በጋምቤላ ክልል በግብርና ሥራ የተሰማራው የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ኩባንያ ሳዑዲ ስታር የግብርና ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የፋይናንስ ቀውስ ስላጋጠመው ፕሮጀክቱ ከመጓተቱም በላይ ከሁለት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ከሥራ መፈናቀላቸው ታወቀ፡፡ ችግሩ ቢኖርም መፍትሔ እንደሚፈለግም እየተነገረ ነው፡፡
አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ሳዑዲ ስታር ሥራ የጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት በ2001 ዓ.ም. አካባቢ ነበር፡፡ ከፕሮጀክቱ ጥቂት ፈቀቅ ብሎ ደግሞ በደርግ መንግሥት የተገነባው የአልዌሮ ግድብ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ግድቡ በዋናና መጋቢ ቦዮች አማካይነት የሳዑዲ ስታርን የሩዝ እርሻ በመስኖ ለማልማት ብቸኛው የውኃ ምንጭ በመሆኑ፣ ለሩዝ እርሻው ወሳኝነቱ ጥያቄ እንደሌለው በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡
ወደ ሥራው ከመገባቱ ቀድሞ ጥናት እንዲያጠና የተወከለው የፓኪስታን ኩባንያ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ጥናቱን ተከትሎም የፓኪስታን ዝርያ የሩዝ ዘር ከመጣ በኋላ፣ ከአልዌሮ ግድብ አጠገብ እንዲተከል ተደርጓል፡፡ የችግኝ ምርምሩና ሙከራው ተሳካና የፓኪስታኑ ኩባንያ እርሻውን እንዲተክል ውል መግባቱን ውስጥ አዋቂዎቹ ይገልጹታል፡፡ ፕሮጀክቱ ስምምነት ተደርጎበት ካለቀ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ2002 ዓ.ም. ሳዑዲ ስታር በ80 ሚሊዮን ዶላር የካተር ፒለር ከፍተኛ የእርሻ የማሽነሪዎች ግዥ ፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ እንዲጓጓዙ አድርጓል፡፡ መሬት የማስተካከልና የመመንጠር ሥራው የግብርና ቴክኒክና እርሻ መሣርያዎች ኢንተርፕራይዝና የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና ለሌሎች የአገር ውስጥ ድርጅቶች ተሰጥቶ በአንድ ዓመት ውስጥ ሦስት ሺሕ ሔክታር መሬት መመንጠሩም ተረጋግጧል፡፡
በዚሁ በ2002 ዓ.ም. የስዊድን ኩባንያዎች እንዲመጡ ቢደረግም ለወራት ያለ ሥራ በመቀመጣቸውና ለቦይ ግንባታ ሥራም ልምድ ያልነበራቸው በመሆኑ ምክንያት ተመልሰው ለመሄድ እንደተገደዱም ጉዳዩን የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ናሽናል ኢንጂነሪንግ ሰርቪስስ ኦፍ ፓኪስታን የተባለ የዲዛይን ሥራ ኩባንያ የ30 ኪሎ ሜትር የዋናውን ቦይ፣ የ13 ኪሎ ሜትር መጋቢ ቦይና የአራት ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን የሚያካትት የመስኖ ሥራ ዲዛይን እንዲያደርግ ቢታጭም ግማሽ ያህሉን ሥራ ብቻ እንዳገባደደ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሚድሮክ ግሩፕ መሐንዲሶችም ቢሆኑ ፕሮጀክቱን ለማከናወን የሚያስችል የሥራ ልምድና ብቃት ስለሌላቸው ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በ2003 ዓ.ም. ፕሮጀክቱን ጥለው እንደወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኤስኤንሲ የተባለ የካናዳ ተቆጣጣሪ ኩባንያም በፕሮጀክቱ እንዲሳተፍ ተደርጎ እንደነበርም ታውቋል፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ በ2003 ዓ.ም. ለመስኖና ለቦይ ሥራዎች የተገባ ልምድ ያለው ኩባንያ መሳተፍ እንዳለበት የፕሮጀክቱ ባለንብረት እንደወሰነ ምንጮች ሲያስታውሱ፣ ውሳኔውን ተከትሎ በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ላይ ሁለት የቻይና እንዲሁም ሦስት የፓኪስታን ኩባንያዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም ጉላም ራሱል ኤንድ ካምፓኒ የተባለ ድርጅት ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረቡ፣ የ30 ኪሎ ሜትር የዋናውን ቦይ ግንባታና የመጋቢ ቦዮች ግንባታ ለማከናወን ጨረታውን ማሸነፉ የተነገረውም ከሦስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ጨረታውን ያሸነፈው ይህ ድርጅት ሥራውን የጀመረ ሲሆን እስካሁን የ30 ከመቶ ሥራ ማከናወኑም ተነግሮለታል፡፡
ሆኖም የቦይ ግንባታ ሥራው ከጥቂት ወራት በፊት የተቋረጠ ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ የፕሮጀክቱ ባለቤት ለተቋራጩ የውጭ ኩባንያን በሠራው መጠን ሊከፍለው የሚገባውን ክፍያ በጊዜው ባለመፈጸሙ እንደሆነ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ተቋራጩ በገጠመው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ምክንያት በሥራ ያሳትፋቸው የነበሩ በርካታ ሠራተኞችን ለመበተን እንደተገደደም ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተመሳሳይ ችግር የካናዳው አማካሪ ኩባንያ ባለፈው ሰኔ ወር፣ የፓኪስታኑ የዲዛይን ኩባንያም በቀጣዩ ሐምሌ ወር ፕሮጀክቱን ተሰናብተው መሄዳቸው ተረጋግጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ ስታር ፕሮጀክት ውስጥ የሚገኘው ብቸኛው ኩባንያ የእርሻ ሥራ የሚያከናውነው ኤምሲጂ የተባለው ድርጅት ብቻ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ምንም እንኳ በሔክታር እስከ ሰባት ቶን የሚደርስ ሩዝ በእርሻ ሞክሮ ውጤታማነቱን ቢያመሰክርም፣ ከሳዑዲ ስታር ጋር የነበረው ውል ሊታደስለት ባለመቻሉ ምክንያት ሥራውን አቋርጦ ሊወጣ እንደሚችል ሪፖርተር ያነጋገራቸው ውስጥ አዋቂዎች አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ኩባንያም ቢሆን ለአንድ ዓመት ያህል ከሳዑዲ ስታር ክፍያ ሳያገኝ ሲሠራ የቆየ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ኤምሲጂ ኩባንያ ከሩዝ እርሻው ባሻገር የሩዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካውንም እንዲገነባ ስምምነት ያለው በመሆኑ በግንባታ ሒደት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
ለሳዑዲ ስታር ፕሮጀክት ቅርበት ያላቸው አካላት የሚደርሱበት ድምዳሜ እንደሚያመላክተው፣ ፕሮጀክቱ እውን ሊሆን የሚችልና ውጤታማነቱም የተረጋገጠ ቢሆንም፣ በአስተዳደር ችግር ምክንያት ማጥ ውስጥ መግባቱን ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ ሲባል ከይዞታቸው የተፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸው እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ተግባራዊ ለማይደረግ ፕሮጀክት መፈናቀላቸውን በመቃወም ድምፃቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡
ከሁለት ሺሕ በላይ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ሥራ ባለመኖሩ ምክንያት ሥራ ፈት ሆነው መቀመጣቸው ሲታወቅ፣ አብዛኞቹ ሠራተኞች በውጭ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው ሊያገኙ ይችሉ የነበረው ልምድና ተሞክሮም መክኖ መቅረቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ያብራራሉ፡፡
ሳዑዲ ስታር የያዘውን አሥር ሺሕ ሔክታርና በአገሪቱ የሚገኙትን ሰፋፊ እርሻዎች የሚያስተዳድረው የግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ጽጌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሳዑዲ ስታር እንቅስቃሴ እየተዳከመ ነው፡፡ ‹‹የኩባንያው እንቅስቃሴ እንደ አጀማመሩ አይደለም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ መስተጓጎል የሳዑዲ ስታር ባለቤት የሆኑትን ሼክ ሙሐመድ አል አሙዲንና የሳዑዲ ዓረቢያን ስም የሚያጎድፍ ከመሆኑም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስኪታክት የተወራለት ይህ ፕሮጀክት መና መቅረቱ ሁለቱን አካላት በሕዝቡ ዘንድ ለከፍተኛ ትችትና ወቀሳ እንደሚያጋልጣቸውም ተቺዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ወደ አገር ውስጥ የገቡት ማሽነሪዎች ያለ ሥራ በመቀመጣቸው ሳቢያ ለብልሽት የመዳረጋቸው ሥጋትም ታሳቢ እንደሚደረግ ሲገለጽ፣ ሳዑዲ ስታር በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ሊፈታ ካልቻለ በፕሮጀክቱ እንዲሳተፉ ከጠራቸው የውጭ ኩባንያዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ሥጋታቸው የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም፡፡
በመሆኑም የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ሳዑዲ ስታር ሥራውን በአፋጣኝ ጀምሮ የተቋረጠው የሥራ ዕድልም ይቀጥል ዘንድ መንግሥት ጣልቃ ይገባ ዘንድ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ በእስካሁኑ የፕሮጀክቱ የሥራ ሒደት አሥር የአገር ውስጥና የውጭ ዜጎች መገደላቸውን ያስታወሱት የክልሉ ተወላጆች፣ ይህን መሰሉን ጥቃት ለማስታገስና ለጉዳቱም ማርከሻ ይሆን ዘንድ የተቋረጠው ሥራ ቀጥሎ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድሉ በአፋጣኝ እንዲሰጣቸው ያደርግ ዘንድ ለመንግሥት ተማፅኖ አቅርበዋል፡፡
ሳዑዲ ስታር በእርሻ ሥራ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት በአሥር ሔክታር መሬት ላይ ሩዝ ሲያለማ አምስት ሺሕ ሠራተኞች እንደሚቀጥር፣ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ፣ በተጨማሪም 13 ሺሕ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሠረተ ልማት በተለይም መንገድና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት እንደሚከፍት ቃል ገብቷል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት ዋነኛው ፋይናንስ አቅራቢ ሳዑዲ ዓረቢያና ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ናቸው፡፡ ነገር ግን የኩባንያው ምንጮች ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንደገባና የማኔጅመንት ችግርም እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የኩባንያው ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሳዑዲ ስታር የፋይናንስ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ ችግሩም የራሱ የኩባንያው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ከዚህ ችግር ውስጥ እንደሚወጣና ሥራው በተቃና መንገድ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ (ሪፖርተር)
Leave a Reply