ከ17ሺህ በላይ ሰዎች ያሳተፈው የሰባት ወር ጥናት ይፋ ሆኗል
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ በደቡብ ክልል የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ያስጠናው ጥናት ውጤት ዛሬ ይፋ ሆነ። በጥናቱ የተሳተፉት ክልል የመሆንን ጥያቄ በዕርጋታ እንዲታይ ተናግረዋል።
ላለፉት ሰባት ወራት በምሁራን የተካሄደው የደቡብ ክልል አዲስ አከላለልን የተመለከተው ጥናት ውጤትን በተመለከተ ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች ረቡዕ ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የደቡብ ክልል የብዝሃነት ምልክት አብሮ የመኖር አርአያ መሆኑን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች የክልል ምስረታ ጥያቄ በክልሉ በስፋት ቀርቧልም ብለዋል።
የጥናት ቡድኑ ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተውጣጡ ምሁራንን የያዘ ሲሆን፥ ምሁራኑ በአንትሮፖሎጂ፣ ታሪክ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ፖለቲካ ሳይንስና ፌዴራሊዝም ተመራማሪና ልሂቃን ናቸው።
በጥናቱ ከአንድ ዞን በስተቀር በሁሉም የደቡብ ክልል ዞኖች የተውጣጡ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች መረጃ ተስብስቧል። ጥናቱ የ1987ቱን የደቡብ ክልል አደረጃጀት ሂደት፣ የክልሉ ሕዝቦች በአከላለሉ ያገኙት ትሩፋት እና የአዳዲስ ክልሎች ምስረታ ጥያቄ መንስኤዎች ተዳስሰዋል።
የ1987ቱን የደቡብ ክልል አወቃቀር በፌዴራል መንግስት ውሳኔ በዘፈቀደ ነው ወይስ የክልሉ ህዝብ ተሳትፏል በሚለው ጉዳይ ህዝብ የሰጠው ምላሽ የደቡብ ክልል በመንግሥት ተጠፍጥፎ የተሠራ አይደለም የሚል ሆኗል። የክልሉ ምሁራን ያለ መንግሥት ተፅእኖ ክልሉ በደቡብ ክልልነት እንዲመሠረት ተስማምተው ክልሉ መመሥረቱን ተናግረዋል።
የጥናት ቡድኑ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት 20 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ላለፉት ሰባት ወራት ሰፊ ጥናት ሲያካሂድ ቆየቷል። በዚህም መሠረት ሶስት አማራጮችን አስቀምጧል ብለዋል ምክትል ሰብሳቢዋ።
በጥናቱ የተለየው የመጀመሪያው አማራጭ አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ አሁን ያለው የክልሉ አደረጃጀት ቢቀጥል የሕዝቦችን አብሮነትና ያጠናክራል፤ ጠንካራ የደቡብ ሕዝቦች ክልልንና የኢትዮጵያን አንድነት ያጠናክራል የሚል ነው።
በጥናቱ የተለየው መጀመሪያ አማራጭ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ተቀባይነት የሚያጣ ከሆነ በጥናቱ በሁለተኝነት የተለየው አማራጭ ደግሞ ክልሉን በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በመክፈል ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ የፍትሐዊነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
በጥናቱ በሶስተኝነት የተቀመጠው ሃሳብ ደግሞ ሁለቱ አማራጮች ተግባራዊ የማይሆኑ ከሆነና ሁኔታው ከክልል አልፎ በአገሪቱ ሰላምና አንድነት ላይ ጫና የሚፈጥር ከሆነ ጉዳዩ ለጊዜው ቢቆይና በእርጋታ ቢታይ የሚል ነው። እንደጥናት ቡድኑ ምክትል ሰብሳቢ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች በላይ ለጥናቱ በመረጃ ሰጪነት ተሳትፈዋል።
ጎልጉል ከኢፕድና ከፋና ካገኘው ዜና ያጠናቀረው
Leave a Reply