ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ስሞኑን በአሸባሪው አይሲስ የተወሰደውን አሰቃቂ ተግባር በማውገዝ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያወጣው መግለጫ እንዲህ ይነበባል:-
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መግለጫ
ባለፈው እሁድ አይሲስ ባሰራጨው ቪዲዮ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ሲገደሉ ተመልክተናል። ስለ ቪዲዮው ብዙ ማለት ቢቻልም ወገኖቻችን ከአገራቸው ወጥተው ወደ ተሻለ ኑሮ ፍለጋ መንከራተታቸው ለዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ ሞት ዳርጓቸዋል። ከአገራቸው የወጡት እየኖሩ ከመሞት ለመትረፍ ቢሆንም በስደት ደግሞ እጅግ መራራውን የሞት ጽዋ ጠጥተዋል። ይህ የወገኖቻችን ዕልቂት በዓለማችን ላይ በሚገኝ በምንም ዓይነት ቋንቋ፣ አገላለጽ፣ አጻጻፍ፣ እንባ፣ ወዘተ ሊገለጽ የማይችል ነው። ረዳት አልባ ሆነው የተመለከትነው ትዕይንታቸውም በውስጣችን ለዘመናት የማይሽር ቁስል ይዞ ይቀመጣል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ቦታ፣ ወዘተ ሳይለዩ ይህ በአገር ወገን ላይ የደረሰው ሐዘን በጋራ በመሆን እርስ በርስ በመጽናናት፣ በመበረታታት እንዲወጡ፤ ሌሎችንም በተመሳሳይ የስቃይና የመከራ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን ወገኖች ለመርዳት የሚችሉበትን መንገድ እንዲቀይሱ አሳስበዋል። አቶ ኦባንግ ሲቀጥሉም፤
“በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእነዚህን ለሃይማኖታቸው የቆሙ ጀግና ወገኖቻችንን ተመልክቷል፤ የሞት ከበሮ ቢደለቅባቸውም ሳይፈሩና በድፍረት ሰብዓዊነታቸውን በናቁባቸው አረመኔዎች ፊት ለእምነታቸው ቆመዋል፤
“እኔም ሆንኩ በጋራ ንቅናቄያችን ሥር የሚገኙ ቤተሰቦችና ሌሎች እጅግ በርካታ ወገኖች የተሰማንንን ጥልቅ ሃዘን በምንም ዓይነት ቃላት መግለጽ አንችልም፤ ይህንን ፍጹም አረመኔያዊ የሆነ፤ አንዳች ሰብዓዊነት የሌለበት ድርጊት ባሉት ቃላት ሁሉ ተጠቅመን እናወግዛለን፤ ልጃቸውን፣ ወንድማቸውን፣ አጎታቸውን፣ ወገናቸውን፣ ወዘተ ላጡት ቤተሰቦች እንደ እነርሱ እኩል ማዘን ባንችልም የአንዲት ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል እንደ መሆናችን ይህንን መራር ሃዘን የራሳችን አደርገን በመውሰድ አብረናችሁ እናዝናለን፤ እናለቅሳለን፤ እናነባለን። በዚህ ሃዘን ውስጥ ከፈጣሪ የተሰጠንን የአብሮነት እና የመተባበር መንፈስ በማጎልበት ሁላችንም ሃይማኖታችንን፣ የፖለቲካ አመለካከታችንን፣ ጾታችንን፣ ዘራችንን፣ ዕድሜያችንን፣ ወዘተ ሳንመለከት እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ከወገኖቻችን ጋር አብረን እንዘን፤ እናንባ፤ ከመሰል ሰቆቃ የምንላቀቅበትን እና ዳግም የማናለቅስበትን መንገድ በትብብር እንፈልግ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአገር ውስጥ በህወሃት/ኢህአዴግ አማካኝነት ከሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ስደት፣ የመሬት ንጥቂያ፣ ጭቆና፣ የዘር መድልዖ፣ አሰቃቂ ድህነት፣ ወዘተ ወደ ተሻለ ኑሮ ፍለጋ በየአገሩ እንደ ጨው ዘር የተበተነው የአገራችን ሕዝብ ባለፉት ትቂት ሳምንታት ውስጥ በተለያዩ አገራት የተቀናጀ ጥቃት ሲደርስበት ቆይቷል።
በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከመደብደብ አልፈው ተገድለዋል። ሁለት ኢትዮጵያውያን ጎማ ተደርጎባቸው በእሣት ተቃጥለዋል፤ ነድደዋል፤ እነርሱ ጨምሮ በአጠቃላይ ሶስት መሞታቸው ተነግሯል። የደረሱበት ለማወቅ ባለመቻሉ እንደ ሞቱ ሳይቆጠሩ የቀሩ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በቅርቡ እንደተነገረው የውጭ ፓስፖርት የያዘ ወይም የደቡብ አፍሪካ መታወቂያ ካርድ የሌለው ማንም ሰው አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል በስፋት በመነገሩ በርካታዎች የሚሄዱበት ባይኖራውም አገሩን ለቅቀው ሄደዋል።
ከዚህም ሌላ ባለፈው እሁድ ከ700 እስከ 950 ስደተኞችን ከመጠን በላይ አሳፍራ ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሜዲተራኒያን ባህር በመገልበጧ እጅግ ብዙዎቹ በውሃው ሰጥመው ሲሞቱ ጥቂቶች እንደተረፉ ተነግሯል። ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ በስፋት ይታመናል።
ባለፈው ወር በየመን የሚገኙ ወገኖቻችን እዚያ በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት መሄጃ አጥተው በመከራ ውስጥ መሆናቸውን ሰምተናል። ከዚህ ባለፈ መልኩም የስደተኛ ካምፓቸው በቦምብ ተደብድቧል ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ ለመናገር ባይቻልም ወገኖቻችን በስደት ምድር ህይወታቸው አልፏል። ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ወገኖቻችን በዚያ እንደሚገኙ ሲታመን ከየመን መውጣት የሚፈልጉት እጅግ በርካታ ቢሆኑም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የሚፈልጉት ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ይህ መረጃ የጋራ ንቅናቄያችን በዚያ ከሚገኙትና መከራው ከሚደርስባቸው ጋር በየጊዜው በሚያደርገው የቅርብ ግንኙነት እነርሱንም በዓለምአቀፍ ድርጅቶች ረጂነት ከዚያ ለማስወጣት በሚያከናውነው ሥራ ያገኘነውና ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያኑ የተነገረን ነው።
በዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ በሊቢያ የተከሰተው ጭፍጨፋ ከሁሉ የበለጠና በምንም መለኪያ የማይሰፈር ነው። እንደ ኢትዮጵያዊነታችን በየጊዜው ከምንሰማውና ከምናየው እጅግ የከፋ በመሆኑ ሃዘናችንን የመረረ ያደርገዋል። አረመኔዎቹ ነፍሰበላዎች ወገኖቻችንን ሲያርዱ የተናገሩት ነገር ይህንን የሚያደርጉት ለፈሰሰው የሙስሊም ደም ለመበቀልና ኢትዮጵያ የመስቀል አገር ስለሆነች ነው ብለዋል። ለመቀበል ያልፈለጉት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ የሙስሊም፣ የክርስቲያን፣ የአይሁድ (ፈላሻ) ዕምነት ተከታዮች በጣምራነት ተጋብተው፣ ወልደው፣ ተዋልደው፣ የኖሩባት አገር ናት። በዚህም ለዓመታት በዘለቀው አብሮ የመኖር ህይወት ኢትዮጵውያን በአንድ አገር ዜግነት ብቻ ሳይሆን በደምም ተሳስረዋል። ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከቋንቋ በላይ ኢትዮጵያዊነት በሚባል ጠንካራ ገመድ ተገምደዋል፤ በሰንሰለቱ ላይለያዩ ተቆራኝተዋል።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ይህንን አሰቃቂ፣ አረመኔና አሸባሪ ተግባር በገሃድ ወጥተው የኮነኑት፤ ያወገዙት። ንጹሃን በመገደላቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በኢትዮጵያዊነት ስም ወጥተው ኮንነውታል። መግለጫው በግልጽ እንዳስቀመጠው የአይሲስ ተግባር “ኢግብረገባዊ፣ ሕገወጥ፣ አረመኔያዊ እና ከዕምነታን ጋር በቀጥታ የሚጋጭ” ነው በማለት ገልጸዋል። “ስለዚህ በሊቢያ የኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ግድያ እጅግ በከረረ መልኩ የምናወግዘው ሲሆን ይህንን በፈጸሙ ላይ ፍትሕ እንዲበየን እንጠይቃለን” በማለት መግለጫው ድርጊቱን አውግዟል።
ስለዚህ ይህ የአይሲስ የጭከና ተግባር ከሃይማኖት ጋር የተገናኘ ሳይሆን የአምላክን ሥራ እየፈጸምን ነው በሚል ሽፋን የፈጣሪን ሕግ እየጣሱ የራስን ምኞች፣ ስግብግብበት፣ የሥልጣን ጥማት፣ ጥላቻ እና የግል ጥቅም ማሳደጃ ጸያፍ ድርጊት ነው።
ለሌሎች እነዚህ በግፍ የተገደሉ ወገኖች ቁጥር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ግን ስም፣ ዕድሜ፣ የሕይወት ታሪክ፣ ማንነት፣ ያላቸው የራሳችንና የቅርባችን የሆኑ ወንድሞቻችን ናቸው። አንዳንዶቹ እየታወቁ በመሆናቸው የእናቶቻቸው፣ የአባቶቻቸው፣ የእህቶቻቸው፣ የወንድሞቻቸው፣ ሃዘን ቅስማቸውን ሰብሮታል። እስካሁን ያልታወቁም አሉ፤ አንዳንዶቹም ሳይታወቁ ሊቀሩ ይችላሉ። እነዚህ ወገኖቻችን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከአገራቸው ተሰደዱ፤ ኑሮ ሲደላቸው መልሰው ቤተሰባቸውን ለመርዳት ዓላማ አድርገው፤ አልመው ከቀዬአቸው ወጡ፤ “የት ደረሱ” እያሉ አብረዋቸው ሲጨነቁ፣ ሲሰቃዩ፣ የነበሩ ቤተሰቦቻቸው ይህንን ዘግናኝ መልዕክት ሲሰሙ በህይወታቸው የተፈጠረው ጉድጓድ እጅግ ጥልቅ ብቻ ሳይሆን መድረሻም የለውም። ስለ ወገኖቻቸው እያሰቡ ፍትህን ይመኛሉ፤ ግን በዚህ ዘመን ላያገኙ ይችላሉ። ሌላ የሚፈርድ ግን አለ፤ በፍርድ የማያጓድል፤ መማለጃን የማይቀበል፤ እንደ ሰው ያልሆነ! መጽሐፉ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋል።” መክብብ12፡14።
ሌላው የወገኖቻችን ጭፍጨፋ ኢህአዴግ በሚመራት ኢትዮጵያ እንደ አንድ ተራ ዜና መቅረቡ ሃዘናችንን ይበልጥ ያስመረረና ያስከፋ ነው። አናሳ በሆኑት የትግራይ ተወላጆች ነን በሚሉ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ህወሃት/ኢህአዴግ የተጨፈጨፉትን ወገኖቻችንን ጉዳይ ዓለም እየተነጋገረበት ባለበት ወቅት “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እናጣራለን” ማለቱ ለብዙዎቻችን ሁለተኛ ሞት፤ ሁለተኛ መታረድ ነበር። እንዲህ ዓይነት በጣም መረን የለቀቀ ስግብግብነትና ራስወዳድነት ሥርዓት በሆነባት ኢትዮጵያ መኖር ስላቃታቸው ነው ወገኖቻችን አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት። ጥቂቶች ሲበለጽጉ እነርሱ የበዪ ተመልካች መሆናቸው፣ የሃብት ክፍፍልና የሥራም ሆነ ማንኛውም ዕድል ለጥቂቶች የሥርዓቱ አቀንቃኞች በመፈቀዱና እነርሱ እንደ ሌላ ዜጋ በመታየታቸው፤ “አገር እያለኝ ከሌለኝ ለምን አገር ፍለጋ አልወጣም” በማለት አገርና ኑሮ ፍለጋ ወጥተው በበረሃ የቀሩ ናቸው። ማነው ለዚህ የዳረጋቸው? ከህወሃት/ኢህአዴግ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል!?
አገራችንን ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በላይ በመቆጣጠር እየገዛ ያለው ኢህአዴግ የሚመራው በአናሣዎች መሆኑ ግልጽ ነው። ለስሙ “ኢትዮጵያ” የሚል በድርጅቱ መጠሪያ ላይ በመኖሩ ሁሉን ዓቀፍ ለመሆን ቢጥርም እውነታ ግን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲነጻጸር አናሣ በሆነው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቁጥጥር ሥር ያለ ድርጅት ነው። ከኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት አንጻር ትግሬዎች 6በመቶ መወከላቸው ለዚህ ጉልህ ማስረጃ ነው። የማዕከላዊው ኮሚቴም በአናሳ ትግሬዎች የሚመራ በመሆኑ የአገሪቱ ቁልፍ ክፍለ ኢኮኖሚዎች የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት እንዲሁም ውሳኔ የሚያስተላልፉት እነርሱው ናቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው አናሳው የትግሬ ድርጅት መሆኑን ይህም ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ስም የሚነግድና እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ በስሙ የሚያጭበረብር አሸባሪ ድርጅት እንደሆነ ታሪኩ ይመሰክራል። ድርጅቱ በበረሃ በነበረበት ወቅት በተለይ የአሸባሪነት ተግባራት ተሰማርቶ እንደነበር፤ በረሃብ የሚንገላቱ የትግራይ ተወላጆችን የዕርዳታ እህል እንዳያገኙ በመንፈግ እና ሌሎችን እጅግ ሰቅጣጭ የሆኑ ኢሰብዓዊ ተግባራትን በመፈጸም ለራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ ማዋሉን የቀድሞ አባላቱ ብቻ ሳይሆኑ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ።
ይህ የህወሓት አሠራር አሁንም አንዲት ሉዓላዊት አገርን በነጻ አውጭ ስም እየገዛ ባለበት ወቅትም ቀጥሏል። እኩይ ተግባሩን ለሚደግፉ ጭፍን ዘረኞችና ሌሎች በገንዘብ ለተገዙ ሆድ አዳሪዎች የአገራችንን ሃብት እንደፈለጉ እንዲመዘብሩ ያለከልካይ ፈቅዶላቸዋል። ይህንን ለማጣፋት ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ “አገሪቱ በድርብ አኻዝ ዕድገት ላይ ትገኛለች” በማለት ቀን ለሌት ራሱ በተቆጣጠረው ሚዲያ ያለማቋረጥ ይለፍፋል። ለሚገዛው ሕዝብ ደንታ የሌለው በመሆኑ በአገራቸው እንደ ዜጋ መቆጠር ያልቻሉና ተመጣጣኝ የሃብት ክፍፍል ዕድል ለማግኘት ያልቻሉ በአገኙት ቀዳዳ ከኢትዮጵያ መሰደድ ቀዳሚ ተግባራቸውና የሕወታቸው ህልም ከሆነ ቆይቷል።
የወገኖቻችን መታረድ እና በጥይት መረሸን በዓለም ዙሪያ እንደተሰማ ህወሃት/ኢህአዴግ “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እናጣራለን” በማለት የተናገረው እስካሁን የብዙዎችን ስሜት የረበሸና እያንዳንዳችን በቁም ያሳረደ ጸያፍ ተግባር በመሆኑ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ያወግዘዋል፤ ይኮንነዋል። ሆኖም ራሱ አሸባሪ የሆነው ህወሃት/ኢህአዴግ የሕዝብ ቁጣ እያየለ ሲመጣ የዜናውን መንፈስ በመቀየር “አሸባሪነትን እዋጋለሁ፤ አወግዛለሁ” በማለት ቢለፍፍም ያቆሰለውንና ያደማውን የህዝብ ልብ ሊጠግን አልቻለም፤ አይችልምም!
ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን፣ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ወዘተ ያለ አንዳች ጭብጥ እና ማስረጃ እስርቤት በመወርወር አገሪቱን ወደ ከፍተኛ እስርቤትነት የቀየረው ኢህአዴግ በዚህ ተግባሩ ብቻ ሳይሆን ንጹሃንን በማሰቃየት፣ ከአገር እንዲሰደዱ በማድረግ፣ ከመኖሪያቸው በማፈናቀል፣ በመግደል፣ ወዘተ ተግባራት “ዝነኝነትን” የተረፈው ህወሃት/ኢህአዴግ በጥቅም በሚደልላቸው ጥቂቶች አማካኝነት ገጹን ለማስተካከል ቢሞክርም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት በኢዴሞክራሲያዊነቱና በመብት ረገጣው ላይ ያወጣበት ዘገባ በራሱ ምስክር ነው።
አቶ ኦባንግ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ ሰሞኑን የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ መ/ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) አራተኛ ባለሥልጣን በሆኑት ዌንዲ ሸርማን አስተያየት ዙሪ የኢትዮጵያውያን መቆጣታቸውን አስመልክቶ ሲናገሩ
“ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ፣ በሊባኖስ፣ በየመን፣ በኬኒያ፣ በማልታ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብጽ፣ በሱዳን፣ በዑጋንዳ፣ ወዘተ ከፍተኛ ስቃይ የሚደርስባቸው እንደው በአጋጣሚ አይደለም፤ ምናልባት በርካታዎች ይህንን የወገኖቻችን ሰቆቃ በተደጋጋሚ ከመስማት የተነሳ ሊሰለቻቸው ይችላል፤ ሆኖም ግን እንደ ዌንዲ ሸርማን ለጆሮ የሚከብድ ጭፍን አስተያየት ቢሰማም ግፉና መከራው ግን ለእኛ አዲስ ነገራችን አይደለም፤
“በዖጋዴን በህወሃት/ኢህአዴግ ነፍጥ አንጋቢዎች የተፈጸመው እጅግ ሰቅጣጭና ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ስልታዊ ጭፍጨፋና የወገን ምክነት፤ በ424 አኙዋኮች ላይ የተፈጸመው ግድያና ዘር ማጥፋት፤ የ1997ቱ ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባ ብቻ በ197 ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግድያ፤ ለቁጥር የሚያታክቱ ኦሮሞ ወገኖቻችን በየጊዜው መገደላቸውና እስርቤቱን ማጣበባቸው፤ በአፋር ሕዝብ ላይ የሚደርሰው የማያቋርጥ ግፍ፤ በእያንዳንዱ የአገራችን ክልል በወገናችን ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፤ ስንቱን ቆጥረን ልንዘልቀው እንችላለን። በአይሲስ ከተገደሉት አንዱ ወገናችን ህወሃት/ኢህአዴግ ኦሮሞዎችን ከአዲስ አበባ ዙሪያ በሚያፈናቅልበት ወቅት ተቃውሞውን ያሰማና የተማሪዎች መሪ የነበረ ሲሆን በዚህ ተግባሩ እንደሚታሰር በሚያውቅበት ጊዜ አገር ጥሎ የወጣ ነው። ስለዚህ እውነተኛው የአገር ውስጥ አይሲስ ህወሃት/ኢህአዴግ ካልሆነ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል በማለት ብዙዎች ለጋራ ንቅናቄያችን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ መልዕክቶች በመላክ ምሬታቸውን እየገለጹ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እየመረመርኩ ነው” በማለት በሞቱት ወገኖቻችን ላይ ሲያላግጥ የነበረው ህወሃት/ኢህአዴግ ሁኔታው አላምር ሲለው ሶስት ቀን የሃዘን አዋጅ አወጀ። ድርጊቱ የለበጣ እንደሆነ እና በግዴለሽነት የተደረገ ለመሆኑ አንዱ ማስረጃ ራሱ በተቆጣጠረው 547 ወንበር ባለው ፓርላማ ጉዳዩ ቀርቦ ሲታወጅ የተገኙት 300 አካባቢ የሚሆኑ የፓርላማ አባላት ወይም 56በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ሌሎቹ የት ሄዱ? ጉዳዩ አይመለከታቸውም? “በልማት ሥራ ተጠምደው” ነው? ሟቾቹ ወገኖቻቸው ስላልሆኑ ይሆን? ወይስ የሟቾቹ ጉዳይ በክልል የሚታይ ይሆን? ወይስ የ30 ወገኖች ህልፈት የአንድ ሟች ጠ/ሚ/ር ህልፈት ጋር የሚወዳደር አይደለም? ሕዝብ እስኪበቃው ታዝቧል፤ ጉዳዩንም መዝግቧል!!
ይህ ብቻ አይደለም ሃዘኑን እንዲገልጽ የተጠራው ሕዝብ ህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን ከእምነታቸውና ከባህላቸው ውጭ እንዴት ሃዘናቸውን መግለጽ እንዳለባቸውና ማዘን እንዳለባቸው “ንቃት” ለመስጠት የሞከረበት እንደሆነ ለማየት ችለናል። ለመለስ ዜናዊ በየመንገዱ፣ በየቱቦውና በየተገኘበት ቦታ እንዲለቀስ ፈቃድ ሲሰጥ፤ ሲደሰኮር፣ ሲተወን፣ ወዘተ አሁን ለምን ተከለከለ? ለምንስ ለቅሶ በትዕዛዝ ሆነ? ይህ በእውነት እጅግ የዘቀጠ የህወሃት/ኢህአዴግ ጸያፍ ተግባር ነው። ሰልፈኛውም ለዚህ ነው “መንግሥት የሌለው እዚህ ብቻ ነው” በማለት ምሬቱ የገለጸው፡፡
ከአገራቸው የሚሰደዱትን “ህገወጥ” በማለት ለመጥራት ምንም የማይጨንቀው ህወሃት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎችን ዜጎች አገር ጥለው እንዳይሰደዱ እንዲመክሩ ትዕዛዝ እየሰጠ እንደሆነ ተሰምቷል። ካልሆነ ቀድሞውኑ “ህገወጥ” ይላቸው እንደነበር አሁን ደግሞ ለሞታቸው ተጠያቂው ራሳቸው መሆናቸውን የሃይማኖት መሪዎች እያስጠነቀቁ እንዲነግሩ ተጽዕኖ እያደረገ ነው።
በመሠረቱ የሃይማኖት መሪዎች የዕምነታቸው ቀኖና በሚያስተምረው መሠረት ሃይማኖታቸውን መከተል እንዲችሉ ነጻነት ሊሰጣቸው ይገባል። እውነትን እንዲናገሩ፤ ግብረገብነትን ያለፍርሃት እንዲያስተምሩ፤ ሕዝቡን ሃይማኖታዊ መብቱን እንዲያስተምሩ ነጻ መሆን ይገባቸዋል። ችግሩ ያለው ህወሃት በሚከተለው እኩይና ኢግብረገባዊ ሥርዓት መሆኑን ያለፍርሃት ያመኑበትን በጨዋነት እንዲያስተምሩ፤ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሊኖር እንደሚገባ፤ ፍትሕ በሚገባ መበየን እንዳለበት፣ ፈጣሪ ሁሉንም በማያዳላ የፍርድ ወንበር ፊት እንደሚያቀርብና ቀኑን ጠብቆ ፍጹም ፍርድን እንደሚሰጥ፣ ሃብት፣ ወርቅና ዝና እንዲሁም የሃሰት እንባ በዚያ የፍርድ ቀን ሊያስጥሉ እንደማይችሉ፤ አገር ማለት ክቡር መሆኗን፤ የአባቶችና ቅድመ አያቶች አጥንትና ደም አገራችንን እንዳስከበሯት ሁሉ አሁን ጥቂቶች የሚፈነጩባት ሳትሆን የሁሉም መሆኗን፤ ብልግና፣ ዋልጌነት፣ በሥልጣን መባለግ፣ ስግብግብበት፣ ዘረኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ጥላቻ፣ ጭከና፣ ወዘተ እኩይ ተግባራት መሆናቸውን በመግለጽ ሕዝቡን ግብረገባዊነት እንዲስተምሩ ፍጹም ነጻነት ሊሰጣቸው ይገባል እንጂ የህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊሆኑ ፈጽሞ አይገባም። እስካሁንም በመሆን ራሳቸውንና ኅሊናቸውን የሸጡ የሃይማኖት መሪዎች ከዚህ እጅግ እርኩስና ጸያፍ ተግባራቸው መታቀብ፤ ካስፈለገም እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው የሰማዓትነት ጽዋ በመጠጣት አርአያ መሆን ካልቻሉም ለእውነት ሲሉ ከያዙት የኃላፊነት ቦታ በራሳቸው ፈቃድ ሊነሱ ይገባቸዋል።
ይህ ብቻ አይደለም የራሱን የሚሰነፍጥ ቁሻሻ ለመሸፈን የሚጥረው ህወሃት/ኢህአዴግ ሰው አስተላላፊዎችን ለዚህ ተግባር ለመወጀልም ይፈልጋል። አቶ ኦባንግ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ፤
“እርግጥ ነው ሰው አስተላፊዎች ራሳቸውን ለአደጋ ባጋለጡ ወገኖች ላይ የራሳቸውን ጥቅም እንደሚያሳድዱ ይታወቃል፤ ግን ዋናው የችግሩ ሥር ምንድነው? ለምንድነው ይህንን ዓይነት አደጋ እያለ እጅግ በርካታ ዜጎች ከአገራቸው አሁንም የሚሰደዱት? ህወሃት/ኢህአዴግ ችግሩን ወደሌላ ለማላከክ ከመሞከሩ በፊት ራሱን በመስታወት ሊያይ ይገባዋል፤ እንዲያውም ከአንዳንድ ዘገባዎች ለመረዳት እንደቻልነው በዚህ ዜጎችን ለአደጋና ለሞት በሚደርስ ህገወጥ የሰው ማስተላለፍ ንግድ ውስጥ የህወሃት/ኢህአዴግ ጥቅመኞች እንዳሉ ማስረጃዎች አሉ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኢህአዴግ የመረጃ አፈና ሊያደርግ ቢሞክርም በተለያዩ የዜና አቀባዮች በግልጽ እንደታየው ሕዝባችን ሐዘኑን በነቂስ በመውጣት ገልጾዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ኦባንግ ሲናገሩ፤
“ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተመለከተው መልካሙ ሳምራዊ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጎሣን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ ወዘተ ሳይመለከት መንገድ ላይ ተዘርሮ ለነበረው ወገን ሰብዓዊነት አነሳስቶት ዕርዳታውን እንደለገሠ ሁሉ የጋራ ንቅናቄያችን የማንንም ጎሣ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ሳንመለከት ዕርዳታ መለገስ በሚገባን ቦታ ሁሉ ፈቃደኝነታችንን ማሳየት እንዳለብን ያምናል፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ የታወቅን ብቻ ሳንሆን በተግባርም የምንፈጽም መሆናችንን በተደጋጋሚ እንዳሳየነው ሁሉ አሁንም በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኘው ወገን ሁሉ ከእኛ ለተለዩን ወገኖች ያሳየው የሃዘን ትብብር የሁላችንንም ስሜት የነካ ነው፤ ይህም ደግሞ ማንም የፈለገውን ያህል ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስ ቢሞክር፤ የፈለገውን ቢጥር እንደማይሳካለት ያረጋገጠ ተግባር ነው፤ ኢህአዴግም ከዚህ ሊማር የሚገባው ታላቅ ትምህርት ቢኖር ለ25 ዓመታት አፈረስኩ ብሎ ያሰበው ኢትዮጵያዊነት የተዳከመ ቢመስልም ፈጽሞ እንደማይፈርስ፤ መሠረቱም የጸና፤ አዲሱ ትውልድ እንኳን ሳይቀር በጽናት የሚጠብቀው እንደሆነ ነው። ከዚህ አንጻር የህወሃት/ኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ መርዝ እንዳልሰራ ይበልጡንም የከሰረ መሆኑን ያረጋገጠ ሃቅ ነው።
“ስለዚህ የእነዚህ ወገኖቻችን ዕልፈት ሁላችንንም በአንድነት ሊያስተሳስረን የሚገባ መሆን አለበት፤ ልዩነቶቻችንን በመከባበር የምንመለከትበትና ኢትዮጵያዊነታችን ከምንም በላይ እንደሆነ የምናሳይበት ሊሆን ያስፈልጋል፤ እንዲህ ባለው ኅብረት ለወገኖቻችን መሰደድና መከራ ማየት ምክንያት የሆነውን ሁሉ የመታገል ኃላፊነት የእያንዳንዳችን ነው፤ በየአረብ አገራትና በየቦታው በስደት እንዲሁም በሌላ ምክንያት ወገኖቻችን እስከመቼ እያለቁ ይኖራሉ? ይህንን የማስቆምና ዳግም በወገኖቻችን ላይ እንዳይደርስ የማድረግ ሃላፊነት ያለው በህወሃት/ኢህአዴግ እጅ ሳይሆን በእያንዳንዳችን ዘንድ ነው፤ መብታችን በማንም የሚሰጠን ወይም እየተቆጠበ የሚሰፈርልን ሳይሆን ስንወለድ አብሮን የተወለደና ከፈጣሪ የተሰጠን የማይገሰስ፣ የማይሻር፣ የማይለወጥ፣ የማይነካ ነው፤ ስለዚህ አስቀድመን በማንም የማይገሰሰውን መብታችንን እንወቅ ከዚያም እናስከብር ቀጥሎም በተግባር እናውለው ለሌሎችም አርአያ እንሁን” በማለት አቶ ኦባንግ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ እነዚህን ህይወታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈውንም ሆነ ከዚህ በፊት በህወሃት/ኢህአዴግ እኩይ ተግባር ህይወታቸውን ያጡትን ወገኖቻችን ሁልጊዜ ሲያስታውስ፣ ሲዘክር ይኖራል። ለቤተሰብና ወዳጆቻቸው ሁሉ ከፈጣሪ ዘንድ መጽናናትን ይመኛል። ሁልጊዜ ግን በሃዘንና በቁዘማ ብቻ አንኖርም፤ ይህ የሚያበቃበት ዘመን እንዲመጣ ከምንጊዜውም በበለጠ ይሰራል፤ አንገታችንን ደፍተን ሳይሆን አባቶቻችን ባጎናጸፉን ነጻነት እንደገና እኛም ይህንን ነጻነት ለወጪው ትውልድ የምናስተላልፍበት አዲስ ኢትዮጵያ እንድትመሠረት ተግባሩን በትጋት ማከናወኑን ይቀጥላል። ዓላማውን የሚደግፉ ሁሉ ከጎኑ እንዲቆሙ በድጋሚ ጥሪ ያቀርባል።
የሃይማኖት መሪዎች ህዝባችንን በማጽናናት ብቻ ሳይሆን ሞራሉንም ከፍ በማድረግ የሚጠበቅባችሁን ተግባር እንድትፈጽሙ የጋራ ንቅናቄያችን ጥሪ ያደርጋል። ያላችሁ ኃላፊነት በሰውና በፈጣሪ መካከል ያለ በመሆኑ በሁለቱም ተጠያቂ መሆናችሁን አውቃችሁ እውነትን በትጋት በመስበክ የህዝባችንን መንፈስ ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ አምላካዊ ግዴታ አለባችሁ። የወሰዳችሁት ስምና “ማዕረግ” የሹመት ወይም ራስን ከፍ የማድረጊያ እንዳልሆነ ከእኛ በላይ እንደምታውቁት ሁሉ ለተሰጣችሁ ስም ኑሩ! ኃላፊነታችሁ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን የምትከተሉት የተቀደሰ መጽሐፍ ተግባራዊ ምሳሌ እየሰጠ የሚያስተምር መሆኑን እንደምታውቁት ሁሉ ታሪካቸውን እንደምታነቧቸውና እንደምትሰብኳቸው የሃይማኖት አባቶች የሰማዕትነት ህይወት መኖርን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እንድትፈጽሙ የጋራ ንቅናቄያችን በጥብቅ ያሳስባል። ይህም የግድ ህይወትን መሰዋት ላይሆን ይችላል፤ መስዋዕትነት ከትንሽ የሚጀምርና በየዕለቱ የሚያጋጥም የግል ጥቅምን ከመሰዋት የሚጀምር መሆኑን በውል ትረዱታላችሁ ብለን እናምናለን። የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩት መንገድ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ድርጅት መርሃግብር ፍጹም የላቀ እንደመሆኑ የህዝባችንን የመንፈስ ልዕልና ከፍ የሚያደርገውና ከፈጣሪ ለተሰጠው መብቱ በጽናት እንዲቆም የሚያደርገው እንደሆነ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ያምናል።
ስለሆነም ሁላችንም በዚህ ሃዘን ተቆጭተን ብቻ ሳንቀር ይልቁንም በህዝባችን መካከል ሰላም ፈጣሪዎች፣ ዕርቅ መስራቾች፣ ስምምነት አድራጊዎች ሆነን በትጋት መስራት አለብን። ይህ ካልሆነ እና ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማናችንም ለብቻችን ነጻ መሆን አንችልም። መውደቃችንም ሆነ መነሳታችን እርስበርሱ የተገመደና የተሳሰረ ነው።
አሁንም በአደጋ ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን አምላክ እንዲታደጋቸው እንመኛለን፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚደርስብንን ግፍና መከራ ተመልክቶ ሰላምን እና ዕረፍትን የምናገኝበትን ዘመን ያቅርብልን። ሁላችንንም በትጋት ለመሥራት እንድንችል ጽናቱ ይስጠን።
በድጋሚ ለወገኖቻችን እና ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከፈጣሪ ዘንድ መጽናናትን እንመኝላቸዋለን።
ኢትዮጵያችን ለሁላችንም ትኑርልን!!
ለተጨማሪ መረጃ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡- Obang@solidaritymovement.org
Leave a Reply