የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ሦስት የውጭ አገር ኩባንያዎች ከፍተኛ ችግር ታይቶባቸዋል፣ የፕሮጀክት አፈጻጸማቸውም ደካማ ነው በሚል የፌዴራል መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ ጠየቀ፡፡
የክልሉ መንግሥት በቅርቡ ለግብርና ሚኒስቴር፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ የህንድ ኩባንያዎች የሆኑትን ካሩቱሪንና ቬርደንታ ሃርቨስት፣ እንዲሁም የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ኩባንያ የሆነው ሳዑዲ ስታር የእርምትና የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቋል፡፡
በጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ኮት ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የክልሉ መንግሥት በነዋሪዎች አስተያየት ላይ ተመርኩዞ የራሱን ግምገማ አካሂዷል፡፡ ክልሉ ባካሄደው ግምገማ በተለይ እነዚህ ሦስት የውጭ አገር ኩባንያዎች ከፍተኛ ችግር እንደታየባቸውና የፕሮጀክት አፈጻጸማቸውም ደካማ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል ካሩቱሪ አግሮ ኢንዱስትሪ ተጠቃሽ ነው፡፡ ካሩቱሪ በ2000 ዓ.ም. በኑዌር ዞንና በኢታንግ ልዩ ወረዳ አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ወስዷል፡፡ ኩባንያው ከወሰደው መሬት ውስጥ 25 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ምንጣሮ አካሂዷል፡፡ ነገር ግን ከመነጠረው መሬት ታርሶ በዘር የተሸፈነው ስምንት ሺሕ ሔክታር መሬት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በ7,750 ሔክታር በቆሎ፣ በ250 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ አልምቷል፡፡ ነገር ግን ኩባንያው ሥራ ከጀመረ አምስት ዓመት ቢሆነውም እስካሁን ከሙከራ የዘለለ ለገበያ የቀረበ ምርት አለመኖሩ በክልሉ ተጠቅሷል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ኩባንያው በቢዝነስ ፕላኑ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎችን እንደሚገነባ ቢገልጽም፣ ግንባታው ካለመካሄዱም በላይ የመሬት ግብርም በወቅቱ አልተከፈለም፡፡
ኩባንያው የባሮ ወንዝ ወደ ማሳው እንዳይገባ በወንዙ ዳር የሠራቸው ግድቦች በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ጎርፍ አደጋና ከፍተኛ የንብረትና እርሻ ውድመት አስከትለዋል ብሏል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የህንዱ ኩባንያ ቬርዳንታ ሃርቨስት አግሮ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በ2000 ዓ.ም. በክልሉ ማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ 3,012 ሔክታር መሬት ተረክቧል፡፡ ‹‹ድርጅቱ ከመነሻው መሬቱን ሲረከብ ሻይ ቅጠል ለማልማት ቢሆንም፣ የእርሻ ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ጥቅጥቅ ደንና ወንዞችና ጅረቶች በሚገኙበት ሥፍራ በመሆኑ፣ ብዙ ደን እየወደመና ወንዞችና ጅረቶችም እየደረቁ መሆናቸው እየተስተዋለ ነው፤›› ሲል ክልሉ ለፌዴራል መንግሥት የጻፈው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡
‹‹ድርጅቱ ከቆመለት ዓላማ በተቃራኒ ከአካባቢው ደን ጣውላ በማምረት ሲያጓጉዝ በተጨባጭ ተይዟል፤›› ሲል ደብዳቤው ጨምሮ ያስረዳል፡፡
ክልሉ ለፌዴራል መንግሥት የጻፈው ይህ ደብዳቤ ያንፀባረቃቸው ሐሳቦች ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት የካዳቸው እንደነበሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያስታውሳሉ፡፡ ይህ ኩባንያ የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች እየሄደበት ያለው መንገድ አግባብ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ታህሳስ 2003 ዓ.ም. ለግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹በምንም ምክንያት የደን መሬት ለእርሻ መሰጠት ስለሌለበት ደኑን ማልማት ለሚፈልጉ ሰዎች፣ ወይም በሕዝብ ተሳትፎ እንዲለማ ተገቢው እንዲፈጸም እጠይቃለሁ፤›› ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
ነገር ግን በወቅቱ የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ የክልሉ መንግሥት ቦታው ቁጥቋጦ እንጂ የደን መሬት አለመሆኑ እየተጠቀሰ የቅሬታ አቅራቢዎች ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ከአራት ሳምንት በፊት የዚህ ኩባንያ ንብረት በእሳት የወደመ ሲሆን፣ በውድመቱ የተጠረጠሩ ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ይህንን እውነት ባመነበት ደብዳቤ ላይ ለኩባንያው የተሰጠው መሬት በደንና በወንዞች የተሞላ መሆኑን ከመግለጹም በላይ፣ ኅብረተሰቡ በቦታው ላይ የይገባኛል ጥያቄ እየቀረበና እሮሮም እያሰማ መሆኑን አምኖአል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ሳዑዲ ስታር ግብርና ልማት ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በ2001 ዓ.ም. በአኙዋ ዞን አቦቦ ወረዳ አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቧል፡፡ ኩባንያው ሰባት ሺሕ ሔክታር መሬት ቢመነጥርም፣ አርሶ በዘር የሸፈነው 135 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡
ኩባንያው ወደ ሥራ ከገባ አምስት ዓመታት ቢያስቆጥርም በርካታ ሥራዎቹ በጅምር ቀርተዋል፡፡ ወደ እርሻ የሚወስደው ዋናው መንገድ በድርጅቱ ከባድ ተሽከርካሪዎች በየጊዜው እየተባላሸ ኅብረተሰቡ እጅግ የሚመረርበት እንደሆነና ይህንን መንገድ ሳዑዲ ስታር በአስፋልት ደረጃ ለመገንባት የገባውን ቃል እንዳላከበረ ክልሉ ለፌዴራል መንግሥት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ ሳዑዲ ስታር በከፍተኛ የማኔጅመንትና የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች እየጠቆሙ ከመሆኑም በላይ የኩባንያው ንብረት ለጉዳት እንደተዳረገ ይነገራል፡፡
የፌዴራል መንግሥት እነዚህ ኩባንያዎች ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ገምግሞ ዕርምጃ እንዲወሰድ ክልሉ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ (ሪፖርተር) (ፎቶ፡ ለማሳያነት ብቻ)
Leave a Reply