ህወሃት/ኢህአዴግን በየቦታው እየናጠው ያለው ተቃውሞ በኢትዮጵያ የገንዘብ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ችግሩ ባንኮች ላይ የገንዘብ እጥረት እንደሚያስከትልና ባንኮችን ሽብር ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው፤ ደምበኞች ስለገንዘባቸው የሚጠነቀቁበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ህዝባዊ ቁጣ ያሰጋቸው የአገዛዙ ተጠቃሚዎች የውጭ ምንዛሬ እየሰበሰቡ ሲሆን በፍርሃቻ ንብረት በማስያዝ ከባንክ የሚበደሩት ክፍሎች ቁጥርም በርካታ ሆኗል።
ከ10 ወራት በላይ ያስቆጠረውና ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ቀን የቆረጠው የኦሮሞ ህዝባዊ እምቢተኛነት (#OromoProtests) ያስከተለውን መንኮታኮት ህወሃት በይፋ ባያሳውቅም በግብር አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ፣ በጠቅላላ የውጭና የውስጥ ንግድ የገቢ ስርዓቱን እንዳናጋው ከፋይናንስ ተቋማት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ እንግዲህ አሁን እየተሰማ ያለው ባንኮችን የመተርከክ (hack የማድረግ) አደጋ ሳያካትት ነው።
ሕዝባዊ እምቢተኛነቱ አድማሱን አስፍቶ መጓዙ ከክልል እስከ ማዕከላዊው አገዛዝ ድረስ የኢኮኖሚ ጫና ማሳደሩ እየተነገረ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ ተቃውሞውን “ሥርዓቱ በቃን፤ መንግሥት ፈርሷል” በማለት የሚቀላቀሉት የህብረተሰብ ክፍሎች የራሳቸውን የጎበዝ አለቃ አስተዳደር አዋቅረው መተዳደር መጀመራቸው የግብር ገቢውን አሽመድምዶታል፤ አድቅቆታል። ህወሃት አሁን በደረሰበት የቁጣ ማዕበል ደፍቆት ጉዳቱን የሚያጣጥም ስሜት ባይኖረውም ወገቡ ደቅቋል የሚሉ በርካታ ናቸው።
ይህ የራስን አስተዳደር አዋቅሮ የመተዳደር ውሳኔ ቆዳውን እያሰፋ ሲሆን አሁን አገዛዙ የሸፋፈነው የኢኮኖሚ መንኮታኮት፣ በቅርቡ ሊደበቅ በማይችል ሁኔታ ራሱን እንደሚገልጽ ባለሙያዎች ከወዲሁ ተንብየዋል። የመንግስት ግምጃ ቤት መረጃ አቀባዮቹን ጠቅሶ የገለጸው የጎልጉል የአዲስ አበባ መረጃ አቀባይ፣ በከፍተኛ ደረጃ ብር ከባንክ የሚያወጡ መበራከታቸው ተጨማሪ ብር ለማሳተምና ገበያ ውስጥ ለማስገባት ዕቅድ እንዳለ እና አሁን አገሪቱ የምትንከላወሰው በድርቅ ስም ከተገኘ የውጭ ምንዛሬ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
በየቦታው የተነሱትን ተቃውሞዎች ለመቆጣጠር የሚመደበው በጀት፣ የፖሊስና ወታደር የውሎ አበል፣ ሰልፍ ለመበተን የሚፈሰው ገንዘብ፣ … ከወጪ በስተቀር ምንም ገቢ የማያስገኝ መሆኑ እየደረሰ ካለው የኢኮኖሚ ድቀት ጋር ተዳምሮ ችግሩን አወሳስቦታ፡፡ አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ምርት በአብዛኛው ከኦሮሚያ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያ 10 ወራትን ያስቆጠረው የኦሮሞ ተቃውሞ (#OromoProtests) እጅግ ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፈለ ቢሆንም የህወሃትን አከርካሪ እየገዘገዘው እንደሆነ ራሳቸው በአገዛዙ ውስጥ ያሉ እያመኑበት የመጡት እውነታ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማራ የተነሳው ተጋድሎና (#AmharaResistance) የቤት ውስጥ አድማ የንግድ እንቅስቃሴን ከመግታት አኳያ የግብር አሰባሰብን በማዳከም የህወሃትን የገንዘብ ቋት እያደረቀው እንደሆነ ከቀናት በፊት በዘገብነው ዜና ላይ በስፋት ተመልክቷል፡፡
ከእነዚህ ተቃውሞዎች ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚካሄደው የአገሪቱን የኢንተርኔት መረብ የመተርከኩ (hack የማድረጉ) ተግባር ህወሃትን በተደጋጋሚ ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎታል፡፡ በተለይ ከወራት በፊት በኦሮሞ ተቃውሞ አመራሮች የተካሄዱት የመተርከክ ሥራዎች ህወሃት በዘርፉ በቂ ባለሙያ የሌለው መሆኑን ያጋለጠ ሆኗል፡፡ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች መ/ቤቶች በየቦታው በተተረከኩ ጊዜ ሁኔታውን ለመከላከል ኤሌክትሪክ ከቆጣሪው የማጥፋት ዓይነት ውሳኔ መወሰዱ ህወሃት ኢንሳ፤ የሳይበር ወንጀል መከላከል፤ … እያለ የሚያወራው ሁሉ ባዶ መሆኑን በይፋ ያሳየ ነበር፡፡ በወቅቱ የተከሰተውን ቀዳዳ ለመድፈንም በይፋ ያልተነገረ በርካታ ሚሊዮኖችን ወጪ እንዳስወጣው በተለያዩ ጊዜያት ለኢህአዴግ ምክርቤት (ባለ መቶ በመቶው ፓርላማ) በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈ ሰሞኑን በቴሌ ላይ የደረሰው የመተርከክ ሥራ በአንዳንዶች በተሰጠው ግምት መሠረት ቢያንስ እስከ100 ሚሊዮን ብር ኪሣራን አስከትሏል ተብሏል፡፡ በተደጋጋሚ የቴሌን ጓዳ የተረከከው ተግባር ሰዎች ያሻቸው አገር የፈለጉትን ያህል ሰዓት ያለአንዳች ክፍያ ስልክ መደወል እንዲችሉ፤ የስልካቸው ባትሪ ያልቃል ብለው ካልተጨነቁ በስተቀር ስልካቸውን ደውለው ከፍተው ቢተዉት አንዳች ኪሣራ በማያስከትል ሁኔታ “የወተት ላም፤ አንሸጥም፤ እናልበዋለን” የሚባለውን “የቀለጠውን ሰፈር” ባዶውን አስቀርተውታል፡፡ ዛሬም (ነሐሴ 24፤2008) እንዲሁ “ግድግዳው ተቀዶ” ስልክ “በነጻ እየተደወለ ነው፤ ወትሮ የማትጠቀሙበትን ሲም በመጠቀም ዘመድ አዝማዳችሁን ጠይቁበት” በማለት “በሩን የበረገዱት ታጋዮች” መልዕክት ማስተላለፋቸው ከ#OromoProtests አመራሮች ተነግሯል፡፡
ከዚሁ ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ተቃውሞ (#OromoProtests) አስተባባሪዎች “ከጳጉሜ አንድ እስከ መስከረም ሁለት 2009 ዓ.ም የሚቆይ በስርዓቱ ኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ይደረጋል” በማለት ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል። “ዓላማውም የስርዓቱን ኢኮኖሚ በመምታት የጭቆና አቅሙን ማንኮታኮት ይሆናል” በሚል ዓላማ ላይ የተመሠረተው ይህ እንቅስቃሴ እስካሁን ከተካሄደው ጋር ተዳምሮ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ጫና ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ ተገምቷል።
የቴሌን መረብ በመተርከክ ያለገደብ በነጻ ስልክ ለማስደወል የበቁት የተቃውሞው አካሂያጆች ወደ ባንኮች ከዞሩ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ እስካሁን ከደረሰው እጅግ የከፋ ይሆናል፡፡ ይህንኑ ዓይነት እንደምታ ያለው ሃሳብ በተቃውሞው አራማጆች ሲሰነዘር ሰሞኑን መሰማቱ በኅብረተሰቡ ላይ ፍርሃት መጫሩን አንዳንድ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ፣ ባንኮች ከወትሮው በተለየ ሥራ በዝቶባቸዋል። ከህወሃት የአታላይነትና የሌባ ዓይነደረቅነት አኳያ ደምበኞች የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው በተለያዩ ቦታዎች እየታየ ነው፡፡
እንደተባለው የባንኮች መረብ የሚተረከክ ከሆነ ባንኮች ያላቸውን ተቀማጭ ባጭር ጊዜ ውስጥ ስለሚሟጠጥ የሚደርሰውን ኪሣራ ለመከላከል የባንክ ተጠቃሚዎች ገንዘባቸውን በእጃቸው ከማድረግ ጀምሮ ያስቀመጡትን ገንዘብ የሚከላከሉበትን መፍትሔ ካሁኑ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ባንኮች ከደንበኞቻቸው የሚሰበስቡትን ሁሉ በእጃቸው ላይ የማያስቀምጡ በመሆናቸው ድንገተኛ የገንዘብ ዕጥረት ውስጥ ስለሚገቡ ይህም ወደ ገንዘብ ቀውስ/ሽብር ውስጥ በቀጥታ ስለሚከታቸው ነው፡፡
የህወሃት አገዛዝ ከየቦታው እየተናጠ ባለበት ባሁኑ ወቅት ራሱ አገዛዙ ያመነው 20.6 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አገሪቱ ላይ ተጭኖባት እያለ የባንኮች መረብ ከተተረከከ (hack ከተደረገ) የገንዘቡ ቋት በየቦታው ይቀደዳል፤ ይህ ደግሞ “የባንክ ሽብር” ይፈጥራል፡፡ ባንኮች በሽብር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ተቀማጭ ጥሬ ገንዘባቸው ይሟጠጣል፤ ይህንን ቀውስ ለማስተካከል ለቀናት ወይም ለሳምንታት ይዘጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ እኤአ በመስከረም 2007ዓም በእንግሊዝ በሚገኝ ባንክ ላይ በደረሰ “የባንክ ሽብር” ምክንያት ደምበኞች ለረጅም ሰልፍ ከመጋለጥ አልፈው በአንድ ቀን ብቻ 1ቢሊዮን ፓውንድ ጥሬ ብር ከባንኩ በማውጣቸው ባንኩ ለመዘጋት ደርሶ ነበር፡፡ በቀጣይም የእንግሊዝ መንግሥት ለደምበኞቹ ማረጋገጫ ዋስትና ቢሰጥም ባንኩ እስኪረጋጋ ለተወሰኑ ቀናት ተዘግቶ ነበር፡፡
ከዚህ አንጻር እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ በመዝረፍ ላይ ኅልውናውን የመሠረተ አካል በትርከካው ምክንያት በሚደርሰው ኪሣራ የዜጎችን የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ “አላውቅም” ብሎ የማይክድበት ምክንያት እንደማይኖር ከረሃብተኛ ላይ እየቀማ ራሱን ያበለጸገበት ታሪኩ ይመሰክራል፡፡
በመሆኑም በአገር ውስጥ አገዛዙን በሁሉም መስክ እያናወጠ ካለው ተቃውሞና በምዕራባውያን ባንኮች ከደረሰው ልምምድ በመነሳት በአገሪቱ የባንክ አገልግሎት ላይ ቀውስ ከመከሰቱና ባንኮች ሽብር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ዜጎች በየባንኩ ባላቸው ተቀማጭ ገንዘብ ላይ መውሰድ የሚገባቸውን እርምጃ ሳይቀደሙ እንዲቀድሙ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ይመክራሉ፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply