የመን ትነድዳለች ኢትዮጵያውያን ግን ወደዚያው ያቀናሉ። ሶማሊያ ዋስትና ቢርቃትም ወገኖች ሊረማመዱባት አሁን ድረስ ምርጫቸው ናት። በሲና በረሃ ሰው በቁሙ ይበለታል። ለእኛ ኢትዮጵያውያኖች ግን አሁንም አማራጭ መንገድ ነው። ሲኦል መሆኑ እየታወቀ እህትና ወንድሞች ወደ አረብ አገር ይተምማሉ። ኬንያን፣ ታንዛኒያን፣ ዛምቢያን፣ … አቆራርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙ ቁጥራቸው ሲቀንስ አይታይም። በደቡብ አፍሪካ ወገኖች በእሳት ሲቃጠሉና በገጀራ ሲጨፈጨፉ ማየት ወደዚያ የሚደረገውን ጉዞ አልቀነሰውም። ለምን?
በቀይ ባህርና በሜዲትራንያን የሰመጡ ወገኖች መርዶ ሳያሰልስ ሌሎች መሰመጥ የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን እያወቁ ይገቡበታል። ሊቢያ የታረዱትን ወገኖች እያዩ ሌሎች ወደ ሊቢያ ለማቅናት አያቀማሙም። ለምን? በኩባ ቪዛ ተነስተው መከራቸውን ለወራት በበረሃ የሚያሳልፉ ወገኖች ቁጥር … ስንቱ ይዘረዘራል? ኢትዮጵያውያኖች እንዲህ ያለውን መከራና አጥንት ዘልቆ የሚገባውን ሃዘን ሳይፈሩ ስደትን የመጨረሻ አማራጭ ያደረጉት ለምን ይሆን? ለገዢውም ሆነ ለተገዢው የሚቀርብ ጥያቄ ነው።
ከሁሉም በላይ ዜጎች በየጊዜው እርዳታ ሲፈልጉና በነፍስ ውጪ ግቢ ውስጥ ሆነው የድረሱልኝ ምልጃ ሲያቀርቡ ሰሚና ተቆርቋሪ የላቸውም። ህወሃት ለእንዲህ ያለው የወገኖች ጥሪ መልሱ “ጥሪ አይቀበልም” መሆኑ ደግሞ ከችግሩ በላይ ቅስም ሰባሪ ነው። ወገኖቻችን ሲታረዱ “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ቆይ ላጣራ” የሚል ገዢ ቢኖር ህወሃት ብቻ ነው። ዶላር ባለበትና የስልጣን ጊዜን የሚያራዝም እስከሆነ ብቻ ተጣድፎ ምላሽ የሚሰጠው ህወሃት፣ በቅርቡ በጋምቤላ ለተጨፈጨፉት ወገኖች የሰጠው ምላሽ የዚሁ ተግባሩ መገለጫው ነው።
ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ በበርካታ ጉዳዮች የሚያዝኑ ወገኖች የሚጽናኑበት አንድ ሰው አግኝተዋል። የተግባር ሰው! በሩ ለሁሉም ወገኖች ክፍት የሆነ። ቂምና በቀልን አጥብቆ የሚጠላ፤ ተንኮልን የሚጸየፍ። ወገኖቹን የሚላላክ፤ ለአንድ ግለሰብም ለብዙሃንም በእኩል የሚቆም። ክብሩ አገልጋይነት ብቻ የሆነ። ዝማሬና ሙገሳ የሚጠላ። በውሱን ድጋፍ ወሰን የሚያልፍ፣ አህጉር የሚያቋርጥ ሥራ የሚያከናውን። ብዙ ሊባልለት ሲገባው ግን ያልተባለለት፤ ያልተጨበጨበለት፤ ያልተዘፈነለት፤ … ሥራውን የሚያውቁ ግን “የጥቁር አልማዝ” የሚሉት!!
“ለወገን ደራሽ” ስሙ ነው። በተጠራበትና ችግር አለ በሚባልበት ቦታ ሁሉ ወገኖቹን ተሟግቶ ነጻ ያወጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ክብር የሚገባው ግን ክብር ያልተሰጠው” በሚል በማህበራዊ ድረገጾች ስሙ እየተነሳ ነው። የእርሱ ፍላጎት ባይጠየቅም “አንተ ምራን” የሚሉት እየበረከቱ ነው። ጀርባው ሁሉ ከምንም የጸዳ በመሆኑ ብዙዎች “እናምነሃለን፣ እናከብርሃለን፣ እንወድሃለን፣ አምላክ ይጠብቅህ …” እያሉት ነው።
ለሰው ልጆች ክብርና እኩልነት ዋጋ መክፈል እንደሚያስደስተው ደጋግሞ ይናገራል። “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ አይወጣም” በሚለውና ግንባሩ ላይ በታተመው “ከጎሣ በፊት ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ” በሚል መሪ ቃል ይታወቃል። በሚመራው ድርጅት ውስጥ ባሉት ባልደረቦቹ የሚታመን። ይህ ሰው ኦባንግ ሜቶ ይባላል። በይቅርታ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለማቆም ከመሰሎቹ ጋር ደፋ ቀና ይላል። ርምጃው በተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገሮች መነጽር ውስጥ ከቶታል። ኢትዮጵያን በመወከል በከፍተኛ ቦታዎች የወገኖቹ ድምጽ ከሆነ ሰነባብቷል። ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባሮች ገሃድ ወጥቶ የሚናገረው በጣም ጥቂቱን ነው። ስለ እሱ ጠንቅቀው የሚያውቁ “ኦባንግ አሁን የኢትዮጵያ ምስል ሆኗል” እያሉ ነው። የጎልጉል የኬኒያ ዘጋቢ በቅርቡ ሰፊቃለ ምልልስ ለማካሄድ ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቆናል። በዚሁ ሰፊ ቃለምልልስ በማህበራዊ ገጾች ስለሚነሱት ጥሪዎች ምላሽ ይሰጣል።
የደቡብ ኮሪያ ዳግም ዘማች – አባ “ቃኘው”
ስደት እንደ ጨው ከረጫቸው ወገኖች መካከል በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ ወገኖችን ያስታወሳቸው አልነበረም። ባለፉት ሳምንታት የተሰማውን ዜና አስመልክቶ አቶ ኦባንግ ሜቶ “ጥቁሩ ሰው” በተለይ ለጎልጉል ሲናገር “የተዘጋን በር አስከፍተናል” ነበር ያለው። ወደዚያው ማቅናቱን የሰሙ “የደቡብ ኮሪያ ዳግም ዘማች አባ – ቃኘው” ሲሉ ጠርተውታል።
“ዘመን የማይሽረው ወዳጅነት ኮሪያና ኢትዮጵያ፤ በኮሪያ ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር ተሳትፎ” በሚል ርዕስ ደራሲ ቲኢ-ጂኢ-ውን የጻፉትና በጋሻው ድረሴ ወ/ሰማያት ወደ አማርኛ የመለሱት መጽሃፍ መግቢያ ላይ ከዛሬ 64 ዓመት በፊት ኮሪያን ነጻ ለማውጣት ዘምቶ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት መጠሪያ ስሙ “ቃኘው” እንደሚባል አስታውሶ ትርጉሙም “ድብልቅልቁን ሥርዓት አስይዘው” ማለት እንደሆነ ተመልክቷል። ለዚህም ይመስላል ኦባንግ “አባ ቃኘው” የሚል ስም የተበረከተለት።
በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ይህ ተጽፎ ይገኛል “… በጦርነቱ ለማያውቁት ሀገርና አይተውት ለማያውቁት ህዝብ በኮሪያ ጦርነት የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉት ያለንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን፡፡ ዕድሜ ለኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የኮሪያ ሪፐብሊክ ከጦርነቱ ቁስል ለማገገም ችላለች፡፡ (በአሜሪካዊው) ጄነራል ማክአርተር በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመግለፅ “እነዚህ ሰዎች ይህቺን ሀገር እንደገና ለመስራት 100 ዓመት ያስፈልጋቸዋል” ተብሎ ከተገለፀበት ሙሉ ውድመት ተነስተን ኮሪያን እንደገና ገንብተናታል፡፡ ዛሬ እንደ G20 እና የ2012 ሶውል ኑክሊየር ስብሰባዎች የመሳሰሉት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ለማካሄድ የምንመረጥበት ክብር ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚመሰክረው የኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከንቱ ሆኖ አለመቅረቱን ነው፡፡ ዛሬ ከእርዳታ ተቀባይነት ወደ ሰጭነት በተሸጋገርንበትና ከዓለማች 10 የበለፀጉ ሀገሮች ሰልፍ በተቀላቀልንበት ሁኔታ ለኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ብድር መላሽ ለመሆንና ከድህረ ጦርነት በኋላ ለመጣውም ትውልድ ዕውነታውን በስፋት እንዲታወቅ ጠንክረን እንሠራለን…”።
በመጽሐፉ ላይ ይህ የሰፈረ ቢሆንም በዚያ የሚገኙ 130 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሁሉም ዓይነት በር ጠብቆ የተዘጋባቸው፣ የህግ ከለላ የሌላቸው፣ በቂ የዕለት ማቆያ የማይቆረስላቸው፣ ጠበቃ ማግኘት የማይችሉ፣ በማይታወቅ የስደተኞች ህግና መመሪያ የሚስተናገዱ፣ ሚዲያው የዘነጋቸው፣ ፍትህ ፍለጋ የሚሄዱበት ያጡ፣ ሳይጨልም ለዓመታት የጠቆረባቸው፣ ሲታመሙ ለመታከም የማይችሉ፣ እዛ የተወለዱ ልጆቻቸው የሚንገላቱባቸው፣ ተዘርዝሮ የማያበቃ መከራ የተሸከሙ እንደሆኑ አቶ ኦባንግ ያስረዳል። “ገሃድ አውጥቼ ልናገረው የማልችለው አሳዛኝ ችግሮችን ስሰማ ውስጤ ታመመ” ያለው ኦባንግ ወደ ደቡብ ኮሪያ ያቀናው በዚያው የሚኖሩ የአኢጋን ቤተሰቦች አማካይነት መረጃው ደርሶት ነው። በዚህ አጋጣሚ ጉዞውን የተቃና በማድረግ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ሥራውን በትጋት ለሠራው ሱራፌል አሰፋ እንዲሁም ለአጋሮቹ መቅደስንና ቢኒያምን ታላቅ ምስጋና እንደሚያቀርብ ተናግሯል፡፡
ኦባንግ ወገኖቹን ሰብስቦ ማዳመጥ የመጀመሪያ ተግባሩ ነበር። አስቀድሞ ችግሩን እንደሰማ ወደ ስፍራው ለማምራት ቢወስንም በአካል ከተገኘ በኋላ እንባ የተቀላቀለበት ስብሰባ ላይ በሰማው ሁሉ ሃዘን ገባው። “አሁን አናለቅስም” ሲል ኦባንግ ሥራውን ጀመረ። “ዛሬ ተደራጁ፣ እንደራጅ፣ በተናጠል አትሩጡ፣ በወሬ ሳይሆን ራሳቸሁን አክብራችሁ ሌላውን ማክበር በምትችሉበት ጥልቅ ስሜት ተዛዘሉ፣ ተረዳዱ፣ አንድ ሁኑ፣ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች ስለሆናችሁ ባገራችሁ ስም ተሰባሰቡ…” ሲል የተደበላለቀውን ስርዓት ማስያዝ ጀመረ።
“እናንተ አሁን ሜዲትራንያን ባህር ውስጥ እየተንሳፈፋችሁ አይደለም፣ ሲና በረሃ አይደላችሁም፣ ደቡብ አፍሪካ በጎማ እየተቃጠላችሁ አይደለም፣ በበረሃ ውስጥ አይደላችሁም፣ መብታቸውን እንደጠየቁ የኦሮሞ ልጆች እስር ቤት አልታጎራችሁም፣ በጥይት እየተደበደባችሁ አይደለም። የማንነት ጥያቄ በማቅረባችሁ ህወሃት በጥይት እየፈጃችሁ አይደለም፣ 20 ሚሊዮን ህዝብ በችጋር ሲጠበስ እናንተ ምግብ አላጣችሁም … አዎ በታሪክ ተመዝግቦብን የማያውቅ ውርደት ውስጥ መውደቃችን ባይካድም ዛሬ በህብረት እንቆማለን። እኛ ሁላችን ከተባበርን ከችግሮቻችን ሁሉ በላይ እንሆናለን…” በማለት ጥቁሩ ሰው የዛለውን መንፈሣቸውን አነቃቃው።
ኦባንግ እንደሚለው ወገኖቹ ላይ የደረሰውን በደል መዘርዘሩ ፋይዳ የለውም። በዚህም የተነሳ በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት ጉዞ ወደ ኢሚግሬሽን ቢሮ ሆነ። አቶ ኦባንግ የደቡብ ኮሪያን ምድር ከረገጠበት ሰዓት ጀምሮ በመንግሥት ለደህንነቱ ልዩ ጥበቃ ተመድቦለት ነበር። ይህ የሆነው በሱ ጥያቄ ሳይሆን “የመታፈን ችግር እንዳያጋጥመው” ለጥንቃቄ ነበር። ይህንን ያስረዱትም ራሳቸው ናቸው ። በዚሁ መሠረት በኢሚግሬሽን ቢሮ ተገኝቶ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኘ። ለኦባንግ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት “the shaker ወይም አባ ነቅንቅ” ያሰኘውን ንግግር አቀረበላቸው። ኢትዮጵያ ላይ የተንሰራፋውን ግፈኛ ኃይልና ተግባሩን አስረግጦ ዘረዘረላቸው።
“የአያቶቻችን ውለታ ይህ ነው? ኢትዮጵያዊያን ህክምና ለማግኘት እንኳን አይመጥኑም? በደቡብ ኮሪያ ሰላማዊ ዋስትና ለማግኘት ብቁ አይደሉም? ጠበቃ ለማግኘትና ጉዳያቸው እስኪታይ የሥራ ፈቃድ አግኝተው እየሰሩ ለመኖር ሚዛን አያነሱም?” ኦባንግ ከማብራሪያው በኋላ ለባለስልጣኖቹ ያቀረበው ጥያቄ ነበር።
ኦባንግ ቀጠለ “… ራሳችሁ በከተማችሁ ያቆማችሁትን ለናንተ ነጻነት ደም ያፈሰሱት ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ ለምን ታፈረሳላችሁ? እነዚህ ወጣቶች እኮ የነሱ ልጅ ልጆች ናቸው” ሲል ታሪክን እያጣቀሰ አስረዳ። አሁን ያለው አገዛዝ ጋዜጠኞችን “አሸባሪ” ብሎ የሚያስር፣ ዘረኛና ለትውልዱ የማያስብ አምባገነን አገዛዝ መሆኑን በግብሩ እያስቃኘ የስደተኛ ህጋቸውን ከአለም አቀፍ ህግ ጋር አዛምደው እንዲያሻሽሉ አስገነዘበ። ጉዳዩንም ለዓለም ይፋ እንደሚያደርገው አስጠነቀቀ። ከሰፊ ውይይትና መረዳዳት በኋላ ባለሥልጣናቱ የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገቡ። ከስደተኞች ዓለም አቀፍ ህግ ጋር ብዙም ትውውቅ ስለሌላቸው የተሰራ ስህተት ስለመኖሩ አምነው ተለያዩ። በስተመጨረሻም ኦባንግ ሁሉም ጥገኛ ጠያቂዎች ከለላ እንደሚያሻቸው አሳምኖ ቢሮውን በክብር ለቀቆ ወጣ።
በሲዑል የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የስደተኞች መስሪያ ቤትም ኦባንግ ተገኝቶ ሁኔታውን አሰረድቷል። ባለስልጣናቱ ከዚህ ቀደም ስለ ስደተኞቹ ሰምተው እንደማያውቁ ገልጸው ጉዳዩን የኮሪያ ባለሥልጣናት በዓለምአቀፉ ህግ መሰረት እንዲያስኬዱት ማሳሰቢያ እንደሚሰጡ ቃል ተገባ። መደራጀታቸው አግባብ በመሆኑ ወኪላቸውን በየጊዜው በማግኘት ችግሩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ አብረው እንደሚሰሩ ማረጋገጫ አገኘ “ቃኘው” የተዘጉትን በሮች አስከፍቶ ወጣ። ዝርዝሩን በቃለ ምልልስ እናትመዋለን።
አስገራሚው – የመረጃ ድርቅ በሴዑል
ኦባንግ በሴዑል ቆይታው ሰፊ ጊዜ ወስዶ ካነጋገራቸው መካከል በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል። እነዚህ ክፍሎች አገራቸው ሚዲያ፣ ከለላ፣ ርዳታ፣ ህክምና፣ ሥራ፣ ወዘተ ተከልክለው ስለሚኖሩት ኢትዮጰያዊያን መረጃ የላቸውም ነበር። የሚያሳዝነው ህወሃት በሚገዛት ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች “አሸባሪ” እየተባሉ ወኅኒ እንደሚወረወሩ አያውቁም ነበር። ኦባንግ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት በያዘው እቅድ መሰረት እነዚህን ክፍሎች በቂ ግንዛቤ አስጨበጠ። የነበረውን የመረጃ ድርቅ ህይወት ዘራበት።
ከ30 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ አካላትና ጠበቆችን ካነጋገረ በኋላ ባገኘው ምላሽ መገረሙን ኦባንግ አልሸሸገም። ደንግጠው “በአገራችሁ ሁሉ ነገር እንደዚህ ከሆነ የአውሮፓ አገሮች እንዴት አብረዋቸው ይቆማሉ” ሲሉ ጥያቄ ሰነዘሩ። “በአሸባሪ ስም የነሱን ጦርነት ይዋጉላቸዋል” በማለት ስለ ሁኔታው ዝርዝር ምላሽ ሰጠ። በስተመጨረሻም ከጥገኝነት ጠያቂዎቹ ወኪሎች ጋር በመሆን ያገራቸው ህዝብ በቂ መረጃ እንዲያገኝ፣ መንግስታቸውም የከለላ ጥያቄያቸውን እንዲያስተናግድ ሁሉን ዓይነት ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋገጡ።
የመረጃው በር ሲከፈት – ሚዲያ ኦባንግ ዘንድ መጣ
የጥቁሩ ሰው የመጨረሻ እቅድ ያገሪቱን መገናኛዎች በመጠቀም የደቡብ ኮሪያን ህዝብ ማንቃት፣ እንዲያስብ ማድረግና የመከራከሪያ አጀንዳ አቀብሎ ሴዑልን መሰናበት ነበር። በዚሁ እቅድ መሰረት የደቡብ ኮሪያ ታዋቂዎቹ ሁለት ሚዲያዎች ኦባንግ አለበት ዘንድ መጡ – በኮሪያ ሲታተም 96ዓመታት ያስቆጠረው Dong-A Ilbo የተሰኘው ጋዜጣ እና በደቡብ ኮሪያ ዋንኛው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የሆነው The Korea Herald። ከጥቂት ዓመታት በፊት አቶ ኦባንግ በህንድ አገር ተገኝቶ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያደረገው ንግግር ድፍን ድጋፍ ያገኘውና ካሩቱሪ ካገሪቱ ባንኮች ብድር እንዳያገኝ የከፈተው ዘመቻ ያስመዘገበውን ውጤት ያስታወሰ ክስተት ተደገመ።
ያገሪቱ ሁለት ታዋቂ ሚዲያዎች በየተራ ሲያነጋግሩት ኦባንግ ከ65 ዓመት በፊት የተከፈለውን የደምና ያጥንት ታሪክ ግንባር አደረገ። የኮሪያ ሚዲያዎች ከዚህ ወርቅ አገር ለመጡ የጀገኖች የልጅ ልጆች በር መቆለፋቸውና ጀርባ መስጠታቸውን ለራሳቸው ህዝብ አሳበቀባቸው። ህግና ደንብ ጠቅሶ ወገኖቹ ከለላ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስረዳ። የኮሪያ አዲሱ ትውልድ ተደብቆት የኖረውንና ባገሩ ምድር እየተፈጸመ ያለውን ችግር አቀረበ። ሚዲያዎቹ ይህንን ከፍተኛ ችግር ዝም ሊሉ እንደማይገባ አሳሰበ። ህወሃት ምን አይነት አገዛዝ እንደሆነም ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውንና የደረሰውን ግፍ በማተት መረጃ አስተላለፈ።
ኦባንግ እና ወገኖቹ ኮሪያ ዘምተው ህይወታቸው ላለፈና አካላቸው ለጎደለ ኢትዮጵያዊያን ማስታወሻ በቆም መታሰቢያ ስር ተሰባሰቡ። ሻማ አብርተው ወገኖቻቸውን አሰቡ። በዚያውም “በኢትዮጵያ ዘረኝነትን፣ የጎሳ ከፋፍልህ ግዛውን አስከፊነት ለመጪው ትውልድ ለማስተማሪያነት የሚውል ምስል በአገራችን እናቆማለን። በዚሁ አስከፊ አገዛዝ ሳቢያ ካገር ሲኮበልሉ ህይወታችው ያለፈ፣ በበረሃ የቀሩ፣ ውሃ የበላቸው፣ የተገደሉ፣ የታሰሩ፣ የታፈኑ፣ የደረሱበት የማይታወቁ፣ የተሰወሩ ወዘተ ስማቸው ከያለበት ተፈልጎ በዝርዝር የሚታይበትና መጪው ትውልድ ያለፉትን መሪዎቹን በተግባር የሚያየበት ይሆናል” ተባብለው ተለያዩ።
ኦባንግ ለመጨረሻ ጊዜ ሲለይ “አንድ ሁኑ። አያቶቻችንና አባቶቻችን በኮሪያ ምድር አንድም ምርኮኛ ሳያስመዘግቡ ታሪክ የሰሩት በኢትዮጵያዊነት ኅብረት ነው እንጂ በጎሣ ወይም በወገን ተከፋፍለው አልነበረም፤ ስለዚህ በኅብረታቸው ድል እንደነሱ እናንተም በፍቅር ተዋደዱ፤ አትበታተኑ። አንድ ስትሆኑ ትደመጣላችሁ። አንድ ስትሆኑ ጭብጨባችሁ ይሰማል። አንድነት ነጻ ያወጣችኋል። አንድነታችሁን ጠበቁ … እከታተላችኋለሁ። ሌሎች ወገኖችም ካሁን በኋላ ያስቡዋችኋል!!” በማለት አባ “ቃኘው” የመጀመሪያ ዙር ዘመቻውን አጠናቀቀ። (በዚህ ዘገባ አቶ ኦባንግን “አንተ” ብለን የጠቀስነው በምክንያት ነው)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
SATT says
Long live Obang! God bless you. The true Ethiopian.
Alemu Admassu says
God bless you my brother.
ተስፋዬ አበራ says
አቶ ኦባንግ የተግባር ሰው መሆኑን እና በተለይ ባህሪውንም ወድጀዋለሁ ።
ኢትዬፕያውያን ወገኖቻችንም ሰብስቦ የሰጠውንም ምክር ወድጄዋለሁ።
ጊዜው የተግባር እንጂ የወሬ አይደለም እንደተገለፀው በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገራት በወገናችን ላይ የሚደርሰው መከራ እና ስቃይ ተዘርዝሮ አይልቅም መፍትሄው አቶ ኦባንግ እንደገለፀው አንድ ሆነን ችግራችንን በተግባር ማስወገድ ብቻ ነው።
habtewold shember says
Mr Obange is emerging as a good leader of Ethiopians in diaspora and in problem.Let God bless him
give additional power to do more,because the problem is increasing as far as the present situation
continues.The diaspora should stand beside him in all aspects.