• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ጋምቤላ ከውስጥም ከውጭም የምትለበለብ ለም ምድር!!

April 22, 2016 07:21 am by Editor 3 Comments

ጋምቤላ ውብ ምድር፣ ጋምቤላ የተፈጥሮ ባለጸጋ፣ ጋምቤላ ድንግል መሬት፤ ጋምቤላ  ያላትን የማትበላ፣ የተረገሙ የሚመሯት፣ የደም መሬት፣ የዕንባ ምድር፤ ጋምቤላ የምትዘረፍ ምድር፣ ግፍ የተትረፈረፈባት የግዞት መሬት፣ የደም አውድ፣ ከውስጥም ከውጭም የምትለበለብ “አካላችን”፤ ጋምቤላ ያላቸውን የማይበሉ ህዝቦች፣ ባላቸው ሃብት የተነሳ የግፍ መከራ የሚጋቱ ምስኪን ወገኖች የሰፈሩባት ገነተ ሲኦል፤ ተቆርቋሪ አልባ “ኢትዮጵያኖች” ፍትህን ስትናፍቁ  ከሁልጊዜውም በላይ በከፋ ሃዘን ተመታችሁ!!

አዎ፣ የጎልጉል ዝግጅት ክፍልን ጨምሮ ዜጎችን ያቃጠለው ዜና ባልተለመደ መልኩ የተበሰረው በህወሃት ንብረት ራዲዮ ፋና አማካይነት ነው። ባለፈው አርብ የተሰማው ክፉ ዜና እነዚያ ለቱሪዝም ማስታወቂያነት ብቻ የሚፈለጉት ወገኖቻችን በድንገት ስለመጨፍጨፋቸው ነው። ከ240 በላይ እናቶችና ህጻናት በጅምላ ተገደሉ። ከ100 በላይ ህጻናት ታገቱ። ይህ ሁሉ ሲሆን “የሰላም አስከባሪ ሃይል” እያሰማራ ላገሪቱ የዘላለም ጠላት፣ ለራሱ የፖለቲካና የህልውና ማስጠበቂያ ካርድ የሚቆርጠው ህወሃት የሚመራው ሰራዊት መልስ ሊሰጥ አልቻለም። በወቅቱ ምላሽ አለመሰጠቱ በራሳቸው አንደበት የተረጋገጠ መሆኑ ደግሞ ሃዘኑ ከሕዝብ አንጀት ውስጥ ሳይወጣ እንዲቀበር አደረገው።

የሙርሌና የዴንካ የፖለቲካ “ፍቅር”

david yau yau
ዴቪድ ያው ያው

ከደቡብ ሱዳን ጎሣዎች ሙርሌዎች አናሳ ቁጥር ያላቸው ናቸው – በብዛታቸው በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክልል የሚገኙት ሙርሌዎች እኤአ በ2010 በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ አንድም የፓርላማ መቀመጫ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ በዚህ የተቆጡት የጎሣው ተወላጅ ጄኔራል ዴቪድ ያው ያው በሳልቫ ኪር መንግሥት ላይ ብረት አነሱ፡፡ በቀጣይም የአመጻቸው ዋና ምክንያት በጎሣቸው ላይ የደረሰው አድልዎ፣ መገለልና የክልላቸው አለማደግ መሆኑን በመናገር የትግሉን ስፋት ለማሳየት ሞከሩ፡፡ በዓመቱ ሳልቫ ኪር ለጄኔራል ያው ያው እና የጦር አዛዦቻቸው ያደረጉትን ምህረት ተቀብለው ወደ ጦር ካምፕ ገቡ። ብዙም ሳይቆዩ ያው ያው እንደገና በማመጽ ወደ ትጥቅ ትግል ተመልሰው ከኪር ኃይሎች ጋር ለሁለት ዓመታት ጦርነት ገጠሙ፡፡ በ2014 በሚያዚያ ወር በተደረገው የድጋሚ ስምምነት የስነመለኮት ትምህርት እንደወሰዱ የሚነገርላቸው ጄኔራል ያው ያው የክልላቸው አስተዳዳሪ ሆኑ፡፡ በማስከተልም በያዝነው ዓመት የጥር ወር ላይ የጄኔራሉ “የኮብራ አንጃ” የሳልቫ ኪርን ፓርቲ መቀላቀሉን ይፋ አደረገ፤ የአማጺ ቡድናቸው በሳልቫ ኪር ለመመራት መወሰኑም አብሮ ተነገረ፤ ዴንካው ሳልቫ ኪር ሙርሌን ከነጄኔራሉ ጠቀለሉ፡፡ የሳልቫ ኪር ዴንካ እና የያው ያው ሙርሌ የፖለቲካ “ፍቅር” ከዚህ በላይ እንደሚዘልቅ የሚናገሩ ቢኖሩም ሁለቱም ኑዌርን እና ሬክ ማቻርን የጋራ ጠላታቸው በማድረጋቸው ነው እንጂ ለመጠፋፋት በዓይነቁራኛ የሚተያዩ ናቸው የሚሉም አሉ፡፡

Machar-VP
ሬክ ማቻር

ያለፈውን የደቡብ ሱዳን ምርጫ ተከትሎ የተነሳው መተላለቅ ዴንካዎችና ኑዌሮች ለከፍተኛ ዕልቂት ዳርጓዋል። የሳልቫ ኪር ተቀናቃኝ የሆኑትና “ሽኮኮ” አቋም አላቸው የሚባሉት ዶ/ር ሬክ ማቻር የኑዌር ጎሳ አባል ናቸው። በዚህ ሒሳብ መሠረት የሁለቱ መሪዎች መቧቀስ ከኋላቸው “አጋር” ጎሳዎቻቸውን እንደሚያሰልፍ እሙን ነው። ሙርሌዎች እንደ ዴንካዎች በአብዛኛው በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ሲሆን ኑዌሮች ግን በደቡብ ሱዳንም በኢትዮጵያም ውስጥ አሉ። የጋምቤላ ሊቀመንበር ጋት ሉዋክ የኑዌር ተወላጅ ናችው።

በደቡብ ሱዳን የብሔራዊ አንድነት የሽግግር መንግሥት (TGoNU) የሚቋቋምበት ሳምንት ላይ ሙርሌዎች የኑዌር ጎሳዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘልቀው መጨፍጨፋቸው ፖለቲካዊ እንደምታ አለው ተብሎ ይታመናል። ሰኞ ጁባ ገብተው በብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ምስረታ ላይ ተሳትፏቸውን ይጀምራሉ ተብለው የሚጠበቁት ማቻር ይህ ትንታኔ ለኅትመት እስከበቃበት ድረስ ገና አልገቡም፤ የወደፊቱም ሁኔታ አወዛጋቢ ሆኗል፡፡ የሳልቫ ኪር አስተዳደር ማቻርን በርካታ የጦር መሣሪያዎችን ይዘው ወደ ጁባ ለመምጣት አይችሉም በማለት ዕገዳ አድርጓል፡፡ የኪር መንግሥት አማጺውን የማቻር ኃይል ከቀላል መሣሪያና ጥይቶች ጀምሮ እስከ ጸረ ታንክና አርፒጂ ድረስ ታጥቀው ወደ ጁባ ለመምጣት ያስባሉ እያለ ይከስሳል፡፡ ማቻር በበኩላቸው ከመጠነኛ የግል ሽጉጥ በስተቀር እሳቸውም ሆነ አጃቢዎቻቸው ከባድ መሣሪያ እንዳልያዙ ለአልጃዚራ ተናግረዋል፤ ማኒፌስቶውንም አሳይተዋል፡፡ ይህ እሰጥ አገባ አዲስ አበባ ላይ በህወሃት አደራዳሪነት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡

manifesto
የመሣሪያ ዝርዝር የሚያመለክትው ማኒፌስቶ

በደቡብ ሱዳን ከንግድ ጀምሮ እስከ ፖለቲካ አመራርነት ያላቸውን ሚና ከፍ አድርገው ጮቤ የሚረግጡት ህወሃቶች የሬክ ማቻር ወገነተኛ መሆናቸው በተደጋጋሚ የታየና በሰላም ድርድሩ ወቅት የተመሰከረ ነው። ህወሃቶች ማቻርን በመደገፍ የሚያካሂዱት የፖለቲካ ሸርተቴ ሳልቫ ኪር በተለያዩ ጊዜያት ፍንጭ ቢሰጡበትም ሰፊ ቅሬታ እንዳለባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ህወሃት አዲስ አበባ ላይ ሁለቱን ወገኖች “አደራድራለሁ” እያለ ስብሰባ በሚጠራበት ወቅት ኪር አልመጣም እስከማለት መድረሳቸው በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡ እንደውም ሳልቫ ኪር የ“ሰላሙን” ስምምነት የፈረሙት ተገድደው እንደሆነ ስሞታ አለ። አንዳንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት ህወሃት ሳልቫ ኪርን የማስወገድ አጀንዳ እንዳለው የሳልቫ ኪር ሃይሎች ከጥርጣሬ ባለፈ መልኩ ደርሰውበታል። ለዚህም ይመስላል ሙርሌዎች ባለፈው አርብ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲያካሂዱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሽቀዳደሞ “የደቡብ ሱዳንም ሆነ አማጺው የሬክ ማቻር ቡድን ከጭፍጨፋው ጋር ግንኙነት የላቸውም” ብሎ መግለጫ ያወጣው። ለወትሮው ዜጎች ሲታረዱና ህይወታቸው ሲያልፍ “ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ላጣራ” የሚለው ህወሃት የወገኖቻችን አስከሬን ሳይሰበሰብ፣ የደማቸው እንፋሎት ሳይደርቅ “ሁለቱም ወገኖች የሉበትም” ማለቱ ከትዝብት የዘለለ አድሮ እርቃኑን የሚወጣ ቁማር እንዳለ ያሳያል የሚሉ በዝተዋል።

ደቡብ ሱዳን እና የህወሃት የፖለቲካ ቁማር

በጎረቤት አገራት ዕርዳታ ሊደገፍ የሚችል የተቃውሞ እንቅስቃሴን አስቀድሞ በመገመትና ሳይቀድሙት በመቅደም የሚታወቀው ህወሃት፤ ደቡብ ሱዳን ገና እንደ አገር ከመመስረቷ በፊት መሠረታዊ የመንግሥት ዘርፎችን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳንን የደኅንነትን፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የፖሊሰን አደረጃጀት በሚፈልገው መልኩ ያዋቀረው ህወሃት ሳልቫ ኪር ወደ ህወሃት ተቃዋሚዎች ፊታቸውን ከማዞራቸው በፊት ነበር በወዳጅነት የያዛቸው፡፡ በተለይ ከአልበሽር አገዛዝ ጋር ሲፋለም ለነበረው የጆን ጋራንግ ሠራዊት የኮ/ሎ መንግሥቱ አገዛዝ ድጋፍና ከለላ ሲያደርግ መኖሩ ለኢትዮጵያ ባለውለታ እንደሚያደርገው በመታመኑ ይመስላል ህወሃት አስቀድሞ የቤት ሥራውን የሠራው፡፡

የህወሃትና የሳልቫ ኪር “ፍቅር” እንደታሰበው አልዘለቀም፡፡ ገና ከመመስረቷ በተለያዩ የአስተዳደራዊ አረንቋ ውስጥ የገባችው ደቡብ ሱዳን ምርጫን ተከትሎ የተነሳው ብጥብጥ አገሪቱን ወደ አልታሰበ አቅጣጫ ወሰዳት፡፡ የህወሃት በደቡብ ሱዳን አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሚና መኖር ያልተዋጠላቸው ሳልቫ ኪር ከተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር ጋር ወደ Ethiopia South Sudanእርስበርስ ጦርነት ሲገቡ ፊታቸውን ያዞሩበት ህወሃት በስዩም መስፍን እና ቴድሮስ አድሃኖም ተወክሎ መዳፉ ሥር ሊያስገባቸው ሲጥር በተደጋጋሚ ተመለከቱት፡፡ ሳልቫ ኪር ይህንን ለሬክ ማቻር ያጋደለ፤ ወገነተኛ፤ … እያሉ የጠሩትን የሰላም ድርድር አልቀበልም፤ አልፈርምም እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡

በአንጻሩ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ወገን ለይተው ኑዌርና ዴንካ የጎሣ ጦርነት ውስጥ በገቡበት ወቅት ሬክ ማቻር በህወሃት ፈቃጅነት ወደ ኢትዮጵያ እንደልባቸው ሲገቡና ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ጋምቤላን ዋንኛ የመተላለፊያና የማረፊያ “ካምፕ” አድርገው ተጠቅመዋል፡፡ በጋምቤላ መስተዳደር ፈቃድ እና ድጋፍ ድንበር እያቋረጡ ያለ ምንም ችግር ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊትነት ኢህአዴግ በክልሉ ያሰማራቸው የኑዌር ተወላጅ ወታደሮች ከሳልቫ ኪር ዴንካዎች ጋር ሲፋለሙ ተሰውተዋል፤ ይህም ህወሃት አሻንጉሊት አገዛዝ በጁባ ለማስቀመጥ “በሰላም ድርድር” ስም ያካሄደው የፖለቲካ ቁማር እንደሆነ አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቷል፡፡

ጉዳዩን በርጋታ የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት ህወሃት ሳልቫ ኪርን ባደባባይ ቢያወግዝ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የሳልቫ ኪር ኃይል አካባቢውን ምን ሊያደርገው እንደሚችል ያውቀዋል። በሽምቅ ውጊያም ሆነ በመሳሪያ የደረጁት ዴንካዎች ከሙርሌዎች ጋር ሆነው ቁጣቸውን ቢያቀጣጠሉት በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠረውን የሁለቱን አገሮች ሰላም አሳሳቢ ያደርገዋል። አሁን በውስጥ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል በተነሳበት ህዝባዊ ተቃውሞና ባጠቃላይ ባገሪቱ በተነሳበት የከረረ ጥላቻ ግራ የተጋባው ህወሃት ችግሩ እንዳይሰፋበት ፍርሃቻ ስላለው መለሳለስን መምረጡ አማራጭ ከማጣት የመነጨ እንደሆነ ይነገራል።

ከኢትዮ-ቲዩብ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የሰብአዊ መብት ተሙዋጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ እንዳሉት ሙርሌዎች ከተማ፣ ልዩ የመኖሪያ ቤት፣ የተማከለ አስተዳደርና ጦራቸው የሚሰፍርበት ካምፕ የሌላቸው ዘላኖች ናቸው። እነሱን አሳድዶ በየጫካው መጨረስ ከባድ ነው። በዚህም ላይ እነሱም በደንብ የታጠቁና ምላሽ የመስጠት አቅም አላቸው። ጉዳዩ በንግግር ከመያዝ ውጪ በጅምላ ቢጨፈጨፉ ጊዜ ጠብቆ ዋጋ የሚያስከፍል አደጋ ያስከትላል። እነርሱ ዘመናዊ መሳሪያ ባለቤት ሲሆኑ የእኛ ወገኖች ያላቸውንም የራስ መከላከያ ተነጥቀው ባዶ እጃቸውን ናቸው። አቶ ኦባንግ ወያኔዎች በጋምቤላ የነበረውን ሰራዊት ወደ ኦሮሚያ ማዛውሩ፣ የክልሉን የፖሊስ ሃይል ትጥቅ አስፈትቶ ለስልጠና ብሎ አዲስ አበባ ማዛወሩ ተጠያቂ ያደርገዋል ሲሉ ካባባቢው ያነጋገሯቸውን በመጥቀስ ተናግረዋል።Salva-Kiir

ያለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጭፍጨፋው ሲካሄድ ተደርጎ በነበረው የነፍስ አውጪኝ ትግል የተገደሉትን ከ60 በላይ ሙርሌዎችን የመከላከያ ሰራዊት እንደገደላቸው አድርጎ የተናገረው ህውሃት፣ የታገቱትን ህጻናት ሲያስመለስና ሌሎች ሽፍቶችን ጨምሮ ገድሎ አስከሬን ሊያሳይ እንደሚችል የሚናገሩት ክፍሎች፣ ህወሃት በሶማሊያ በጣልቃ ገብነትና ለዶላር ሲል፣ በደቡብ ሱዳን ለንግድና የወደፊት ትልም አስቀምጦ የሚፈጸመው ተግባርና የሚከተለው መንገድ ዞሮ አገርን ዋጋ የሚያስከፍል የወደፊት እዳ ነው ባይ ናቸው። ወደ ዋናው ጉዳይ በመመለስ ሲያበራሩ፣ በባህሪያቸው “በቀለኛ” የሚባሉት ኑዌሮች ለበቀል ከተነሱ ዴንካዎች ሙርሌዎችን ከማገዝ ወደኋላ እንደማይሉ ነው። ዴንካዎች ሙርሌዎችን ለማገዝ ከተነሱ የሬክ ማቻር ጎሳ የሆኑት ደቡብ ሱዳን ያሉት ኑዌሮች ዘሮቻቸን ተነኩ በሚል ዴንካዎች ላይ ይነሳሉ። ይህ ከሆነ ሳልቫ ኪርን አስልሎ ለመብላት የተዘረጋው የህወሃት ወጥመድ ብል ይበላዋል። ይልቁኑም ግጭቱ መልኩን ይቀይራል። በመለስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ከ400 በላይ ቤተሰቦቻቸውን በህወሃት ታጣቂዎች ያጡት የአኙዋክ ጎሳዎች ጉዳይም ጊዜ የሚጥብቅ ሌላው ፈንጂ ነው። ስትራቴጂካዊ መስሎ የቀረበው የህወሃት የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ቁማር ራሱኑ ጠልፎ ወደ ጉድጓድ የሚጥለው ድራማ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚፈራውም ከዚሁ አንጻር ነው፡፡

ሕዝብ ጥቃቱን እንዴት መመከት ተሳነው?

ይህ ቁልፍ ጥያቄ የሚቀርበው ህወሃት ለሚባለውና በተገንጣይ ስም አገር ለሚመራው የወንበዴ ቡድን ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በድንበር አካባቢ ችግር ሲከሰት ዜጎች አጣዳፊ ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ይታጠቁ ነበር። ቢያንስ የታሰበውን ያህል ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከሉ ነበር። ላለፉት 21 ዓመታት አገሪቱን በጠመንጃ እየመራ ያለው ተገንጣይ የወንበዴ ቡድን ራሳቸውንና ድንበራቸውን የሚከላከሉ ዜጎችን ትጥቅ አስፈትቶ ባዶ ቤት አስቀርቷቸዋል። ለህወሃት ሁሌም ትጥቅ የማይፈቱ፣ ይልቁንም የዱሮውን በዘመናዊ መሳሪያ የሚቀየርላቸው ራሱ “ዜጎቼ” ብሎ ለሚጠራቸው ክፍሎች ብቻ ናቸው። ሌሎችን ግን በራሱ ግብርና ምግባር እየመዘነ ስለማያምናቸው የራሳቸውን መከላከያና መጠበቂያ ራሱ በፈጠረው ስጋት ተነሳስቶ ይነጥቃቸዋል።

የኑዌር ወገኖቻችን ይህን አይነቱን መራር ሃዘን መመከት ያልቻሉት በሙርሌ ጎሳዎች ጥበብና ሃያልነት ተበልጠው ሳይሆን ባዶ እጅ በመሆናቸው ነው። ሙርሌዎች ባዶ ቤት አግኝተው ፈነጩ። ጨፈጨፉን። ልጆቻቸንን ዘረፉን። ቅምጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም እንዳሉት ነገም ቦታ ቀይሮ ላለመደገሙ ዋስትና የለም። ባዶ እጁን የቀረና በሚገዛው ገዢ የማይታመን ህዝብ ሁሌም ይጠቃልና “መጪውን ጊዜ ከመለስ ራዕይ ጋር ወደፊት” እያሉ ጥቃቱን መቀበል ግድ ነው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የሙት ሌጋሲ እያወደሰች እንድትኖር ስትገደድ፤ ቪኦኤ ያነጋገራቸው የማኅበረሰብ አጥኚ ዶ/ር ደረጀ ፈይሳ የሙርሌ ጎሳዎች ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም በደንብ ታጥቀዋል ሲሉ የተናገሩትን መጥቀስ አግባብ ይሆናል። ሰሚ ካለ!!

“መከላከያ” ያገሪቱን ድንበር ለማስከበር ከተመድ አበል ያስፈልገው ይሆን?

ማንም ዜጋ ለአገሩ የመከላከያ ሃይል ክብር፣ ውዳሴ፣ ድጋፍ፣ አለው። በእነርሱ ይመካል። ይተማመናል። በልቡ ማህተም አትሞ ያስቀምጣቸዋል። ህወሃት የፈጠረውና ለየስሙላ የተሰባጠረ ነው የሚባለው ሃይል ግን በነፍሰ ገዳዮችና በወንበዴዎች የሚታዘዝ ስለሆነ ወገኖቹን ይገድላል። በወገኖቹ ላይ ጉልበቱን የሚያበረታና መሳሪያ የሚወድር በመሆኑ ያለው ድጋፍ የተዥጎረጎረ ነው። በህወሃት ትእዛዝ ኦሮሚያ ሰላማዊ ዜጎችን ሲጨፈጭፍ የነበረው ነፍጠኛ፤ የኑዌር ብሔረሰብ አባላትን እንዴት መታደግ አቃተው? ለምን ዘገየ? አቶ ሃይለማርያም እንዳሉት ችግሩ የቆየ ነው። አካባቢው በጎሣዎች መካከል ከሚካሄድ ጥቃት የጸዳ ባለመሆኑ ቁጥሩ እንደዚህ አይብዛ እንጂ በተደጋጋሚ እናቶችና ህጻናት ተገድለዋል፤ ታፍነው ተወስደዋል። ነገሩ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ከሆነ በወቅቱ ለምን ምላሽ አልተሰጠም? ወይም የቅድሚያ ዝግጅት አልተደረገም? አንድ አገር እመራለሁ የሚል ሰው ስለዛሬ አደጋ ሲናገር “ከዚህ ቀደምም ነበር” ብሎ መርዶ መደርደር ለምን ያስፈልገዋል? ይልቁኑ እንዲህ ያለውን ትዕግስት ለምን ኦሮሚያ፣ አማራና አፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡብና መላው አገሪቱ ላይ ባሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አታደረጉትም የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ምላሹ ምን ይሆን? ችግሩ ያለው የድንበር አካባቢዎች በታጠቁ ሕዝባዊ ሚሊሺያ የሚጠበቁ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትጥቅ ማስፈታት፤ መሣሪያ መንጠቅ የኅልውና ጉዳይ ለሆነበት ህወሃት ሊዋጥለት የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ራሴን እከላከላለሁ ብሎ ያወጣው ፖሊሲ ጁባ ላይ ሊተውን ያሰበውን ድራማ ባልተጠበቀ ሁኔታ አኮላሸበት፡፡

የህወሃት የጦር አዛዦች አበል በዶላር ስለለመዱ የጋምቤላን ጉዳይ ለተባበሩት መንግስታት አቅርበው የህወሃት ሃይል “ሰላም ለማስከበር” በሚል ጉዳዩን ሊመለከተው ይሆን? በማኅበራዊ ገጾች ላይ ብዙ ተብሏል። ህዝብ የሚናገረው ስሜቱን ነው። ህዝብ በብዙ ነገር እየተቀየመ ነው። በብረት በሚጠበቀው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር እና የዶላር አበል በሚፈስበት አካባቢ ብቻ አይደለም። የኮንትራታችሁ ዘመን እስኪያበቃ ድረስ አገር ስትገዙ ከዝርፊያው ባሻገር የህዝብ ሰላም ማስጠበቅ ግዳጃችሁ ነውና ስራችሁን እየሰራችሁ ዝረፉ!!

ከዚህ ቀደም ግድያና እገታ ሲከናወን ለምን ዝም ተባለ? ችግሩ የኖረ ከሆነ ለምን ጥንቃቄ አልተወሰደም? አሁንስ ከ2000 በላይ ከብቶች ተዘረፈው ሲነዱ፣ ከ100 በላይ ህጻናት ሲታገቱ፣ ከ240 በላይ እናቶችና ህጻናት ሲጨፈጨፉ እንዴት ቀድሞ መከላከል አልተቻለም? የሚል ጥያቄ የማያነሱ ተላላኪዎች ያሉበት ፓርላማ አዘነ፣ ሃዘን አወጀ፣ ተከዘ፣ አጉረመረመ ቢባል ከንቱ ውዳሴ ከመሆን አያልፍም። ይልቁኑም የጋምቤላ ተፈናቃዮች ደም ይጮህባችኋል። ይልቁኑም የተፈናቀሉና ግፍ የተፈጸመባቸው ወገኖች እምባ ይፈጃችኋል። ምንም የማያውቁ ወገኖችን አስሮ እንደ ባርያ ፈንጋይ ዘመን ሲሰቃዩ ማየት ቀን ሲጎድል ያስጠይቃል … ሶስት ሺ ብር ለማይሞላ ደመወዝና ተራ የኮንዶሚኒየም የኮንትራት ቤት ስትሉ እስከመቼ ተሽጣችሁ ትኖሩ ይሁን? በተገንጣይ ስም አገር የሚመራው ህወሃት ባሰፋላችሁ ጥብቆ ውስጥ ሆናችሁ ብታስቡ እንኳን እንዴት ወገኖቻችሁን በባርነት ትቀይራላችሁ? እንዴት ወንድምና እህቶቻችሁን ታሳንሳላችሁ? የንጹሃን መቀበሪያ የሆነችው ጋምቤላ በውስጧ አፍና የያዘችው የደም እምቅ የፈነዳ ዕለት ሙቀቱን፣ ማቃጠሉንና መለብለቡን መቋቋም የሚችል መኖሩ ያጠራጥራል፡፡


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News Tagged With: Full Width Top, Middle Column

Reader Interactions

Comments

  1. zt says

    April 22, 2016 11:58 pm at 11:58 pm

    Ethiopia hagere mogni neshe telala: Lijochish aleku zarem begambella.

    Reply
  2. daachee maanii says

    April 24, 2016 06:04 pm at 6:04 pm

    በእዉነቱ በሀገራችን እየሆነ ያለዉ ነገር በፍፁም ግልፅ ያልሆነ፤በፍፁም ኢትዮጵያዊነትን ያጣ እና ከነበረን ኢትዮጵያዊ እሴት በተፃረረ ሂደት ሰጥመናል። በገሀድ አስከፊ ከሚባለዉ ቢሮክራስያዊ ስርአተ-ፖለቲካ ከሚያራምዱ ስነ-ምግባረብልሹ ቡድን እጅ የገባን አሳዛኝዜጎች/ ትዉልድ ሆነናል።በህልም ልፍለፋ የምንመራ ሆነናል የራሱን ቅዠት የማያይ፣ የማያይ፣የማያፍር ጀነሬሽን ሆነናል።ስም ካለዉ አገዛዝ (collony) ወደ ሀገርበቀሉ ክፉዉ የዉስጥ አገዛዝ ገባን ከሰበአዊነት ራቅን፤በግላዊ/ ቡድናት የስሜት ባሪያዎች ሆነን ሌሎች ኢትጵያዉያን ወንድሞች እህቶቻችንን እያጣን እነሆ ዛሬ ላይ ማንም እንደምፈነጭብን አየን። ይቀጥላልም።

    Reply
  3. ሸመልስይማም says

    April 25, 2016 01:42 pm at 1:42 pm

    አሁንህወሀትኢሀዴግሰራለይአይደሉምመከንያቱምለአለፈት25አመበመዝረፍናበማጭበርላይስለሆኑአነሱመንምአይመስላቸዉም

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የሲኖዶሱ ውዝግብ አካሄድና መጪው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ February 6, 2023 02:03 am
  • የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ተራዘመ፤ ተጠባቂው ዕርቅ ፍንጭ እያሳየ ነው February 3, 2023 05:17 pm
  • የብላቴ: የውጊያ ማርሽ ቀያሪ ሠራዊት መፍለቂያ ማዕከል February 3, 2023 10:06 am
  • በኢትዮጵያ 27 በመቶ የሚሆነው የአእምሮ በሽተኛ ነው ተባለ February 3, 2023 09:47 am
  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule