናው እንደሚከተለው ይነበባል:-
ሪፖርተር ጋዜጣ 3ምክትል ርእሰ መስተዳድሮች ከሃላፊነታቸው ተነሱ በማለት ያወጣው ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው-የደቡብ ክልል
ሪፖርተር ጋዜጣ በነሃሴ 29/2005 እትሙ “የደቡብ ክልል 3 ምክትል ርእሰ መስተዳድሮች ከሃላፊነታቸው ተነሱ” በማለት ያወጣው ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
መግለጫው የክልሉ መንግስት የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራትን በአንድ መንፈስ እያካሄደ በሚገኝበት ወቅት ጋዜጣው ይህን መሰል መሰረተ ቢስ ዘገባ ማሰራጨቱ አሳዛኝ ድርጊት ነው ብሏል፡፡
የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ የሀገሪቱን ህጎች የሚፃረር በመሆኑ የክልሉ መንግስት ተግባሩን የፈፀሙት አካላት ህጉን በሚያዘው መሰረት ተከታትሎ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ምንጭ፡- የደቡብ ክልል የመንግስት ጉዳዮች ፅህፈት ቤት
Leave a Reply