1. መግቢያ
ከደርግ የ17 አመታት የአገዛዝ ውደቀት በኋላ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በስፋት ሲንጸባረቁ ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ ዋነኛው ነው:: በዚህ ወቅት ውስጥ ለብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ በፖለቲካ ኃይሎች የቀረቡት የመፍትሔ ሃሳቦች የተለያዩ ቢሆንም የመፍትሔ ሃሳቦቹ የሚመነጩት ግን በዋናነት ከሁለት ተገዳዳሪ አስተሳሰቦች ነው:: አንደኛው አስተሳሰብ የሚያጠነጥነው የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄው የሚካትተው ከኢትዮጵያ ዘመናዊ የሃገር ግንባታ ጋር ተያይዞ የተፈፀሙ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትንና በደሎችን እንዲሁም በያ ትውልድ ውስጥ የተፈፀሙ መጠፋፋትን አካቶ ሁሉን-አካታች መድረክ በማዘጋጀት ያለፈውን በደሎች ዕውቅና በመስጠት በፖለቲካ ሊህቃን መካከል መግባባትን ማስፈንን ነው:: ሁለተኛው አስተሳሰብ የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄን የሚመለከተው ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በአዲስ መሰረት ላይ የመገንባት ሂደት አድርጎ ነው:: ይህም ማለት የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ የሚያቅፈው ሁሉንም አይነት ማለትም ብሔር፣ ሃይማኖት እንዲሁም መደብ ላይ መሰረት ያደረገ ኢ-ፍትሃዊነትና መገለልን ከኢትዮጵያ ዘመናዊ የሃገር ግንባታ (1855 እ.ኤ.አ) ጀምሮ የኢህአዴግን የአገዛዝም የሚያካትት ነው::
በሁለቱ አስተሳሰቦች መካከል ያለው ልዩነቶች የሚከተሉት ናቸው:: የመጀመሪያው አስተሳሰብ ብሔራዊ ዕርቅን እንደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲያይ፤ ሁለተኛው አስተሳሰብ ብሄራዊ ዕርቅን እንደ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮችን የሚያካትት እንደ ሁሉን አቀፍ የመፍትሔ ሃሳብ ነው:: በተጨማሪም፣ ብሔራዊ ዕርቅን እንደ ፖለቲካ መፍትሔ የሚያራምዱት በአብዛኛው እራሳቸውን <<የአንድነት ኃይሎች>> ብለው የሰየሙት የፖለቲካ ኃይሎች ሲሆኑ፤ብሔራዊ ዕርቅን እንደ-ሁሉን አቀፍ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያዩት በአብዛኛው ብሔር ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች ናቸው:: <በአንድት ኃይሎች> ውስጥም ቢሆን በሀገር ቤት የሚንቀሳቀሱት ኢህአዴግን እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል በብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንደለበት ሲያመለክቱ(ዕርቅን ከፍትህ ሲያስቀድሙ)፤ከሀገር ውጭ የሚንቀሳቀሱት(ፍትህን ከዕርቅ የሚስቀድሙ ናቸው::) ግን ይህን አይደግፉም:: በብሔር ላይ የተመሰረቱትም ውስጥም ኢህአዴግ የብሔራዊ ዕርቅን አሁን ባለው “ህገ መንግስት” ላይ መግባባትን የመፍጥር ሂደት አድርጎ ሲመለክት (reconciliation as a means of defending the status quo)፣ በተቃዋሚነት ጎራ ውስጥ ያሉት ደግሞ የብሔራዊ ዕርቅ ሂደትን ባለፉት አገዛዞች (የኢህአዴግን ዘመንንም ይጨምራል) ለተፈጸመባቸው በደሎችና መገለሎች ዕውቅና የመስጠትንና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍትሃዊነትን (reconciliation as an instrument to create and maintain a system of balance of power) እንደሚያሰፍን ሂደት አድርገው ይገልጹታል:: በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ የሚያራምዱ ቢሆንም የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄና አስፈላጊነቱ ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ የላቸውም:: ስለዚህም ሁሉም <የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ> ቢያራምዱም ቃሉ ያዘለው የተለያዩ ትርጓሜዎች ከመሆኑም በላይ የተግባር እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል::
የዚህ ፁሁፍ አላማ ከላይ በተጠቀሱት የአስተሳሰብ ልዩነቶች ምክንያት የብሔራዊ እርቅ ከገባበት ቅርቃር (deadlock) ውስጥ የሚወጣበትንና በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሰረት ለምንፈልገው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እንደ አንድ ዋና ምሶሶ ጭምር የምንጠቀምበትን አግባብ ለመጠቆም ነው:: ስለዚህም፣ ይህ ጹሁፍ መጀመሪያ የብሔራዊ ዕርቅ ትርጓሜና አስፈላጊነት በአጭሩ ይዳስሳል፤ ቀጥሎም ለምን በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዕርቅ አስፋላጊነት እንደሆነ ያመላክታል፣ በመቀጠል የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎችና የመፍትሄ ሃሳቦችን ያስቀምጣል፤ በስተመጨረሻም የፁሁፉ ማጠቃለያ ሃሳብ ይቀርባል::
2. ብሄራዊ ዕርቅ ትርጓሜና አስፈላጊነቱ
በአንድ መህበረሰብ ውስጥ ጉልበትን መሰረት ያደረጉ የቅራኔ አፈታት ሂደቶች ከሚያስከትሏቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በተጨማሪ ውድ የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት መጥፋትን፣ በሰዎች ልቦናና ህሊና ውስጥ የበቀልና የጥላቻ ስሜትን ያስከትላሉ:: ብሔራዊ ዕርቅም በሰው ልጆች ልብና አእምሮ ውስጥ የሰረጹትን የበቀልና የጥላቻ ስሜት የሚሻርበትና በምትኩ በሰላምና ፍቅር ላይ የተመሰረቱ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች እንዲያብቡ መንገድ የሚከፍት ነው:: ምንም እንኳን የተለያዩ ምሁራኖች የተለያዩ ፍቺ ቢሰጡትም በአመዛኙ የሚስማሙበት ትርጓሜ- ብሔራዊ ዕርቅ ያለፈውን በደልና ጥላቻ እንዳይደገሙ የሚያረግና የሁሉም የጋራ የሆነች አገርን የመገንባትና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ማለት ነው [i]::
የጋራ ነገን የመፍጠር ሂደት የሚመሰረተው ደግም ያለፍን የቁርሾ ማህበረሰባዊ ግንኙነት በመሻርና አዲስ አስተሳሰብና የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ማህብረሰባዊ ግንኙነት ሲተካ ነው:: ብሔራዊ ዕርቅ ሀገራዊ መግባባትን ከማስፍን፣ ያለፈን በጎ ያልሆነ ማህበረሰባዊ ክፍፍሎሽንና ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ከማስወገድ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ እና ሁሉን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ሀገራዊ አንድነትን ከመገንባት አንጻር ያለው ጠቃሚነት ጉልህ ነው [ii]::
ይኸም ማለት ብሔራዊ ዕርቅ የአጭር ጊዜ ፕሮጀክት ሳይሆን የራሱ የሆነ ሂደት ያለው ሆኖ ያለፉት በደሎችና ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ድርጊቶች ለመፈጸማቸው እውቅና መስጠትን (Acknowledgment)፣ የተፈጸሙትን በደሎች ያስከተሉት ውጤቶች ላይ፣ ተጎጂዎች የከፈሉት መስዋትነት እና እንድምታ ላይ ስምምነት መድረስን (Consensus building)፣ የተፈጸሙት በደሎች በድጋሚ እንዳይፈጸሙና የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎትና ደህንነት የሚያረግገጥ ስርአት ለመፍጠር መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣትና የፖለቲካ ውህደትን ማሳለጥን (Structural changes and institutionalization of the process of political integration)፣ ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በማምጣት የኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማረጋገጥና (enhancing socio-economic development and economic integration) እንዲሁም በባለፉት ስርአቶች የተገለሉትን የማህበረሰብ ክፍሎች ይበለጥ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻልን የሚጠይቅ ነው [iii]::
ስለዚህም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ስኬታማነትም ሆነ ዘላቂነት የሚወሰነው ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች መሟላት አለሟሟላት ላይ ነው:: በመሆኑም ብሔራዊ ዕርቅ በራሱ እንደ ውጤት የሚታይ ነው:: ብሔራዊ ዕርቅን ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጋር አያይዘን ካየነው፤ ብሔራዊ ዕርቅ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እንደ ግብአትም የሚታይ ነው [iv]:: በአንባገነናዊ ስርአቶች ውስጥ ስርአቶቹ ከሚፈቅዷቸው ውጭ ያሉ ተጻራሪ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን ለማዳፈን ጉልበትን መሰረት ያደረገ አካሄድ ይከተላሉ:: ዴሞክራሲያዊ ስርአቶች ከአምባገነን ስርአቶች የሚለዩበት ዋናው ቁም ነገር ተጻራሪ ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን ከጉልበት ነጻ በመሆነ መንገድ የማመቻመች (compromise) እና ተቋማዊ ገጽታ በማላበስ (institutionalization of conflicts) ስርአት አልበኝነትና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መድረግ መቻላቸው ነው:: ይኸም ማለት አንባገነናዊ አገዛዞች ልዩነቶችን የሚያስተናግዱበት መንገድ አንዱን ወገን ተጠቃሚ አንዱን ደግሞ አግላይ ያደረገ ሰለሚሆን በማህበረሰቡ ውስጥ የአሸናፊና የተሸናፊን ስነ-ልቦና የሚፈጥር ነው:: አሸናፊው ቡድን አሸናፊ ሆኖ የሚቆየው የራሱን አቅም በቀጣይነት በመገንባትና ተሸናፊውን ይበልጥ አቅመ-ቢስ ለማድረግ በሚደረገው ትግል ውጤታማነት ልክ ነው:: ተሸናፊው ቡድንም ተሸናፊ ሆኖ የሚቆየው የራሱን አቅም በመገንባትና የአሸናፊውን አቅም በማዳከም ተገዳዳሪ ኃይል እስኪሆን ድረስ ነው:: በመሆኑም በአምባገነን ስርአቶች ውስጥ የሚፈጠሩት የማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ምቹ ያልሆኑ ናቸው::
በዴሞክራሲያዊ ስርአቶች ውስጥ ግን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ያሏቸውን ፍላጎቶችና ጥያቄዎቻቸውን የሚዳኙባቸውን ህጎችና አግባቦች በስምምነት(ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ወይም አብዛኛው ክፍሎች) የሚያጸድቋቸው በመሆኑ ለነዚህ ህጎችና አግባቦች እንዲሁም እነዚህን ህጎችና አግባቦች ተፈጻሚ ለሚያደርጉ ተቋሞች ስር ለመዳኘት የውዴታ ግዴታ የሚገቡበት ነው[v]:: ብሔራቂ ዕርቅም ባለፉት የአንባገነናዊ የአገዛዝ ስርአቶች የተፈጠሩ ኢ-ፍትሃዊ ድርቶችና በደሎች ያስከተሉትን በጎ ያልሆነ ማህበረሰባዊ ክፍፍሎሽ እና አንዱን የማህበረሰብ ክፍል ጠቃሚ ሌላውን ጎጂ (win-lose) ያደረገውን የፖለቲካ ባህል በመሻር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች አሸናፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ (win-win) ፖለቲካዊ ባህል ለመገንባት አስተጽኦው ከፍተኛ ነው:: ስለዚህም፣ ብሔራዊ ዕርቅ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት መሳካት ከሚጫወተው ሚና አንጻር እንደ አንድ ወሰኝ ምሶሶ የሚታይ ነው::
3. በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዕርቅ አስፈላጊነት
በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ ዕርቅ የሚስፈልግበት ምክንያቶችን በ ሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል:: እነርሱም:-
ሀ) በኢትዮጵያ የሀገር ምሰረታ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማረም
የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ሌሎች ሀገሮች ታሪክ ለታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተተወ ሳይሆን የፖለቲካ አቋሞች የሚያዝበት ጉዳይ ነው:: ከአጼ ቴዎድሮስ የዘመናዊ መንግስት ምስረታ እንቅስቃሴ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተነሱ የፖለቲካ ልዩነቶችና የፍላጎቶች ግጭቶች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሊፈቱ የተሞከሩት ጉልበትን መሰረት ባደረገ የአፈታት ዘዴ ነው:: በዚህም የተነሳ ችግሮች እየተንከባለሉ ሳይፈቱ በመቅረታቸው ውስብስብና በጣም ስር እንዲሰዱ ሆነዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገር ምስረታ ሂደት ፖለቲካዊው እንድምታው ያልተማከለና በጣም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መመስረት ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊው እንድምታው ደግሞ በጦር አሸናፊ ሆነው የማዕከላዊ መንግስት ምስረታን ሂደት የተቆጣጠሩትን ኃይሎች የኢኮኖሚ ጥቅሞችን የማስከበር ሂደት ነበር [vi]:: ይህ የሀገር ምስረታ ሂደት በመሰረቱ ሁለት አይነት ልሂቃንን ፈጥሯል:: አንደኛው የልሂቃን ክፍል እራሱን እንደ <ሀገር አቅኚ> እና <የዘመናዊ ስልጣኔ ምንጭ> ሲቆጥር ሁለተኛው የልሂቃን ክፍል ደግሞ እራሱን <ኢኮኖሚያዊ መሰረቱን> እንደተነጠቀና እና ከፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስልጣን እንደተገፋ የሚቆጥሩ ናቸው:: ስለዚህም፣ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሀገር አመሰራረት ሂደት ላይ ተቀራራቢ የሆነ አረዳድ በተለያዩ ልሂቃን ውስጥ የለም:: እነዚህ ልሂቃኖች የሚያራምዱት ፖለቲካና በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ የሚፈልጉት ዴሞክራሲያዊ ስርአት መነሻ ምንጩ ባላቸው የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ አረዳድ ነው::
ይህ የልሂቃኖቻችን የዴሞክራሲ አረዳድ በመሰረቱ ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸው አረዳድ ነጸብራቅ ነው:: የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሀገር ምስረታ ሂደት በጦርነትና በማስገበር የታጀበ ነው:: ምንም እንኳን በኢትዮጵያም እንደሆነው ሁሉ በተወሰነ መልኩ ሁሉም ሀገሮች ሲመሰረቱ ጉልበትን መሰረት ያደረገ አካሄድ ቢጠቀሙም፤ የኢትዮጵያ የሀገር ምስረታ ፕሮጀክት ሲያልቅ የተተከለው የአገዛዝ ስርአት ግን ሄዶ ሄዶ ፍጹም ግለሰባዊ አገዛዝንና ሁሉን አካታች ያልሆነ ማህበረሰዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ስርአቶችን ወልዷል:: ስለዚህም የሀገር ምስረታ ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ብሄረሰቦች (ethnic groups) መካከል የተዛባ ግንኙነትን ሲፈጥር በተለያዩ ልሂቃን መሀካል ደግሞ ቁርሾ ላይ ባስ ሲልም ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖር አስችሏል:: ይህ <እኛ-እነርሱ> አስተሳሰብ ዛሬም ቢሆን በፖለቲካ ልሂቃኖቻችን ውስጥ በስፋት የሚታይ ነው:: ስለዚህም ይህንን ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በብሔራዊ ዕርቅ ሂደት አድሶ የጋራ የሆነች አገርን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ሁሉም የማህበረሰቦች ክፍሎች አተዋጽኦ እስካላደረጉ ድረስ የተሻለ ብሩህ ቀንና ዴሞክራሲያዊት የሆነች ኢትዮጵያ ሊፈጠሩ አይችሉም:: ለዚህም አላማ ሲባል ብሔራዊ ዕርቅ በጣም አስፈላጊ ነው::
የአገራችን ፖለቲካዊ ባህል ጉልበት ላይ የተመሰረተ ነው:: አጼ ቴዎድሮስ የነጉሰ ነገስትነት ዙፋን ላይ የተቀመጡት በጠበንጃ ኃይል ሁሉንም ተገዳዳሪዎቻቸውን በማንበርከክ ነው:: አጼ ዮሃንስ፣ አጼ ሚኒሊክ፣ አጼ ኃይለ ስላሴ የንጉሰ-ነገስትነት ዙፋኑን የተቆጣጠሩት ከተገዳዳሪዎቻቸው በወታደራዊ ኃይል በተነጻጻሪነት በልጠው ስለተገኙ ነው:: ፕሬዘዳንት መንግስቱ ሆነ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ የፖለቲካ ስልጣኑን ቆንጮ ቦታ የተቆጣጠሩት በጠበንጃ ኃይል ታግዘው ነው:: ይህ ጉልበትን መሰረት ያደረገ የስልጣን ዝውውር በመሰረቱ በጊዜ ሂደት የሚፈጥረው የፖለቲካ ባህል ሁሉን አካታች የሆነ የአስተዳደር ስርአት ለመዘርጋት አመቺ የሆነ ስነ-ልቦናን አይደለም:: የኛ የፖለቲካ ባህል የጠበንጃ የፖለቲካ ባህል ነው:: ለዚህም ነው ትናንሽ ልዮነቶቻችን ሳይቀር አጉልተን በማውጣት ሊያስተባብሩን የሚችሉትን አያሌ ነገሮች ወደ ጎን በመግፋት ለእርስ-በእርስ መጠላለፍ ቅርብ የሆነው:: ይህ አካሔድ የሚፈጥረው ነገር ቢሆር ሁሉም የየራሱን ትናንሽ ገነት የማደራጀት አካሄድን እንጂ በትልቁ ሊያስተሳስረን የሚችልን አካሄድ አይደለም:: በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከ 73 በላይ በሀገር ቤት የተመዘገቡ ትናንሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው የሚያመላክተው ቁም ነገር ይሄንኑ እውነታ ነው:: ይህ ትናንሽ ገነቶችን የመፍጠር ሂደት የሀገራችንን የፖለቲካ ዕድገት ወደ ፊት አንድ እርምጃ ከማራመድ አንጻር ምን አስተዋጽኦ አደረገልን? ይህንን በጉልበት ላይ እና የራስን ፍላጎት ብቻ በማየት የሌሎቹን የፖለቲካ ኃይሎች ህልውናን የመካድ ባህልን ለማስወገድና በመተባበርና በተወሰነ መልኩም ቢሆን በመተማመን ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ባህል ከመፍጠር አንጻር ብሔራዊ ዕርቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው::
ለ) በሀይማኖቶች መካከል የተዛባ ግንኙነቶችን ለማስተካከል
የዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሰረታ የተመራው <አንድ ሀገር፣ አንድ ኃይማኖት> በሚለው መርህ ነው:: ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖትን ከተቀበሉት ሀገሮች ቀደምት ብትሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ሚና በጣም ዝቅተኛ ነበር:: ይህ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሚናን እንዲቀጭጭ ያደረገው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስታዊ ሃይማኖት መኖሩና በዚህም ምክንያት ሙስሊሞች በፖለቲካው መስክ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ ስለሆኑ ነው:: የአጼ ኃይለ ስላሴ የአገዛዝ ዘመን ማክተም ሁለት አበይት ክስተቶችን አስከትሏል:: አንደኛው መንግስታዊ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ማክተሙ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የእስልምናን ሃይማኖታዊ በዓላት ብሔራዊ በዓላት በማድረግ በሀገረ-አቀፍ ደረጃ መከበር መጀመሩ ነው:: ሆኖም ግን በደርግ-ዘመነ መንግስትም ሆነ በኢህአዴግ አገዛዝ ሙስሊም ኢትዮጵያውን ከሁለተኛ የዜግነት ደረጃ ወደ እኩል የዜግነት ደረጃ የማምጣቱ ሂደት ግን እምብዛም ግቡን አልመታም[vii]::
ይልቁንም ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ከኢህአዴግ መንግስት መሰረታዊ ባህሪና ኢትዮጵያ ተሳታፊ ከሆነችበት አሜሪካ መራሹ አለም አቀፍ የጸረ-ሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባትና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ሂደት በተወሰነ መልኩ በሀገሪቱ ውስጥ አክራሪነት እንዲስፋፋ አድርጓል:: እዛም እዚ በተወሰኑ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና በክርስቲያን በተለይ ደግሞ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች የሚያመላክቱት ነገር በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ግጭቶች እየተስፋፉ መሆናቸውን ነው:: እነዚህ እየተስፋፉ ያሉ ግጭቶች <<በመቻቻል>> ላይ የተመሰረተ የሃይማኖታዊ ግንኙነቶች እሴቶች እየተሸረሸሩ ስለመሄዳቸው የሚጠቁሙ ናቸው [viii]::
በሌላም በኩል ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የሆነና የሁሉን የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎቶች ያማከለ አገዛዝ የለም ካልን፣ የሙስሊሞችን እንደ አንድ ማህበረሰብ ክፍል ሃይማኖታዊ ነጻነትን የሚያከብርም ሆነ ማህበረሰባዊ ፍላጎቶችንና ጥያዌዎች የሚመለስ የአገዛዝ ስርአት የለም ማለት ነው:: ይህም ማለት በህዘበ-ክርስቲያኑና በህዘበ-ሙስሊሙ መሀከል ያለው <<በመቻቻል>> ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የአገዛዝ ስርአቱን በሚያራምዱት ጥቂት ልሂቃን ምክንያት ሊበረዝ የሚችልበት አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል:: ምክንያቱም፣ በቀላሉ የእስልምና አክራሪነትን የሚያራምዱ ኃይሎች የሀገሪቱን ስልጣን በተቆጣጠሩትና በህዝቡ መካከል ያሉ ግንኙነቶች (state-society relationships) የአገዛዝ ልሂቃኑን ማህበረሰባዊ መደብ በመውሰድ እንደ ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ የጨቋኝ-ተጨቋኝ ግንኙነቶች ሊተረጉማቸው ይችላሉ:: የጽንፈኝነት ማህበረሰባዊ መሰረቱን የሚሰጡት ጭቆና፣ አግላይ ስርአትና ድህነት መኖራቸው ነው:: ስለዚህም፣ በታሪካዊ አጋጣሚም ሆነ በፖለቲካዊ ምክንያት የተፈጠሩ በሀገሪቱ ለረጅም ዘመን ዘልቆ የቆየውን “በመቻቻል” ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለማስቀጠልና ተቋማዊ ገጽታ ሰጥቶ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ብሔራዊ ዕርቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው::
ሐ) በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸውን የፖለቲካ ኃይሎች ለማስታረቅ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ጠበንጃ ላይ የተመሰረተ ፓለቲካ ባህል ነው ካልን፣ ይህ ባህል የሚወልዳቸው በጥላቻና እርስ በእርስ ህልውናን በመካካድ ላይ የተመሰረተ ግንኙነቶች መኖራቸው የማይቀር ሃቅ ነው:: እነዚህ ግንኙነቶች አንድም በተለያዩ ልሂቃኖች ውስጥ የተዛባ ግንኙነቶች እንዲስፋፉ ሲያረጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን የጋራ ጥቅምን የሚያስከብርንና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ህብረትን መመስረት እንዳይችሉ አርጓቸዋል:: ለዚህም ትልቁ ምሳሌ፣ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ የመጀመሪዎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች (ኢህአፓ እና መኢሶን) መሀከል ከነበረው እርስ በእርስ የመጠፋፋት ፖለቲካ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ልዩነቶችን ሰላማዊ መንገድ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በመሆን በመነጋገር የፈቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሉንም:: ጨካ የነበሩት ልዩነታቸውን የፈቱት በተለመደው በጠበንጃ ነው፤ ከተማ ውስጥ ያሉትም ቢሆን ስም በመጠፋፋት፣ እርስ በእርስ እቅውና በመነሳሳትና አልፎ አልፎም በመደባደብ ነው የፈቱት አሊያም ደግሞ ለመፍታት እየሞከሩ ያሉት::
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተሞከሩት ጥምረቶች፣ መድረኮች፣ ቅንጅቶች እና በአጠቃላይ ስብስቦች ውጤታማ ያልሆኑበት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ በዋናነት ግን እነዚህ ስብስቦች የተመሰረቱበት ችግሮች መሰረታዊ ስህተት ስላለበት ነው:: ስብስቦቹ የተቋቋሙበት መሪ መርህ <<ፖለቲካ ፓርቲዎች ለየብቻ ገዢውን ፓርቲ መቋቋምና መገዳደር (<አንድ-ለአንድ>) አንችልም፣ ተሰባስበን (<አንድ-ለብዙ>) ገዢውን ፓርቲ ከስልጣን እናውረደው>> የሚል ነው:: ይህ መርህ በመሰረቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸውን ልዩነቶች በማጥበብ የተሻለ ብሩህ ቀን ለመፍጠር የሚያደርጉት አካል ሳይሆን (ስብስቦቹ ያወጧቸውን መለስተኛ-ማኒፌስቶዎችና የየፓርቲዎቹን የፖለቲካ ፕሮግራም በመሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ያላቸው መልሶች ምን ያህል እንደሚራራቅ ልብ ይሏል)፣ <ትልቁ ጠላት> የሚሉትን ገዢውን ፓርቲ በጋራ ከስልጣን በማውረድ ከዛ በኋላ ደግሞ እርስ በእርስ በመጠላለፍ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የሚቆምሩት ፖለቲካዊ አካሄድ ነው:: በዚህ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩ ስብስቦች ሲፈርሱ የፈጠሩት ትልቁ ፖለቲካዊ ጠባሳ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል የጥላቻና እርስ በእርስ የመጠራጠር ባህል ይበልጥ ስር እንዲሰድ ማድረጋቸው ነው::
ስለዚህም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም አካታች የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመፍጠር እና ፍትሃዊ-ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማስፈን የተሻለ ነገን ለመፍጠር፣ የግዴታ ከአገዛዝ ለውጥ (Regime change) በላይ የሆነ ማህበረሰባዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል:: በማህበረሰባችን ውስጥ የተፈጸሙ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችንና በደሎችን እንዳይደገሙ ለማድረግ፣ በሃይማኖቶች መካከል እየተስፋፋ የመጣው ያለመቻቻል ባህልና ለመቀነስ እና በፖለቲካ ልሂቃኖቻችን መካከል ጠልፎ የመጣል የግለኝነት ፖለቲካን ለማስወገድ ብሔራዊ ዕርቅን እንደትልቅ የመፍትሄ ቁልፍ መውሰድ ይገባናል:: ብሔራዊ ዕርቅን በፖለቲካ ሊህቃኖች መካከል ያሉትን ቁርሾዎች ብቻ ለመሻር ሳይሆን ማህበረሰባዊ ለውጥን ለማምጣት ጭምር መጠቀም አማራጭ የሌለው አካሄድ ነው:: ሆኖም ግን፣ ብሔራዊ ዕርቅን ለማስፈን የተጋረጡ ብዙ ፈተናዎች በአገራቸን ውስጥ አሉ:: እነዚህ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? የመፍትሄ አቅጣጫዎቹስ?
4. የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎች የሚመነጩት ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ባለን ግንዛቤና እኛ ከለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ለመቃኘት በምናደረገው ጥረት ውስጥ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ሲነሳ እንድ ዋነኛ መነጻጸሪያ ሁኖ የሚቀርበው በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተካሄደውን ብሔራዊ ዕርቅን ነው:: በአብዛኛው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የሚታሰበው የደቡብ አፍሪካ ዕርቅ ምንም እንከን እንደሌለውና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም አንጻር ሊደገም እንደሚችል ነው:: ነገር ግን፣ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ዕርቅ ሂደት የራሱ የሆኑ ጉድለቶች ያሉበት ከመሆኑም በላይ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም ብዙ ልዩነቶች አሉት:: ስለዚህም፣ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ብሔራዊ ዕርቅ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን መሆን አለበት:: ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንደሚከተለው ቀርቧል::
ሀ) እውቅና ስለመስጠትና የብሔራዊ ዕርቁ አካሄድ ላይ ያሉ ፈተናዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች
ላለፉት ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችና በደሎች እውቅና መስጠት ላይ የሚታዩት ችግሮች ሁለት አይነት ናቸው:: አንደኛው ችግር ያለፉትን በደሎች እውቅና መስጠት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ ነው:: ይኸ ማለት ላለፉት በደሎች እውቅና መስጠት ማለት በደሎችን የፈጸሙ ኃይሎች ለፈጸሙት በደሎች ተጠያቂነት ስለሚያመጠና በደሉን ፈጽመዋል የሚባሉት ደግም እንደ <ሀገር-መስራች፣ ስልጣኔ አስተዋዋቂና ሰላምና ብልጽግና አምጪ> በሚል በተለምዷዊው የኢትዮጵያ ታሪክ (meanistream Ethiopian history) ተክለ-ሰውነታቸው ስለተሳለ ነው:: ሁለተኛው ችግር ያለፉት በደሎች ዕውቅና ቢሰጥ ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለው ነገር ላይ ብዥታ መኖሩ ነው:: ይህም ማለት ዕውቅና ቢሰጥ ተበድለናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ የሚል ፍራቻ መኖሩ ነው:: እነዚህ ዕውቅና በመስጠት ላይ ያሉ ተግዳሮቶች በምንም መልኩ በደሎችን በመካድ ሊፈቱ አይችሉም:: እንደ አቅጣጫ መወሰድ ያለበት አካሄድ ያለፉትን በደሎች አለመካድና በድጋሚ እንዳይፈጸሙ ማድረግን ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በደሎቹ የተፈጸሙበት ወቅት ያለውን የአስተሳሰብ ደረጃና የአገዛዛ ባህሪ ከጭፍን ስሜታዊነት ውጭ መመልከት ተገቢ ነው:: ታሪክ ለፖለቲካዊ ግብ መምቻ ብቻ ከመጠቀም ወጥተን ታሪክን ለታሪክ ተመራማሪዎች መተውን መልመድ መቻል አለብን:: በሀገራችን ሊኖረን የሚገባው ፖለቲካ ትላንትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን በነገው ብሩህ ቀንና አብሮነታችን ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል:: ይህ ማለት፣ ሙሉ ለሙሉ ታሪክን ከፖለቲካ መነጥል ይቻላል ማለት አይደለም:: ይልቁኑም ፖለቲካችን በባለፈው ታሪካችንና በነገው አብሮነታችን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታችን ላይ ያለውን ሚዛን ማስተካከል ቁልፍ መሳሪያ መሆን ይገባዋል::
በአገራችን የነበሩ አገዛዞች ምንም እንኳን ማህበረሰባዊ መሰረታቸውን በስነ-ልቦና ደረጃ ተጠቃሚ ያደረጉ ቢመስልም፣ በሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህዝቦች በባለፉት አገዛዞች ተበዳዮች ናቸው፤ የበደላቸው መጠንና የበደላቸው አይነት ምንም እንኳን ቢለያዩም:: ያለፉት አገዛዞችም ሆነ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የጠቀሙት ጥቂት ከስርአቱ ጋር ቅርበት ያላቸው ልሂቃንን እንጂ በአጠቃላይ ልሂቃኑ የወጡበትን ወይም እንወክለዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ አይደለም:: ስዚህም፣ ያለፉትን በደሎች ዕውቅና መስጠት ማለት ይህ ህዝብ በዚህ ህዝብ ተበድሏል፤ እከሌ የሚባል ህዝብ በዳይ እከሌ የሚባል ህዝብ ተጎጂ በሚል መንፈስ መሆን የለበትም:: ሁሉም ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችም ሆነ በደሎች መታየት ያለባቸው በደሎቹን የፈጸሙት አገዛዞች ከተመሰረቱበት ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረቶች የመነጩ መሆናቸውን ነው::
ይህ አካሄድ አንድ በኩል በህዝቦች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን በቂም በቀል የታጀለ ማህበረሰባዊ ግንኙነት መሰረት እንዳይዝ ሲያረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከባለፈው ታሪካችን ተምረን የተሻለ ነገን ለመፍጠር ለምናደርገው ሂደት ማህበረሰባዊ መነቃቃትን ይፈጥርልናል:: ስለዚህም፣ በዚህ አካሄድ ላለፉት በደሎች ዕውቅና በመስጠት ሊከሰት የሚችለው የፖለቲካ ኃይሎች ያለፉትን በደሎች ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት ለፖለቲካ ጥቅም የሚያውሉበትን እድል ማጥበብ ይቻላል:: በመሆኑም፣ የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ መታየት ያለበት የባለፈውን ጠበሳ በመነካከት ቅራኔን በማባባስ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማስገኘት ሳይሆን ከባለፈው ታሪክ በመማርና ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትን በማረም የተሻለ ነገንና ብሩህ-ተስፋን ከመፍጠር አንጻር መሆን ይገባዋል::
ለ) የተፈጸሙትን በደሎች ያስከተሉት ውጤቶች ላይ፣ ተጎጂዎች የከፈሉት መስዋትነት እና እንድምታ ላይ ስምምነት መድረስን (Consensus building) በተመለከተ ያሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር <ብሔራዊ ዕርቅ የሚያስፈልገው ለየትኛው ታሪካዊ በደል ነው> የሚለው ጥያቄ በተፈጸሙ በደሎች ላይ ስምምነት ለመድረስ ወሳኝ ጥያቄ ነው:: ኢትዮጵያ የአሁኗን ቅርጽ እንድትይዝ ካደረጋት የሀገር ግንባታ ሂደት አንስቶ አሁን እስከምንገኝበት ዘመን ውስጥ የተፈጠሩትን ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትና በደሎችን ማካተት አለበት:: እነዚህን ሁሉ በደሎች አንድ ሰው ወይም አንድ አገዛዝ ሳይሆነ የፈጸመው፣ በየወቅቱ በሀገራችን የሰፈኑት አገዛዛችና አገዛዛቹን የመሰረቱት እና ተጠቃሚ በሆኑት ለአገዛዛቹ ቅርበት ባላቸው ጥቂት ልሂቃን ነው:: ስለዚህም፣ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት የጎደላቸው ነገሮች ተደግረዋል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገዛዛቹ ተበድለዋል፤ የበደሉ አይነትና መጠን ቢለያይም:: ስለዚህም የተፈጸሙት በደሎች ያስከተሏቸው ውጤቶች በደንብ ተመርምረው ለታሪክ መማሪያነት መቀመጥ አለባቸው:: እንደ ሁሉም ሀገር፣ ሀገራችን ኢትዮጵያም ያላት ታሪክ <ጥሩም መጥፎ> ነው:: ከ<ጥሩ> ታሪካችን አንድነታችንን የበለጠ በማጠናከር <ከመጥፎው> ታሪካችን ደግሞ በመማር ማህበራዊ ግንኙነታችንን ይበልጥ በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሰረት ማድረግ እንችላለን:: ስለዚህም፣ የተፈጸሙት በደሎች ያስከተሉት ውጤቶችና ተጎጂዎች የከፈሉት መስዋትነትና እንድምታ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ተመዝግቦ መያዝ ይገባዋል::
ለዚህም አላማ ሲባል ሊደረጉ የሚችሉ ተግባራት የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ:: አንደኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የነበሩና ያሉ ግንኙነቶች፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ሳይንሳዊ መሆነ መንገድ ተጠንተው እንዲቀመጡ በየዩኒቨርስቲዎቻችንና መንግስታዊ በሆኑ የምርምር ተቋማት ውስጥ እንደ አንድ ፕሮግራም ተቀርጾ ሊዘረጋ ይችላል:: በዚህም ሂደት የብሔራዊ ዕርቁን ተቋማዊ ገጽታ ማላበስ ይቻላል:: ሁለተኛ፣ ብሄራዊ ዕርቁን የሚመለከት መታሰቢያ ብሄራዊ ቀን ቢመረጥና በየዓመቱ የምርምር ስራዎች የሚቀርቡበት፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ በመከባበርና ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በማህበረሰባችን ውስጥ ሊመጡ በሚችሉ ተግባራት ታስቢ እንዲውል ማድረግ ይቻላል:: ሶስተኛ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በታሪካዊ በደሎች ምክንያት ውድ ህይወታቸውን ላጡ፣ ከመኖሪያቸውና ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ እና የተለያዩ መሰዋትነት የከፈሉትን ሰዎች ለማስታወስ ሃውልት እንዲቆም ማድረግ የሚቻል ነው::
ሐ) የተፈጸሙት በደሎች በድጋሚ እንዳይፈጸሙና የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎትና ደህንነት የሚያረግገጥ ስርአት ለመፍጠር መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣትና የፖለቲካ ውህደትን ማሳለጥን (Structural changes and institutionalization of the process of political integration)፣
ብሔራዊ ዕርቅ ማህበራዊ ለውጥን ለማማጣትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት እንደ ወሳኝ ግብአት የምንጠቀምበት ከሆነ፤ ብሔራዊ ዕርቅ ሂደት በራሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው:: ይህ ማለት የተፈጸሙት በደሎች በድጋሚ እንዳይፈጸሙና የተገለሉ የማህበረሰቦች ክፍሎች ፍላጎትና ደህንነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መፈጠር አለበት:: ይህን ለማድረግም፣ የፖለቲካ ስርአቱ የሚመራበትን የጨዋታ ህግ ማውጣትና የጨዋታውን ህግ የሚመሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ይጠይቃል:: ይህም ማለት በማህበረሰባችን ውስጥ መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣትን የሚጠይቅ ነው:: የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎቶችና ደህንነት ለማስከበር የፖለቲካዊ ስርአቱ ውስጥ ሁሉንም ተሳታፊ ማድረግ ግድ ነው::
ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ውጪ በሀገራችን ያለውን ብዝሃነት ሊያስተናግድ የሚችል ስርአት የለም:: ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በመሰረቱ ሁለት ግቦች ላይ ማነጣጠር አለበት:: አንደኛ፣ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ሂደት ውስጥ ተቋማት የሚወክሉት ግለሰቦችን አሊያም የተወሰኑ የልሂቃን ቡድኖችን አይሆንም:: ተቋማት የሚወክሉት ስምምነት የተደረሰባቸውን የጨዋታ ህጎችን ሲሆን እነዚህም ህጎች በልሂቃን ውስጥ የሚፈጠሩ የጥቅምና የፍላጎት ግጭቶችን ለመዳኘት ዋና መሳሪያ ይሆናሉ:: ስለዚህም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ዴሞክራሲያዊ ተቋማትንና የጨዋታ ህጎችንና ደንቦችን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሚስማሙበት መልኩ ለመቅረጽ የሚያስችል ሂደትን ይፈጥራል:: ይኸም ማለት ብሄራዊ ዕርቅ ከሚመጣባቸው ዋነኛ ሂደቶች መካከል የጨዋታ ህጎቹ የሚወጡበት አግባብና ሂደት ወሳኝ ነው:: ኢህአዴግ ብሔራዊ ዕርቅን የሚመለከትበት አግባብ ማለትም << ብሔራዊ ዕርቅ ማለት አሁን በለው ህገመንግስና ህገመንግስታዊ ስርአቱ ላይ መግባባት መፍጠር ነው::>> የራሱን ፖለቲካዊ የበላይነት ለማስጠበቅ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም:: ምክንያትቱም የጨዋታ ህጎቹ የወጡበት አግባብና ሂደት ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ያገለለ ከመሆኑም በላይ ዋነኛ ተገዳዳሪ የሚባሉትን በተለይ ደግሞ ሀገር-አቀፍ ፖለቲካ የሚያራምዱትን ያላካተተ ነው::
ሁለተኛ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ስርአት የስልጣን ክፍፍልን ስለሚያመጣ፣ ተጠያቂነትን ስለሚያሰፍንና ፖለቲካዊ ስልጣን በጉልበት ሳይሆን በህዝብ ፍላጎት ላይ በተመሰረተ አካሄድ ስለሚያዝ አዲስ ፖለቲካዊ ባህልን በሃገራችን ውስጥ እንዲሰፍን ያደርጋል:: ስለዚህም፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ የስልጣን ክፍፍሎሽ ስለሚኖር በልሂቃኖች መካከል ሊኖር የሚችለው የስትራተጂና የታክቲክ ጉዳይ እንጂ ጫፍ የወጣ ፖለቲካዊ ልዩነት አይሆንም:: በመሆኑም የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣትና ፖለቲካዊ ውህደትን ከማሳለጥ አንጻር መታየት ያለበት ነው:: ይኸም፣ ፖለቲካዊ ውህደት የጋራ ነገን ከመፍጠርና የጋራ ራዕይ እንዲኖረን እና አዲስ ሲቪክ ፖለቲካዊ ባህል እንዲገነባ ከማስቻሉም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መሰረት ይሆናል::
መ) ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በማምጣት ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማረጋገጥ (enhancing socio-economic development and economic integration)
በታሪካችን እንደምንመለከተው ከሆነ በአብዛኛው በልሂቆቻችን መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በፖለቲካ ሃሳቦች ልዩነት ላይ የተመሰረቱ ሳይሆን አንዱ አንዱን ጥሎ በማለፍ የፖለቲካ ስልጣን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ግብግቦች ላይ የተመሰረቱ ናቸው:: የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ በዋናነት የሚያያዘው ደግሞ የሀገሪቱን ሀብት ከመቆጣጠር ጋር ነው:: በግልጽ ለማስቀመጥ ያክል የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገር ምስረታ ሂደት ፖለቲካዊው እንድምታው ያልተማከለና በጣም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መመስረት ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊው እንድምታው ደግሞ በጦር አሸናፊ ሆነው የማዕከላዊ መንግስት ምስረታን ሂደት የተቆጣጠሩትን ኃይሎች የኢኮኖሚ ጥቅሞችን የማስከበር ሂደት ነበር:: ይህ ሂደት በደርግ አገዛዛም ሆነ በኢህአዴግ አገዛዝ የተደገመ ነው:: በዘውዳዊው፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ አገዛዞች የተዘረጉት ኢኮኖሚያዊ ስርአቶች የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነት ያላረጋገጡና የአገዛዞቹን ቀጣይነት ብቻ ለማረጋገጥ ያለሙ ናቸው:: ይህም በመሆኑ የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነትንና የህዝብ ተጠቄሚነት ላይ ያነጣጠረ መሆን ይገባዋል::
እንደ ደቡብ አፍሪካ ፖለቲካዊ ስልጣን ላይ ብቻ የተመሰረት የብሄራዊ ዕርቅ ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ርቀት የማይወስድ ብቻ ሳይሆን ወደ በለጠ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሚያጋልጥ ነው:: ስለዚህም የኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አንዱ የብሔራዊ ዕርቅ ዋና አላማ መሆን ይገባዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማረጋገጥ እና በክልሎች መካከል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው:: ድህነት በራሱ ሰዎች በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ፣ ጨለምተኛ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ የሚያረጉት አንድ ነገር ይፈልጋሉ፤እራስን ከጥፋተኝነት ነጻ ለማውጣት:: ስለዚህም ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችን ለዛሬው ውድቀት ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆኑ ሲታሰብ፣ በተወሰኑ ልሂቃን ደግም ይህን ስሜት ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም እንዲውል ያደርጋሉ፣ እያደረጉም ነው:: ስለዚህም፣ ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማስፋን የብሔራዊ ዕርቅ ውጤታማነትንና ዘላቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር ወሳኝ ነው::
ከዚህ ጎን ለጎን፣ ሙስናን ማስወገድ የሚያስችሉ ተቋማዊ፣ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ሪፎርሞችን ማካሄድ ግድ የሚል ነው:: በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሶስት ኢኮኖሚያዊ ሃይላት ናቸው:: እነርሱም፣ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠራቸው ድርጅቶች፣ የሚድሮክ ድርጅቶች እና በኢፈርት ድርጅቶች ናቸው:: ይህም፣ የአሁን ኢኮኖሚ ስርአት በዋናነት የፖለቲካ ስልጣን የተቆጣጠሩት ጥቂት ልሂቃን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በቀጥታ የሚቆጣጠሩበትን አግባብ ተቋማዊ ገጽታ የሚያላብስ ነው:: ስለዚህም፣ ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ከዚህ ልማት እኩል ተጠቃሚነትን ከማስፈን አንጻር ሙስናን ማስወገድና ተወዳዳሪነትን የተላበሰ ኢኮኖሚያዊ ስርአት መዘርጋትን ግድ የሚል ነው:: በሌላም በኩል፣ በባለፉት የአገዛዝ ስርአቶች ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ትሩፋት የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል:: ይኸም፣ በባለፉት አገዛዞች ተበድለናል የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን ጫፍ የወጣ የፖለቲካ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ የሚስገድዳቸው፣ የማያስተካክሉ ከሆነ የማህበረሰባዊ መሰረታቸው እንዲያጡ የሚያደርግ፣ ከተናጥል ጉዞ የአብሮነት ጉዞ እንደሚበልጥ ሰፊው ህዝብ እንዲረዳ የሚደርግ ነው:: በመሆኑም፣ ይህ ሁኔታ የብሄራዊ ዕርቅ ዘላቂነትን ከማረጋገጡም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ ነው::
ሠ) ለብሔራዊ ዕርቅ ምቹ ሁኔታን ስለመፍጠርና አማራጭ መፍትሄዎች
እስካሁን ድረስ ብሔራዊ ዕርቅን ለማሳካት ምቹ ሁኔታን አልተፈጠረም:: ይህ ምቹ ሁኔታ አለመኖር የሚመነጨው ከገዢው ፓርቲ ከፋፍሎ የመገዛዝ ባህል እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ደካማነትና የጋራ አላማ መፍጠር አለመቻላቸው ነው:: ብሔራዊ ዕርቅ እንዲሳካ ስልጣን ላይ ያሉ ገዢዎችን የሚያስገድድና የሚገዳደር ተቃዋሚ ኃይል መኖርን ግድ የሚል ነው:: ካለ ጠንካራ ተቃዋሚ ኃይል የሚገኝ ብሔራዊ ዕርቅ፣ ዕርቅ ሊባል የሚቻል አይደለም:: ምክንያቱም የዕርቅ ሂደቱ ስልጣን ላይ ያሉ ልሂቃንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው፤ ሁሉን የፖለቲካና ማህበረሰባዊ ኃይላትን የሚያካትት አይደለም:: ከዚህ ቀደም በወጡ ጹሁፎቼ እንዳመለከትኩት፣ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ኃይሎች በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉት በብዙ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው:: የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ ግማሹ ምላሽ በተቃውሞ ኃይላት ጥንካሬ ላይ የሚመሰረት ነው:: አንድነት ጥንካሬ፣ መከፋፈል ድክመትን እንደሚያመጣ ከባለፈው ታሪካችን በተሻለ ሁኔታ ልንማርበት የምንችልበት መድረክ የለም:: ስለዚህም፣ በተቋማዊ ብቃት፣ በስትራተጂ፣ በታክቲክ እና አባላትን በማፍራት ተቃዋሚ ሃይላት ከገዢው ፓርቲ ጋር ተገዳዳሪ መሆን አለባቸው::
አብዛኞቹ የሀገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸው ርዕዮተ አለማዊ፣ ስትራተጂያዊ ወይም ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በግለሰቦች ቁርሾ ላይ የተመሰረተ ነው:: ስለዚህም፣ ግለሰባዊ ቁርሾዎችን ከብሔራዊ ፖለቲካ ጥያቄ መለየት መቻል አለብን:: በሌላም በኩል፣ አሁን የሚታየው የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብ ይበል የሚያስብል ሲሆን፣ እዚያው ሳለም ሁሉን ማህበረሰብ የሚያቅፍና የሚያንቀሳቅስ አጀንዳ መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል:: ተቃዋሚ ኃይላት ማህበረሰባዊ መሰረታቸውን መስፋትና ሁሉን የማህበረሰብ ክፍል (cross-cutting social cleavages) ማቀፍና ማንቀሳቀስ መቻል አለባቸው:: ይህን በማድረጋቸው፣ ገዢው ፓርቲ ስልጣን ላይ ብቻውን ለመቀመጥ የሚከፍለው መሰዋትነት በዕርቅ ሂደት ውስጥ በመሳተፍና ፖለቲካዊ ስርአት ለውጥ በመምጣቱ ከሚያጣው ጥቅም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል:: ይኸም፣ ለዘብተኛ የአገዛዙን ልሂቃን ወደ ብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄን እንዲያራምዱ ሲያስችላቸው፣ አክራሪ ልሂቃንን ደግሞ የበለጠ ደካማ ያረጋቸዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የብሔራዊ ዕርቅ ስትራተጂያዊ ውጤቶችና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባት ሂደት ተጠቃሚዎች ጥቂት ልሂቃን መሆን የለባቸውም:: በብሔራዊ ዕርቁ ሂደት ማንም የፖለቲካ ኃይል ሳይሆን አሸናፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት፣ አንድነት እና ሉአላዊነት ነው:: ስለሆነም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ማነጣጠር ያለበት ማን ስልጣን ላይ ወጣ የሚለው ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ የጨዋታ ህጎች ማውጣት እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ላይ ነው:: ይኸም፣ የብሄራዊ ዕርቁ ስተራተጂያዊ ውጤቶች (ዴሞክራሲያዊ ስርአት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ መግባባት) እና ታክቲካዊ ግቦች መካከል አንድነትንና ሚዛንን የሚያስጠብቅ ይሆናል:: በመሆኑም፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ለብሔራዊ ዕርቅ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ ግብአት ነው::
5. ማጠቃለያ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ውስብስብ ታሪካዊ ሂደት ያለፈች ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ ያሉብን ችግሮች መጠነ ሰፊና ውስብስብ ናቸው:: እስካሁን ድርስ ጉልበት ላይ የተመሰረተ ልዩነቶችን የመፍታት ሂደቶች የበለጥ ልዩነቶችን ውስብስብ እንዲያደርግና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስር እንዲሰድ ሆኗል:: ምንም እንኳን ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ውድቀት በኋላ የተለያዩ የብሔራዊ ዕርቅ አስተሳሰቦች በሙሁሯንና በፖለቲካ ኃይላት ቢራመዱም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄን የፖለቲካ ኃይላት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ማሳኪያ መሳሪያ ያደረጉበት አረዳድ እንደሰፈነ መረዳት አያዳግትም:: የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ውስብስብ ችግሮችን የምንፈታበት ሂደት እንደመሆኑ መጠን በእንዳንዱ ጥቃቅን በደሎች ላይ የምናተኩርበት፣ ፖለቲካዊ ትርፍ የምናሰላበት፣ አግላይ ስርአት የሚመሰረትበት ሂደት ሳይሆን የተሻለች ኢትዮጵያንና ብሩህ ቀን የመፍጠር ሂደት አካል መሆን ይገባዋል::
የተመረጡ ዋቢ መጽሃፍትና ሰነዶች
[i] Bloomfield, David, Teresa Barnes, and Lucien Huyse. 2003. Reconciliation After violent conflict: A Handbook. Stockholm: Interna-tional IDEA.
[ii] Lederach, John Paul. 1997. Building Peace: Sustainable Reconciliation in Divided Societies. Washington, D.C. : United States Institute of Peace.
[iii] Solimano, Andres (Ed.). 2000. Colombia: Essays on Conflict, Peace and Development. Washington, D.C., The World Bank.
[iv] Liebenberg, Ian and Abebe Zegeye. 1998. “Pathway to Democracy? The Case of the South African Truth and Reconciliation Process.” Social Identities, Volume 4, Number 3, pp. 541-558.
[v] Diamnond, Larry. 2008. The Spirit of Democracy: The Struggle to Build Free Societies Throughout the World. New York, Henry Holt and Company, LLc,.
[vi] Bahru Zewde. 2005. A History of Modern Ethiopia, 1855-1991. Ohio: Ohio University Press. 2nd Edition.
[vii] Dereje Feyissa. 2013.“Muslims Struggle for Recognition in Contemporary Ethiopia”. In Muslim Ethiopia: The Christian Legacy, Identity Politics and Islamic Reformism, eds. Patrick Desplat and Terje Østebø. New York, Palgrave Macmillan.
[viii] Desplat, Patrick; Terje Østebø . 2013. “Muslims in Ethiopia: The Christian Legacy, Identity Politics, and Islamic Reformism”. In Muslim Ethiopia: The Christian Legacy, Identity Politics and Islamic Reformism, eds. Patrick Desplat and Terje Østebø. New York, Palgrave Macmillan.
Leave a Reply