“ዕርቅ ብቸኛ አማራጭ ነው” በሚል እምነታቸው ሁሉንም ወገኖች ነጻ ለሚያወጣ ትግል ራሳቸውን የሰጡት ኦባንግ ሜቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጥሪ የመልስ ጥሪ አሰሙ፡፡ ከአቶ ሃይለማርያም የሰሙትን የእንነጋገር ጥሪ በአዎንታዊነቱ ተመልክተውታል፡፡
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ይህንን የተናገሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ያቀረቡትን “ለጋራ አገራችን በጋራ እንወያይ የሚል ጥሪ ማቅረብ ግን እፈልጋለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በተናጠል መወያየት አንደማይቻል የገለጹት ሃይለማርያም፤ በሦስት ደረጃዎች የመደቧቸውን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባወገዙበት መግለጫቸው ማገባደጃ ላይ የእንነጋገር ጥሪ አሰምተዋል፡፡ በግልጽ ተለይቶ ያልቀረበው የእንነጋገር ጥሪ ለአኢጋን መሪ ምላሽ መነሻ ሆኗል፡፡
“ምንም ይሁን ምን ከኢህአዴግ መሪ በጋራ የአገራችን ጉዳይ በጋራ እንወያይ የሚል ጥሪ መሰማቱ አኢጋን የጀመረው የረጅም ጉዞ ውጤት ስለመሆኑ ጥሩ ምልከታ ያሳየ ነው” በማለት አቶ ኦባንግ ተናግረዋል፡፡
“አኢጋን ለጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ሌላ የመልስ ጥሪ አለው” ያሉት “ጥቁሩ ሰው”፣ ኢህአዴግ እኛ እንደጀመርነው ከራሱ ጋር ተነጋግሮ በጋራ አገራችን ጉዳይ ለመወያየትና ለመምከር ከወሰነ በቀጣዩ ዓመት (2015) በኦስሎ በሚካሄደው የዕርቅ ማመቻቻ ጉባዔ እንዲገኝ መጋበዙን ከወዲሁ ማብሰር እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ወደ ዕርቅ ጎዳና መምጣት እንደሚያዋጣው ከማንም በላይ ጠንቅቆ እንደሚረዳ የገለጹት አቶ ኦባንግ “የጋራ ንቅናቄው ለሁሉም ቦታ ስላለው ከኢህአዴግ የሚጠበቀው በሃሳቡ መጽናትና ለጽናቱ ተግባራዊነት የቀረበለትን ግብዣ መቀበል ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ “ቃል እምነት ነው” ያሉት ኦባንግ ከዚህ ካነሰ እና በተግባር የማይገለጽ የጥሪ ቃል ከሆነ እንደተለመደው ተራ የሚዲያ ፍጆታ ከመሆን አያልፍም ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ለቃላቸው እንዲታመኑ አሳስበዋል፡፡
በአውሮጳውያን አዲስ ዓመት የዕርቅ ቦርድ (ኮሚሽን) ለማቋቋም በኦስሎ የሚደረገውን ጉባዔ አስመልክቶ አቶ ኦባንግ ዝርዝር መግለጫ ለጊዜው አልሰጡም፡፡ ይሁን እንጂ የዕርቅን ሥራ ለመሥራት የተጀመረው እንቅስቃሴ አሜሪካንን ጨምሮ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ አገራት ድጋፍ እንዳለው አልሸሸጉም፡፡ “ለአገራችሁ የሚያስፈልጋት ትክክለኛ መፍትሔ ይህ ነው” በማለት ከላይ የተጠቀሱት አካላት “ከዲሲው የአኢጋን ጉባዔ በኋላ አጋርነታቸውን በግልጽ አረጋግጠውልኛል፡፡ ለጊዜው ከዚህ በላይ አስተያየት የለኝም” የሚል ሃሳብ የሰነዘሩት አቶ ኦባንግ “በእርግጠኝነት ጉዞውን ስንጀምር መድረስ የምንፈልግበት ግብ ላይ እንደምንደርስ አውቀን ነው፤ ጉዞው ተጀምሮ እዚህ ደርሰናል ቀጣዩ ጉዞ ይቀጥላል፤ የኦስሎ ጉባዔ አስቀድሞ የተቀመጠ የጉዞው አንድ ፌርማታ ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም አቶ ስብሃት ነጋ በተመሳሳይ የዕርቅን አስፈላጊነት መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ የህወሃት የቅርብ ሰዎች ህወሃት ወደ ዕርቅ እንዲመጣ የማሳመን ሥራ መጀመራቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን አቶ ሃይለማርያም ያቀረቡት የእንነጋገር ጥሪ ድንገት አፈትልኮ የወጣ ሃሳብ እንዳልሆነ አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ ጎልጉል ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ከተለያዩ የማጎሪያ ቦታዎች የሚሰሙት ድምጾች፣ ዓለምአቀፍ ሪፖርቶች፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስና፣ ጥላቻ፣ ወገናዊነት፣ በእምነት ደጆች የተነሱ ተቃውሞዎች፣ ያለ አንዳች ርህራሄ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች፣ ተፈናቃዮች፣ ባይተዋሮች፣ የበይ ተመልካቾች፣ ወዘተ የእነዚህ ሁሉ ድምር በአንድነት የሚያስከትለው መዘዝ ሊጸዳ የሚችለው በይቅርታ ብቻ እንደሆነ ኢህአዴግ በአግባቡ ስለሚረዳ ጥሪውን አናንቆ ማየት አግባብ አይደለም፡፡ የኢህአዴግ በጀት ደጓሚ ምዕራባውያንም ህወሃት/ኢህአዴግን ያነገሡ እንደመሆናቸው እጅ መጠምዘዙንም በውል ያውቁበታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ዘለቀ የከፋቸው ሲበዙ ዓመጽ መነሳቱና አብዮት መቀጣጠሉ እንደማይቀር የተለያዩ አምባገነኖችን መጨረሻ ዋቢ በማድረግ ተናገሩ፡፡ ሐሙስ ዕለት ቪኦኤ ባቀረበው ዘገባ የተደመጡት ይልቃል “ያለአንዳች ፍርሃት እናገራለሁ” በማለት እንደገለጹት ኢህአዴግ በማስፈራራትና በማሰር የሕዝብን ቁጣና ምሬት የማስቆም አቅም ሊኖረው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ሥርዓቱ ከአንገት እስከ እግሩ በሙስና መነከሩን አመልክተዋል፡፡ በእስር ቤት ያሉት ጓዶቻቸው እስር ቤት ካልገቡት ጓዶቻቸው የተለየ የፈጸሙት ተግባር እንደሌለም መስክረዋል፡፡
የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ኢህአዴግን የማስገደድና የማስጨነቅ ሥራ ተጠናቅሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቻ ግመል ሰርቆ የሚለውን ተረት በመተረት የኢህአዴግን ታላቁ የንግድ ኢምፓየር የዝርፊያ ማዕከል መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የአገሪቱን ሃብት ኢህአዴግ ለግል የፖለቲካ ሥራ እንደሚጠቀምበትም አረጋግጠዋል፡፡ በቪኦኤ የቀረቡት ሦስቱም የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎች ይህንን ምላሽ የሰጡት ሃይለማርያም ደሳለኝ ላቀረቡት ውንጀላ ምላሽ ለሰጡት መግለጫ ነው፡፡
በሌላ ዜና ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ የተፈጸመውን ግድያና ድብደባ ተከትሎ የቁጭት አመጽ እንዳይነሳ ሥጋት መኖሩ ተጠቆመ፡፡ ከአካባቢው የሚሰሙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢህአዴግ ለፈጸመው ግድያና ድብደባ የነዋሪዎች ቁጣና የበቀል ስሜት ሊሸሸግ የሚችል አይደለም፡፡ ለዚህ ይመስላል ቪኦኤ ያናገራቸው ሰው ጥበቃው በከፍተኛ ደረጃ መጠናከሩን ያረጋገጡት፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት እዚሁ ባህርዳር እንግሊዛዊው በነፍጥ አንጋቢ መገደሉ የውጥረቱ መጠን የት እንደደረሰ እንደሚያሳይ ተነግሯል፡፡ ከጸጥታው ጋር በተያያዘ የበቀል ዓመጹ ወደ ወረዳና ቀበሌ አድባራት ብሎም ወደ ሌሎች ዞኖች እንዳይዛመት የኢህአዴግ የገጠር መዋቅር ሌት ተቀን የመረጃ ልውውጥ እንደሚያካሂድ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ወደ ከተማዋ ከተላኩት ነፍጥ አንጋቾች በተጨማሪ ሲቪል የለበሱ ሰላዮች ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ ከአካባቢው የሚገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ት/ቤቶችና በአጠቃላይ የትምህርት ማዕከላት የክትትሉ ቁልፍ ቦታዎች ናቸው፡፡
የባህር ዳር ሟቾች ቁጥር ስድስት መድረሱን ቪኦኤ ያነጋገራቸው የሆስፒታል ምንጮቻቸውን ጠቅሰው አመልክተዋል፡፡ በወቅቱ ምንጮቼ ሰው እንደሞተ ማረጋገጥ አልቻሉም በማለት የዘገበው ሪፖርተር በረቡዕ ዕትሙ ፖሊስን ጠቅሶ አንድ ሰው ሞተ፤ ምንጮቹን ጠቅሶ ሦስት ሰው ሞተ፤ የተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ደግሞ ጠቅሶ አምስት ሰው ሞተ ሲል ወጥነት የሌለው ዜና ማቅረቡ ለዜናው የሰጠውን ደንታቢስነት የሚያሳይ እንደሆነ ቅሬታ የተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ አስቀድሞም ቢሆን የሟቾቹ ቁጥር በትክክል አይገለጽ እንጂ ሪፖርተር ከስፍራው በቂ መረጃ ደርሶት እንደነበር የሚያውቁ ትዝብታቸውን “ጊዜ ይፍረድ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጉዳት ደረሰባቸው የተባሉትን አስመልክቶ ማኅበራዊ ገጾች በፎቶ አስደግፈው ካቀረቡት መረጃ በስተቀር ቁጥራቸው፣ የጉዳታቸው መጠን፣ ግለ መረጃዎች፣ ወዘተ ዘርዝሮ ያቀረበ አካል የለም፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ተቋምነት የሚታወቁ ማኅበራት፣ አድባራት፣ ሰባካ ጉባዔዎች፣ የፓትርያርኩ ጽ/ቤት፣ ሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ያቀረቡት ውግዘትም ሆነ አንዳች ነገር እስካሁን አልተሰማም፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply