ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም የሚለው አስተያየት አሁን አሁን አከራካሪ ሊሆን አይችልም። በብዥታ ውስጥ የነበሩት እንኳን አሁን “ምን እየሆነ ነው” በሚል ራሳቸውን እየጠየቁ ያለአስረጂ ምላሹን እያገኙ ህወሓትን በጥርጣሬ የሚያዩበትን መነጽር አውልቀዋል። ይህ እንግዲህ በውጪውም ዓለም ጭምር እየሆነ ነው።
በአስገንጣይነትና በተገንጣይነት ሲርመጠመጥ የነበረው ህወሓት ባላሰበው መልኩ፣ በህልሙም አስቦት የማያውቀውን፤ የአገር መሪነት ያስረከቡት “ቀጣሪዎች” ሳይቀሩ አሁን አሁን ፊት ለፊት “አናምንህም” ባይሉትም፣ ዙሪያውን እየዞሩትና እያዞሩበት ይገኛል። ብዙ ምልክቶች አሉ። አንደበታቸውን የከፈቱና “ዋ” የሚሉም እየተነሱ ነው።
ከየአቅጣጫው የሚነሳውን ይህ ከላይ ጨምቀን ያቀረብነውን ጉዳይ የሚያጠናክር መረጃ ጎልጉል ስለደረሰው ነው። በአሜሪካ የህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ግቢ /ኤምባሲ ለማለት ነው/ ውስጥ ከሚሠሩ ታማኝ ምንጮችና ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ክፍሎች የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በሶማሊያ ከደረሰው አሰቃቂ እልቂት ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ቁማሩ ተጧጡፏል።
“እኛ ከሶማሊያ ስንወጣ የሚሆነውን ጅማሮ አያችሁ?”
ጉዳዩ እንዲህ ነው። በአሜሪካ የህወሓት የፖለቲካ ጊቢ የህወሓት ሹመኛ ለአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክርቤት የአብላጫው (ማጆሪቲ) መሪ ቢሮ ብቅ ይላል። በሶማሊያ ከ300 በላይ ንጹሃንን የቀጠፈውን ፍንዳታ ያነሳል። ከዚያም “ያልነው አልቀረም! ይኽው አያችሁት” ይላል፤ አስከትሎም “ይህ የአሁኑ አደጋ እኛ ከሶማሊያ ስንወጣ የሚሆነውን ጅማሮ የሚያሳይ ነው። አያችሁ?” ሲል አክሎ ይናገራል።
ለጎልጉል መረጃውን ያቀረቡት ሁለቱም ክፍሎች እንዳረጋገጡት “አልሸባብ እኛን ብቻ ነው የሚፈራው። እኛ ጠቅልለን ከወጣን አገሪቱ ትደበላለቃለች። ይህ አሁን የተከሰተው የወደፊቱ ማሳያ ነው …” በማለት ሹመኛው ለአብላጫው መሪ ቢሮ ተናግሯል። የመረጃው ባለቤቶች ለጎልጉል ሲያስረዱ ይህ ሁሉ ዘመቻና ሩጫ የHR 128 አናቂ ህግ እንዳይጸድቅ ለመከላከልና ለመደራደር ነው። እስካሁን ከሚደረጉት ሩጫዎች በተጨማሪ።
ጥርጣሬውና – ሰንሰለት የሆኑ ጭብጦች
አደባባይ ወጥቶ ያወጀ ክፍል ባይኖርም ህወሓት በሶማሊያ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ እጁ አለበት የሚሉ ፍንጮች እየተሰሙ ነው። ጎልጉል ባሰባሰበው ማስረጃ ጥርጣሬው ያላቸው ክፍሎች ህወሓት የተሟላ መልስ የማይሰጥባቸው የኮለሉ ንጹህ ጭብጦችን ያነሳሉ። (ህወሓት በዓለምአቀፍ የአሸባሪዎች ቋት በአሸባሪነት ተመዝግቦ የሚገኝና የፈጸመው የሽብር ተግባር እዚያው በዝርዝር የሚገኝ መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል)
- ህወሓት በአገር ውስጥ ፖለቲካ መፈናፈኛ አጥቶ መላወሻ ባጣበት በአሁኑ ወቅት አዲስ የተረቀቀው (የHR 128) ህግ የህይወትና የሞት ጥያቄ መሆኑ፣ ህጉ ተጠያቂ የሚሆኑ ባለስልጣኖችን ለይቶ አንገታቸው ላይ ሽምቀቆ የሚያስገባ መሆኑ፣ ከሁሉም በላይ አብዛኛው በግልና በድርጅት የተዘረፈ ንብረት ላይ ማተኮሩ ይህም ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ማስጨነቁ፤
- ከዚህ ጭንቀት መውጣት አማራጭ የሌለው ግብ በመሆኑ ህጉ ከመጽደቁ በፊት ማናቸውንም ዓይነት ዋጋ መክፈል። ለሚከፈለው ዋጋና ዘመቻውን ለሚመሩት ተከፋይ ባንዳዎች ግብዓት የሚሆን ተግባራትን መፈጸም፤
- በዚህ መነሻ፣ ከስር በሚቀርቡ አብረቅራቂ ምክንያቶች ህወሓት በሶማሊያ በደረሰው ዘግናኝ አደጋ እጁ እንዳለበት ከግምት በላይ የዘለሉ ፍንጮች እየተሰሙ ነው።
በአሜሪካ ባለው የሕግ አሠራር መሠረት የአንድ አገር የፖለቲካ ሹመኛ በቀጥታ በአሜሪካ የህግ አውጪ አካል ላይ (ህወሓት ሰሞኑን በፈጸመው መልኩ) ተጽዕኖ በማድረግ ሕግ እንዳይወጣ የማስቀልበስ ተግባር መፈጸም አይችልም በማለት አንዳንድ ወገኖች ይናገራሉ። የወትዋቾች አስፈላጊነት እየገነነ የመጣውም ከዚህ ሕግ በመነሳት እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህ የሰሞኑ የህወሓት ተግባር አገሪቷን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዳት እንደሚችል አብሮ እየተነገረ ያለ ጉዳይ ነው።
ጭብጦች
- እልቂት ጀብድ የሆነለት አልሸባብ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት) ለደረሰው አደጋ ኃላፊነት አልወሰደም፤
- ህወሓት በሶማሊያ ምድር የድሮውን ሳይጨምር፣ እየለቀቀ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን አልሸባብ እግር በግር እየተከተለ ከተሞቹን መቆጣጠሩ ውስጣዊ ግንኙነት እንዳለ ጠቋሚ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት መጠቆሙ፤
- አሚሶም ከሚባለው የሰላም ግብረኃይል ቁጥጥር ውጪ የሆነ የህወሓት የጦር መሪዎች የሚያዙት ሠራዊት በተደራቢነት በሶማሊያ መሰማራቱ። ይህ ከአሚሶም ማዕቀፍ ውጭ የሆነውና የሕወሃት መሪዎች የሚያዙት ጦር በስትራቴጂና በወል በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንቅፋት መሆኑ በአሚሶም አመራሮች በተደጋጋሚ በቅሬታ ደረጃ መቅረቡ፤ (በዚህ ጉዳይ ላይ ጎልጉል የዘገበውን እዚህ ላይ ይመልከቱ)
- የህወሓት አመራሮች ሲፈልጉ የሚቆልፉት፣ ሲፈልጉ የሚከፍቱት ኮሪደር ማበጀታቸውና ከሁሉም የሶማሊያ የጎሳ መሪዎች ጋር የቆየ ትሥሥር ያላቸው መሆኑ፤ ኢትዮጵያን የማፈራረሱን ትግል በእንጭጩ ደረጃ ሲያካሂዱ ይህንኑ ስልታዊ የፖለቲካ ንግድ ለማዋቀራቸው መረጃ ያላቸው ምስክር መሆናቸው፤
- አልሸባብ በከፍተኛ ደረጃ የስለላና የደህንነት መዋቅር ያደራጁትን ታላላቅ የሚባሉ አገሮች ሲያተራምስ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ጥቃት አለመውሰዱ የሽርክናቸው ማሳያ ስለመሆኑ። ይህንን የሚናገሩ ክፍሎች “ኢትዮጵያውያን ለምን አልሞቱም” ከሚል ርካሽ አስተሳሰብ በመነሳት ሳይሆን ትሥሥሩን ለማሳየት ብቻ ሲሉ መሆኑን መረዳት እዚህ ላይ ልብ ይሏል።
- በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እስካሁን በሰላም ይኖሩ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎች በዘር ሳቢያ ሲፈናቀሉ ዝምታን መምረጡና ከድራማው በስተጀርባ ህወሓቶች ስለመኖራቸው መረጃ መውጣቱ፤
በጥቂቱ የሚወሱ ጭብጦች ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም አክለው እንዲሁም ከህወሓት አጠቃላይ የአሸባሪነት ባህርይ በመነሳት የሰሞኑን አሰቃቂ የሶማሊያ ፍንዳታና ዕልቂት ውስጥ ህወሓት እጁ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት የሚሰጡት።
የHR 128 ጦስ በርካታ የችግር ናዳ የሚያወርድበት መሆኑን የተገነዘበው ህወሓት ከኅልውናው አንጻር ይህንን ረቂቅ ሕግ ለመቀልበስ የማይፈነቅለው የፖለቲካ ድንጋይ አይኖርም በሚለው ሃሳብ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ነው። ወትዋች ከመቅጠር ጀምሮ እኛ ሕጉ ከጸደቀ ከሶማሊያ እንወጣለን፤ ሲቀጥልም አልሸባብ ሶማሊያን ያፈርሳታል፤ እንዲያውም “ሠርቶ ማሳያው” ይህ ነው እስከማለት የቦንብ ፍንዳታውን ለማቀነባበር ህወሓት ቅንጣት ወደኋላ አይልም በሚለው የሚስማሙ ህወሓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያደረገውን እንደ አስረጂ ያቀርባሉ።
መስከረም 6፤ 2009ዓም (September 16, 2006) በአዲስ አበባ በሚኒባስ የፈነዳ ቦምብ በኦነግና በኤርትራ ላይ የተሳበበ መሆኑን የሚያስታውሱ ወገኖች ህወሓት ያኔ የፈጸመውን የአሸባሪነት ተግባር ላሁኑ እንደ ግብዓት ያነሳሉ። ሆኖም ቆየት ብሎ የታተመው የዊኪሊክስ (ሹልክ ዓምድ) ዘገባ ፍንዳታውን አቀነባብሮ ያከናወነው ህወሓት ስለመሆኑ እዚህ ላይ በዝርዝር አስረድቷል። ከበረሃ ጀምሮ ማሸበር ሙያው የሆነው ህወሓት ሥልጣን ይዞም ይህንኑ በደም የተነከረ ታሪኩን ቀጥሎበታል። ታዲያ አሁን ደግሞ HR 128ን ለማምከን ሶማሊያ ቢዘምት ምን ይደንቃል? ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply