ትናንት ኅዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በመላው ዓለም ይፋ የሆነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ተቋም የሙስና አመላካች ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከሙስና ጽዱነት ተርታ ውጭ ከሆኑና በሙስና ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈረጁ አገሮች አንዷ ሆና መገኘቷን ይፋ አደረገ፡፡
ሪፖርቱ በሚከተለው የሙስና መለኪያ ሚዛን መሠረት፣ ከሙስና ጽዱ የሚባሉ አገሮች ከዘጠና እስከ መቶ ነጠብ የሚያገኙት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል፣ የሙስና ጎሬ ሆነዋል ተብለው የሚታሰቡ አገሮች ደግሞ ከመለኪያው ከ50 በመቶ በታች የሚያስመዘግቡት ናቸው፡፡ በመንግሥት ተቋሞች ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል ተብለው ከተለዩት ውስጥ ኢትዮጵያ 33 ከመቶ የመለኪያውን ነጥብ በማስመዝገብ ከከፍተኛ ሙስኞች ተርታ እንደምትሰለፍ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ ከ177 አገሮች ውስጥ 111ኛውን ደረጃ መያዟም በሪፖርቱ ይፋ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው አገሮች ለሙስና ተጋላጭነት ከሚለኩባቸው መመዘኛዎች መካከል፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የተጠያቂነትና የሰዎች የመደመጥ መብት፣ የፍትሕ አካላት ከተፅዕኖ ነፃ መሆን፣ የሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ ልማት መለኪያና ሌሎችም ጠቋሚዎች እንደሚካተቱ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በድረ ገጹ ይፋ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከ179 አገሮች 127 ደረጃን በመያዝ የፕሬስ ነፃነት ከሌሉባቸው አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ በፍትሕ አካላት ነፃነትና ከተፅዕኖ ውጭ ካልሆኑ አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን ከ142 አገሮች ውስጥም 93ኛ መሆኗ ይፋ የተደረገው ዓምና ነበር፡፡
ተቋሙ 177 አገሮችን በሙስና እንደሚጠረጠሩበት ደረጃቸው በመመዘን ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገሮች 90 ከመቶው ለሙስና በሚያስጠረጥራቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆነው አግኝቷቸዋል፡፡ ቦትስዋና ከሰሐራ በታች አገሮች ዝቅተኛ የሙስና ወንጀል የሚፈጸምባት ስትሆን፣ ሶማሊያ ከሁሉም አገሮች በታች በመሆን ሙስና የተንሰራፋባት ተብላለች፡፡ በዓለም ላይ ከ177ቱ ውስጥ 69 ከመቶ አገሮች ከፍተኛ የሙስና መናኸሪዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያረጋግጣል፡፡
ከሰሐራ በታች የሚገኙትን አገሮች በሙሰኝነት ተፈርጀው የሚመሩት የምሥራቅ አውሮፓና እስያ አገሮች ሲሆኑ፣ 95 ከመቶ በላይ አገሮች ከፍተኛ ሙሰኞች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
በዓለም ላይ ከፍተኛ ሙስና ከተንሰራፋባቸው አሥር አገሮች ስድስቱ ከሰሐራ በታች አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ (ሪፖርተር)
Leave a Reply