• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የኃይሌ ወደ ፖለቲካው መድረክ መምጣት እያነጋገረ ነው

July 24, 2013 10:16 pm by Editor 1 Comment

“ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ መብቱ ቢሆንም እንደስፖርቱ በፖለቲካውም የሚያንጸባርቅ አይመስለኝም” ዶ/ር መረራ

“በአገሪቱ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የለም። አገሪቱ የጡንቸኞች ሀገር ናት። … ገብቶ ይሞክረው” ፕሮፌሰር በየነ

“እኔ ኃይሌን ብሆን ኖሮ በግል ወደ ፖለቲካ ከምገባ ወደ ፓርቲ መግባቱን ነው የምመርጠው። ከፓርቲው ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫዬ የሚሆነው አንድነት ፓርቲ ነው” ዶ/ር ነጋሶ

“ኃይሌ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ በግሉ ወይም በፓርቲ ወደ ምርጫ መግባቱን እንኳ ግልፅ አላደረገም … ፖለቲካ በግል ፍላጎት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ፖለቲካ እራሱን የቻለ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል። … ፖሊሲ ማስፈፀም የሚቻለው በፓርላማው አብላጫ ወንበር ሲያዝ ነው፤ … አንድ ሰው ብቻ ከሆነ ግን “አጃቢ” የመሆን አደጋ አለው። አቶ ገብሩ

“አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክብር እንግድነት እንዲገኝ ጥያቄዎችን ባለመቀበል በአንፃሩ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ ማህበራት ላይ በክብር እንግድነትና በንግግር አድራጊነት መገኘቱ የሚያመለክተው የኃይሌ የፖለቲካ ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ ይሁንታ ያገኘ መሆኑ ነው … ወደ ፓርላማ ለመግባት የወሰነውም የግሉን ክብርና ዝና መሻት እንጂ አዳዲስ የፖሊሲ ኀሳቦችን በመያዝ (አይደለም)…” አቶ ሀብታሙ

_______________________________________________________________________________

ዝነኛው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው በ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ አዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በመወዳደር ወደ ፓርላማ ለመግባት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ በግል ወይም በፓርቲ ውስጥ ገብቶ ለመወዳደር ግልፅ ባያደርግም ከሁለት ዓመት በኋላ በምርጫው ተሳታፊ በመሆን የፖለቲካ ጅማሮውን እውን እንደሚያደርግ አስታውቋል። በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ “ፕሬዝዳንት ይሆናል” የሚለውን ዘገባ በማስተባበል ፕሬዝዳንት መሆን ግን እንደማይጠላ  ተናግሯል።

ታዋቂው አትሌት ይሄንን አስተያየቱን በግልፅ ከሰጠ በኋላ በውጪና በሀገር ውስጥ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። የኃይሌን የፖለቲካ ተሳትፎ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመዳበርና አስቸጋሪነት አንጻር እያነሱ የአትሌቱን ተሳትፎ አምርረው የተቹ እንዳሉ ሁሉ መግባቱንም የሚያበረታቱ አልጠፉም።

በሀገሪቱ ያሉ የፓርቲ አመራሮችም የሻለቃ ኃይሌን የፖለቲካ ተሳትፎ የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባቸው ከሰጡት አስተያየት መረዳት ተችሏል።

ሰንደቅ ካነጋገራቸው የፓርቲ አመራሮች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ መብቱ ቢሆንም እንደስፖርቱ በፖለቲካውም የሚያንጸባርቅ አይመስለኝም ሲሉ ባልተለመደ ሁኔታ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ኃይሌ ለሁሉም ክፍት ወደሆነው ፖለቲካ መግባቱ አዲስ ነገር እንደሌለው ገልጸዋል።

“በተለይ እንደሱ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካ መድረኩ መምጣታቸው ተገቢ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ለሀገሩ ብዙ የደከመ፣ ላቡን ያንጠፈጠፈ ሰው በመሆኑ ለሀገሪቱ ቀና ነገር እስካሰበ ድረስ ወደመድረኩ መምጣቱ የሚደገፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን የሀገሪቱ ፖለቲካ የህይወት መስዋዕትትን ጨምሮ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ያለስም ስም የሚያሰጥ አስቸጋሪ ውጣውረድ ያለበት በመሆኑ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።

“በአገሪቱ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የለም። አገሪቱ የጡንቸኞች ሀገር ናት። የሀገሪቱ ፖለቲካ ያልሰከነ፣ ሊገመት የማይችል ነው። የጎበዝ አለቃ ሁሉ ፖለቲከኛ ነኝ የሚልበት ሀገር ነው። ስለዚህ ሻለቃ ኃይሌም ገብቶ ይሞክረው” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ የኃይሌ የፖለቲካ ውጤታማነት የሚለካው በሀገሪቱ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

“ኃይሌ ገብረስላሴ ፓርላማ መግባት ያቅተዋል ብዬ አላስብም” የሚሉት ፕሮፌሰሩ “ኃይሌ በቂ ሀብት አለው። እኛ ድሆቹም ሀሳብ ብቻ ይዘን ለምንንቀሳቀሰው ሊያስቸግር ይችላል” ብለዋል። በተጨማሪም ኃይሌ ከተንኮልና ከመሰሪነት ካልተተበተቡ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ በመሆኑ አመጣጡ ጤነኛ ነው ብለዋል።

“ኃይሌ ፓርቲ አቋቁሞ ቢገባ ይሻላል” ስለሚባለው አስተያየት የተጠየቁት ፕሮፌሰር በየነ ፓርቲ ማቋቋም የተሰለቸ ጉዳይ በመሆኑ እንደ አዲስ ፓርቲ ከሚያቋቁም ይልቅ ለኃሳቡ በሚመቸው ፓርቲ ውስጥ ቢቀላቀል የሚመከር ነው ብለዋል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች በውስጥ ችግር እየተነታረኩ መሆኑ ለጊዜው በፓርቲዎቹ ላይ ተስፋ ሊያስቆርጠው ችሎ ይሆናል ብለዋል። ነገር ግን በፖለቲካ ግለሰብ ለብቻው የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለም ገልጸዋል።

የአንድንት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበርና የቀድሞ የፓርላማ የግል ተወዳዳሪ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ወደ ፖለቲካ እንዲገባ የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ይፈቅድለታል ብለዋል።

ኃይሌ ተሳክቶለት ወደ ፓርላማ ከገባም ስፖርቱንና የፓርላማ ተግባሩን በአንድ ጊዜ መወጣት እንደማይችል የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ በፓርላማውም ቢሆን ከእሳቸው ልምድ በመነሳት ለግል ተወዳዳሪ የሚኖረው መብት እጅግ በጣም የተመጠነ ከመሆኑም በላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለዋል።

“ኃይሌ በግል ተወዳድሮ ወደ ፓርላማ ቢገባ የመናገር ዕድል ሊያገኝ የሚችለው ቢያንስ ሁለት ደቂቃ ቢበዛ ሶስት ደቂቃ ነው። ይሄንንም ዕድል ሊያገኝ የሚችለው በአፈ-ጉባኤዎቹ መልካም ፈቃድ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በፓርላማው ውስጥ በሚቋቋሙ ቋሚ ኮሚቴዎችም ውስጥ ሊገባ አይችልም። በአጠቃላይ በግል ተወዳድሮ ፓርላማ መግባት ቦታ የሌለው ጉዳይ ነው” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ለኃይሌ ጥሩ አማራጭ እራሱን በፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ ለማስገባት ቢሞክሩ ጥሩ ነው ሲሉ ምክር ለግሰዋል።

“እንደምታውቀው ኃይሌ በአሁኑ ወቅት ባለሀብት ሆኗል። ከዚህ አኳያ የካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ አመቺው የሊብራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው። ስለዚህ ለአትሌቱ ጥሩ ፓርቲ ሊሆን የሚችለው እንደ አንድነት ፓርቲዎች ውስጥ ቢገባ ነው የምመክረው” ብለዋል።

“እኔ ኃይሌን ብሆን ኖሮ በግል ወደ ፖለቲካ ከምገባ ወደ ፓርቲ መግባቱን ነው የምመርጠው። ከፓርቲው ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫዬ የሚሆነው አንድነት ፓርቲ ነው” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ኃይሌን በቅርብ ስለማያውቁት በግሉ ምን አይነት ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ስለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።

“ኃይሌ ፕሬዝዳንት ይሆናል ብለው ይገምታሉ” ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር ነጋሶ ሲመልሱ፤ “ፕሬዝዳንት ለመሆን አይችልም። ምክንያቱም ገና ወጣት ነው። ቦታው ለወጣት አይሆንም። ምናልባት የሀገሪቱ መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ልጁ በዓለም ስለታወቀ በዚያ አቅጣጫ ከማንም በላይ ሊያስተዋውቅ ይችላል። ነገር ግን ቦታው ብዙ መስራት ለሚፈልግ ወጣት አመቺ አይደለም። ከዚህ ጎን ለጎን የመንግስትን አቋም ማንፀባረቅ ይጠበቅበታል። በ2007 ምርጫ ኢህአዴግ መልሶ የሚያሸንፍ ከሆነም የኢህአዴግን አቋም እንዲያንፀባርቅ ሊገደድ ይችላል” ብለዋል።

የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ (አረና) ሊቀመንበርና የቀድሞ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው የኃይሌ ወደ ፖለቲካ መምጣት መብቱ እንደሆነ ገልጸው፤ ዋናው መታየት ያለበት አትሌቱ ወደ ፖለቲካ ገብቶ በምርጫ ሲፎካከር የሚያቀርበው መርሃ ግብር ወሳኝ ነው ብለዋል።

“አትሌቱ ወደ ፖለቲካ መግባቱን፣ በምርጫ መሳተፉን ከመግለፅ ባለፈ ስላነገበው ፕሮግራም የጠቀሰው ነገር አለመኖሩን ያወሱት አቶ ገብሩ፤ ኃይሌ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ በግሉ ወይም በፓርቲ ወደ ምርጫ መግባቱን እንኳ ግልፅ አላደረገም ብለዋል።

አነጋጋሪው ጉዳይ አትሌት ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ ሳይሆን ምን ይዞ ገባ? የሚለው ነው መታየት ያለበት ያሉት አቶ ገብሩ፤ ኃይሌ ወደ ፖለቲካ ሲገባ ምን አይነት ለውጥ ለማምጣት ነው? የሚለው በግልፅ መታወቅ አለበት። ያለውን ለማስቀጠል ከሆነ ትርጉም የለውም። ለለውጥ ከተዘጋጀ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው። ኃይሌ የለውጥ አጀንዳ ከሌለው ግን ቀደም ሲል የነበረውንም ዝና ሊንድበት እንደሚችልም ገልፀዋል።

“ኃይሌ የአፈፃፀም ችግሮችን መሰረት አድርጎ ወደ ፖለቲካ የሚገባ ከሆነ ዋጋ የለውም። እራሱ ኢህአዴግም የአፈፃፀም ችግር እንዳለበት ነው የሚገልፀው። ከኃይሌ የሚጠበቀው አዲስ የፖሊስ አቅጣጫ ነው። ወሳኙ ነገር ምን ፖሊሲ ለማስፈፀም ነው ወደ ፖለቲካ የሚገባው የሚለው ነው። ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ የፖሊስ ለውጥ እየፈለገች ነው። የኢህአዴግን ፖሊሲ የመድገምና የእሱን ፕሮግራም የማስቀጠል ዓላማ ለዚህች ሀገር ፋይዳ የለውም” ብለዋል።

“ፖለቲካ በግል ፍላጎት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ፖለቲካ እራሱን የቻለ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል። ለፖሊሲው መተግበርም የፀና አቋም ሲኖር ነው” የሚሉት አቶ ገብሩ ኃይሌ ያመነበት ፖሊሲ እስከሌለው በግሉ የሚፈጥረው ነገር የለም ብለዋል። ፖሊሲ ማስፈፀም የሚቻለው በፓርላማው አብላጫ ወንበር ሲያዝ እንደሆነም አቶ ገብሩ ገልጸው አንድ ሰው ብቻ ከሆነ ግን “አጃቢ” የመሆን አደጋ እንዳለውም ገልጸዋል።

የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ም/ቤት አባልና የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ የሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ወደ ፓርላማ የመግባት ፍላጎት በርካታ መልኮች እንዳሉት ገልጸዋል። ነገር ግን ሻለቃ ኃይሉ ከአዲስ አበባ ወጣት ማህበር ጋር ተደጋግፎ መስራት መጀመሩ ማህበሩን ለምርጫ ተግባር ለማዋል ማቀዱን ያሳያል ብለዋል።

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክብር እንግድነት እንዲገኝ ጥያቄዎችን ባለመቀበል በአንፃሩ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ ማህበራት ላይ በክብር እንግድነትና በንግግር አድራጊነት መገኘቱ የሚያመለክተው የኃይሌ የፖለቲካ ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ ይሁንታ ያገኘ አስመስሎበታል ብለዋል።

ሻለቃ ኃይሌ ወደ ፓርላማ ለመግባት የወሰነውም የግሉን ክብርና ዝና መሻት እንጂ አዳዲስ የፖሊሲ ኀሳቦችን በመያዝ እንዳልሆነ የገመቱት አቶ ሀብታሙ፤ ለሻለቃ ኃይሌ አመቺ መንገድ ሊሆን የሚችለው በፓርቲ በኩል ተደራጅቶ ከፕሬዝዳንትነቱ ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ የተረከበ እንደሆነ ብቻ ነው ብለዋል።

የመጀመሪያው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ እ.ኤ.አ. በ1996 አትላንታ በ10ሺ ሜትር በ2000 ሲዲኒ በ10ሺ ሜትር፣ በአለም ሻምፒዮና በ1993 በስቱትጋርት ፣ በጉተንበርግ አቴንስ፣ በሲቪላ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በስቱትጋርት፣ ሲቪላ በ10ሺ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በኤድመንተን በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ እና ሌሎችም በርካታ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። (ዘሪሁን ሙሉጌታ፤ ሰንደቅ)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Politics Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. በለው ! says

    July 25, 2013 05:42 am at 5:42 am

    …በአነስተኛና ጥቃቅን የታቀፉ ሴቶችን፣ አርቲሰቶችን፣ ሙዘቀኞችና ታዳጊ የብሔር ካድሬዎችን የጨበጠው ኢህዴግ፣ የእስፖርት ቤተሰቦችን ሊያስተዛዝል ነው።***ምን አባቱ የተናቀ ሠፈር በዲያስፖራ ይከበባል አሉ! መቼም በስታዲየም መሮጥና በፖለቲካ መሮጥ አንድ ነው። ቢያንስ ፓርላማ ገብቶ ሥቆ ማሳቅ ያቅተዋል? ። በእንግሊዘኛ ከአቶ መለስ አያንስም! ለነገሩ ልጆቹም አማርኛ አይችሉም በእንግሊዘኛ ይረዱታል መውለድ ጉዱ!? በፈገግታ ከአቶ ኅይለመልስ አይተናነስም!። ሰውዬው በፈገግታ ነው የተመረቁት ? በሚያናድድ የሀገር ጉዳይ “ኢሳያስ ኦፌወርቄ አሸባሪ! የቀጠናው አተራማሽ! ወንበዴ! ብለው ሲደነፉ ጠረጴዛ ሲነርቱ ከርመው እቤቱ ሄጄ ጸሎት አድርጌ እግሩ ላይ ወድቄም ቢሆን እደራደራለሁ አሉ። እሪ በይ ወያኔ አለ የእኛ ሀገረ ሰብ …

    ***ሻለቃው ፻ ዓለቃውን ከሀገር አቋራጭ (ማራቶን)በሥልጣን መተካካት የዱላ ቅብብል የብሔር ማሟያ ሆኖ በፈግታው ሊያናድደን ነው?”

    *ኢህአዴግን(ራዕይና ሌጋሲውን)የሚያውቀው የለም።ኢትዮጵያም አውሮፕላን እንዳላት ደሪምላነርም ገዝተን ለምነን እንደምንበላ ‘ደሮነርም’ የሚሠራ አትራፊ የመከላከያ ኅይል እንዳለን የሚመሠክረውና የሚያውቀው ያው የፓርላማ አባል፣አርቲስቱ፣ የኤምባሲ ካድሬና ቤተሰቦች ተሰብስበው ቡና በማፍላትና በመጨፈር ነው። ስለዚህ ፖለቲካን ከእስፖርት ጋር እናደባልቀው፣ ውሃና መብራት፣ የሌለው፣ ረዕይና ወኔ አልባ ትውልድ! “ወንድማችን በእውቀቱ ሥዩም ልጁ ከሱዳን የላከለትን ደብዳቤ ለሕዝብ እንዳነበበው “ሱዳን መብራት ጠፋ የሚባለው ሳሎን ጠፍቶ መኝታቤት ሲበራ ነው” ኢትዮጵያ መብራት ተቋረጠ የሚባለው ህዝብ በፈረቃ ለ፫ አብርቶ ጅቡቲ ሌሊቱን ስትጠቀም ነው። መብራት ጠፋ የሚባለው ግን የተቦካው ሊጥ ተበላሽቶ ሲደፋ ብቻ ነው። ቲማቲም ፲፭ብር ኪሎውን የሚገዛ የወያኔ ትውልድ ፣፷ሺህ ተመልካች የሚይዝ፣ አፉን ከፍቶ፣ ቂጡን የሚያደነዝዝበት፣ እንዳያነብ፣ እንዳይፅፍ፣ እንዳይጠይቅ፣ የሚጀዝብበትና የሚሞላፈጥበት፣ እስታዲየም ሊገነባለት ነው። ታዲያ ኅይሌ ፕሬዘዳንት ካልሆነ እንዲህ ያለ የውድቀት ዕድገት ይገኛልን? የፖለቲካውን ምሕዳር መስፋት በእስታዲየም ስፋት ቀሸበው ይሉሃል ይህ ነው።ጭንቅላታቸው ጠቧልን?”የጎበዝ አለቃ ሁሉ ፖለቲከኛ ነኝ የሚልበት ሀገር ነው።የሀገሪቱ ፖለቲካ የህይወት መስዋዕትትን ጨምሮ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ያለስም ስም የሚያሰጥ አስቸጋሪ ውጣውረድ ያለበት በመሆኑ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ሊቀ/ጠ በየነ ጴጥሮስ ጠቆሙት።

    **(አብዮታዊ ዴሞክራሲያውዊና ኦሎምፒካዊት ኢትዮጵያ !) ሆነችልህ በለው!*

    ኅይሌ ገብረስላሴ ስንት ታላላቅ ሰዎችን ጨብጧል ሲሸነፍ የሚስቅ ተብሏል፡ በሀገር ውስጥም በሠራው አድርባይነትም ተጨብጧል!። ምንም ቢሆን ከ፻ ዓለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በምን ያንሳል? ዶ/ር ነው። ሻለቃ ነው። ቢያንስ ደብዳቤ ተቀብሎ ደብዳቤ ላይ ፈርሞ፣ ተነስቶ ጨብጦ ተቀምጦ ስቆ በፈገግታው ሀገራችንን ማንነት ከፍ ያደርግልናል።ኢትዮጵያ አውሮፕላን አላትን? ሲሉ ለመሆኑ ሀይሌገብረስላሴ ለሩጫ ይህንን ሁሉ ሀገር የሄደው እየሮጠ ነው ወይንስ በበቅሎ ነበር ብለው ነው? እኛስ የተጠቀለሉ መሪ አፍሪካን የወከሉት በባዶ እግራቸው ሄደው ነበር? ወይ ንቀት ብታምኑም ባታምኑም ኢህአዴግ ተደፍሯል! ተንቋል!ተዋርዷል! አትሌት ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ ሳይሆን ምን ይዞ ገባ?ምን አይነት ለውጥ ለማምጣት ነው? “አጃቢ” የመሆን አደጋ እንዳለውም አቶ ገብሩ አስራት ልምዳቸውን አካፍለውታል። አብዮት ልጇን ትበላለች መለት ይህ አደለም! ማን ይናገር? የደረሰበት !ማን ያርዳ? የገደለ ልክ እንደ ወያኔ ማለት ነው!ማን ይምከር የታዘበ በለው!

    **በዓለም ኢህአዴግ ለመኖሩና ሥልጣን ለሠፊው ሆዳም ህዝብ እንደሚሰጥ ከመድብለ ፓርቲ የተዳበለ ወንበር በ፪ጠ/ሚኒ በ፩ ምጠ/ሚ በ፪ም/ጠ ሚኒ መሳይ (በደቦ)የምትመራ ፓርቲ ለፈገግታ እንግደህ ኅይሌን ትጨምርና ይህ ሰው ይገደል ሲሉት ይፈርም ፣ ይህ ሰው ምህረት ያግኝና ይፈታ ሲሉት ሮጦ ይጠፋል። ግን በአበባ ተከቦ በተቀመጠ ቁጥር መናፈሻው(እሪዞርትቱ) ያለ መስሎት በቁምጣ እንዳይቀመጥና እንግዳ እንዳይመጣ! ፻ አለቃ ግራማ ወ/ጊዮርጊስ እንዲሁ የሹመት ደብዳቤ ለአመጣው ሁሉ አምባሳደር ሁሉ “እስቲ ትኩስ የማር ጠጅ ይላሉ አሉ።”
    ኅይሌ ገብረስላሴ በገንዘብ ከሼክ አላሙዲን አይተናነስም! እንዲያውም በአንድ ደምፅ “እኛ ኢንቨስተሮች ሥራ ሥለምንከፍት ስንሳሳትም ዝም በሉን ብታዩንም እንዳላያችሁ ሁኑ እንስራባችሁ አደለም ያሉት !!”በአርግጥ በኢንቨስትመንት ሥም ቦታ አጥሮ ያለ ግብር መቆየትስ ባህሪያቸው አደለምን!”አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክብር እንግድነት እንዲገኝ ጥያቄዎችን ባለመቀበል በአንፃሩ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ ማህበራት ላይ በክብር እንግድነትና በንግግር አድራጊነት መገኘቱ የሚያመለክተው የኃይሌ የፖለቲካ ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ ይሁንታ ያገኘ አስመስሎበታል”በማለት የሚገረሙት የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሀብታሙ አያሌው ሲሆኑ ሌላው ከሩጫ በኋላ ባንዲራ ይዞ ይሮጣል ፕሬዘዳንቱም ሲሆኑ ሁልጊዜ በመኪና ላይ ያውለበልባል ለነገሩ ትርጉሙን ቢያውቁት ባትሉኝ እንጂ!… ታላቁ እሩጫ የአጃቢ እሩጫ ይሆን ይሆን?
    እንግዲያውስ መለስ ከቻይና(የቡድን) ቤተሰባዊ ብሔር ተኮር አመራር ፣ ኅይለማርያም ከህንድ(የኀብርት)(የደቦ)ከፊት ያላችሁ ሁሉ መሪ ናችሁ አመራር ፣ ኅያሌ ገ/ስላሴ ከኦሎምፒክ( በይቻላል)(በይሆናል) እየመከረ ወይ ከመካከለኛ ወይ ከመጨረሻ አጥር ግቢ ውጭ እንሠለፋለን ! እግዝኦ…የቡድን የኅብረትና ኦሎምፒክ አመራር ያለህ…ኅይለመንግስቱመለሰማርያምገብረስላሴ…..በለው!!በቸር ይግጠመን ከሀገረ ከናዳ

    Reply

Leave a Reply to በለው ! Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm
  • አሜሪካ ሁለገብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት – አንቶኒ ብሊንከን March 15, 2023 08:52 am
  • ጠቅላላ ጉባኤን ያስተጓጎሉ ላይ ክስ እንዲመሰረት ምርጫ ቦርድ ጠየቀ March 15, 2023 08:48 am
  • በኦሮሚያ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ ገጠማ ያለ አግባብ ለአንድ ግለሰብ ተሰጥቷል ተባለ March 15, 2023 01:43 am
  • ምርጫ ለተወዳደሩና እውቅና ላላቸው ፓርቲዎችመንግሥት 106 ሚሊዮን ብር መደበ March 15, 2023 12:52 am
  • አረመኔና Transgender “ደፋር ሴቶች” ተብለው በተሸለሙበት መዓዛም ተሸለመች  March 10, 2023 10:45 pm
  • ዓድዋ 127 በዓድዋ ከተማ March 2, 2023 09:56 am
  • በምኒሊክ አደባባይ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ምን ተፈጠረ? March 2, 2023 09:43 am
  • አውቶቡሶቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብር ነው የተገዙት February 24, 2023 10:44 am
  • በአውቶቡሶቹ ግዢ ቢያንስ 1 ቢሊዮን ብር ተሰርቋል፤ ዶ/ር ዐቢይ አስቸኳይ ማብራሪያ ጠይቀዋል February 24, 2023 08:39 am
  • የውርደት ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ! February 24, 2023 08:19 am
  • “አማርኛን የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ በማድረግ የኢትዮጵያ ብቻ ሣይኾን የአፍሪካም ማድረግ ይገባል” ራህማቶ ኪታ February 21, 2023 10:09 am
  • አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ እንዲሆን የቀረበ ጥሪ February 21, 2023 10:01 am
  • በገፊና ጎታች ሤራ ከመፈንቅለ ሲኖዶስ እስከ መፈንቅለ መንግሥት February 17, 2023 06:39 pm
  • ኦነግ ሸኔ አሸባሪነቱ ሳይነሳለት በሽመልስ የሰላምና የእርቅ ጥሪ “በክብር” ቀረበለት February 17, 2023 12:35 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule