* “ባለውለታችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ አዝኖባችኋል፣ አርቃችሁ እዩ”
“በትግሉ ወቅት ለነጻነት ስትዋደቁ ኢትዮጵያ በጋምቤላ አኙዋክ ምድር ላይ ሙሉ ከለላና ዋስትና በመስጠት ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሚረሳ ነው? ከነጻነት ታጋዮችችሁ ጎን በመሰለፍ ብረት ያነሱ የአኙዋክ ኢትዮጵያውያን ልጆች መስዋዕትነት ይዘነጋችኋል? አሁን ድረስ የትግሉ የመስዋዕትነት ቁስላቸው ያልዳነ የአኙዋክ ልጆች እንዳሉ ትዘነጋላችሁ?” በማለት የተናገሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ /ጥቁሩ ሰው/ ናቸው።
በታላላቅ መድረኮችና በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተሰሚነታቸውና ስብዕናቸው እየጎላ የሄደው ጥቁሩ ሰው ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ከላይ የተገለጸውን ህሊና የሚፈታተን ጥያቄ ያቀረቡት ለደቡብ ሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን ነው። ለረዥም ሰዓት ጊዜ ወስደው ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ የጎልጉል የአሜሪካ ዘጋቢ እንደዘገበው አቶ ኦባንግ ዶ/ር ባርናባን ያገኟቸው አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ነበር።
በጁባ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ ይፋ ከተደረገበት አንድ ቀን በፊት አስቀድሞ በተያዘ የውይይት መርሃ ግብር የተገናኙት ዶ/ር ባርናባና አቶ ኦባንግ በርካታ ወቅታዊ ጉዳዮችን አንስተው መነጋገራቸው ታውቋል። አቶ ኦባንግ የደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል ወቅት ኢትዮጵያ በመንግስት ደረጃ የሰጠችውን ሙሉ ድጋፍና፣ ድንበር ሳይከልላቸው በሁለቱም አገራት የሚገኙት የአኙዋክ ልጆች ትግሉን የነፍስ ዋጋ በመክፈል መደገፋቸውን በማስታወስ በውይይቱ ወቅት ያነሱት ያለ ምክንያት አልነበረም።
“በጆን ጋራንግ ይመራ የነበረው ትግል ፍሬ አፍርቶ ደቡብ ሱዳን ነጻ ስትወጣ የማይረሳ ውለታ ለሰራቸው ኢትዮጵያና የአኙዋክ ልጆች የተከፈላቸው ብድር አሳዛኝና የወደፊቱን ጊዜ ያላገናዘበ ነው” በማለት በውይይቱ ስለተነሱ ነጥቦች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኦባንግ፣ “ለህዝቦች ነጻነትና ለሰብአዊ መብት መከበር የታገለ ድርጅትና አመራሮች ለነጻነታቸው የተከፈለላቸውን የደም ዕዳ ያወራረዱትና እያወራረዱ ያሉት ከወያኔ መሪዎች ጋር በማበር ከለላ የጠየቁ ህጋዊ ስደተኞችን እያፈኑ ለወያኔ አሳልፎ በመስጠት መሆኑ አሳዝኖኛል። ኢትዮጵያዊያን አዝነዋል” በማለት ነበር።
ህጋዊ ከለላ የጠየቁ ስደተኞች ቶርቸር እንዲደረጉ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲታሰሩና ኢሰብአዊ ግፍ እንዲፈጸምባቸው ለአምባገነኖች አሳልፎ መስጠት ዘግይቶም ቢሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል አቶ ኦባንግ አስረግጠው ተናግረዋል። በ1993 የአኙዋክ ጄኖሳይድ /የጅምላ ጭፍጨፋ/ ሸሽተው በስደት ደቡብ ሱዳን የገቡ የአኙዋክ ልጆችን ለገዳዩ የወያኔ አንጋች ሃይል ማስረከብ መቆም እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ኦባንግ “ይህንን ተግባር የፈጸሙትም ቢያንስ ዓለም አቀፋዊውን ህግ ተላልፈዋልና ሊጠየቁ ይገባል። እርስዎም ይህንኑ የማስፈጸም ሃላፊነት ይኖርብዎታል” በማለት ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የአኙዋክና የበኩር ልጆችና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት ከድንበር ያለፈ የደም ትስስርና ኢትዮጵያ የማይረሳ ውለታ በመክፈል ያከበረችው ውህደት በመሆኑ መንግስታቸው ቆም ብሎ ሊያስብ እንደሚገባው አቶ ኦባንግ ምክር አዘል መልዕክት ማስተላለፋቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ አስተማማኝ ከለላና ዋስትና በመስጠት የፈጸመችውን ሊዘነጋ የማይችል ተግባር አለማክበር ለወደፊቱ ወዳጅ የሚያሳጣ ብድር ለራስ የማስቀመጥ ያህል እንደሆነም በወጉ እንዲገነዘቡ ሚኒስትሩን ተማጽነዋል።
አምባገነኑና በህዝብ የሚጠላው የህወሃት አገዛዝ እድሜ አሁን ካለው ትውልድ እድሜ በላይ ዘሎ የሚሄድ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማቅረብ፣ መተዋወቅና መልካም ግንኙነት መመስረት ለወደፊቱ ጠቃሚ መሆኑንም አስረድተዋል። እርሳቸው በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄም /አኢጋን/ ከተመሰረተበት ዓላማ አንጻር የደቡብ ሱዳን መንግሥት ህወሃት/ኢህአዴግን ለማስደሰት ሲል ኢትዮጵያዊያን ላይ ፈጸመውና እየፈጸመ ባለው ተግባር ያዘኑ ወገኖች የቀድሞውን የፍቅር መንገድ እንዲከተሉ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ሕዝብ ያልወደደው መንግስትና ህዝብ ያልተቀበለው ኢንቨስትመንት መጨረሻው ኪሳራ በመሆኑ የደቡብ ሱዳን መንግስት ሊጠነቀቅ እንደሚገባው አቶ ኦባንግ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል። ከደቡብ ሱዳን ተነስቶ በጋምቤላ አድርጎ ወደ ኬኒያና ጅቡቲ ይዘረጋል የተባለው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ሕዝብን በመግፋትና በመበደል ከቶውንም ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ያለማቅማማት ጠቁመዋል።
ህዋሀት በጋምቤላ ንጹሃንን ከቀያቸው በጠመንጃ ሃይል በማባረር፣ መሬታቸውን በሳንቲም ቸብችቦ፣ የህይወታቸው ዋስትና የሆነውን ደናቸውን አስጨፍጭፎ፣ ለምን በማለት የጠየቁትን አስሮና ገድሎ ያቋቋመው ኢንቨስትመንት በዜሮ መጣፋቱን ለአብነት ጠቅሰው ማስረዳታቸው የጠቆሙት ጥቁሩ ሰው “ኢንቨስትመንት መልካም ነው። ህዝብ ካልተቀበለው ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ህዝብ ይሁንታ የማይሰጠው ኢንቨስትመንት ፍሬ አያፈራም። ከውስጥም ከውጪም ያላችሁን ግንኙነት መርምሩ። ያዘኑባችሁ ተበራክተዋል” ሲሉ መክረዋል።
በአዲስ የምትቋቋመው “አዲሲቷ ኢትዮጵያ” ለደቡብ ሱዳን ወንድምና እህቶች ጭምር ቦታ በማዘጋጀት መሆኑንን አቶ ኦባንግ አረጋግጠው “በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዲሞክራሲ መከበርና ለነጻነት በተከፈለው መስዋዕት የተገኘውን ድል የደቡብ ሱዳን መንግስት በአግባቡ እየተጠቀመበት አለመሆኑን አቶ ኦባንግ ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል። አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ከድል በኋላ የትግሉን መሐላ ሙሉ በሙሉ ረግጣለች በማለት መሪዎቹን ወቅሰዋል።
ከድል በኋላ በደቡብ ሱዳን በርካታ ችግሮች መከሰታቸውን በመዘርዘር የማስጠንቀቂያ ምክር መሰንዘራቸውን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አሁን ባለው ሁኔታ በደቡብ ሱዳን ባሉ ሃያ አንድ ጎሳዎች መካከል ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም። ስለዚህ በራችሁን ዘግታችሁ እርቅ አውርዱ። በቀደሙት ሰማዐታቶች ደምና አጥንት ላይ ዴሞክራሲን መስርቱ። ይህንን ካላደረጋችሁና አሁን በያዛችሁት የአምባገነንነትና የአንድ ሰው ወይም ጎሣ የበላይነት መንገድ ከቀጠላችሁ ጣጣው ወደኛም ያመራል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አስጠንቅቀዋቸዋል። አሁን ያለው የውስጥ ሽኩቻ መልኩን ሳይቀይር መፍጠን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋቸዋል። (አቶ ኦባንግ ይህንን ለውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ የተናገሩት እሁድ መፈንቅለ መንግሥት ከመሞከሩና አሁን ደግሞ በዘር /ጎሣ/ መስመር ተከፋፍለው ደቡብ ሱዳናውያን መጫረስ ከመጀመራቸው አንድ ቀን በፊት ነበር)
በደቡብ ሱዳን እውነተኛ እርቅ ለማውረድ የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት አንድ ግብረ ሃይል ወደ ጁባ እንደሚልክ መረጃ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ኦባንግ በውይይቱ ወቅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀና ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክተዋል። በመጨረሻም አቶ ኦባንግ የሚመሩት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የእርቅ ደጆች የሚከፈቱበት አግባብ ላይ ከሚመለከታቸው ተጽዕኖ አድጊራዎችና አቅሙ ካላቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል። በማያያዝም “እኛ ሩቅ እያየን እየሰራን ነው። እኛ በስፋት እያሰብን በመራመድ ላይ ነን። በስፋት አስበን፣ ሩቅ እያየን ስንሰራ እናንተንም አንዘነጋም። በተቃራኒው እናንተ ለነጻነታችሁ የተዋደቁላችሁን የራሳችሁን ዜጎች እያነቃችሁ ለወያኔ አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ። ደም ያፈሰሱላችሁንና አጥንታቸውን የከሰከሱላችሁን ውድ ዜጎች ሳትታረቁ በምድራቸው ላይ ቱቦ ዘርግታችሁ ብር ልታመርቱ ታቅዳላችሁ። ይህ ከቶውንም ጤነኛ አካሄድ አይደለምና ህዝብን አስቀድሙ። አብረን እንስራ። ይህ መልካም ጅምር ነው” በማለት መሰናበታቸውን አቶ ኦባንግ ለጎልጉል ተናግረዋል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክትር አቶ ኦባንግ ሜቶ ከደቡብ ሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ጋር ለመወያየት የቻሉት ሚኒስትሩ አሜሪካ ከመምጣታቸው በፊት በኤምባሲያቸው አማካይነት አስቀድሞ በተያዘ መርሃ ግብር መሰረት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሩ ስለ ሰጡት አስተያየትና ምላሽ አቶ ኦባንግ በዝርዝር ለመናገር አልፈለጉም። አቶ ኦባንግ በትውልድ አኙዋክ ቢሆኑም እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት /አኢጋን/ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጭ በስደት በሚሰቃዩበት ቦታ ዘር፣ ቀለም፣ ጎሣ፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ሳይለይ ፈጥኖ በመድረስ እርዳታ በማድረግ እርሳቸውም በተመሳሳይ ተግባር ተጠምደው በቅንነት በማገልገል እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የእርቅ ደጆች እንዲከፈቱ አግባብ ካላቸውና አቅሙ ካላቸው ክፍሎች ጋር እየሰራን ነው በማለት አቶ ኦባንግ ለሚኒስትሩ የገለጹላቸውን ሃሳብ እንዲያብራሩ ከጎልጉል ተጠይቀው “ሁሌም የእርቅ ደጆች እንዲከፈቱ እንሰራለን። ይህ የጋራ ንቅናቄውና አርቀው የሚመለከቱ ዜጎች ሁሉ እምነት ነው። ብዙ ስራ እየሰራን ነው። ስንጨብጠውና ለህዝብ ሪፖርት የምናቀርብበት አሳማኝ ጊዜ ላይ ስንደርስ ብቻ ይፋ እናደርጋለን። ስራው በባህሪው ከንግግር በመቆጠብ ተግባር ላይ ማተኮርን ስለሚጠይቅ እኛም ባናወራው ጊዜው ሲደርስ ሁሉም በየፊናው የሚገልጸው ይሆናል። ስራው ሳይሰራ ፕሮፓጋንዳው ከቀደመ በሁሉም ወገን ተዓማኒነትን የማጣትና የመጣል አደጋ አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ ተግባር የናፈቀው ይመስለኛል” የሚል ድፍን መልስ ሰጥተዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Musie says
Good work mr Obang metto
Obang Jobi says
When did this meeting took over? Was it before the Sunday chaos in South Sudan or before the Sunday.
fre says
publicity stunt ,that is all Mr Obang