ለአዲስ አበባ ከተማ ክብር ያላችሁ እንስማማለን። አዲስ አበባ አንጀቷ ርህሩህ ነው። ከገዢዎች ክፋት በተጨማሪ አዲስ አበባ ፊቷን ብታጠቁር ምን ይኮን ነበር? ሎሬት ጸጋ ስለ አዲስ አበባ ተቀኙት ወደው አይደለም። በውነት ላስተዋለው የአዲስ አበባ ቆዳና ያዲስ አበቤዎች ትከሻ “ላይችል አይሰጥም” የሚሉት አይነት ነው።
በየቀኑ አዲስ አበባ በማለዳ በትና በምሽት የምትሰበስባቸው ልጆቿ ተቃምሰው ማደራቸው ባዲሳባ በረከት እንጂ በገዢዎች አቅርቦት አይመስልም። ከአራቱም ማዕዘን የሰው ደራሽ ወደ አዲስ አበባ ይንፎለፎላል። አዲስ አበባ ሞልታ የምትፈስ አትመስልም። እምዬ ምኒሊክ ሲቆረቁሯት ጀምሮ አዲስ አበባ ተቀባይ ነች። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የሰው ልጅ እምብርት፣ አዲስ አበባ፣ ፊንፊኔ። ምንም ትባል ምን አዲስ አበባ ሁሉም ጓዳ የተባረከች ናት። “ዘላለማዊነት ለአዲስ አበባ” የቀጭኑ ቄራ መፈክር ነው።
ባለፈው ሳምንት በሬ ለምኔን አሳይቼ፣ ዝግ ቤቶች አቆይቻችሁ፣ እንስራ እርቃን ቤት ስለሚካሄደው ድራማ አውግተን ነበር የተለያየነው። ሰላም አንባቢዎቼ። ጎልጉል ድረገጽ ጋዜጣ ላይ መለቅለቅ መጀመሬ አስከሚነቃ ለመቀጠል በገባሁት ቃል መሰረት የዛሬው ተረኛ ማስታወሻዬን ከፈትኩ።
የመሬት ውስጥ ነዋሪዎች
“ከመሬት በታች የሚኖሩት ሙታኖች ብቻ ናቸው” ያለው ማን ነው? አዲስ አበባ ሁሉን ቻይ ነች። ከርሷ የማይችለው የለውም። ሁሉንም አቻችላ የመንግስትን ሚና በመጫወት ታኖራለች።ሰዎቹ ሲያቀታቸው እየቀበረች የማስተዳደር ስራዋን ከሰው በላይ ታከናውናለች። ሰባተኛ በመባል የሚታወቀው ያራዶች ሰፈር ላፍታ ቆምኩ። ከምሽቱ አንድ ሰአት አካባቢ ይሆናል። መርካቶ ሸቅለው ወደ ቤታቸው የሚተሙ ብዛታቸው ያስደነግጣል። ድሮ አውሬው ሳይኖር የምታውቁት በአንድ ብርና በሽልንግ ጭን የሚሞቅበት ሰባተኛ ዛሬ የተለየ ነው።
ከመርካቶ ነቅለው ወደ ማደሪያቸው የሚተሙት ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ ወይም ከስታዲየም የሚለቀቁ እንጂ ለጉዳይ ወጥተው ወደቤታቸው የሚገቡ አይመስሉም። በሰባተኛ ወደ አማኑኤል የሚተሙት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ፌስታል ማንጠልጠል አይዘነጉም። አብዛኞቹ የሚይዙት ላስቲክ ዳቦ የያዘ ነው። ማባያውን ያዲሳባ አምላክ ይወቀው።
ያየሁት የሚፈሱትን ሰዎች እንጂ ማረፊያቸውን አይደለም። ፈሰው እንደሚገቡት ሁሉ ማለዳ ተነስተው ወደ መርካቶም የሚፈሱት በተመሳሳይ በግፊያ ነው። ግፊያው በአገሪቱ የስነ ህዝብ ፖሊሲ ስለመኖሩ ያጠራጥራል። እግረ መንገዴን አነሳሁት እንጂ የዛሬው ዋና ርዕሴ ከመሬት ውስጥ በህይወት ስለመሸጉ ወገኖች ለማሳወቅ ነው። ጊዜው ትንሽ ቢቆይም!!
በ“ግራውንድ ሲቀነስ አንድ” አንድ ደረጃ ወደ መሬት ዝቅ ብለው የሚኖሩ ብዙ ናቸው። በየቦታው አሉ። ለዛሬ የማስተዋውቃችሁ ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ አውቶቡስ ተራ በየመንገዱ አካፋይ መሃል ለመሃል በተዘረጋው ውሃ መውረጃ ቱቦ ውስጥ ስለሚኖሩት ነው። ግራውንድ ሲቀነስ አንዶች!!
አቡነ ጴጥሮስን ይዛችሁ ወደ መስጊድ ስትጓዙ የመንገዱን አካፋይ ትመለከታላችሁ። ለበርካታ ዓመታት መንገዱን እያየሁ ተሸጋግሬበታለሁ። ከስሩ ሰው ስለመኖሩ አስቤም አልሜም አላውቅም ነበር። አንድ ቀን አትክልት ተራ የሚያቆየኝ ጉዳይ አጋጠመኝ። ጉዳዬ በአጋዥ የሚከናወን ነበርና አንድ ጎረምሳ እንዲተባበረኝ ጠየኩት። ስራችንን እንደጨረስን በመንገዱ አካፋይ በግምት በመቶ ሜትር ርቀት የሚታየውን ጉድጓድ ስለሸፈነው ስብርባሪ መስታወት ድንገተኛ ጥያቄ አነሳሁ። ጎረምሳው ተረከልኝ። እንዲህ ሲል።
“የመኖሪያ ቤት በር ነው” ከላይ ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ መስጊድ መብራቱ ድረስ ውስጡ ክፍት ነው። በግንብ የተሰራ የውሃ መውረጃ ቱቦ አለ። ከላይ እስከታች በስምምነት እንኖርበታለን። ቤተሰብ ያፈሩ። የልጅ ልጅ ያዩ አሉ። ቤታችን ነው። ለቤት በር ያስፈልገዋል።…”
ደነገጥኩ። የመንገዱን አካፋይ በመያዝ በግምት በመቶ ሜትር ርቀት ያሉትን “በሮች” እየተመለከትኩ አስጎብኚዬን እቀዳው ጀመር። ሃብተ ጊዮርጊስ ስንደርስ ቆመና ወደ ድልድዩ ወሰደኝ። ወንዙ አፍ ላይ የሚቀረውን የአንዱን ቱቦ ጫፍ አሳየኝና የአስከሬን መውጫ በር መሆኑን ነገረኝ። ይህን ጊዜ አንድ ራሱን የቻለ ማህበረሰብ ከመሬት በታች እንደሚኖሩ ተረዳሁና ዝርዝር ነገሮችን የማወቅ ጉጉቴ ነደደ።
አዎ! አስገራሚ ታሪክና የኑሮ ወግ ያላቸው ውብ ፍጡሮች ከመሬት በታች ይኖራሉ። በአገሪቱ ፖለቲካና ባገራቸው ጉዳይ አያገባቸውም። የአዲስ አበባ እንብርት ውስጥ ይኖራሉ ግን አድራሻ ያለቸውም። ቀበሌና ቤት ቁጥር አያውቁም። ቀበሌ ስለሌላቸው አይመርጡም ለመመረጥም እድል የላቸውም – የሁሉም ዜጎች መብት በተከበረባት ኢትዮጵያ!!
ወደ አትክልት ተራ ተመልሰን ዘላለም ደስታ ሆቴል በር ፊትለፊት ባለው በራቸው ላይ ጸሃይ እየሞቁ ያሉትን ጓደኞቹን አስተዋወቀኝና በስፋት አወጋን። ሞገስ እንደሚባል የገለጸልኝ ሃያ ሁለት ዓመት የሚጠጋ “ጎዳና አዳሪ”፣ በነገራችን ላይ “ጎዳና አዳሪ አይደለንም ቤት አለን። ቀበሌ የቤት ቁጥር ከልክሎን ነው” በማለት “የመሬት ውስጥ ነዋሪዎች” ተብለው መጠራት እንዳለባቸው ይከራከራሉ።
ሞገስ በርጋታ ማብራሪያ አቀረበልኝ። በሞገስ ማብራሪያ መሰረት የውሃ መውረጃው ቱቦ ይህን ይመስላል። ጎንና ጎኑ በግንብ የተሰራ ሲሆን ርዝመቱ በውል አያውቁትም። ጎኑ በጣም አጭር በመሆኑ እግር ዘርግቶ አያስተኛም። ቀን ቀን ነዋሪዎቹ ግራና ቀኝ በመቀመጥ ያወጋሉ። ቡና ይፈላና ይጠጣሉ። ቡና የምታፈላዋን ሴት የማየት እድል ያላቸው አጠገቧ ያሉት ብቻ ናቸው። ማታ ማታ የሚተኙት እንደ አገባባቸው እግርና ጭንቅላት በማገናኘት ሲሆን ባልና ሚስቶች አብረው ቢተኙም ምንም ዓይነት ግንኙነት አያደርጉም። በመሬት ውስጥ ነዋሪዎች ህግ መሰረት በህብረት በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ወሲብ መፈጸም የሌሎችን ስሜት ስለሚጎዳ አይቻልም።
በስመ ጎዳና ተዳዳሪነት ዝቅ ተደርገው እንደሚታዩ የገለጸው ሞገስ ፍቅረኞች ወሲብ እንዴት እንደሚፈጸሙ ሲነግረኝ አንዳችም መገረም አይታይበትም። ባለትዳሮች አሉ። አስፈላጊውን የወሲብ ግንኙነት ከፈለጉ አሜሪካን ጊቢ በርካሽ የሚከራዩ፣ በወቅቱ ለቀን አንድ ብር የሚከራዩ አልቤርጎ በመያዝ ጣጣቸውን እዛው ጨርሰው ይመጣሉ። አለበለዚያም ነዋሪዎች ለዕለት ጉርስ ፍለጋ ጠዋት ተነስተው በየፊናቸው ሲሰማሩ ፍቅረኛሞች በሩን ዘልቀው ይገባሉ። የደላቸውም ያልደላቸውም አዲስ አበቤዎችከመሬት በላይ ከወዲህ ወዲያ ሲራወጡ እነሱ ከመሬት ስር ሆነው ወሲብ ያደራሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ላወጡት ህግ ተገዢ ለመሆን ሲሉ ነው።
በመሬት ውስጥ የተወለዱ ህጻናት ሲጃራ፣ ሶፍት፣ ሳንቲም መዘርዘር፣ ቀላሉና ገና ኮልታፋ እያሉ የሚሰማሩበት ስራ ነው። ስለ ልጆች ሲወራ እናት ወልዳ ጉድጓድ ውስጥ እንዴት ትታረሳለች? የሚለው ጥያቄ የሁላችንም ይሆናልና የሰማሁትን እንዳለ ላቅርብ።
በነጻ ወሊድ አገልግሎት ያገኘች እናት የምትታረሰው በወጉ ነው። በርግጥ የጠረን መቀየርና አንዳንድ የጽዳት ችግሮች ቢኖሩም መላው የመሬት ውስጥ ነዋሪዎች አራስ እህቶቻቸውን ለማረስ የሚያደርጉት ትብብርና በተግባር የሚያቀርቡት ቁስ ከየትኛውም ዜጋ የሚተናነስ አይደለም። ራሳቸውን የቻሉ ማኅበረሰቦች በመሆናቸው ማህበራዊ ግንኙነታቸው ከጉድጓዱ አንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ያሉትን አንድ ላይ የሚያሳትፍ በመሆኑ የጎላ ችግር አያጋጥምም።
የሚያሳዝነው ጉዳይ አንድ የማህበረሰቡ አባል በሞት ሲለይ ማህበረሰቡን የሚለይበት አግባብ ነው። ሞገስ ቅሬታ እየተሰማው ሲናገር ሰው ሲሞትባቸው ተንጠላጥለው በሚገቡበት በር ለማውጣት ያስቸግራል። ስለዚህም በቱቦው አንድ ጫፍ ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ በኩል አስከሬን ተሸክመው ውስጥ ለውስጥ መጓዛቸውን በመጠቆም የአጋጣሚውን አሳዛኝነት ይናገራል። በወቅቱ ሞገስ ሲናገር በርግጥም እውነታው ልብን የሚወጋ ሆኖብኝ ነበር። ከመሬት በታች ኖረው ከመሬት በታች መቀበር!!
ሞገስ ከነገረኝ ነገር እጅግ ያስገረመኝ የመሬት ውስጥ ነዋሪዎች በሚኖሩበት አካባቢ ማንኛውም ሰላማዊ ሰው ላይ ለዝርፊያ በሚል ጉዳት እንዲደርስ አይፈቅዱም። አንድ ዝርፊያና ለዝርፊያ ሲባል አደጋ ቢደርስ ፖሊስ ከሚኖሩበት ጉድጓድ ውስጥ ስለሚያባርራቸው ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ሰው ሲመለከታቸው ሌባ አድርጎ ያስባቸዋል። ላያቸውን በመመልከትና በጎዳና ላይ ስለሚታዩ አይታመኑም። ከቢሮና ከሚሰሩበት ቦታ፣ አየር በአየር ሲያጭበረብሩ የሚውሉ ወሮበሎች የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሌባ አድርገው ይስሏቸዋል።
የሰከሩ ሰዎች ሲያጋጥሙዋቸው በክልላቸው ተዘዋዋሪ ሌቦች አደጋ እንዳያደርሱባቸው ጥበቃ ያደርጋሉ። ከቻሉም ይንከባከባሉ። አንዳንዴም እስኪነጋ አስጠግተው ይሸኛሉ። ሁሉም እንደነገሩኝ ከሆነ በየቢሮውና በየቀበሌው ተሰግስገው ከድሃ ህዝብ ላይ ከሚዘርፉት ይልቅ እነርሱ የተሻለ ስብዕና አላቸው። በዘመቻ ከሚኖሩበት ዋሻ ያባርሩናል ብለው እንጂ ጨለማን ተገን በማድረግ ብዙ ብዙ ድርጊቶች በፖሊስ፣ በደህንነት ሃይሎችና በሹማምንቶች ሲፈጸሙ ስለማየታቸው ጥርጥር የለውም።
ሌብነትን አስመልክተው ሲናገሩ “ብንሰርቅ እዚህ ምን እንሰራ ነበር? ወይ ዘግተን ሌላ ኑሮ እንኖር ነበር፣ ከተያዝንም እስር ቤት እንገባ ነበር” የሚል ቀና የሚመስል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ሲሆን ውስን ቦታ የሚያድሩ ወገኖቻችን በፍጹም አይሰርቁም የሚል ጠንካራ መከራከሪያ አላቸው።
ትራፊ ዋናው ቀለባቸው ነው። የአትክልት ተራ ፍራፍሬ መጣያ በርሜሎች ለተመጣጠነ ምግብ ዋስትና ሰተዋቸዋል። አገር አደገ በሚል ወደ ሰማይ የሚደረደሩ ቤቶችና ህንጻዎችን የሚያሳየን መንግስት ከመሬት በታች ያሉትን አስታውሶ ኮንዶሚኒየም ቤት ወይም ኮንደም ስለመስጠቱ ማስረጃ የለም። ወይም ባሉበት የቱቦ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስለመያዙ “ባለ ራዕዩ መሪ” የተናገሩት ወይም የተናዘዙት ኑዛዜ እንዳለ እስካሁን አልተደመጠም። ቆሻሻ እየተመገቡ ከመሬት በታች ስለሚኖሩት ውድ ዜጎች “የህዳሴው ጀግና” የያዙት ዕቅድ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት አልተሰማም።
የመሬት በታች ነዋሪዎች ፍሳሽና ጎርፍ አያሰቃያቸውም። በክረምትም በበጋም ሙቀት ነው። ቱቦው ውሃ እንዳይፈስበት የተደረገበትን ምክንያት ባያውቁትም ለሰራው ክፍል ምስጋና አላቸው። ጠልጠል ብዬ እንዳየሁት ዙሪያው ግንቡ ስዕሎች ይታዩበታል – የግድግዳ ስዕል መሆኑ ነው። ከጋዜጣ ላይ የተቀደደ የመንግስቱ ሃይለማርያም ምስልም ይታያል። ቱቦው የተሰራው በንጉሱ ዘመን ሆኖ ሳለ የመንግስቱ ፎቶ የተለጠፈበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። የውሃ መጠጫ ቁሳቁሶችና በላስቲክ የተቋጠሩ ልብሶች ይታያሉ። እንፋሎቱ አፍንጫ ወጋ ያደርጋል። እነ አጅሬም አሉ። እግሬ ከመዝለቁ ተቀበሉኝ። ቢምቢ እንደበላው ገላዬ ድብድብ አለ። ከየአይነቱ ነፍሳተ ሰራዊቶች አሉ። እኔን ለደቂቃዎች እንዲህ ያጣደፉኝ እነሱን እንዴት እንደሚያስቸግሯቸው አሰብኩ። ሃይሌ ገ/ስላሴ እንዳለው “ይቻላል” ብሎ ማለፍ ይከብዳል። የግድ ሌላ መላ አለ። በወር አንዴ ማላታይል ይረጫሉ። መስኮት በሌለው “ቤት” ውስጥ ማላታይል!!
ሞገስን ጨምሮ አስቀድሞ የነበሩት የመሬት ውስጥ ነዋሪዎች ስለያቸው ገንዘብ ጠይቀውኝ ነበር። እነሱን አስለፍልፌ ታሪካቸውን በመሸጥ ገንዘብ እንደማገኝ ነግረውኝ ነበር። ያለኝን ሰጥቼ አዝኜ ተለየኋቸው። ለዛሬ ይበቃሃል ብሎ ያጫወተኝ ጋዜጠኛ ዛሬ ከጎኔ የለም። ሰላም ሁኑ፤ በሚቀጥለው ሳምንትም እንዲሁ እያነሳን እንጥላለን። ክብር ሁሉን ቻይ ለሆነችው አዲስ አበባችን!! ክብር እድሜዋን ሁሉ ከመፈክር ይልቅ በተግባር ሁሉንም ስብስብ አድርጋ ለምታኖረው አንዷ ገነት። ሃዋሳም ሌላ ታሪክ አለ። አሞራ ገደል!!
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Jemal M. says
Once i was there .