በተለያዩ ወቅቶች የሰውን ልጅ ከእንስሳ በማሳነስ የተፈጸሙ ወንጀሎች ስለመኖራቸው መረጃዎች ይወጣሉ። በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚፈበረኩትና ሆን ተብለው እንዲሰራጩ የሚደረጉት የበሽታ መነሻዎች የክቡር ሰው ልጆችን ህይወት በሚዘገንን ሁኔታ አራግፈውታል። አባት፣ እናት፣ ልጅ፣ የልጅ ልጅ፣ አልፎ ተርፎ ትውልድ … የሰው ልጅ በሽታ ኢንቨስት ተደርጎበት፣ የሕዝብ ብዛት መቀነሻና የባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ መመራመሪያ ተደርጓል፣ አሁንም እየተደረገ ነው፤ የበሽታ ማምከኛ መሞከሪያና ማፈላለጊያ ሆኖ ኖሯል። ዛሬም እየኖረ ነው። የሌላውን አገር ሕዝብ ከህይወት በታች፤ የራሳቸውን ግን ድርብ ህይወት እንዳላቸው አድርገው የሚቆጥሩት ምዕራባውያን እንደመልካቸው ለማሳመር የሚሞክሩት ታሪካቸው ለማመን የሚያስቸግር እና ለመቀበል የሚከብድ ፍትሕ ያልተሰጠባቸው “ወንጀሎች” አካሂደዋል፤ አሁንም በረቀቀ መንገድ እያካሄዱ ነው፡፡ በዚሁ መነሻና እሳቤ ይመስላል ኢቦላን ለድሆች የቀረበ የወረርሽኝ ኢንቨስትመንት እንደሆነ አድርገው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እየተቹ ያሉት።
አጀንዳው ሰፊና ቢጎለጉሉት የማያልቅ፣ ዙሪያ ገባው ሁሉ መርገምት የሆነ ወንጀል ነው። በእኛም አገር አማራው ህዝብ ላይ የዘር ፍሬን የማምከን ጸያፍ ወንጀል ስለመፈጸሙ ማስረጃ ቀርቧል። ሰለባዎች አደባባይ ወጥተው ተናግረዋል። ድርጊቱ የተፈጸመው ቴድሮስ አድሃኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እያሉ መሆኑ እየታወቀ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ (“ተልዕኮ” አስፈጻሚ በመሆናቸው ይመስላል) ተሸላሚና ተሿሚ ለመሆን በቅተዋል። ለአማራው እንቆረቆራለን የሚሉ “የሰው ብሎች” ድርጊቱን ተቀብለው ባቃጣሪነት ለመዝለቅ መወሰናቸው ከተፈጸመው ወንጀል በላይ የሚዘገንን ይሆናል።
የአንድ መንደር ህዝብ በባዮሎጂካል መሳሪያ ተመሳጥሮ ማስጨፍጨፉ የተመሰከረበት ህወሃት ቢታጠበው የማይጸዳለት ግፍ የሚፈጽምበት የአማራ ህዝብ እንዲመክን መደረጉን የሚያሳየው ቪዲዮ ወደታች ስለሚገኝ ለአንባቢ ዕይታ ቀርቧል፡፡
ለኢቦላ “ወረርሽኝ” ወታደራዊ ዘመቻ – የአሜሪካ ምላሽ
“የላይቤሪያ መንግሥት ባቀረበልን ጥያቄ መሠረት በቀጣናው ለሚገኙ አገራት ለምናደርገው ህዝባዊ ድጋፍ ይሆን ዘንድ ባለፈው ሃይቲ በመሬት መንቀጥቀጥ በተጎዳች ጊዜ እንዳደረግነው ዓይነት ምላሽ አሁን ደግሞ በላይቤሪያ የወታደራዊ ዕዝ ማዕከል እንመሠርታለን፤ በአፍሪካ ያለንን የጦር ኃይል የሚያዙት ሜጀር ጄኔራል ዴርል ዊሊያምስ ይህንን ወታደራዊ ዕዝ የሚመሩ ይሆናሉ፤ ዛሬ እዚያው ላይቤሪያ ደርሰዋል፤ … ይህ በዓለምአቀፍ ደረጃ የደረሰ ጥቃት በመሆኑ ዓለምአቀፋዊ ምላሽ ያሻዋል፤ … የመከላከያ ኃይላችን በምድር ላይ ካሉ ድርጅቶች ሁሉ በላቀ ሁኔታ ለዚህ አገልግሎት የተዘጋጀ ነው፡፡”
አትላንታ ከተማ ጆርጂያ ጠቅላይ ግዛት በሚገኘው የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል መስከረም 6፤2007ዓም በመገኘት ይህንን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ነበሩ፡፡ ይህንንም ብለው 3ሺህ የአሜሪካ ወታደሮች ኢቦላን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአንድ ሜጀር ጄኔራል አዝማችነት ጦራቸውን ወደ ምዕራብ አፍሪካ ላኩ፡፡ ለበሽታ “ወረርሽኝ” በጦር መሣሪያ የታጀበ ወታደር “ሳንጃ መዘዘ”!
የኢቦላ በሽታ በምዕራብ አፍሪካ አገራት መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሲባል ቆይቷል፡፡ በሽታውን እንደ ወረርሽኝ ስለመነሳቱ ከሚጠራጠሩ ጀምሮ “የአሜሪካ ፈጠራ ነው” የሚሉና ከዚያም ሲያልፍ ድብቅ የጂኦፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ጉዳይ ነው እንዲሁም የባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ ነው የሚሉ በተለይ በምዕራቡ ዓለም እጅግ በርካታዎች ናቸው፡፡ ኢቦላ የሚተላለፍበት መንገድ ምን እንደሆነ (በትንፋሽ ይሁን በንክኪ) እርግጠኛ አይደለም ከሚሉ ጀምሮ፤ በሽታው በወረርሽኝ መልክ በምዕራብ አፍሪካ እየተዛመተ ባለበት ሁኔታ በተለይ የዜጎቿ ህይወት ከማንኛውም የዓለም ሕዝብ ይበልጥብኛል የምትለው አሜሪካ ከምዕራብ አፍሪካ የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችን እስካሁን አለማቋረጧ፣ ለወረርሽኝ ጦር ሠራዊት መላኳ፣ ባለፈው ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት አካባቢ የተነሳውን የመተንፈሻ በሽታ ወረርሽኝ (MERS) አስመልክቶ አሜሪካ ወደዚያ ስለሚደረጉ በረራዎች የሰጠችውን ያህል ማስጠንቀቂያ ለኢቦላ አለማድረጓ፣ … የበርካታዎች ጥያቄ ነው፡፡
የአሜሪካ መንግሥት “ዋሽቷል”!
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሥነወንጀል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄሰን ኪስነር ኢቦላን አስመልክቶ የአሜሪካ መንግሥት “ዋሽቷል” ይላሉ፡፡ በቅድሚያ የካናዳው የሕዝብ ጤና ኤጀንሲ ባደረገው ምርምር ኢቦላ በሰዎች ዘንድ በትንፋሽ የመተላለፉ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ይታመናል ብሎ ያወጣውን መረጃ ከቀናት በኋላ መቀየሩና የአሜሪካው የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከልም ይህንኑ ማስተጋባት መቀጠሉ ለምን እንዳስፈለገ ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ገና በዳላስ ቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት የኢቦላ ጉዳይ መከሰቱ ሳይታወቅ ለሥርዓተቀብር ማከናወኛ ቤቶች ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መሰጠት ያስፈለገበት ምክንያት ሌላው አጠያያቂ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ “ለጥንቃቄ” ተብሎ ነው የሚል ከሆነም የኢቦላ የሚመስሉ ምልክቶች በሳክራሜንቶ ካሊፎርኒያና በኒው ዮርክ ተከስተው በሽታው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ምንም ዓይነት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለአስከሬን ቤቶች አለመሰጠቱን ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዥነት የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም ኢቦላ ከዚህ በፊት በጭራሽ በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ አያውቅም፡፡ በፊት ተከስቶ የነበረው የኢቦላ በሽታ አሁን ከተከሰተው ጋር ሲነጻጸር የአሁኑ በተላላፊነቱ ከፍ ያለ እንደሆነ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ (እስካሁን ከ2ሺህ በላይ ተመዝግቧል) ይህ አኻዝ ከ1969-2006 ዓም ባሉት 37 ዓመታት ከኢቦላ ጋር በተያያዘ ከተመዘገበው ይልቅ ባለፉት ጥቂት ወራት የተከሰተው ይበልጣል፡፡ ከዚህም ሌላ ዶ/ር ኪስነር በቅርቡ የታተመ የህክምና ጆርናል (New England Journal of Medicine in April 2014) በመጥቀስ ሰሞኑን የተከሰተውና በዓይነቱ ለየት ያለው ኢቦላ ከዚህ በፊት በኮንጎ እና ጋቦን ከተከሰተው የተለየ ብቻ ሳይሆን አሁን እንደሚባለው ክስተቱ የሆነው ባለፈው ሰኔ/ሐምሌ ሳይሆን በሚያዚያ እንዲያም ሲል በታህሳስ 2006 ዓም ታይቷል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ እንደከዚህ በፊቱ የማዕከላዊ አፍሪካ አገራት የኢቦላ ክስተት ጋር የመመሳሰል ሁኔታ ስለማይታይበት (የአሁኑ የመተላለፍ ሁኔታ ከፍተኛ ነው) ኢቦላ ምዕራብ አፍሪካ እንዴት እንደደረሰ ማንም መናገር አለመቻሉን ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህ ሁሉ “ውሸቶች” በተጨማሪ ለኢቦላ በሽታ የሚሰጠው ZMapp የተሰኘው መድሃኒት ከዚህ በፊት ተሰምቶ በማይታወቅ ነገርግን ከአሜሪካው የመከላከያ መ/ቤት ጋር ቅርብ ግንኙነት ባለው ድርጅት መፈብረኩ እንዲያም ሲል መድሃኒቱ በውጭ ለሚገኙ የአሜሪካ የዕርዳታ ሠራተኞች እንዲሰጥ ያዘዘው አካል ማን እንደሆነ የተምታታ መረጃ መነገሩ (በአብዛኛው የአሜሪካ መንግሥት መድሃኒቱ እንዲፈበረክና እንዲሰጥ አዝዟ የሚለው መረጃ ተዓማኒነት አለው) ከሕዝብ የተደበቀ ሌላው ውሸት እንደሆነ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሚያቀርቡት መረጃ መሠረት መድሃኒቱ በሁለት የመድሃኒት ፋብሪካዎች እንዲሁም በአሜሪካና ካናዳ መንግሥታት የጤና ጥበቃዎች ተባባሪነት በጥር ወር 2006ዓም አካባቢ እንደተፈበረከ የራሱ የድርጅቱ መግለጫ ያሳያል፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአሜሪካና የካናዳ ጤና ጥበቃዎች “ኢቦላ በሰዎች ዘንድ በትንፋሽ የመተላለፉ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ይታመናል” የሚለውን ሳይንሳዊ ማስረጃቸውን መቀየራቸው አይዘነጋም፡፡ ስለሆነም ZMapp በመድሃኒትነት ከመዋሉ በፊት ቢያንስ በሽታው ከጥር ወር አስቀድሞ (በታህሳስ አካባቢ) ተከስቷል ለማለት ያስገድዳል፡፡ እዚህ ላይ የሰሞኑ ኢቦላ ከዚህ ቀደም ከተከሰቱት የኢቦላ ዓይነቶች የተለየ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ዶ/ር ኪስነር እነዚህንና ሌሎች ማስረጃዎችን በመጥቀስ የአሜሪካ መንግሥት ኢቦላን በተመለከተ የራሱን ዜጎችንም ሆነ ሌሎችን ዋሽቷል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በሽታው እንደ ሌሎች በሽታዎች የተከሰተ ሳይሆን ምናልባትም ለፖለቲካዊና ሌሎች ጥቅሞች ሲባል በቤተሙከራ የተፈጠረ ሰው ሰራሽ ነው በማለት ለሚከራከሩ ደጋፊ ሆኖ ይቀርባል፡፡
ኢቦላ – የቤተሙከራ በሽታ?
በይፋ በመገናኛ ብዙሃን እንደሚነገረው ሳይሆን ኢቦላ በቤተሙከራ የተፈጠረ በሽታ ነው ብለው የሚያምኑ የጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች አሉ፡፡ ለድርጊቱም አሜሪካንን በኃላፊነት ይጠቅሳሉ፡፡ ቀድሞ የላይቤሪያ ዩኒቨርሲቲ መምህርንና ሳይንቲስት የሆኑት ዶ/ር ሲርል ብሮዴሪክ በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ በሽታ አሜሪካንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በአገራቸው በሚታተመው ዴይሊ ኦብዘርቨር ላይ እንደጻፉት ኢቦላ በሰዎች ላይ እንዲሞከር የአሜሪካው የመከላከያ መ/ቤት በጀት እንደመደበ ይናገራሉ፡፡ ሙከራውም ኢቦላ በሴራሊዮንና ጊኒ ተከሰተ ከመባሉ ጥቂት ሳምንታት በፊት እንደተጀመረ ያስረዳሉ፡፡ ሲቀጥሉም በኢቦላ ላይ ምርምር እንዲደረግ ቴክሚራ ከተባለ የካናዳ መድሃኒት ፋብሪካ ጋር የአሜሪካው መከላከያ ሚ/ር በ140 ሚሊዮን ዶላር መስማማቱን እና በምርምሩም መሠረት ለጤነኛ ሰዎች ገዳዩን የኢቦላ ቫይረስ በመውጋት የመድሃኒት መሞከሪያ (ጊኒፒግ) ማድረግ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ምርምሩ በመጋቢት ወር የኢቦላ ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪካ ተከሰተ ከመባሉ በፊት በጥር ወር 2006ዓም እንደተጀመረም ይናገራሉ፡፡
ተዛማጅነት ባላቸው ጽሁፎችም “ኢቦላ ተከሰተ” በሚባልባቸው ቦታዎች የምዕራብ አገራት ታዋቂ ድርጅቶች ምን እንደሚያደርጉ የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እነዚህም፡- በባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ ምርምር ተቋምነት የሚታወቀው የአሜሪካ የጦር ምርምር የተላላፊ በሽታዎች ተቋም፣ ከብሔራዊው የጤና ተቋም ለምርምር ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያገኘው ቱሌን ዩኒቨርሲቲ፣ ድንበር የለሽ ሃኪሞች፣ የብሪታኒያው ግላስኮስሚዝክላይን፣ … የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዶ/ር ብሮዴሪክ ሲናገሩ የአሜሪካ መንግሥት በሴራሊዮን ኬኔማ በተባለ ቦታ የምርምር ቤተሙከራ (ላቦራቶሪ) እንዳላት ይጠቁማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ቦታ ላይ “ተላላፊ የትኩሳት ባዮአሸባሪነት” በሽታ እንደሚጠና በመጥቀስ ይህ ቦታ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት መካከል የኢቦላ በሽታ ለየት ባለ ሁኔታ የታየበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ አገራት መሪዎችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በተለይ የአፍሪካ ህጻናትን፣ አዛውንቶችን፣ ደጋፊ አልባ ምስኪኖችን፣ … ከምዕራባውያን ጋር በማበር ዜጎቻቸውን የመድሃኒት መሞከሪያ ከማድረግ እንዲታቀቡ፤ የሚያደርጉትን ነገር በሙሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለሕዝባቸው እንዲጠቅም እንዲያደርጉ ዶ/ር ብሮዴሪክ ተማጽነዋል፡፡
አሜሪካ ባለፉት በርካታ ዓመታት በአገሯና በውጭ ተመሳሳይ ሙከራ ማድረጓን የሚጠቅሱ ወገኖች ከላይ የተሰጠውን የዶ/ር ብሮዴሪክን ገለጻ በቀላሉ አይመለከቱትም፤ ተራ ፕሮፓጋንዳ ወይም የሴራ ንድፈሃሳብ (ኮንስፒራሲ ቲዎሪ) በማለት አያጣጥሉትም፡፡
የታስኪጊ ቂጥኝ ምርመራ
በ20ኛው ክፍለዘመን መግቢያ አካባቢ ከኦስሎ ኖርዌይ የሕክምና ተቋም ሳይታከም የቆየ የቂጥኝ በሽታን አስመልክቶ የወጣው ዘገባ በአሜሪካ ያሉትን ተመራማሪዎች ቀልብ የሳበ ሆነ፡፡ በምርምሩ ዘገባ መሠረት ህክምና ሳያገኝ የቆየ የቂጥኝ በሽታ በነጮች ላይ የሚያሳየው ሁኔታ በጥቁሮች ላይ ከሚያሳየው የተለየ ይሆናል የሚል ግንዛቤ የወሰደ በመሆኑ በአሜሪካ በሚገኙ ጥቁር የበሽታው ተጠቂዎች ላይ ምርምር ቢካሄድ የተለየ መረጃ የሚያሳይ መሆኑን ግምት ተወሰደ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የሚቆጣጠራቸው የጤና ጥበቃና የበሽታ መቆጣጠሪያ ተቋማት ከሮዝንዋልድ ተቋም ባገኙ ገንዘብ በጥቁር አሜሪካውያኑ ላይ እኤአ በ1932 ዓም ምርምር ጀመሩ፡፡
በወቅቱ በአሜሪካ የቂጥኝ በሽታ ከተስፋፋባቸው ወረዳዎች መካከል አምስት ተመረጡ፤ ከእነዚህም መካከል ወደ 40በመቶ የሚሆነው ጥቁር የበሽታው ተጠቂ የሆነበት በአላባማ ጠቅላይ ግዛት የሜኮን ወረዳ ታስኪጊ ዋንኛውን ምርምር የማድረጊያ ቦታ ሆነች – በዚህም በአጸያፊነቱ የሚጠቀሰው ይህ ምርምር “በህያው የሰው ልጅ ላይ የተደረገ የታስኪጊ የቂጥኝ ሙከራ” ተብሎ የሚጠራው ተጀመረ፡፡ ከ1924 – 1964 (እኤአ ከ1932-1972) ባሉት አርባ ዓመታት ምርምሩ በተካሄደበት ጊዜ ለጥናቱ 600 ድሃ ጭሰኛ ወንድ ጥቁሮች የተመረጡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 399ኙ በበሽታው የተጠቁና 201 ደግሞ በሽታው ከዚህ በፊት ያልያዛቸው ነበሩ፡፡ ግለሰቦቹ ህክምና የሚሰጣቸው መስሏቸው በምርምሩ የተሳተፉ ሲሆን በወቅቱ ነጻ የህክምና ዕርዳታ፣ ነጻ ምግብ፣ በነጻ የመቀበሪያ መድህን በሚል “አበል” ተለግሶላቸዋል፤ ለበሽታው ማዳኛ የሚሆን ህክምና ግን አልተደረገላቸውም፡፡ ምርምሩ በተካሄደባቸው ዓመታት ሁሉ የቂጥኝ በሽታ ምርምር አየተካሄደባቸው እንደነበር ሳይገለጽላቸው ነገር ግን “መጥፎ ደም” ስላላቸው ለዚያ እየታከሙ እንደሆነ ነበር የተነገራቸው፡፡ ይህ “መጥፎ ደም” የሚለው መጠሪያ ደግሞ በወቅቱ ለሌሎች በሽታዎችም እንደሚውል በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ይናገራሉ፡፡
ምርምሩ በተካሄደባቸው ዓመታት በበጀት ማጠርና በወቅቱ በተካሄደው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት እየተስተጓጎለ ቢሄድም ሰዎችን እንደ በሽታ መሞከሪያ አድርጎ መጠቀም ኢሰብዓዊ ነው በሚል ጩኸታቸውን ያሰሙ ነበሩ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ለጉዳዩ ዝምታን መርጦ በመጨረሻ ላይ የቀረበ የምርመራ ዘገባ መንግሥት ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት በማሳሰብ በወቅቱ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ክሊንተንን ጠየቀ፡፡ በኋላም ግንቦት 8 ቀን 1989 ዓም (ሜይ 16፤1997) ክሊንተን በነጩ ቤታቸው ባደረጉት ስነሥርዓት በይፋ ይቅርታ ጠየቁ፡፡ በህይወት እያሉ ምርምር ሲደረግባቸው ከነበሩት መካከል የተረፉት ስምንት ብቻ የነበሩ ሲሆን ከእነርሱም መካከል አምስቱ በስነሥርዓቱ ላይ ተገኙ፡፡ ፕሬዚዳንቱም እንዲህ አሉ፡- ወደኋላ ሄደን የተፈጸመባችሁን እንዳይፈጸም ማድረግ አንችልም፤ ዝምታውን ግን ማቆም እንችላለን፤ አሁን ዓይናችሁን እያየን በአሜሪካ ሕዝብ ስም የአሜሪካ መንግሥት ያደረገባችሁን አሳፋሪ ተግባር በመናገር ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ … የፌዴራል መንግሥት ይህንን ዓይነቱን በዘር ላይ የተመሠረተ ጥናት በጥቁር አሜሪካውያን ዜጎቻችን ላይ በማድረጉ አዝናለሁ፤ … ይቅርታ እንጠይቃለን፤ እናንተ ደግሞ ይቅርታ የማድረግ ኃይል አላችሁ፤ ከዓመታት በፈት መንግሥታችሁ ካደረሰባችሁ ይልቅ የተሻለው መንገድ ምን መሆን እንዳለበት ዛሬ እዚህ በመገኘታችሁ አሳይታችኋል፤ የይቅርታን ኃይል ለራሳችሁ ይዛችሁ አላስቀራችሁትም፤ (ይፋ አድርጋችሁታል)፤ አሁን ያለው እያንዳንዱ አሜሪካዊና መጪው ትውልድ የእናንተን ትምህርት ማስታወስ ይኖርበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እንደ እንስሳ የበሽታ ሙከራ ከተደረገባቸው መካከል በህይወት ኖረው በሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት በወቅቱ በዘጠናዎቹ አጋማሽ የነበሩት ኸርማን ሾው ያለፈውን ህይወታቸውን በማስታወስ እንዲህ አሉ፤ “እርግጥ ነው የደረሰብንን ቁስል ወደኋላ ሄዶ እንዳልተደረገ ማድረግ አይቻልም፤ አለአግባብ በደል ተፈጽሞብናል፤ እንደ እንስሳ መድሃኒት መሞከሪያ (ጊኒፒግ) ተደርገናል፤ … ነገርግን በእኔ አመለካከት፣ እምነትን እና መተማመንን እንደገና ለማስፈን አሁንም የዘገየን አይመስለኝም” በማለት የይቅርታን ኃይል በማሳየት የወደፊት ትውልድ ከዚህ እንዲማር ቋሚ መዘክር እንዲኖር አሳሰቡ፡፡
በታስኪጊው ምክንያት ጥቁር አሜሪካውያን በአገራቸው በሚካሄደው የጤና አጠባበቅ ላይ የሚሰነዝሩት በርካታ ጥያቄ ግን እስካሁንም እንዳለ ነው፤ በዚህ ኢሰብዓዊ ምርምር ምክንያት በአሜሪካ የጤና አጠባበቅ ላይ ጥቁር አሜሪካውያን አሁንም ጥርጣሬ አላቸው የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ የታስኪጊው ምርምር በወቅቱ ሲጠናቀቅ በጥናቱ ያልተሳተፉ ግን ምርምሩ ከተካሄደባቸው ወንዶች ሌላ 22 ሚስቶች፣ 17 ልጆች እና 2 የልጅ ልጆች የቂጥኝ በሽታ እንዳለባቸው ታውቋል፡፡
ታስኪጊ በጓቴማላ
በታስኪጊው ምርምር ከተሳተፉት ሐኪሞች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ጆን ከትለር ከአሜሪካ ውጭ በሌላ አገር እጅግ አስከፊ ምርምር ማድረጋቸው የታስኪጊውን ሰቆቃ ሲያጠኑ የነበሩት የሕክምና ታሪክ ተማራማሪዋ ዶ/ር ሱዛን ሪቨርቢ በቅርቡ ይደርሱበታል፡፡ ምርምሩ የተካሄደው በአሜሪካ መንግሥት ጠያቂነት እና በጓቴማላ መንግሥት ተባባሪነት እንዲሁም በጓቴማላ የጤና ጥበቃ ሚ/ር አስተባባሪነት ነበር፡፡ የምርምሩ ዋና ዓላማ ለቂጥኝ በሽታ የሚሰጠው ፔኒሲሊን በቂጥኝና በሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ላይ ያለው ብቃት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ነበር፡፡ 1,500 ጓቴማላውያን ለዚህ ምርምር መጠቀሚያነት ውለዋል፡፡ ለሰለባዎቹ የሚከራከሩ ጠበቃዎች ግን ቁጥሩ እስከ አምስት ሺህ እንደሚደርስና እስከ ስድስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው በህጻናት ማሳደጊያ የሚገኙ ዕጓለ ማውታን ለምርምሩ መጠቀሚያ ተደርገዋል በማለት ይከራከራሉ፡፡
እንደ ታስኪጊው የጓቴማላው የሰው ላይ በሽታ ሙከራ ለበርካታ ዓመታት የተካሄደ አልነበረም፡፡ እኤአ ከ1946 – 1948 ለሁለት ዓመታት ብቻ የተካሄደ ቢሆንም በአሰቃቂነቱና በዘግናኝነቱ ግን ከታስኪጊው እጅግ የላቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ለምርምሩ መገልገያነት የተደረጉት ጓቴማላውያን ከዚህ በፊት በበሽታው ያልተለከፉ ነገር ግን እነርሱ ሳያውቁትና ሳይፈቅዱ በቂጥኝ፣ ጨብጥና ሌሎች አባላዘር በሽታዎች እንዲለከፉ የተደረጉ ናቸው፡፡ በሽታውን ለማስተላለፍና ምርምሩን ለማካሄድ በቅድሚያ የተመረጡት ሴተኛ አዳሪዎች ሲሆኑ እነርሱም ለእስረኞች፣ ለወታደሮች፣ በአእምሮ ሆስፒታል ለሚገኙ የአእምሮ በሽተኛ ታካሚ እስረኞች በሽታውን እንዲያስተላልፉ ተደርጓል፡፡ ሴተኛ አዳሪዎቹ በሽታውን ማስተላለፍ ባልተቻሉበት ሁኔታ ደግሞ በእስረኞቹ የቆሰሉ ብልቶች እንዲሁም እጅና ፊት ላይ የበሽታው ባክቴሪያ እንዲፈስ በማድረግ ይህም ካልሆነ የአከርካሪ አጥንታቸውን በመብጣት በበሽታው እንዲለከፉ መደረጉ ታውቋል፡፡
ምርምሩን ለማድረግ የአሜሪካው ብሔራዊ የጤና ተቋም እንዲሁም የፓን አሜሪካ የጤና ቢሮ የግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ ገንዘብ የተጠቀሙ ሲሆን በርካታ የጓቴማላ መንግሥት ሚ/ር መ/ቤቶች ተሳትፈውበታል፡፡ መጠቀሚያዎቹ ሰብዓዊ ፍጡራን በበሸታው እንደተያዙ ሲረጋገጥ አንቲባዮቲክስ እንዲሰጣቸው የተደረገ ቢሆንም የበሽታውን አካሄድ ለማወቅ እንዲያስችል በበቂ ሁኔታ እንዳልታከሙ በዚህም ምክንያት የሞቱ እንዳሉ ይነገራል፡፡
ምርምሩ ግን ከሁለት ዓመት በላይ አልዘለቀም፡፡ በወቅቱ በህክምናው መንደር የተነዛው “ሐሜት” አንዱ ምክንያት ሲሆን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የፔኒሲሊን አቅርቦት እያነሰ እንዲሁም ዋጋው ከፍ እያለ መምጣት በተጨማሪ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
የታስኪጊውን ሰቆቃ እየተመራመሩ የነበሩት ዶ/ር ሱዛን ሪቨርቢ በመካከል ሌላ ማመን ያልቻሉትን ሰነድ በመዝገብ ቤት ውስጥ ያገኛሉ፤ ዓመቱ እኤአ 2009ዓም ነበር፡፡ ይህንን ሰነድና ሌሎችን ሲመረምሩም የጓቴማላውን የቂጥኝ በሽታ ሰቆቃ እና በሰው ልጅ ላይ የተደረገውን እጅግ ጸያፍ ተግባር ይደርሱበታል፡፡ ጉዳዩንም ይፋ ያወጣሉ፡፡ የኦባማ አስተዳደርም ተናወጠ!
በ2010 ዓም ማለትም አሰቃቂው ምርምር ከተካሄደ 62 ዓመታት በኋላ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት የለመዱትን ይቅርታ ለመጠየቅ መጣደፍ ያዙ፡፡ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የነበሩት ሒላሪ ክሊንተንና የጤና ጥበቃዋ ካተሊን ሲቤሊየስ በወቅቱ የጓቴማላ ፕሬዚዳንት ለነበሩት አላቫሮ ኮሎም ስልክ ደውለው በሁኔታው “እጅግ ተቆጥተናል፣ ሁኔታው እንዴት ሊደርስ እንደቻለ አናውቅም፤ አዝነናል፣ …” አሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማም በፊናቸው “አዝኛለሁ፣ ተቆጥቻለሁ፣ …” በማለት አሜሪካ ይቅርታ እንደምትጠይቅ ተናገሩ፡፡ ጉዳዩ እንዲጠና ትዕዛዝ ሰጥቻለሁም አሉ፡፡
ማርታ ኦሪላና ይባላሉ፡፡ የ74 ዓመት አዛውንት ናቸው፤ የልጅ ልጅ አይተዋል፡፡ አሜሪካ በጓቴማላ በቂጥኝ ላይ ባደረገችው ምርምር ያለፈቃዳቸው በሽታው ተሰጥቷቸው ለከፍተኛ ስቃይ ተዳርገዋል፡፡ በሽታውን ሲወጉ የዘጠኝ ዓመት ልጅ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ የቀረውን እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡፡ “(የዛሬ 68ዓመት) በእጓለ ማውታን ውስጥ ካሉት እኩዮቼ ጋር ውጭ ስንጫወት ነበር፤ ወዲያው “ማርታ ወደ መታከሚያ ክፍል ትፈለጊያለሽ!” ተብዬ ተጠራሁ፤ ስደርስ ሃኪሞች እየጠበቁኝ ነበር፤ አንዱ በእንግሊዝኛ የሚናገር ረጅም እንዲሁም ጓቴማላዊ ሐኪም እና ሌሎች ነበሩ፤ መርፌ እና ትንንሽ ብልቃጦች ይዘዋል፤ ተኚ ተባልኩ፤ እግርሽን ክፈቺ ተባልኩ፤ አፍሬ ስለነበር እግሮቼን ቆልፌ ጭንቅላቴን ቀበርኩ፤ እምቢ አልኩ፤ ከጓቴማላ ሐኪሞች አንዱ በጥፊ መታኝ፤ ከዚያ አድርጊ የተባልኩትን አደረኩኝ፤ ምን እንደሚያደርጉብኝ አላውቅም፤ እምቢ የማለት መብትም አልነበረኝም፤ እስካሁን የተሸከምኩት ሕመም፣ ውርደትና ሰቆቃ ማንም አያውቀውም፤ እነርሱን ግን እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው፡፡”
በምርምሩ ሰለባ የሆኑትን ስንት እንደሆኑና በሽታው እስከምን ድረስ የቤተሰባቸውን አባላት (ልጆች፣ ልጅ ልጆች፣ …) እንዳጠቃ የሚናገር በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በብዙ ሺዎች ግን እስካሁን እየተሰቃዩ እና እየሞቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ቂጥኝ ተላላፊ በሽታ ሲሆን የብልት አካባቢዎችን የሚያቆስል ነው፡፡ በቂ ህክምና ካልተደረገ ሰውነትን ሽባ ያደርጋል፣ ዕውርነት ያስከትላል፣ እስከ ሞት ለሚያደርስ ሌሎች እጅግ ውስብስብ ለሆኑ የጤና ችግሮችም ያጋልጣል፡፡
ቅድሚያ ለኢቦላ ወይስ ለነዳጅ?
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ተራማጅ አመለካከት ለነበራቸው በርካታ አሜሪካውያን ተስፋ በመስጠት የብዙ ምሁራንን ቀልብ ስበው ነበር፡፡ ጦርነቶችን በማስቆም፣ ሰላም በማስፈን፣ የሕግ የበላይነት በማስከበር፣ … ምሳሌ ይሆናሉ ተብለው በሚጠበቁበት ወቅት ሥልጣናቸውን እንደያዙ ብዙም ሳይቆዩ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሆኑ፡፡ በሽልማቱ ያልተደሰቱ አምርረውም የተቃወሙ ቢኖሩም ወደፊት ስለሚመሩት የሰላም አስተዳደር መልካም ተነሳሽነት ይኖረዋል በሚል ተስፋ የተከራከሩላቸው ግን ጥቂት አይደሉም፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለው የኦባማን አስተዳደር የሚገመግሙ ግን ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አስከፊ ጦርነቶችን ያካሄዱ በንጽጽርም ጆርጅ ቡሽና ዲክ ቼይኒ ካስከተሉት ውድመት በልጠው እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ከንቱ የሰላም ኖቤል ሎሬት!
ኖቤል ሰርቲፊኬታቸው ላይ የሰፈረው ቀለም ገና ሳይደርቅ ፕሬዚዳንት ኦባማ በጦርነት ተጠመዱ፡፡ አፍጋኒስታን ተጨማሪ ጦር አዘመቱ፣ በኢራቅ ሌላ ውጊያ ጀመሩ፣ ጥቂት ዘግየት ብለው ደግሞ በሊቢያ ጋዳፊን ጦር ገጠሙ፤ በሊቢያ የፈሰሰው ደም ገና ሳይደርቅ ባሽር አል አሳድን ከሥልጣን ለማስወገድ ሶሪያን የማያባራ ጦርነት ውስጥ ከተቱ፡፡ እነዚህ ሁሉ በዩክሬን አሁን ደግሞ ከአይሲስ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ደም መፋሰስ ሳይጨምር ነው፡፡ “አሁን ያለው አዲስ ዕቅድ” ይላሉ በዓለምአቀፍ ግንኙነት ታዋቂ ባለሙያ የሆኑት ኤፍ ዊሊያም ኢንግዳል “የኦባማ አማካሪዎች ደም በጠማቸው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሱዛን ራይስ እየተመሩ አዲስ ጦርነት ከፍተዋል – ይህም የጸረ ኢቦላ ዘመቻ ነው” ይላሉ፡፡
ከላይ በተጠቀሰው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ እንደሰፈረው የኢቦላን በሽታ አሜሪካ በቀላሉ የምትመለከተው እንዳልሆነ እና የጦር ሠራዊት ለማዝመት መገደዷ ተገልጾዋል፡፡ ለዚህም 3ሺህ ወታደር አዝምታለች፡፡ ለበሽታ ወታደር ለመላክ ለምን እንዳስፈለገ ግራ የገባቸው አንዳንዶች አንዳሉት ከሆነ “ምናልባት ወታደሮቹ የኢቦላን ቫይረስ እያሳደዱ እንዲገድሉ ይሆን ያስፈለጉት?” በማለት ይሳለቃሉ፡፡
የኢቦላ ስርጭትም ይሁን አካሄድ እንዴት እንደሆነ እርግጠኛ በሆነ ሁኔታ ገና ሳይታወቅ የመድሃኒት ፋብሪካዎች ገና በቅጡ ያልተሞከረ “የኢቦላ ክትባት” ይዘው ብቅ ማለታቸው “ለጤና” ነው ወይስ የብሪቱ ነገር ደውላባቸው ነው አሰኝቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ “መዓት መጣ” በሚል የዓለም የጤና ድርጅት ሃላፊዎች “የክትባት ውሰዱ” ዘመቻ መጀመራቸው በተለይ በሽታው በስፋት ታየባቸው በተባሉት ጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን አካባቢ የሚገኙ የጤና ሠራተኞች መከተብ እንዳለባቸው ገና ከጅምሩ ማሳሰባቸው አጠያያቂ እንደሆነ ዊሊያም ኢንግዳል ይናገራሉ፡፡ ሲቀጥሉም ይኸው ድርጅት ከዚህ በፊት “የአሣማ ጉንፋን” ገባ በማለት ያስነጠሰው፣ ያሳለው፣ ያናፈጠው፣ ትን ብሎት ያሳለው፣ ያቀረሸው፣ … ሁሉ “የአሣማ ጉንፋን ተጠቂ ነው” በሚል ድርጅቱ የበሽታውን ትርጓሜው ቀይሮ በርካታ ህዝብ በማሸበር የአሜሪካ እና የአውሮጳ መድሃኒት አምራቾች ኪስ እንዲዳብር ማስደረጉን ብዙዎች የሚያስታውሱት ጉዳይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አሁንም ይኸው በኢቦላ ላይ እየተደረገ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው ከሆነ የዓለም የጤና ድርጅት መዘገብኩ የሚላቸው 62 በመቶ የሚሆኑት የኢቦላ ተጠቂዎች የደም ናሙናቸው ተወስዶ በበሽታው ተለካፊ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ እንደሌለ ተናግሯል፡፡ የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ባለሥልጣን የሆኑት ዶ/ር ማርግሬት ቻን “የኢቦላ ቫይረስን (በሽታን) ከሌሎች እንደ ወባ በሽታ፣ የተስቦ ትኩሳት እና ጆሮ ደግፍ ከመሳሰሉት በቀላሉ ለመለየት እንደማይቻል” በተናገሩት መሠረት ከ69 በመቶ በላይ ኢቦላ ነው ተብለው የተዘገቡት በሙሉ በቅጡ ምርመራ ተደርጎባቸው ያልተረጋገጡ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ አነጋገር በላይቤሪያ በሺዎች ሞቱ ተብሎ የተዘገበው በእርግጥ በኢቦላ ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ የማይቻል መሆኑን ዊሊያም ኢንግዳል ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “የኢቦላ ወረርሽኝ ተነሳ” የተባለባቸው አገራት በነዳጅና በአልማዝ የከበሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ኢቦላ ሳይሆን ነዳጅ ዘይት ነው ወደሚል ድምዳሜ እንዲደረስ እንደሚገፋፋ አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ኢቦላ ተከሰተ የተባለባቸው አገራት ከከበሩ ማዕድናት በተጨማሪ እነስካሁን ምንም ባልተነካ የነዳጅ ዘይት ክምችት የበለጸጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዶ/ር ዴቪድ ሺን “ሶስት የአፍሪካ ነዳጅ አቅራቢዎች” በሚል በጻፉት ላይ ቻይና የበርካታ አፍሪካ አገራትን የነዳጅ ዘይት እየተቆጣጠረች እንደሆነች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ የቻይና በአፍሪካ መንሰራፋት አሜሪካንን እና ምዕራባውያንን በእጅጉ ያስደሰተ አይደለም፡፡ የአሜሪካ መከላከያ ሚ/ር የአፍሪኮም የዕዝ ማዕከል በአፍሪካ ያቋቋመበት አንዱ ዓላማም ቻይናን በቅርብ ርቀት ከመቆጣጠር አንስቶ እስከ ፕሮጀክቶቿን ማምከን አንደሚዘልቅ አስተያየት የሚሰጥበት ነው፡፡
“ነዳጅ ዘይትን የሚቆጣጠር አገራትን በሙሉ ይቆጣጠራል” በማለት የቀድሞ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር እንደገለጹት የነዳጅ ዘይት ጉዳይ በቸልታ የሚታይ አይደለም፡፡ ኪሲንጀር በነዳጅ ዘይት ዙሪያ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ በተለይ የሶስተኛውን ዓለም የሕዝብ ቅነሳ ላይ ከፍተኛ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አስተያየት መስጠታቸው ይነገራል፡፡ ይህ ከአስተያየት ያለፈ የኪሲንጀር ሃሳብ የእነርሱ ህይወት ከሌላው ይበልጣል ብለው የሚያስቡ ሁሉ የሚጋሩት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የማዕድን ሃብት ግብዓትን ይፈልጋል ለዚህም ደግሞ ያላደጉ አገራት የሚሰጡት “አገልግሎት” ቀላል እንዳልሆነ የሚታመንበት ነው፡፡
የአፍሪካ የነዳጅ ዘይት ምርት እኤአ ከ2002 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት በ91 በመቶ እንደሚመነደግ የአሜሪካው የኃይል ሚ/ር ትንበያ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ አኻዝ አብዛኛው አቅርቦት የሚገኘው በአሁኑ ወቅት የኢቦላ ወረርሽኝ ተነሳ በተባለበት አካባቢ ነው፡፡ የቻይና የነዳጅ ኩባንያዎች እንደ በሌላው የአፍሪካ አገራት እንደሚያደርጉት በምዕራብ አፍሪካ አቅጣጫም ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ካሁኑ መላ ካልተፈለገላቸው የወደፊቱን ለመገመት አዳጋች የሚሆንበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በሚገኙ አጋጣሚዎች ጦር ማዝመትና የቻይናን አንቅስቃሴ ራዳር ውስጥ ማስገባት ወሳኝነት ያለው ጉዳይ እንደሆነ ምዕራባውያን የሚያጡት አይደለም፡፡
ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ጊኒ የሚያያዙበት ሌላው ገመድ ደግሞ የቀድሞ የላይቤሪያ መሪ የነበሩት ቻርልስ ቴይለር ናቸው፡፡ ላይቤሪያን አውድመው፣ ሴራሊዮንን አጋይተው አሁን በእስር የሚገኙት ቴይለር የጀመሩት ጦርነት በጎረቤት ጊኒም ፈልሷል፡፡ ከሁለቱም አገራት በተለይ በቅርቡ ደግሞ ከሴራሊዮን እየፈለሱ ድንበር ያቋረጡት ስደተኞች ጊኒን ማጨናነቃቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ በሴራሊዮን ተነሳ የተባለው በሽታ ድንገት ወደ ጊኒ ቢፈልስ የሚያስደንቅ ሊሆን አይገባም፡፡ ምክንያቱም በፖለቲካው ዓለም ያለምክንያት የሚሆን ነገር የለምና፤ ፖለቲካ ሳይንስ ነው፤ ሳይንስ ደግሞ በመላ ሳይሆን በዕቅድና በአመክንዮ የሚመራ ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ ትንተና በሌላ መልኩ “ኢቦላ ለሕዝብ ቅነሳ ሆን ተብሎ የተፈበረከ በሽታ ነው” በሚለው አመለካከት የማይስማሙ አሉ፡፡ እነዚሁ ወገኖች በቀን በሺዎች የሚቆጠሩ በሚወለዱባት አፍሪካ በቀን ቁጥራቸው ሁለት መቶ ያልሞላ ሰዎችን በኢቦላ እየገደሉ ሕዝቡን ለመቀነስ ማሰብ ዘበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህንን የሚቃወሙ ግን በሽታው በፍጥነት እየተዛባ የሚሄድበትንና በርካታዎችን ቶሎ የሚገድልበት ኃይል ጥናት እየተደረገበት ያለበት ደረጃ ላይ ስለሆነ አሁን ይህንን መናገር እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም በተገኘው አጋጣሚ ለአሜሪካና ምዕራባውያን ወታደራዊ የበላይነትን ማስፈን እና ሌሎች ተግባራትን በተጓዳኝ መፈጸም አማራጭ የሌለው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለሆነም “ቦኮ ሃራምን” ተከትሎ በርካታ ጦር ወደ ናይጄሪያ ለመላክ ዓለምአቀፍ ድጋፍ ያላገኘችው አሜሪካ አሁን ጥሩ ምክንያት እንዳገኘች እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ ቦኮ ሃራም አሜሪካና ኔቶ ጋዳፊን ለመጣል ለምድር ውጊያ ያስታጠቁት ኃይል እንዳልሆነ ሁሉ ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ እርሱን አስወግዶ ሌላ ዓላማ ለማሳካት መሞከር አዲሱ አካሄድ እንደሆነ አስተያየት ይሰጣል፡፡ በርካታ ሙስሊም ባለባት ናይጄሪያ አሜሪካ በተደጋጋሚ የጦር ኃይሏን ለመላክ ብትሞክርም ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ ከመግዛት በስተቀር ናይጄሪያ እስካሁን በሯን አልከፈተችም፡፡ አፍሪኮምም እስካሁን በአፍሪካ ምድር ማረፊያ ማግኘት አቅቶት ለአፍሪካ የተቋቋመው ዕዝ በአውሮጳ (ጀርመን) ከትሟል፡፡
ከዚህ ሌላ ደግሞ ሴራሊዮን በዓለም የአልማዝ ምርት ቀዳሚ ነች፡፡ ማዕድን ቆፋሪዎች የሚደርስባቸውን አሰቃቂ የሥራ ሁኔታዎች በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ ሲመቱ ቆይተዋል፤ ወራትንም አስቆጥረዋል፡፡ ከአፍሪካ “የደም አልማዝ” የሚዝቁት ምዕራባዊ ኩባንያዎች እንደዚህ ዓይነቱ የሥራ ማቆም አድማ የሚዋጥላቸው አይደለም፡፡ ኪሳራው ከፍተኛ ነው፤ አልማዝ ደም ነው – የጥቁር አፍሪካ ደም፡፡ ይህ ደግሞ በደንብ መመጠጥ አለበት ስለዚህ ዓመጸኛ ማዕድን ቆፋሪዎችን ሰጥ ለጥ አድርጎ የሚያሠራ ሠራዊት በፈራረሰችው ሴራሊዮን ያስፈልጋል፡፡ ኢቦላ ለዚህ አስፈላጊ ነው – ድርብ ጥቅም ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ጋናዊቷ የሕክምና ባለሙያና አርታኢ ናና ክዎሜ አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡
ባለሙያዋ በዚህ ብቻ አያቆሙም፤ የጦር ሠራዊት ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ አስገድዶ ለመክተብ ሥራ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ስለዚህ “የኢቦላን ቫይረስ ለመከላከል” እየተባለ የሚሰጠውን ክትባት እምቢ የሚሉ ዜጎችን ለማስገደድ እንዲሁም የቀይ መስቀልን የኢቦላ ክትባት የተቃወሙትን ላይቤሪውያንን እና ናይጄሪውያንን ከማስገደድ ባለፈ መልኩ ቀይ መስቀልንም ከጥቃት ለመከላከል የግድ ጦር ማስፈለጉ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ሌላ ደግሞ ኢቦላ በጥቁርና በነጭ መካከል የልዩነት መልክ እንዲያሳይ መደረጉ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያዋ ይናገራሉ፡፡ ሲያጠናቅቁም በእርግጥ ኢቦላ እንደሚባለው አደገኛና ዓለምአቀፋዊ ወረርሽኝ ከሆነ አሜሪካ መጀመሪያ ማድረግ የነበረባት ከምዕራብ አፍሪካ የሚነሱ የአውሮፕላን በረራዎች ያለአንዳች ምክንያት መሠረዝ ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን የተፈጥሮ ሃብት፣ ጂኦፖለቲካዊ፣ የባዮአሸባሪነት፣ ወዘተ ውስብስብ ይዞታ ስላለው ይህ እስካሁን አለመደረጉ ምክንያት እንዳለው የሚስማሙ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የአፍሪካ አምባገነኖችም የምዕራብ ቁራሽ ተጠቃሚ ለመሆን ሲሉ ሕዝባቸውን መድሃኒት መሞከሪያ ከማድረግ መቆጠብ እንዳለባቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በጓቴማላ ክቡር የሰው ልጅን ባክቴሪያ እየወጉና በተለያየ መንገድ እየሰጡ የተፈጸመው የቂጥኝ በሽታ ሙከራ ከ62 ዓመታት በኋላ ይፋ ሆነ፤ የኢቦላስ!? በአገራችንስ በተመሳሳይ ሁኔታ የምዕራብን ብጣሽ ለመቀበል ሲባል “በማይፈለግ” ወይም “ወርቃማ ባልሆነ” ሕዝብ ላይ መድሃኒት ተሞክሮ ይሆን?
“ማምከን፣ ማኮላሸት” የህወሃት ስጦታ
“የታመመ የለም በግድ ቤት እየገቡ ከተቡን” መካን የተደረጉ ዜጎች
“እሱ ቢልልኝማ መውለድ እፈልጋሉ” ስትል የተማጽኖ ምላሽ ትሰጣለች። ሌላዋ “በቀን አስር ሊትር ጸበል እጠጣለሁ” በማለት ትናገራለች። የተቀሩት ሁሉም “በሽታ ገብቷል ብለው በግድ ከተቡን” ይላሉ። ሁሉም የአማራ ክልል ነዋሪዎች ናቸው። የተሰባሰቡት ሩፋኤል በሚባል ጸበል ስፍራ ነው። ዓመትና ሁለት ዓመት የተቀመጡ አሉ። ሁሉም ወልዶ መሳም፤ ልጅ ማቀፍ ይፈልጋሉ።
“ቀረጻና ቅንብር የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ” በሚል የቅጂ ባለቤትነት በተለያዩ የማህበራዊ ገጸች ይፋ የሆነው የምስል ማስረጃ ተከራካሪ የተራበ ታላቅ አገራዊ ጉዳይ ነው። በዚሁ ልብን በሚሰብር ቪዲዮ የሚታዩት “የመከኑ” ወገኖች የተፈጸመባቸው ግፍ (እንደ ጓቴማላው) ይቅርታ ለመጠየቅ እንኳን የሚበቃ አልሆነም። ይቅርታው ቀርቶ ጉዳዩ በዝርዝር አልተጠናም፤ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ድርጅቶች፣ ባለሙያዎች፣ … ድርጊቱ ለታሪክ በሚቀር መልኩ አቀናብረው በሰነድነት የማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ኃይልን አስተባብሮ ለትግል የመነሻ አጀንዳ የማድጉ ሃሳብ አልታየም፡፡ ቪዲዮው የሚታዩት ወገኖች እንደሚናገሩት ክትባቱ በተሰጠበት ስፍራ ህጻናት እንደሌሉና ሁሉም ሰለባዎች ልጅ አልባ መደረጋቸውን መስክረዋል። (ቪዲዮው ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ)
ስማቸውን እየተናገሩ የተፈጸመባቸውን ግፍ የሚዘረዝሩት በሃያዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙት እህቶች ድንገት ውር ውር ሲሉ የሚታዩ ልጆች የተወለዱት በወቅቱ ከክትባቱ ያመለጡ ወይም ሳይከተቡ የተዘለሉ እህቶች የወለዷቸው ናቸው። በአሜሪካ በጥቁሮች ላይ ቂጢኝን ተንተርሶ ከተፈጸመው በደልና ግፍ እንዲሁም ከጓቴማላው አሰቃቂ በሰው ልጅ ላይ ከተደረገ የበሽታ ሙከራ ይህኛውን ምን ይለየዋል? ደግሞስ ለምን አማራ ተለይቶ ተመረጠ? ሌሎች ዜጎች ላይም ስላለመፈጸሙ ማስረጃ ባይቀርብም ይፋ የሆነው ማስረጃ እንደሚያረጋግጠውና በ2007 የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር ከሚገመተው በ2 ሚሊዮን ማቆልቆሉ የዚሁ የዘር ማምከን ውጤት ስለመሆኑ ከግምት በላይ የሚናገሩ አሉ። ምዕራባውያን “መልኩ ያማረውን ዘራቸውን” ከበሽታ በእርግጠኝነት ለመከላከል እንስሳትን ብቻ ሳይሆን “የሰው እንስሳትንም” ይፈልጋሉ፡፡ ልክስክስና ለዜጎቹ ግድ የማይለው አገዛዝ ካገኙ መድሃኒት፣ ክትባት፣ ገንዘብ፣ … ከጥሩ ፈገግታ ጋር ይሰጣሉ፡፡ “የ … በሽታን በ … ዓ.ም. ለማጥፋት የመድሃኒትና የገንዘብ ድጎማ ተገኘ” ተብሎ ይለፈፋል፡፡ ፈገግታ፣ ፊርማ፣ ሰነድ ልውውጥ፣ ጭብጨባ፣ … ሲደረግ በፎቶና በቲቪ ይታያል፡፡ በየአገሩ የራሱን ዘር ወርቃማ አድርጎ የሚቆጥር ስላለ ዘሩን አብዝቶ የማይፈልገውን ለማምከን “ክትባቱንና ገንዘቡን” በ“ጤና ጥበቃና በሽታ መከላከል” እንዲሁም “በጤናው ዘርፍ በሚካሄደው ልማት” ስም ይቀበላል፤ ለዚህ “አስተዋጽዖው” በአገር ውስጥ “ሥልጡን፣ ዘመናዊ፣ …” ተብሎ ይጨበጨብለታል፤ በበሽታ አስሞካሪዎቹ ምዕራባውያን ደግሞ ወደ አገራቸው ዘለቅ ባለ ቁጥር “ሽልማት” ይወርድለታል፡፡ በዜጋው ደም “ይከብራል፤ ይሞገሳል”፡፡
ከኤችአይቪ ኤድስና ኢቦላ ጋር በተያያዘ ጠለቅ ያለ ጥናት በማካሄድ አንደኛ ደረጃና እውነተኛ ምስክርነት የያዘ የምርምር ውጤት EMERGING VIRUSES: AIDS & EBOLA Nature, Accident or Intentional? በሚል ርዕስ ዶ/ር Leonard G. Horowitz, D.M.D., M.A., M.P.H ያሳተሙትን መጽሐፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የዘር ማምከን ብቻ ሳይሆን በአበባ እርሻ ዘርፍ በሚሰሩ እህቶች ላይም ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ ተረጋግጧል። እህቶች ያለ በቂ ዋስትናና መከላከያ ኬሚካል መጠቀማቸው ለመካንነት ዳርጓቸዋል። ኢህአዴግ ከአበባ ሽያጭ የሚያገኘውን ምንዛሬ እየቆጠረ ዜጎቹን ረስቷቸዋል። ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በድንግዝግዝ “የገዙት” (በነጻ ያህል የተሰጣቸው) የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ተረፈ ምርት ያስከተለው የጤና ችግርም መዘዙ ብዙ ነው። ዜጎች እንደ መብት ተጎዳን ቢሉ እስርና ዱላ ነው የገጠማቸው። ከርሳም ዳኞችና አቃጣሪ ፖለቲከኞች የመንደራቸው ህዝብ ላይ ክስ መስርተው፣ ራሳቸው ፈርደው፣ የወህኒ ደረሰኝ የተቆረጠላቸው ወገኖች አሁን ድረስ “ጸረ ልማት” ተብለው በማጎሪያ አሉ። ለህወሃት እየሰገዱ “የሰው ብል” የሆኑት ኦህዴድና ብአዴንም ህዝብ እንወክላለን ብለው እየኖሩ ነው። ከሁሉም በላይ ይህ ሁሉ ጉድ ሲፈጸም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩትን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን የጠየቃቸው አካል የለም። እርሳቸው ግን በአካል ቤተመንግስት፣ በሳይበር ዓለም ኮምፒውተር ላይ “እንደ ፍንዳታ” በትዊተርና በፌስቡክ ይጭራሉ፤ የዘፈንና የዳንኪራ ፎቷቸውን ይለጥፋሉ፤ ራሳቸውን እና “ተከታዮቻቸውን አፕዴት” ያደርጋሉ፤ በአገር ውስጥ ጓደኞቻቸው እና በምዕራባዊ ሸላሚዎቻቸው “ከተቀቡ” ቀጣዩ ጠቅላይ ሚ/ር ይሆናሉ። ይህ ነው እንግዲህ የህወሃት ገጸ በረከት!!
ማብቂያ
እጅግ በርካታ ግፍ የተሸከመችው ዓለማችን አሁንም የበርካታ ምስኪናንን ዕንባ እና ውርደት እንዲሁም ሰቆቃ መሸከም አልበቃትም፡፡ በዜጎች ላይ እጅግ አስከፊ የሆኑ ነገር ግን እስካሁን ይፋ ያልወጡ “ወንጀሎች” ሲፈጸሙ ኖረዋል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ የእነርሱ ህይወት ከሌሎች እጅግ የበለጠ እንደሆነ የሚሰማቸው ሁሉ “ተመልካች ወይም ተከራካሪ የላቸውም” በሚሏቸው ላይ የፈለጉትን ሲያደርጉ ኖረዋል፤ እያደረጉም ነው፡፡ ሲሻቸው ጦርነት ይፈጥራሉ፤ ከፈለጉም የበሽታ ወረርሽኝ ያስነሳሉ፤ ለሃብትና ረጅም ዕድሜ ሲሉ የደሃውን ደም መስዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ ከዚያ ያመለጠውን በሽታ ይሞክሩበታል፤ በደዌ አልሞት ያለውን ደግሞ ዘሩን ያመክናሉ፡፡ ግዛታቸውን ያሰፋሉ፤ ዘራቸውን ያበዛሉ፤ ይገነባሉ፤ ያንጻሉ፤ ብዙ ዘመንም ለመኖር ያቅዳሉ፡፡ ሕግ ያወጣሉ፤ ሕግን በፍትህ ስም ያረክሳሉ፤ ፍትህንም በሕግ ስም ያዋርዳሉ፡፡ ይህንን ግን የረሱት ይመስላል፡-
“ፍትህ ከሚበየንባቸው ፍርድ ቤቶች በላይ የሆነ ፍርድ ቤት አለ፤ ይህም የኅሊና ፍርድ ቤት ነው፤ እርሱ ከሁሉ የላቀ ነው፡፡” መሃትማ ጋንዲ!!
ጠቢቡ እንዲህ ይላል፡ “በአገር ውስጥ ድሃ ተጨቁኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብት ተረግጦ ብታይ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ ከእነዚህ ከሁለቱም በላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ” መክ.5፡8፡፡
ይህንን ዘገባ ለማጠናከር በርካታ ድረገጾችንና መረጃዎችን ተጠቅመናል፡፡ ሆኖም ከዘገባው ጋር አብሮ ለማተም አመቺ ባለመሆኑ የተውነው ቢሆንም በአስፈላጊው ጊዜ ለመጥቀስ የምንችል መሆኑን እንገልጻለን፡፡ መረጃ በማቀበል የተባበሩንን ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply