ሀገራችን በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ አደጋ ላይ ነች። ይኼን ሁላችንም እናውቀዋለን። የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰውና በማድረስ ላይ ያለው ልክ የለሽ በደል፤ ተጽፎም ሆነ ተነግሮ አላበቃም። ገና ብዙ ይጻፋል። ገና ብዙ ይተረካል። ለነገሩ መቼ ይኼ ጉደኛ የወንበዴዎች ድርጅት በደሉን አበቃና! የመጨረሻው ለመቃረቡ ግን፤ የመውደቂያ ደወሉን ራሱ አስምቶናል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መውደቁ አይቀሬ ነው፤ ቀን ከመቁጠር ባሻገር። ይኼ ሲከሰት ግን ምን ይከተላል የሚለው ጥያቄ እንደተንጠለጠለ ነው።
ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች ዙሪያችንን አጥረውናል። ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ሀገር፣ ድርጅት፣ ፓርቲ፣ ኅብረተሰብ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ የነፃ አውጪ ድርጅት፣ ግንባሮች፣ ጥምረቶች፣ ትብብሮች፣ ደጋፊዎች፣ ተደጋፊዎች፣ . . . እነዚህ ሁሉ ፅንሰ ሃሳቦች በመካከላችን ተመሣሣይ ደወል አያሰሙም። አንዳንዶቹ ላንዳችን ከሚያሰሙት በተቃራኒ ትርጉም ለሌላው ይሠጣሉ። በዚህ በያዝነው ሂደት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሲወድቅ የሚተካው ምንድን ነው? የሚለው አሳስቦኛል። የዚህ ጽሑፍ ዘገባ ይኼን በደንብ እንመርምር ነው። ሊከሰቱ የሚችሉ ገፅታዎችን በማመልከት፤ በኔ እምነት ማድረግ አለብን የምለውን አስቀምጣለሁ።
ከፊታችን ከተጋረጠው አደጋ መሰስ አድርጎ የሚያወጣን የተደበቀ ማዳኛ ሚስጥር የለንም። ሁሉን በደንብ ከመርምረን ደግሞ፤ ነገ የሚከሰተውን መተንበዩ ከባድ አይሆንም። አሁን ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ ስመረምረው፤ ነጋችን ተስፋ ሠጪ አይደለም። ለድፍረቴና ረዘም ላለው አስተያዬቴ፤ ብዙ ተጨንቄበታለሁ። በዚህ ስጋት ብቻዬን እንዳልሆንኩ ይገባኛል። አማራጭ ግን አላገኘሁም። እንዳለ ማቅረቡን ግዴታዬ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የትግል አዟሪት ከመካከላችን ጠፍቶ፣ ሀገራችን ሰላም ወርዶ፣ በትክክለኛ መንገድ ረሀብንና በሺታን አስወግደን፣ ሀገራችን ወደ ብልፅግና ጎዳና እንድታቀና፤ መሠረታዊ የሆነውን የአስተዳደር ጥያቄ ለአንዴና ለሁሌም መመለስ ይኖርብናል። ከውስጡ በስብሶ፣ አለያም በሰላማዊ አመፅ ሆነ በታጠቁ አማፅያን፤ ይኼ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሚንኮታኮትበት ጊዜ፤ በቦታው ማን ይተካል?
አንድ ሀገር አንድ ብሔር ከሚለው እስከ አንድ ሀገር ብዙ ብሔሮች ባዮች ድረስ ባንድ ጎራ አለን። የብሔሮች ስብስብ ሀገር ከሚሉት አንስቶ አንድ ሀገር የአንድ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ እስከሚሉት ባንድ ጎራ አለን። ታሪካችን ባዮችና የኛ ታሪክ አይደለም ባዮች ባንድ ላይ ባንድ ጎራ አለን። እንዴት ባንድ እንሠለፍ? እውነት አንድ ነገር፣ አንድ ግብ፣ አንድ ውጤት ነው የምንፈልገው? አሁን ባለንበት ሁኔታ የታጋዩ ክፍል ማዕከል ካለማበጀቱ አልፎ፤ አንድ ራዕይና አንድ ተልዕኮ የለንም።
አንዳንዶች፤ “ብቻ የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት ይውደቅ እንጂ፤ ምንም ችግር የለም” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ፤ “የለም! ምን ይከተላል የሚለውን ከወዲሁ ካልተዘጋጀንበት፤ በኋላ አደጋ ላይ እንወድቃለን።” ይላሉ። ከትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት ውድቀት በኋላ የሚመጣው ያስጨነቃቸውና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ውድቀት ብቻ ያሳሰባቸው ባንድ ጎራ አሉ። እንዴት ባንድ ይሠለፉ? እውነት አንድ ግብ አላቸው? ባለንበት ሁኔታ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሲፈረካከት፤ ሀገራችን የበለጠ አደጋ ላይ ትወድቃለች። መፈረካከሳቸው ተወዳጅና አይቀሬ ቢሆንም፤ ተተኪው በጣም የሚያሰጋ ነው።
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መውደቁ አንድና ሁለት የለውም። ምን ይከተላል በሚለው ላይ ሳተኩር፤ በኔ ግምት አምስት ሊከሰቱ የሚችሉ ገፅታዎች አሉ። ዋናው ማጠንጠኛ ማዕከሉ፤ ሀገር አቀፍ ሆኖ፤ በሀገሪቱ ሁሉ መረቡን የዘረጋ፣ የሕዝቡ ወገን የሆነ አንድ ጠንካራ አካል በቦታው አለመገኘቱ ነው። በርግጥ በአሁኑ ሰዓት የአንድነት ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ ጠንካራ ሆነው ይገኛሉ። አንድነት ከፈጠሩና ከተባበሩ፤ ወደ ሕዝባዊ ወገንነት አንድ ዕርምጃ ቀረብ ያለ ጉዞ ይሆናል። በሂደት ደግሞ ሊራራቁ ይችላሉ። አንድነት ፓርቲ በብዙ ቦታዎች መረቡን የዘረጋ ይመስላል። ሰማያዊ ፓርቲ ገና ከአዲስ አበባ እግሩን ያልነቀለ ይመስላል። አንድነት ብቻውን ለመገስገስ የሚሯሯጥ ይመስላል። መራራቃቸው ትልቅ ጉዳት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ አንድ ፓርቲ ብቻውን የሚገፋው ማንኛውም መንገድ፤ የብቻው ጉዞ ነው።
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሚፈረካከስበት ወቅት ሊከሰቱ ይችላሉ ብዬ የገምትኳቸው አምስቱ ገፅታዎች ከዚህ በታች አቀርባለሁ።
፩ኛ፤ በቦታው አንድ ጠንካራ የሆነ ተኪ የሕዝብ አካል ባለመገኘቱ፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ውስጥ፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ተመሳጥረው ሌሎችን በማጥፋት፤ አንዱ ክፍል ወይንም አንዱ ግለሰብ ጠንክሮ ወጥቶ፤ እራሱን በተለዬ ስም አንግሦ፤ ያንኑ አምባገነንነት የሚቀጥልበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል።
፪ኛ፤ በቦታው አንድ ጠንካራ የሆነ ተኪ የሕዝብ አካል ባለመገኘቱ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በውስጥ ቅራኔው ተተብትቦ ራሱን ጠልፎ በሚወድቅበት ወቅት፤ እንደ እስካሁን ቀደሙ፤ ወታደራዊው ክፍል ወይንም ወታደራዊ ክፍሉን በሥሩ የያዘ ክፍል በክፍተቱ ራሱን አግብቶ፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ተተክቶ ወታደራዊ አምባገነን ሆኖ የሚቀጥልበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል።
፫ኛ፤ በቦታው አንድ ጠንካራ የሆነ ተኪ የሕዝብ አካል ባለመገኘቱ፤ የነፃ አውጪ ግንባሮችና በየክልላቸው የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ከውጭ ሀገሮች ጋር በመመሳጠርና የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች በጎናቸው በማሰለፍ፤ ኢትዮጵያን በታትነው እንደ ዘመነ መሳፍንቱ የየጎጡ መንግሥት የሚመሠርቱበት ገፅታ ለከሰት ይችላል። አንዳንዶች ድርጅቶች ከባዕድ ሀገር መንግሥታት ጋር በማበር የራሳቸውን ሀገር ለባዕድ አሳልፈው ሊሠጡ የሚችሉበት ገፅታ ሊከተል ይችላል።
፬ኛ፤ በቦታው አንድ ጠንካራ የሆነ ተኪ የሕዝብ አካል ባለመገኘቱ፤ በታጋዮች ወገን መካከል እኔ እገዛ እኔ እገዛ እርስ በርሳቸው የሚዋጉበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል። በውጭ ሀገር እርዳታና ኃይሎች በመታገዝ፤ ወይንም ከርዝራዥ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ቀሪ ክፍል ጋር በማበር፣ አንዱ ጠንከር ብሎ ወጥቶ፤ የትግሬዎች ነፃ አውቺ ግንባርን ወታደራዊ ክፍል በማሰብሰብ ወይንም የራሱን ወታደራዊ ክፍል መሥርቶ በማጠናከር፤ ሌሎችን ጨፍልቆ የራሱን አምባገነንነት የሚመሠርት ገፅታ ለከሰት ይችላል። አንዳንዶቹ ድርጅቶች ለትራፊ ሥልጣን ሌሎችን ድርጅቶች ከድተው ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ጋር በማበር፤ ሌሎችን የሚወጉበትና የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር ዕድሜ የሚያራዝሙበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል።
፭ኛ፤ በቦታው አንድ ጠንካራ የሆነ ተኪ የሕዝብ አካል ባይገኝም፤ በተዓምርና በኔ ምኞት፤ ታጋይ ድርጅቶች በሙሉ፤ ሀገራቸውን ለማስቀደም በመስማማት፤ ከድርጅቶቻቸው ይልቅ የሀገራቸውን አጀንዳ በማስቀደምና የየድርጅቶቻቸውን አጀንዳ ወደኋላ በማድረግ፤ ለሀገራቸው በአንድነት ቆርጠው ለመነሳት ወስነው፤ የአደጋው ክብደት አሳስቧቸው፤ ሁሉም ታጋይ ድርጅቶች አንድ ግንባር ሊፈጥሩ የሚችሉበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል። ይህ የድርጅቶች ኅብረት የሀገር አንድነት ራዕይና ተልዕኮ አውጥቶ ሲነሳ፤ እናም አንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ ሕዝብ፣ የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ፣ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብት ይከበር፣ አንድ ትግል በሚል ራዕይ፤ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ገርስሶ፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመሠርትበትና የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ ለሕዝቡ የበላይነትን የሚሠጥበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል።
እኒህ ከላይ የተዘረዘሩትን አምስት ገፅታዎች እያንዳንዳቸውን ለይቶ ትንትኖ ማየቱ ይጠቅማል።
በመጀመሪያ ደረጃ፤ ልድገመውና አሁንም፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የመጨረሻ ትንፋሹን እየወሰደ ነው። በምንም ጉዳይ ይሁን በምንም መንገድ፤ መውደቂያ ቀኑ ቀርቧል። በመካከላቸው ክፍፍል መፈጠሩ አይቀሬ ነው። እስካሁን በግልፅ የምናወቀው የለም ብንልም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የተለያዩ አውታሮች፤ አንድነት የመቆማቸው ዕድል ከዜሮ በታች ነው። ሌሎች እስካሁን አብረው ሲያሽቃብጡለት የነበሩትም እንደ እስካሁኑ፤ ለጥ ሰጥ ብለው የማጎብደዳቸው ሁኔታ አብቅቶለታል። ሕዝቡም ግፊቱን ያጠነክራል። ሕዝቡ ግን በአንድ አጀንዳና በአንድ ድርጅት ሥር አልተካተተም። እናም ሥልጣን በሕዝቡ እጅ የመግባት ዕድሉ የተዘጋ ነው። ምን አልባት በተዓምር ፭ኛው ከላይ የተጠቀሰው ገፅታ ተከታይ ሁኔታ ገሃድ ከሆነ፤ ይህ መቼም ከምኞት አልፎ ገሀድ የመሆን ቀዳዳ ስላልታዬኝ፤ ተዓምር ብዬዋለሁ፤ ሥልጣን በሕዝቡ እጅ የመግባቱ ዕድል ይከሰታል። አለያ ግን ከላይ ከአንድ እስከ አራት ቁጥር በተዘረዘሩት ገፅታዎች መከሰት፤ ሕዝቡ ሥልጣኑን ያጣል። የኤርትራ ግንባሮች እርስ በርሳቸው መተላለቃቸውን ልብ ይሏል! የሶማሊያ ፀረ-ባሬ ክፍሎች ሀገራቸውን ምን እንዳደርጓት ያስተውሏል! በዩጎዝላቪያ ከቲቶ በኋላ የተከሰተውን ይመለከቷል! የሶቪየት ኅብረትን የመጨረሻ ያጤኗል! በኛ ሀገር ይኼ አይሆንም ብሎ መድረቅ፤ ያለፍንበትን አርባ ዓመት አለማገናዘብ ነው። ለሞኝ ሞኝነቱን ማወቁ፤ ለወደፊት ሞኝ እንዳሆን ይረዳዋል። ችግሩ ግን ሞኝ ነኝ ብሎ አለማመኑ ነው።
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች ሰርቀው በግል ካዝናቸው የሸጎጡትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረትና በጉልበታቸው ከሕዝቡ የነጠቁትን ሥልጣን፤ የትግራይን ወጣቶች፤ “የበላይነታችሁን፣ መብታችሁንና ንብረታችሁን ጠብቁ!” በማለት፤ የትግራይ ወጣቶችን እንደጭዳ ሊማግዷቸው ተዘጋጅተዋል። በትግራይ ክልል ያሉትን፤ “አማራና ኦሮሞ መጣብህ! ራስህን ተከላከል!” በማለት ወጣቱን ያስታጥቁታል። ሶሪያ በኢትዮጵያ! የጊዜያዊ ጥንካሬያቸውን በመመካት፤ የትግራይ ክልልን እንደ ሀገር ሊቆርሱም ወደ ኋላ አይሉም። ከኤርትራም ጋር ለመወገን መሯሯጣቸው አይቀርም። የመወዳጀታቸው ስኬት ግን ጠባብ ነው። በሁሉም መንገድ ቢሆን ትልቁ ችግራቸው በአንድነት መቆም አለመቻላቸው ነው። በአንድነት የሚቆሙት፤ በአንድነት ተቃውሞ ሲነሳባቸውና፤ ሁሉን አዛዥ ናዛዥ አንድ ግለሰብ ከላይ ሆኖ “የትአባክ!” ሲል ነበር። ያን የሚጫወት ግለሰብ በቦታው የለም። ከሰነበቱ ይፈጠራል። ላሁኑ ግን የለም። የዚህ አምባገነን ቡድን ችግሩ ደግሞ ሁሉም በእኩል የግንዛቤ ደረጃ ላይ አይደሉም። አንዱ ክፍል ዘለዓለማዊ ነን፤ ማንም አይደፍረንም ብሎ ያምናል። ሌላው ክፍል ፍርሃት ይዞት፤ በውጭ ያስቀመጣትን የስርቆት ብር አስልቶ፤ መውጫ ቀዳዳውን ያዘጋጃል። ሌላው ደግሞ አሁንም ሌሎችን በማሞኘትና፤ እንደ ልደቱ አያሌው ያሉ ከሀዲዎችን በጎኑ በማንኮልኮል አምባገነንነቱን ለመቀጠል ይሻል። እናም ሁሉም የየራሳቸውን የበላይነት ለማስፈንና የየራሳቸውን ጥቅም ማስጠበቂያ ዘዴ ለማበጀት በየጎራቸው ይቀምማሉ። ጨለም ሲል፤ ከኃይል ይልቅ ፍርሃት በውስጣቸው ቤት ሠርቶ፤ ነፍሴ አውጪኝ ይነግሣል። ሕዝቡን ማረድ፤ ያንኑ ያህል ይቀጥላሉ።
እንግዲህ በዚህ መነፅር ነው ሊከሰቱ የሚችሉትን ገፅታዎች የምናየው። ከታጋዩ ክፍል የጥንካሬ ጉድለት አንፃር፤ አሁንም የተከፋፈለ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቡድን፤ ከያንዳንዱ የታጋይ ክፍል የጠነከረ ይሆናል። ይህ ደግሞ ዕድሜ የሌለው ክስተት ስለሆነ፤ አንዱ ክፍል ሌላውን አውድሞ ብቻውን የበላይ ይሆናል። እናም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቢበታተንም፤ አንዱ ክፍል የበላይነቱን ወስዶ አምባገነንነቱን የሚቀጥልበት ገፅታ አለ። በዚህ ሂደት፤ የተባበሩ ስብጥሮች በአንድነት ወይንም አንድ ግለሰብ የበላይነቱን ሊወስድ ይችላል። በማንኛውም መንገድ፤ አቸናፊ ሆኖ የሚወጣው፤ የነበረውን አምባገነንነት ከመቀጠል ሌላ፤ የተለዬ የሚያራምደው አጀንዳ የለውም።
ሌላው የዚሁ አካል የሆነው ገፅታ ደግሞ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሚፈረካከስበት ጊዜ፤ በቦታው ጠንካራ የሕዝብ ወገን የሆነ ኃይል በቦታው ባለመገኘቱ፤ ያሉት የተለያዩ ታጋይ ድርጅቶች በራሳቸው አጀንዳ ተኮፍሰው አንድነት ባለመፍጠራቸው፤ የታጠቀና የተደራጀው ወገን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወታደራዊ ክፍል ይሆናል። እናም በፀረ ሽብርነት አጀንዳ፤ ከውጪም በምዕራባዊያን በመደገፍ ሥልጣኑን የሚወስድበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል። ይህ ክፍል በሀገር ደህንነት ስም፤ የበለጠ የሕዝቡን መብት የሚረግጥና አምባገነንነቱን የሚቀጥለበት ገፅታ ሊከሰት ይችላል።
እኒህ ከላይ የተዘረዘሩት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ፍርክራኪ ክፍሎች ሊፈጥሩ የሚችሉት ገፅታዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በኔ እምነት፤ በሀገራችን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀቅ፤ አሁን በታጋዩ መካከል ያለው እውነታ፤ መፍትሔ ይሻል። ኢትዮጵያዊያን ታጋዮች፤ ለዚህ የፖለቲካ ሀቅ ትክክለኛ የሆነ የመፍትሔ ሃሳብ መፈለግና ማቅረብ እንችላለን። ፍላጎቱ፣ ትምህርቱና ልምዱ አለን። የፖለቲካ ስሌታችን ግን ያን ከማድረግ አግዶናል። እኔ የበላይነትን የማላገኝበትን የወደፊት ጉዞ አልከተልም በማለት በየጎራችን የተከተትንበት ሀቅ፤ በያለንበት ተብትቦና ቀፍድዶ ይዞናል። እንዴት ይኼን ትብታብ በጣጥሰን እንውጣ? አምስተኛውን ገፅ የያዘ ነገ እንዲኖረን ምን እናደርግ? ይህ ነው ጥያቄው!
አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ፤ ብዙዎቻችን ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያንን፤ በከፍተኛ ሥጋት ላይ ጥሎናል። በታጋዩ ጎራ ያለው ሁኔታ የተመሰቃቀለ ነው። ይህን ተገንዝበን ሁላችን በያለንበት የምናደርገውን ጥረት ወደ አንድ ማዕከል ካላመጣነው፤ በየግላችን የምናደርገው ሩጫ የከፋ ውጤት ያስከትላል። የአፄውን መንግሥት ለመጣል ስንሯሯጥ የተከተለው የሰው በላ መንግሥት ሊያስጠነቅቀን ይገባል። ከመጥፎ ታሪኩ የማይማር መጥፎ ታሪኩን ይደግማል። ከዚህ መውጣት የሚቻለው ደግሞ፤ ሀገራዊ የሆነ ውይይት ለማድረግ ሀገራዊ የሆነ መድረክ ስንፈጥር ነው። የዚህ መድረክ መፈጠር ግዴታ ነው። ሀገራችን አሁን ካለችበት ማጥ ልትወጣ የምትችለው በአንድነት ሆነን ሁላችን ስንነሳ ለመሆኑ ማንም ሊጠራጠር አይገባውም።
የተመሰቃቀለው የታጋይ ክፍል ጎራ የመርማሪ ያለህ እያለ እየጮኸ ነው። የግለሰቦች ግጭት፣ የድርጅቶች እሽቅድድም፣ የአጀንዳዎች መደበላለቅ፣ በትውልድ ቆጠራ ቦታ ማካለሉ ሩጫ፣ አባላትን ለማብዛት የሚደረገው ርብርብና የመሳሰሉት ለትብብሩ ከባድ እንቅፋት ሆነዋል። የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ ደግሞ ከትብብር አልፎ አንድነት ካልተመሠረተ፣ ድል እንደማይገኝ ከወዲሁ አውጇል። ችግሩ ምንድን ነው? በእውነት ይኼን አጥንቶ መፍትሔ የሚፈልግ ፈቃደኛና የተማረ ክፍል የለንም? ወይንስ እያንዳንዱ ታጋይና ምሁር፤ ወገን የለዬ የፖለቲካ ቡድን አምላኪ ሆኗል ማለት ነው? እውነት ለዚህ መፍትሔ ማግኘቱ ለኛ የፖለቲካ ታጋዮችና ምሁራን ይከብዳቸዋል? እነሱስ ከከበዳቸው፤ ነብይ እስኪወለድልን መጠበቅ አለብን?
በእውነት፤ ለኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች አብረው መሥራት ፈፅሞ አይቻላቸውም? ወይንስ በየድርጅቱ ያሉ አባላት አብሮ እንደመንጋ መነዳት እንጂ፤ ነፃ ሃሳብ የመያዝና ላመኑበት መቆም የተሳናቸው ናቸው? መቻቻል የሚለው ግንዛቤ በአእምርሯቸው ቤት መዝገብ ውስጥ ቦታ የለውም? ለሀገሪቱ ሕልውና ሲባል አንገታቸውን ትንሽ መቀልበስ ተስኗቸዋል? አብረው ላለመሥራት ከወሰኑስ ለምን በጠላትነት ይተያያሉ? ባልተገኘ ሥልጣን ከመነታረክና ከመራራቅ ይልቅ፤ ለምን ባለው ተጨባጭ ሀቅ አብረው አይሠለፉም?
መፍትሔውን በክፍል ሁለት ይዤላችሁ እቀርባለሁ።
Leave a Reply