“አርቲስት ቴዲ አፍሮ የጥምቀት በዓልን ወደ አደባባይ ወጥቶ ማክበሩን የሚያሳይ ፎቶ ተለቋል” ሲሉ ነው በርካቶች ባሰራጩት አስተያየት “ነገሩ ምንድን ነው?” ሲሉ ግራ በመጋባት ማብራሪያ የጠየቁ ቢበዙም፣ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመው የነበሩ አካላት ላይ ውግዘት መድረሱን ያስታወሱም አልታጡም።
የሚያደርገውን በማወቅ፣ ጊዜና ሰዓት በማስላት በሚያከናውናቸው ተግባሮቹ ስኬት የለኩት “ቴዲ ሳያውቅ ይህን ለበሰ ለማለት ያስቸግራል” ሲሉም ተድምጠዋል።
የዲዛይን ችሎታ አካታ እንዳያዘች የሚነገርላት ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ በጥንቃቄ እንደምትሞሽረው የሚያውቁ “ይህን እንደ ስህተት መቀበል ያዳግታል” ሲሉ አስቸኳይ ማብራሪያ እንደሚሹ አመልክተዋል።
ፎቶውን በማጋራት ሰፋ ያለ አስተያት ከጻፉት መካከል ቶማስ ጃጃው በቴሌግራም ገጹ “እንደ ማንኛውም በብርሃነ ጥምቀቱ እንደሚያምን ክርስቲያን በዓሉን በማክበሩ ከማንም በላይ የበዓሉ በረከት ተካፋይ የሚያደርገው ደስተኛው ራሱ የሚሆን መሆኑ ቢታወቅም፣ በሙዚቃው ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት አርቲስቶች አንዱ እንደመሆኑ የጥምቀት በዓልን በአደባባይ ተገኝቶ ታቦታቱን በእልልታ በጭብጨባና በዝማሬ እያጀቡ ከሸኙት ታዋቂ ሰዎች መካከል እንደመታየቱ የእሱ አድናቂ የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ብዙዎችን እንደተለመደው ሊያስደስት የመቻሉ ጉዳይ አያጠራጥርም” ሲል አስተያየቱን በጥቅል እውነት ይጀምራል።
ያክልና “በእውነቱ እኔም ጥምቀትን ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተገኝቶ ማክበር በመቻሉ ጊዜውን በመልካም ቦታ አሳልፏል ብዬ አምናለሁና ደስ ይለኛል። ነገር ግን ቴዲ አፍሮ ለጥምቀት በዓል ለብሶት የወጣው ልብስ ላይ የመስቀል ምልክቱ የተዘቀዘቀ በመሆኑ ጥምቀትን ሲያከብር ተመልክቶ ደስ ይላል ያለ የእምነቱ ተከታይ የእሱ አድናቂዎች ጭምር እንኳን ቢሆን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይና በጥምቀት በዓል ላይ ለብሶት የታየ ስለሆነ ብለው ጉዳዩን በቀላሉ ሊመለከቱት ይችላሉ ብዬ መደምደም አይቻለኝም” ብሎ መከራከሪያውን ያቀርባል።
“በተዘቀዘቀው መስቀል ግራ የሚጋቡበትና ሊቆጡበት የሚችሉ የእምነቱ ተከታዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው የማስበው” የሚል ፍርድ የሰጠው ቶማስ፣ ሲያስረዳ “ምክንያቱም የቴዲ አፍሮ አድናቂ የሆኑት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታዮች ‘መስቀል ሃይላችን ነው፣ መስቀል ቤዛችን ነው’ የሚሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ከዚህ በፊት የመስቀል ምልክቱን እንደ ቴዲ አፍሮ ዘቅዝቆ ለበሰ የተባለ ሰውን አንዴ ‘666’ ሌላ ጊዜ ‘ደግሞ ፀረ-ኦርቶዶክስ’ የሚል ዘመቻ ተከፍቶበት እንደነበር የሚታወቅ ነውና”
የቶማስ አመላካችና ንፅፅራዊ አስተያየት የሙግት ሃሳቡን ሲያጸና “እርግጥ ነው ቴዲ አፍሮ የተዘቀዘቀ የመስቀል ምልክት ያለበትን ልብስ ራሱ ያሰራው፣ ሱቅ ላይ የገዛው፣ ወይም በስጦታ የተሰጠው፣ የመስቀሉን ሁኔታ ያላስተዋለው ጉዳይ ነው ሊባል ይችል ይሆናል” የሚል ግምት ያስቀድምና “የታዋቂ ለዛውም እንደ ቴዲ አፍሮ ላሉት ለአለባበሳቸው፣ ለአነጋገራቸውና ለአረማመዳቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፤ ነገሮችን በጥንቃቄ ይከታተላሉ ተብሎ የሚነገርላቸው ሰዎች ሺዎች በሚሰበሰቡበትና በሚገኙበት በጥምቀት ለሚለበስ ልብስ ልዩ ትኩረት በሚሰጥበት አደባባይ የተዘቀዘቀ መስቀል ያለበት ልብስ ያለማስተዋል የተለበሰ አድርጎ ለመቁጠር እንዴት እንደሚቻል አላውቅም” በሚል ድርጊቱ ሆን ብሎ የተደረገ የሚመስልበትን ማሳያ ያመላክታል።
“የመስቀሉ መዘቅዘቅ ችግር የለበትም ከተባለ” ይላል ጸሃፊው “ከዚህ ቀደም መስቀል ዘቅዝቀው ለብሰዋል በሚል የተሰጡ ትርጉሞች የተደረጉ ውግዘቶች ዋጋ ያጣሉ እንደማለት ይሆናል” ሲል ቴዲ አፍሮን ለእይታና ለግምገማ አንገዋሎ አቅርቦታል።
ጉዳዩ ውሎ አድሮ የሚያስነሳውና የሚከተለው አስተያየት ምን እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ቢያስቸግርም፣ “በጥቁር ልበሱ” ዘመቻ ወቅት የመሪነቱን ተግባር ከሚወጡ አስተባባሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ “ነገሩን ታቃናዋለች” የሚል አስተያየት የሰጡ ጥቂቶች ታይተዋል። ይህ እስከተባለ ድረስ ቴድሮስ ካሳሁን በግሉ ያለው ነገር የለም። (ኢትዮ12)
ከዚህ በፊት የተዘቀዘቀ መስቀል ለበሰ በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰነዘረበት ዮናታን አክሊሉ ተሰፍቶ የተሰጠውና ሳያስተውል ማድረጉን በማመን ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል። ለቅድስት ቤተክርስቲያን፣ ለምዕመናን፣ ለአድናቂዎቹ ከሁሉም በላይ ለመስቀሉ ክብር ሲል ይህንን መሰል ምላሽ ከቴዲ አፍሮ ባለመሰማቱ ያሳዘናቸው በየማኅበራዊ ሚዲያ ቀሬታቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
አይ ሃበሻ ነገር ስንቆረጥም ጥርሳችን አለቀ። ተዘቀዘቀ አልተዘቀዘቀ መስቀሉ እኮ ለሚያምኑት እንጂ ላላመነው ምንም ትርጉም የለውም። ግን ያለ እኛ ሃይማኖት መንግስተ ሰማያት መግቢያ የለም የሚሉ ወስላቶች በሞሉበት ምድር ይህ ወሬ ተብሎ መወራቱ የቱን ያህል እምነቱ እንደተጣረሰ ያሳያል። ሲጀመር ሃይማኖት የማዘናጊያና ሰውን የመጨቆኛ መሳሪያ ነው። ጥቂት ብልጦች መስቀልና መጽሃፍ ቅድስ እያሳዪ የስንቱን ቤት እንዳራቆቱ፤ የስንቱን ሃገር እንዳፈረሱ ታሪክ ዘግቦ የያዘው ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ አሁን በዘርና በቋንቋ ተከፍላ በክልል የተተለተለችው ሃገራችን በእነዚህ ጠምባራ ፓለቲከኞች የተነሳ በቋንቋዬ ካልተቀደሰ ወይም ካልተሰበከ አልሰማም በማለት በሃገርና በውጭ ሰውን ሲያዋክቡና የተለመደውን እሬት ፓለቲካቸውን በሃይማኖት ስም ሲያስፋፉ ማየት ያማል።
እውነተኛ ሃይማኖት የሰዎችን እንበለ ፍርድ አይቶና ሰምቶ ይሟገታል። በመንግስትም ሆነ በሌሎች ታጣቂዎች እጅ ለሚደርስባቸው በደል ድምጽ ይሆናል። ካለው ያካፍላል። ሳይኖረው በሃሳብና በምክር ይረዳል። ዝም ብሎ የእምነት ጠበቃ ለመሆን ያለ የሌለውን ወሬ እየነዙ ሰውና ሰውን ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩ የእምነት ሰዎች ነን የሚሉ ሁሉ መንገድ የሳቱ ወስላቶች ናቸው። ጠመጠመ፤ ወንጌላዊ፤ ነብይ፤ ፓስተር፤ ሃጂ ተባለ ተግባር የሌለው እንባቸው በግፍ የተነሳ ለሚፈስ ደጋፊ ለሌላቸው ያልቆመ እምነት በአፍንጫዬ ይውጣ።
እዚህ ግባ የማይባልን ነገር ከተቀበረበት እየቆፈሩ እያወጡ ደረት ማስደቃቱና እግዚኦ ማህረነ ማሰኘቱ መቆም አለበት። ሰው በተሰጠው ጭንቅላት አስቦና ተሳስቦ መኖር መቻል አለበት። በዚህም በዚያም እያሳበቡ ሰውን አፍኖ መያዝና የማሰቢያ ብልሃቱን መቀማት ወንጀል ነው። ለእኛ የሰማይ ቤትን እያሳዩ ከስራችን ስንቱን ዘረፉ? ስንቱን በሌለ ቤቱ ጾም አዳሪ አደረጉት። እኔ መስቀሉ በቲሽርት ላይ ሆነ በሌላ ነገር ላይ ተዘቀዘቀ ተንጋደደ የመነጋገሪያ ነጥብ ሊሆን አይገባም ባይ ነኝ። እንዲሁ ለትንኝን እንደማጽዳት ይቆጠራል። ጽዳቱ ቀርቶ ሞቷ እንዲሉ። አየን እኮ በአንገታቸው ላይ መስቀል ያንጠለጠሉ፤ አልፎ ተርፎም ማተብ ያሰሩ በቀን አምስት ጊዜ የሚሰግድ አይደሉ እንዴ በሰሜን እናቶችን የደፈሩት፤ መነኩሴዎችን የገደሉት፤ እንስሳትና እጽዋትን የጨፈጨፉት። በወለጋ ቤት ዘግተው ሰውን ወደ ገደል የሰደድት አውሬዎች መሪ ሚሽን ውስጥ ያደጉ አይደሉምን? በአርሲ ያ ሁሉ ሲጨፈጨፍና ወደ ገደል ሲጣል ሃይማኖተኛ ነን በሚሉ ሰዎች የዘር ጥላቻ አልነበረምን? ውጊያው ከእነዚህ አውሬዎች ጋር እንጂ ከሸሚዝ መስቀል መዘቅዘቅና መንጋደድ ጋር አይደለም። ጥያቄው ባንተ ልብ ውስጥ ያለው መስቀል ተዘቅዝቆ ይሆን? እሱን ስጋልኝ። በቃኝ!