ከአዲስ አበባ ወደ አክሱም ይጓዝ የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ረቡዕ ለት በጭንቅ እንዲያርፍ መደረጉ ተገለጸ፡፡ አደጋው ከአምስት ደቂቃ በፊት ቢከሰት ኖሮ አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ሊፈነዳ ይችል እንደነበር ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡
78 መንገደኞችንና ሠራተኞችን አሣፍሮ ይጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ (Bombardier Q400) አውሮፕላን ከክንፎቹ በአንዱ ጭስ መነሣቱን የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ በመደወሉ እጅግ አስጨናቂ በሆነ መልኩ እንዲያርፍ መደረጉን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡ ጋዜጣው ስማቸው ከመግለጽ የተቆጠቡ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደጻፈው አውሮፕላኑ ከማረፉ ከአንድ ደቂቃ በፊት የግራው ክንፍ እየጨሰ መሆኑን ማስጠንቀቂያው ማመልከቱንና አንዱ ሞተር ደግሞ እንደሚገባው ይሰራ እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡
ሱዳን ትሪቢዩን በስልክ ያነጋገራቸው ተሳፋሪ ጭስ ከአውሮፕላኑ ክንፍ ሲወጣ መመልከታቸውን፤ ተሳፋሪው ሁሉ በጭንቅ ውስጥ የነበረ መሆኑንና ሁኔታው በጣም አስደንጋጭ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በመጥቀስ የአየር መንገዱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ አደጋው አውሮፕላኑ ከማረፉ አምስት ደቂቃ በፊት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ሊፈነዳ ይችል ነበር፡፡
ሁኔታውን በጥንቃቄ ያስተዋለው የአውሮፕላኑ አብራሪ ካፒቴን ፈጣን እርምጃ በመውሰድ አውሮፕላኑ ወደ ዋናው ማቆሚያ ከመድረሱ በፊት በማቆምና ተሣፋሪዎቹ በፍጥነት እንዲወጡ በማድረግ ሊከሰት የነበረውን የእሣት አደጋ መከላከሉ ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡ የካፒቴኑ ውሳኔ የሚደነቅ መሆኑን ባለሥልጣናቱ የገለጹ ሲሆን ተሣፋሪዎቹም ህይወታቸውን ከአደጋው በመታደጉ የጀግና ክብር በመሥጠት ማመስገናቸው ጨምሮ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሥልጣናት የጭሱ መነሻ እየተመረመረ ነው ቢሉም አየር መንገዱ አደጋውን አስመልክቶ እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አላወጣም፡፡
ባለፈው ሳምንት በቆመበት እሣት የተነሳበት ሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋው ከታወቀ ጀምሮ የውጭ አገር የዜና ወኪሎች በየደቂቃው ዘገባ ሲያቀርቡበት የነበረ መሆኑ ቢታወቅም ከዚህ በባሰ መልኩ በርካታ ተሣፋሪዎችን ጭኖ ለአደጋ ተጋልጦ የነበረው አውሮፕላን ጉዳይ አደጋው ከተከሰተበት ረቡዕ ጀምሮ እስካሁን በመንግሥትም በኩል ሆነ በአየር መንገዱ ይፋ አለመሆኑ በበርካታዎች ዘንድ ጥያቄ መጫሩ የማይቀር ነው፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
አለም says
ውድ ጎልጉል፣ የአየር መንገዱ አስተዳደርና መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት እየተከሰተ ያለ ችግር ነው። አንደኛ፣ ጥራት ያላቸው አብራሪዎችና ሜካኒኮች ለቅቀው እንዲሄዱ ተደርጓል። ጥያቄ ማንሳት መንግሥትን እንደ መቃወም ስለ ተቆጠረ የተከለከለ ነው። ስለዚህ ጥራት ቀንሷል። ሁለተኛ፣ ሠራተኛው ተመጣጣኝ ደመወዝ ሳይከፈለው ረጅም ሰዓት እንዲሠራ እየተገደደ ነው። ሦስተኛ፣ የአየር መንገዱን ቁልፍ ቦታዎች [ከቦርድ አባልነት ጀምሮ] የያዙት መንግሥት የመደባቸው [አብዛኛው ከትግራይ] እንጂ ብቃት ያላቸው አይደሉም። በምሥጢር ለመውጣትና ለመግባት፣ ገንዘብ ለማውጣትና እቃ ለማስገባት እንዲመች ቁልፍ ቦታዎች ላይ ከገዥው መደብ የሆኑ ብቻ ተመድበዋል። በስፖርት ፌዴሬሽን የተከሰተው ይኸው ነው። ቴሌኮሙኒኬሽን ብትሄድም ይኸው ነው።
አለም says
አደጋ ሲደጋገም ግን አየር መንገዱ ተፈላጊነቱ እንደሚቀንስ የታሰበ አይመስልም። በንግዱ ዓለም አንዴ ከወደቁ መነሳት እጅግ ከባድ ይሆናል። በተጨማሪ የሰውን ሕይወት ለአደጋ የተጋለጠ ያደርገዋል። አቶ ግርማ ዋቄ ከአረብ አገር ተጠርተው የመጡት ችግር ስለ ተፈጠረ እንዲያቃኑት ነው። አንዴ ተቃንቶ ማትረፍ ሲጀምር በጡረታ አሰናብተዋቸው የራሳቸውን ሰው [ተወልደን] ሾሙ። በቅድሚያ ግን ተወልደን እንዲያሠለጥኑ ተደረገ። ከተወልደ የሚሻሉ ብዙዎች አሉ። ግን አልተፈለጉም። በጡረታ ሰበብ የተገፉት አቶ ግርማ ባሁኑ ወቅት የሩዋንዳን አየር መንገድ እያደራጁ ይገኛሉ። የተወልደን ብቁ አለመሆን ለመሸፋፈን ስንት ጊዜ ይህን ሽልማት ተሸለመ እየተባለ እንደ ሆነ ጉግል አድርጋችሁ እዩ። በሊባኖስ ላይ የፈነዳው ጉዳይ ተደባብሶ ለምን እንደ ቀረ ማን አወቀ? ኢትዮጵያውያንን እንደ ብቃታቸውና በዜግነት መብታቸው አለማሳተፉ ይህ መንግሥት ከፈጸማቸው ግፎች የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛሉ። ይኸን የምለው ስለ ጥላቻ አይደለም። ቁጭ ብዬ አጣርቼ ሐቁን ለማወቅ ጥረት አድርጌ ነው። በየመ/ቤቶች ቁልፍ ቦታ የያዙትን ስምና ችሎታ ገምግሜ ነው። አሳፋሪ ሥራ እየተደረገ ነው። ከየብሔሩ እኩል ዕድል ለመስጠት ነው እያሉ ያታልላሉ። ጎልጉሎች ምን ይመስላችኋል?