ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅና ከዚያ በፊት በነበረው ሁኔታ የኢንተርኔት መቆራረጥና መታገድ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ማድረሱ የተጠቀሰ ሲሆን ባለፈው አንድ ዓመት አገሪቱን 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማሣጣቱን የአሜሪካው ብሩኪንግስ ኢንስቲቲዩት ይፋ ያደረገው ጥናት አመልክቷል። ዴልዮት የተባለው ዓለማቀፍ አማካሪ ተቋም በበኩሉ፤ የሞባይል ኢንተርኔት መዘጋት ሀገሪቱን በቀን 5 መቶ ሺህ ዶላር እያሳጣት ነው ብሏል።
በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተቃውሞና ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎቶች መቆራረጥ፣ ሃገሪቱን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥቷል ብሏል – ዴልዮት።
የኢንተርኔት አገልግሎት መቃወስ የኢኮኖሚ እድገቱን እንዲቀዛቀዝ አድርጓል ያለው “አፍሪካን ቢዝነስ”፤ ፈጠራዎች እንዳይበረታቱ፣ የገቢ ታክሶች በአግባቡ እንዳይሰበሰቡና ነጋዴዎች በቴክኖሎጂው ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር ማድረጉን … የብሩኪንግ ኢንስቲቲዩት ም/ፕሬዚዳንት ዳረል ዌስትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዘመናዊ የኢኮኖሚ እድገት በኢንተርኔት ላይ ጥገኛ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ታዳጊ ሃገራት በአመታዊ ጠቅላላ አገራዊ ምርት እድገታቸው ላይ የ1.35 በመቶ ድርሻ እንዳለው ያመለክታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በተለይ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት ግንኙነት መቋረጡ፣ በመንግስት ገቢ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ የዕለት ተለት ስራቸው በቀጥታ ከኢንተርኔት ጋር ለተቆራኙ ነጋዴዎችም ከፍተኛ ኪሳራ እያስከተለባቸው እንደቆየ ጠቁሟል።
ከኢንተርኔት አገልግሎት ባሻገር ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዱ የሆነው የተለያዩ የተንቀሳቃሽ ስልኮች መተግበሪያ (Application) እየተገደበ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል – ቫይበር፣ ዋትሳፕና ሜሴንጀር የመሳሰሉ የኢንተርኔት የግንኙነት አውታሮች በዚህ መንገድ እየተገደቡ መሆኑን በመጥቀስ።
ባለፈው አመት በኢንተርኔት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ላይ የተደረገው ጥናት፤ በአሜሪካ የኢንተርኔት አገልግሎት በአመት እስከ 966 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት፣ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ 6 በመቶ ድርሻ እንዳለው የተጠቆመ ሲሆን ሌሎች ሃገራት ግን ከዚህ ቴክኖሎጂ ማግኘት የሚገባቸውን ከፍተኛ ገቢ አገልግሎቱን በመገደብ እያጡ መሆኑ ተመልክቷል።
የኢንተርኔት አገልግሎትን በመገደብ ከአፍሪካ በቀዳሚነት የተጠቀሰችው ሞሮኮ፤ በአመት 320 ሚሊዮን ዶላር ማጣቷ የተጠቀሰ ሲሆን ኮንጎ 72 ሚሊዮን ዶላር፣ አልጄሪያ 20 ሚሊዮን ዶላር፣ በአመት አጥተዋል ተብሏል። ኢትዮጵያ በበኩሏ፤ ባለፈው 1 ዓመት 9 ሚሊዮን ዶላር ማጣቷን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ከአፍሪካ ሃገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ግብፅ የተሻለ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳላቸው የተጠቆመ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ናሚቢያና ደቡብ ሱዳን የኢንተርኔት አገልግሎታቸው ዝቅተኛና አርኪ አለመሆኑ ተመልክቷል። በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤትም ሆነ ከኢትዮ-ቴሌኮም ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች “ስብሠባ ላይ ናቸው” ተብለን ሳይሳካልን ቀርቷል። (አለማየሁ አንበሴ፣ አዲስ አድማስ)
Leave a Reply