
የዘወትር የድረገጻችን ተሳታፊ የሆኑ ይህንን ጽሁፍ እንድናነበውና እንድናትመው በላኩልን መሠረት እነሆ ለአንባቢዎቻችን አቅርበነዋል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለጸሐፊዋ ማሕሌት ፋንታሁን ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
የደሞዝ Vs. የጠብሽ* ሰሞን
አነጋገራችንን፣ አካሄዳችንን፣ አበላላችንን፣ አስተያየታችንን ባጠቃላይ የምናደርገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ቀጥጠኛ አስተዋፅኦ ካላቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው በኪሳችን ያለው ገንዘብ ዋነኛው ነው፡፡ ገንዘብ ከምናገኝባቸው አንዱ መንገድ ደግሞ ተቀጥሮ መሥራትና ወር ሲያልቅ የሠራንበትን ክፍያ/ደሞዝ ማግኘት ይገኝበታል፡፡ አብዛኛው በከተማ አካባቢ የምንኖር በዚህ መስመር ውስጥ እንገኛለን፡፡
ደሞዝ ተቀብሎ ቀጣዩን የደሞዝ ቀን እንደ ምፅአት ቀን በጉጉት የማይጠብቅ ካለ ይህ ሰው ከደሞዙ ውጪ ሌላ ተጨማሪ ገቢ አለው ወይም አንድ ቀልድ ላይ እንደሰማሁት በአስማት ነው የሚኖረው ማለት ነው፡፡ ደሞዛችን እዛው እንዳለ ወይም በተወሰነ ጭማሪ… ብቻ ኑሮ ግን በብዙ እጥፍ ጨምሮ መኖር መቻላችን እውነትም አስማተኛ ያስብላል፡፡ እንደየደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ አብዛኛው ደሞዝተኛ ደሞዝ ከተቀበለ በኋላ ካሉት የተወሰኑ ቀናት ውጪ ለመጪው የደሞዝ ቀን ስንት ቀን እንደቀረው በመቁጠር፤ ቀሪውን ጊዜ በብድር እንዴት እንደሚያሳልፍ በማውጠንጠን፤ የሰቀቀን ኑሮ መኖሩን የተለማመድነው ይመስላል፡፡
የደሞዝ ሰሞንና የጠብሽ ሰሞን እንደየሰው ይለያያል፡፡ በአብዛኛው ደሞዝ ከተቀበሉ ከ10-15ኛው ቀን በኋላ ሰሞነ ጠብሽ ይገባል፡፡ ደሞዝ የተቀበሉ እለትም ደሞዟ ብድር ብቻ ከፍላ የዕለቱለት ጠብሽ የሚጀምርበት አጋጣሚም አለ፡፡ የበዓል ወቅቶች እና ጳጉሜ ወር “የጠብሽ” ወቅትን ከሚፋጥኑ/ከሚያረዝሙ ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጳጉሜ ወር ግን ለምን ደሞዝ እንደሌላት ሁሌም ይገርመኛል፡፡ በዛ ላይ የአዲስ ዓመት ወጪ ተጨምሮበት አስቡት፡፡
Leave a Reply